ግብርናችንን ለማዘመን፤ የጤፉ ጠቢብ፣ዶክተር ክበበዉ አሰፋ፤ ክፍል 2

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነው ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነው፡፡

የጤፉ ጠቢብ፣ ዶክተር ክበበ አሰፋ፤ ክፍል 2

በዛሬዉ ክፍል 2 ጽሑፌ ዶክተር ክበበው አሰፋ ላለፉት 40 ዓመታት በጤፍ ምርምር ላይ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ ያደረኩላቸውን ቃለ መጠይቅ አስነብባችኋለሁ።

ጥያቄ፤ እርስዎ ከሥራ ባልደረቦችዎ ጋር በርካታ የጤፍ ዝርያዎች እንዲጸድቁ አድርገዋል፡፡ ቢሆንም የሀገሪቱ አማካይ የጤፍ ምርታማነት ከ18 ኩንታል በሄክታር ሊያልፍ አልቻለም፡፡ ይህ ለምን ሊሆን ቻለ?

ዶክተር ክበበዉ፤ በአሁኑ ጊዜ የጤፍ ሀገራዊ አማካይ ምርት 18 ኩንታል በሄክታር ነው፡፡ ለዚህ ዝቅተኛ ምርታማነት አያሌ ምክንያቶች አሉ፡፡ 1ኛ) በምርምር የወጡት ዝርያዎች በተገቢው ሁኔታ በመላው ሀገሪቱ ላሉት የጤፍ አምራች አርሶ አደሮች በሚገባ አልተዳረሱም፡፡ 2ኛ) የወጡት ዝርያዎች ከፍተኛ ምርት ለመስጠት እንዲችሉ የሚያሰፈልጋቸው ተጓዳኝ የአመራረት ቴክኖሎጂዎችና ዘዴዎች ግብአቶችን ጨምሮ በተገቢው መንገድና መጠን በአርሶ አደሮች ዘንድ በጥቅም ላይ አልዋሉም፡፡ 3ኛ) ምንም እንኳን በርካታ ዝርያዎች በምርምር የወጡ ቢሆንም ለሁሉም የተለያዩ ጤፍ አብቃይ ስነ-ምህዳሮችና እንዲሁም የግብርናና ሰብል አመራረት ሥርዓቶች ተስማሚ የሆኑ ዝርያዎችና ቴክኖሎጂዎች ወጥተዋል ማለት አይቻልም፡፡ 4ኛ) የጤፍ ምርታማነትን የበለጠ ለማሳደግና ተወዳዳሪ ለማድረግ በኢትዮጵያ የሚያስፈልገውን ያህል ለጤፍ ምርምርና ልማት የመዋዕለ ንዋይ (ሀብት) ፍሰትና የሳይንሳዊ ዕውቀት ግብዓት ከነአካቴውም የሚገባውን ያህል ትኩረት አልተሰጠውም፡፡  ከዚህ አኳያ በዓለም ላይ ዋነኛ የሆኑት ታዋቂ ሰብሎች (ለምሳሌ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሩዝ፣ ወዘተ) አሁን ያሉበት ደረጃ የደረሱት ምን ያህል የትየለሌ አለም-አቀፍ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ለሳይንሳዊ ምርምርና ልማታቸው ስለተደረገባቸው መሆኑንና አሁንም በቀጣይነት እየተደረገባቸው እንዳለ በአንፃራዊነት መገመት ይቻላል፡፡

ጥያቄ፤ ይህ በዚህ እንዳለ ሞዴል ገበሬዎች የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን እና ግብአቶችን በመጠቀም በሄክታር እስከ 30 እና 35 ኩንታል ሊያገኙ ችለዋል፡፡ በአንጻሩ የጤፍ ምርጥ ዝርያና ቴክኖሎጂ ለአብዘኛዉ አርሶ አደር ባለመዳረሱ የሚገኘዉ ምርት አነስተኛ በመሆኑ ይህንን እንዴት መቀየር እንችላለን ይላሉ?

ዶክተር ክበበዉ፤ ለሀገራችን የጤፍ ልማት አንደኛውና ዋነኛው ክፍተት በምርምር የተገኙ የተሻሻሉ ዝርያዎች አንዲሁም ተጓዳኝ የአመራረት ቴክኖሎጂዎችና ዕውቀቶች በአርሶ አደሮች ዘንድ በስፋት ስላልተዳረሱ እና በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ አለማዋላቸዉ ነዉ፡፡ ስለሆነም አነዚህን ቱክኖሎጂዎችና ዕወቀቶች ለአርሶ አደሮች በተገቢው ሁኔታና መጠን ቀርበው በስፋት በጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም ከዚህ በፊት በነበሩት የጤፍ ቴክኖሎጂዎች ቅድመ-ማሰፋፋትና ማሰፋፋት መርሀ-ግብሮች በተገኘው ተሞክሮ መሠረት እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት የምርምር፣ የዘርና ኤክስቴንሽን ሥርዓቶቹ ተቀናጅተውና ተጠናክረው የጋራ ርብርብ ማድረግና መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡

ምስሉ የሚያሳየዉ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ውስጥ የተዘራዉና በገበሬዎች ዘንድ ተፈላጊ እየሆነ በመጣዉ የኤባ የጤፍ ዝርያ ፊት ለፊት ዶ/ር ክበበው አሰፋ የተነሱት ነዉ፡፡ ፎቶ ዘሪሁን ታደለእ አ አ ኦክቶበር 2022

ጥያቄ፤ በብሔራዊ የጤፍ ምርምር እስካሁን ድረስ ወደ 55 የሚጠጉ ዝርያዎች የተለቀቁ ሲሆን ከነዚህ ዉስጥ አብዘኛዎቹ ነጭ የዘር ሽፋን ያላቸዉ ናቸዉ፡፡ የጤፍ ምርምር ለምን በጥቁር ጤፍ ላይ ትኩረት አላደረገም? በአሁኑ ጊዜስ የምርምር አቅጣጫዉ የዘር መልክን በተመለከተ ምን ይመስላል?

ዶክተር ክበበዉ፤ ቀደም ብሎ ምርምሩ በሁለቱም ማለትም በነጭና በጥቁር የጤፍ ዓይነቶች ላይ በአንድ ላይ በጥምረት እየሰራ የነበረ ቢሆንም የጥቁር ጤፍ ዝርያዎች በአርሶ አደሮቹ እምብዛም ተፈላጊ አልነበሩም። በኋላም የአርሶ አደሮችንና የሌሎችንም ተጠቃሚዎች የጤፍ ዝርያ ዓይነት ፍላጎትና ዝርያዎቹ እንዲኖራቸው የሚፈልጓቸውን ባህርያት ለማወቅ በተደረገው ተሳትፏዊ የዝርያ መረጣ ጥናት አርሶ አደሮች ከገበያ ፍላጎትና ዋጋ አንጻር ከምርታማነትም ባሻገር ለዘር ንጣት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ስለሆነም የጤፍ ዝርያ ምርምር ሥራውን በመካከል ሙሉ በሙሉ በነጭ ጤፍ ላ እንዲያተኩር ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ጤፍ በአጠቃላይ እና በተለይም ጥቁር ጤፍ በዓለም ገበያ ላይ እንዲሁም በሀገራችንም በተለይም በዘመናዊ ሆቴሎችና በተለያዩ የምግብ ዝግጅቶች ላይ የጥቁር ጤፍ እንጄራ እንደ ተወዳጅ ተማራጭ አንዳንዴም የነጭና ጥቁር ጤፍ ቡራቡሬ እንጄራ እጅግ ተፈላጊ  እየሆነ በመምጣቱ ምርምሩ በአሁኑ ጊዜ በነጭና ጥቁር ጤፎች ላይ በሁለቱም ምድብ በመለያየት በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡

ጥያቄ፤ እርስዎ በግልዎ ከነጭ ወይስ ከጥቁር ጤፍ የተጋገረ እንጄራ ነዉ የሚመርጡት? ለምን?

ዶክተር ክበበዉ፤ በአብዛኛው በቤት በቀለብነት የምንጠቀመው ነጭ ጤፍ ቢሆንም በአማራጭነትና በተለይም በበዓላት ጊዜ የጥቁር ጤፍ እንጄራም እንጠቀማለን፡፡ በዝግጅቶች ላይ የጥቁር ጤፍ እንጄራ በተለይም በጥሩ ሁኔታ ከተዘጋጀ መብላት ደስ ይለኛል፡፡

ጥያቄ፤ የሀገራችን ቡና ይርጋጨፌ፣ ሲዳሞ ወዘተ የሚባሉ የምርት ስሞች ወይም ብራንድ (brand) እንዳላቸዉ ሁሉ በጤፍ የሚታወቁ ብራንዶች አሉ? ካሉ የትኞቹ ብራንዶች በተመጋቢዎች ዘንድ በይበልጥ ይመረጣሉ?

ዶክተር ክበበዉ፤ ምንጃር ማኛ፣ አደኣ ማኛ፣ የጊንጪ (ጥቁር) ጤፍ፣ የእንቡር ጤፍ፣ የበቾ ጤፍ፣ የጎጃም (በተለይም የቢቸና) ጤፍ፣ ስማዳ ጤፍ፣ እና የመሳሰሉት በተለያዩ ሀገሪቱ ክፍሎች በአካባቢ ዕውቅና የተሰጣቸው የጤፍ ዓይነቴዎች አሉ፡፡ በሳይንሳዊ ምርምሩም ረገድ የእነዚህን አይነቴዎች ተለያይነትና ልዩ መገለጫ ባህርያታቸውን በመለየት ልክ እንደቡናው ሁሉ ብራንድ (brand or geographical indication) ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

ጥያቄ፤ ብዙ ጊዜ በኮንፈረንሶች ወይም ስብሰባዎች ላይ እርስዎ ንግግር ሲያደርጉ ጤፍ ሲፈጭ ዱቄቱ ይጨምራል፣ ነገር ግን የስንዴ ይቀንሳል ሲሉ እሰማለሁ፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?

ዶክተር ክበበዉ፤ ጤፍ ሲፈጭ ሙሉ በሙሉ ሁሉም እህሉ ዱቄት ይሆናል፡፡ ስንዴን ብንወስድ ግን የዱቄት ምርቱ ከ60-80 ፐርሰንት ብቻ ነው፡፡ ይህ ማለት 100 ኪሎ ጤፍ ብናስፈጭ ሙሉ በሙሉ መቶ ኪሎ ዱቄት እናገኛለ። ስንዴ ከሆነ ግን የምናገኘው ዱቄት ተነፍቶ ከ60-80 ኪሎ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም በሌሎች ሰብሎች እንዲያዉም ከስንዴ በእጅጉ በበለጠ ሁኔታ በተለይም ገብስ፣ በቆሎ እና ማሽላ የመሳሰሉት ሲፈጩ ብዙ ዱቄት ያልሆነ ተረፈ-ምርት (ለምሳሌ ፉርሽካ፤ ገለባና እንቅጥቃጭ) ይወጣል፡፡ ከዚህ እውነታ አኳያ ጤፍ ሲፈጭ ዱቄቱ ይጨምራል የሚለውን ለማሳየት በይዘት (volume) ስንገልፀው በአንድ ከረጢት ሙሉ አድርገን ጤፍንና ሌሎች እህሎችን ወደ ወፍጮ ቤት ይዘን ብንሄድ ለጤፉ ተጨማሪ ሌላ መያዣ ካልያዝን በስተቀር በአንዱ ከረጢት ብቻ ዱቄቱን ሙሉ በሙሉ ይዘን መመለስ የማንችል ሲሆን ለሌሎቹ ሰብሎች ግን ተጨማሪ መያዣ ሳያስፈልገን ዱቄቱን ይዘን መመለስ እንችላለን፡፡ ይህ ማለት ግን የጤፍ ዱቄት መጠኑ በክብደት ሲመዘን ከመጀመሪያው የእህል መጠኑ ጨመረ ማለት ሳይሆን በሚይዘው ቦታ (volume) ይጨምራል ማለት ነዉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በሃገራችን በተለምዶ በተለይም ሴቶች የጤፍ ዱቄት በረከት ያለው ሲሆን የሌሎቹ እህሎች ዱቄት ግን ይናዳል ይላሉ። ይህም የሚሆነው ለምግብ ዝግጅት ዱቄቶቹን ወንፊት በመጠቀም ሲያዘጋጁ ከጤፉ ብዙም የሚጣል የሌለው ሲሆን ከሌሎቹ ሰብሎች ግን ብዙ ጥቅም ላይ የማይውል ከላይ የተገለፀው ተረፈ-ምርት በወንፊት ስለሚወጣ ነዉ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ከጤፍ የምናገኘው የእንጄራ ምርትም ከሌሎች ሰብሎች ከምናገኘዉ ጋር ስናወዳድር  ከጤፍ የምናገኘዉ በቁጥር የበለጠ ነው። ይህ ማለት አንድ ኩንታል (100 ኪሎ) የጤፍ እህል በእንጄራ መልክ ሲጋገር በአማካይ 500 ያህል እንጄራ የሚወጣው ሲሆን ከሌሎች ሰብሎች የምናገኘው የእንጄራ ብዛት ግን በእጅጉ ያነሰ ነው። ይህም የሚሆነው የጤፍ ዱቄት ሲቦካ ብዙ ውሃ ስለሚያነሳ ነው። ከጠቀሜታ አንፃር የጤፍ እንጄራ ምርት ከፍተኛ መሆኑ ብዙ ሰዎችን ለመመገብ ያስችላል ማለት ነው። ምክንያቱም በተለምዶ በሀገራችን ለአንድ ሰዉ በአንድ ጊዜ የሚቀርበው ለምሳሌ በሆቴሎች አንድ እንጄራ አድርገን ብንወስድ ማለት ነዉ።

ሌላው ከዚህ ጋር በተገናኘ ማንሳት የምፈልገው ጤፍ በተፈጥሮው ራሱ እህሉ ለሰው ምግብነት ከሌሎች የብርና አገዳ ሰብሎች እህሎች ጋር ሲወዳደር የተፈለጊ ንጥረ ምግብ ይዘቱ የላቀ ከመሆኑም ባሻገር ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ እንጄራን (ከጤፍም ሆነ ከሌሎች ሰብሎች እህሎች) በዘወትር የቀለብ ምግብ ዓይነትነት የመጠቀማችን ባህል ለምግባችን በንጥረ ምግብ ይዘት መመጣጠን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ይህም የሚሆነው እንጄራ ብቻውን ሳይሆን በወጥ ስለሚበላ ነው፡፡ ስለሆነም በእንጄራው ላይ በአበይነት የተለያዩ ነገሮች (ሽሮ፣ የምስር ወይም የአተር ክክ፣ሥጋ እንዲሁም አትክልት ለምሳሌ ጎመን፣ ሰላጣ፣ ድንች የመሳሰሉት) ሊቀርቡ ስለሚችሉ የንጥረ ምግብ ይዘቱን ያሳድገዋል፡፡ ወጡ ውስጥ ደግሞ በተጨማሪ የተለያዩ ቅመማት እና ስብ (ዘይት ወይም ቅቤ) ሰለሚኖር ምግቡ በአስፈላጊ ንጥረ ምግቦች ይዘት የተሟላ እንዲሆን ይረዳል፡፡

ጥያቄ፤ ብዙ ጊዜ ገበሬዎቻችን መሬቱ ማዳበሪያ ከለመደ በኋላ ሰብሎቻችንን ያለ ማዳበሪያ መዝራት አንችልም ሲሉ ይደመጣል፡፡ መሬት እንዴት ማዳበሪያን ይለምዳል? ይህንን አባባል እርስዎ እንዴት ይረዱታል ወይም ይገልጹታል?

ዶክተር ክበበዉ፤ በአንድ ማሣ ላይ ማዳበሪያ በተለይም የኬሚካል መዳበሪያ ስንጠቀም ለሰብሉ ጠቀሜታ የተጨመሩት በማዳበሪያው ውስጥ ያሉ ለተክል አስፈለጊ ንጥረ ነገሮች ብቻ ሲሆኑ ሰብሉ ግን ሌሎቹን አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች የሚያገኘው በአፈሩ ውስጥ ቀድሞውኑ ከነበረው ይዘት ነው። ይህ ማለት ማዳበሪያ በመጨመራችን ምክንያት ቀድሞውኑ በአፈሩ ውስጥ የነበሩት ንጥረ ነገሮች በተክሉ ጥቅም ላይ በመዋላቸው የአፈሩ የነባር ንጥረ ነገሮች ይዘት እቀነሰ ይመጣል፡፡ ይህንን በተሻለ ሁኔታ በምሳሌ እንደሚከተለው ማስረዳት ይቻላል፡፡ አንድ ከዚህ በፊት ማዳበሪያ ተደርጎበት የማያውቅ ማሣ ወስደን ሌሎች ሁኔታዎችን በሙሉ ተመሳሳይ አድርገን ግማሹን ያለማዳበሪያ ጤፍ ብንዘራውና ሌላውን ግማሽ ደግሞ ለሰብሉ የሚያስፈልገውን የማዳበሪያ ዓይነትና መጠን አድርገን ብንዘራው በማዳበሪያ ከዘራነው ግማሽ መሬት ላይ የበለጠ ምርት እናገኛለን። ሆኖም በሚቀጥለው ዓመት በመጀመሪያ ማዳበሪያ ያደረግንበትን ግማሽ አንዲሁም ማዳበሪያ ያላደረግንበትንም ግማሽ ሁለቱንም ያላማዳበሪያ ብንዘራቸው በመጀመሪያው ዓመት ማዳበሪያ ያደረግንበት ግማሽ ማዳበሪያ ተደርጎበት ካልነበረው ግማሽ ያነሰ ምርት ይሰጣል። ከዚህ አንፃር አርሶ አደሮች በራሳቸው ብሂል መሬቱ ማዳበሪያ ለመደ ማለታቸው ትክክል ነው፡፡

ምስሉ የሚያሳየዉ እ አ አ በ2014 የዚህ ብሎግ ጸሐፊ ያዘጋጀዉንና ከተለያዩ የሀገራችን ምርምር ማዕከላትና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተውጣጡ ሠልጣኞች From Agricultural Problem Identification and Diagnosis to Experimentation and Communication በሚል ርዕስ ሥር የሁለት ሳምንት ሥልጠና በወሰዱበት ጊዜ የተነሱትን ፎቶ ሲሆን ዶክተር ክበበዉ አሰፋ (ከፊት ረድፍ ከመሃከል የሚታዩት) የአሰልጣኞች ቡድንን በመቀላቀል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ጥያቄ፤ ብዙ ጊዜ የጤፍን ምርታማነት በገንዘብ መልክ ስንገለጽ የምናሰላዉ እኛ የምንመገበዉን የፍሬዉን ወይም የዘሩን ምርት ብቻ ነዉ፡፡ ነገር ግን ለተለያዩ ግልጋሎቶች ጥቅም ላይ የሚዉለዉን በተለይም ለከብቶቻችን እንደ ምርጥ መኖነት የሚያገለግለውንና ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣዉን የጤፍን ገለባ ስሌት ዉስጥ አናስገባም፡፡ ይህ ትክክል ነዉ ይላሉ?

ዶክተር ክበበዉ፤ እህሉን ወይም ፍሬውን ብቻ ታሳቢ ማድረግ ተገቢም ትክክልም አይደለም፡፡ ምክንያቱም የጤፍ ሰብል ተረፈ-ምርቱ ማለትም ጭዱ በሀገራችን በዋናነት ለከብት መኖነት እንዲሁም ለቤት ምርጊት ከፍተኛ ኦኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ጭዱ ከሌሎች የብርና አገዳ ሰብሎች ተረፈ-ምርት ወይም ገለባ የበለጠ ለከብቶች አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ-ነገሮች አሉት፡፡ ጭዱ ከላይ የተገለፁት ጠቀሜታዎች ስላሉት ደግሞ በሀገራችን እጅግ በጣም በገበያ ተፈላጊነትና ያለው ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ዋጋ ያወጣል፡፡ ይህንንም በምሳሌ ለማስረዳት የወቅቱን ሀገራዊ አማካይ የጤፍ ምርት ስንወስድ አንድ አርሶ አደር ከአንድ ሄክታር የጤፍ ማሳ ላይ በአማካይ 19 ኩንታል የእህል ምርት ሲያገኝ በተጨማሪ 13280 ኪሎ ግራም ጭድ ያገኛል፡፡ የዘንድሮን የገበያ ዋጋ መሠረት አደርገን ብናሰላ ከእህሉ ሽያጭ 123500 ብር (19 ኩንታል X በ6500 ብር በኩንታል) ያገኛል፡፡ በተጨማሪ አንደ እስር ጭድ (Bale) 18 ኪሎ ግራም ያህል ይመዝናል በሚለው ስሌት ብንወስድ የጭዱ ጠቅላላ ምርት በግምት ወደ 740 እስር (Bale) በሄክታር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህንን አሁን ባለው የገበያ ዋጋ እጅግ አሳንሰን አንድ እስር (Bale) 50 ብር ነው ብለን ብንወስድ ከጭዱ ሽያጭ ብቻ አርሶ አደሩ ከአንድ ሄከታር 37000 ብር (740 እስር X 50 ብር በአንድ እስር) ያገኛል ማለት ነው። ስለዚህ የጤፍ ሰብልን ምርታማነት በገንዘብ ስሌት ስንገልፀው በእህሉ ብቻ ሳይሆን በተጨማሪ ጭዱንም ታሳቢ አድርገን መሆን ይኖርበታል፡፡

ጥያቄ፤ የኮታቻ መሬት ከስንዴ ይልቅ በይበልጥ ለምን ለጤፍ እርሻነት ሊመረጥ ቻለ?

ዶክተር ክበበዉ፤ የኮትቻ አፈር ዋነኛ ባህርያት በዝናብ ጊዜ ከመጠን በላይ የእርጥበት ዕዝለት ወይም ውሃ አለመጠንፈፍ (Waterlogging) በደረቅ ጊዜ ደግሞ መኮማተረና መሰንጠቅ ናችው፡፡ ጤፍ የአፈር ወይም የመሬት የበዛ እርጥበት ዕዝለትን (waterlogging) ከሌሎች ሰብሎች (ማለትም ስንዴ፣ በቄሎ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ ወዘተ) ይልቅ የመቋቋም ችሎታ ስላለው ለመረሬ ኮትቻ አፈር ተስማሚና ተመራጭ ሰብል አድርጎታል፡፡

ጥያቄ፤ ሜካናይዜሽን በጤፍ ግብርና ላይ ለምን በሰፊዉ ሊተገበር አልቻለም?

ዶክተር ክበበዉ፤ ሜካናይዜሽን በጤፍ ግብርና ላይ በሰፊዉ ሊተገበር ያልቻለበት ምክንያቶች በርካታ ናቸው፡፡ ከነዚህም መካከል ዋናዎቹ፤ 1ኛ) የጤፍ  የዘር መጠን በጣም ትንሽ (ደቃቃ) በመሆኑ የለሰለሰና የተስተካከለ የመሬት ዝግጅት ስለሚፈልግ እንዲሁም ለመዝራትም ሆነ ለማጨድና ለመውቃት ለሰብሉ ተስማሚ የሆነ መሳሪያ ሰለሚያስፈልገው፣ 2ኛ) የጤፍ ሰብል በአብዛኛው የሚዘራዉ በመረሬ ኮትቻ አፈር ላይ ስለሆነና በሚዘራበት ወቅትም በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት መሬቱ በጣም ጭቃ ሆኖ በላቆጠበት ጊዜ መሆኑ፣ 3ኛ) የጤፍ ሰብል ከፍተኛ የመውደቅና መጋሸብ ባህርይ ስላለው ለማጨድና ለመውቃት አስቸጋሪ ስለሚያደርገው፣ እና 4ኛ) ሰብሉ በእህልነት በዓለም ላይ በዋናነት በኢትዮጵያና ኤርትራ የሚመረት በመሆኑ ተስማሚ የሆኑ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን ያላወጣንለት ወይም ያልሰራንለት ከመሆኑም በላይ በሌሎች ዓለማት ለሌሎቹ ተመሳሳይ (ለምሳሌ ስንዴ፣ ገብሰ፣ ሩዝና ወዘተ የመሳሰሉት) ሰብሎች የተሰሩት ማሽኖችና መሳሪያዎች በቀጥታ ለጤፍ ልንገለገልባቸው የማይቻል መሆኑ ናቸው፡፡

ጥያቄ፤ በሀገራችን የጤፍ አብቃይ ሥፍራዎች ዉስጥ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡት የትኞቹ ናቸዉ?

ዶክተር ክበበዉ፤ ሰሜን ሸዋ (ምንጃር ሽንኮራ፣ ሞረትና ጅሩ)፣ ምስራቅ ሸዋ (አደኣ፣ ሉሜ፣ ጊምቢቹ፣ አቃቂ)፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ደቡበ ምዕራብ ሸዋ፣ ሆሮጉደሩ ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም) ናቸዉ።

ጥያቄ፤ የጤፍ ምርምርና እና ልማትን ለመጎብኘት እርስዎ የተጓዙባቸዉን የሀገራችንን ሥፍራዎች ቢገልጹልኝ፡፡

ዶክተር ክበበዉ፤ በአጠቃላይ እንደ አንድ በጤፍ ላይ ሙሉ ዕድሜውን (ለአርባ ዓመታት ያህል) በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሰራ ተመራማሪ በሁሉም በተለይም በዋና ዋና የጤፍ አምራች የሀገራችን ሥፍራዎች ከምስራቅ እሰከ ምዕራብ እንዲሁም ከሰሜን እሰከ ደቡብ ሄጃለሁኝ ማለት እችላለሁ፡፡ ለዚህም የረዳኝ በአብዛኛው በተለያዩ ጊዜያት የጤፍ ነባር የአርሶ አደር ዝርያዎችን ናሙና ለመሰብስብ፣ ለጤፍ ግብርና ተስማሚ ሊሆኑ የሚችሉ ሥፍራዎችን የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ፣ እና እንዲሁም በጤፍ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪነት የሥራ ድርሻዬ ጊዜ እና በሌሎችም መርሃ ግብሮች ላይ በመሳተፍ በሀገሪቱ በተለያዩ ክፍሎች ለመዘዋወር እድሎችን ማግኘቴ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይህ ማለት ያልሄድኩባቸው ጥቂት ጤፍ የሚመረትባቸው ኪስ (pocket) ቦታዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡

ጥያቄ፤ በከተሞች መስፋፋት ምክንያት የጤፍ አብቃይ ሥፍራዎች በከፍተኛ ደረጃ እየተመናመኑ ይገኛል፡፡ ይህም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ከሚመጣዉ ህዝባችን ጋር ተያይዞ በምግብ ዋስትናችን ላይ አሉታዊ ጎን ይኖረዋል የሚል ሥጋት አለኝ፡፡ እርስዎም የኔን ሥጋት ይጋራሉ?

ዶክተር ክበበዉ፤ እኔም ይህንን ሥጋት ሙሉ በሙሉ እጋራለሁ፡፡ ምክንያቱም አሁን እዚህ ባለንበት መካከለኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች በምናየው እንኳን በከተማዎችና እንዱስትሪዎች መስፋፈት ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ በዋናነት የጤፍ አብቃይ መሬቶች ለምሳሌ በዱከም፣ ቢሾፍቱ፣ኡዴ፣ድሬ፣ አቃቂ፣ ገላን፣ አዲስ አበባ፣ እና ሉሜ አካባቢዎች በእጅጉ እየተመናመኑ ናቸው፡፡ ብዙ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮች ጭምር እንደሚሉት አሁን ባለው ሂደት ከቀጠለ ለምሳሌ በብራንድ ደረጃ የሚታወቀው የአደአ ማኛ ጤፍ ወደፊት በቅርብ ዓመታት ውስጥ ሊኖር አይችልም። ይህ ማለት ግን ከተሞችም ሆኑ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የለባቸውም ማለት ሳይሆን ከተሞች ለከት በሌለው ሁኔታ የጎንዮሽ መለጠጥ ሳይኖርባቸው ያሉትን ቦታዎች በተገቢው ሁኔታ አሟጦና ወደ ላይ እንዲያድጉ አድርጎ በመጠቀም እንዲሁም ከተሞችም ሆኑ ኢንዱስትሪዎች በሌሎች ለግብርና ልማት አመቺ ባልሆኑ መሬቶች ላይ እንዲያርፉ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ እንደ መርህ ከተሞችና እንዲስትሪዎች ለግብርና ልማት የበለጠ አመቺ የሆኑት መሬቶች ላይ ጫና እምብዛም ሳይኖራቸው መስፋፋት ያለባቸው በጥናት የመሬት አጠቃቀም እና ምደባን (land use and capability classification) መሠረት አድርገው መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

ጥያቄ፤ የዛሬ 10 ዓመት እርስዎ የሚያስተባብሩት የብሔራዊ ጤፍ ምርምር ቡድን የብሔራዊ ሽልማት የሚባል ሽልማትና ዋንጫ መሸለማችሁ ይታወቃል፡፡ የዚህ ታላቅ ሽልማትና ዕዉቅናን እንዴት የጤፍ ምርምር ቡድን ሊያሸንፍ ቻለ?

ዶክተር ክበበዉ፤ የብሔራዊ ጤፍ ምርምር ቡድን እ አ አ በ2012 ብሔራዊ የአንደኛ ደረጃ የዋንጫና የሜዳልያ ሽልማት ያገኘው በጊዜው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በችግር ፈቺ የምርምር ውጤት በሀገር አቀፍ ደረጃ ባደረገው ውደድር ቡድኑ በተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎች በተለይም በቁንጮ የጤፍ ዝርያ ማፍለቅ በተገኘው የላቀ ውጤት በቀደምትነት አሸናፊ በመሆን ነው። ቡድኑን በመወከልም በወቅቱ ከነበሩት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒሰቴር እጅ ሽልማቶቹን ተቀብለናል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይም የቁንጮ ጤፍ ቴክኖሎጂን ከማፍለቅ አኳያ ግንባር ቀደም የነበሩት ሌሎች ተመራማሪዎች በተለይም ዶክተር ኃይሉ ተፈራና ዶክተር ጌታቸው በላይ በወቅቱ በሽልማቱ ጊዜ ስላልነበሩ እንጂ የአንበሳውን ድርሻ ሊሰጣቸው ይገባል ብዬ አምናለሁ።

በክፍል 3 ጽሑፌ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ በኢትዮጵያ ግብርና እና ዕድገት በሚመለከት ያደረኩላቸዉን ቃለ መጠይቅና የሰጡኝን መልስ አስነብባችኋለሁ፡፡ እስከዛዉ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መጋቢት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. (April 2, 2023)

One thought on “ግብርናችንን ለማዘመን፤ የጤፉ ጠቢብ፣ዶክተር ክበበዉ አሰፋ፤ ክፍል 2

አስተያየት ያስቀምጡ