ግብርናችንንለማዘመን፤ ሞሎኪያ፣ ትኩረት ያላገኘዉ ጎመናችን

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡

ሞሎኪያ፣ ትኩረት ያላገኘዉ ጎመናችን

በዛሬዉ ጽሑፌ ሞሎኪያ ተብሎ ስለሚጠራዉና እንደ ምግብ በሀገራችን ስላልታወቀዉ የጎመን አይነት ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ በዉጭው አለም ይህ ተክል ሞሎኪያ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የግብጽ ስፒናች በመባልም ይታወቃል፡፡ በሳይንሳዊ ስሙ Corchorus olitorius ወይም Corchorus. Capsularis ተብሎ ይጠራል፡፡ በግብጽ ሀገር ሞሎኪያ በጣም ተፈላጊ ጎመን ሲሆን ከዚህ ተክል የሚሰራ ምግብም እንደ ብሔራዊ ምግባቸዉ ይቆጠራል፡፡

የሞሎኪያ ተክል ይህንን ይመስላል፡፡

የምስሉ ምንጭ፤ https://www.herbcottage.com.au/products/egyptian-spinach-plant

እኔ የሞሎኪያ ተክልን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ከዩኒቨርስቲ ተመርቄ የዛሬ 37 አመት በመልካ ወረር እርሻ ምርምር ማእከል (በአሁኑ የወረር ግብርና ምርምር ማእከል) በተመደኩበት ወቅት ነዉ፡፡ አግሮኖሚስት ሆኜ በመመደቤ በማእከሉ ባሉ ሰብሎች ሁሉ ማለትም ጥጥ፣ የቆላ ስንዴ፣ የአበሻ ሱፍ፣ ኦቾሎኒና ኬናፍ የተባለ የጭረት ተክል ላይ ምርምር አካሄድ ነበር፡፡ በማእከሉ ከእጽዋት በተጨማሪ በእንስሳት ላይም ምርምር ይካሄድ ነበር፡፡የወረር ማእከል ከአዲስ አበባ በሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ወደ 400 ሄክታር የሚጠጋ መሬት የሚሸፍን ሥፍራንም ይዞ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳ የበርካታ ስብሎችና እንስሳት ምርምር በማእከሉ ቢካሄድም በትኩረት የሚሰራዉ በጥጥ ላይ ነበር፡፡ ምክንያቱም ማእከሉ በሚገኝበት በመካከለኛዉ አዋሽ እና ከማእከሉ ራቅ ብለዉ በታችኛዉ አዋሽ የሚገኙ ሰፋፊ የመንግሥት እርሻዎች የሚያለሙት ጥጥ ስለሆነ ለነዚህ እርሻዎች አስፈላጊ የምርምር ውጤቶችን ለመስጠት ታስቦ ነዉ፡፡

ባልሳሳት በማእከላችን ባሉ የጥጥ ማሳዎች ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚበቅሉና የጥጥ ሙከራዎቻችንን ከሚፈታተኑት አረሞች ዉስጥ ሞሎኪያ ከፍተኛዉን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይህንን በዉጭዉ አለም የታወቀዉን በእኛ ሀገር ግን ለምግብነት ያልታወቀውን የሞሎኪያ ተክል ከጥጥ ማሳዎቻችን ለማስወገድ በርካታ ሰራተኞች መቅጠር ይኖርብን ነበር፡፡ ከማሳዎቻችን ከነቀልናቸዉ በኋላ በማሳዎቹ ዳርና ዳር ጥለናቸዉ እዚያወ እንዲበሰብሱ ይደረግ ነበር፡፡

በወቅቱ የአንድ በካናዳ መንግሥት የሚደገፍ ፕሮጀክት አማካሪ የነበሩ አባስ የሚባሉ ግብጻዊ ለሥራ ጉዳይ በየሁለት ሳምንት ከአዲስ አበባ ወደ ማእከላችን ብቅ ይሉ ነበር፡፡ ከመምጣታቸዉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በወቅቱ ብቸኛዉ የመገናኛ መስመራችን በነበረዉ የሬዲዮ መልእክት ወደ ወረር እንደሚመጡ ያሳውቁን ነበር፡፡ ይህም ማለት ከሚመጡበት ሥራ በተጨማሪ ከማሳዎቻችን ነቅለን የምንጥለዉን ሞሎኪያን እንደሚወስዱም ለማሳወቅ ነዉ፡፡ ለማጓጓዣም እንዲያመቻቸዉ ፒክ አፕ መኪናቸዉን ይዘዉ ይመጡ ነበር፡፡  በሀገራቸዉ ግብጽም እጅግ ተፈላጊ ተክል እንደሆነም ይነግሩን ነበር፡፡ እኛ ጥቅሙን ሳናዉቅ እኔ ማእከሉን ለቅቄ ወጣሁ፡፡በርግጥ ለአረም ሥራ የምንቀጥራቸዉ ከማእከሉ ውጭ ይኖሩ የነበሩ የተወሰኑ ሰራተኞች እንደ ጎመን ይጠቀሙ ነበር፡፡

ሞሎኪያ በግብጽ አባባል የአትክልቶች ንጉሥ እንደማለት ነዉ፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሞሎኪያ በርካታ  ለሰዉነታችን አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ይዟል፡፡ ከነዚህ ዉስጥ በሞሎኪያ የሚገኘዉ የካሮቲን መጠኑ ከስፒናች በ4.6 እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን የካልሺየም መጠኑም ከስፒናች በዘጠኝ እጥፍ ይበልጣል፡፡ ቫይታሚንም በተመለከተ ሞሎኪያ ቫይታሚን ቢ1 እና ቢ2 እስፒናች ከያዘዉ በአስር እጥፍ ልቆ ይገናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሞሎኪያ በታመምን ጊዜ ከህመማችን ለመፈወስ ጠቃሚ እንደሆነ በሰፊዉ ይነገራል፡፡ አፈታሪክ እንደሚነግረን የግብጽ ንጉስ የነበሩት ፈርኦ በታመሙ ጊዜ  ከሞሎኪያ የተሰራ ሾርባ ጠጥተዉ ከህመማቸዉ እንደዳኑ ነዉ፡፡

ሞሎኪያ በተለያዩ መንገዶች ጥቅም ላይ ይዉላል፡፡ ከነዚህ ዉስጥ ዋናዎቹ በሻይ፣ ሾርባ፣ ሰላጣ እና ተቀቅሎ በወጥ መልክ ናቸዉ፡፡ ሞሎኪያ በግብጽ ብቻ ሳይሆን በበርካታ የመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች ለምግብነት ያገለግላል፡፡

ስለዚህ ሞሎኪያ እና ሌሎች በጥቅም ላይ ያልዋሉ ነገር ግን በቀላሉ በሀገራችን ልናበቅላቸዉ የምንችለዉን ተክሎችን ለምግብነት የምንጠቀምበት መንገድ መፈለግ ይኖርብናል እላለሁ፡፡

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ የካቲት24 ቀን 2015 ዓ.ም. (March 3, 2023)

አስተያየት ያስቀምጡ