ግብርናችንን ለማዘመን፤ የማሽላዉ አባት፣ ክፍል 1

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የማሽላዉ አባት፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን

ክፍል 1

የዛሬዉ ጽሑፌ በግብርናዉ መስክ ላለፉት 55 ዓመታት በሀገር አቀፍም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉትና በአሁኑ ጊዜም በማድረግ ላይ ለሚገኙት አንጋፋ የግብርና ባለሙያ ላይ ያተኩራል። እኝህ ባለሙያም ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን ይባላሉ። ዶክተር ብርሃኔ ያልተሳተፉበት የሥራ መስክ አለ ማለት አይቻልም። ለረጅም ጊዜ በዩኒቨርስቲ የእርሻ ባለሙያዎችን አሰልጥነዋል፣ በተመራማሪነት በተለያዩ ሰብሎች ላይ ሠርተዋል፣ እንዲሁም በሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለበርካታ ዓመታት በኃላፊነት ሠርተዋል።

የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸዉን በእርሻ ለመማር አንጋፋዉን የአለማያ እርሻ ኮሌጅ (የአሁኑ የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ) ከተቀላቀሉበት 1957 ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የድርሻቸዉን እያበረከቱ ይገኛሉ። እኔ ራሴ በቅርቡ ባዘጋቸዋቸዉና በርካታ የግብርና ምርምርና ልማት ባለሙያዎች በተሳተፉበት ሁለት መድረኮች ልምዳቸዉን እንዲያካፍሉ ላደረኩላቸዉ ጥሪ በደስታ ነበር የተቀበሉት።


ማስገንዘቢያ፣ ካልተገለጸ በስተቀር በጽሁፉ ውስጥ የተጠቀሱት ቀናት ሁሉ እንደ አዉሮፓውያን አቆጣጠር ነዉ።

ስለ ዶክተር ብርሃኔ የሚተርከዉ የዛሬዉ ጽሑፌን በቃለ መጠይቅ መልክ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።

ጥያቄ፤ በቅድሚያ ትምህርትዎን የት ተማሩ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ የመጀመሪያ ዲግሬዬን በዕጽዋት ሳይንስ በከፍተኛ ማዕረግ ያገኘሁት በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር በሚገኘዉ የአለማያ እርሻ ኮሌጅ (የአሁኑ ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ) በ1961 ሲሆን የማስትሬት ዲግሪዬን በአግርኖሚ በአሜሪካ ሀገር ከሚገኘዉ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኔብራስካ በ1964 ነዉ። የዶክትሬት ዲግሪዬን ደግሞ እዚያዉ አሜሪካ ከሚገኘዉ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሚኔሶታ በ1969 ነዉ። ሰለዚህ ሶስተኛ ዲግሬዬን ካገኘሁ ዘንድሮ 50 ዓመት ሞላዉ ማለት ነዉ። ጊዜዉ ይሮጣል ልበል።

ጥያቄ የዩኒቨርስቲ መምህር ሆነው የትና መቼ አገለገሉ? ያስተምሩ የነበረዉስ የትኛዉን ኮርስ ነበር?

ዶክተር ብርሃኔ፤ የቀድሞ የአለማያ እርሻ ኮሌጅ (የአሁኑ ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ) ባልደራባ ሆኜ በመምህርነት ያገለገልኩት ከ1964 እስከ 1982 ባሉት ዓመታት ሲሆን በመሃከሉ ለዶክትሬት ትምህርቴ ወደ ዉጭ ከሄድኩበት ሶስት ዓመታት በስተቀር ለ15 ዓመታት በኮሌጁ አስተምሬአለሁ። አስተምራቸዉ የነበሩት ኮርሶች በርካታ የነበሩ ሲሆን እነርሱም ፕላንት ቢሪዲንግ፣ ጄኔቲክስ፣ ባዮሜትሪ፣ ክሮፒንግ ሲስቴም የሚባሉትን ያካትታል።

ጥያቄ፤ እኔ እንደማዉቀዉ አንድ መምህር አንድ ወይም ሁለት ኮርስ ብቻ ነዉ የሚያስተምረዉ። እርስዎ እንዴት እነዚህ የተለያዩ ኮርሶችን ሊያስተምሩ ቻሉ? እውቀቱ ቢኖርዎትም ከፍተኛ የዝግጅት ጊዜ መውሰዱ አይቀርም ብዬ ነዉ የምጠይቅዎት?

ዶክተር ብርሃኔ፤ በርግጥ ኮርሶቹን አስተምር የነበረዉ በተለያዩ የትምህርት ወቅቶች ነዉ። ነገር ግን አንድ ኮርስ እንኳ ለማስተማር ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልግ ነበር። ምክንያቱም ተማሪዎቹ በትምህርታቸዉ ጠንካራ ስለነበሩ የሚጠይቁንን ጥያቄዎች መመለስ እንድንችል በቂ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልገን ነበር። ከማስተማር ሥራዬ በተጨማሪ ምርምርና የዲፓርትመንት አስተዳደር እሠራ ነበር።

ጥያቄ፤ ምርምርን በተመለከተ በሀገር ዉስጥ በምን መስክ ተሳትፈዋል?

ዶክተር ብርሃኔ፤ በአለማያ ኮሌጅ ተቀጥሬ የመጀመሪያ የምርምር ሥራዬን የጀመርኩት በ1964 ሲሆን የሥራ ድርሻዬም የገብስ አዳቃይ ነበር። በገብስ ምርምር ለሁለት ዓመታት ብቻ ነዉ የቆየሁት። ምክንያቱም ለዶክትሬት ትምህርቴ ወደ አሜሪካን ሀገር መሄድ ስለነበረብኝ። ለዶክትሬት የሚያበቃኝን ምርምር በገብስ ማሻሻል ነዉ የሠራሁት። አለማያ እንደተመለስኩ የምርምር አቅጣጫዬም ወደ በቆሎ አዳቃይነት ተቀየረ። ብዙም ሳይቆይ ከሁለት ዓመታት በኋላ ምርምሬን ከበቆሎ ወደ ማሽላ በመቀየር በሰፊዉ ወደ ምታወቅበት የማሽላ ምርምር ውስጥ ገባሁ። የማሽላ አዳቃይ በመሆንም ከ1973 እስከ 1982 ድረስ ለ10 ዓመታት በአለማያ ኮሌጅና በአዳማ መልካሳ በሚገኙ ጣቢያዎች አገልግያለሁ።

ጥያቄ፤ ወደ ውጭ ሀገር ከመሄድዎ በፊት በሀገር ውስጥ በኃላፊነት የሠሩባቸዉ ጊዜያት ካሉ ቢገልጹልኝ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ በሥራ ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ በኃላፊነት የሠራሁት የሀረማያ እርሻ ኮሌጅ የዕጽዋት ሣይንስ ዲፓርትመንት ኃላፊ ሆኜ ነዉ። በዚህ ኃላፊነቴም ከ1969 እስከ 1975 ለስድስት ዓመታት ቆይቻለሁ። በተጨማሪም ከ1973 እስከ 1982 ባሉት 10 ዓመታት የብሔራዊ ማሽላ ምርምር አስተባባሪ በመሆን አገልግያለሁ።

ጥያቄ፤ ለበርካታ ዓመታት ከኢትዮጵያ ዉጭ በነበሩበት ወቅት የሠሩባቸዉ የኃላፊነት ቦታዎች የትኞቹ ናቸዉ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ ከ1982 እስከ 2002 ባሉት 21 ዓመታት በተለያዩ ሀገራት እና የኃላፊነት ደረጃዎች ሠርቻለሁ። እነዚህም ይህንን ይመስላሉ።

  • 1982 እስከ 1986፤ በአፍሪካ ህብረትና ኢክሪሳት የሚባል አለም አቀፍ ድርጅት የተቋቋመ የማሽላ ምርምር ፕሮግራም ውስጥ የምሥራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ አስተባባሪ
  • ከ1986 እስከ 1987፤ ዋና መሥሪያ ቤቱ ሜክሲኮ ሀገር የሚገኘዉ ሲሚት የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት በዋና መሥሪያ ቤቱ የበቆሎ ተመራማሪ
  • ከ1987 እስከ 1991፤ በናይሮቢ ኬኒያ የሲሚት የምሥራቃዊ አፍሪካ የበቆሎ ተመራማሪና የቡድን መሪ
  • ከ1991 እስከ 1993፤ በሀራሬ ዚምባብዌ የሲሚት የደቡባዊ አፍሪካ የበቆሎ ተመራማሪና የቡድን መሪ
  • ከ1993 እስከ 1994፤ በአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኔብራስካ ኢንትሶርሚል የሚባል የዓለም አቀፍ የማሽላና ቡልቱክ ፕሮግራም ተባባሪ ዳይሬክቴር
  • ከ1994 እስከ 2002፤ በአሜሪካ የሚገኘዉ የቪርጂኒያ ቴክ ዩኒቨርሲቲ የተቀናጀ የተባይ አጠባበቅ ፕሮግራም ዳይሬክቴር

ጥያቄ፤ ይህ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ የዘለቀዉን በተለያዩ ሀገራት ያደረጉትን አገልግሎት ካጠናቀቁ በኋላ ወዴት ሄዱ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ በ2002 ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩ። አማረዉ የሚባል በአሜሪካን መንግሥት የሚደገፍ ፕሮጀከት ኃላፊ በመሆን ሠርቻለሁ። ይህ ሁለገብ የሆነ ፕሮጀክት ትኩረት አድርጎ ይሠራ የነበረዉ በአማራ ክልል በማክሮ ፋይናንስ፣ ግብርና ምርምርና ስርጸት እንዲሁም የዉሃ ተፋሰሶች ጥበቃ ላይ ነበር። የፕሮጀክቱን መምራትና ማስተባበር ሥራ እሠራ የነበረው ከባህር ዳር ከተማ ሆኜ ነበር። በዚህ ፕሮጀከት በኃላፊነት እስከ 2008 የቆየሁ ሲሆን ይህም ለሰባት ዓመታት መሆኑ ነዉ።

ጥያቄ፤ የአማረዉ ፕሮክጀት ከተጠናቀቀ 11 ዓመታት ሆነዉ። እርስዎ ግን እስካሁንም በቃኝ አላሉም። በአሁኑ ጊዜ በምን ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ አቅሜ በፈቀደዉ መጠን በሙያዬ እያገለገልኩ እገኛለሁ። በአሁኑ ወቅት የቨርጂኒያ ቴክ የተቀናጀ የተባይ አጠባበቅ ፕሮግራም የአፍሪካ ክፍል አማካሪ ነኝ።የኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚም ምክትል ፕሬዘዳንት ሆኜ ሳገለግል ቆይቼ አሁን ለተረኛ አስረክቤ ወጥቼአለሁ። ከዚህ በተጨማሪ በርካታ ድርጅቶችን በቦርድ አባልነት ወይም ፈቃደኝነት እያገለገልኩ እገኛለሁ።

በዶክተር ብርሃኔ ላይ የሚያተኩረዉ ጽሑፌ በዚህ አያበቃም። በሚቀጥለዉ ጽሑፌ በሰፊዉ ስለሚታወቁበት የማሽላ ምርምር እንዲሁም ለኢትዮጵያ ግብርና ያላቸዉን ራዕይና መልእክት አስነብባችኋለሁ።

እስከዚያዉ መልካሙን እመኝላችኋለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መስከረም 25፣ 2012 ዓ.ም. (October 6, 2019)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ ስለ ግብርናችን የጻፉልን

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ስለ ግብርናችን የጻፉልን

ሰለ አንድ ማንኛዉም ነገር ግንዛቤ እንዲኖረን በቅድሚያ የምናደርገዉ መሥራት ባቀድነው መስክ ላይ ቀደም ብሎ የተሠራ ነገር ካለ መረጃ ማሰባሰብ ነዉ። የምናሰባስበዉ መረጃም ባብዘኛዉ ሊገኝ የሚችለዉ ቀድም ብሎ ከታተሙ የተለያዩ ጽሑፎች ነው። እነዚህ ጽሑፎች ለአንባቢያን የሚቀርቡበት መንገድም እንዲሁ ይለያያል። ኦሪጂናል የሆኑ የምርምር ዉጤቶች ባብዘኛዉ የሚቀርቡት ወቅታቸዉን ጠብቀዉ በሚታተሙ ጆርናል በሚባሉ የህትመት ዓይነቶች ነዉ። ከዚህ ዉጭ ሌሎች ጽሁፎች በመጽሐፍ፣ በሪፖርት ወይም በሌላ መልክ ሊቀርቡ ይችላሉ።

ስለ ኢትዮጵያ የሚጠቅሱ የጆርናል ጽሑፎች ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት (ከ1900 እስከ ዛሬ መስከረም 18 ቀን 2012) ስንት ይሆናሉ ብዬ ዌብ ኦፍ ሳይንስ የሚለዉን ድህረ ገጽ ስጠይቅ 26,886 ናቸዉ የሚል መልስ አገኘዉ። ሌላዉ ጥያቄዬ ኢትዮጵያና እርሻ የሚሉትን ቃላት አጣምሮ የያዙ ጽሑፎች የሚለዉ ሲሆን የዚህ መልሱም 1,024 ብቻ እንደሆኑ ነዉ። ከዚሁ በተጓዳኝ ኢትዮጵያና ደን የሚሉ ቃላትን አጣምረዉ የያዙ 1,169 ሲሆኑ ኢትዮጵያና ጤና የሚሉትን ቃላት አጣምረዉ የያዙ ደግሞ 6,418 ናቸዉ። በርግጥ በራሴም ግምገማ በጤናዉ መስክ ኢትዮጵያን በተመለከተ በርካታ የጆርናል ጽሑፎች ይታተማሉ። ይህ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ቃላትን በጣምራ በመጠቀም የሚገኘዉ ዉጤት ትክክለኛ ቁጥርን ሊያሳይ አይችልም። ምክንያቱም በተጻፈዉ ጽሑፍ ውስጥ ሁለቱ ቃላት ባንድነት ላይታዩ ሰለሚችሉ ነዉ። ቢሆንም ጥሩ አመላካች ሊሆን ይችላል።

የሀገራችን ግብርናን የሚመለከቱ የተውሰኑ መጽሐፍት ይኖራሉ። ነገር ግን ሁሉንም በተማከለ ሥፍራ ማግኘት አዳጋች ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰባሰቡበት ቤተ መጽሐፍ ስለሌለ ነዉ። ከዚህ በታች የተጠቀሱት ጥቂት መጽሐፍት ለማስረጃ እንዲሆኑ ብዬ ያቀረብኳቸዉ ናቸዉ እንጂ በርካታ መጽሐፍት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

  • Agricultural Systems in Ethiopia by Westphal E. (1975)
  • Agricultural Transformation in Ethiopia: State Policy and Smallholder Farming by Beyene A. (2018)
  • Coffee Atlas of Ethiopia by Davis A, Wilkinson T, Challa ZK, Baena S, Gole TW, Moat J. (2018)
  • Food and Agriculture in Ethiopia: Progress and Policy Challenges by Dorosh PA, Rashids S. Eds. (2012)
  • Foreign Direct Investment in Large-Scale Agriculture in Africa: Economic, Social and Environmental Sustainability in Ethiopia by Persson AGM. (2019)
  • Guidelines for Development Agents on Soil Conservation in Ethiopia by Author Hurni H. (1986)
  • People of the Plow: an Agricultural History of Ethiopia, 1800–1990 by McCann JC. (1995)
  • Plant Genetic Resources of Ethiopia by Engels JMM, Hawkes JG, Worede M. (1991)

የዛሬዉ ጽሑፌ የሚያተኩረዉ በቅርቡ በዶክተር ጌታቸዉ ድሪባ የታተመዉና ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን ስላገኘዉ መጽሐፍ ነዉ። የመጽሐፉ ርዕስ ‘Overcoming Agricultural and Food Crisis in Ethiopia: Institutional Evolution and the Path to Agricultural Transformation’ የሚባል ሲሆን የታተመዉም ከአንድ ዓመት በፊት እ.ኤ.አ. በ2018 ነዉ። መጽሐፉ በ11 ምዕራፎች የተከፈለና በአጠቃላይ 417 ገጾች ያሉት ነዉ። እኔም መጽሐፉን በኦንላይን ገዝቼ እያነበብኩ ነኝ። መጽሐፉን በተመለከተ የተጻፉ የግምገማ ጽሑፎችና እንዲሁም በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ደራሲዉ የሰጡትን ቃለ መጠይቅም ለማንበብ ችያለሁ።

ጸሐፊዉ የመጀመሪያ ድግሪያቸዉን ከሀረማያ ዩኒቨርሲቲ፣ የማስትሬት ዲግሪያቸዉን ጀርመርን ሀገር ከሚገኘዉ የዶርትሙንድ ዩኒቨርሲቲ በመቀጠልም ፒ ኤች ዲ እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘዉ የኢስት አንግሊያ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። በሙያቸዉም የእርሻ ኢኮኖሚክስት ናቸዉ። በሥራ ልምድም በኢትዮጵያ ዉስጥም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ በተለያዩ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለበርካታ ዓመታት ሠርተዋል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ዋና ጽሕፈት ቤቱ ሮም በሚገኘዉ የዓለም ምግብ ድርጅት ዉስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ይሠሩ ነበር።


ዶክተር ጌታቸዉ የተወለዱት ከአሰላ ከተማ በቅርበት በምትገኘዉና ከታዋቂዉ የጭላሎ ተራራ ሥር ካለችዉ ዶሻ በምትባል መንደር ነዉ። የዶሻ መንደርም የአሰላ ብቅል ፋብሪካና የቁሉምሳ እርሻ ምርምር ማዕከል ካሉበት በ20 ኪ.ሜ. የሚገኝ ቦታ ነዉ። በመጽሐፋቸዉ መግቢያ ላይም ዶክተር ጌታቸዉ የዚህ የተወለዱበትን አካባቢ የግብርና ለውጥን ይተርካሉ። ይህ አካባቢም በኢትዮጵያ ዉስጥ ዘመናዊ የግብርና አሠራርን ካገኙ ሥፍራዎች ቀደምትነቱን ይይዛል። በመጀመሪያ ካዱ በመቀጠልም አርዱ በሚል መጠሪያ ከስዊዲን መንግሥት ጋር በተደርገ ትብብር ሠፊ የልማት ሥራ የተከናወበት ሥፍራ ነዉ። ዶክተር ጌታቸዉ በመጽሐፋቸዉ ውስጥ የሀገራችን ግብርና በሶስቱ መንግሥታት ያደረገዉን ዕድገት ወይም ለዉጥ በዝርዝር ያቀርባሉ።

በዛሬዉ ጽሁፌ በመጽሐፉ ላይ ያለኝን የራሴን ግምገማ ለማቅረብ ሳይሆን ባጋጣሚ መጽሐፉን ላላያችሁ አንብባችሁ የራሳችሁን ግንዛቤ እንድትወስዱ ብዬ ነዉ። ከመጽሐፉ በተጨማሪ ተሾመ ሁንዱማ እና ሰላም ኃይለሚካኤል የተባሉት ጸሐፊያን ጃኑዋሪ 6፣ 2019 ኢትዮጵያ ኦብዘርቨር ላይ ስለ መጽሐፉ ያደረጉትን ግምገማና በሪፖርተር ላይ የታተመዉን የደራሲዉን ቃለመጠይቅ ማንበብ ጠቃሚ ነዉ።

ማጠቃለያ፤ ስለ ሀገራችን ግብርና የሚያወሳ ብዙ መረጃ በሌለበት ዉድ ጊዜያቸዉን ሰዉተዉ ስለሀገራችን ግብርና አመጣጥም ሆነ ሂደት እንዲሁም ለወደፊት ያለዉን ተስፋ የጻፉልን ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል። ምክንያቱም የድርሻቸዉን አበርክተዋልና ነዉ። የዛሬ ጽሑፌን የማበቃዉ የሪፖርት ጋዜጠኛ የሆነዉ ብርሃኑ ፍቃዴ ለዶክተር ጌታቸዉ ካደረገላቸዉ ቃለ መጠይቅ ዉስጥ መጽሐፉን ለመጻፍ ምን እንዳነሳሳቸው ሲጠይቃቸዉ በመለሱት መልስ ነዉ። “መጽሐፉን ለመጻፍ ያነሳሳኝ በዉስጤ ያለዉ ቁጭት ነዉ። በሥራ ምክንያት በበርካታ ሀገራት ለመጓዝ ዕድል አግኝቻለዉ። የሀገራቱን የግብርና ዕድገትም በቅርበት ለማየት ችያለዉ። የኛ ሀገር ግብርና ግን ገና ብዙ ይቀረዋል።” ትርጉሙን ቃል በቃ አልተረጎምኩትም።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መስከረም 18፣ 2012 ዓ.ም. (September 29, 2019)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለውጥን እንግታ!!!

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለውጥን እንግታ!!!

በምሥሉ የሚታየዉ የዓለምን ህዝብ ያነቃነቀችዉ የ16 ዓመቷ ግሬታ ቱንበርግ ሰሞኑን ከቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ጋር በተገናኘችበት ወቅት ነዉ። የምሥሉ ምንጭ

ከሁለት ቀናት በፊት ዓርብ መስከረም 9፣ 2012 (እ. ኤ. አ. ሴፕቴምቤር 20, 2019) በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአለማችን ወጣቶች ድምጻቸዉን ለማሰማት አደባባይ ወጥተዉ ነበር። ወደ አደባባይ ለመዉጣት ያበቃቸዉም የአየር ንብረት ለውጥ በማድረስ ላይ ያለዉንና በቅርቡም ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቀዉን መጥፎ ክስተቶች እንዲታደጉላቸዉ በመንግስቶቻቸዉ ላይ ተጽእኖ ለማድረግ ነዉ። በራሳቸዉ ሀገራትም ብቻ ሳይወሰኑ ሰሞኑን በኒዉዮርክ በሚደረገዉ የተባበሩት መንግስታት ጉባኤ ላይም የአየር ንብረት ለዉጥ ከፍተኛ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ ነዉ። ከላይ እንደገለጽኩት በዚህ ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ በተለየ ሁኔታ የተሳተፉት ወጣቶች ናቸዉ። ምክንያቱም የአየር ንብረት ለዉጥ ከፍተኛ ተጽእኖ የሚያደርሰዉ በእነርሱ ላይ እንደሆነ ሰለተረዱና ይህንንም ለህብረተሰቡ ለማስገንዘብ ነዉ። በተጨማሪም ይህ የአየር ንብረት ለውጥ ሊያደርስ ይችላል ተብሎ የሚጠበቅዉን መጥፎ ክስተትም ለመግታት ዕርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ ለማድርግ ነዉ።

ይህ አዉስትራሊያ፣ አዉሮፓ፣ አፍሪካ፣ እንዲሁም ሰሜንና ደቡብ አሜሪካ በሚገኙ 150 ሀገራት የተደረገዉ የተቃዉሞ ሰልፍ የተመራዉ ግሬታ ቱንበርግ በምትባል ወጣት አክቲቪት ነዉ። ስለዚች ቆራጥ ወጣት የስዊድን ዜጋ ከዚህ በፊት የአየር ንብረት ለዉጥን አስመልክቶ በጻፍኳቸዉ ብሎጎች ውስጥ ህብረተሰቡ ምን ይላል በሚል ሰኔ 16 ቀን 2011 በከተብኩት ጽሑፍ ለማሳየት ሞክሬአለሁ። በሀገሯ ስዊዲንና በርካታ የአውሮፓ ከተሞች እየተዘዋወረች ካደረገቻቸዉ ንግግሮች በተጨማሪ ሰሞኑን በአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት አስተዋጾ እንዲያደርጉ አሳስባለች። ወደ አሜሪካ የተጓዘችዉም ከአንድ ወር በፊት ሲሆን 15 ቀናት በፈጀ የጀልባ ጉዞ ሲሆን ይህም በጸሐይ ብርሃን በመታገዝ የሚነዳ ነዉ። በመሆኑም ለጤናችን ጎጂ የሆነዉ ካርቦን ወደ ከባቢያችን እንዳይረጭ ታሳቢ በማድረግ ነዉ።

ከሁለት ቀናት በፊት በተደረጉት ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በርካታ መሳጭ መፈክሮችም ተይዘዉ ነበር። በየሀገራቱም ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን አግኝተዉ ነበር። ከነዚህ ውስጥ ‘ሌላ ዓለም የለንም’ የሚለዉ ልብ የሚነካ ነዉ። ከአፍሪካ ሀገራት ዉስጥ የተሟላ መረጃ ባይኖረኝም በደቡብ አፍሪካና ኬኒያ የሚገኙ ወጣቶችም ወደ አደባባይ ውጥተዉ ድምጻቸዉን አሰምተዋል።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መስከረም 11፣ 2012 ዓ.ም. (September 22, 2019)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች

ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች በመባል የሚታወቀዉ እጅግ አደገኛ ተባይ ሲሆን በእንግሊዘኛዉ አጠራር Fall armyworm የሚባል ሲሆን በሳይንሳዊ ስያሜው ደግሞ Spodoptera frugiperda ይባላል። ይህ የገበሬዎቻችን ክፉ ጠላት አባ ጨጓሬ የሚመስል ሲሆን በእድገቱ የመጨረሻዉ ዘመን ወደ የእሳት እራትነት ይቀየራል። የእሳት እራቶቹ ከሚጥሉት እንቁላሎች የሚፈለፈሉት አባ ጨጓሬዎች ናቸዉ ሰብሎቻችንን በአጭር ጊዜ ዉስጥ ያለርህራሄ አመድ የሚያደርጉት። ደጋጎቹ እናት የእሳት እራቶች ግን መልካቸዉ ለተመልካች ከመማረኩም በላይ እራሳቸዉ በቀጥታ በሰብል ላይ የጎላ ጉዳት አያደርሱም። ቢሆንም ራቅ ወዳለ ሥፍራ በቀላሉ በመብረርና በርካታ እንቁላሎችን በመጣል እንዲሁም ከእንቁላሎቹ የሚፈለፈለዉ ተምች በአጭር ጊዜ መጠነ ሰፊ ጥቃት እንዲያደርስ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ። ምክንያቱም ጉልምሱ የእሳት እራት በአንድ ሌሊት እስከ 100 ኪ. ሜ . መብረር ይችላልና ነዉ። ለዚህ ረዥም ርቀት በረራ ዋና ምክንያቱ የእሳት ራቶቹ ጠንካራ ክንፎች ናቸዉ።

በምስሉ በስተግራ የሚታየው ጉልምሱ የእሳት እራት ሲሆን በስተቀኝ የሚታየዉ ደግሞ በሰብሎቻችን ላይ ከፍተኛ ጥቃት የሚያደርሰዉን አባ ጨጓሬ መሳዩን ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች ነዉ።

በሞቃታማ አካባቢዎች ያሉ ምቹ የአየር ሁኔታዎች እና እፅዋቶች ይህ ተባይ በዓመት በርካታ ጊዜ እንዲራባ ያስችለዋል። ይህ አባ ጨጓሬ መሳዩ አደገኛ ተባይ የማያጠቃዉ የሰብል ዓይነት የለም ማለት ይቻላል። እስካሁን በተደረገዉ ጥናት ወደ 80 የሚጠጉ የሰብል ወይም የተክል ዓይነቶች በዚህ ተባይ ይጠቃሉ። በተለይ በእድገት ላይ ያሉ የበቆሎ ተክሎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቁ ሲሆን እንደ ዳጉሳና ማሽላ የመሳሰሉትም ለከፋ አደጋ ይጋለጣሉ።

የተባዩ ሥርጭት

የዚህ አደገኛ ተምች መነሻዉ ሰሜናዊና ደቡባዊ አሜሪካ ሲሆን በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየዉ በናይጄሪያ ሲሆን ይህም የተከሰተዉ ከሶስት አመት በፊት እ.ኤ.አ. በጃኒዋሪ 2016 ነበር፡፡ ለዘመናት ከኖረበት ሁለቱ የአሜሪካ አህጉራት ወደ አፍሪካ የመጣዉ ከመንገደኛ ወይም ከዕቃ ጋር በአይሮፕላን ተሳፍሮ እንደሆነ ይገመታል። አንዴ የአፍሪካን አህጉር ከረገጠ በኋላ ግን የማንንም የትራንስፖርት ዕርዳታ ሳያስፈልገዉ በራሳቸዉ ክንፍ እየበረሩና እንቁላሎቻቸዉን በበቆሎ እርሻ ላይ መዝራት ተያያዙት። የተዘሩት እንቁላሎችም ሲፈለፈሉ አባ ጨጓሬዎቹ በሰብል ላይ ጥቃት ማድረስ ጀመሩ። በዚሁ መሠረት በጃኒዋሪ 2016 በናይጄሪያ ብቻ የታየዉ ይህ ተባይ ከ10 ወራት በኋላ በኖቮምበር 2017 በተጨማሪ ሰድስት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ላይ ጥቃት ያደረሰ ሲሆን ከሶስት ተጨማሪ ወራት በኋላ በፌብሪዋሪ 2017 በደቡባዊ የአህጉሪቱ ክፍል ወደሚገኙ ሰባት ሀገሮች ሊስፋፋ ችሏል። ከሁለት ተጨማሪ ወራት በኋላ በአፕሪል 2017 የጥቃት አድማሱን በማስፋፋት ዘጠኝ ተጨማሪ አገራት ላይ ጥቃት ሊያደርስ ችሏል። የሚገርመዉ ተባዩ በአፍሪካ አህጉር በታየ በአንድ ዓመቱ በዲሴምቤር 2017 ወደ 38 የአፍሪካ አገሮች ሊዛመት ችሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህ ተባይ የአፍሪካን አህጉር አዳርሶ ወደ ኤሺያም ተሸጋግሯል። በዚሁ መሠረት በ2019 በህንድ፣ ሚያንማር፣ ሲሪላንካ፣ ታይላንድና የመን ድረስ ሊዛመት ችሏል።

ይህ ፈጣን ሁሉን አውዳሚው ተምች ተብሎ የተሰየመዉ ተባይ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየዉ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ሸካ ዞን እ.ኤ.አ. ማርች 2017 ሲሆን የዛሬ አመት የወጣ ሪፖርት እንደሚያሳዉ ተባዩ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በ417 ወረዳዎች እንደ ተሰራጨ ነዉ።

ምስሉ የሚያሳየዉ በአፍሪካ የፈጣን ሁሉን አውዳሚው ተምች ሥርጭትን ነዉ። የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ተባዩ ባንድ ዓመት ውስጥ 38 የአፍሪካ ሀገራትን አዳርሷል። የምሥሉ ምንጭ፣ CIMMYT

የጥቃቱ ሁኔታና መጠን

አባጨጓሬው የበቆሎ ቅጠልን ከመብላቱም በተጨማሪ የሰብሉ ዋናውንና አናቱ ላይ የሚገኘውን የእድገት ክፍሉን ያጠቃል፡፡ በትልልቆቹ የበቆሎ ሰብሎች ላይ ደግሞ ቆረቆንዳቸው ድረስ በመዝለቅ እየቦረቦረ ሊያጠቃ ይችላል፡፡ በቅርቡ በተሰላዉ ግምት በኢትዮጵያ በቆሎ ከሚዘራበት 2.1 ሚሊየን ሄክታር ማሳ ዉስጥ 22 ፐርሰንቱ በዚህ ተምች ተጥቅቶ ነበር፡፡ ተገቢዉ የቁጥጥር እርምጃ ካልተወሰደ በዚሁ ጥቃት ከ12.3 እስከ 31 ሚሊየን ኩንታል የሚሆን የበቆሎ ምርት ሊወድም የሚችል ሲሆን ይህም በገንዘብ ሲተመን ከ8.2 እስከ 20.3 ቢሊዮን ብር ይደርሳል፡፡

ተባዩን በቁጥጥር ሥር ለማድረግ በሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ደረጃ በመደረግ ላይ የሚደረገዉን ርብርብና ስለ መከላከያ ዘዴዎች ወደፊት እዘግባለሁ።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆንልን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መስከረም 1፣ 2012 ዓ.ም. (September 12, 2019)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ ክብረ ወሰን በዛፍ ተከላ!!

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ክብረ ወሰን በዛፍ ተከላ!!

የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባደረጉት ጥሪ መሠረትና ህብረተሰቡ ባደረገዉ ከፍተኛ ተሳትፎ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በአንድ ጀምበር ብቻ 353,633,660 የዛፍ ችግኞች በሀገሪቱ ሊተከሉ ችለዋል። ይህ የዛፍ ተከላ ቆጠራም የተከናወነዉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተመርኩዞ በመሆኑ ከፍተኛ ተቀባይነት አለዉ። ለዚሁ ሲባል የግብርና፣ ኢኖቬሽንና ሌሎች የሚመለከታቸዉ መሥሪያ ቤቶች በተቀናጀ ሁኔታ እንደተሣተፉበት ተከላዉ በተደረገበት ቀን ምሽት ከተሰጠዉ ጋዜጣዊ መረጃ መረዳት ችያለዉ።

ኢትዮጵያኖች በሙሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ እንዲሁም በሀገሪቱ የሚገኙ የዉጭ ሀገር ዲፕሎማቶች የተሳተፉበት ይህ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በሀገሪቱ ከተደረጉትና ሀብረተሰቡን በአንድ ወቅት በጋራ በማሳተፍ ከተሰሩ ሥራዎች ሁሉ ግዙፉ ነዉ ማለት ይቻላል። ስለዚህ ለዚህ የልማትና በጎ ሥራ ለህዝቡ ጥሪ ላቀረቡት ለጠቅላይ ሚኒስትሩና እንዲሁም መርሀ ግብሩ ተፈጻሚነት እንዲያገኝ ከፍተኛ ርብርብ ላደረጉት በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች ከፍተኛ ምሥጋና ሊደርሳቸዉ ይገባል።

ከዛፍ ወይም ደን ጋር ተዛማች የሆኑ በቅርቡ የጻፍኳቸዉ ሶስት ብሎጎች ከዚህ በታች በተገለጹት ሊንኮች ማግኘት ይቻላል።

1ኛ) የአየር ንብረት ለውጥ — በደናችን (ዛፎቻችን)

2ኛ፟) የአየር ንብረት ለውጥ — የካርቦን ገበያ፣ ታክስና ፈንድ፣ እና

3ኛ) ባህር ዛፍ ጠቀመን ወይስ መጠመጠን? የሚሉት ናቸዉ።

በነዚሁ ጽሑፎኝ እንደተገለጸዉ ዛፍ ከሚያስገኝልን በርካታ ጥቅሞች በተጨማሪ ለአየር ንብረት ለዉጥ መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርገው ካርቦንዳይኦክሳይድ ወደ ከባቢያችን እንዳያፈተልክና ለጉዳት እንዳይዳርገን አምቆ በመያዝ ይጠቅመናል።ከአንድ ዛፍ ጠቅላላ ክብደቱ ዉስጥ ግማሹን የሚይዘዉ ካርቦን ነዉ። በዚሁ መሠረት 12 ዓመት የሆነውና 600 ኪ.ግ. የሚከብድ ዛፍ በዉስጡ 859 ኪ.ግ. ካርቦንዳይኦክሳይድ አምቆ የሚይዝ ሲሆን በአንድ ሄክታር ላይ ያለ ደን (በአንድ ሄክታር 650 ዛፍ ቢኖር) በ12 ዓመት 0.56 ሚሊዮን ኪ.ግ. ካርቦንዳይኦክሳይድ አምቆ ይዟል ማለት ነዉ። ከላይ በተገለጸዉ ስሌት መሠረት በሐምሌ 22 ቀን ብቻ በኢትዮጵያ የተተከሉት 353,633,660 ችግኞች በ544,051 ሄክታር መሬት ላይ ያረፉ ቢሆን በሚቀጥሉት 12 ዓመታት በጠቅላላዉ 304.7 ቢሊዮን ኪ.ግ. ካርቦንዳይኦክሳይድ አምቀዉ ይይዛሉ ማለት ነዉ። ስለዚህ የአየር ንብረት ለዉጥን በመግታት ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታሉ ማለት ነዉ።

ይህ ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ የነበረዉ የዛፍ ተከላ በሀገር ዉስጥ ካለዉ ሚዲያ ባልተናነሰ መልኩ በውጭ የሚገኙ ታዋቂ ሚዲያዎች ከፍተኛ ሽፋን ሰጥተዋል። የዚህን ዜና ከነዚህ ሚዲያዎች የሰሙ ወይም ያነበቡ የሥራ ባልደረቦቼም አድናቆት በተሞላበት መልኩ ጠይቀዉኛል። በወቅቱ ዜናዉን ከዘገቡት ዉስጥ ጥቂቶቹ ከዚህ በታች ተገልጸዋል። የጽሑፉን ሙሉ ይዘት ርዕሱን በመጫን ማግኘት ይቻላል።

CNN: Ethiopia plants more than 350 million trees in 12 hours

New York Times: Ethiopia Plants More Than 200 Million Trees in 1 Day

Washington Post: Ethiopia plants more than 200 million trees in 1 day

BBC: Ethiopia ‘breaks’ tree-planting record to tackle climate change

The Guardian: Ethiopia plants 250 million trees in a day to help tackle climate crisis

Bloomberg: Ethiopia plants 350 million trees in one day to combat drought

Africa news: Ethiopia breaks world record for tree planting in a single day

Metro: Ethiopia breaks record by planting 350,000,000 trees in a day to fight climate change

The Hill: Ethiopia plants more than 350 million tree seedlings in one day to fight climate change

Almariam (አልማሪያም)፣ ታዋቂዉ የህግ ባለሙያና የካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር Ode to 4 Billion Tree Saplings by the River Ghion (Ethiopia)

ሰሞኑን ባርሴሎና ነበርኩ። ደራርቱ የዛሬ 27 ዓመት በ10 000 ሜትር ድል የተቀዳጀችበት የ1992ቱ የባርሴሎና ኦሎምፒክ ሥፍራ ማየት አለብኝ ብዬ በመጀመሪያው ቀን ቦታዉን ለማግኘት አዳጋች ቢሆንብኝም በማግስቱ አግኝቼዋለዉ። የመሮጫ ትራኩንና ሙዚየሙን እንዲሁም ለማሸነፍ በተቃረበችበት ጊዜ የነበረዉን ሁኔታ የሚያሳዩ ምሥሎች ከዚህ በታች ማየት ይቻላል።

ከላይ የሚታየዉ ደራርቱ የሮጠችበት ትራክና ስታዲየም ነዉ።

ይህ በባርሴሎና የሚገኘዉ የኦሎምፒክ ሙዚየም የተሰየመዉ በታዋቂዉ አንቶኒዮ ሳማራንች ነዉ። ሳማራንች በባርሴሎና የተወለዱ ሲሆን የኢንተርናሽናል ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዘዳንት በመሆን ለ21 ዓመታት ያገለገሉ እጅግ ተወዳጅ መሪ ነበሩ። በሙዚየሙ ዉስጥ እስከ 2000 የሲድኒ ኦሎምፒክ የነበሩ አበበ ቢቂላን ጨምሮ የታዋቂ አትሌቶች ምስልና ቪዲዮ ይገኛል።

ከላይ የሚታየዉ ምሥል የሚያሳየዉ ደራርቱ ድል ልትቀዳጅ በተቃረበችበት ወቅት የነበረዉን ሁኔታ ነዉ።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ነሐሴ 1፣ 2011 ዓ.ም. (August 7, 2019)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የከተማ ግብርና

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የከተማ ግብርና

ግብርና የተለመደዉ በገጠር ቢሆንም ባንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች መጠነ-ሰፊ ግብርና በከተሞችም ይካሄዳል። እነዚህ የከተማ እርሻዎች የተለያዩ ሰብሎችን የሚያመርቱ ሲሆን ለምግብነት የሚዉሉ እንስሳዎችንም ያረባሉ። በተለይም በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ ያተኮረ የከተማ ግብርና ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል። በዓለማችን ወደ 800 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በከተማ ግብርና እንደሚሳተፍ ይገመታል

የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት ሪፖርት እንደሚያሳየዉ የሰብል ከወሰድን የከተማ ግብርና ገጠር ካለዉ ግብርና እስከ 15 እጅ የበለጠ ምርታማ ነዉ። በሪፖርቱ መሠረት ከአንድ ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ እስከ 20 ኪሎ ግራም ምግብ ማምረት ይቻላል። በዚሁ መሠረት አንዳንድ የዓለማችን ከተሞች የከተማ ግብርናን አስፋፍተዉ ይገኛሉ። በከተሞች ዉስጥ የመሬት ጥበት በመኖሩ ምክንያት የከተማ ግብርና በመሬት ላይ ብቻ ሳይሆን በህንፃዎች ጣራ ላይም በሰፊዉ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል።  ለምሣሌ የፓሪስ ከተማ ከሶስት ዓመት በፊት እ.ኤ.አ. በ2016 በነደፈዉ ዕቅድ መሠረት በአራት ዓመት ዉስጥ 100 ሄከታር የሚሸፍን በቤቶች ጣራ ላይ የሚመረት አትክልት ለማልማት አቅዶ ነበር። በዚህ ተግባሯም ከተማዪቱ በዓለማችን ታዋቂነትን አትርፋለች። ይህችዉ ከተማ በአሁኑ ዓመት ደግሞ 32 አዳዲስ የከተማ ግብርና ሥፍራዎችን አስጀምራለች። ስለዚህ እንደ ቲማቲም፣ ጎመን፣ ሰላጣ፣ ካሮት፣ ሃባብ፣ ወዘተ በቤታቸዉ ጣራ ላይ በማምረት ከራሳቸዉ ፍጆታ አልፈዉ ለሽያጭም የሚያቀርቡ የከተማ ገበሬዎች ብቅ እያሉ ነዉ። በተለይ ይህ ተግባራዊ ሊሆን የሚሆነው የህንፃቸዉ ጣራ ጠፍጣፋ የሆነ እንደሆነ ነዉ።

ከላይ በምሥሉ የሚታየዉ ፉኩኦካ በምትባል የጃፓን ከተማ በሚገኝ ህንፃ ላይ የለማ እርሻ ሲሆን ለህንፃውም መልካም ዉበት አሰጥቶታል። ምሥሉ የተወሰደዉ ከዚህ ድህረ ገጽ ነዉ።

በኢትዮጵያ የከተማ ግብርና በሰፊዉ ተስፋፍቶ ባይገኝም ባንዳንድ ክፍት ቦታዎችና የመስኖ ዉሃ በሚደርስባቸዉ ሥፍራዎች የጓሮ አትክልቶች ሲተከሉ የታያል። ለምሣሌ በአዲስ አበባ የትንሿ አቃቂ ወንዝን በመጠቀም በመካኒሣ፣ ጎፋና ላፍቶ የተወሰኑ እርሻዎች ነበሩ። ቴዎድሮስ ፊርዲሳ የተባሉ ለማስተርት ዲግሪ ለሚያበቃቸዉ ያደረጉት ጥናት እንደሚያሳየዉ እ.ኤ.አ. በ2007 በአዲስ አበባ ውስጥ ካሉት 10 ክፍለ ከተሞች ዉስጥ ሰባቱ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የከተማ ግብርና ያካሄዱ ነበር። የከተማ ግብርናን የማያካሂዱት ሶስቱ ክፍለ ከተሞች አዲስ ከተማ፣ አራዳና ቂርቆስ ናቸዉ።

በከተማ ግብርና የተለመዱትን የአትከልትና ፍራፍሬ ዓይነቶች ብቻ ሳይሆን እንደ እንጉዳይ የመሳሰሉትንም በማሳደግ የአመጋገብ ሥርዓታችንን ማስፋት ብቻ ሳይሆን እንደ ገቢ ምንጭነትም ልንጠቀምበት እንችላለን። ጠቃሚ ከሆኑ የምግብ ንጥረ ነገሮች መካካል እንጉዳይ በቂ የሆነ ፕሮቲን፣ ቫይታሚን ቢ፣ ቫይታሚን ሲ፣ ካልሺየም፣ ወዘተ በውስጡ ይዟል። ከዚህ በተጨማሪ ሴሎቻችንን ከተለያዩ የበሽታ ጥቃቶች ሊከላከልን ይችላል ተብሎ የሚገመተዉ ሴሊኒየም የተባለ ንጥረ ነገር እንጉዳይ ከሌሎች ተክሎች በተሻለ ሁኔታ በዉስጡ ይዟል።.

በዓለማችን የተለያዩ ዓይነት የእንጉዳይ ዓይነቶች ያሉ ሲሆን ጥቅማቸዉም እንዲሁ የተለያየ ነዉ። ከምግብ በተጨማሪ ለመድሃኒትነትም ያገለግላል። ለምሳሌ በአይጦች ላይ የተደረገዉ ሙከራ እንደሚያሳየዉ ፒዮፒኖ የተባለዉ የእንጉዳይ ዓይነት የካንሰር በሽታን እንዳይስፋፋ ከማድረጉም በተጨማሪ የስኳር በሽታ ባለባቸዉ አይጦች ወስጥ በደማቸዉ ዉስጥ ያለዉ የስኳር መጠን ከሚፈለገዉ በላይ እንዳይጨምር ሊቆጣጠር ችሏል

የእንጉዳይ እርሻ ትንሽ ቦታ የሚጠይቅ ሲሆን ሰብሉም በማንኛዉም የአየር ንብረት ጊዜ ሊመረት ይችላል። ምክንያቱም በቤት ውስጥ ስለሚተከል ተለዋዋጭ ከሆነ የአየር ንብረት ከለላ ይኖረዋል ማለት ነዉ። ከእንጉዳይ እርሻ የሚገኘዉ ምርትም ከፍ ያለ ነዉ።  ለምሳሌ በ10 ካሬ ሜትር ላይ ካለ የእንጉዳይ እርሻ እስከ 10 ኪሎ ግራም እንጉዳይ ማምረት የሚቻል ሲሆን ከተተከለበት እስክሚታጨድበት በጠቅላላ የሚፈጀዉ ከሶስት እስከ አራት ሣምንታት ብቻ ነዉ

በኢትዮጵያም እንጉዳይን በተመለከተ የተወሰኑ ጥናቶች ተካሂደዋል። እንደ ቀርቅሃ ከመሳሳሉ ቁሳቁሶች እንጉዳይ የሚያድግበት ቤት ለመሥራት እንደሚቻል እነዚሁ ጥናቶች ያስረዳሉ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር አሻግሬ ዘዉዱ ለዶክትሬት ተምህርታቸዉ ማሟያ Laetiporus Sulphureus በሚባለዉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ለመዲሃኒትነት በሚያገለግለዉ የእንጉዳይ ዓይነት ላይ ጥናት አካሂደዋል። ቢሆንም የእንጉዳይ እርሻም ይሁን አመጋገብ በሀገራችን በሚፈለገዉ ደረጃ ያደገ አይደለም ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። ስለዚህ እንጉዳይ ከሌሎቹ የወጥ ዓይነቶች ጋር በማዕዳችን የሚሰለፍበት ጊዜ ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ምሥሉ የሚያሳየዉ በደህና ሁኒተአ ያደገ እንጉዳይ ነዉ። ምሥሉ የተገኘዉ ከዚህ ድህረ ገጽ ነዉ።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሐምሌ 5፣ 2011 ዓ.ም. (July 12, 2019)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ ባህር ዛፍ ጠቀመን ወይስ መጠመጠን?

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ባህር ዛፍ ጠቀመን ወይስ መጠመጠን?

ባህር ዛፍ የተባለዉ ዛፍ የተለያዩ ዝርያዎች ሲኖሩት መነሻቸዉም ባብዘኛዉ ከአዉስትራሊያ ነዉ። ባህር ዛፍ ከአውስትራሊያ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ የተደረገዉ በአጼ ሚኒሊክ ዘመነ መንግሥት የዛሬ 124 ዓመት እ.ኤ.አ. በ1895 ነዉ። በወቅቱ በመስፋፋት ላይ የምትገኘዉ የአዲስ አበባ ከተማ የማገዶ እንጨት እጥረት በከፍተኛ ደረጃ በማጋጠሙ ምክንያት እንደ መፍትሔ ተደርጎ የተወሰደዉ ይህንን በፍጥነት የሚያድገዉን ዛፍ ወደ ሀገር ዉስጥ እንዲገባና እንዲስፋፋ ማድረግ ነበር። በኢትዮጵያ በብዛት ተስፋፍተዉ የሚገኙት በተለምዶ ነጭ ባህር ዛፍ (Eucalyptus globules) እና ቀይ ባህር ዛፍ (Eucalyptus camaldulensis) ተብለዉ የሚጠሩት ናቸዉ።

እንደሚታወቀዉ ሁሉ በሀገራችን ባህር ዛፍ በሰፊዉ ጥቅም ላይ የዋለ ዛፍ ነዉ። እንደ አንዳንዶች ግምት በምሥራቅ አፍሪካ ካሉት ሀገራት ባህር ዛፍን በመትከል ኢትዮጵያን የሚደርስባት የለም። በሀገሪቱ ባህር ዛፍ ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬትን ሸፍኖ እንደሚገኝ ይገመታል። ይህንኑ ለመረዳት ለአዲስ አበባ ቅርብ የሆኑትን የእንጦጦ ጋራና መናገሻ አካባቢ ማየት ይቻላል። ባህር ዛፍን የምንጠቀምበት ለማገዶ፣ ለቤት ቁሳቁስ መሥሪያ፣ ለአጥር፣ ለቤት ሥራ፣ ለስልክ እና ኤሌትሪክ ማስተላለፊያ ምሰሶች፣ ለመድሃኒትነት፣ ወዘተ ነዉ። በተተከለ ባጭር ጊዜ ዉስጥ የሚያድግ ከመሆኑም ሌላ ቢቆረጥም ተመልሶ የሚያቆጠቁጥ በመሆኑ ባህር ዛፍ እጅግ ተፈላጊ ዛፍ ነዉ። በዚሁ መሠረት እንደ ባህር ዛፍ ኢትዮጵያ ዉስጥ በጥቅም ላይ የዋለ ዛፍ የለም ማለት ይቻላል።

ባህር ዛፍ ለምን ተወዳጅ ሊሆን ቻለ?

  • በአጭር ጊዜ የማደግ ችሎታዉ፤ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአማካይ በአንድ ሄከታር ላይ ያለ ባህር ዛፍ በዓመት ከ10 እስከ 20 ኪዊቢክ ሜትር እንጨት የሚሰጥ ሲሆን ከሌሎች ዛፎች ጋር ሲወዳድር ከፍ ያለ ነዉ።
  • ከተቆረጠ በኋላ ተመልሶ የሚያቆጠቁጥ በመሆኑ፣
  • ለማደግ ብዙ እንክብካቤ የማይፈልግ በመሆኑ፣
  • በተለያየ የአየር ንብረት አካባቢዎች ማደግ የሚችል በመሆኑ፣
  • የአፈር ለምነቱ በተሟጠጠበት ሥፍራ ማደግ የሚችል በመሆኑ፣
  • የውሃ እጥረት ባለበት ሥፍራ ማደግ የሚችል በመሆኑ፣
  • የእሳት አደጋን መቋቋም የሚችል በመሆኑ፣
  • ተባይንና በሽታን መቋቋም የሚችል በመሆኑ፣
  • የባህር ዛፍ አበባ ሰብሎቻንን በማዳቀል ለሚያገለግሉን በርካታ አእዋፍት እና ነፍሳት እንደምግብነት ስለሚያገለግል፣
  • ረግረገማ ወይም ዉሃ የሚያቁሩ ሥፍራዎችን ወደ ለምነት መቀየር በመቻሉ
  • የወባ አስተላላፊ ትንኞች ወይም ቢምቢዎች መራቢያ የሆኑ ረግረጋማ ሥፍራዎችን ማድረቅ በመቻሉ

ምንም እንኳ ባህር ዛፍ በሀገራችን በሰፊዉ ጥቅም ላይ የዋለ ቢሆንም በአካባቢያችን በሚያደርሰዉ ጉዳት የተነሣ በተወሰነ መጠን ብቻ እንዲተከል አንዳንዶች ይመክራሉ።

የባህር ዛፍ አሉታዊ ጎኖች ምንድን ናቸዉ?

  • በከፍተኛ ሁኔታ በአካባቢ ያለዉን ዉሃ ይመጣል፤ ስለዚህ አካባቢዉን በአጭር ጊዜ ሊያደርቅ ይችላል።
  • መሬቱን ለአፈር መሸርሸር የሚያጋልጠዉ በመሆኑ፤ ይህንን አንዳንዶች አይቀበሉትም፤ ምክንያቱም የአፈር መሸርሸርን በከፊል ሊጠብቁ የሚችሉት ከዛፉ ላይ የሚረግፉት ቅጠሎች ሲሆኑ እነዚህ ደግሞ ለማገዶነት ስለሚወሰዱ አፈሩ ለአደጋ ይጋለጣል። ስለዚህ የባህር ዛፍ ጫካ ባለበት አካባቢ የሚያጋጥመዉ የአፈር መሸርሸር ከዛፉ ባህርይ ጋር እንደማይገናኝ ይሞግታሉ።
  • የአፈር ለምነትን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ በመሆኑ፤
  • በአካባቢ ያሉ ተክሎች እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያለዉ በመሆኑ። ለምሳሌ በባህር ዛፍ አጠገብ የተዘራ የበቆሎ፣ ሽምብራ፣ አተርና ጤፍ ምርታቸዉ አነስተኛ እንደሆነ ተረጋግጧል
  • የዱር አራዊትም ሆኑ ለወፎች መጠለያ ወይም መኖሪያ ሊሆን አለመቻሉ።
ይህ በምሥሉ የሚታየዉ ባህር ዛፍ እንጦጦ በሚገኘዉ የአፄ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በኢትዮጵያ በዕድሜ ትልቁ እንደሆነ ይነገርለታል። ስለዚህ በመጀመሪያዉ ዙር ወደ ሀገር ከገቡት ዉስጥ ከሆነ ወደ 124 ዓመት ይጠገዋል ማለት ነዉ። ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ፣ ኅዳር 22፣ 2011

ባህር ዛፍ በኢትዮጵያ–አደጋ ወይስ ዕድል (Eucalyptus in Ethiopia: Risk or Opportunity?) በሚል ፕሮፌሰር መስፍን አበበና ዶክተር ዉብአለም ታደሰ እ.ኤ.አ. በ2014 ባሳተሙት መጽሐፍ ከባህር ዛፍ ጋር በተገናኘ በርካታ ነጥቦችን ዳስሰዋል። ከነዚህ ዉስጥ መጠቀስ የሚገባዉ ባህር ዛፍ ለሌሎች ተክሎች ዕድገት አዳጋች የሆኑበት ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ለማደግ መቻሉን ከዛፉ የቅጠል፣ ሥር እና ሌሎች ተዛማች ነገሮች ጋር ያገናኙታል። እንደ ምሳሌም የሚያነሱት የባህር ዛፍ ቅጠል ሰም በመሰለ ነገር የተሸፈነ በመሆኑ በቅጠሉ በኩል የሚወጣዉ የዉሃ ትነት አናሳ በመሆኑ፣ የውሃ እጥረት ሲያጋጥመዉ እንደመተንፈሻ የሚያገለግለዉንና ዉሃንም ወደ አየር የሚያስወጣዉን ስቶማታ የተባለዉን አካል ለመዝጋት መቻሉ እና ረጅም ርቀት የሚጓዙ ሥሮች ስላሉት በመሬት ዉስጥ ተደብቆ የሚገኝ ውሃ ሊደርስበት መቻሉ ናቸዉ።

በተመሣሣይ መልኩ ዳንኤል ጃለታና ባልደረቦቹ እ.ኤ.አ. በ2016 Eucalyptus Expansion as Relieving and ProvocativeTree in Ethiopia በሚል በጻፉት ጽሑፍ ለባህር ዛፍ የተሰጡት መጥፎ ስሞች በጥናት ያልተረጋገጡ ስለሆነ በአብዘኞቹ አይስማሙባቸዉም። እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱት ባህር ዛፍ የውሃና የአፈር ንጥረ ነገር አጠቃቀም እንዲሁም በአካባቢ የሚያድጉ ሰብሎችን በሚያመነጨዉ ኬሚካል ይቀናቀናል የሚባለዉ ተጨባጭነት የላቸዉም ይላሉ። እንደ ጸሐፊዎቹ አባባል ከሌሎች የዛፍ ዓይነቶች ጋር ስናወዳድርዉ ባህር ዛፍ ከአፈር የሚገኙ ንጥረ ነገሮችንና ውሃን በአግባቡ ወይም ቀልጠፍ ባለ መንገድ የሚጠቀም ነዉ። ምክንያቱም ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ በመሆኑ ነዉ።  ስለ ባህር ዛፍ ጥቅምና ጉዳት በተመለከተ በሀገራችን በርካታ ጥናቶች ተካሂደዋል። የተወሰኑት በዚሁ ጽሑፍ እንደ ዋቢ ተጠቅሰዋል።

ማጠቃለያ፤ ከላይ መጥቀስ እንደሞከርኩት እንደ ባህር ዛፍ በጥቅም ላይ ያዋልነዉ ዛፍ የለም ማለት ይቻላል። አገር-በቀል የሆኑ እንደ ጥድ፣ ዝግባ፣ ኮሶ፣ ወይራ፣ ዋንዛ፣ ወዘተ ያሉት እንደ ባህር ዛፍ ቶሎ የማያድጉ በመሆናቸዉና ከተቆረጡም በኋላ ተመልሰዉ የማደግ ዕድል ስለሌላቸዉ ባህር ዛፍ እጅግ ተመራጭ ሆኖ ቆይቷል። ወደፊትም የሚቆይ ይመስለኛል። ቢሆንም አንዳንድ የተረጋገጡ የባህር ዛፍ አሉታዊ ጎኖችንም ለህብረተሰቡ ማሳወቅ ያስፈልጋል። አማራጭ የሆኑ ዛፎችንም ማስተዋወቅ ያስፈልጋል። በአዲስ አበባ ከተማ ሥር የሚተዳደርዉ የጉለሌ የዕፅዋት ማዕከልም በባህር ዛፍ ምትክ ሀገር-በቀል ዛፎችን በመትከል ላይ እንደሚገኝ ባንድ ወቅት ሰምቼ ነበር። ቢሆንም ባህር ዛፍን የአፈር ለምነቱ በተሟጠጠበትና የውሃ እጥረት ባለበት ሥፍራዎች ቢተከል ይመከራል። ምክንያቱም ባህር ዛፍ እነዚህን እክሎች በመቋቋም ሊያድግ የሚችል በመሆኑ ነዉ። ስለዚህ ባህር ዛፍ እጅግ ጠቅሞናል። አንዳንድ የተሰጡት መጥፎ ስሞችም በጥናት መረጋገጥ አለባቸዉ። ቢሆንም በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚመጠምጠዉ ውሃችን ጉዳይም ሊታሰብ ይገባል እላለሁ።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 30፤ 2011 ዓ.ም. (July 7, 2019)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ ቫቪሎቭ ባለዉለታችን

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ቫቪሎቭ ባለዉለታችን

ኒኮላይ ቫቪሎቭ እ.ኤ.አ. ኖቨምበር 25፣ 1987 ተወልዶ በ1943 ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ የሩሲያ ሣይንቲስት ነበር። በሕይወት ዘመኑ ከሠራቸው ሥራዎች ሁሉ በዓለም የታወቀበት የሰብሎች ወይም የተክል መገኛ ሥፍራዎችን ለይቶ በማስቀመጡ ነዉ። እነዚህ የሰብል መገኛ ሥፍራዎች ስምንት ዋና ማዕከላት ሲሆኑ ከንዑስ ማዕከላት ጋር አሥር ይሆናሉ። ቫቪሎቭ ባለዉለታችን ነዉ ያልኩትም ኢትዮጵያን አንድ ዋና የሰብል መገኛ ማዕከል አድርጎ በመሰየሙ ይህንንም ለዓለም በማስተዋወቁ ነዉ። ከታች በምሥሉ እንደሚታየዉ ከዚህ ሥራዉ በተጨማሪ ቫቪሎቨ በሀገሩ በርካታ የምርምር ማዕከላትን በማቋቋም ይታወቃል።

ምሥሉ የሚያሳየዉ በተለምዶ የቫቪሎቭ የዝርያዎች ወይም የዕፅዋት መገኛ ማዕከላት ሲሆኑ እነርሱም (1) ሜክሲኮ-ጉቴማላ፣ (2) ፔሩ-ኢኳዶር-ቦሊቪያ፣ (2A) ደቡባዊ ቺሌ፣ (2B) ደቡባዊ ብራዚል፣ (3) ሜዲቴራኒያን፣ (4) መካከለኛዉ ምሥራቅ፣ (5) ኢትዮጵያ፣ (6) መካከለኛዉ ኤሲያ፣ (7) ሕንድ እና በርማ፣ (7A) ሲያም-ማላያ-ጃቫ እና (8) ቻይናና ኮሪያ ናቸዉ።

ቫቪሎቭ ወዴት ተጓዘ? ቫቪሎቭ ከላይ የተጠቀሰት ሥፍራዎች የሰብሎች መገኛ ወይም መነሻ ናቸዉ ብሎ ከመሰየሙ በፊት ለ17 ዓመታት (እ.ኤ.አ. ከ1916 እስከ 1933) በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች መጠነ-ሰፊ ጉዞ አድርጓል። በዚህ ጉዞዉ በኤሲያ፣ አፍሪካና አሜሪካ የሚገኙ 50 ሀገሮችን የጎበኘ ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸዉ የሰብል ዝርያዎችን ለመሰብሰብ ችሏል። አንዳንዶች እስከ 250 ሺህ የሚደርሱ ዝርያዎች በማሰባሰብ በሴንትስበርግ (በቀድሞ ስሟ ሌኒንግራድ) የዘር ማከማቻ እንዳስቀመጠ ይገመታሉ።

የቫቪሎቭ የኢትዮጵያ ጉዞ እንዴት ነበረ? ቫቪሎቭ እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 1926 (የዛሬ 93 ዓመት) የኢትዮጵያ (በወቅቱ ወደምትጠራበት “አብሲኒያ”) ጉዞዉን ጀመረ። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በጂቡቲ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገባ ሲሆን በጉዞዉ ያለፈባቸዉ ሥፍራዎች እንደ ቅደምተከተላቸዉ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ፍቼ፣ አዲስ አበባ፣ አንኮበር፣ ደብረ ሊባኖስ፣ ጎንደር፣ አክሱም፣ አሥመራ፣ ምጽዋ ናቸዉ። ቫቪሎቭ ጉዞዉን የጨረሰዉም ከአራት ወራት በኋላ በአፕሪል 1927 ነዉ። ቫቪሎቭ አዲስ አበባ ሲደርስ ራስ ተፈሪ በክብር ተቀብለዉታል። በፌብሪዋሪ 7፣ 1927 ቫቪሎቭ ከአዲስ አበባ ወደ አንኮበር ጉዞወን ጀመረ። በዚህ ጉዞዉም 11 አባላት ያሉት የጦር መሣሪያ የታጠቁና ጦር የያዙ ሰዎች ሲከተሉት 12 በቅሎዎችም ነበሩት። ቫቪሎቭ በኢትዮጵያ በነበረዉ ጉዞዉ በሀገሪቱ ባለዉ የብዝሀ ሕይወት ዓይነትና ብዛት እጅግ እንደተደነቀ መረጃዎች ያሳያሉ።

ኢትዮጵያ መገኛ ወይም መነሻ የተባለችዉ ለየትኞቹ ሰብሎች ነወ? ጤፍ፣ ቡና፣ ኑግ፣ ሰሊጥ፣ ዳጉሣ፣ የጉሎ ፍሬ፣ እንሰት፣ ጌሾ፣ ጫት፣ ኮሶ እና የመሳሰሉት ናቸዉ።

ቫቪሎቭ ዕድሜዉ ለምን በአጭሩ ተቀጨ? ቫቪሎቭ የሞተዉ በ55 ዓመቱ በእስር ቤት ውስጥ ነዉ። ያገኘሁት መረጃ እንደሚያሳየዉ ለእስር ያበቃዉ ምክንያት በወቅቱ የሩሲያ መሪ ለነበሩት ቅርበት ካለዉ ሣይንቲስት ጋር መግባባት ባለመቻሉ ነዉ። በዚሁ መሠረት እ.ኤ.አ. ኦግስት 6፣ 1940 ከሥልጣኑ ተነሥቶ ወደ እስር ቤት ተወረወረ። በዓመቱ ጁላይ 19፣ 1941 የሞት ቅጣት ተፈረደበት። ይሁን እንጂ በጁን 23፣ 1942 የሞት ፍርዱ ወደ 20 ዓመት ቢቀየርለትም አንድ ዓመትም ሳይቆይ በጃንዋሪ 26፣ 1943 በታሰረበት እስር ቤት ዉስጥ ከዚህ ዓለም ተሰናበተ። የሞት መንስኤዉም ረሃብ እንደሆነ ይገመታል።

ቫቪሎቭ ያከማቸዉ ዘር እንዴት ከጥቃት ሊተርፍ ተረፈ? በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወቅት ወደ ሩብ ሚሊዮን የሚጠጋዉ ዘር ከጀርመን ወታደሮች ጥቃት ለመጠበቅ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች በተራ በመጠበቅ ከጥቃት ሊያድኑ ችለዋል። ምንም እንኳ የሚጠብቁት ዘር ነፍሳቸዉን ሊታደግ እንደሚችል ቢያዉቁም ይህን ብርቅዬ ዘር አንነካም ብለዉ በነበረዉ ከፍተኛ ረሃብ ምክንያት ዘጠኝ ጠባቂዎች በረሃብ ሊሞቱ ችለዋል።

ቫቪሎቭ ከሞተ በኋላ ምን ተፈጠረ? ቫቪሎቭ ከሞተ 12 ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ. በ1955 ክሱ ተነሳለት። በማስከተልም ቀድሞ የነበሩ የቫቪሎቭ ዝናና የተረፉ ሥራዎቹን መንግሥት በኦፊሲያል አወቀ። የሶቭየት ጀግናም ተባለ። በሴንትስበርግ የሚገገኘዉና በዋናነት በቫቪሎቭ የትሰበሰበዉ ትልቁ የብዝሀ ዘር መንከባከቢያ መሥሪያ ቤት የቫቪሎቭ ኢንሲቲትዩት ተብሎ ተሠየመ።

ማጠቃለያ፤ ከላይ በጥያቄና መልስ ለማሳየት እንደሞከርኩት ቫቪሎቭ ለአለማችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን ሀገራችንንም በውጭዉ ዓለም በማስተዋወቅ ባለዉለታችን ነዉ። ምንም እንኳ የበለጠ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ በሚገኝበት ወቅት ወደ እስር ቤት ተወርዉሮ የሕይወቱ ፍጻሜ ሊሆን ቢችልምም የሀገሪቱ መሪ ሲቀየር በቫቪሎቭ የተበየነበት የዉሸት ፍርድ ተነስቶለትና የቀድሞ ዝናዉ ሊመለስለት ችሏል።

በሚቀጥለዉ በቸር ይግጠመን።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 27፤ 2011 ዓ.ም. (July 4, 2019)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ ዲጂታላይዜሽን

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ዲጂታላይዜሽን

ዲጂታላይዜሽን የሚለዉ ቃል በቅርቡ በብዙ መስኮች በጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። የሚያመለክተዉም የምናገኛቸዉን መረጃዎች በዲጂታል ወይም በኮምፒተር ወይም በተመሣሣይ ቴክኖሎጂ ሊነበቡና ጥቅም ላይ የሚዉሉበት መንገድ ማለት ነዉ። በግብርና ላይ በጥቅም ላይ የምናዉለውን የዚህን ቴክኖሎጂ ዲጂታላይዜሽን ፎር አግሪከልቸር (Digitalization for agriculture) ወይም በምህጻረ ቃል D4Ag ይባላል። ይህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ረቀቅ ባለና ዘመናዊነትን በተላበሰ መልኩ ግብናችንን እንድናዘምን ያስችለናል ማለት ነዉ። ለምሣሌ በመስኖ ዉሃ የሚታገዝ ግብርና ባለበት ሥፍራ መቼና የት አካባቢ ተጨማሪ ውሃ እንደሚያስፈልግ ማወቅ ያስችለናል። ይህንን ለምሳሌ ጠቀስኩ እንጂ ዲጂታላይዜሽን በበርካታ መስኮች ግብርናችንን ያግዛል።

በአፍሪካ ውስጥ በግብርና ዲጂታላይዜሽን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ከሚገኙት ድርጅቶች መካከል ሲ ቲ ኤ (CTA) አንዱ ነዉ። ይህ እ.ኤ.አ. በ1983 የተቋቋመዉና መቀመጫዉን በሆላንድ ሀገር በምትገኘዉ ዋገኒንገን ያደረገዉ ዓለም-አቀፍ ማዕከል በአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት እና በአዉሮፓ ህብረት መካከል የተመሠረት ሲሆን በመዋዕለ ንዋይ የሚደገፈዉም በአዉሮፓ ህብረት ነዉ። ላላፉት ዘጠኝ ዓመታት ማዕከሉን በዳይሬክትሬነት በመምራት ላይ የሚገኙት በመስኩ ከፍተኛ ልምድ ያላቸዉ ኢትዮጵያዊዉ አቶ ሚካኤል ኃይሉ ናችው። ምንም እንኳ ይህ ማዕከል አነስተኛ ቢሆንም ከእርሻ ጋር ተዛማችነት ባላቸዉ መስኮች በተለያዩ ሀገሮች መጠነ-ሰፊ ሥራ ይሠራል። ባሁኑ ጊዜ ትኩረት አድርጎ የሚሠራዉ በወጣት፣ ዲጂታላይዜሽን እና የአየር ንብረት ለዉጥ መቋቋም ላይ ነዉ። ዲጂታላይዜሽንን በተመለከተ ማዕከሉ ረቀቅ ያለ ወይም ፒሪሲሽን ግብርናን ማስተዋወቅ፣ የሳተላይት መረጃን ለዚሁ ተግባር ማዋል፣ ድሮን የተባሉ ዘመናዊ መሣሪዎችንና ሌሎች ተዛማች ያላቸዉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በመልማት ላይ ባሉ ሀገሮች ያሉ ያሉ ገበሬዎች ምርታማነትን እንዴት እንደሚያሳድጉ አስተዋጾኦ ማድረግ ናቸዉ።

በምሥሉ የሚታየዉ ድሮን ሲሆን በተለያዩ መስኮች ሥራ ላይ ይዉላል። ምሥሉ የተገኘዉ ከዚህ ድህረ-ገጽ ነዉ። https://www.geospatialworld.net/blogs/drones-revolutionizing-agriculture/

በግሌም ሲ ቲ ኤ ባለዉለታዬ ነዉ። የዛሬ 25 ዓመታት ገደማ በኢትዮጵያ እርሻ ምርምር ኢንስትቲዩት በምሠራበት ወቅት እኔና የሥራ ባልደረቦቼ ስፖር (SPORE) የተባለውን የድርጅቱ መጽሔትና ሌሎች መጽሐፍት ያለ አንዳች ክፍያ ባለንበት ድረስ ይልኩልን ነበር። እነዚህ ሕትመቶችም በምርምር ሥራዎቻችን ላይ ከፍተኛ እገዛ አድርገዉልናል። ከዚህ በተጨማሪ የዛሬ 12 ዓመት ባዘጋጀሁት ዓለም-አቀፍ ኮንፈረንስ ከአፍሪካ ሀገራት ተሳታፊ ለነበሩ በርካታ ተመራማሪዎች ወጪአቸዉን ሸፍኖልኛል። ለዚህ ሁሉ ዉለታ ማዕከሉ ምሥጋና ሊደርሰዉ ይገባል።

ወደ ተነሣሁበት ነጥቤ ስመለስ ሲ ቲ ኤ “The Digitalisation of African Agriculture Report, 2018-2019” በሚል ርዕስ 241 ገጽ ያለዉ መጽሐፍ  በቅርቡ አሳትሟል። በፒ ዲ ኤፍ መልክ ያለዉን የመጽሐፉን ሙሉ ይዘት ከላይ ካለዉ ድህረ ገጽ ማግኘት ይቻላል። ከርዕሱ መረዳት እንደሚቻለዉ መጽሐፉ በአፍሪካ አህጉር በግብርናዉ መስክ ዲጂታላዬዜሽን ያስመዘገበዉንና ወደፊትም ያለዉን ተስፋ ያሳያል። እኔም በመጽሐፉ ወስጥ ካሉት ዋና ነጥቦች ውስጥ የተወሰኑትን በአጭሩ አሳያለሁ።

በሪፖርቱ መሠረት በአሁኑ ጊዜ በአህጉሩ ያለዉ የግብርና ዲጂታላዬዜሽን የሚከተለዉን ይመስላል።

  • በዛ የሚሉ የግብርና ዲጂታላዬዜሽን ሥራዎች ያሉት በምሥራቅ አፍሪካ ሲሆን በተለይም ኬኒያ ከፍተኛ ድርሻዉን ትይዛላች።
  • የግብርና ዲጂታላዬዜሽን በመጠቀም የሰብል ምርታማነት ሊያድግ ችሏል።
  • በአጠቃቀም በኩል ቴክኖሎጂዉን ከተጠቀሙት ዉስጥ 70% ቱ ወጣቶች ናቸዉ።
  • የግብርና ዲጂታላዬዜሽን የአየር ንብረት ለዉጥን ለመቋቋም አስተአጽኦ አድርጓል።
  • ምንም እንኳ ከ40 እስከ 50% የሚጠጉ ገበሬዎች ሴቶች ቢሆኑም የግብርና ዲጂታላዬዜሽን ለመጠቀም የተመዘገቡት ግን 25% ብቻ ናቸዉ።

ከዚህ በተጨማሪ ሪፖርቱ የግብርና ዲጂታላዬዜሽንን በአፍሪካ ውስጥ ለማስፋፋት ያለዉን ተስፋና እክሎች ያሳያል። ይህንን የግብርና ዲጂታላዬዜሽን በአፍሪካ ለማስፋፋት ይረዳሉ ተብለዉ የተገመቱትን የመፍትሔ ሃሳቦችንም አቅርቧል። ከነዚህ ዉስጥ ዋናዎቹ የሰው ሥልጠና ደረጃን ማሳደግ፣ ለተከታታይነቱ የሚረዳ የቢዝነስ ሞዴል መሥራት፣ የሴቶችን ሚና መጨመር፣ ጥራት ያለዉ መረጃ ማደራጀትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መሥራት ይገኙበታል።

አዳዲስ ቴክሎሎጂዎች በተመለከተ በአፍሪካ በሥራ ላይ ከዋሉት ውስጥና በሪፖርቱ ከተገለጹት የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል።

  1. The internet of things (IoT) የሚባለዉ ግዙፍ የሆኑ መረጃዎችን በስማርት ስልክ፣ ድሮንና ሳተላይት በመጠቀም የሚሰበሰብና የሚያጠናቅር ሲሆን በኬኒያ፣ ናይጄሪያ፣ ሩዋንዳ እና በተወሰነ ደረጃም በሴኔጋል በጥቅም ላይ ዉሏል
  2. Big data፤ ግዙፍ ዳታ ወይም መረጃ የሚያጠናቅርና በተግራዊነትም ላይ የሚያተኩር ነው።
  3. Machine learning›፤ አርቲፊሻል ኢንተሊጄንስ በመጠቀም የሚሠራና ሲስተሙ ራሱን አስተምሮና አሻሽሎ እንዲቀርብ የሚያስችለዉ ሲሆን በኬኒያና በኡጋንዳ ሥራ ላይ ዉሏል።
  4. BLOCKCHAIN፤ በብዙ መስኮች ለገበሬዎች ጥቅም የሚሰጥ ሲሆን በማላዊና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጥቅም ላይ ዉሏል።

በዓለም በቴክኖሎጂ የታወቁ ድርጅቶችም የግብርና ዲጂታላዬዜሽን የፈጠራ ሥራ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ሪፖርቱ ያሳያል። በሪፖርቱ ትንበያ መሠረት በአፍሪካ የግብርና ዲጂታላዬዜሽን ተጠቃሚዎች ቁጥር አሁን ካለው 26 ሚሊዮን በሶስት ዓመታት ዉስጥ ማለትም እ.ኤ.አ. በ2022 ወደ 80 ሚሊዮን እንደሚያድግና በ2030 ወደ 200 ሚሊዮን ከፍ እንደሚል ትንበያ ይሰጣል።

ሪፖርቱ ከዚህ በተጨማሪ ስድስት የአፍሪካ ሀገሮች በግብርና ዲጂታላዬዜሽን ያሉበትን ሁኔታ በአባሪነት አቅርቧል። እነርሱም ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ሴኒጋል፣ ኬኒያና ሩዋንዳና ሲሆኑ የሳህል አካባቢ ሀገሮች ስብስብ የሆኑትም ኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ቻድ እና ሞሪታኒያ ተካተዋል። ኢትዮጵያን በተመለከተ በሪፖርቱ የተለያየ ክፍል ከተገለጸዉ በተጨማሪ ከገጽ 175 እስከ 177 በኢትዮጵያ ከግብርና ዲጂታላዬዜሽን ጋር የተገናኘ የሚከተለውን መረጃ ይሰጣል። በግብርናዉ መስክ ዲጂታላዬዜሽን እንዲተዋወቅ እየተደረገ ሲሆን ይህም እ.ኤ.አ. በ2010 በተቋቋመዉ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ ሲሆን ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በጋራ ይሠራል። በዚሁ መሠረት ለገበሬዉ የምክር አገልግሎት የሚሰጥ 80-28 የኤስ ኤም ኤስ መስመር በመክፈት እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። ይህ Ethiopia 80-28 hotline የሚባለዉ የምክር አገልግሉት አራት ሚሊዮን የተመዘገቡ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን ከአፍሪካ ትልቁ ነዉ። የተደራሽነት አድማሱንም ለማስፋት በግብርና ኢክስቴንሽን ሠራተኞች፣ በመምህራን እና በጤና ሠራተኞች በኩል ይሠራል።

በአጠቃላይ የግብርና ዲጂታላዬዜሽን ለገበሬዉ ብቻ ሳይሆን በምርምሩም፣ በንግዱም እንዲሁም በሌሎች ሴክተሮች ለሚገኘዉ ህብረተሰብ አስፈላጊ ነዉ። ከላይ እንደተጠቀሰዉ በኢትዮጵያ ለገበሬዎች የምክር አገልግሎት የሚሰጥ የኤስ ኤም ኤስ አገልግሎት በሥራ ላይ እንደዋለ ያሳያል። ዋናዉ ጥያቄ በኢትዮጵያ አገልግሎቱን ለመጠቀም የተመዘገቡ አራት ሚሊዮን ተጠቃሚዎች (ገበሬዎች) ሁሉ በአግባቡ አገልግሎቱን ያገኛሉን? የሚያገኙትስ አገልግሎትስ ምን ዓይነት መረጃዎች በዉስጡ ያካትታል? የመረጃዉ ጥራትና አስታማማኝነትስ ምን ያህል ነዉ? ከምክር አግልግሎት በተጨማሪ በኬኒያና ሌሎች ሀገራት ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችስ መቼ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ?

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 23፤ 2011 ዓ.ም. (June 30, 2019)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ ትኩረት ለሀገር-በቀሉ ጤፋችን

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ትኩረት ለሀገር-በቀሉ ጤፋችን

ሀገር-በቀል የሚለዉን ቃል የተጠቀምኩት ኢንዲጂነስ የሚለዉን የእንግሊዘኛ ቃል ለመተካት ነዉ። በዚሁ መሠረት የጤፍ መነሻ ወይም መፈጠሪያ ኢትዮጵያ መሆኗን ለማሳየት ነዉ። ከጤፍ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የቡና፣ የእንሰት፣ የኑግና የመሣሣሉትም ሰብሎችም መነሻ ሀገር ናት።

ኢትዮጵያ ለጤፍ መነሻ ሀገር ብቻ ሳትሆን ስብሉ በሰፊዉ ጥቅም ላይ የዋለባትም ሀገር ናት። ስለዚህ ጤፍ በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጄንሲ መረጃ እንደሚያሳየዉ በያመቱ 6.5 ሚሊዮን አባወራዎች ጤፍን ይዘራሉ። በኢትዮጵያ የአንድ ቤተሰብ አማካይ አምስት ሰዉ አድርግን ብንወስድ 32.5 ሚሊዮን ሰዉ በጤፍ ግብርና ይሳተፋል ማለት ነዉ። ከዚያ ደግሞ ወደ ሻጩ ከሄድን ከጅምላ ነጋዴ እስከ ቸርቻሪ ድረስ በርካታ የማህረሰቡ ሰዎች በጤፍ ንግድ ይሳተፉሉ። በተመሣሣይ መልኩ ጤፍን በመፍጨት፣ በመጋገር፣ ወዘተ የሚሳተፉትን ካሰላን ደግሞ ቁጥሩ የበለጠ ይጨምራል። የጤፍ ፍሬ ከገለባዉ ከወጣ በኋላ የሚገኘዉ ጭድ ወይም ተረፍ-ምርትም ለከብት መኖ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለዉ በመሆኑ በከብት ማደለብና ሌሎች ተዛማች መስኮች የሚሳተፉትንም መገመት ይቻላል። ለዚህ ነዉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ጤፍን ሁለቴ የምንመገበዉ። የቀጥታዉ የጤፍ ፍሬ ተፈጭቶ በሚጋገረዉ ወይም በሚሠራዉ እንጄራ፣ ገንፎ፣ ጨጨብሳ፣ ጩኮ፣ ኬክ፣ ወዘተ ሲሆን የተዘዋዋሪዉ ደግሞ የጤፍ ጭድን የተመገቡ ከብቶችን ስንመገብ ነዉ። ከሁሉ የሚገርመዉ የጤፍ ገበያ በኢትዮጵያ ውስጥ ለዋጋ ንረት እንደማሳያነት መዋሉ ነዉ። ለዚህም እንድ ማሳያነት የሚሆነዉ ስለ ገበያ ውይይት ሲኖር መጀመሪያ የሚነሳዉ የጤፍ ዋጋ ስንት እንደደረሰ በመጠያየቅ ስለሆነ ነዉ።

በኢትዮጵያ ሰብሎቻችን የሚዘሩበትን የመሬት ስፋት ከወሰድን ጤፍን የሚወዳደረዉ የለም። በያመቱ ወደ ሶስት ሚሊዮን በሚጠጋ መሬት ላይ ይዘራልና ነዉ። ከዚህ በታች በምሥል 1 (በስተግራ) እንደሚታየዉ ከሌሎች የብርዕና አገዳ ሰብሎች ጋር ስናወዳድረዉ ጤፍ 29% የመሬት ድርሻ ሲይዝ፣ በቆሎ 21% እና ማሽላ 19% ይዘዉ ይከተላሉ። ነገር ግን ከእያንዳንዱ ሰብል የሚመረተዉን አጠቃላይ ምርት ከወሰድን ጤፍ በአንደኛ ደረጃ አይገኝም (ምሥል 1 በስተቀኝ)። ቦታዉን ለበቆሎ መልቀቅ ስለሚገደድ። ለዚህም ዋና ምክንያቱ የጤፍ ምርታማነት አነስተኛ በመሆኑ ነዉ።

ምሥል 1. ከብርዕና አገዳ ሰብሎች ጋር ሲወዳደር እያንዳንዱ ሰብል በሀገር ደረጃ የነበረዉ የመሬት ድርሻ (በስተግራ) እና የምርት ድርሻ (በስተቀኝ)። መረጃዉም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር የ2007 ዓ.ም. ሲሆን የተገኘዉም ከማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጄንሲ ነዉ። ለዚህ ጽሑፌ እንዲያመቸኝ ወደ ምሥሎቹ ቀይሬአለሁ።

በዚሁ ዝቅተኛ የጤፍ ምርታማነት ምክንያት የጤፍ ማሣዎች በሌሎች ከፍተኛ ምርታማነት ባላቸዉ ሰብሎች እንዲተኩ ጥረት ተደርጎ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። እዚህ ላይ “አጥፍቶ መጥፋት” በሚል ርዕስ ሙሉጌታ በሚባሉ ጸሐፊ የዛሬ 25 ዓመት የታተመ 292 ገጽ ያለዉ መጽሐፍን መጥቀስ ይቻላል። ምንም እንኳ በአሁኑ ጊዜ ይህ መጽሐፍ በእጄ ባይኖርም ከረጅም ጊዜ በፊት ባነበብኩበት ወቅት በገጽ 152 የተጻፈዉን ማስታሻዬ ላይ ጽፌ ነበር። የመጽሐፉ ደራሲ በዚህ ገጽ የሚተርከዉ ፕሬዘዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ለጉብኝት ወደ አርሲ ከፍለ ሀገር በሄዱብት ወቅት አጠገባቸዉ ከነበሩት ባለሥልጣን ጋር የተነጋገሩትን ነዉ። ፕሬዘዳንት መንግሥቱ ለባለሥልጣኑ እንዲህ ይሉታል “ጤፍ ዋጋ የሌለዉ ሰብል ስለሆነ በሶስት ዓመት ወስጥ በሌላ ሰብል መተካት አለብን”። ባለሥልጣኑም ”ጓድ መንግሥቱ እኔ ያለ ጤፍ አይሆንልኝም” ይላቸዋል። ፕሬዘዳንት መንግሥቱም መልሰዉ “እኔም ውሸቴን ነዉ እንጂ ያለ ጤፍ አይሆንልኝም” አሉ ይላል። መጽሐፉ ባሁኑ ጊዜ አጠገቤ ስለሌለ ከላይ ያሰፈርኩት በትክክል በመጽሀፉ ውስጥ እንደ ተገለጸዉ ለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም።

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ፕሬዘዳንት መንግሥቱ ከባለሥልጣኑ ጋር ባደረጉት ንግግር ብቻ ሳይወሰኑ በፖሊሲ ደረጃም ጤፍ የምርት መጠኑ ዝቅተኛ ስለሆነ በሌሎች ምርታማ በሆኑ ሰብሎች መተካት እንዳለበትና ይህንኑ ለማስፈጸም ሙከራ ተደርጎ እንደነበረ ነዉ። ነገር ግን ይህ ሊሳካ አልቻለም። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ ልክ እንደ ባለሥልጣኑና እንደ ፕሬዘዳንት መንግሥቱ ያለ ጤፍ ስለማይሆንለት ነዉ። ምንም እንኳ በርካታ ምክንያቶች ሊዘረዘሩ ቢቻልም ገበሬዉ ጤፍን የሚዘራዉ በሁለት ዋና ምክንያቶች ይመስለኛል። የመጀመሪያዉ ከሌላዉ ሰብል በተሻለ ሁኔታ ጤፍ ገበያም ሆነ ተፈላጊ ስላለዉ ነዉ። ምክንያቱም ከማዕዳችን የማይለየዉ ጥራት ያለዉ እንጄራ የሚጋገረዉ ከጤፍ ስለሆነ ነዉ። ስለዚህ የዋጋ ንረት ቢኖርም ጤፍ ገዢ እንደማያጣ ገበሬዉ ጠንቅቆ ስለሚረዳ ነዉ። ሁለተኛዉ ምክንያት ደግሞ ከሌሎች ሰብሎች በተሻለ ደረጃ ጤፍ ለበርካታ የምርት እንቅፋቶች በቀላሉ እጁን ስለማይሰጥ ነዉ። ይህም ማለት ጤፍ ዝናም በሚያጥርበትም ሆነ በሚበዛበት ሥፍራ ከነ ስንዴና በቆሎ በተሻለ ሁኔታ የሚከሰተውን ነባራዊ ሁኔታ በመቋቋም ሊያድግና ምርት ሊሰጥ ስለሚችል ነዉ። በተለይም የሀገሪቱን 10% የሚሸፍነዉ የኮትቻ ወይም መረሬ መሬት ላይ ዝናም ሲበዛ የሚከሰትዉን የዉሃ ማቆር ተቋቁሞ የሚያድግ ሰብል ከጤፍና ሩዝ ዉጭ ማግኘት አዳጋች ስለሆነ ነው።

የኮትቻ መሬት ከተነሣ የዛሬ 25 ዓመታት ገደማ የሆለታ እርሻ ምርምር ማዕከል ተመድቤ በምሠራበት ወቅት የጊንጪን ኮትቻ መሬት አልረሳውም። ለጤፍ ምርምራችን በጊንጪ የሚገኘዉን ንዑስ ማዕከል እንደ መስክ የሙከራ ጣቢያ እንጠቀምበት ነበር። መሬቱ በደህና ሁኔታ ሳይርስ ጤፍ መዝራት ስለማንችል ጤፍን የምንዘራዉ ከሌሎቹ ሰብሎች ዘግየት ብለን ነበር። በዚህን ወቅት መሬቱ መራስ ብቻ ሳይሆን እጅግ ስለሚያጣብቅ በማሣችን ውስጥ የሙከራችንን ፕላን በአግባቡ ለማዉጣትና ለመዝራትም እንቸገር ነበር። ይህ እንደ ማስቲሽ የሚያጣብቅ ማሣ የቦት ጫማችንን ጥለን በባዶ እግራችን ጭቃውን እንድናቦካ ያስገድደን ነበር። እንደ ጊንጪ ዓይነት ጠንከር ያለ የኮትቻ አፈር ያየሁት በ1977 ድርቅ ምክንያት ለሠፈራ ለሚሄዱ ወገኖቻችን መጠለያ ለመሥራት ጊሎ አቦል በሚባል ጋምቤላ ወስጥ በሚገኝ ሥፍራ በዘመትን ጊዜ ነወ። ደግነቱ በጊሎ አቦል እንሠራ የነበረው መጠለያ እንጂ ከእርሻ ጋር የተገናኘ ስላልሆነ እንደ ጊንጪዉ ዓይነት ፈተና አላጋጠመንም ነበር። የጋምቤላዉ ዘመቻ የራሱ የሆኑ ተዳርጎቶች ነበሩት። ከእርሻ ጋር የተገናኝ ስላልሆነ አሁን አላነሳዉም።

ጤፍን በተመለከተ ምንም እንኳ ጫና ቢደረግበትም እንደተፈለገዉ የጤፍ መሬት እየቀነሰ ሳይሆን እየጨመረ ነዉ የመጣዉ። በምሥል 2 እንደሚታየዉ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1989 ዓ.ም. 1.84 ሚሊዮን ሄክታር የሚሸፍነዉ የጤፍ እርሻ በ2007 ወደ 2.87 ሚሊዮን ሄክታር ሊያድግ ችሏል። ይህ የ56% ዕድገት በሁለት አሥርት ዓመታት ዉስጥ ከፍተኛ ይመስለኛል።

የዓለም አቀፉ ማህረሰብ ጤፍንና አንዳንድ በመልማት ሀገር ያሉ ሰብሎችን “ወላጅ-አልባ ሰብሎች” ወይም በእንግሊዘኛዉ “ኦርፋን ክሮፕስ” ብለዉ ይጠሯቸዋል። ይህ “ወላጅ-አልባ” የሚለዉ ቃል ትክክለኛ ሥያሜ ባይሆንም የሚያመለክትዉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት አልተሰጠዉም ለማለት ነዉ። እነዚህ ወላጅ-አልባ የሚባሉት ሰብሎች ባብዘኛዉ በድሀ ሀገሮች እጅግ ጠቃሚና ተፈላጊ የሆኑ ሰብሎች ሲሆኑ በሰለጠኑት ሀገራት ግን ተጠቃሚነታቸዉ አነስተኛ ነዉ። በዚሁ መሠረት በምርምርም ሆነ በሌላ መስክ እነዚህ ሰብሎች ወደ ኋላ የቀሩ ናቸዉ። ሆኖም ባለፉት ሰላሳ እና አርባ ዓመታት በተለያየ የዓለማችን ክፍሎች የተቋቋሙ ዓለም-አቀፍ የምርምር ማዕከላት በተለምዶ ወላጅ-አልባ ተብለዉ ከሚታወቁት ውስጥ በተወሰኑት ላይ የምርምርና የልማት ሥራ በማስፋፋት ከፍተኛ ዉጤት ሊያገኙባቸዉ ችለዋል። ነገር ግን አንድም የዚህ ዓለም-አቀፍ የምርምር አካል ለጤፍ ትኩረት አድርጎ ሊሠራ አልቻለም። በዚህ የተነሣ ነዉ አንዳንዶቻችን ጤፍን “ትክክለኛዉ ወላጅ-አልባ” ብለን የምንጠራዉ። ምክንያቱም አንዳንድ “ወላጅ-አልባ” ሰብሎች ጉዲፈቻ ሲያገኙ ጤፍ ግን የሚያየዉ አልተገኘምና ነዉ።

በሀገራችንም ከሌሎቹ ሰብሎች ጋር ስናወዳድረዉ በቀድሞ ጊዜ የጤፍ ምርምር በቂ አቅርቦት አልነበረውም። ለዚህ እኔ ራሴ ምስክር ነኝ። በሆለታ እርሻ ምርምር የጤፍ ተመራማሪ በነበርኩበት ወቅት የምርምር ክፍላችን ምንም ዓይነት ተሽከርካሪ አልነበረዉም። ቢሆንም በሆለታ ማዕከል ከምንሠራዉ በተጨማሪ በርካታ የመስክ ሥራዎች በጊንጪ፣ ደንቢና ሌሎች ሥፍራዎችም ነበሩን። ታዲያ ምንም ተሽከርካሪ ሳይኖረን አርባና ሰማንያ ኪሎ ሜትር ድረስ በመጓዝ የምርምር ሥራዎችንን በታቀደዉ መሠረት ለማከናወን አዳጋች ይሆንብን ነበር። በወቅቱ ተሽከርካሪ የነበራቸው የምርምር ክፍሎች ትብብር ባይደረጉልን ኖሮ ምርምሮቻችንን ዳዋ በልቷቸዉ ይቀሩ ነበር፤ ማለቴ አረም ውጧቸዉ ለማለት ነዉ።

ምሥል 2. እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1989 እስከ 2007 በያመቱ ለጤፍ እርሻ የዋለ መሬት (በሚሊዮን ሄክታር)። መረጃዉ የተገኘዉም ከማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጄንሲ ሲሆን ለዚህ ጽሑፌ እንዲያመቸኝ ወደ ምሥል ቀይሬአለሁ።

ስለ ጤፍ በዚህ ብቻ አላበቃም። ወደፊት በርካታ የምጽፍባቸዉ ነጥቦች አሉ። በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 21፤ 2011 ዓ.ም. (June 28, 2019)