በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡
19ኛዉ የኢትዮጵያ ሰብል ሳይንስ ባለሙያዎች ኮንፈረንስ
በየሁለት ዓመት የሚካሄደዉ 19ኛዉ የኢትዮጵያ ሰብል ሳይንስ ባለሙያዎች ኮንፈረንስ አዲስ አበባ በሚገኘዉ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ምስሪያ ቤት ህሩይ አዳራሽ ከየካቲት 17 እስከ 18፣ 2015 (ወይም እ አ አ ፌብሪዋሪ 24 እስከ 25፣ 2023) ተካሂዷል፡፡ በዚሁ ኮንፈረንስ ላይ ከ200 ያላነሱ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የመስኩ ባለሙያዎችና የማህበሩ አባላት ተሳትፈዋል፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የማህበሩ ፕሬዘዳንት ዶክተር ታዬ ታደሰ ሲሆኑ ኮንፈረንሱን በንግግር የከፈቱት ደግሞ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክቴር ዶክተር ድሪባ ገለቴ ናቸዉ፡፡
በመቀጠልም ሁለት ኪ ኖት መልእክቶች (keynote addesses) የተሰጡ ሲሆን እነርሱም
ዶክተር ድሪባ ገለቴ (ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት)፤ ‘‘የተሻሻለ ግብርና ለምታድግ ኢትዮጵያ‘‘
ዶክተር ፍሬው መክብብ (ከሀረማያ ዩኒቨርሲቲ)፤ ‘’የተሻሻለ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ግብርና ላይ ያለው ሚና’’
በተጨማሪም የፓናል ውይይት የተዘጋጀ ሲሆን በውይይቱ እንዲሳተፉ የተጋበዙት ሶስት ምሁራን በሚከተሉት ርዕሶች ጽሑፍ እንዲያቀርቡም ተጋብዘዉ ነበር፡፡
ዶክተር ይልማ ከበደ (ኪዊንስላንድ ዩኒቨርሲቲ፣ አዉስትራሊያ)፤ ‘’የሰብል ማሻሻያን ዘመናዊ ለማደረግ የሚደረገዉ ጥረትና አዳዲስ የፈጠራ ዉጤቶችን በተከታታይነት ለመጠቀም ያለዉ ዉስንነት’’
ፕሮፌሰር ዘሪሁን ታደለ (ከበርን ዩኒቨርሲቲ፣ ስዊዘርላንድ)፤ ‘’በኢትዮጵያ የሰብል ማሻሻያ ላይ የባዮቴክኖሎጂ አተገባበር፡ ተግዳሮቶቹ እና የወደፊት የተፅዕኖ አቅጣጫ’’
ዶክተር ዳዊት አለሙ (የዋግንገን ኔዘርላንድ ምርምር የኢትዮጵያ ተወካይ)፤ ‘’ለታዳጊ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች የምግብ፣ መኖና ግብአት ለማርካት በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት በማስተካከል፣ ወቅታዊ ትምህርቶችና የወደፊት አቅጣጫዎች’’
በመቀጠልም የፓናል ዉይይቱን ከሚመሩት (moderator) በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ በፓናል ተሳታፊዎች ውይይት የተደረገ ከመሆኑም በላይ የኮንፈረሱ ተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችንና ምክረ ሀሳቦችን ለግሰዋል፡፡
በሁለተኛዉ የኮንፈረንስ ቀንም በሁለት ምሁራን የፓናል ውይይት የቀረበ ሲሆን እነርሱም
ዶክተር መልካሙ በየነ (ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)፤ ‘’የኢትዮጵያ ሰብል ሳይንስ ጆርናል ህትመትን ዘመናዊነት ማላበስ’’
ፕሮፌሰር ሽመልስ አድማሱ (ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)፤ ‘’የሰብሎችን የአመጋገብ ጥራት ለማሻሻል እና የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ የለውጥ ፈጠራዎች’’
ሁለቱ ምሁራን ባቀረቧቸዉ ጽሑፎች በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች ከኮንፈረንሱ አወያይና ተሳታፊዎች የቀረቡ ሲሆን ሰፊ ውይይትም ተደርጎባቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በሁለቱ ቀናት የኮንፈረንሱ ዉሎ በርካታ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን እነርሱም የሰብል ማሻሻያን፣ አግሮኖሚን፣ የሰብል ጥበቃን፣ የምግብ ሣይንስንና ኤክስቴንሽን የተመለከቱ ናቸው፡፡
ኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ ግብርና በተለያዩ መስኮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁለት ምሁራን የህይወት ዘመን ዕዉቅና ሰጥቷል፡፡ እነዚሀ ዕዉቅና የተሰጣቸዉ ምሁራን ዶክተር በዳዳ ግርማ እና ዶክተር ክበበዉ አሰፋ ናቸዉ፡፡
ዶክተር በዳዳ ግርማ ለረጅም አመታት በወረር ግብርና ምርምር ማእከል የብሔራዊ የጥጥ ምርምር አስተባባሪ ሆነዉ ሰርተዋል፡፡ በመቀጠልም በቁሉምሳ የምርምር ማእከል በስንዴ ምርምር በተለይም የዋግ በሽታን ለመከላከል በተደረገዉ አለም አቀፍ ዘመቻ ከፍተኛ አሰተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በርካታ ዝርያዎችም እንዲለቀቁና ለገበሬዉ እንዲደርሱ ጉልህ ድርሻ አበርክተዋል፡፡
ዶክተር ክበበዉ አሰፋ ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪያቸዉን ካጠናቀቁበት የዛሬ 40 አመት ወዲህ ጊዜያቸውን በጤፍ ምርምር ያሳለፉ ሲሆን በርካታ የጤፍ ዝርያዎች ተለቀዉ በአምራቹ ዘንድ እንዲደርሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ለነዚህ ከፍተኛ እዉቅና ለተሰጣቸዉ ምሁራን በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ፡፡ በድጋሚ ያልኩበት ምክንያት የመጀመሪያዉን እንኳን ደስ አላችሁ በወቅቱ በሥፍራዉ ስለነበርኩ እዚያዉ ስላደረስኩ ነዉ፡፡ በአጋጣሚ ከሁለቱም ተሸላሚዎች ጋር ከፍተኛ ቅርበት አለኝ፡፡ ዶክተር በዳዳ የብሔራዊ የጥጥ ምርምር አስተባባሪ በነበሩት ወቅት እኔም አግሮኖሚን በመወከል የአስተባባሪዉ ኮሚቴ አባል ስለነበርኩ በቅርበት አብረን ከመስራታችንም በላይ የወረር ምርምር ማእከልን በሃላፊነት በመሩበት ወቅት የቅርብ አለቃዬ ነበሩ፡፡ ዶክተር ክበበዉ ደግሞ የጤፍ ምርታማነትን ለማሳደግ ታስቦ በተቋቋመዉ የጤፍ ማሻሻያ ፕሮጀክት ዉስጥ ላለፉት 15 አመታት በትብብር እየሰራን እንገኛለን፡፡

ምስሉ የሚያሳየዉ የህይወት ዘመን ዕዉቅና ለዶክተር በዳዳ ግርማ እና ለዶክተር ክበበዉ አሰፋ የተሰጠበት ሥነ ሥርዓት ነዉ፡፡ ከግራ ወደ ቀኝ ዶክተር በዳዳ ግርማ፣ ዶክተር ድሪባ ገለቲ፣ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ፣ ዶክተር ታዬ ታደሰ እና ዶክተር ካሳዬ ቶለሳ፡፡ ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፣ የካቲት 17 ቀን 2015።

ዶክተር በዳዳ ግርማ (በስተግራ) እና ዶክተር ክበበው አሰፋ በጋራ ዳቦ ሲቆርሱ፡፡ ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፣ የካቲት 17 ቀን 2015።

ዶክተር በዳዳ ግርማ (በስተግራ) እና ዶክተር ክበበዉ አሰፋ ስለተሰጣቸዉ ከፍተኛ እዉቅና ሲወያዩ፡፡ ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፣ የካቲት 17 ቀን 2015።
ከኮንፈንሱ ተሳታፊች ከቀረቡት ምክረ ሀሳቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
- ወደፊት በመድረክ የሚቀርቡ ጽሑፎች የጥራት ደረጃቸዉ እንዲጠበቅ በቅድሚያ በኮሚቴ ታይተዉ እና እርማት ተደርጎባቸዉ እንዲሆን ቢደረግ፤ ለዚሁም ዶክተር ይልማ ከበደ መርዳት እንደሚችሉ ቃል ገብተዋል፡፡
- በፓዎር ፖይንት ለሚቀርቡ ጽሑፎችም የፎንት መጠናቸዉ ጎላ ብሎ ለተሳታፊች በቀላኡ እንዲታዩ ቢደረግ፤
- በመድረክ የሚቀርቡ ወረቀቶችም የተወሰኑ እንዲሆኑና ተጋባዥ እንግዶች በቂ ጊዜ እንዲሰጣቸዉ ቢደረግ፤
- በኮንፈንሱ ተሳታፊዎች የምርምር ዉጤታቸዉን በፖስተር መልክ የሚያቀርቡበት መንገድ ቢመቻቸና ለተመረጡ የፖስተር አቅራቢዎች ሽልማት ቢሰጥ፤
- ለኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መሳተፋቸዉን የሚገልጽ የምስከር ወረቀቀት ቢሰጥ ናቸዉ፡፡
በአጠቃላይ ኮንፈረንሱ በጥሩ ሁኔታ የተካሄደ ሲሆን በአካል መገኘት ያልቻሉ ነገር ግን የኢንተርነት ግንኙነት የነበራቸዉ መከታተል እንዲችሉ ያስቻለ ነበር፡፡ ለምሳሌ የኪ ኖት ንግግር ያደረጉት ዶክተር ፍሬዉ መክበብ ከሀረር ከተማ ሆነው መልእክታቸዉን ያስተላለፉት፡፡ ወደፊትም ወደ ኮንፈረንሱ ሥፍራ በአካል መገኘት ያልቻሉ አባላት በተለያዩ መንገዶች የሚሳተፉበት መንገድ ቢመቻች እላለሁ፡፡
በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. (March 6, 2023)
It was interesting event. I appreciated the organizers for their effort and recognition.
I think your work also a lesson for us to write and put the occasion as a history and considering every details .
Wondafrash
Regards!
LikeLike