ግብርናችንን ለማዘመን፤ የጤፉ ጠቢብ፣ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ፤ ክፍል 3

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሑፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡

የጤፉ ጠቢብ፣ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ፤ ክፍል 3

በዛሬዉ ክፍል 3 ጽሑፌ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ የሀገራችን ግብርናን በተመለከተ ላደረኩላቸዉ ቃለ መጠይቅ የሰጡኝን መልስ አስነብባችኋለሁ።

ጥያቄ፤በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብል ሣይንስ ባለሙያዎች ማህበር የዕድሜ ልክ የስኬት ሽልማት  (Life Time Achievement Award) ሰጥቶታል፡፡ ይህ ከፍተኛ ሽልማት ለምን እንደተሰጥትዎት ሊነግሩኝ ይችላሉ?

ዶክተር ክበበዉ፤ ይህ የዕድሜ ልክ የስኬት ሽልማት (Life Time Achievement Award) በኢትዮጵያ ሰብል ሣይንስ ባለሙያዎች ማህበር እ አ አ በፌብሪዋሪ 24 ቀን 2023 የተሰጠኝ በሰብል ምርምርና ልማት እንዲሁም ለሰብል ሣይንስ ባለሙያዎች ማህበር ላበረከትኩት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ነው፡፡

ምስሉ የሚያሳየዉ የዕድሜ ልክ የስኬት ሽልማት ለዶክተር ክበበዉ አሰፋ (በግራ ያሉት) በዶክተር ድሪባ ገለቴ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክቴር ር ሲበረክትላቸዉ ነዉ፡፡ ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ፣ እ አ አ ፌብሪዋሪ 24 ቀን 2023

ጥያቄ፤ የብሔራዊ የጤፍ ምርምርን በማስተባበር እያሉ ለሶስት ዓመታት በሽምብራ ምርምር ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ፕሮጀክትን ሲያስተባብሩ ነበር፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? በአንድ ጊዜ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ማስተባበር አይከብድም?

ዶክተር ክበበዉ፤ በጊዜዉ ቲ ኤል-ሁለት (TLII) በተባለው ፕሮጄክት በተለይም በሽምብራው ክፍል ኢትዮጵያን አስመልክቶ በዋና ተመራማሪነት ወይም አስተባባሪነት (Principal Investigator) ሆኜ ተመድቤ አገልግያለሁ፡፡ ይህ ፕሮጄከት በICRISAT በኩል በቢል እና ሜሊንዳ ጌትሰ ፋውንዴሽን (BGMF) የሚደገፍ ነበር፡፡ የተለያዩ ፕሮጄክቶችን ማሰተባበርና መምራት ምንም እንኳን ከፍተኛ ሃላፊነት ያለበትና ጥረት የሚጠይቅና ጫና የሚያሳድር ቢሆንም በጣም ካልበዙ በስተቀር ከባድ አይሆንም፡፡ የምርምር ፕሮጄክቶቹ ሥራዎች የጤፉም ሆነ የሽምብራው የሚሰሩት በየክፍሎቹ ስለነበር የእኔ ሃላፊነት ማስተባበር ስለነበረ እምብዛም አስቸጋሪ አልነበረም፡፡

ምስሉ የሚያሳየዉ የዕድሜ ልክ የስኬት ሠርቲፊኬት ለዶክተር ክበበዉ አሰፋ ሲበረክትላቸዉ ነዉ፡፡ ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ፣ እ አ አ ፌብሪዋሪ 24 ቀን 2023

ጥያቄ፤ በዩኒቨርቲዎች ዉስጥ በማስተማርና የማስተርና የፒ ኤች ዲ ተማሪዎችን እያማከሩ እንደነበረም ይታወቃል፡፡ እስካሁን ድረስ የስንት ተማሪዎችን ቴሲስ ሱፐርቫይዘር እንዳደረጉ ሊነግሩኝ ይችላሉ?

ዶክተር ክበበዉ፤ ለፒ ኤች ዲ (PhD) ለ12 በአብዛኛው በሀገር ውስጥና ጥቂቶች ደግሞ በውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች የድህረ-ምረቃ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ተማሪዎች አማካሪ ሆኜ አግልግያለሁ ወይም በማገልገል ላይ እገኛለሁ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ግማሹ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን የተቀሩት ስድስቱ ግን አሁንም በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ በኤም ኤስ ሲ (MSc) ከ24 በላይ ለሚሆኑ በተለያዩ ሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች (በተለይም ሀረማያ፣ ሀዋሳ፣ አዲስ አበባና ጂማ ዩኒቨርሲቲዎች) የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ተማሪዎች በምርምር አማካሪነት አገለግያለሁ፡፡

ጥያቄ፤ እነዚህ ያማከሯቸዉ ተማሪዎች ሁሉም ምርምራችውን የሠሩት በጤፍ ላይ ነዉ ወይስ ሌሎች ሰብሎችንም ያካትታል?

ዶክተር ክበበዉ፤ ብዙዎቹ በጤፍ ላይ ነው ምርምራቸውን የሰሩት ወይም የሚሰሩት፡፡ ሆኖም በሌሎች ሰብሎች ላይ ለምሳሌ ከኢትዮጵያ በተሰበሰቡ ጥቁር አዝሙድ እና አንጮቴ እንዲሁም በስንዴና በሌሎችም ሰብሎች ላይ የሰሩና እየሰሩም ያሉ ይገኙባቸዋል፡፡

ጥያቄ፤ እስከ ሁለት ሳምንት የሚቆይ አጫጭር ሥልጠናዎችንም በተለያዩ ጊዜያት ለገበሬዎች፣ ለቴክኒሻኖች እና ለጀማሪ ተመራማሪዎች ይሰጡ እንደነበረ አውቃለሁ፡፡ ላለፉት 40 ዓመታት በግምት ስንት ሰልጣኞችን አሰልጥኛለሁ ይላሉ?

ዶክተር ክበበዉ፤ በነዚህ በርካታ ዓመታት በሰጠኋቸው ሥልጠናዎች ላይ የተሳተፉትን ሠልጣኞች ቁጥር መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡  እንዲሁ በግርድፍ ግምት ስሌት ግን ከ450 ሺህ እስከ 500 ሺህ ያህል ይሆናሉ ማለት ይቻላል፡፡

ጥያቄ፤ የጤፍን እና የሌሎች ዓለም አቀፍ ትኩረት የተነፈጋቸዉ ሰብሎች (orphan crops) ምርምር እንዴት ማሳደግ እንችላለን ይላሉ?

ዶክተር ክበበው፤ በአጠቃላይ ጤፍን እና የሌሎች ዓለም አቀፍ ትኩረት የተነፈጋቸዉ ሰብሎች (orphan crops) ላይ ምርምር መሥራት አያሌ አስቸጋሪ ጉዳዮች አሉት፡፡ ከነዚህም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ 1ኛ) በእንደዚህ አይነት ሰብሎች ላይ የመሠረታዊ ዕውቀት ውሱንነት ስላለ ምርምር ለመስራት በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ 2ኛ) በእነዚህ አይነት ሰብሎች ላይ ለሚሰራ ተመራማሪ ከሌሎች በዓለም ላይ ታዋቂ ሰብሎች ላይ ከሚሰሩ ሳይንቲስቶች የተነጠለና ብዙ ሳይንሳዊ መድረኮች ላይ ተሳትፎው የተገደበ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ 3ኛ) በእነዚህ ሰብሎች ላይ ለሚሰራ ምርምር ከውጭ አለም አቀፍ የምርምር ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች የማቴሪያልና የገንዝብ እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፎችን ማግኘት በእጅጉ የተገደበ ይሆናል፡፡ 4ኛ) የምርምር ውጤቶችን በአለም አቀፍ ታዋቂ በሆኑ መድረኮች ለማቅረብና ፅሁፎችንም በጆርናሎች ለይ ለማሳተም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ 5ኛ) ከሁሉም በላይ ደግሞ በሀገር ውስጥ ራሱ በእንደዚህ አይነት ሰብሎች ላይ ለሚደረገው ምርምር የሚሰጠው ትኩረትና ድጋፍ አብዛኛውን ጊዜ እጅግ ዝቅተኛ ሲሆን ለዚህም በሀገራችን ኢትዮጵያ ጤፍን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ምንም እንኳን እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ቢኖሩም በጤፍና እና የሌሎች ዓለም አቀፍ ትኩረት የተነፈጋቸዉ ሰብሎች (orphan crops) ምርምር ለማሳደግ ቁርጠኝነት በመጀመረያ ደረጃ የሚያስፈልግ ሲሆን ትልቁ ጉዳይ ግን በእነዚህ ችግሮችም ውስጥ ቢሆን ሰርቶ ውጤት ማምጣትና የምርምሩን አስፈላጊነት በተጨባጭ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሳይንስ ተመጋጋቢ ስለሆነ በሌሎች በዓለም ላይ ታዋቂ በሆኑስውሰብሎች ላይ በምርምር የተገኙትን ዕውቀቶችና ውጤቶች መውሰድና ለእነዚህ ታዋቂ ላልሆኑ ሰብሎች እንዲውሉ ማድረግና መጠቀም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ሌላው ጉዳይ በጊዜ ሂደት እነዚህ በዓለም ላይ ትኩረት የተነፈጋቸው ሰብሎች እጅግ ተፈላጊ የሚሆኑበት ሁኔታ ይከሰታል፡፡ ለዚህም በአሁኑ ጊዜ ጤፍ በዓለም ላይ በተለይም እንደ የጤና እና የብቃት ሰብል (health and performance food) እጅግ ተፈላጊ ሆኖ መምጣቱን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ጥያቄ፤ እኔ በግሌ በሀገራችን ያሉ ሁሉንም መልክአ ምድሮችን በተለይም በሰብል ወቅት ማየት ቢያስደስተኝም ከሁሉም በላይ በየዓመቱ መጎብኘት የምወደዉ (my favorite) ከዚህ በታች ያለዉ በምንጃር የሚገኘዉ መልክአ ምድር ነዉ፡፡ ምክንያቱም በዚህ መልክአ ምድር ባንድ ጊዜ በተለያዩ ደረጃ ያሉ ሰብሎችን ማየት የሚቻል ከመሆኑም በተጨማሪ በየማሳዎቹ ዳር እና ዳር ለተለያየ አገልግሎት የሚዉሉ ዛፎችም ይታያሉ፡፡ ለመሆኑ እርስዎ በየጊዜዉ ለማየት የሚወዱትን (your favorite) ሥፍራ ሊገልጹልኝ ይችላሉ?

ዶክተር ክበበዉ፤አንደኛው ይኸው አንተ የጠቀስከው ቦታ በተለይም ወደ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ዋና ከተማ አሬሪቲ ስትሄድ ሣማ ሰንበትን ወረድ ስትል ከአስፋልት መንገዱ ግራና ቀኝ የምታያቸው ረባዳ ቦታዎች ናቸው፡፡ የሚያሰደስተኝም የሰብል ስብጥር ብዛት እጅግ በጣም በጥሩ ሁኔታ የተያዙ ማሳዎች በተለይም ደግሞ የባህላዊ የእርሻና ደን ስብጥር (Agro-forestry) እና አርሶ አደሮቹ በማሳቸው ዳር በጥቂት ቦይ ላይ አጅግ ዘር አብዝተው (ምስግ አድርገው ዘርተው) ለከብቶች መኖነት የሚያበቅሉዋቸው ማሽላ ወይም በቆሎ ናቸው፡፡ ሌላው በሁለተኛነት የሚያሰደስተኝ ቦታ በምስራቅ ጎጃም ደጀንን አለፍ ብሎ የጤፍ ሰብል ታጭዶ ክምሮች ተኮልኩለው የሚታዩበት ሜዳ ኮትቻ መሬቶች ናቸው፡፡ ክምሮቹን ስትመለከት ያ ሁሉ የጤፍ ክምር በእውነቱ በሰው ተበልቶ የሚያልቅ አይመስልም፡፡

ጥያቄ፤ በሥራ ዓለም በነበሩበት በርካታ ዓመታት የተለያዩ ገጠመኞች እንደነበርዎት እገምታለሁ፡፡ ከነዚህ ዉስጥ ጥቂቶቹን ቢያጋሩኝ፡፡

ዶክተር ክበበዉ፤ በመጀመሪያ በሥራ አለም ሳይሆን በትምህርት ላይ እያለሁ የነበሩኝን ሁለት ገጠመኞች ባነሳ ደስ ይለኛል፡፡ የመጀመሪያዉ ትምህርት ላይ በተለይም ሶስተኛ ክፍል በነበርኩበት ጊዜ የእንግሊዝኛ አስተማሪያችን (አፈር ይቅለላቸውና መምህር ይልማ ሂርጳዬ) እንግሊዝኛን እንዴት በድምፅ አናባቢ ፊደላት (vowels) በራሳቸው ብቻቸዉን አናባቢ ያልሆኑ ወይም ተነባቢ ፊደላትን (consonant) መፃፍና ማንበብ እንደሚገባን ያስተማሩበት ስልት እስካሁን አልረሳውም፡፡ በጣም መሰረታዊ በመሆኑም አስከ አሁንም እንዴት እንደጠቀመኝና እየጠቀመኝም እንዳለ አጉልቼ ማድነቅና መናገር እወዳለሁ፡፡ በጣም የሚገርመኝ ያኔ ሶስተኛ ክፍል በነበርኩበት ጊዜ ልክ ከኤ እሰከ ዜድ (A to Z) እንደ መውጣት ሁሉ ጊዜ ከዜድ ጀምሮ እሰከ ኤ (Z to A) ወደ ላይ ያለምንም መደነቃቀፍ እወጣው ነበር፡፡ የሚገርመው ግን አሁን እንደያኔው በነበረኝ ክህሎት ልወጣው አልችልም፡፡ በትምህርት ላይ በነበርኩበት ጊዜ የነበረኝ ሁለተኛዉ ገጠመኜ የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከተፈተን በኋላ የሚቀጥለውን የትምህርት መስክ ስመርጥ እኔ ምን መሆን ትፈለጋለህ ለሚለው መጠይቅ የህክምና ዶክተር ካልኩኝ በኋላ የት ነው መማር የምትፈልገው ለሚለው መጠይቅ ግን አለማያ እርሻ ኮሌጅ ብዬ መሙላቴ ነበር፡፡ የአለማያ እርሻ ኮሌጅን የመረጥኩት በጊዜው የዕድገት በህብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ ከአሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ስዘምት በያኔው የሐረርጌ ክፍለ ሀገር በጋራ ሙለታ አውራጃ በኩርፋ ጨሌ ወረዳ ተመድቤ ዘምቼ ስለነበር ስለኮሌጁና አካባቢው ሰላወቅሁና አድናቆትም ስለነበረኝ ነበር፡፡

በሥራው ዓለም ከነበሩኝ ገጠመኞች ሁሌም ትዝ የሚለኝና የምናገረው የዛሬ አርባ ዓመት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቄ የምርምር ሥራ ስጀምር በመስክ ላይ ሙከራዎችን ስንዘራ የቴክኒክ ረዳት የነበሩት እነ ጋሼ ተክለ ሃይማኖት ኃይለማርያም 3 – 4 – 5 የሚለውን የጂኦሜትሪ ፅንሰ-ሃሳብ (Pythagoras Theorem, 32 + 42 = 52) ትክክለኛ የአራት ማዕዘን መሬት ላይ ለማምጣት ተጠቅላይ ሜትር በመጠቀምና ሲባጎ ገመድ በመወጠር እንዲሁም እኔ በባዮሜትሪ በቲኦሪ ደረጃ ጥሩ ውጤት አምጥቼ ያለፍሁትን በተግባር ግን ምን እንደሆነ አይቼ ያልነበረውን የራንዶማይዝድ ኮምፕሊት ብሎክ ዲዛይን (RCBD) የሙከራው መሬት ላይ ሲያስቀምጡት ማየቴ ነበር፡፡ ሌላኛው ላነሳወ የምፈልገው ሥራ በጀመርኩባቸው አመታት ኮምፒዩተር ከመምጣቱ በፊት ለብዙ አመታት ለመረጃ ትንተና የምንጠቀመው የጠረጴዛ ላይ ካልኩሌተር (ያውም የሜሞሪ አማራጭ ያለው ከሆነ በጣም ይደንቃል) ለፅሁፍ ደግሞ በእጅ ተፅፎ ለታይፒስት ፀሐፊ በመስጠት ነበር፡፡ ሆኖም በወቅቱ በየካቲት ከዘገየ በመጋቢት መግቢያ በጊዜው ለነበረው አመታዊ ብሄራዊ የሰብል ማሻሻያ ኮንፈርንስ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሪፖርት የሚቀርብበት ነበር፡፡ በመጀመሪያ ኮምፒተርን መጠቀም የተለማመድነው ከአለም አቀፍ በቆሎና ስንዴ ማሻሻያ ድርጅት (CIMMYT) በልገሳ በተገኘ አሮጌ (2 KB) ኮምፒዩተር ነበር፡፡ ዕድሜ ለ Douglas Tanner መጀመሪያ ኮምፒዩተር መጠቀም በተለይ የመረጃ ትንተና ስልቱን (MSTATC or MSTAT4C) ያስተማረን እርሱ ነበር፡፡ የሚገርመኝ ነገር ታዲያ አሁን ኮምፒዩተሮች ያውም ትልቅ ችሎታ ያላቸወ በብዛት እየተጠቀምን እያለን ሪፖርቶች መቅረብ ባለባቸው ጊዜ ማቅረብ አለመቻላቸው ነው፡፡

ምስሉ የሚያሳየዉ እ አ አ በ1994 በሃረማያ ዩኒቨርስቲ በተካሄደ የተማሪዎች ምረቃ ቀን የዚህ ብሎግ ጸሐፊ በማስትሬት የተመረቀበት ቀን ነበር፡፡ በምስሉ የሚታዩት ከግራ ወደ ቀኝ ዘሪሁን ታደለ፣ ሙሉ አየለ፣ ኃይሉ ተፈራ እና ክበበዉ አሰፋ ሲሆኑ በወቅቱ አራቱም የጤፍ ተመራማሪዎች ነበሩ፡፡ ከለበሱት ልብስ እንደሚታየዉ ከዶክተር ኃይሉ በስተቀር የተቀሩት የማስትሬት ምሩቆች ነበሩ፡፡ በርካታ የጤፍ ተመራማሪዎች በዚህ ሥፍራ ሊገኙ የቻሉትም በወቅቱ ከእኔ በስተቀር የተቀሩት ሶስት ተመራማሪዎች የሚሰሩት በሀረማያ ዩኒቨርስቲ ሥር በሚገኘዉ የደብረ ዘይት ምርምር ማእከል ስለነበረ መሥሪያ ቤታቸዉ በአመታዊ የምረቃ በአላት ላይ ይጋብዛቸዉ ስለነበረ ነዉ፡፡

በማጠቃለያ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ ላለፉት 40 ዓመታት ከፍተኛ ዕዉቀትና የሥራ ልምድ በማካበት የተወሰኑ ሳይሆኑ በጤፍ ምርምር እና ልማት ካደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በተጨማሪ ዕዉቀታቸዉን ለወጣት ተመራማሪዎች፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ገበሬዎች እና ሌሎችም ሲያጋሩ ነበር፤ በአሁኑ ጊዜም በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ይህንንም በአግባቡ መጠቀም አለብን እላለሁ፡፡

በዚሁ በሶስት ክፍሎች ዶክተር ክበበዉ አሰፋን በተመለከተ የጻፍኩትን ብሎጎቼን አበቃለሁ፡፡

ወደፊት በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. (April 5, 2023)

2 thoughts on “ግብርናችንን ለማዘመን፤ የጤፉ ጠቢብ፣ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ፤ ክፍል 3

  1. የኢትዮጵያ ሰብል ሳይንሰ ባለሙያዎች ማህበር ዶ/ር ክበበውን የዕድሜ ልክ የስኬት ሽልማት ተሸላሚ በማደረረጉና አነንተም ዶ/ር ክበበውን በማስተዋወቅህ አመሰግናለሁ፡፡ ሌላው ከዶ/ር ክበበው ያላቸው ባህሪ በምርምር ዘርፍ ሰውን ለመርዳት ያላቸው ቅንነትን አደንቃለሁ፡፡
    ወንድአፍራሽ

    Like

አስተያየት ያስቀምጡ