ግብርናችንን ለማዘመን፤ ባህር ዛፍ ጠቀመን ወይስ መጠመጠን?

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ባህር ዛፍ ጠቀመን ወይስ መጠመጠን?

ባህር ዛፍ የተባለዉ ዛፍ የተለያዩ ዝርያዎች ሲኖሩት መነሻቸዉም ባብዘኛዉ ከአዉስትራሊያ ነዉ። ባህር ዛፍ ከአውስትራሊያ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ የተደረገዉ በአጼ ሚኒሊክ ዘመነ መንግሥት የዛሬ 124 ዓመት እ.ኤ.አ. በ1895 ነዉ። በወቅቱ በመስፋፋት ላይ የምትገኘዉ የአዲስ አበባ ከተማ የማገዶ እንጨት እጥረት በከፍተኛ ደረጃ በማጋጠሙ ምክንያት እንደ መፍትሔ ተደርጎ የተወሰደዉ ይህንን በፍጥነት የሚያድገዉን ዛፍ ወደ ሀገር ዉስጥ እንዲገባና እንዲስፋፋ ማድረግ ነበር። በኢትዮጵያ በብዛት ተስፋፍተዉ የሚገኙት በተለምዶ ነጭ ባህር ዛፍ (Eucalyptus globules) እና ቀይ ባህር ዛፍ (Eucalyptus camaldulensis) ተብለዉ የሚጠሩት ናቸዉ።

እንደሚታወቀዉ ሁሉ በሀገራችን ባህር ዛፍ በሰፊዉ ጥቅም ላይ የዋለ ዛፍ ነዉ። እንደ አንዳንዶች ግምት በምሥራቅ አፍሪካ ካሉት ሀገራት ባህር ዛፍን በመትከል ኢትዮጵያን የሚደርስባት የለም። በሀገሪቱ ባህር ዛፍ ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬትን ሸፍኖ እንደሚገኝ ይገመታል። ይህንኑ ለመረዳት ለአዲስ አበባ ቅርብ የሆኑትን የእንጦጦ ጋራና መናገሻ አካባቢ ማየት ይቻላል። ባህር ዛፍን የምንጠቀምበት ለማገዶ፣ ለቤት ቁሳቁስ መሥሪያ፣ ለአጥር፣ ለቤት ሥራ፣ ለስልክ እና ኤሌትሪክ ማስተላለፊያ ምሰሶች፣ ለመድሃኒትነት፣ ወዘተ ነዉ። በተተከለ ባጭር ጊዜ ዉስጥ የሚያድግ ከመሆኑም ሌላ ቢቆረጥም ተመልሶ የሚያቆጠቁጥ በመሆኑ ባህር ዛፍ እጅግ ተፈላጊ ዛፍ ነዉ። በዚሁ መሠረት እንደ ባህር ዛፍ ኢትዮጵያ ዉስጥ በጥቅም ላይ የዋለ ዛፍ የለም ማለት ይቻላል።

ባህር ዛፍ ለምን ተወዳጅ ሊሆን ቻለ?

  • በአጭር ጊዜ የማደግ ችሎታዉ፤ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአማካይ በአንድ ሄከታር ላይ ያለ ባህር ዛፍ በዓመት ከ10 እስከ 20 ኪዊቢክ ሜትር እንጨት የሚሰጥ ሲሆን ከሌሎች ዛፎች ጋር ሲወዳድር ከፍ ያለ ነዉ።
  • ከተቆረጠ በኋላ ተመልሶ የሚያቆጠቁጥ በመሆኑ፣
  • ለማደግ ብዙ እንክብካቤ የማይፈልግ በመሆኑ፣
  • በተለያየ የአየር ንብረት አካባቢዎች ማደግ የሚችል በመሆኑ፣
  • የአፈር ለምነቱ በተሟጠጠበት ሥፍራ ማደግ የሚችል በመሆኑ፣
  • የውሃ እጥረት ባለበት ሥፍራ ማደግ የሚችል በመሆኑ፣
  • የእሳት አደጋን መቋቋም የሚችል በመሆኑ፣
  • ተባይንና በሽታን መቋቋም የሚችል በመሆኑ፣
  • የባህር ዛፍ አበባ ሰብሎቻንን በማዳቀል ለሚያገለግሉን በርካታ አእዋፍት እና ነፍሳት እንደምግብነት ስለሚያገለግል፣
  • ረግረገማ ወይም ዉሃ የሚያቁሩ ሥፍራዎችን ወደ ለምነት መቀየር በመቻሉ
  • የወባ አስተላላፊ ትንኞች ወይም ቢምቢዎች መራቢያ የሆኑ ረግረጋማ ሥፍራዎችን ማድረቅ በመቻሉ

ምንም እንኳ ባህር ዛፍ በሀገራችን በሰፊዉ ጥቅም ላይ የዋለ ቢሆንም በአካባቢያችን በሚያደርሰዉ ጉዳት የተነሣ በተወሰነ መጠን ብቻ እንዲተከል አንዳንዶች ይመክራሉ።

የባህር ዛፍ አሉታዊ ጎኖች ምንድን ናቸዉ?

  • በከፍተኛ ሁኔታ በአካባቢ ያለዉን ዉሃ ይመጣል፤ ስለዚህ አካባቢዉን በአጭር ጊዜ ሊያደርቅ ይችላል።
  • መሬቱን ለአፈር መሸርሸር የሚያጋልጠዉ በመሆኑ፤ ይህንን አንዳንዶች አይቀበሉትም፤ ምክንያቱም የአፈር መሸርሸርን በከፊል ሊጠብቁ የሚችሉት ከዛፉ ላይ የሚረግፉት ቅጠሎች ሲሆኑ እነዚህ ደግሞ ለማገዶነት ስለሚወሰዱ አፈሩ ለአደጋ ይጋለጣል። ስለዚህ የባህር ዛፍ ጫካ ባለበት አካባቢ የሚያጋጥመዉ የአፈር መሸርሸር ከዛፉ ባህርይ ጋር እንደማይገናኝ ይሞግታሉ።
  • የአፈር ለምነትን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ በመሆኑ፤
  • በአካባቢ ያሉ ተክሎች እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያለዉ በመሆኑ። ለምሳሌ በባህር ዛፍ አጠገብ የተዘራ የበቆሎ፣ ሽምብራ፣ አተርና ጤፍ ምርታቸዉ አነስተኛ እንደሆነ ተረጋግጧል
  • የዱር አራዊትም ሆኑ ለወፎች መጠለያ ወይም መኖሪያ ሊሆን አለመቻሉ።
ይህ በምሥሉ የሚታየዉ ባህር ዛፍ እንጦጦ በሚገኘዉ የአፄ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በኢትዮጵያ በዕድሜ ትልቁ እንደሆነ ይነገርለታል። ስለዚህ በመጀመሪያዉ ዙር ወደ ሀገር ከገቡት ዉስጥ ከሆነ ወደ 124 ዓመት ይጠገዋል ማለት ነዉ። ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ፣ ኅዳር 22፣ 2011

ባህር ዛፍ በኢትዮጵያ–አደጋ ወይስ ዕድል (Eucalyptus in Ethiopia: Risk or Opportunity?) በሚል ፕሮፌሰር መስፍን አበበና ዶክተር ዉብአለም ታደሰ እ.ኤ.አ. በ2014 ባሳተሙት መጽሐፍ ከባህር ዛፍ ጋር በተገናኘ በርካታ ነጥቦችን ዳስሰዋል። ከነዚህ ዉስጥ መጠቀስ የሚገባዉ ባህር ዛፍ ለሌሎች ተክሎች ዕድገት አዳጋች የሆኑበት ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ለማደግ መቻሉን ከዛፉ የቅጠል፣ ሥር እና ሌሎች ተዛማች ነገሮች ጋር ያገናኙታል። እንደ ምሳሌም የሚያነሱት የባህር ዛፍ ቅጠል ሰም በመሰለ ነገር የተሸፈነ በመሆኑ በቅጠሉ በኩል የሚወጣዉ የዉሃ ትነት አናሳ በመሆኑ፣ የውሃ እጥረት ሲያጋጥመዉ እንደመተንፈሻ የሚያገለግለዉንና ዉሃንም ወደ አየር የሚያስወጣዉን ስቶማታ የተባለዉን አካል ለመዝጋት መቻሉ እና ረጅም ርቀት የሚጓዙ ሥሮች ስላሉት በመሬት ዉስጥ ተደብቆ የሚገኝ ውሃ ሊደርስበት መቻሉ ናቸዉ።

በተመሣሣይ መልኩ ዳንኤል ጃለታና ባልደረቦቹ እ.ኤ.አ. በ2016 Eucalyptus Expansion as Relieving and ProvocativeTree in Ethiopia በሚል በጻፉት ጽሑፍ ለባህር ዛፍ የተሰጡት መጥፎ ስሞች በጥናት ያልተረጋገጡ ስለሆነ በአብዘኞቹ አይስማሙባቸዉም። እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱት ባህር ዛፍ የውሃና የአፈር ንጥረ ነገር አጠቃቀም እንዲሁም በአካባቢ የሚያድጉ ሰብሎችን በሚያመነጨዉ ኬሚካል ይቀናቀናል የሚባለዉ ተጨባጭነት የላቸዉም ይላሉ። እንደ ጸሐፊዎቹ አባባል ከሌሎች የዛፍ ዓይነቶች ጋር ስናወዳድርዉ ባህር ዛፍ ከአፈር የሚገኙ ንጥረ ነገሮችንና ውሃን በአግባቡ ወይም ቀልጠፍ ባለ መንገድ የሚጠቀም ነዉ። ምክንያቱም ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ በመሆኑ ነዉ።  ስለ ባህር ዛፍ ጥቅምና ጉዳት በተመለከተ በሀገራችን በርካታ ጥናቶች ተካሂደዋል። የተወሰኑት በዚሁ ጽሑፍ እንደ ዋቢ ተጠቅሰዋል።

ማጠቃለያ፤ ከላይ መጥቀስ እንደሞከርኩት እንደ ባህር ዛፍ በጥቅም ላይ ያዋልነዉ ዛፍ የለም ማለት ይቻላል። አገር-በቀል የሆኑ እንደ ጥድ፣ ዝግባ፣ ኮሶ፣ ወይራ፣ ዋንዛ፣ ወዘተ ያሉት እንደ ባህር ዛፍ ቶሎ የማያድጉ በመሆናቸዉና ከተቆረጡም በኋላ ተመልሰዉ የማደግ ዕድል ስለሌላቸዉ ባህር ዛፍ እጅግ ተመራጭ ሆኖ ቆይቷል። ወደፊትም የሚቆይ ይመስለኛል። ቢሆንም አንዳንድ የተረጋገጡ የባህር ዛፍ አሉታዊ ጎኖችንም ለህብረተሰቡ ማሳወቅ ያስፈልጋል። አማራጭ የሆኑ ዛፎችንም ማስተዋወቅ ያስፈልጋል። በአዲስ አበባ ከተማ ሥር የሚተዳደርዉ የጉለሌ የዕፅዋት ማዕከልም በባህር ዛፍ ምትክ ሀገር-በቀል ዛፎችን በመትከል ላይ እንደሚገኝ ባንድ ወቅት ሰምቼ ነበር። ቢሆንም ባህር ዛፍን የአፈር ለምነቱ በተሟጠጠበትና የውሃ እጥረት ባለበት ሥፍራዎች ቢተከል ይመከራል። ምክንያቱም ባህር ዛፍ እነዚህን እክሎች በመቋቋም ሊያድግ የሚችል በመሆኑ ነዉ። ስለዚህ ባህር ዛፍ እጅግ ጠቅሞናል። አንዳንድ የተሰጡት መጥፎ ስሞችም በጥናት መረጋገጥ አለባቸዉ። ቢሆንም በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚመጠምጠዉ ውሃችን ጉዳይም ሊታሰብ ይገባል እላለሁ።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 30፤ 2011 ዓ.ም. (July 7, 2019)

አስተያየት ያስቀምጡ