ግብርናችንን ለማዘመን፤የጤፍ ምርትና ምርታማነትን የበለጠ ለማሳደግ

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሑፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡

የጤፍ ምርትና ምርታማነትን የበለጠ ለማሳደግ

ጤፍ በሀገራችን እጅግ ተፈላጊና ጠቃሚ ሰብል ነዉ። በተለይም በየእለቱ የምንመገበዉን እንጄራ ለማዘጋጀት እንደዋና ግባት የምንጠቀመዉ ጤፍን በመሆኑ ነዉ። ከእንጄራ በተጨማሪ ጤፍ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን ለመሥራት ጥቅም ላይ ይዉላል። ባለፉት ዓመታት የሀገራችን ህዝብ በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ የጤፍ ተጠቃሚም እንዲሁ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሀገራችን ህዝብ ቁጥር በየ 25 አመታት በእጥፍ ያድጋል። በዚሁ መሠረት የሰብል ምርታችን በተመሣሣይ ደረጃ ካላደገ የምግብ አቅርቦታችን ላይ ላይ የጎላ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል። የምርት ዕድገት ለሁሉም የሰብል አይነቶች ቢያስፈልግም በጤፍ ላይ ግን ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ጤፍ የምግባችን ቁልፍ ስብል ነውና።

ምስል 1 እንደሚያሳየዉ ጤፍ በየአመቱ ወደ ሶስት ሚሊዮን በሚጠጋ መሬት ላይ የሚመረት ሲሆን ከሌሎች በሀገሪቱ ከሚመረቱ ሰብሎች ጋር ሲወዳደር ከፍተኛዉ ነው። ጤፍን ተከትሎ በሀገራችን በሰፊው የሚዘሩ ሰብሎች እንደ ቅደም ተከተላቸዉ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ማሽላ እና ገብስ ናቸዉ።

ምንም እንኳ ጤፍ የሚዘራበት የመሬት ስፋት ከሌሎች ሰብሎች ጋር ሲወዳደር በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ቢቀመጥም አጠቃላይ ምርትን በተመለከተ ግን ጤፍ በቆሎና ስንዴን ተከትሎ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ምክንያቱም የጤፍ ምርታማነት ከሁሉም የብርእና አገዳ ሰብሎች ጋር ሲወዳደር እጅግ ዝቅተኛዉ በመሆኑ ነዉ፡፡ በምስሉ እንደሚታየዉ አማካይ የሀገሪቷ የጤፍ ምርታማነት 19 ኩንታል በሄክታር ብቻ ሲሆን የበቆሎ 42 እና የስንዴ 31 ኩንታል በሄክታር ናቸዉ፡፡

ስለዚህ ይህን ዝቅተኛ የጤፍ ምርታማነት ለማሳደግ በሁሉም መስክ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጤፍ በኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ አግሮኢኮሎጂዎች የሚዘራ ሲሆን ከሌሎች ሰብሎች በተሻለ ድርቅንና የዉሃ ማቆርን ይቋቋማል፡፡

ምስል 1፤ በ2014 ዓ ም በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ የተመረቱ የብርእና አገዳ ሰብሎች የመሬት ስፋት፣ አጠቃላይ የምርት መጠን እና ምርታማነት፡፡ ምንጭ፤ Ethiopian Statistics Service. 2022. Agricultural Sample Survey 2021/22 (2014EC). Vol. 1. Reports on Area and Production of Major Crops Meher Season. Statistical Bulletin 593, Addis Ababa, Ethiopia.

በኢትዮጵያ በ2014 ዓ ም አጠቃላይ የጤፍ ምርት 56.1 ሚሊዮን ኩንታል የነበረ ሲሆን ከዚህ ዉስጥ 93.5% የሚሆነዉ የተመረተዉ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ነዉ፡፡ በዚሁ መሠረት 29.9 ሚሊዮን ኩንታል ከኦሮሚያ ክልል እና 22.5 ሚሊዮን ኩንታል ከአማራ ክልል ነዉ፡፡ ምስል 2 እንደሚያሳየዉ እያንዳንዳቸዉ ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚያመርቱ ዞኖች 18 ሲሆኑ ሰባቱ ከአማራ ክልል የተቀሩት 11 ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ናቸዉ፡፡ እያንዳንዳቸዉ ከሶስት ሚሊዮን ኩንታል ጤፍ የሚያመርቱ ዞኖች ደግሞ ምስራቅ ጎጃም፣ ሰሜን ሸዋ እና ደቡብ ጎንደር ከአማራ ክልል ሲሆኑ ምእራብ ሸዋ፣ ደቡብ ምእራብ ሸዋ፣ ምስራቅ ሸዋና ሰሜን ሸዋ ከኦሮሚያ ክልል ናቸዉ፡፡ ይህ የሚያሳየን የጤፍ ምርት በከፍተኛ ደረጃ የሚመረተዉ በመካከለኛዉና በምእራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ነዉ፡፡ ሰለዚህ የጤፍን ከፍተኛ ፍላጎት በከፊልም ለመመለስ በነዚህ ከፍተኛ አምራች የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት በማድረግ ምርታማነት የሚሻሻልበትን መንገድ መቀየስ ያስፈልጋል፡፡ ምርጥ ዝርያዎችን ጨምሮ የምርት ግባቶች ለገበሬዉ እንዲዳረሱ የኢክስቴንሽን ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ምስል 2፤ በየአመቱ እያንዳንቸዉ ከአንድ ሚልዮን ኩንታል በላይ ጤፍ የሚያመርቱ ዞኖች፡፡ ሁም ዞኖች በአማራና በኦሮሚያ የሚገGእኙ ናቸዉ፡፡ ምንጭ፤ Ethiopian Statistics Service. 2022. Agricultural Sample Survey 2021/22 (2014EC). Vol. 1. Reports on Area and Production of major crops Meher Season. Statistical Bulletin 593, Addis Ababa, Ethiopia.

በመለስተኛ የጤፍ አምራች ሥፍራዎችም የጤፍ ምርታማነትን ማሳደግ አስፈላጊ ነዉ፡፡ ያለበለዚያ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየናረ የመጣዉን የጤፍ ዋጋ ከዚህም በበለጠ ደረጃ እንዳያጨምር ከፍተኛ ሥጋት ስላለኝ ነዉ፡፡

የዚህን ጥረት ላማገዝ ያህል፣ በ2014/15 የመኸር ዘመን በጤፍ ምርምር ፕሮጀክታችን ከሚደረገዉ የምርጥ ዘር ሥርጭት በተጨማሪ ለሙከራ ያህል ጤፍ በአነስተኛ ደረጃ በሚበቅልበት በምእራብ አርሲ ዞን በአዳባ ወረዳ ሶስት የጤፍ ዝርያዎችን ፈቃደኛ በሆኑ ገበሬዎች ማሣ ላይ ፈትሸን ነበር፡፡ ዉጤትም እጅግ የሚያመረቃ ነበር፡፡ በተለይም ኤባ የተባለዉን ዝርያ የዘራ ገበሬ በሄከታር 40 ኩንታል ለማግኘት ችሏል፡፡ ውጤቱን ያዩ እና የሰሙ ገበሬዎችም የዚህን ምርጥ ዘር ጥያቄ በከፍተኛ ደረጃ አቅርበዉልናል፡፡ በተጠየቀዉ ደረጃ ምላሽ መስጠት ባንችልም በ2015/16 መኸር ዘመን የሚሆን ሶስት ምርጥ ዝርያዎችን (ማለትም ኤባ፣ ፍላጎት እና ኩሊ የተባሉትን) በወረዳዉ ሥር ለሚገኙ ሶስት ቀበሌዎች እና 35 ገበሬዎችች እንዲከፋፈል በወረዳዉ የግብርና ጽ/ቤት በኩል ዘር ለማቅረብ ችለናል፡፡ ከነዚህ ሥፍራዎች የሚገኘዉ ምርትም ለዘር ብቻ እንዲሆን በማድረግ የምርጥ ዝርያዎች ሥርጭትን ለማስፋፋት እንችላለን፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በገበሬዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን ለማትረፍ የቻለዉ የኤባ ዝርያ በምስል 3 ታይቷል፡፡

በአንዳንድ ምርጥ የጤፍ ተስማሚ ሥፍራዎች የከተሞች መስፋፋትም አሉታዊ ጎን አለዉ፡፡ ስለዚህ የከተሞች ማስፋፊያ ፕላን ስናውጣ የግብርና ምርታችንን በማይጎዳ መልኩ ቢሰራ መልካም ነዉ፡፡

ምስል 3፣ ከፍተኛ አድናቆትን በገበሬዎቻችን ዘንድ እያተረፈ የመጣዉ ኤባ ተብሎ የተሰየመዉ የጤፍ ዝርያ በምንጃር፣ ሸንኮራ እና አዳባ ፉሩና፡፡ ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ፡፡

በአጠቃላይ ጤፍ በተጠቃሚዉ ዘንድ ያለዉን ከፍተኛ ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት ትኩረት ይሰጠዉ እላለሁ፡፡ ሌሎች የሀገራችን ሰብሎች እንደ ስንዴ፣ በቆሎ እና ማሽላ ያሉት የምርምር ፕሮግራማቸዉ በከፍተኛ ደረጃ በአለም አቀፍ የምርምር ተቋማት ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ በተቃራኒዉ የጤፍ ምርምር በዚህ በኩል የሚያገኘዉ ጥቅም እጅግ አነስተኛ ነው፡፡

ወደፊት በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. (August 7, 2023)

ግብርናችንንለማዘመን፤ዶክተር መላኩ ወረደ፣ የብዝሀ ህይወታችን ባለዉለታ ሲታወሱ

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሑፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡

ዶክተር መላኩ ወረደ፣ የብዝሀ ህይወታችን ባለዉለታ ሲታወሱ

ብዝሀ ህይወት (biodiversity) በምድራችን በሚገኙ ህይወት ባላቸዉ ፍጡራን መካከል ያለዉን ልዩነቶችን ያሳየናል፡፡ በዚሁ መሰረት የብዝሀ ዘር ጥናት በተለያዩ ዕፅዋት፣ እንስሳት እና ረቂቅ ህዋሳት መካከል ያለዉን ልዩነት በሳይንሳዊ መንገድ የምንፈትሽበትን መንገድ ያስችለና፡፡ ቀደም ባለዉ ቫቪሎቭ ባለዉለታችን በሚለዉ ብሎጌ ኢትዮጵያ ቁልፍ ለሆኑ ሰብሎች መገኛ እንደሆነች ለማሳየት ምክሬአለሁ፡፡

ምሥሉ የሚያሳየዉ በተለምዶ የቫቪሎቭ የዝርያዎች ወይም የዕፅዋት መገኛ ማዕከላት ሲሆኑ እነርሱም (1) ሜክሲኮ-ጉቴማላ፣ (2) ፔሩ-ኢኳዶር-ቦሊቪያ፣ (2A) ደቡባዊ ቺሌ፣ (2B) ደቡባዊ ብራዚል፣ (3) ሜዲቴራኒያን፣ (4) መካከለኛዉ ምሥራቅ፣ (5) ኢትዮጵያ፣ (6) መካከለኛዉ ኤሲያ፣ (7) ሕንድ እና በርማ፣ (7A) ሲያም-ማላያ-ጃቫ እና (8) ቻይናና ኮሪያ ናቸዉ።

ኢትዮጵያም ለጤፍ፣ ቡና፣ ኑግ፣ ሰሊጥ፣ ዳጉሣ፣ የጉሎ ፍሬ፣ እንሰት፣ ጌሾ፣ ጫት፣ ኮሶ እና የመሳሰሉት መገኛ ወይም መነሻ ተብላ ትገመታለች፡፡ ይህም ማለት በሀገራችን በርካታ ከላይ የተጠቀሱት ሰብሎች ዝርያዎች ይገኛሉ ማለት ነው፡፡ እነዚህን የተለያዩ ሰብሎች ዝርያዎች አሰባስቦ፣ በተገቢ ሁኔታ አስቀምጦና ጥናት ማድረግ አስፈላጊ ነዉ፡፡ ምክንያቱም ለተለያዩ ጥናቶች የሚያገለግሉ ዝርያዎች ከነዚህ ናሙናዎች ዉስጥ ሊገኙ ስለሚችሉ ነዉ፡፡

በዚህ ጉዳይ በሀገራችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉት ዶክተር መላኩ ወረደ ናቸዉ ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ ዶክተር መላኩ በወቅቱ PGRC/E Plant Genetic Center of Ethiopia (የአሁኑን EBI የኢትዮጵያ ብዝሀ ዘር ኢንስቲትዩት) የተባለዉን ተቋም በዳይክሬትነት እ አ አ ከ1979 እስከ 1993 ለ14 ዓመታት በመምራት ባገለገሉበት ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ የተለያዩ ሰብሎች ዝርያዎች እንዲሰባሰቡና በተገቢ ሁኔታ እንዲቀመጡ ለማድረግ ችለዋል፡፡ ይህም ማለት አስፈላጊ የሆነ የሙቀት መጠንና ሌሎች አስፈላጊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልክ ማለት ነዉ፡፡

ዶክተር መላኩ ወረደ እኚህ ነበሩ፡፡ ምንጭ፤  https://rightlivelihood.org/the-change-makers/find-a-laureate/melaku-worede/

ከዚህ በተጨማሪ ዶክተር መላኩ የሚታወቁበት ገበሬዎችን ያማከለ የብዝሀ ዘር ጥበቃ እንዲደረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ከመሆናቸዉም በላይ ይኸዉ ገበሬዎችን ያሳተፈዉ መንገድ ብዝሀ ዘርን በዘላቁነት ለመንከካበብ እንደ ግንባር ቀደም የመፍትሔ አካል እንዲሆን ያደረጉ እና ይህንንም በዓላም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን ለማደረግ ያስቻሉ ናቸዉ፡፡ ይህንኑ በሥልጠና መልክ በተለያዩ ሀገራት በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ዶክተር መላኩ ወረደ በርካታ  ሽልማቶችና እዉቅናቸዎች የተበረከቱላቸዉ ሲሆን ከነዚህ ዉስጥ ሁለቱ፤ 1ኛ) እ አ አ በ1989 የተሰጣቸዉና ዘ ራይት ላይቪሊሁድ (The Right Livelihood) ሽልማት ወይም እንደ አማራጭ የኖብል ሽልማት የሚታወቀዉ ሲሆን የተሰጣቸዉም የኢትዮጵያን በርካታ ብዝሀ ዘር በተገቢዉ ሁኔታ ለማስጠበቅ ምርጥ ማዕከላት እንዲገነቡ በማስቻላቸዉ ነዉ፡፡ ይኸዉ ሽልማት ሎሬት የሚባል የክብር ስም እንዲሰጣቸዉ አስችሏል፡፡ እንደሚታወቀዉ ሁሉ ቢሊሃሪዚያ ተብሎ የሚጠራዉን አደገኛ በሽታ በቀላል ወጪ ለመከላከል እንዶድን በጥቅም ላይ ያዋሉት ፕሮፌሰር አክሊሉ ለማና ዶክተር ዶክተር ለገሠ ወልደ ዮሀንስም ይህንኑ የላይቪሊሁድ ሽልማት በጋራ ማሸነፋቸዉ ይታወሳል፡፡

2ኛ) እ አ አ በ2008 ላደረጉት ከፍተኛ ዓለም አቀፍ አስተዋፅዖ ከኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ተሸልመዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካበረከቷቸዉ አስተዋጽዎች መካከል ዋነኞቹ በዓለም አቀፍ የምግብና እርሻ ድርጅት የዕፅዋት ብዝሀ ዘር የሚመለከት ኮምሽን ሊቀመንበር፣ የዕፅዋት ብዝሀ ዘር ኢንስቲትዩት የቦርድ አባልና በተለያዩ ተቋማት የሰጧቸዉ ሥልጠናዎችን ያካትታል፡፡

ሕትመትን በተመለከተ ዶክተር መላኩ የተለያዩ ጽሁፎችን ያሳተሙ ሲሆን ከነዚህ መካከል የሚከተሉት መጽሐፍት ይገኙባቸዋል፡፡

  • Plant genetic Resources of Ethiopia  እ አ አ በ1991 የታተመ
  • Seeds of survival እ አ አ በ1999 የታተመ
  • The race to save Africa’s seed እ አ አ በ2005 የታተመ

በዶክተር መላኩ ወረደ እና ባልደረቦቹ የታተመዉ መጽሐፍ የፊት ሽፋን

ከዚህም በተጨማሪ የዶክተር መላኩን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እዉቅና ለመስጠት ጊያ ፋዉንዴሽን የሚባል ተቋም በዶክተር መላኩ ሥራ ላይ ያተኮረ Seeds of Justice : in the hands of Farmers የተባለ 40 ደቂቃ የሚፈጅ ዶኩመንታሪ ፊልም እ አ አ በ2015 አዘጋጅቷል፡፡

እኚህ የብዝሀ ህይወታችንን በተገቢዉ ሁኔታ በማሰባሰብና በማስጠበቅ ከፍተኛ አስተጽኦ ያደረጉልን ከሀገራችንም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እዉቅናን ያተረፉ ምሁር ከሁለት ቀናት በፊት ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በተወለዱ በ87 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዉናል፡፡ ለቤተሰቦቻቸዉ፣ ጓደኞቻቸዉ እና የሥራ ባልደረቦቻቸዉ መጽናናትን እመኛለሁ፡፡

ወደፊት በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. (August 2, 2023)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የጤፉ ጠቢብ፣ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ፤ ክፍል 3

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሑፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡

የጤፉ ጠቢብ፣ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ፤ ክፍል 3

በዛሬዉ ክፍል 3 ጽሑፌ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ የሀገራችን ግብርናን በተመለከተ ላደረኩላቸዉ ቃለ መጠይቅ የሰጡኝን መልስ አስነብባችኋለሁ።

ጥያቄ፤በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብል ሣይንስ ባለሙያዎች ማህበር የዕድሜ ልክ የስኬት ሽልማት  (Life Time Achievement Award) ሰጥቶታል፡፡ ይህ ከፍተኛ ሽልማት ለምን እንደተሰጥትዎት ሊነግሩኝ ይችላሉ?

ዶክተር ክበበዉ፤ ይህ የዕድሜ ልክ የስኬት ሽልማት (Life Time Achievement Award) በኢትዮጵያ ሰብል ሣይንስ ባለሙያዎች ማህበር እ አ አ በፌብሪዋሪ 24 ቀን 2023 የተሰጠኝ በሰብል ምርምርና ልማት እንዲሁም ለሰብል ሣይንስ ባለሙያዎች ማህበር ላበረከትኩት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ነው፡፡

ምስሉ የሚያሳየዉ የዕድሜ ልክ የስኬት ሽልማት ለዶክተር ክበበዉ አሰፋ (በግራ ያሉት) በዶክተር ድሪባ ገለቴ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክቴር ር ሲበረክትላቸዉ ነዉ፡፡ ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ፣ እ አ አ ፌብሪዋሪ 24 ቀን 2023

ጥያቄ፤ የብሔራዊ የጤፍ ምርምርን በማስተባበር እያሉ ለሶስት ዓመታት በሽምብራ ምርምር ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ፕሮጀክትን ሲያስተባብሩ ነበር፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? በአንድ ጊዜ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ማስተባበር አይከብድም?

ዶክተር ክበበዉ፤ በጊዜዉ ቲ ኤል-ሁለት (TLII) በተባለው ፕሮጄክት በተለይም በሽምብራው ክፍል ኢትዮጵያን አስመልክቶ በዋና ተመራማሪነት ወይም አስተባባሪነት (Principal Investigator) ሆኜ ተመድቤ አገልግያለሁ፡፡ ይህ ፕሮጄከት በICRISAT በኩል በቢል እና ሜሊንዳ ጌትሰ ፋውንዴሽን (BGMF) የሚደገፍ ነበር፡፡ የተለያዩ ፕሮጄክቶችን ማሰተባበርና መምራት ምንም እንኳን ከፍተኛ ሃላፊነት ያለበትና ጥረት የሚጠይቅና ጫና የሚያሳድር ቢሆንም በጣም ካልበዙ በስተቀር ከባድ አይሆንም፡፡ የምርምር ፕሮጄክቶቹ ሥራዎች የጤፉም ሆነ የሽምብራው የሚሰሩት በየክፍሎቹ ስለነበር የእኔ ሃላፊነት ማስተባበር ስለነበረ እምብዛም አስቸጋሪ አልነበረም፡፡

ምስሉ የሚያሳየዉ የዕድሜ ልክ የስኬት ሠርቲፊኬት ለዶክተር ክበበዉ አሰፋ ሲበረክትላቸዉ ነዉ፡፡ ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ፣ እ አ አ ፌብሪዋሪ 24 ቀን 2023

ጥያቄ፤ በዩኒቨርቲዎች ዉስጥ በማስተማርና የማስተርና የፒ ኤች ዲ ተማሪዎችን እያማከሩ እንደነበረም ይታወቃል፡፡ እስካሁን ድረስ የስንት ተማሪዎችን ቴሲስ ሱፐርቫይዘር እንዳደረጉ ሊነግሩኝ ይችላሉ?

ዶክተር ክበበዉ፤ ለፒ ኤች ዲ (PhD) ለ12 በአብዛኛው በሀገር ውስጥና ጥቂቶች ደግሞ በውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች የድህረ-ምረቃ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ተማሪዎች አማካሪ ሆኜ አግልግያለሁ ወይም በማገልገል ላይ እገኛለሁ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ግማሹ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን የተቀሩት ስድስቱ ግን አሁንም በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ በኤም ኤስ ሲ (MSc) ከ24 በላይ ለሚሆኑ በተለያዩ ሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች (በተለይም ሀረማያ፣ ሀዋሳ፣ አዲስ አበባና ጂማ ዩኒቨርሲቲዎች) የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ተማሪዎች በምርምር አማካሪነት አገለግያለሁ፡፡

ጥያቄ፤ እነዚህ ያማከሯቸዉ ተማሪዎች ሁሉም ምርምራችውን የሠሩት በጤፍ ላይ ነዉ ወይስ ሌሎች ሰብሎችንም ያካትታል?

ዶክተር ክበበዉ፤ ብዙዎቹ በጤፍ ላይ ነው ምርምራቸውን የሰሩት ወይም የሚሰሩት፡፡ ሆኖም በሌሎች ሰብሎች ላይ ለምሳሌ ከኢትዮጵያ በተሰበሰቡ ጥቁር አዝሙድ እና አንጮቴ እንዲሁም በስንዴና በሌሎችም ሰብሎች ላይ የሰሩና እየሰሩም ያሉ ይገኙባቸዋል፡፡

ጥያቄ፤ እስከ ሁለት ሳምንት የሚቆይ አጫጭር ሥልጠናዎችንም በተለያዩ ጊዜያት ለገበሬዎች፣ ለቴክኒሻኖች እና ለጀማሪ ተመራማሪዎች ይሰጡ እንደነበረ አውቃለሁ፡፡ ላለፉት 40 ዓመታት በግምት ስንት ሰልጣኞችን አሰልጥኛለሁ ይላሉ?

ዶክተር ክበበዉ፤ በነዚህ በርካታ ዓመታት በሰጠኋቸው ሥልጠናዎች ላይ የተሳተፉትን ሠልጣኞች ቁጥር መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡  እንዲሁ በግርድፍ ግምት ስሌት ግን ከ450 ሺህ እስከ 500 ሺህ ያህል ይሆናሉ ማለት ይቻላል፡፡

ጥያቄ፤ የጤፍን እና የሌሎች ዓለም አቀፍ ትኩረት የተነፈጋቸዉ ሰብሎች (orphan crops) ምርምር እንዴት ማሳደግ እንችላለን ይላሉ?

ዶክተር ክበበው፤ በአጠቃላይ ጤፍን እና የሌሎች ዓለም አቀፍ ትኩረት የተነፈጋቸዉ ሰብሎች (orphan crops) ላይ ምርምር መሥራት አያሌ አስቸጋሪ ጉዳዮች አሉት፡፡ ከነዚህም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ 1ኛ) በእንደዚህ አይነት ሰብሎች ላይ የመሠረታዊ ዕውቀት ውሱንነት ስላለ ምርምር ለመስራት በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ 2ኛ) በእነዚህ አይነት ሰብሎች ላይ ለሚሰራ ተመራማሪ ከሌሎች በዓለም ላይ ታዋቂ ሰብሎች ላይ ከሚሰሩ ሳይንቲስቶች የተነጠለና ብዙ ሳይንሳዊ መድረኮች ላይ ተሳትፎው የተገደበ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ 3ኛ) በእነዚህ ሰብሎች ላይ ለሚሰራ ምርምር ከውጭ አለም አቀፍ የምርምር ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች የማቴሪያልና የገንዝብ እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፎችን ማግኘት በእጅጉ የተገደበ ይሆናል፡፡ 4ኛ) የምርምር ውጤቶችን በአለም አቀፍ ታዋቂ በሆኑ መድረኮች ለማቅረብና ፅሁፎችንም በጆርናሎች ለይ ለማሳተም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ 5ኛ) ከሁሉም በላይ ደግሞ በሀገር ውስጥ ራሱ በእንደዚህ አይነት ሰብሎች ላይ ለሚደረገው ምርምር የሚሰጠው ትኩረትና ድጋፍ አብዛኛውን ጊዜ እጅግ ዝቅተኛ ሲሆን ለዚህም በሀገራችን ኢትዮጵያ ጤፍን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ምንም እንኳን እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ቢኖሩም በጤፍና እና የሌሎች ዓለም አቀፍ ትኩረት የተነፈጋቸዉ ሰብሎች (orphan crops) ምርምር ለማሳደግ ቁርጠኝነት በመጀመረያ ደረጃ የሚያስፈልግ ሲሆን ትልቁ ጉዳይ ግን በእነዚህ ችግሮችም ውስጥ ቢሆን ሰርቶ ውጤት ማምጣትና የምርምሩን አስፈላጊነት በተጨባጭ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሳይንስ ተመጋጋቢ ስለሆነ በሌሎች በዓለም ላይ ታዋቂ በሆኑስውሰብሎች ላይ በምርምር የተገኙትን ዕውቀቶችና ውጤቶች መውሰድና ለእነዚህ ታዋቂ ላልሆኑ ሰብሎች እንዲውሉ ማድረግና መጠቀም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ሌላው ጉዳይ በጊዜ ሂደት እነዚህ በዓለም ላይ ትኩረት የተነፈጋቸው ሰብሎች እጅግ ተፈላጊ የሚሆኑበት ሁኔታ ይከሰታል፡፡ ለዚህም በአሁኑ ጊዜ ጤፍ በዓለም ላይ በተለይም እንደ የጤና እና የብቃት ሰብል (health and performance food) እጅግ ተፈላጊ ሆኖ መምጣቱን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ጥያቄ፤ እኔ በግሌ በሀገራችን ያሉ ሁሉንም መልክአ ምድሮችን በተለይም በሰብል ወቅት ማየት ቢያስደስተኝም ከሁሉም በላይ በየዓመቱ መጎብኘት የምወደዉ (my favorite) ከዚህ በታች ያለዉ በምንጃር የሚገኘዉ መልክአ ምድር ነዉ፡፡ ምክንያቱም በዚህ መልክአ ምድር ባንድ ጊዜ በተለያዩ ደረጃ ያሉ ሰብሎችን ማየት የሚቻል ከመሆኑም በተጨማሪ በየማሳዎቹ ዳር እና ዳር ለተለያየ አገልግሎት የሚዉሉ ዛፎችም ይታያሉ፡፡ ለመሆኑ እርስዎ በየጊዜዉ ለማየት የሚወዱትን (your favorite) ሥፍራ ሊገልጹልኝ ይችላሉ?

ዶክተር ክበበዉ፤አንደኛው ይኸው አንተ የጠቀስከው ቦታ በተለይም ወደ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ዋና ከተማ አሬሪቲ ስትሄድ ሣማ ሰንበትን ወረድ ስትል ከአስፋልት መንገዱ ግራና ቀኝ የምታያቸው ረባዳ ቦታዎች ናቸው፡፡ የሚያሰደስተኝም የሰብል ስብጥር ብዛት እጅግ በጣም በጥሩ ሁኔታ የተያዙ ማሳዎች በተለይም ደግሞ የባህላዊ የእርሻና ደን ስብጥር (Agro-forestry) እና አርሶ አደሮቹ በማሳቸው ዳር በጥቂት ቦይ ላይ አጅግ ዘር አብዝተው (ምስግ አድርገው ዘርተው) ለከብቶች መኖነት የሚያበቅሉዋቸው ማሽላ ወይም በቆሎ ናቸው፡፡ ሌላው በሁለተኛነት የሚያሰደስተኝ ቦታ በምስራቅ ጎጃም ደጀንን አለፍ ብሎ የጤፍ ሰብል ታጭዶ ክምሮች ተኮልኩለው የሚታዩበት ሜዳ ኮትቻ መሬቶች ናቸው፡፡ ክምሮቹን ስትመለከት ያ ሁሉ የጤፍ ክምር በእውነቱ በሰው ተበልቶ የሚያልቅ አይመስልም፡፡

ጥያቄ፤ በሥራ ዓለም በነበሩበት በርካታ ዓመታት የተለያዩ ገጠመኞች እንደነበርዎት እገምታለሁ፡፡ ከነዚህ ዉስጥ ጥቂቶቹን ቢያጋሩኝ፡፡

ዶክተር ክበበዉ፤ በመጀመሪያ በሥራ አለም ሳይሆን በትምህርት ላይ እያለሁ የነበሩኝን ሁለት ገጠመኞች ባነሳ ደስ ይለኛል፡፡ የመጀመሪያዉ ትምህርት ላይ በተለይም ሶስተኛ ክፍል በነበርኩበት ጊዜ የእንግሊዝኛ አስተማሪያችን (አፈር ይቅለላቸውና መምህር ይልማ ሂርጳዬ) እንግሊዝኛን እንዴት በድምፅ አናባቢ ፊደላት (vowels) በራሳቸው ብቻቸዉን አናባቢ ያልሆኑ ወይም ተነባቢ ፊደላትን (consonant) መፃፍና ማንበብ እንደሚገባን ያስተማሩበት ስልት እስካሁን አልረሳውም፡፡ በጣም መሰረታዊ በመሆኑም አስከ አሁንም እንዴት እንደጠቀመኝና እየጠቀመኝም እንዳለ አጉልቼ ማድነቅና መናገር እወዳለሁ፡፡ በጣም የሚገርመኝ ያኔ ሶስተኛ ክፍል በነበርኩበት ጊዜ ልክ ከኤ እሰከ ዜድ (A to Z) እንደ መውጣት ሁሉ ጊዜ ከዜድ ጀምሮ እሰከ ኤ (Z to A) ወደ ላይ ያለምንም መደነቃቀፍ እወጣው ነበር፡፡ የሚገርመው ግን አሁን እንደያኔው በነበረኝ ክህሎት ልወጣው አልችልም፡፡ በትምህርት ላይ በነበርኩበት ጊዜ የነበረኝ ሁለተኛዉ ገጠመኜ የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከተፈተን በኋላ የሚቀጥለውን የትምህርት መስክ ስመርጥ እኔ ምን መሆን ትፈለጋለህ ለሚለው መጠይቅ የህክምና ዶክተር ካልኩኝ በኋላ የት ነው መማር የምትፈልገው ለሚለው መጠይቅ ግን አለማያ እርሻ ኮሌጅ ብዬ መሙላቴ ነበር፡፡ የአለማያ እርሻ ኮሌጅን የመረጥኩት በጊዜው የዕድገት በህብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ ከአሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ስዘምት በያኔው የሐረርጌ ክፍለ ሀገር በጋራ ሙለታ አውራጃ በኩርፋ ጨሌ ወረዳ ተመድቤ ዘምቼ ስለነበር ስለኮሌጁና አካባቢው ሰላወቅሁና አድናቆትም ስለነበረኝ ነበር፡፡

በሥራው ዓለም ከነበሩኝ ገጠመኞች ሁሌም ትዝ የሚለኝና የምናገረው የዛሬ አርባ ዓመት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቄ የምርምር ሥራ ስጀምር በመስክ ላይ ሙከራዎችን ስንዘራ የቴክኒክ ረዳት የነበሩት እነ ጋሼ ተክለ ሃይማኖት ኃይለማርያም 3 – 4 – 5 የሚለውን የጂኦሜትሪ ፅንሰ-ሃሳብ (Pythagoras Theorem, 32 + 42 = 52) ትክክለኛ የአራት ማዕዘን መሬት ላይ ለማምጣት ተጠቅላይ ሜትር በመጠቀምና ሲባጎ ገመድ በመወጠር እንዲሁም እኔ በባዮሜትሪ በቲኦሪ ደረጃ ጥሩ ውጤት አምጥቼ ያለፍሁትን በተግባር ግን ምን እንደሆነ አይቼ ያልነበረውን የራንዶማይዝድ ኮምፕሊት ብሎክ ዲዛይን (RCBD) የሙከራው መሬት ላይ ሲያስቀምጡት ማየቴ ነበር፡፡ ሌላኛው ላነሳወ የምፈልገው ሥራ በጀመርኩባቸው አመታት ኮምፒዩተር ከመምጣቱ በፊት ለብዙ አመታት ለመረጃ ትንተና የምንጠቀመው የጠረጴዛ ላይ ካልኩሌተር (ያውም የሜሞሪ አማራጭ ያለው ከሆነ በጣም ይደንቃል) ለፅሁፍ ደግሞ በእጅ ተፅፎ ለታይፒስት ፀሐፊ በመስጠት ነበር፡፡ ሆኖም በወቅቱ በየካቲት ከዘገየ በመጋቢት መግቢያ በጊዜው ለነበረው አመታዊ ብሄራዊ የሰብል ማሻሻያ ኮንፈርንስ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሪፖርት የሚቀርብበት ነበር፡፡ በመጀመሪያ ኮምፒተርን መጠቀም የተለማመድነው ከአለም አቀፍ በቆሎና ስንዴ ማሻሻያ ድርጅት (CIMMYT) በልገሳ በተገኘ አሮጌ (2 KB) ኮምፒዩተር ነበር፡፡ ዕድሜ ለ Douglas Tanner መጀመሪያ ኮምፒዩተር መጠቀም በተለይ የመረጃ ትንተና ስልቱን (MSTATC or MSTAT4C) ያስተማረን እርሱ ነበር፡፡ የሚገርመኝ ነገር ታዲያ አሁን ኮምፒዩተሮች ያውም ትልቅ ችሎታ ያላቸወ በብዛት እየተጠቀምን እያለን ሪፖርቶች መቅረብ ባለባቸው ጊዜ ማቅረብ አለመቻላቸው ነው፡፡

ምስሉ የሚያሳየዉ እ አ አ በ1994 በሃረማያ ዩኒቨርስቲ በተካሄደ የተማሪዎች ምረቃ ቀን የዚህ ብሎግ ጸሐፊ በማስትሬት የተመረቀበት ቀን ነበር፡፡ በምስሉ የሚታዩት ከግራ ወደ ቀኝ ዘሪሁን ታደለ፣ ሙሉ አየለ፣ ኃይሉ ተፈራ እና ክበበዉ አሰፋ ሲሆኑ በወቅቱ አራቱም የጤፍ ተመራማሪዎች ነበሩ፡፡ ከለበሱት ልብስ እንደሚታየዉ ከዶክተር ኃይሉ በስተቀር የተቀሩት የማስትሬት ምሩቆች ነበሩ፡፡ በርካታ የጤፍ ተመራማሪዎች በዚህ ሥፍራ ሊገኙ የቻሉትም በወቅቱ ከእኔ በስተቀር የተቀሩት ሶስት ተመራማሪዎች የሚሰሩት በሀረማያ ዩኒቨርስቲ ሥር በሚገኘዉ የደብረ ዘይት ምርምር ማእከል ስለነበረ መሥሪያ ቤታቸዉ በአመታዊ የምረቃ በአላት ላይ ይጋብዛቸዉ ስለነበረ ነዉ፡፡

በማጠቃለያ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ ላለፉት 40 ዓመታት ከፍተኛ ዕዉቀትና የሥራ ልምድ በማካበት የተወሰኑ ሳይሆኑ በጤፍ ምርምር እና ልማት ካደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በተጨማሪ ዕዉቀታቸዉን ለወጣት ተመራማሪዎች፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ገበሬዎች እና ሌሎችም ሲያጋሩ ነበር፤ በአሁኑ ጊዜም በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ይህንንም በአግባቡ መጠቀም አለብን እላለሁ፡፡

በዚሁ በሶስት ክፍሎች ዶክተር ክበበዉ አሰፋን በተመለከተ የጻፍኩትን ብሎጎቼን አበቃለሁ፡፡

ወደፊት በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. (April 5, 2023)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የጤፉ ጠቢብ፣ዶክተር ክበበዉ አሰፋ፤ ክፍል 2

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነው ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነው፡፡

የጤፉ ጠቢብ፣ ዶክተር ክበበ አሰፋ፤ ክፍል 2

በዛሬዉ ክፍል 2 ጽሑፌ ዶክተር ክበበው አሰፋ ላለፉት 40 ዓመታት በጤፍ ምርምር ላይ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ ያደረኩላቸውን ቃለ መጠይቅ አስነብባችኋለሁ።

ጥያቄ፤ እርስዎ ከሥራ ባልደረቦችዎ ጋር በርካታ የጤፍ ዝርያዎች እንዲጸድቁ አድርገዋል፡፡ ቢሆንም የሀገሪቱ አማካይ የጤፍ ምርታማነት ከ18 ኩንታል በሄክታር ሊያልፍ አልቻለም፡፡ ይህ ለምን ሊሆን ቻለ?

ዶክተር ክበበዉ፤ በአሁኑ ጊዜ የጤፍ ሀገራዊ አማካይ ምርት 18 ኩንታል በሄክታር ነው፡፡ ለዚህ ዝቅተኛ ምርታማነት አያሌ ምክንያቶች አሉ፡፡ 1ኛ) በምርምር የወጡት ዝርያዎች በተገቢው ሁኔታ በመላው ሀገሪቱ ላሉት የጤፍ አምራች አርሶ አደሮች በሚገባ አልተዳረሱም፡፡ 2ኛ) የወጡት ዝርያዎች ከፍተኛ ምርት ለመስጠት እንዲችሉ የሚያሰፈልጋቸው ተጓዳኝ የአመራረት ቴክኖሎጂዎችና ዘዴዎች ግብአቶችን ጨምሮ በተገቢው መንገድና መጠን በአርሶ አደሮች ዘንድ በጥቅም ላይ አልዋሉም፡፡ 3ኛ) ምንም እንኳን በርካታ ዝርያዎች በምርምር የወጡ ቢሆንም ለሁሉም የተለያዩ ጤፍ አብቃይ ስነ-ምህዳሮችና እንዲሁም የግብርናና ሰብል አመራረት ሥርዓቶች ተስማሚ የሆኑ ዝርያዎችና ቴክኖሎጂዎች ወጥተዋል ማለት አይቻልም፡፡ 4ኛ) የጤፍ ምርታማነትን የበለጠ ለማሳደግና ተወዳዳሪ ለማድረግ በኢትዮጵያ የሚያስፈልገውን ያህል ለጤፍ ምርምርና ልማት የመዋዕለ ንዋይ (ሀብት) ፍሰትና የሳይንሳዊ ዕውቀት ግብዓት ከነአካቴውም የሚገባውን ያህል ትኩረት አልተሰጠውም፡፡  ከዚህ አኳያ በዓለም ላይ ዋነኛ የሆኑት ታዋቂ ሰብሎች (ለምሳሌ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሩዝ፣ ወዘተ) አሁን ያሉበት ደረጃ የደረሱት ምን ያህል የትየለሌ አለም-አቀፍ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ለሳይንሳዊ ምርምርና ልማታቸው ስለተደረገባቸው መሆኑንና አሁንም በቀጣይነት እየተደረገባቸው እንዳለ በአንፃራዊነት መገመት ይቻላል፡፡

ጥያቄ፤ ይህ በዚህ እንዳለ ሞዴል ገበሬዎች የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን እና ግብአቶችን በመጠቀም በሄክታር እስከ 30 እና 35 ኩንታል ሊያገኙ ችለዋል፡፡ በአንጻሩ የጤፍ ምርጥ ዝርያና ቴክኖሎጂ ለአብዘኛዉ አርሶ አደር ባለመዳረሱ የሚገኘዉ ምርት አነስተኛ በመሆኑ ይህንን እንዴት መቀየር እንችላለን ይላሉ?

ዶክተር ክበበዉ፤ ለሀገራችን የጤፍ ልማት አንደኛውና ዋነኛው ክፍተት በምርምር የተገኙ የተሻሻሉ ዝርያዎች አንዲሁም ተጓዳኝ የአመራረት ቴክኖሎጂዎችና ዕውቀቶች በአርሶ አደሮች ዘንድ በስፋት ስላልተዳረሱ እና በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ አለማዋላቸዉ ነዉ፡፡ ስለሆነም አነዚህን ቱክኖሎጂዎችና ዕወቀቶች ለአርሶ አደሮች በተገቢው ሁኔታና መጠን ቀርበው በስፋት በጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም ከዚህ በፊት በነበሩት የጤፍ ቴክኖሎጂዎች ቅድመ-ማሰፋፋትና ማሰፋፋት መርሀ-ግብሮች በተገኘው ተሞክሮ መሠረት እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት የምርምር፣ የዘርና ኤክስቴንሽን ሥርዓቶቹ ተቀናጅተውና ተጠናክረው የጋራ ርብርብ ማድረግና መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡

ምስሉ የሚያሳየዉ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ውስጥ የተዘራዉና በገበሬዎች ዘንድ ተፈላጊ እየሆነ በመጣዉ የኤባ የጤፍ ዝርያ ፊት ለፊት ዶ/ር ክበበው አሰፋ የተነሱት ነዉ፡፡ ፎቶ ዘሪሁን ታደለእ አ አ ኦክቶበር 2022

ጥያቄ፤ በብሔራዊ የጤፍ ምርምር እስካሁን ድረስ ወደ 55 የሚጠጉ ዝርያዎች የተለቀቁ ሲሆን ከነዚህ ዉስጥ አብዘኛዎቹ ነጭ የዘር ሽፋን ያላቸዉ ናቸዉ፡፡ የጤፍ ምርምር ለምን በጥቁር ጤፍ ላይ ትኩረት አላደረገም? በአሁኑ ጊዜስ የምርምር አቅጣጫዉ የዘር መልክን በተመለከተ ምን ይመስላል?

ዶክተር ክበበዉ፤ ቀደም ብሎ ምርምሩ በሁለቱም ማለትም በነጭና በጥቁር የጤፍ ዓይነቶች ላይ በአንድ ላይ በጥምረት እየሰራ የነበረ ቢሆንም የጥቁር ጤፍ ዝርያዎች በአርሶ አደሮቹ እምብዛም ተፈላጊ አልነበሩም። በኋላም የአርሶ አደሮችንና የሌሎችንም ተጠቃሚዎች የጤፍ ዝርያ ዓይነት ፍላጎትና ዝርያዎቹ እንዲኖራቸው የሚፈልጓቸውን ባህርያት ለማወቅ በተደረገው ተሳትፏዊ የዝርያ መረጣ ጥናት አርሶ አደሮች ከገበያ ፍላጎትና ዋጋ አንጻር ከምርታማነትም ባሻገር ለዘር ንጣት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ስለሆነም የጤፍ ዝርያ ምርምር ሥራውን በመካከል ሙሉ በሙሉ በነጭ ጤፍ ላ እንዲያተኩር ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ጤፍ በአጠቃላይ እና በተለይም ጥቁር ጤፍ በዓለም ገበያ ላይ እንዲሁም በሀገራችንም በተለይም በዘመናዊ ሆቴሎችና በተለያዩ የምግብ ዝግጅቶች ላይ የጥቁር ጤፍ እንጄራ እንደ ተወዳጅ ተማራጭ አንዳንዴም የነጭና ጥቁር ጤፍ ቡራቡሬ እንጄራ እጅግ ተፈላጊ  እየሆነ በመምጣቱ ምርምሩ በአሁኑ ጊዜ በነጭና ጥቁር ጤፎች ላይ በሁለቱም ምድብ በመለያየት በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡

ጥያቄ፤ እርስዎ በግልዎ ከነጭ ወይስ ከጥቁር ጤፍ የተጋገረ እንጄራ ነዉ የሚመርጡት? ለምን?

ዶክተር ክበበዉ፤ በአብዛኛው በቤት በቀለብነት የምንጠቀመው ነጭ ጤፍ ቢሆንም በአማራጭነትና በተለይም በበዓላት ጊዜ የጥቁር ጤፍ እንጄራም እንጠቀማለን፡፡ በዝግጅቶች ላይ የጥቁር ጤፍ እንጄራ በተለይም በጥሩ ሁኔታ ከተዘጋጀ መብላት ደስ ይለኛል፡፡

ጥያቄ፤ የሀገራችን ቡና ይርጋጨፌ፣ ሲዳሞ ወዘተ የሚባሉ የምርት ስሞች ወይም ብራንድ (brand) እንዳላቸዉ ሁሉ በጤፍ የሚታወቁ ብራንዶች አሉ? ካሉ የትኞቹ ብራንዶች በተመጋቢዎች ዘንድ በይበልጥ ይመረጣሉ?

ዶክተር ክበበዉ፤ ምንጃር ማኛ፣ አደኣ ማኛ፣ የጊንጪ (ጥቁር) ጤፍ፣ የእንቡር ጤፍ፣ የበቾ ጤፍ፣ የጎጃም (በተለይም የቢቸና) ጤፍ፣ ስማዳ ጤፍ፣ እና የመሳሰሉት በተለያዩ ሀገሪቱ ክፍሎች በአካባቢ ዕውቅና የተሰጣቸው የጤፍ ዓይነቴዎች አሉ፡፡ በሳይንሳዊ ምርምሩም ረገድ የእነዚህን አይነቴዎች ተለያይነትና ልዩ መገለጫ ባህርያታቸውን በመለየት ልክ እንደቡናው ሁሉ ብራንድ (brand or geographical indication) ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

ጥያቄ፤ ብዙ ጊዜ በኮንፈረንሶች ወይም ስብሰባዎች ላይ እርስዎ ንግግር ሲያደርጉ ጤፍ ሲፈጭ ዱቄቱ ይጨምራል፣ ነገር ግን የስንዴ ይቀንሳል ሲሉ እሰማለሁ፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?

ዶክተር ክበበዉ፤ ጤፍ ሲፈጭ ሙሉ በሙሉ ሁሉም እህሉ ዱቄት ይሆናል፡፡ ስንዴን ብንወስድ ግን የዱቄት ምርቱ ከ60-80 ፐርሰንት ብቻ ነው፡፡ ይህ ማለት 100 ኪሎ ጤፍ ብናስፈጭ ሙሉ በሙሉ መቶ ኪሎ ዱቄት እናገኛለ። ስንዴ ከሆነ ግን የምናገኘው ዱቄት ተነፍቶ ከ60-80 ኪሎ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም በሌሎች ሰብሎች እንዲያዉም ከስንዴ በእጅጉ በበለጠ ሁኔታ በተለይም ገብስ፣ በቆሎ እና ማሽላ የመሳሰሉት ሲፈጩ ብዙ ዱቄት ያልሆነ ተረፈ-ምርት (ለምሳሌ ፉርሽካ፤ ገለባና እንቅጥቃጭ) ይወጣል፡፡ ከዚህ እውነታ አኳያ ጤፍ ሲፈጭ ዱቄቱ ይጨምራል የሚለውን ለማሳየት በይዘት (volume) ስንገልፀው በአንድ ከረጢት ሙሉ አድርገን ጤፍንና ሌሎች እህሎችን ወደ ወፍጮ ቤት ይዘን ብንሄድ ለጤፉ ተጨማሪ ሌላ መያዣ ካልያዝን በስተቀር በአንዱ ከረጢት ብቻ ዱቄቱን ሙሉ በሙሉ ይዘን መመለስ የማንችል ሲሆን ለሌሎቹ ሰብሎች ግን ተጨማሪ መያዣ ሳያስፈልገን ዱቄቱን ይዘን መመለስ እንችላለን፡፡ ይህ ማለት ግን የጤፍ ዱቄት መጠኑ በክብደት ሲመዘን ከመጀመሪያው የእህል መጠኑ ጨመረ ማለት ሳይሆን በሚይዘው ቦታ (volume) ይጨምራል ማለት ነዉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በሃገራችን በተለምዶ በተለይም ሴቶች የጤፍ ዱቄት በረከት ያለው ሲሆን የሌሎቹ እህሎች ዱቄት ግን ይናዳል ይላሉ። ይህም የሚሆነው ለምግብ ዝግጅት ዱቄቶቹን ወንፊት በመጠቀም ሲያዘጋጁ ከጤፉ ብዙም የሚጣል የሌለው ሲሆን ከሌሎቹ ሰብሎች ግን ብዙ ጥቅም ላይ የማይውል ከላይ የተገለፀው ተረፈ-ምርት በወንፊት ስለሚወጣ ነዉ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ከጤፍ የምናገኘው የእንጄራ ምርትም ከሌሎች ሰብሎች ከምናገኘዉ ጋር ስናወዳድር  ከጤፍ የምናገኘዉ በቁጥር የበለጠ ነው። ይህ ማለት አንድ ኩንታል (100 ኪሎ) የጤፍ እህል በእንጄራ መልክ ሲጋገር በአማካይ 500 ያህል እንጄራ የሚወጣው ሲሆን ከሌሎች ሰብሎች የምናገኘው የእንጄራ ብዛት ግን በእጅጉ ያነሰ ነው። ይህም የሚሆነው የጤፍ ዱቄት ሲቦካ ብዙ ውሃ ስለሚያነሳ ነው። ከጠቀሜታ አንፃር የጤፍ እንጄራ ምርት ከፍተኛ መሆኑ ብዙ ሰዎችን ለመመገብ ያስችላል ማለት ነው። ምክንያቱም በተለምዶ በሀገራችን ለአንድ ሰዉ በአንድ ጊዜ የሚቀርበው ለምሳሌ በሆቴሎች አንድ እንጄራ አድርገን ብንወስድ ማለት ነዉ።

ሌላው ከዚህ ጋር በተገናኘ ማንሳት የምፈልገው ጤፍ በተፈጥሮው ራሱ እህሉ ለሰው ምግብነት ከሌሎች የብርና አገዳ ሰብሎች እህሎች ጋር ሲወዳደር የተፈለጊ ንጥረ ምግብ ይዘቱ የላቀ ከመሆኑም ባሻገር ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ እንጄራን (ከጤፍም ሆነ ከሌሎች ሰብሎች እህሎች) በዘወትር የቀለብ ምግብ ዓይነትነት የመጠቀማችን ባህል ለምግባችን በንጥረ ምግብ ይዘት መመጣጠን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ይህም የሚሆነው እንጄራ ብቻውን ሳይሆን በወጥ ስለሚበላ ነው፡፡ ስለሆነም በእንጄራው ላይ በአበይነት የተለያዩ ነገሮች (ሽሮ፣ የምስር ወይም የአተር ክክ፣ሥጋ እንዲሁም አትክልት ለምሳሌ ጎመን፣ ሰላጣ፣ ድንች የመሳሰሉት) ሊቀርቡ ስለሚችሉ የንጥረ ምግብ ይዘቱን ያሳድገዋል፡፡ ወጡ ውስጥ ደግሞ በተጨማሪ የተለያዩ ቅመማት እና ስብ (ዘይት ወይም ቅቤ) ሰለሚኖር ምግቡ በአስፈላጊ ንጥረ ምግቦች ይዘት የተሟላ እንዲሆን ይረዳል፡፡

ጥያቄ፤ ብዙ ጊዜ ገበሬዎቻችን መሬቱ ማዳበሪያ ከለመደ በኋላ ሰብሎቻችንን ያለ ማዳበሪያ መዝራት አንችልም ሲሉ ይደመጣል፡፡ መሬት እንዴት ማዳበሪያን ይለምዳል? ይህንን አባባል እርስዎ እንዴት ይረዱታል ወይም ይገልጹታል?

ዶክተር ክበበዉ፤ በአንድ ማሣ ላይ ማዳበሪያ በተለይም የኬሚካል መዳበሪያ ስንጠቀም ለሰብሉ ጠቀሜታ የተጨመሩት በማዳበሪያው ውስጥ ያሉ ለተክል አስፈለጊ ንጥረ ነገሮች ብቻ ሲሆኑ ሰብሉ ግን ሌሎቹን አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች የሚያገኘው በአፈሩ ውስጥ ቀድሞውኑ ከነበረው ይዘት ነው። ይህ ማለት ማዳበሪያ በመጨመራችን ምክንያት ቀድሞውኑ በአፈሩ ውስጥ የነበሩት ንጥረ ነገሮች በተክሉ ጥቅም ላይ በመዋላቸው የአፈሩ የነባር ንጥረ ነገሮች ይዘት እቀነሰ ይመጣል፡፡ ይህንን በተሻለ ሁኔታ በምሳሌ እንደሚከተለው ማስረዳት ይቻላል፡፡ አንድ ከዚህ በፊት ማዳበሪያ ተደርጎበት የማያውቅ ማሣ ወስደን ሌሎች ሁኔታዎችን በሙሉ ተመሳሳይ አድርገን ግማሹን ያለማዳበሪያ ጤፍ ብንዘራውና ሌላውን ግማሽ ደግሞ ለሰብሉ የሚያስፈልገውን የማዳበሪያ ዓይነትና መጠን አድርገን ብንዘራው በማዳበሪያ ከዘራነው ግማሽ መሬት ላይ የበለጠ ምርት እናገኛለን። ሆኖም በሚቀጥለው ዓመት በመጀመሪያ ማዳበሪያ ያደረግንበትን ግማሽ አንዲሁም ማዳበሪያ ያላደረግንበትንም ግማሽ ሁለቱንም ያላማዳበሪያ ብንዘራቸው በመጀመሪያው ዓመት ማዳበሪያ ያደረግንበት ግማሽ ማዳበሪያ ተደርጎበት ካልነበረው ግማሽ ያነሰ ምርት ይሰጣል። ከዚህ አንፃር አርሶ አደሮች በራሳቸው ብሂል መሬቱ ማዳበሪያ ለመደ ማለታቸው ትክክል ነው፡፡

ምስሉ የሚያሳየዉ እ አ አ በ2014 የዚህ ብሎግ ጸሐፊ ያዘጋጀዉንና ከተለያዩ የሀገራችን ምርምር ማዕከላትና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተውጣጡ ሠልጣኞች From Agricultural Problem Identification and Diagnosis to Experimentation and Communication በሚል ርዕስ ሥር የሁለት ሳምንት ሥልጠና በወሰዱበት ጊዜ የተነሱትን ፎቶ ሲሆን ዶክተር ክበበዉ አሰፋ (ከፊት ረድፍ ከመሃከል የሚታዩት) የአሰልጣኞች ቡድንን በመቀላቀል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ጥያቄ፤ ብዙ ጊዜ የጤፍን ምርታማነት በገንዘብ መልክ ስንገለጽ የምናሰላዉ እኛ የምንመገበዉን የፍሬዉን ወይም የዘሩን ምርት ብቻ ነዉ፡፡ ነገር ግን ለተለያዩ ግልጋሎቶች ጥቅም ላይ የሚዉለዉን በተለይም ለከብቶቻችን እንደ ምርጥ መኖነት የሚያገለግለውንና ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣዉን የጤፍን ገለባ ስሌት ዉስጥ አናስገባም፡፡ ይህ ትክክል ነዉ ይላሉ?

ዶክተር ክበበዉ፤ እህሉን ወይም ፍሬውን ብቻ ታሳቢ ማድረግ ተገቢም ትክክልም አይደለም፡፡ ምክንያቱም የጤፍ ሰብል ተረፈ-ምርቱ ማለትም ጭዱ በሀገራችን በዋናነት ለከብት መኖነት እንዲሁም ለቤት ምርጊት ከፍተኛ ኦኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ጭዱ ከሌሎች የብርና አገዳ ሰብሎች ተረፈ-ምርት ወይም ገለባ የበለጠ ለከብቶች አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ-ነገሮች አሉት፡፡ ጭዱ ከላይ የተገለፁት ጠቀሜታዎች ስላሉት ደግሞ በሀገራችን እጅግ በጣም በገበያ ተፈላጊነትና ያለው ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ዋጋ ያወጣል፡፡ ይህንንም በምሳሌ ለማስረዳት የወቅቱን ሀገራዊ አማካይ የጤፍ ምርት ስንወስድ አንድ አርሶ አደር ከአንድ ሄክታር የጤፍ ማሳ ላይ በአማካይ 19 ኩንታል የእህል ምርት ሲያገኝ በተጨማሪ 13280 ኪሎ ግራም ጭድ ያገኛል፡፡ የዘንድሮን የገበያ ዋጋ መሠረት አደርገን ብናሰላ ከእህሉ ሽያጭ 123500 ብር (19 ኩንታል X በ6500 ብር በኩንታል) ያገኛል፡፡ በተጨማሪ አንደ እስር ጭድ (Bale) 18 ኪሎ ግራም ያህል ይመዝናል በሚለው ስሌት ብንወስድ የጭዱ ጠቅላላ ምርት በግምት ወደ 740 እስር (Bale) በሄክታር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህንን አሁን ባለው የገበያ ዋጋ እጅግ አሳንሰን አንድ እስር (Bale) 50 ብር ነው ብለን ብንወስድ ከጭዱ ሽያጭ ብቻ አርሶ አደሩ ከአንድ ሄከታር 37000 ብር (740 እስር X 50 ብር በአንድ እስር) ያገኛል ማለት ነው። ስለዚህ የጤፍ ሰብልን ምርታማነት በገንዘብ ስሌት ስንገልፀው በእህሉ ብቻ ሳይሆን በተጨማሪ ጭዱንም ታሳቢ አድርገን መሆን ይኖርበታል፡፡

ጥያቄ፤ የኮታቻ መሬት ከስንዴ ይልቅ በይበልጥ ለምን ለጤፍ እርሻነት ሊመረጥ ቻለ?

ዶክተር ክበበዉ፤ የኮትቻ አፈር ዋነኛ ባህርያት በዝናብ ጊዜ ከመጠን በላይ የእርጥበት ዕዝለት ወይም ውሃ አለመጠንፈፍ (Waterlogging) በደረቅ ጊዜ ደግሞ መኮማተረና መሰንጠቅ ናችው፡፡ ጤፍ የአፈር ወይም የመሬት የበዛ እርጥበት ዕዝለትን (waterlogging) ከሌሎች ሰብሎች (ማለትም ስንዴ፣ በቄሎ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ ወዘተ) ይልቅ የመቋቋም ችሎታ ስላለው ለመረሬ ኮትቻ አፈር ተስማሚና ተመራጭ ሰብል አድርጎታል፡፡

ጥያቄ፤ ሜካናይዜሽን በጤፍ ግብርና ላይ ለምን በሰፊዉ ሊተገበር አልቻለም?

ዶክተር ክበበዉ፤ ሜካናይዜሽን በጤፍ ግብርና ላይ በሰፊዉ ሊተገበር ያልቻለበት ምክንያቶች በርካታ ናቸው፡፡ ከነዚህም መካከል ዋናዎቹ፤ 1ኛ) የጤፍ  የዘር መጠን በጣም ትንሽ (ደቃቃ) በመሆኑ የለሰለሰና የተስተካከለ የመሬት ዝግጅት ስለሚፈልግ እንዲሁም ለመዝራትም ሆነ ለማጨድና ለመውቃት ለሰብሉ ተስማሚ የሆነ መሳሪያ ሰለሚያስፈልገው፣ 2ኛ) የጤፍ ሰብል በአብዛኛው የሚዘራዉ በመረሬ ኮትቻ አፈር ላይ ስለሆነና በሚዘራበት ወቅትም በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት መሬቱ በጣም ጭቃ ሆኖ በላቆጠበት ጊዜ መሆኑ፣ 3ኛ) የጤፍ ሰብል ከፍተኛ የመውደቅና መጋሸብ ባህርይ ስላለው ለማጨድና ለመውቃት አስቸጋሪ ስለሚያደርገው፣ እና 4ኛ) ሰብሉ በእህልነት በዓለም ላይ በዋናነት በኢትዮጵያና ኤርትራ የሚመረት በመሆኑ ተስማሚ የሆኑ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን ያላወጣንለት ወይም ያልሰራንለት ከመሆኑም በላይ በሌሎች ዓለማት ለሌሎቹ ተመሳሳይ (ለምሳሌ ስንዴ፣ ገብሰ፣ ሩዝና ወዘተ የመሳሰሉት) ሰብሎች የተሰሩት ማሽኖችና መሳሪያዎች በቀጥታ ለጤፍ ልንገለገልባቸው የማይቻል መሆኑ ናቸው፡፡

ጥያቄ፤ በሀገራችን የጤፍ አብቃይ ሥፍራዎች ዉስጥ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡት የትኞቹ ናቸዉ?

ዶክተር ክበበዉ፤ ሰሜን ሸዋ (ምንጃር ሽንኮራ፣ ሞረትና ጅሩ)፣ ምስራቅ ሸዋ (አደኣ፣ ሉሜ፣ ጊምቢቹ፣ አቃቂ)፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ደቡበ ምዕራብ ሸዋ፣ ሆሮጉደሩ ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም) ናቸዉ።

ጥያቄ፤ የጤፍ ምርምርና እና ልማትን ለመጎብኘት እርስዎ የተጓዙባቸዉን የሀገራችንን ሥፍራዎች ቢገልጹልኝ፡፡

ዶክተር ክበበዉ፤ በአጠቃላይ እንደ አንድ በጤፍ ላይ ሙሉ ዕድሜውን (ለአርባ ዓመታት ያህል) በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሰራ ተመራማሪ በሁሉም በተለይም በዋና ዋና የጤፍ አምራች የሀገራችን ሥፍራዎች ከምስራቅ እሰከ ምዕራብ እንዲሁም ከሰሜን እሰከ ደቡብ ሄጃለሁኝ ማለት እችላለሁ፡፡ ለዚህም የረዳኝ በአብዛኛው በተለያዩ ጊዜያት የጤፍ ነባር የአርሶ አደር ዝርያዎችን ናሙና ለመሰብስብ፣ ለጤፍ ግብርና ተስማሚ ሊሆኑ የሚችሉ ሥፍራዎችን የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ፣ እና እንዲሁም በጤፍ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪነት የሥራ ድርሻዬ ጊዜ እና በሌሎችም መርሃ ግብሮች ላይ በመሳተፍ በሀገሪቱ በተለያዩ ክፍሎች ለመዘዋወር እድሎችን ማግኘቴ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይህ ማለት ያልሄድኩባቸው ጥቂት ጤፍ የሚመረትባቸው ኪስ (pocket) ቦታዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡

ጥያቄ፤ በከተሞች መስፋፋት ምክንያት የጤፍ አብቃይ ሥፍራዎች በከፍተኛ ደረጃ እየተመናመኑ ይገኛል፡፡ ይህም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ከሚመጣዉ ህዝባችን ጋር ተያይዞ በምግብ ዋስትናችን ላይ አሉታዊ ጎን ይኖረዋል የሚል ሥጋት አለኝ፡፡ እርስዎም የኔን ሥጋት ይጋራሉ?

ዶክተር ክበበዉ፤ እኔም ይህንን ሥጋት ሙሉ በሙሉ እጋራለሁ፡፡ ምክንያቱም አሁን እዚህ ባለንበት መካከለኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች በምናየው እንኳን በከተማዎችና እንዱስትሪዎች መስፋፈት ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ በዋናነት የጤፍ አብቃይ መሬቶች ለምሳሌ በዱከም፣ ቢሾፍቱ፣ኡዴ፣ድሬ፣ አቃቂ፣ ገላን፣ አዲስ አበባ፣ እና ሉሜ አካባቢዎች በእጅጉ እየተመናመኑ ናቸው፡፡ ብዙ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮች ጭምር እንደሚሉት አሁን ባለው ሂደት ከቀጠለ ለምሳሌ በብራንድ ደረጃ የሚታወቀው የአደአ ማኛ ጤፍ ወደፊት በቅርብ ዓመታት ውስጥ ሊኖር አይችልም። ይህ ማለት ግን ከተሞችም ሆኑ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የለባቸውም ማለት ሳይሆን ከተሞች ለከት በሌለው ሁኔታ የጎንዮሽ መለጠጥ ሳይኖርባቸው ያሉትን ቦታዎች በተገቢው ሁኔታ አሟጦና ወደ ላይ እንዲያድጉ አድርጎ በመጠቀም እንዲሁም ከተሞችም ሆኑ ኢንዱስትሪዎች በሌሎች ለግብርና ልማት አመቺ ባልሆኑ መሬቶች ላይ እንዲያርፉ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ እንደ መርህ ከተሞችና እንዲስትሪዎች ለግብርና ልማት የበለጠ አመቺ የሆኑት መሬቶች ላይ ጫና እምብዛም ሳይኖራቸው መስፋፋት ያለባቸው በጥናት የመሬት አጠቃቀም እና ምደባን (land use and capability classification) መሠረት አድርገው መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

ጥያቄ፤ የዛሬ 10 ዓመት እርስዎ የሚያስተባብሩት የብሔራዊ ጤፍ ምርምር ቡድን የብሔራዊ ሽልማት የሚባል ሽልማትና ዋንጫ መሸለማችሁ ይታወቃል፡፡ የዚህ ታላቅ ሽልማትና ዕዉቅናን እንዴት የጤፍ ምርምር ቡድን ሊያሸንፍ ቻለ?

ዶክተር ክበበዉ፤ የብሔራዊ ጤፍ ምርምር ቡድን እ አ አ በ2012 ብሔራዊ የአንደኛ ደረጃ የዋንጫና የሜዳልያ ሽልማት ያገኘው በጊዜው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በችግር ፈቺ የምርምር ውጤት በሀገር አቀፍ ደረጃ ባደረገው ውደድር ቡድኑ በተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎች በተለይም በቁንጮ የጤፍ ዝርያ ማፍለቅ በተገኘው የላቀ ውጤት በቀደምትነት አሸናፊ በመሆን ነው። ቡድኑን በመወከልም በወቅቱ ከነበሩት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒሰቴር እጅ ሽልማቶቹን ተቀብለናል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይም የቁንጮ ጤፍ ቴክኖሎጂን ከማፍለቅ አኳያ ግንባር ቀደም የነበሩት ሌሎች ተመራማሪዎች በተለይም ዶክተር ኃይሉ ተፈራና ዶክተር ጌታቸው በላይ በወቅቱ በሽልማቱ ጊዜ ስላልነበሩ እንጂ የአንበሳውን ድርሻ ሊሰጣቸው ይገባል ብዬ አምናለሁ።

በክፍል 3 ጽሑፌ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ በኢትዮጵያ ግብርና እና ዕድገት በሚመለከት ያደረኩላቸዉን ቃለ መጠይቅና የሰጡኝን መልስ አስነብባችኋለሁ፡፡ እስከዛዉ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መጋቢት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. (April 2, 2023)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የጤፉ ጠቢብ፣ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ፤ ክፍል 1

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሑፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡

የጤፉ ጠቢብ፣ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ፤ ክፍል 1

በዛሬዉ ጽሑፌ በግብርናዉ መስክ ከፍተኛ ዕዉቀትና የሥራ ልምድ ስላካበቱትና በተለይም በጤፍ ላይ ላለፉት 40 ዓመታት በምርምርና ልማት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ስላሉት ስለ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ አስነብባችኋለሁ፡፡ የጤፉ ጠቢብ የሚል መጠሪያ የሰጠኋቸዉም እስካሁን ድረስ ከነበሩት የጤፍ ተመራማሪዎች መካከል እንደ ዶክተር ክበበዉ ለረጅም ጊዜ በአንድ ሰብል ላይ የሰራ ወይም ያገለገለ ስላላጋጠመኝ ነዉ። ምናልባትም በሀገራችን ካሉ ተመራማሪዎች ሁሉ በአንድ ሰብል ላይ ብቻ ለረጅም ጊዜ በማገልገል ዶክተር ክበበዉ ግንባር ቀደም እንደሚሆኑ አልጠራጠርም።

በነሐሴ 22 ቀን 1951 (እ አ አ ኦጎስት 28፣ 1959) አርሲ ውስጥ በምትገኘዉ ሁሩታ የተወለዱት ዶክተር ከበበዉ የመጀመሪያ ዲግሪያቸዉን ካገኙበት እ አ አ 1983 ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ቢሾፍቱ በሚገኘዉ የደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ምስሉ የሚያሳየዉ እ አ አ በ2012 በደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል በተዘጋጀዉ አጭር ሥልጠና ላይ ተሳታፊዎችን የሚያሳይ ሲሆን ዶክተር ክበበዉ (ከፊት ረድፍ ካሉት ከግራ ወደ ቀኝ አራተኛዉ) ሥልጠናዉን ከሰጡት መካከል አንዱ ነበሩ፡

ከዚህ በታች የዶክተር ክበበዉ አሰፋን የትምህርት ዝግጁነትና የሥራ ልምድ እንዲሁም አስተዋጽኦ በአጭሩ አቀርባለሁ፡፡

የትምህርት ዝግጁነት

  • ፒ ኤች ዲ፣ እ አ አ በ2003፣ በዕጽዋት ቢሪዲንግ እና ጄኔቲክስ፣ ከስዊዲሽ ዩኒቨርስቲ ኦፍ አግሪከልቸራል ሳይንስ፣ ስዊድን
  • የሁለተኛ ወይም የማስተር ዲግሪ፣ እ አ አ በ1991፣ በአግሮኖሚ፣ ከሃረማያ ግብርና ዩኒቨርሲቲ፣ ኢትዮጵያ
  • የመጀመሪያ ዲግሪ፣ እ አ አ በ1983፣ በዕጽዋት ሣይንስ (በማዕረግ)፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ኢትዮጵያ
  • የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት፣ እ አ አ በ1979፣ ከአሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ አሰላ
  • የመጀመሪያ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት፣ እ አ አ በ1973፣ ከንጉሥ ሐይለመለኮት ትምህርት ቤት፣ ሁሩታ

ተጨማሪ ሥልጠናዎች

  • ሙቴሽን ቢሪዲንግ ለሰብል ማሻሻያ (Mutation for Crop Improvement)፣ ለአንድ ዓመት እ አ አ 1994/95፣ ሲሌሲያን ዩኒቨርስቲ፣ ፖላንድ
  • ፕሮጀክት ዲዛይን፣ ለአንድ ወር እ አ አ በ1993፣ ዩኒቨርስቲ ኦፍ አምስተርዳም

የሥራ ልምድ (በከፊል)

  • መሪ ተመራማሪ (Lead Researcher)፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ እ አ አ ከ2017 አንስቶ እስከ አሁን
  • ከፍተኛ ተመራማሪ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ደብረ ዘይት ምርምር ማዕከል፣ እ አ አ አ ከ2004 እስከ 2017
  • ረዳት ፕሮፌሰር፣ ሃረማያ ዩኒቨርስቲ፣ እ አ አ ከ2003 እስከ 2004
  • ሌክቸረር፤ ሃረማያ ዩኒቨርስቲ፣ እ አ አ ከ1985 እስከ 2003

በኃላፊነት የሰሩባቸዉ ቦታዎች (በከፊል)

  • መሪ ተመራማሪ (Lead Researcher)፤ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፤ እ አ አ ከ2017 አንስቶ እስከ አሁን
  • ዋና ተመራማሪ (Principal Investigator)፤ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ ፕሮጀከት፤ እ አ አ ከ2015 እስከ 2017
  • አስተባባሪ፤ የብሔራዊ የጤፍ ፕሮግራም፤ እ አ አ ከ2008 አንስቶ እስከ 20018
  • ዳይሬክተር፤ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የደብረ ዘይት ምርምር ማዕከል፤ እ አ አ ከ2006 እስከ 2009
  • ብሔራዊ አስተባባሪ እና ዋና ተመራማሪ፤ ትኩረቱን በሽንብራ ላይ ያደረገዉ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እና የኢክሪሳት ትብብር ፕሮጀክት፤ እ አ አ ከ2007 እስከ 2009
  • ዋና ተመራማሪ፤ በጤፍ ምርምር ትኩረት ያደረገ የማክናይት ትብብር ፕሮጀክት

ምስሉ የሚያሳየዉ እ አ አ በ2019 በተካሄደዉ ሶስተኛዉ ዓለም አቀፍ የጤፍ ኮንፈረንስ ላይ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ሲያደርጉ ነዉ፡፡ ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ፡፡

ያሳተሟቸዉ ጽሑፎች፤ በአጠቃላይ 150 ሲሆኑ ከነዚህ ዉስጥ 100 የሚሆኑት በሳይንሳዊ ጆርናሎች የታተሙ ናቸዉ፡፡

የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎች ማጸደቅ፤ በሀገራችን የተለያዩ ወካይ አግሮኢኮሎጊዎች ተገምግመዉ እንዲጸድቁ ከተደረጉት የጤፍ ዝርያዎች መካከል ዶክተር ክበበዉ በአብዘኛዎቹ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳትፈዋል፡፡

የተበረከተላቸዉ ሥጦታዎች ወይም ዕውቅናዎች (በከፊል)

  • የዕድሜ ልክ የስኬት ሽልማት (Life Time Achievement Award)፤ በኢትዮጵያ የሰብል ሣይንስ ባለሙያዎች ማህበር፤ ለሰብል ሣይንስ ምርምር እና ልማት ላደረጉት የላቀ አስተዋጽኦ፤ እ አ አ ፌብሪዋሪ 2023
  • የኢትዮጵያ ስጦታ (Gifts of Ethiopia Award)፤ በዋን ኦፍ ዘጊፊት ኦፍ ኢትዮጵያ አዋርድ የጤፍ ምርምር እና ልማትን ለማስፋፋት ላደረጉት ቁርጠኝነት፤ እ አ አ ዲሴምቤር 2021
  • ከፍተኛ የክብር ተሸላሚ (Higher Honor Laureate)፤ የአብሲኒያ ሽልማት፤ የእድሜ ልክ የግብርና ምርምር ምድብ፤ እ አ አ 2019
  • ባልደረባ (Fellow)፤ የኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ፤ እ አ አ ከ2015 ጀምሮ
  • የብሔራዊ ሽልማት፤ ለጤፍ ምርምር ቡድን፤ በጤፍ ምርምር ላገኙት ከፍተኛ ግኝት በተለይም የቁንጮ ዝርያ ቴክኖሎጂን በሚመለከት፤ በኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፤ እ አ አ በ2012

ምስሉ የሚያሳየዉ እ አ አ በፌብሪዋሪ 2023 በተካሄደዉ የኢትዮጵያ የሰብል ሳይንስ ባለሙያዎች ኮንፈረንስ ላይ ለዶክተር ክበበዉ አሰፋና ዶክተር በዳዳ ግርማ የህይወት ዘመን ዕዉቅና ሽልማት (Life Time Achievement Award) የተሰጠበት ሥነ ሥርዓት ነዉ፡፡ ከግራ ወደ ቀኝ ዶክተር በዳዳ ግርማ፣ ዶክተር ድሪባ ገለቲ፣ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ፣ ዶክተር ታዬ ታደሰ እና ዶክተር ካሳዬ ቶለሳ፡፡ ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፣ የካቲት 17 ቀን 2015።

ከላይ እንደተገለጸዉ ዶክተር ክበበው በርካታ አስተዋጽዎችን ማድረጋቸዉ ብቻ ሳይሆን ለነዚህ የላቁ አስተዋጽዎችም በርካታ ስጦታዎችንና ዕዉቅናዎችን አግኝተዋል።

በክፍል 2 ጽሑፌ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ በጤፍ ምርምር እና ልማት ላይ ያደረጉትን አስተዋጽኦ በሚመለከት ለቃለ መጠይቄ የሚሰጡኝን እጽፋልሁ፡፡ እስከዛዉ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. (March 28, 2023)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ ስትራቴጂስቱና የግብርና ባለሙያዉ፣ ዶክተር ይልማ ከበደ፤ ክፍል 1

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡

ስትራቴጂስቱና የግብርና ባለሙያዉ፣ ዶክተር ይልማ ከበደ፤ ክፍል 1

በዛሬዉ ጽሑፌ በግብርናዉ መስክ ከፍተኛ ዕዉቀትና የሥራ ልምድ ስላካበቱትና ይህንንም ለተተኪዉ ትውልድ በማስተላለፍ ላይ ሰለሚገኙት ስለ ዶክተር ይልማ ከበደ አስነብባችኋለሁ፡፡

ዶከተር ይልማ ከበደ ከ40 ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ በምግብ ዋስትና ላይ የሰሩ ሲሆን በተለይም በሰብል ማሻሻያ፣ በዘር ሲስተም እና በመሳሰሉት ላይ በሀገር ዉስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸዉ፡፡ እስካሁን ድረስ የሠሩባቸዉ ድርጅቶችም በርካታ ሲሆኑ እነርሱም የምርምር ማዕከላትን፣ የግል ድርጅቶችን፣ እና ግብረ ሠናይ ድርጅቶችን ያካትታል። ከነዚሁ ድርጅቶች ጋር በምርምር እና ስትራቴጂ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገዉ ሰርተዋል፡፡ ለዚሁም ነዉ ከግብርና ባለሙያነታቸዉ በተጨማሪ ስትራቴጂስቱ የሚል መጠሪያ የሰጠኋቸዉ፡፡

የዶክተር ይልማ ከበደን የትምህርት ዝግጁነትና የሥራ ልምድ እንዲሁም አስተዋጽኦ ከዚህ በታች በአጭሩ አቀርባለሁ፡፡

የትምህርት ዝግጁነት

  • ፉል ብራይት ፖስት ዶክ (post doc)፣ ከፐርዱ ዩኒቨርስቲ፣ አሜሪካ
  • ፒ ኤች ዲ፣ በዕጽዋት ቢሪዲንግ እና ጄኔቲክስ፣ ከቴክሳስ ኤ ኤንድ ኤም ዩኒቨርስቲ፣ አሜሪካ
  • የሁለተኛ ወይም የማስተር ዲግሪ፣ በሰብል ፊዚዮሎጂ፣ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ገልፍ፣ ካናዳ
  • የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በዕጽዋት ሣይንስ፣ ከሃረማያ ዩኒቨርስቲ፣ ኢትዮጵያ

የሥራ ልምድና ቀደም ብሎ የነበራቸዉ ከፍተኛ ኃላፊነቶች

  • አባል፤ የምርምር ፕሮግራም መሪ ኮሚቴ፤ የደረቅ ሥፍራ ሰብሎች (Dryland Cereals-CGIAR)
  • አባል፣ የመማክርት ቡድን፤ የአግራ ፓስ (AGRA-PASS)
  • አባል፤ ዓለም አቀፍ የስኮላር ሺፕ ኮሚቴ፤ ፓዮኒር ሃይ ብሪድ (Pioneer Hi-Bred)
  • አባል፤ የሰብል ብዝሀ ዘር ኮሚቴ፣ ዩ ኤስ ዲ ኤ /ኤ አር ኤስ (USDA/ARS)
  • ኃላፊ፣ የሰብሎች ማሻሻያ ፕሮግራሞችን የሚገመግም ታስክ ፎርስ፤ ኢክሪሳት (ICRISAT)
  • ኃላፊ፤ በምዕራብ፣ ምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የሰብል ማሻሻያ ፕሮግራሞች ላይ ምክር የሚሰጥ ቡድን፣ ኢክሪሳት (ICRISAT)
  • ከፍተኛ የፕሮግራም ኦፊሰር፤ ቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን (BMGF)፤ እ አ አ ከ2008 እስከ 2016 ይህንን ፕሮግራም ሲመሩ የብዕርና አገዳ ሰብሎች ምርታማነት እንዲያድግ የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፈዋል። በተለይም የማሽላና ዳጉሣ ምርታማነት እንዲያድግ በሚያስችል ፕሮጀክት ውስጥ በመሳተፍ ጉልህ ሚና ተጫዉተዋል። በዚሁ በተሳተፉበት የስትራቴጅ ንድፍም በኢትዮጵያ የግብርና ልማት ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ የኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ (በአሁኑ አጠራር የኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት) እንዲቋቋም መሠረት ጥሏል።
  • አስተባባሪ እና ተመራማሪ፤ ዱ ፑንት /ፓዮኒር ሃይ ብሪድ (DuPont/Pioneer Hi-Bred)፤ እ አ አ ከ1992 እስከ 2008  በካምፓኒዉ የማሽላ ፕሮግራምን በቴክሳስ፣ ሜክሲኮ፣ ህንድ እና አዉስትራሊያ ባስተባበሩበት ወቅት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንዲወጡ ከማስደረጋቸዉም በላይ በርካታ የበቆሎ፣የማሽላ እና የሱፍ ዝርያች በተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች እንዲጸድቁና እንዲሰራጩ አስችለዋል
  • ተመራማሪና አስተባባሪ፤ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የማሽላ ፕሮግራም
  • የማዕከል ዳይሬክቴር፤ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የመልካሳ ምርምር ማዕከል

ባሁኑ ጊዜ የሚሳተፉባቸዉ የኮሚቴ ወይም የማማከር ኃላፊነት

  • አባል፣  የአስተዳድር ቦርድ፤ ኢክሪሳት (ICRISAT)
  • ሊቀመንበር፣ የፕሮግራም ኮሚቴ፤ ኢክሪሳት (ICRISAT)
  • አባል፣ የሰብል ማሻሻያ ፕሮግራሞችን ገምጋሚ ቡድን። ቴክኖሎጂዎችን መፈተሽ፣ የዘር አቅርቦትን ማሳደግን እና የፕሮግራሞች ተጽዕኖን መገምገም፤ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኪዉንስላንድ፣ አውስትራሊያ
  • አባል፤ የአማካሪ ቦርድ፤ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቱት

ያሳተሟቸዉ ጽሑፎች፤ ከ40 የሚበልጡ በተለያዩ የግብርና መስኮች ላይ ያተኮሩ ጽሑፎችን አበርክተዉልናል፡፡

መዋዕለ ንዋይ የማስገኘት (grant making) ችሎታቸዉና ልምዳቸዉ፤ ዶክተር ይልማ የተለያዩ ሀገራት በጋራ ፕሮጀክቶች ነድፈዉ ከለጋሽ ድርጅቶች ወይም ሀገራት የፋይናንስ ዕርዳታ የሚያገኙበትን መንገድ በመንደፍና በማስተባበር ሰርተዋል። ለምሳሌቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን (BMGF) ይሰሩ በነበረበት ወቅት በአፍሪካ በተለይ የማሽላና የዳጉሳ ምርጥ ዘሮች እንዲገኙ በሚደረጉ ምርምሮችና ምርጥ ዝርያዎችን ለማሰራጨት ተብሎ የተፈቀደዉን ከ200 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ለአግራና ኢክሪሳት እንዲፈቀድ ከፍተኛ ሚና ተጫዉተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ፋይናንስ የማስገኘት ፕሮጀክቶች ዉስጥ ቁልፍ ሚና ተጫዉተዋል።

ምስሉ የሚያሳየዉ ኢክሪሳት (ICRISAT) በሚባለዉና መቀመጫዉን ህንድ ሀገር ያደረገ ዓለም አቀፍ የሰብል ምርምር ድርጅት የቦርድ አባላትን ሲሆን ዶክተር ይልማም (በስተግራ የሚታዩት) በአሁኑ ወቅት የዚሁ ከፍተኛ ኃላፊነት የተሰጠዉ ቦርድ አባል ሆነዉ በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ምንጭ፤ https://www.icrisat.org/101st-governing-board-meeting-at-icrisat-headquarters-in-hyderabad/

የላቀ የግብርና ሣይንስ (Advaces in Agricultural Science) ሲምፖዚየም በዚህ ርዕስ ሥር እኔ (የዚህ ብሎግ ጸሐፊ) ሁለት ሲምዚየሞችን በአዲስ አበባ አዘጋጅቼ ነበር። በሁለቱም ሲምፖዚየሞች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ተመራማሪዎች፣ የየኒቨርስቲ መምህራንና የተጋበዙ እንግዶች የተገኙ ሲሆን ዶከተር ይልማም በሁለቱም ሲምፖዚሞች ጉልህ ሚና ተጫውተዋል። 
ጥቅምት 14 ቀን 2007 (እ አ አ ኦክቶበር 24፣ 2014) በተካሄደዉና ምርምር በኢትዮጵያ ግብርና ልማት፤ የሚጠበቁ ነገሮች እና ዕድሎች (R4D in the Ethiopian Agriculture: Expectations and Opportunities) በሚል ርዕስ ሥር በተካሄደዉ በመጀመሪያዉ ሲምፖዚየም ላይ ዶክተር ይልማ በምርምር እና በልማት ሥራ የተገኙ ትምህርቶች፣የግል ተሞክሮዬ (Lessons learned from a career in research and development: a personal experience) በሚል ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆነ በተካሄደዉ የፓናል ውይይትም ላይ ተሳትፈዋል። 

በተጨማሪም ጥቅምት 14፣ 2012 ዓ.ም. (እ. ኤ. አ. ኦክቶበር 25, 2019) በተካሄደዉ ሁለተኛዉ የላቀ የግብርና ሣይንስ (Advances in Agricultural Science) ሲምፖዚየም ከመሳተፋቸዉም በተጨማሪ በተካሄዱ ውይይቶች ላይ ተሳትፈዋል።

ምስሉ የምያሳየዉ ጥቅምት 14 ቀን 2007 (እ አ አ ኦክቶበር 24፣ 2014) በተካሄደዉ የመጀመሪያዉ የላቀ የግብርና ሣይንስ (Advances in Agricultural Science) ሲምፖዚየም ተሳታፊዎችን ሲሆን  ዶክተር ይልማ ከፊት ተርታ (ከግራ ወደ ቀኝ) ሶስተኛዉ ናቸዉ። ፎቶ፤ ዘሪሁን ታደለ

ምስሉ የሚያሳየዉ ጥቅምት 14፣ 2012 ዓ.ም. (እ. ኤ. አ. ኦክቶበር 25, 2019) በተካሄደዉ ሁለተኛዉ የላቀ የግብርና ሣይንስ (Advances in Agricultural Science) ሲምፖዚየም ተሳታፊዎችን ነዉ።

በአጠቃላይ  ዶክተር ይልማ ያላቸዉን ዕዉቀትና ረዘም ያለ የሥራ ልምድ በመጠቀም በሙያዉና በሥራዉ  ጠንካራ የሆነ ትዉልድ ለመገንባት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዚሁም ምስክር የሚሆነዉ በቅርቡ በተካሄደዉ 19ኛዉ የኢትዮጵያ የሰብል ባለሙያዎች ኮንፈረንስ ላይ ወጣት ተመራማሪዎች ጽሑፎቻቸዉን ለማሳተም እና የምርምር ዉጤታቸዉን በኮንፈረንስ ለማቅረብ በሚያስቡበት ወቅት ሊያማክሯቸው እንደሚችሉ ቃል መግባታቸዉ ነዉ፡፡ እኔም እኚህን ታላቅ ምሁር እንጠቀምባቸዉ እላለሁ፡፡

በክፍል 2 ጽሑፌ ዶክተር ይልማ በማሽላ ምርምር እና ልማት ላይ ያደረጉትን አስተዋጽኦ በሚመለከት እጽፋልሁ፡፡ እስከዛዉ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መጋቢት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. (March 18, 2023)

ግብርናችንን ለማዘመን፤19ኛዉ የኢትዮጵያ ሰብል ሳይንስ ባለሙያዎች ኮንፈረንስ

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡

19ኛዉ የኢትዮጵያ ሰብል ሳይንስ ባለሙያዎች ኮንፈረንስ

በየሁለት ዓመት የሚካሄደዉ 19ኛዉ የኢትዮጵያ ሰብል ሳይንስ ባለሙያዎች ኮንፈረንስ አዲስ አበባ በሚገኘዉ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ምስሪያ ቤት ህሩይ አዳራሽ ከየካቲት 17 እስከ 18፣ 2015 (ወይም እ አ አ ፌብሪዋሪ 24 እስከ 25፣ 2023) ተካሂዷል፡፡ በዚሁ ኮንፈረንስ ላይ ከ200 ያላነሱ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የመስኩ ባለሙያዎችና የማህበሩ አባላት ተሳትፈዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የማህበሩ ፕሬዘዳንት ዶክተር ታዬ ታደሰ ሲሆኑ ኮንፈረንሱን በንግግር የከፈቱት ደግሞ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክቴር ዶክተር ድሪባ ገለቴ ናቸዉ፡፡

በመቀጠልም ሁለት ኪ ኖት መልእክቶች (keynote addesses) የተሰጡ ሲሆን እነርሱም

ዶክተር ድሪባ ገለቴ (ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት)፤ ‘‘የተሻሻለ ግብርና ለምታድግ ኢትዮጵያ‘‘

ዶክተር ፍሬው መክብብ (ከሀረማያ ዩኒቨርሲቲ)፤ ‘’የተሻሻለ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ግብርና ላይ ያለው ሚና’’

በተጨማሪም የፓናል ውይይት የተዘጋጀ ሲሆን በውይይቱ እንዲሳተፉ የተጋበዙት ሶስት ምሁራን በሚከተሉት ርዕሶች ጽሑፍ እንዲያቀርቡም ተጋብዘዉ ነበር፡፡

ዶክተር ይልማ ከበደ (ኪዊንስላንድ ዩኒቨርሲቲ፣ አዉስትራሊያ)፤ ‘’የሰብል ማሻያን ዘመናዊ ለማደግ የሚደረገዉ ጥረትና አዳዲስ የፈጠራ ዉጤቶን በተከታታይነት ለመጠቀም ያለዉ ዉስንነት’’

ፕሮፌሰር ዘሪሁን ታደለ (ከበርን ዩኒቨርሲቲ፣ ስዊዘርላንድ)፤ ‘’በኢትዮጵያ የሰብል ማሻሻያ ላይ የባዮቴክኖሎጂ አተገባበር፡ ተግዳሮቶቹ እና የወደፊት የተፅዕኖ አቅጣጫ’’

ዶክተር ዳዊት አለሙ (የዋግንገን ኔዘርላንድ ምርምር የኢትዮጵያ ተወካይ)፤ ‘’ለታዳጊ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች የምግብ፣ መኖና ግብአት ለማርካት በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት በማስተካከል ወቅታዊ ትምህርቶችና የወደፊት አቅጣጫዎች’’

በመቀጠልም የፓናል ዉይይቱን ከሚመሩት (moderator) በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ በፓናል ተሳታፊዎች ውይይት የተደረገ ከመሆኑም በላይ የኮንፈረሱ ተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችንና ምክረ ሀሳቦችን ለግሰዋል፡፡

በሁለተኛዉ የኮንፈረንስ ቀንም በሁለት ምሁራን የፓናል ውይይት የቀረበ ሲሆን እነርሱም

ዶክተር መልካሙ በየነ (ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)፤ ‘’የኢትጵያ ሰብል ሳይንስ ጆርናል ህትመትን ዘናዊነት ማላበስ’’

ፕሮፌሰር ሽመልስ አድማሱ (ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)፤ ‘’የሰብሎችን የአመጋገብ ጥራት ለማሻሻል እና የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ የለውጥ ፈጠራዎች’’

ሁለቱ ምሁራን ባቀረቧቸዉ ጽሑፎች በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች ከኮንፈረንሱ አወያይና ተሳታፊዎች የቀረቡ ሲሆን ሰፊ ውይይትም ተደርጎባቸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በሁለቱ ቀናት የኮንፈረንሱ ዉሎ በርካታ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን እነርሱም የሰብል ማሻሻያን፣ አግሮኖሚን፣ የሰብል ጥበቃን፣ የምግብ ሣይንስንና ኤክስቴንሽን የተመለከቱ ናቸው፡፡

ኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ ግብርና በተለያዩ መስኮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁለት ምሁራን የህይወት ዘመን ዕዉቅና ሰጥቷል፡፡ እነዚሀ ዕዉቅና የተሰጣቸዉ ምሁራን ዶክተር በዳዳ ግርማ እና ዶክተር ክበበዉ አሰፋ ናቸዉ፡፡

ዶክተር በዳዳ ግርማ ለረጅም አመታት በወረር ግብርና ምርምር ማእከል የብሔራዊ የጥጥ ምርምር አስተባባሪ ሆነዉ ሰርተዋል፡፡ በመቀጠልም በቁሉምሳ የምርምር ማእከል በስንዴ ምርምር በተለይም የዋግ በሽታን ለመከላከል በተደረገዉ አለም አቀፍ ዘመቻ ከፍተኛ አሰተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በርካታ ዝርያዎችም እንዲለቀቁና ለገበሬዉ እንዲደርሱ ጉልህ ድርሻ አበርክተዋል፡፡

ዶክተር ክበበዉ አሰፋ ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪያቸዉን ካጠናቀቁበት የዛሬ 40 አመት ወዲህ ጊዜያቸውን በጤፍ ምርምር ያሳለፉ ሲሆን በርካታ የጤፍ ዝርያዎች ተለቀዉ በአምራቹ ዘንድ እንዲደርሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ለነዚህ ከፍተኛ እዉቅና ለተሰጣቸዉ ምሁራን በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ፡፡ በድጋሚ ያልኩበት ምክንያት የመጀመሪያዉን እንኳን ደስ አላችሁ በወቅቱ በሥፍራዉ ስለነበርኩ እዚያዉ ስላደረስኩ ነዉ፡፡ በአጋጣሚ ከሁለቱም ተሸላሚዎች ጋር ከፍተኛ ቅርበት አለኝ፡፡ ዶክተር በዳዳ የብሔራዊ የጥጥ ምርምር አስተባባሪ በነበሩት ወቅት እኔም አግሮኖሚን በመወከል የአስተባባሪዉ ኮሚቴ አባል ስለነበርኩ በቅርበት አብረን ከመስራታችንም በላይ የወረር ምርምር ማእከልን በሃላፊነት በመሩበት ወቅት የቅርብ አለቃዬ ነበሩ፡፡ ዶክተር ክበበዉ ደግሞ የጤፍ ምርታማነትን ለማሳደግ ታስቦ በተቋቋመዉ የጤፍ ማሻሻያ ፕሮጀክት ዉስጥ ላለፉት 15 አመታት በትብብር እየሰራን እንገኛለን፡፡

ምስሉ የሚያሳየዉ የህይወት ዘመን ዕዉቅና ለዶክተር በዳዳ ግርማ እና ለዶክተር ክበበዉ አሰፋ የተሰጠበት ሥነ ሥርዓት ነዉ፡፡ ከግራ ወደ ቀኝ ዶክተር በዳዳ ግርማ፣ ዶክተር ድሪባ ገለቲ፣ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ፣ ዶክተር ታዬ ታደሰ እና ዶክተር ካሳዬ ቶለሳ፡፡ ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፣ የካቲት 17 ቀን 2015።

ዶክተር በዳዳ ግርማ (በስተግራ) እና ዶክተር ክበበው አሰፋ በጋራ ዳቦ ሲቆርሱ፡፡ ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፣ የካቲት 17 ቀን 2015።

ዶክተር በዳዳ ግርማ (በስተግራ) እና ዶክተር ክበበዉ አሰፋ ስለተሰጣቸዉ ከፍተኛ እዉቅና ሲወያዩ፡፡ ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፣ የካቲት 17 ቀን 2015።

ከኮንፈንሱ ተሳታፊች ከቀረቡት ምክረ ሀሳቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

  • ወደፊት በመድረክ የሚቀርቡ ጽሑፎች የጥራት ደረጃቸዉ እንዲጠበቅ በቅድሚያ በኮሚቴ ታይተዉ እና እርማት ተደርጎባቸዉ እንዲሆን ቢደረግ፤ ለዚሁም ዶክተር ይልማ ከበደ መርዳት እንደሚችሉ ቃል ገብተዋል፡፡
  • በፓዎር ፖይንት ለሚቀርቡ ጽሑፎችም የፎንት መጠናቸዉ ጎላ ብሎ ለተሳታፊች በቀላኡ እንዲታዩ ቢደረግ፤
  • በመድረክ የሚቀርቡ ወረቀቶችም የተወሰኑ እንዲሆኑና ተጋባዥ እንግዶች በቂ ጊዜ እንዲሰጣቸዉ ቢደረግ፤
  • በኮንፈንሱ ተሳታፊዎች የምርምር ዉጤታቸዉን በፖስተር መልክ የሚያቀርቡበት መንገድ  ቢመቻቸና ለተመረጡ የፖስተር አቅራቢዎች ሽልማት ቢሰጥ፤
  • ለኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መሳተፋቸዉን የሚገልጽ የምስከር ወረቀቀት ቢሰጥ ናቸዉ፡፡

በአጠቃላይ ኮንፈረንሱ በጥሩ ሁኔታ የተካሄደ ሲሆን በአካል መገኘት ያልቻሉ ነገር ግን የኢንተርነት ግንኙነት የነበራቸዉ መከታተል እንዲችሉ ያስቻለ ነበር፡፡ ለምሳሌ የኪ ኖት ንግግር ያደረጉት ዶክተር ፍሬዉ መክበብ ከሀረር ከተማ ሆነው መልእክታቸዉን ያስተላለፉት፡፡ ወደፊትም ወደ ኮንፈረንሱ ሥፍራ በአካል መገኘት ያልቻሉ አባላት በተለያዩ መንገዶች የሚሳተፉበት መንገድ ቢመቻች እላለሁ፡፡

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. (March 6, 2023)

ግብርናችንንለማዘመን፤ ሞሎኪያ፣ ትኩረት ያላገኘዉ ጎመናችን

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡

ሞሎኪያ፣ ትኩረት ያላገኘዉ ጎመናችን

በዛሬዉ ጽሑፌ ሞሎኪያ ተብሎ ስለሚጠራዉና እንደ ምግብ በሀገራችን ስላልታወቀዉ የጎመን አይነት ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ በዉጭው አለም ይህ ተክል ሞሎኪያ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የግብጽ ስፒናች በመባልም ይታወቃል፡፡ በሳይንሳዊ ስሙ Corchorus olitorius ወይም Corchorus. Capsularis ተብሎ ይጠራል፡፡ በግብጽ ሀገር ሞሎኪያ በጣም ተፈላጊ ጎመን ሲሆን ከዚህ ተክል የሚሰራ ምግብም እንደ ብሔራዊ ምግባቸዉ ይቆጠራል፡፡

የሞሎኪያ ተክል ይህንን ይመስላል፡፡

የምስሉ ምንጭ፤ https://www.herbcottage.com.au/products/egyptian-spinach-plant

እኔ የሞሎኪያ ተክልን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ከዩኒቨርስቲ ተመርቄ የዛሬ 37 አመት በመልካ ወረር እርሻ ምርምር ማእከል (በአሁኑ የወረር ግብርና ምርምር ማእከል) በተመደኩበት ወቅት ነዉ፡፡ አግሮኖሚስት ሆኜ በመመደቤ በማእከሉ ባሉ ሰብሎች ሁሉ ማለትም ጥጥ፣ የቆላ ስንዴ፣ የአበሻ ሱፍ፣ ኦቾሎኒና ኬናፍ የተባለ የጭረት ተክል ላይ ምርምር አካሄድ ነበር፡፡ በማእከሉ ከእጽዋት በተጨማሪ በእንስሳት ላይም ምርምር ይካሄድ ነበር፡፡የወረር ማእከል ከአዲስ አበባ በሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ወደ 400 ሄክታር የሚጠጋ መሬት የሚሸፍን ሥፍራንም ይዞ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳ የበርካታ ስብሎችና እንስሳት ምርምር በማእከሉ ቢካሄድም በትኩረት የሚሰራዉ በጥጥ ላይ ነበር፡፡ ምክንያቱም ማእከሉ በሚገኝበት በመካከለኛዉ አዋሽ እና ከማእከሉ ራቅ ብለዉ በታችኛዉ አዋሽ የሚገኙ ሰፋፊ የመንግሥት እርሻዎች የሚያለሙት ጥጥ ስለሆነ ለነዚህ እርሻዎች አስፈላጊ የምርምር ውጤቶችን ለመስጠት ታስቦ ነዉ፡፡

ባልሳሳት በማእከላችን ባሉ የጥጥ ማሳዎች ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚበቅሉና የጥጥ ሙከራዎቻችንን ከሚፈታተኑት አረሞች ዉስጥ ሞሎኪያ ከፍተኛዉን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይህንን በዉጭዉ አለም የታወቀዉን በእኛ ሀገር ግን ለምግብነት ያልታወቀውን የሞሎኪያ ተክል ከጥጥ ማሳዎቻችን ለማስወገድ በርካታ ሰራተኞች መቅጠር ይኖርብን ነበር፡፡ ከማሳዎቻችን ከነቀልናቸዉ በኋላ በማሳዎቹ ዳርና ዳር ጥለናቸዉ እዚያወ እንዲበሰብሱ ይደረግ ነበር፡፡

በወቅቱ የአንድ በካናዳ መንግሥት የሚደገፍ ፕሮጀክት አማካሪ የነበሩ አባስ የሚባሉ ግብጻዊ ለሥራ ጉዳይ በየሁለት ሳምንት ከአዲስ አበባ ወደ ማእከላችን ብቅ ይሉ ነበር፡፡ ከመምጣታቸዉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በወቅቱ ብቸኛዉ የመገናኛ መስመራችን በነበረዉ የሬዲዮ መልእክት ወደ ወረር እንደሚመጡ ያሳውቁን ነበር፡፡ ይህም ማለት ከሚመጡበት ሥራ በተጨማሪ ከማሳዎቻችን ነቅለን የምንጥለዉን ሞሎኪያን እንደሚወስዱም ለማሳወቅ ነዉ፡፡ ለማጓጓዣም እንዲያመቻቸዉ ፒክ አፕ መኪናቸዉን ይዘዉ ይመጡ ነበር፡፡  በሀገራቸዉ ግብጽም እጅግ ተፈላጊ ተክል እንደሆነም ይነግሩን ነበር፡፡ እኛ ጥቅሙን ሳናዉቅ እኔ ማእከሉን ለቅቄ ወጣሁ፡፡በርግጥ ለአረም ሥራ የምንቀጥራቸዉ ከማእከሉ ውጭ ይኖሩ የነበሩ የተወሰኑ ሰራተኞች እንደ ጎመን ይጠቀሙ ነበር፡፡

ሞሎኪያ በግብጽ አባባል የአትክልቶች ንጉሥ እንደማለት ነዉ፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሞሎኪያ በርካታ  ለሰዉነታችን አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ይዟል፡፡ ከነዚህ ዉስጥ በሞሎኪያ የሚገኘዉ የካሮቲን መጠኑ ከስፒናች በ4.6 እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን የካልሺየም መጠኑም ከስፒናች በዘጠኝ እጥፍ ይበልጣል፡፡ ቫይታሚንም በተመለከተ ሞሎኪያ ቫይታሚን ቢ1 እና ቢ2 እስፒናች ከያዘዉ በአስር እጥፍ ልቆ ይገናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሞሎኪያ በታመምን ጊዜ ከህመማችን ለመፈወስ ጠቃሚ እንደሆነ በሰፊዉ ይነገራል፡፡ አፈታሪክ እንደሚነግረን የግብጽ ንጉስ የነበሩት ፈርኦ በታመሙ ጊዜ  ከሞሎኪያ የተሰራ ሾርባ ጠጥተዉ ከህመማቸዉ እንደዳኑ ነዉ፡፡

ሞሎኪያ በተለያዩ መንገዶች ጥቅም ላይ ይዉላል፡፡ ከነዚህ ዉስጥ ዋናዎቹ በሻይ፣ ሾርባ፣ ሰላጣ እና ተቀቅሎ በወጥ መልክ ናቸዉ፡፡ ሞሎኪያ በግብጽ ብቻ ሳይሆን በበርካታ የመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች ለምግብነት ያገለግላል፡፡

ስለዚህ ሞሎኪያ እና ሌሎች በጥቅም ላይ ያልዋሉ ነገር ግን በቀላሉ በሀገራችን ልናበቅላቸዉ የምንችለዉን ተክሎችን ለምግብነት የምንጠቀምበት መንገድ መፈለግ ይኖርብናል እላለሁ፡፡

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ የካቲት24 ቀን 2015 ዓ.ም. (March 3, 2023)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የባህር አረም ሰብሎቻችንን ለማንቃትና ምርት ለማሳደግ ያለዉ ሚና

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡

የባህር አረም ሰብሎቻችንን ለማንቃትና ምርት ለማሳደግ ያለዉ ሚና

የባህር አረም ብዬ የተጠቀምኩት በእንግሊዘኛ seaweed ተብለዉ የሚታወቁትንና በባህር ውስጥ የሚያድጉትን የተለያዩ የአልጌ (algae) ዓይነቶችን የሚካትተዉን ለማሳየት ነዉ። እንዚህ የባህር አረሞች ከዚህ በታች በሚታዩት ምስሎች ይወከላሉ።

ምስሎቹ የሚያሳዩት የባህር አረም ከባህር ሥር እንዴት እንደሚያድግ (በስተግራ) እና በተናጠል ያለ የባህር አረምን ነዉ። ምንጭ፤ https://businesswales.gov.wales/farmingconnect/news-and-events/technical-articles/seaweed-agriculture (በስተግራ ላለዉ) https://stock.adobe.com/search?k=seaweed (በስተቀኝ ላለዉ)

መረጃዎች እንደሚያሳዩት እነዚህ የባህር አረሞች ተብለዉ የሚጠሩት ተክሎች ለበርካታ አገልግሎት ጥቅም ላይ ይዉላሉ። እነዚህም ለሰዉ እና ለእንስሳት ምግብነት፣ ለመዲሃኒትነት፣ ለማዳበሪያ፣ ለተለያዩ የፋብሪካ ግባቶች፣ ወዘተ ናቸዉ። ለሰዉ ምግብነት በተለያዩ መልኮች ያገለግላል። ለምሳሌ እንደ ሾርባ፣ ብስኩት፣ ሻይ ቅጠል፣ ወዘተ በመሆን ጥቅም ላይ ይዉላል። እኔም የዛሬ 25 ዓመት ገደማ የሥራ ባልደረባዬ የነበረዉ ጃፓናዊ ሳይንቲስት በተለያየ ወቅት ከሀገሩ የሚያስመጣዉን ከባህር አረም የሚሰሩ የተለያዩ ብስኩቶችን ያጋራኝ ነበር። በሀገሩ በጣም ተወዳጅ እንደነበሩም ይነግረኝ ነበር።

በዛሬዉ ጽሑፌ ትኩረት የማደርገዉ ይኸዉ የባህር አረም በግብርና መስክ ስለሚሰጠዉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በተለይም ሰብሎቻችንን እንደ አነቃቂ ወይም አንቂ ሆኖ በማገልገል ምርት እንዲያድግ በሚያስችለዉ ላይ ነዉ።

ከታች በምስሉ እንደሚታየዉ የባህር አረም በርካታ ምርትን ለማሳደግ የሚረዱ የአፈርና የተክል ባህርያትን ለማሻሻል ይችላል። ለዚህም ነዉ አንቂ ወይም Biostimulant የሚለዉ ስም የተሰጠው። የምርት መጠን ብቻ ሳይሆን ጥራትንም በማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋል። የሚገርመዉ በሌሎች መስኮች ካለዉ ጥቅም በተጨማሪ በሰብሎቻችን ላይ ይህ የባህር አረም ያለዉ ጉልህ አስተዋጽኦ ያስደንቃል። ስለዚህ የባህር አረም ሰብሎቻችን ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን ከአፈር ውስጥ እንዲያገኙ ማመቻቸት ብቻ ሳይሆን ሰብሎቻችን ለድርቅና ጨዋማ አፈር በተጋእጡ ጊዜም እነዚህን አስቸጋሪ ክስተቶች እንዲቋቋሙ ይረዷቸዋል።

ምስሉ የሚያሳየዉ ከባህር አረም የሚቀመመዉ በፈሳሽም ሆነ በፓዉደር መልክ የሚዘጋጀዉ ለአፈር ለምነትና እና የተክል ዕድገት ጠቃሚ መሆኑን ነዉ። + ሚለዉ ምልክት የሚያሳየዉ የባህር አረም ሰብላችንን ለማሻሻል ወይም  አፈራችንን ለማበልጸግ ጠቃሚ እንደሆነ ነዉ። በዚሁ መሠረት የባህር አረም ከላይ ለተገለጹት ባህርያት ጥቅም ይሰጣል። ምንጭ፤ Plants (2020) 9: 359. doi: 10.3390/plants9030359

ምንም እንኳ የባህር አረም እነዚህን በርካታ የተክልና የአፈር ባህርያትን ለማሻሻል እንደ አንቂ ሆኖ ቢያገልግልም እንዴት እነዚህን ሁሉ ሚናዎች ሊጫወት እንደቻለ ገና በጥናት ላይ ነዉ። አንደ አንዳንድ  ተመራማሪዎች ግምት የባህር አረም በዉስጡ የተለያዩ ፖሊሳካራይድ፣ ፌኖል እና ሆርሞኖችን የያዘ በመሆኑ እነዚህ ንጥረ ነገሮች እንደ አንቂ ሆነዉ ሊያገለግሉ እንደሚችሉ ነዉ። በአሁኑ ጊዜ ተመራማሪዎች የባህር አረምን ጥቅም በተለያዩ ሰብሎች እየፈተሹ ይገኛሉ። እንዴትስ በተመጣጣኝ ወጪ ጥቅም ላይ የሚዉልበትን መገድም ያጠናሉ።

ማጠቃለያ

የባህር አረም በሚል ስም የተሰሙት የተክል ዓይነቶች በርካታ ከመሆናቸዉ በላይ በባህር ዉስጥ ብቻ ሳይሆን በሐይቆችና ወንዞችም ጭምር የሚያድጉ ስለሆነ በጥቅም ላይ ልናዉላቸዉ የምንችልበትን መንገድ መፈለግ ይኖርብናል። ምንም እንኳ ስለሚመረትበት ሥፍራ መረጃ ባላግኝም እ አ አ በ 2012 ኢትዮጵያ የባህር አረምን ኤክስፖርት በማድረግ ወደ ሶስት ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ አግኝታለች። የመረጃዉ ምንጭ፤https://www.selinawamucii.com/insights/prices/ethiopia/seaweed/

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ። ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. (February 12, 20

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የጤፍን ፍሬ በእንክብል የማሳደግ አስፈላጊነት፤ ክፍል 2

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡

የጤፍን ፍሬ በእንክብል የማሳደግ አስፈላጊነት፤ ክፍል 2

ባለፈዉ ጽሑፌ የዘር እንክብል (seed pelleting) ስለሚባለዉና የዘር ፍሬን በእንክብል መንገድ በመሥራት ምርታማነትን ማሳደግ እንደምንችል ለማሳየት ሞክሬአለሁ። በዛሬዉ ጽሑፌ ደግሞ ይህንን የዘር እንክብል በጤፍ ላይ በመጠቀም የተደረገዉን ጥረትና ውጤት በአጭሩ ለማስነበብ እሞክራለሁ።

ባለፈዉ ብሎጌ እንደገለጽኩት የዘር እንክብል በርካታ ጥቅሞች አሉት። ይህ የሰብል ማሻሻያ መንገድ ጤፍንም በዘመናዊ መንገድ ለማሻሻል ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል። ምክንያቱም የጤፍ ዘር ወይም ፍሬ በጣም አነስተኛ በመሆኑ ገበሬዎች አስፈላጊ የሆነ የዘር መጠን ሊጠቀሙ አይችሉም። ለጤፍ የሚመከረዉ የዘር ብዛት 10 ኪሎ ግራም በሄክታር ሲሆን ገበሬዎቻችን ግን ይህ የዘር መጠን በቂ መስሎ ሰለማይታያቸዉ እስከ 30 ወይም 40 ኪሎ በሄክታር ድረስ ይጠቀማሉ። ይህ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የዘር መጠን የጤፍን ተክሎች ለከፍተኛ መተፋፈግ ከመዳረጉም በላይ ሰብሉን ለመጋሸብ ያጋልጣል። የጋሸበ ተክል ደግሞ የምርት ብዛቱም ሆነ ጥራቱ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ማለት ነዉ። በጤፍ ላይ የሚከሰተዉን ይህን ከፍተኛ መጋሸብ ለመቀነስ ወይም ለመቋቋም የተለያዩ መንገዶች መጠቀም ይቻላል።

እነዚህ መንገዶችም በመጠኑ በጥናት ላይ ሲሆኑ ሌሎችም በጥቅም ላይ እየዋሉ ነዉ። ለምሳሌ የጤፍ ተክል ቁመት በማሳጠር ጠንከር ያለና መጋሸብን መቋቋም የሚችል ተክል ማግኘት ይቻላል። ሌላዉ መንገድ ደግሞ ቁመት የሚያሳጥሩ ሆርሞኖች (plant hormone) በተወሰነ መልክ በጤፍ ላይ የሚያጋጥመውን መጋሸብ መግታት ይቻላል። የዛሬዉ ጽሑፌ የሚያተኩረዉ የዘር እንክብልን በመጠቀም የጤፍ የዘር መጠንን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ብቻ ሳይሆን መጋሸብንም እንደሚቀንስ ነዉ።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉና ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ተመራማሪዎችና ተቋማት የጤፍ መጋሸብን ችግር ለመፍታት ከፈተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። አንዳንዶቹም አመርቂ ዉጤት እያገኙ ነዉ።

በዚሁ መሠረት በኢትዮጵያ እና ስዊዘርላንድ ባሉ ተመራማሪዎችና ተቋማት የተመሰረተዉ የጤፍ ማሻሻያ ፕሮጀክት የጤፍን ዘር ወይም ፍሬ በእንክብል መልክ ለማሳደግ ዕቅድ ነድፎ ወደ ሥራ ገብቷል። በዚሁ መሠረት የዘር እንክብልን ለመሥራት የሚያገለዉን በላቦራቶሪ ውስጥ የሚቀመጥ አነስተኛ ፔሌቴር (pelleter) ገዝቶ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቱት ሥር በሚገኘዉ የደብረ ዘይት ግብርና ማዕከል እንዲመሠረት ተደረገ፤ ሥልጠናም አስፈላጊ ለሆኑ ተመራማሪዎችና ቴክኒሻኖች ተሰጥቷል።

በምስሉ የሚታየዉ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቱት ሥር በሚገኘዉ የደብረ ዘይት ግብርና ማዕከል ውስጥ የሚገኘዉ የዘር እንክብልን ለመሥራት የሚጠቅመዉ ፔሌቴር (pelleter) ነዉ። ፎቶ፤ ዘሪሁን ታደለ

ምስሉ የሚያሳየዉ የዘር እንክብልን በጤፍ ላይ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሥልጠና በደብረ ዘይት ግብርና ማዕከል የሚገኙ ተመራማሪዎችና ቴክኒሻኖች ሲወስዱ ነዉ። ፎቶ፤ ዘሪሁን ታደለ

ከዚህ በታች በምስሉ እንደሚታየዉ የጤፍን ዘር በተለያየ መጠን በእንክብል መልክ በማሳደግ ተስማሚ የሆነዉን ለመምረጥ ሙከራ ተደርጓል። በክፍል 1 ጽሑፌ በገለጽኩት መሠረት የዘር እንክብል ለመሥራት ዘሩን ለማሳደግ ፓዉደር፣ ውሃ፣ ማጣበቂያ እና ዘር ያስፈልጋሉ። ዘሩን ለማሳደግ በዋናነት የሚረዳዉ ፓዉደር ከተለያዩ ነገሮች መጠቀም ይቻላል።

ከላይ በምስሉ የሚታየዉ በጤፍ ዘር ዙሪያ እንክብል በመሥራት የጤፍ ዘርን ለማሳደግ እንደምንችል ነዉ። በዚሁ መሠረት የ1000 ጤፍ ዘር በአማካይ ከሚመዝነዉ 0.38 ግራም እስከ 7.57 ግራም በማሳደግ በብቅለት እና እድገት ላይ ያለዉን ሁኔታ ለማጥናት ችለናል። በእንክብል ያልተሰራዉን ጤፍ እንደ አንድ ብንቆጥር (በምሥሉ በቀኝ በኩል የሚታየው ለማለት ነዉ) በግራ በኩል የሚታየዉ እስከ 20 እጥፍ ክብደት ይጨምራል ማለት ነዉ። ከላይ የሚታዩትን እንክብሎች ለመሥራት አገልሎት ላይ የዋሉት ፓውደሮች ለ5 እና15 እጥፍ የእንጨት ፍቅፋቂ ሲሆን ለ20 እጥፉ ደግሞ የሸክላ አፈር ነዉ። ፎቶ፤ ዘሪሁን ታደለ

የጤፍን ዘር በእንክብል መልክ መጠቀሙ ጤፍን በእጅና በብተና ከመዝራት ወጥታ በመዝሪያ ማሽን ወደ መዝራት ሊያሸጋግራት ይችላል። የጤፍ መዝራትን ለማቀላጠፍ የተለያዩ የመዝሪያ ማሽኖች ሊሰሩ የቻሉ ሲሆን አንዳንዶቹም በሙከራ ላይ ናቸዉ። የተለያዩ ተቋማትም ትኩረት አድርገዉ በመሥራት ላይ ሲሆኑ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰዉ በግብርና ምርምር ማዕከል ሥር የሚገኘዉ የመልካሳ ምርምር ማዕከል ነዉ። ማዕከሉ ከሰራቸዉ የጤፍ መዝሪያ መሣሪያዎች ውስጥ ከዚህ በታች የሚታየዉ በተለይም የኮትቻ አፈር ባለበት ቦታ ተመራጭ ነዉ። ምክንያቱም በጤፍ የዘር ወቅት ከመሬቱ እጅግ የመርጠብና የመጣበቅ ባህርይ የተነሳ ግዙፍ መሣሪያዎችን ወደ ማሣ ማስገባት አስቸጋሪ ስለሆነ ነዉ።

ምስሉ የሚያሳየዉ የጤፍ ዘርን በተለይም በኮትቻ ማሣ ላይ ለመዝራት በመልካሳ ምርምር ማዕከል የተሰራዉን መዝሪያ ነዉ። ፎቶ፤ ዘሪሁን ታደለ

በአጠቃላይ የጤፍ እንክብልን በመጠቀም የምንዘራዉን ዘር በተፈለገዉ ርቀት እንዲቀመጥ በማድረግ የሚፈለገዉን የተክል ብዛት ማግኘት እንችላለን። ያለበለዚያ የተክሉ ብዛት ከተወሰነ መጠን በላይ የበዛ ከሆነ ተክሎቹ እርስ በርሳቸው ለብርሃን፣ ለውሃ እና ለማዕድን ሽሚያ ያደርጋሉ። የሚደርሰዉ ጉዳት በዚህ ብቻ ሳያበቃ ተክሎቹ ስለሚጋሸቡ ወይም ስለሚወድቁ የምርት ጥራትና መጠን በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ ይችላል። በእንክብል መልክ የተሰራዉን የጤፍ ዘርንም በዘመናዊ የጤፍ መዝሪያ በመጠቀም የጤፍ ሜካናዜሽን ለማሳደግ እንችላለን።

በዚሁ በሁለት ክፍሎች ያቀረብኩትን ‘የጤፍን ፍሬ በእንክብል የማሳደግ አስፈላጊነት’ የሚለዉን ጽሑፌን አበቃለሁ።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥር 21 ቀን 2015 ዓ.ም. (January 29, 2023)