ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለውጥ — ምልክቶቹ

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለውጥ — ምልክቶቹ

የአየር ንብረት ለዉጥ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ከመጣ ሰንበትበት ብሏል። አብዘኛዉ የዓለማችን ሕዝቦች የአየር ንብረት ለዉጥ በአጠቃላይ በኑሮዋቸዉ ላይ እያደረሰ ያለዉንና ወደፊትም ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቀዉን እጅግ ስላሳሰባቸዉ በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲፈልጉለት መንግሥታቸዉንና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በየመድረኩ እየወተወቱ ይገኛሉ። የአንደኛ ተማሪዎች ሳይቀሩ የአየር ንብረት ለዉጥ መጥፎ ጠባሳ ጥሎብን ሳያልፍ እንታደገዉ እያሉ ነው። በዚህ የተነሣ ከአየር ንብረት ለዉጥ መንስኤዎች ጀምሮ ወደፊት ሊያጋጥም የሚችለዉን ክስተት የሚያካትት ሰፊ ጥናት ተካሂዷል። በሣይንስ የተደገፈ ትንበያም ተሰጧል።

የዛሬዉ ጽሁፌ የሚያተኩረዉ የአየር ንብረት ለዉጥ በአሁኑ ጊዜ እየተከሰተ እንደሆነና ወደፊትም ለመከሰቱ ፍንጭ እንዳለ የተወሰኑ አሀዞችን ለማሳየት ነዉ።

1ኛ) የአየርና የባህር ሙቀት መጨመር፤ የዓለማችን የአየር ሙቀት ከሰላሳ ዓመታት በኋላ ማለትም እ.ኤ.አ. በ2050 በአማካይ ሁለት ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንደሚጨምር ይገመታል።ይህ አማካይ ሙቀት ነዉ እንጂ ባንዳንድ ሥፍራዎች የሚጨምረዉ የሙቀት መጠን ከዚህ በላይም ሊሆን ይችላል።

2ኛ) የዝናም እጥረት ወይም ድርቅ መባባስ፤ ባለፉት ሀምሳ ዓመታት በዝናም ማነስ የተነሳ በድርቅ የተጠቁ ሥፍራዎች ከዚያ በፊት ከነበሩት በእጥፍ ጨምረዋል።

3ኛ) የጎርፍ መብዛት፤ በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች የዝናም መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያንስ እንደሚጠበቀዉ ሁሉ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ዝናምና እሱን ተከትሎ የሚመጣዉ ጎርፍ ይጠበቃል።

4ኛ) የግሪንሃዉስ ጋዝ (Greenhouse gas) መጠን መጨመር፤ ለጤና ጠንቅ የሆኑና ግሪንሃዉስ ጋዝ የሚል ስያሜ የተሰጣቸዉ ወደ ሰባት ይጠጋሉ። እነርሱም የዉሃ ትነት (H2O)፣ ካርቦንዳይኦክሳይድ (Carbon dioxide CO2)፣ ሚቴን (Methane CH4)፣ ኦዞን (Ozone O3)፣ ናይትረስ ኦክሳይድ (Nitrous oxide N2O)፣ ክሎሮፍሎሮካርቦንስ (Chlorofluorocarbons CFCs) እና ሃይድሮፍሎሮካርቦንስ (Hydrofluorocarbons HCFCs & HFCs) ናቸዉ። ከዚህ በፊት የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየዉ ጥርት ባለ ሰማይ ቀን ከከባቢያችን አየር ዉስጥ የዉሃ ትነት 60% እጅ ሲይዝ ካርቦንዳዮክሳይድ 26%፣ ኦዞን 8% እና ሚቴን 6% በመያዝ ይከተላሉ። የግሪንሃዉስ ጋዞች ዋናዉ ባህሪያቸዉ ከከባቢያችን የአየር ክልል ወጥቶ የሚሄደዉን ሙቀት በማስቆም ተመልሶ ወደ መሬታችን እንዲደርስና ሙቀት እንዲሰጠን ማድረግ ነዉ። እነዚህ የግሪንሃዉስ ጋዞች በመጠኑ ሲሆኑ ከፍተኛ ጥቅም አላቸዉ፣ ያለእነርሱም በምድር ላይ መኖር አዳጋች ይሆን ነበር። ምክንያቱም የምድራችን ሙቀት በአማካይ ከዜሮ በታች 20 ድግሪ ሴንቲግሬድ አካባቢ ስለሚሆን ነዉ። ታዲያ እነዚህ እንደ ብርድ ልብስ ከላይ ሆነዉ መሬታችንን ባይሸፍኑልን ምን ይዉጠን ነበር። በሌላ በኩል የነዚህ ጋዞች በከባቢያችን ባለዉ አየር ሲከማቹ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላሉ። በአሁኑ ጊዜም በማስከተልም ላይ ይገኛሉ። ለወደፊቱ ደግሞ የከፋ ችግር እንዳያስከትሉ ከፍተኛ ሥጋት አለ። የዓለም ሜትሮሎጂካል ድርጅት ሪፖርት እንደሚያሳየዉ በአሁኑ ጊዜ ያለዉ የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን 250 ዓመታት በፊት ከነበረዉ በ146% ከፍ ያለ ሲሆን ሚቴን በ257% እንዲሁም ናይትረስ ኦክሳይድ በ122% ብልጫ አሳይተዋል።

5ኛ) የበረዶ ክምችት መመናመን፤ በቀዝቃዛዉ የአለማችን ክፍል በተለይም በከፍተኛ ተራሮች ላይ ዓመቱን ሙሉ ተክማችቶ የሚገኝ ግሌሸር ተብሎ የሚጠራ በረዶ አለ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዚህ ግሌሸር መጠን እየተመናመነ መጥቷል። ከዚህ በተጨማሪ በሰሜንና ደቡብ ዋልታ አካባቢ የሚገኙ የአርክቲክ እና የአንታርክቲክ ባህሮች የበረዶ መጠናቸዉ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መጥቷል።

6ኛ) የባህር ወለል ከፍ ማለት፤ በብዙ የዓለማችን ክፍሎች በተለይም በባህርና ዉቅያኖስ ዳርቻ የሚኖሩ ሕዝቦች የባህር ወለል ቀድሞ ከነበረበት ከፍ ማለቱን ከተገነዘቡ ቆይተዋል። የቀድሞ ቀዬአቸዉንም ለቀዉ ከፍ ወዳሉ ሥፍራዎች ለመሄድ ተገደዋል። የባህር ወለል ከፍ ሊል የቻለዉ በሁለት ዋና ምክንያቶች ነዉ። አንደኛዉ ከላይ እንደተገለጸዉ ከፍ ባሉ ተራሮች ላይ ተከማችቶ የሚገኘዉ ግሌሸር መቅለጥና ከውሃዉ አካል ጋር መቀላቀል ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚሞቀዉ የባህር አካል ሰፋ ያለ ሥፍራ ስለሚይዝ ወደ የብስ ስለሚስፋፋ ነዉ።

7ኛ) የባህር ዉሃ ወደ አሲዳማነት መቀየር፤ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአየር ውስጥ ካለው የካርቦንዳይኦክሳይድ መጠን ውስጥ 25% የሚሆነዉ ወደ ባህር ወይም ሌላ የዉሃ አካል ይገባል። ካርቦንዳይኦክሳይዱ ከውሃ ጋር ሲገናኝ ካርቦኒክ አሲድ ይፈጥራል። ከላይ እንደተገለጸዉ በአከባቢያችን ያለዉ የካርቦንዳይኦክሳይድ መጠን እየጨመረ ስለሆነ በዉሀ ወይም በባህር ዉስጥ የሚፈጠረዉ የአሲድ መጠንም በከፍተኛ ደረጃ ይጨመራል ማለት ነዉ። ይህም ዓሣን ጨምሮ በዉሃ ውስጥ ለሚኖሩ ፍጥረታት ጠንቅ ይሆናል ማለት ነዉ።

የነዚህ መጥፎ ከስተቶች አሳሳቢ አይደለም ትላላችሁን? ምድራችን አንድ ናት። ባንዱ ሀገር የደረሰዉ ክስተት ድንበር ሳይገድበዉ ወደ ሌላ ሀገር መሻገሩ አይቀርም። በርግጥ አንዳንድ ከስተቶች በአንድ አህጉር ብቻ ሊታዩ ይችላሉ። ይህ ግን ሁሌም እንደዛ ይሆናል ማለት አይደለም።  ይህን በመገንዘብ ነዉ የዓለም መንግሥታት ለመፍትሔዉ በጋራ ለመሥራት ያቀዱት። በሚቀጥሉት ጽሁፎቼ የአየር ንብረት ለዉጥ በሰብሎቻችን፣ በእንስሳቶቻችን፣ በጤናችን፣ በዉኃችን ወዘተ ላይ የሚያደርሱትን እዘግባለሁ። በተጨማሪም ይህንን ለመታደግ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በማድረግ ላይ ያሉትን ጥረትና የተገኙ ዉጤቶችን በአጭሩ ለማሳየት እሞክራለሁ።

እስከዚያዉ በቸር ይግጠመን።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 3፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና!!!

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና!!!

የዛሬዉ ርዕሴን የወሰድኩት ቡና በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ ያለዉን ከፍተኛ ሚና በማስመልከት የጂማ ቦንሳ 04 ቀበሌ ታዳጊ የኪነት ቡድን አባላት ከረጅም ዓመታት በፊት በዚያ ጣፋጭ የልጅነት ድምጻቸዉ ያዜሙልን ከነበረዉና ዘወትር በኢትዮጵያ ሬዲዮ እንሰማዉ ከነበረዉ መዝሙራቸዉ ነዉ። ባልሳሳት የመዝሙሩ ስንኝ ከዚህ በታች ያለዉ ነዉ።

“የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና

የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና

የህይወታችን ገንቢ ቡና ቡና

አዉታር ነው ቡናችን ቡና ቡና”

ታዲያ በዚያን ወቅት ቡና ለኢትዮጵያ 60% የሚሆነውን የዉጭ ምንዛሬ በማስገኘት በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ግንባር ቀደም ሚና ይጫወት ነበር። ነገር ግን አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ጊዜ የቡና ድርሻ ከጠቅላላ የኤክስፖት ዉስጥ ከ30-35% የሆነዉን ብቻ ነዉ። ለምን የቡና ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ ቀነስ? የእገር ዉስጥ ፍጆታ ከፍተኛ ሰለሆነ ነዉን? ከዚህ በፊት ”የቡናችን ነገር እጅግ ያሳስባል” በሚለው ክፍል ሁለት ጽሑፌ ማሳየት እንደሞከርኩት በዓለም በቡና ምርታቸዉ ከታወቁት የላይኞቹ 10 ሀገራት መካከል ከፍተኛ ድርሻ ያለዉን ቡና ለሀገር ዉስጥ ፍጆታ የምታዉለዉ ሀገር ኢትዮጵያ ናት። በዚሁ መሠረት ከጠቅላላ ምርቷ 66.1 % ቱን ለሀገር ዉስጥ ፍጆታ ታዉላለች። በሌላ በኩል በዓለም በቡና ምርቷ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኮሎምቢያ ከጠቅላላ ምርቷ 2.6% ብቻ አስቀርታ የተቀረዉን ለዉጭ ሀገር ገበያ ታቀርባለች። እ.ኤ.አ. በ2016 ብቻ 2.53 ቢሊዮን ዶላር አግኝታበታለች።

ወደ ሀገራችን ስንመለስ ቡና በዉጭ ሀገር ገበያ የነበረዉን ሚና ለመረዳት እንድንችል በዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት መረጃ ላይ በመመርኮዝ ያዘጋጀሁትን ሶስተ ግራፎች ከዚህ በታች ማየት ይቻላል። ሶስቱ ግራፎች በቅድም ተከተል የሚወክሉት ሀገሪቷ እ.ኤ.አ. ከ1993 እስከ 2016 ባሉት 24 ዓመታት ውስጥ በያመቱ የላከችዉ የቡና መጠን፣ ከሽያጩ ያገኘችዉ የዉጭ ምንዛሪ መጠን እና በእያንዳንዱ ኪሎ ግራም የተከፈላት የገንዘብ መጠንን ነዉ።

ኤክስፖርት የተደረገ ቡና መጠንን በተመለከተ፤ ምንም እንኳ በተወሰኑት ዓመታት መጠነኛ መዋዥቅ ቢታይም መረጃዉ መወሰድ ከጀመረበት ዓመታት ወዲህ የቡና ኤክስፖርት መጠን ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል። እ.ኤ.አ. በ1993 ወደ ዉጭ የተላከዉ 70 ሚሊዮን ኪ.ግ. ቡና ሲሆን በ2015 ግን ወደ 234 ሚሊዮን ኪ.ግ. በማደጉ በ23 ዓመታት ዉስጥ የ234% እድገት አሳይቷል። ከፍተኛ የኤክስፖርት ማሽቆልቆል የታየዉ ለሶስት ዓመታት ሲሆን ይህም በ2001፣ 2009 እና 2011 ነዉ። በኔ ግምት የ2016 ዝቅተኛ የኤክስፖርት መጠን ሊመዘገብ የቻለው መረጃዉ ይፋ ሲደረግ የዓመቱ አጠቃላይ የኤክስፖርት መጠን አልተጠናቀቀም ይሆናል።

ከቡና ኤክስፖርት ሀገሪቷ ያገኘችዉ የዉጭ ምንዛሪን በተመለከተ፤ በመረጃዉ መሠረት በቡና የተገኘዉ የዉጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል። እ.ኤ.አ. በ1993 ከነበረዉ 129 ሚሊዮን ዶላር ተነስቶ በ2015 ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሊያድግ ችሏል። ይህም የ688% ዕድገት መሆኑ ነዉ። ከላይ እንደተገለጸዉ በተወሰኑት ዓመታት ወደ ዉጭ የተላከዉ ቡና መጠን ቢያሽቆለቅልም ባንዳንድ ዓመታት ካልሆን በስተቀር የውጭ ምንዛሪ መጠን ላይ ቅናሽ አልታየም። ለምሳሌ በ2011 ወደ ዉጭ የተላከዉ ቡና በ2010 ከተላከዉ ጋር ሲወዳደር በ 52.7 ሚሊዮን ኪ.ግ. ዝቅ ብሎ ቢገኝም ያስገኘዉ መዋዕለ ንዋይ ግን በ 2011 የተገኘዉ በ 2010 ከተገኘዉ ማነስ ሲጠበቅበት በ24.8% አድጎ ተገኝቷል። ይህም ሊሆን የቻለዉ በ2011 የአንድ ኪ.ግ. ቡና ዋጋ መረጃዉ ባለበት 24 ዓመታት ሁሉ ከፍተኛዉ ሆኖ በመመዝገቡ ነዉ።

የአንድ ኪ.ግ. ቡና ዋጋን በተመለከተ፤ በሥዕሉ እንደሚታየዉ የቡና ዋጋ በኪ.ግ. ዕድገት አሳይቷል። በ 1993 አንድ ኪ.ግ. ቡና ኢትዮጵያ የሸጠችወ በ1.85 ዶላር ሲሆን በ 2016 ወደ 4.48 ዶላር ከፍ ብሏል። ቢሆንም በተወሰኑት ዓመታት በተለይ ከ2001 እስከ 2004 ባሉት አራት ዓመታት የአንድ ኪ.ግ. ቡና ከ1.50 ዶላር በላይ መዝለል አልቻለም። ነገር ግን የቡና ዋጋ ከዚህ አገግሞ እጅግ የተሻለ ደረጃ ሊደርስ ችሏል። እስካሁን በሪኮርድነት የተመዘገበዉ ዋጋ በ 2011 የተገኘዉ 5.31 ዶላር በኪ.ግ. ነው። ለዚህ ከፍ ያለ ዋጋ እንደ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለዉ በተጠቀሰዉ ዓመት በአቅርቦት ላይ የነበረዉ ዝቅተኝነት ነዉ። በአቅርቦት ማነስ ምክንያት የቡና ዋጋ ከፍ ሊል ስለሚችል።

ስለዚህ ኢትዮጵያ ወደ ዉጭ የምትልከዉ ቡና በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ ሳይሆን አማራጭ የዉጭ ምንዛሪ ማስገኛ በማግኘቷ ጭምር ይመስለኛል። ምንም እንኳ የተወሰነ መዋዠቅ ቢያሳይም በሥዕሉ እንደሚታየዉ የተላከዉ ቡና መጠን እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም። ሰለዚህ ኢትዮጵያ ወደ ዉጭ ከምትልካቸዉ ዕቃዎች ጋር ስናወዳድር የቡና ድርሻ ቀድሞ ከነበረዉ ቀንሶ የታየዉ የሌሎች ወደ ዉጭ የሚላኩ ዕቃዎች ድርሻ በመጨመሩ ነዉ። ይህም እንደ ሰሊጥና አበባ የመሳሰሉትን ያካትታል። ለምሳሌ አንድ የዓለም አቀፍ መረጃ እንደሚያሳየዉ እ.ኤ.አ. በ2016 ኢትዮጵያ ከአበባ ሽያጭ 225 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እንገናኝ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 2፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ ቀለማት ምንን ይወክላሉ?

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

በግብርና ቀለማት ምንን ይወክላሉ?

የቀለማት አጠቃቅም በዓለማችን በተለይ በቢዝነሱ መስክ በከፍተኛ ጥንቃቄ ይሰራል። ምክንያቱም በማስታወቂያ ወይም በዌብ ሳይት የምንጠቅማቸዉ ቀለማት ደንበኛን በመሳብም ሆነ በማራቅ አስተዋጾኦ ስለሚያደርጉ ነዉ።

የዛሬዉ ጽሑፌ በቀለማት አመራረጥ ላይ ለማተኮር ሳይሆን በተለምዶ ከግብርና ጋር በተያያዘ በሰፊዉ ጥቅም ላይ የዋሉ የቀለማት ዓይነት ላይ ነዉ።  የምንጠቅማችዉ ሰብሎችና እንስሳት በሚመለከት የተለመዱ ቀለማትና የሚወክሏቸዉ ሴክተሮች ከዚህ በታች ቀርበዋል።

  • አረንጓዴ          ለምግብ የሚሆኑ ሰብሎች
  • ቢጫ              የቅባት ሰብሎች
  • ወርቃማ          አትክልትና ፍራፍሬ
  • ነጭ               ወተት
  • ሰማያዊ           ዓሣ
  • መዳብ            ዶሮና ዕንቁላል
  • ቀይ               ሥጋና ቲማቲም
  • ዳለቻ             ማዳበሪያ

ከቀለማት የተለያ ሰያሜ ያላቸዉም አሉ። ለምሳሌ፣

  • ክብ               ድንችን ይወክላል።
ከላይ በሥዕሉ እንደሚታየዉ የተለያዩ ቀለማት ከግብርና ጋር የተገናኙ የተለያዩ ሴክተሮችን ይወክላሉ።

በሀገራችን ታዋቂ ሰብሎቻችንን ለመግለጽ ከምንጠቀምባቸዉ ቀለማት ዉስጥ ሁለቱን ከዚህ በታች ማየት ይቻላል።

  • ነጩ ወርቃችን              ጥጥን ለማመልከት ሲሆን ጨዉንም ለማመልከት ጥቅም ላይ ይዉላል
  • ቡኒዉ ወርቃችን             ቡናን ለማመልከት እንጠቀምበታለን።

በኔ ግምት ከሁለትና ሦስት አሥርት ዓመታት በፊት ቡና የሀገሪቱን እስከ 60% የሚሆነዉን የዉጭ ምንዛሪ ያስገኝ ነበር። በዚያን ወቅት ነበር “የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና…” የሚል መዝሙርም የተዘመረለት።

†

እዚህ በሥዕሉ የሚታየዉ የኢትዮጵያን ቡና ሻጮች የሚስተዋዉቁበት ማስታወቂያ ሲሆን “ወርቃማዉ ቡና ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ የመጣ” በሚል ተጽፎበታል። የዚህ ማስታወቂያ ዋናዉ መልዕክት ኢትዮጵያ የምታመርተዉ በተጠቃሚዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነዉን የአረቢካ ቡና ብቻ ስለሆነ ለሽያጭ የቀረበዉ ቡና ከሌላ የቡና ዓይነት ጋር አለመደባለቁን ያሳያል። ሌላዉ ደግሞ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሀገር በመሆኗ ተጠቃሚዎች ከዚህ የቡና መነሻ ከሆነች ሀገር የመጣ ቡናን ሲጠጡ ከፍተኛ እርካታ እንደሚሰማቸዉ ስለሚታወቅ ነዉ። በዚሁ መሠረት የዚህ ቡና የመሸጫ ዋጋዉ ከፍ ይላል።

ባሁኑ ጊዜ ቡና ለኢትዮጵያ ከ30-35% የሚሆነዉን የዉጭ ምንዛሪ ብቻ ያስገኛል። ወደ ውጭ የሚላከዉ ቡና መጠን ቀነሰ ወይስ ሌላ ምክንያት ተፈጠረ? በሚቀጥለዉ ጽሑፌ ይህንን በተመለከተ ለመጻፍ እሞክራለሁ።

እስከዚያው በቸር ይግጠመን።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 2፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የኢትዮጵያ የስንዴ አብዮት

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የኢትዮጵያ የስንዴ አብዮት

እንደሚታወቀዉ ሁሉ “አብዮት” የሚለዉ ቃል የሚወክለዉ በአጭር ጊዜ ዉስጥ መሠረታዊ ለዉጥ የሚያመጣ መዋቅርን ነዉ። ቢሆንም አንዳንድ ረዘም ያለ ጊዜ የወሰዱ ሂደቶችም እንደ አብዮት የተቆጠሩ ሂደቶች አሉ።

ከግብርና ጋር በተያያዘ “አብዮት” የሚል ቅጥያ ያላቸዉ በርካታ ስያሜዎች ጥቅም ላይ ዉለዋል።  ጥቂቶቹን ከዚህ በታች ማየት ይቻላል።

  • የመጀመሪዉ የግብርና አብዮት፣ ይህ የተከናወነዉ የሰዉ ልጅ እህል አሳድጎ መጠቀም በጀመረበት ጊዜ ሲሆን ይህም የዛሬ አሥር ሺህ ዓመት ገደማ ነበር።
  • ሁለተኛዉ የግብርና አብዮት፣ ይህ የተከናወነዉ በዘመናዊ የእርሻ መሣሪዎች በመታገዝ ምርትና ምርታማነት በአዉሮፓ ያደገበት ወቅት ሲሆን ይህም ከዘሬ 100 እስከ 200 ዓመታት በፊት ነበር።
  • አረንጓዴዉ አብዮት (ወይም ሶስተኛዉ የግብርና አብዮት)፣ በተለምዶ “አረንጓዴዉ አብዮት” ተብሎ የሚታወቀዉ እ.ኤ.አ. በ1960 ዎቹና 70ዎቹ የስንዴና የሩዝ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ያደረገበት ክስተት ነበር። ይህ ከፍትኛ የምርት እድገት ሊመጣ የቻለዉ ቁመታቸዉ አጠር ያሉና መጋሸብን ወይም መውደቅን የሚቋቋሙ ዝርያዎች በገበሬዎች ዘንድ እንዲደርሱ በመደረጉ ነዉ። በአረንጓዴዉ አብዮት ዕድሉን አግኝተዉ  ምርታማነታቸዉን ማሳደግ የቻሉት በኤሲያና በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ ገበሬዎች ሲሆኑ በአፍሪካ የነበሩት ግን የዚህ አብዮት ተጠቃሚ ሊሆኑ አልቻሉም። ምክንያቱም በአፍሪካ በብዛት የሚበቅሉት ሰብሎች አረጓዴዉ አብዮት ትኩረት የሰጠቻቸዉ ስንዴና ሩዝ ሳይሆኑ እንደ ማሽላ፤ በቆሎ፣ዳጉሣ እና ጤፍ የመሳሰሉት ናቸዉ። አረንጓዴዉ አብዮት እንዲሳካ በተለይ በስንዴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉት ዶክተር ኖርማን ቦርሎግ የተባሉና ለዚሁ ሥራቸዉ የኖብል ሽልማት ያገኙ ናቸዉ። የአረንጓዴዉ አብዮት አባትም ተብለዉ ይጠራሉ። በተመሣሣይ መልኩ በሩዝ ምርምርና ሥርፀት ከፍተኛ ዉለታ የዋሉትና የህንድ አረንጓዴ አብዮት አባት የሚባሉት ዶክተር ስዋሚናታን ናቸዉ።
  • ሁሌ አረንጓዴ አብዮት፤ ይህ ስያሜ የተሰጠዉ ምርትና ምርታማናትን በዘላቂነት ለማሳደግ ተብሎ ነዉ።
  • አራተኛዉ የግብርና አብዮት፣ በአቡኑ ጊዜ እየተካሄድ ያለዉን የዲጂታሊዜሽንና ፕሪሲሺን እርሻ የሚባለዉን ይወክላል።
  • የአፍሪካ አረንጓዴዉ አብዮት፣ ይህን አብዮት በአፍሪካ ለማሳካትና የሰብሎችን ምርታማነት ለማሳደግ  መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ አስተዋጾ እያደረጉ ናቸዉ። ከነዚህ ውስጥ አግራ የሚባለዉና መቀመጫዉን በናይሮቢ ያደረገዉ መንግሥታዊ ያልሆነ ደርጅት በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀስ ይችላል።
  • የቀስተ ዳመናዉ አብዮት፣ ይህ አብዮት እስካሁን ድረስ ተግባራዊ መሆኑ በትክክል ባይታወቅም ለአፍሪካ ግብርና እንደ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ የቀረበ ነበር። ሀሳቡን ያቀርቡት ምሁራን እንደሚሉት ለአፍሪካ ግብርና መፍትሔዉ አንድ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ እንደሆኑ ለማሳየት ነዉ። ምክንያቱም በአህጉሩ ያሉ ሰብሎች ዓይነት፣ የምርት ግብአት አጠቃቀም፣ ወዘተ የተለያየ ስለሆነ ነወ።

የኢትዮጵያ የስንዴ አብዮት፣ በቅርቡ ማለትም ሚያዚያ 12 ቀን 2011 አዲስ አበባ በሚገኘዉ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ የግብርና ሚኒስትር በመስኩ ከተሰማሩ ምሁራን ጋር ዉይይት አድርጎ ነበር። በዚህ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ባቀረቡት የመነሻ ጽሁፍና በመቀጠል በመሩት ስብሰባ ላይ እኔም ለመሳተፍ ዕድሉን አግኝቼ ነበር። በቀረበዉ ጽሁፍ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ስንዴን በማምረት ከአፍሪካ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ብትገኝም (ከግብጽና ሞሮኮ ቀጥሎ) የሀገሪቱን የስንዴ ፍላጎት ማርካት አልታቻለም። ስለዚህ ሀገሪቷ በያመቱ ስንዴ ወደ ሀገር ዉስጥ ለማስገባት ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሪ ታወጣለች። ይህንን ከዉጭ የምታስገባዉን ስንዴ በሂደት በመቀነስና ከአራት ዓመታት በኋላ (ማለትም እ.ኤ.አ. በ2023) ከነጭራሹ ለማቆም ዕቅድ ተይዟል። በዕቅዱ መሠረት ከአራት ዓመት በኋል የስንዴ ምርታማነትን በሄክታር ወደ አርባ ኩንታል ለማሳደግ ታስቧል። ከአንድ ሄክታር የሚመረተውም ይሁን በአጠቃላይ በሀገሪቱ ምርት ሊያድግ የሚችለዉ በዋናነት የመስኖ እርሻን፣ ኩት ገጠም እርሻን እና የምርት ግብአቶችን በመጠቀም እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን ለተግባርነቱም የምሁራንም ሆነ የሌሎች ባለድርሻ አካላት አስፈላጊነት ተገልጿል። በዚሁ መሠረት ምሁራንን ከሚኒስትሩ መሥሪያ ቤት ጋር የሚያገናኝ አማካሪ ቡድን እንደሚቋቋም ተውስኗል። በግብርና በኩል ከገበሬዎች ጋር በቅርበት የሚሰሩ ወደ ሰስሳ ሰባት ሺህ የሚጠጉ ባለሙያዎች በምርምር የተገኙ ዉጤቶችን ገበሬ ዘንድ እንደሚያደርሱና የድርሻቸዉን እንደሚያበረክቱ ተገልጿል። ይህ የመንግሥትን ዕቅድ በቅርቡ ከመገናኛ ብዙሀንም ሰምቻለሁ።

ማጠቃለያ

ከዚህ ቀደም “በምግብ ዋስትና ጥራትም ቢታከልበት” በሚል ርዕስ ሥር የሚከተለዉ ጽፌ ነበር። “ኢትዮጵያን ብቻ ብንመለከት የአለም የእርሻና የምግብ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየዉ አ.ኤ.አ. በ2016 ብቻ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የተለያዩ የእርሻ ዉጤቶችን ወደ ሀገር ዉስጥ አስገብታለች። ከነዚህ ውስጥ ከፍተኛዉን ድርሻ የሚይዙት የፓልም ዘይት 522.7 ሚሊዮን ዶላር፣ ስንዴና የስንዴ ዉጤቶች 305.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ስኳር 260.6 ሚሊዮን ዶላር እና ሩዝ 201.7 ሚሊዮን ዶላር ናቸዉ። ነገር ግን በተመሣሣይ ዓመት ቡና፣ ሰሊጥንና የቁም ከብቶችን ጨምሮ ወደ ውጭ ከምትልካችዉ የእርሻ ዉጤቶች ሀገሪቷ ባጠቃላይ ያገኘችዉ 2.2 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነዉ። ይህ የሚያሳየዉ ከሰማኒያ ፐርሰንት በላይ ህዝቧ በእርሻ ቢተዳድርም ከዚህ ሴክተር የሚገኘዉ ምርት የሀገሪቷን የምግብ ፍላጎት እንደማያሟላ ነዉ።”

ስለዚህ በግብርና ሚኒስቴር በኩል ሀገሪቱን በስንዴ ፍላጎት ራስን ለማስቻል የቀረበዉ ዕቅድ አስፈላጊና ወቅታዊም ነዉ። ለተግባሪነቱም ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል። ሀገሪቷ በስንዴና በሌሎች የእርሻ ምርቶች (ስኳርና ዘይትን ጨምሮ) ራሷን ከቻለች ደስታችን ወሰን አይኖረዉም። ምክንያቱም ከሰማንያ ፐርሰንት በላይ የሚሆነዉ ህዝባችን በግብርና እየተዳደረ ለዜጋዉ በቂ የሆነ የምግብ እህል አለመመረቱ ያሳዝናልና ነዉ። ከዚህ በታች የራሴን ምክር ለመለገስ እወዳለሁ።

1ኛ) ሁለት ሰብል በዓመት፤ በአንዳንድ ሥፍራዎች (በተለይም በመካከለኛዉና ታችኛዉ አዋሽ) ስንዴን ለመዝራት የታቀደዉ የጥጥ እርሻን ተከትሎ በዓመት ሁለት ሰብል ለማምረት ነዉ። ይህም እንደሚቻል የተረጋገጠዉ በቅርቡ ከዚሁ አካባቢ በሰፋፊ ማሳዎች በተደረጉ ሰርቶ ማሳያዎች ነዉ። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በጥጥ ለቀማና የስንዴ ማሳ ዝግጅት መካከል ያለዉ ጊዜ እጅግ አነስትኛ ይሆናል። ይህ ሲያጋጥም በቂ የማሳ ዝግጅት ሳደረግበት ስንዴ ይዘራል፣ የተዘራዉ ስንዴም በአግባቡ ሊያድግ አይችልም።

2ኛ) ትክክለኛ ዝርያ በትክክለኛ ሥፍራ፤ እንደሚታወቀዉ ሁሉ እያንዳንዱ ዝርያ የራሱ የሆነ ተስማሚ የአየር ንብረትና የአፈር ሁኔታ አለዉ። ለምሳሌ ጨዋማነት፣ አሲዳማነት፣ ድርቅ፣ ወዘተ የሚያጠቃቸዉ ሥፍራዎች የሚላኩት ዝርያዎች በሚላኩበት ሥፍራ ያሉትን እክሎች የሚቋቋሙ መሆን ይገባቸዋል።

3ኛ) ከፍተኛ ጥንቃቄ ለስንዴ በሽታዎች፤ ስንዴ ለበርካታ ዓይነት በሽታዎች የተጋለጠ ስብል ነዉ። በተለይ ዋግ ለሚባል በሽታ ተጠቂ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ጸድቅዉ የወጡ ዝርያውች እንኳ በአጭር ጊዜ በሽታዉንዉን የመቋቋም አቅም ሊያጡ ይችላሉ። ስለዚህ የስንዴ እርሻን ስናስፋፋ በስንዴ በሽታ ላይ ጥልቅ ዕውቅት ካላቸዉ ባለሙያዎች ጋር በቅርበት መሥራት ያስፈልጋል።

4ኛ) የምርት ግብአቶች በወቅቱና ለሁሉም ተደራሽ፤ የምርት ግብአቶች አስፈላጊነትና በወቅቱ ለገበሬው እንዲደርሱ ማድረግ አጠያያቂ አይደለም። ነገር ግን አንዳንድ ገበሬዎች በቂ መዋዕለ ንዋይ ላይኖራቸዉ ስለሚችል ብድር የሚያገኙበት መንገድ ቢመቻች። በተለይ ማዳበሪያና የመስኖ ዉሃን እንዴት እነስተኛ ገበሬዎች ዘንድ ሊደርስ እንድሚችል ዕቅድ ማዉጣት ያስፈልጋል። ከአርባና ሀምሳ ዓመታት በፊት በህንድ ሀገር ተግባራዊ የሆነዉ አረንጓዴዉ አብዮት ከተቸቸባቸዉ ነጥቦች ዋነኛዉ በድሃና ሀብታም ገበሬዎች መካከል ያለዉን የኢኮኖሚ ልዩነት ማስፋቱ ነዉ። ምክንያቱም ለመስኖና ሌሎች ግብአቶች ክፍያ በመፈጸም መጠቀም የቻሉት ሀብታሞቹ ገበሬዎች ብቻ ሲሆኑ ድሀዎቹ ገበሬዎች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ሊሆኑ አልቻሉም፤ ኑሮአቸዉም ብዙ መሻሻል አልታየበትም።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እንገናኝ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 1፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ አንድ ሚሊዮን ፍጥረታት ሊጠፉ 2 !!!

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

አንድ ሚሊዮን ፍጥረታት ሊጠፉ!!!

ክፍል ሁለት

በክፍል አንድ ጽሁፌ እ.ኤ.አ. ሜይ 6 ቀን 2019 IPBES በሚባል ዓለም አቀፍ ድርጅት ይፋ የሆነዉን በብዝሀ ህይወት ላይ ያትኮረ ነገር ግን አስደንጋጭ የሆን ሪፖርት ባጭሩ አቅርቤ ነበር። በዛሬዉ ጽሁፌ ስለ አህጉራችን አፍሪካ በዝርዝር ከቀረቡት መካከል የተወሰኑትን ለማሳያነት አቀርባለሁ። በመጨረሻም የራሴን ማጠቃሊያ ከትቤ ጽሁፌን እደመድማለሁ።

ድርጅቱ ከላይ በተጠቀሰዉ ዕለት ለህዝብ ይፋ ያደረገዉ ሪፖርት መነሻ ያደረገዉ ጥቂት ቀደም ብሎ በድርጅቱና በአጋሮቹ በታተሙ ወደ ስምንት የሚደርሱ በጥናት ላይ የተመረኮዙ ሥራዎች ላይ ነዉ። ከስምንቱ ሥራዎች አንዱ በአፍሪካ ላይ ያተኮረ ነዉ። ይህ በአፍሪካ ላይ ያተኮረዉ ሪፖርት እንደ ሀገሮቹ ቅርበት፣ የአየር ንብረት ተመሳሳይነትና የብዝሀ ሕይወት ሁኔታ አህጉሪቷን በአምስት ዋና አካባቢዎች ከፍሎ በተለያዩ መለኪያዎች ያሳያል። እነዚህ አምስት ክፍሎች ሰሜን አፍሪካ፣ ምዕራብ አፍሪካ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ደቡባዊ አፍሪካ እና ምሥራቅ አፍሪካና በአካባቢዉ ያሉ ደሴቶች ናቸዉ። እነደሚታወቅዉ ሀገራችን በመጨረሻ በተገለጸዉ ክፍል ውስጥ ትካተታለች። ሪፖርቱ ከዚህ በታች በተገለጹት ነጥቦች ሥር አህጉሪቷ አሁን ያለችበትን ሁኔታና የወደፊት ዕድሏን ይገመግማል። ሆኖም ግን በጽሁፌ ጥቂቶቹን ብቻ እገልጻለሁ።

አፍሪካ ያላት የተፈጥሮ ጸጋ

  • አህጉሪቷ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ብዝሀ ሕይወት አላት
  • ከሌላዉ የዓለማችን ክፍል ሲወዳደር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ግዙፍ አጥቢ እንስሳት የሚኖሩበት አህጉር ነዉ።እነዚህ ግዙፍ እንስሳት እንድ ጉማሬ፣ ዝሆን፣ ጎሽ እና ቀጭኔን የመሳሰሉትን ያካትታሉ።
  • ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ የአህጉሯ ህዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የዚህ ብዝሀ ሕይወት ተጠቃሚ ነዉ
  • ቢሆንም አፍሪካ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋ በአግባቡ አልተጠቀመችም
  • በአሁኑ ጊዜ በሰፊዉ በጥቅም ላይ ከዋሉት ሰብሎች መካካል እንደ ስንዴ፣ ገብስ፣ ዳጉሣ፣ ማሽላ፣ ጤፍ፣ ቡና ወዘተ መገኛቸዉ ወይም መነሻቸዉ አፍሪካ ነዉ
  • የራሴ ማስታወሻ፣ ርፖርቱ የሀገራችንን ጤፍን በተመለከተ በምግብ ዋስትና የሚኖረዉን ከፍተኛ አስተዋጾ ከመግለጹም በተጨማሪ በሥዕል የተደገፈ መረጃም አቅርቧል። ሪፖርቱ ጤፍ በዉስጡ የያዛቸዉ ለሰዉነታችን ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮች መጠን ያሳያል። ቢሆንም በዚህ ሪፖርት መሠረት በ100 ግራም የጤፍ ፍሬ ውስጥ ያለዉ የፕሮቲን መጠን 3.87 ግራም ብቻ እንደሆነ ቢያሳይም ከዚህ በፊት የታተሙ ጽሁፎች እንደሚያሳዩት ግን በተመሳሳይ የጤፍ ፍሬ ክብደት ውስጥያለዉ የፕሮቲን መጠን 13 ግራም እንደሆነና ይህም በስንዴ ዉስጥ ካለዉ የፕሮቲን መጠን ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ነዉ።

አፍሪካ የሚደርስባት ጫና

  • ወደ 20% የሚጠጋ ወይም 6.6 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሆን የአፍሪካ መሬት ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጧል። ዋና ምክንያቶቹም የአፈር መሸርሸር፣ የመሬት ጨዋማነት፣ የአፈር ብክለት፣ የዛፎች መቆረጥና የአፈር ለምነት መቀነስ ናቸዉ።
  • በአሁኑ ጊዜ በአህጉሯ የሚኖረዉ 1.25 ቢሊዮን ህዝብ እ.ኤ.አ. በ2050 (ማለትም ክ31 ዓመታት በኋላ) በእጥፍ ያድጋል። በከተማ የሚኖረዉ የአህጉሯ የህዝብ ቁጥርም ከላይ በተገለጸዉ ጊዜ በሦስት እጥፍ ያድጋል ተበሎ ይጠበቃል። አስፈላጊ የሆኑ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ካልተነደፉና በተግባር ላይ ካልዋሉ በብዝሀ ሕይወትና በሌሎች ሴክተሮች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና ይፈጥራል።
  • የአየር ንብረት ለውጥ በአህጉሪቱ ባሉ የተክሎችም ሆነ የእንስሳት ብዝሀ ሕይወት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ዉጤት እንደሚያመጣ ይጠበቃል። በዚሁ መሠረት በአማካይ ወደ እስከ 25% የሚጠጋ የአህጉሯ ብዝሀ ሕይወት ለአደጋ ይጋለጣል።
በሥዕሉ እንደሚታየዉ በሆራ ሀይቅ አካባቢ (ቢሾፍቱ) በአፈር መሸርሸርና በአካባቢዉ ባለዉ ንጣፍ ድንጋይ ምክንያት አብዘኛዉ  የዛፉ ሥር ለአደጋ ተጋልጧል። ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ

አፍሪካ ያላት ተስፋ

  • የአፍሪካ ህብረት የነደፋቸዉን የተለያዩ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ተፈጻሚ ለማድረግ የማህበሩ አባል ሀገራት  በትኩረት እየሠሩ ይገኛሉ።

ማጠቃሊያ፣ ይህ የአንድ ሚሊዮን ፍጥረቶቻችን ሊጠፉ እንደሆነ ያበሰረዉ አስደንጋጭ ዜና በመላዉ ዓለም በሚገኙ መንግሥታትና ሚዲያዎች ከፍተኛ ሽፋን አግኝቶ ነበር። በሀገራችን ያሉ ሚዲያዎች በዚህ አሳሳቢ በሆነውና በበርካታ ፍጥረቶቻችን ላይ የተጋረጠዉን አደጋ የሚገልጽ ሪፖርት ምን ያህል ትኩረት እንደሰጡትና ህብረተሰባችንም ምን ያህል ግንዛቤ እንዳገኘ ማወቅ አልቻልኩም። በርግጥ የዚህ ሪፖርት ይፋ መሆንን የኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ በድህረ ገጹ ላይ አውጥቶታል።

በብዝሀ ሕይወት እንክብካቤ የሚኖረን አመለካከትም ሆነ አስተዋጽኦ ትንሽ ከሚመስል ነገር ግን ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊኖረዉ ከሚችል ነገር መጀመር ይኖርብናል። እንደሚታወቀዉ ላስቲክ ወይም ፌስታል በቀላሉ ወደ አፈርነትም ሆነ ወደ ሌላ ነገር ስለማይለወጥ በየብስም ሆነ በባህር ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት ይመገቡታል። በብዝሀ ሕይወትም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። በዚህ መሠረት እስካሁን ድረስ በ127 ሀገሮች ውስጥ በፌስታል አጠቃቀም ላይ ህግ ወጥቷል፡ ከአፍሪካ እስካሁን ድረስ በፌስታል ላይ ማዕቀብ ያደረጉ አገሮች 34 የደረሱ ሲሆን በቅርቡ ዕገዳዉን የተቀላቀለችዉ ታንዛኒያ ናት። ተግባራዊ ያደረገችዉም ከአምስት ቀናት በፊት እ.ኤ.አ. ከጁን 1፣ 2019 ጀምሮ ነዉ።ኬኒያ ከሁለት ዓመት በፊት ባወጣችዉ ጠንከር ያለ ህግ በግልጽ እንዳስቀመጠችዉ ከላስቲክ የተሠራ ከረጢት ያመረተም ሆነ የሸጠ እንዲሁም የተጠቀመ 1.1 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ቅጣት ወይም የአራት ዓመታት እስር ይጠብቀዋል። በታንዛኒያ ቅጣቱ ፌስታል ይዞ ለተገኘ 2,487 ብር ወይም የአንድ ሣምንት እስር ሲሆን ላስቲኩን ላመረተ ደግሞ 13.3 ሚሊዮን ብር ወይም የሁለት ዓመት እስር ነዉ። የታንዛኒያ ፕሬዘዳንትም ለህዝባቸዉ ምሳሌ ለመሆን በትላንትናዉ ዕለት በሀገራችን እንጠቅም የነበረዉን ከቃጫ የተሠራ ዘንቢል ይዘዉ ሲገበያዩ ታይተዋል። በሀገራችን የነበሩት እነዚያ ቆንጆ ዘንቢሎች ፍጥረታቶቻችንን ለማጥፋት ቆርጦ በተነሣዉ ፌስታል ከተተኩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህ ብቻም ሳይሆን ፌስታሎቹ በየሥፍራዉ ወድቀዉ አካባቢያችንን ከማቆሸሽ አልፈው በቂ የግጦሽ መሬት ሳያገኙ ለሚንከራተቱት ለማዳ እንስሳዎችንም ጠንቅ እየሆኑ ነዉ። ታዲያ አብዘኛዉ የዓለም ህዝብ ሊያያቸዉ እንኳ እየተጠየፈ ባለዉ ፌስታል ላይ መቼ ነዉ እርምጃ የምንወስድበት? በማጠቃለዬ የፌስታሉ ነገር ትኩረቴን ሳበዉ እንጂ የብዝሀ ህይወት እንክብካቤና የሌሎች ተዛማች ሥራዎች የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ማሳትፍ ያለበት ሲሆን ይህም መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ይጨምራል።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እንገናኝ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ግንቦት 28፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ አንድ ሚሊዮን ፍጥረታት ሊጠፉ 1 !!!

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

አንድ ሚሊዮን ፍጥረታት ሊጠፉ!!!

ክፍል አንድ

የዛሬዉ ጽሑፌ የሚያተኩረዉ ከአንድ ወር በፊት እ.ኤ.አ. ሜይ 6 ቀን 2019 IPBES በሚል ምህጻረ ቃል የሚታወቀዉና በብዝህ ሕይወትና አካባቢ ላይ የሣይንስ ፖሊሲ መድረክ ሆኖ በሚያገለግለዉ ዓለም አቅፍ ድርጅት ይፋ በሆነዉ አስደንጋጭ ሪፖርት ዙሪያ ነዉ። የዚህ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤቱ በቦን ጀርመን ቢሆንም በተወሰኑ የዓለማችን ክፍሎች መለስተኛ ቢሮ አላቸዉ። ይህ በበቂ መረጃ ላይ ተመርኩዞ የቀረበዉ ሪፖርት የድርጅቱ አባል የሆኑ 128 ሀገራት የተወከሉቡት ሲሆን ኢትዮጵያም በብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክቴር (ዶክተር መለሰ ማርዮ) እና ምክትል ዋና ዳይሬክቴር (ዶክተር ፈለቀ ወልደየስ) ተወክላለች። ከዚህ በተጨማሪ የአፍሪካ አህጉርን በመወከል በቢሮ ደረጃ እንዲሳተፉ ከተመረጡት ሶስት ታዋቂ ግለሰቦች መካከል በመስኩ ከፍተኛ አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ የሚገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰዉ አንዱ ናቸወ። ስለ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ከዚህ ቀደም የቡናችን ነገር እጅግ ያሳስባል በሚለዉ ክፍል አንድ ጽሑፌ በአጭሩ ገልጬ ነበር። ከዚህ በተረፈ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተዉጣጡ በመስኩ የታወቁ ባለሙያዎች በሪፖርቱ ላይ ተሳትፎ አድርገዋል።

ሪፖርቱ ለማመን የሚያስቸግሩ ነገር ግን ትክክለኛ የሆኑ መረጃዎችን አካቷል። የቀረበዉ መረጃ በርካታ ቢሆንም በዚህ አጭር ጽሑፌ የተወሰኑትን ብቻ አቅርቤአለሁ። የሪፖርቱን ሙሉ አካልና ተዛማች መረጃዎች ከዚህ ቀጥሎ ባለዉ ሊንክ ማግኘት ይቻላል https://www.ipbes.net/news/ipbes-global-assessment-preview

ይህ ጥልቅ ምርምር የተካሄደበት ሪፖርት በሚቀጥሉት ርዕሶች ሥር እስካሁን ያጋጠመዉንና ወደፊትም ሊያጋጥሙ ይችላሉ ተብሎ የሚገመቱትን በዝርዝር አቅርቧል። እነዚህም ፍጥረታት፣ ምግብና እርሻ፣ ውቅያኖስና ዓሣ፣ ጫካ፣ ማዕድን ማዉጣትና ኢነርጂ፣ የከተሞች መስፋፋትና ሶሽዮ ኢኮኖሚክስ፣ ጤናና የአየር ንብረት ለዉጥ ናቸዉ። ከዝርዝሮቹ ውስጥ ለዛሬዉ ጽሁፌ ጥቂቶቹን ከዚህ በታች አቀርባለሁ።

ከላይ በሥዕሉ የሚታየዉ በደህና ሁኔታ ተጠብቆ የሚገኘዉ የኮኒዝ ጫካ ሲሆን የሚገኘዉም በበርን ካንቶን በስዊዘርላንድ ሀገር ነዉ። ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ

ፍጥረታትን በተመለከተ

  • ባሁኑ ጊዜ ስምንት ሚሊዮን ዓይነት የተክል እና እንስሳት (ነፍሳትን ጨምሮ) በምድር ላይ ይገኛሉ
  • ከነዚህ ዉስጥ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚገመቱት በቅርቡ ከምድር ገጽታ እንደሚጠፉ ይጠበቃል!!!
  • በየብስ ከሚኖሩት 5.9 ሚሊዮን ፍጥረታት ውስጥ ወደ 500 ሺህ የሚጠጉት በቂ መኖሪያ አይኖራቸዉም
  • በቂ ጥናት ከተደረገባቸዉ ፍጥረታት መካከል በአማካይ 25%ቱ የመጥፋት አደጋ ያጋጥማቸዋል
  • በ21 ሀገሮች በተደረገዉ ጥልቅ ጥናት መሠረት አደገኛ የሆኑና ኢንቬዚቭ ተብለዉ የሚጠሩ አረሞች ብዛት ባለፉት 50 ዓመታት ብቻ በ70% ጨምሯል

ምግብና እርሻን በተመለከተ፤

  • እ.ኤ.አ. ከ1980 እስክ 2000 ባሉት 20 ዓመታት ብቻ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ መሬት ወደ እርሻ ተለዉጧል
  • የአደገኛ አየር ብክለት መንስኤ ተብለወ ከሚታወቁት በተለይ ለግሪን ሀዉስ ጋዝ መንስኤ ይሆናሉ ተብለው ከተለዩት ውስጥ ወደ 25% የሚጠጉት መነሻቸዉ እርሻ ነዉ

ጫካን በተመለከተ

  • ወደ 50% የሚጠጋ የእርሻ መሬት እንዲስፋፋ የተደረገዉ ጫካን በመመንጠር ነዉ
  • እ.ኤ.አ. ከ1990 እስከ 2015 ባሉት 25 ዓመታት ብቻ ወደ 290 ሚሊዮን የሚጠጋ የተፈጥሮ ደን ተመንጥሯል
  • እ.አ.ኤ. በ2017 ብቻ ዛፍን በመቁረጥ አራት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሆነ ጠዉላ ተመርቷል
  • ከሁለት ቢሊዮን በላይ የሆነ የዓለማችን ህዝብ ምግብ ለማብሰልም ሆነ ለሌላ አገልግሎት እንጨትን ይጠቀማል

ማዕድን ማዉጣትና ኢነርጂን በተመለከተ

  • ምንም እንኳ ከአንድ ፐርሰንት በታች የሆነ የዓለማችን መሬት ለማዕድን አገልግሎት ቢዉልም ይህ ሴክተር በብዝሀ ሕይወት፤ በአየር ብክለት፣ በዉሃ ጥራት እና በሰዉ ጤና ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጎን አለዉ
  • በዓለም ወደ 17 ሺህ የሚጠጉና በ171 ሀገራት ያሉ ትላልቅ የማዕድን የቁፋሮ ሥፍራዎች ይገኛሉ

ጤናን በተመለከተ

  • በያመቱ ከ300 እስከ 400 ሚሊዮን ቶን የሚሆን ከፋብሪካዎች የሚወጣ መርዛማም ሆነ ሌላ ዓይነት ቆሻሻ ሳይታከም ወደ ወንዝ ወይም ሌላ የዉሃ አካል እንዲደባልቅ ይደረጋል
  • ወደ 40% የሚሆን የዓለማችን ህዝብ ንፁህ የመጠጥ ዉሃ አያገኝም
  • ባለፉት 40 ዓመታት ፕላስቲክን በመጠቀም የደረሰዉ ብክለት በአሥር እጅ አድጓል

የአየር ንብረት ለዉጥ በተመለከተ፤

  • የዓለማችን አማካይ የአየር ሙቅት ከፍ ብሎ ታይቷል
  • የአየር ምቀቱ በ2 ሴንቲ ግሬድ ሲያድግ 5% የሚሆኑ ፍጥረታት ለአደጋ ይጋለጣሉ፤ ሙቀቱ በ4.3 ሴንቲ ግሬድ ከጨመረ ደግሞ ወደ 16% የሚጠጉ ፍጥረታት ከነጭራሹ ከዓለማችን ሊጠፉ ይችላሉ
  • ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ብቻ የባህር ወለል በያመቱ የሶስት ሚሊ ሜትር ከፍታ አስመዝግቧል
  • እ.ኤ.አ. ከ1980 ጀምሮ ባሉት 40 ዓመታት ብቻ የግሪ ሀዉስ ጋስ ብክለት በእጥፍ አድጓል

በክፍል ሁለት ጽሑፌ በሪፖርቱ አህጉራችንን በተመለከተ የተዘገበዉንና የራሴንም ማጠቃለያ አቀርባለሁ።

እስከዚያዉ በቸር ይግጠመን።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ግንቦት 27፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ ዕንቁ ዝርያዎቻችንን ለመጪዉ ትዉልድ 2

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ዕንቁ ዝርያዎቻችንን ለመጪዉ ትዉልድ

ክፍል ሁለት

በክፍል አንድ ስለ ብዝሀ ሕይወት ጥቅምና እነርሱን ለመጪዉ ትዉልድ ለማቆየት ኢትዮጵያን ጨምሮ ባንዳንድ ሀገራት በመደረግ ላይ ያሉ ተሞክሮዎችን ገልጬ ነበር። በዛሬዉ ጽሁፌ ደግሞ በዓለም የሚገኙ የተክሎች ብዝሀ ሕይወት ጥራታቸው ሳይቀንስ ለበርካታ ዓመታት ሊጠበቁ ይቻላል ተብሎ ሰለታመነበት የስቫልባርድ ጥብቅ የዘር ባንክ (Svalbard Seed Vault) ለመግለጽ እወዳለሁ።

አንባቢያን በቀላሉ እንዲረዱ የዛሬዉ መጣጥፌን በጥያቄና መልስ መልክ አቀርባለሁ።

የስቫልባርድ የዘር ማከማቻ የት ይገኛል? የስቫልባርድ የዘር ማከማቻ የሚገኘዉ በኖርዌ ግዛት ሥር ቢሆንም ከሀገሪቷ መዲና ከሆነችዉ ከኖርዌ እጅግ ርቆ በአንድ ደሴት ላይ ይገኛል። የቦታዉ ቅርበትም ለሰሜን ዋልታ ሲሆን ለዚያ ያለዉ ርቀትም አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ያህል ብቻ ነዉ።

የዓለማችንን ምርጥ ዘሮች ለማስቀመጥ ስቫልባርድ ለምን ተመረጠ? ይህ ሥፍራ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘር ባንክ ሆኖ የተመረጠበት በርካታ በጎ ጐኖች ቢኖሩትም የሚከተሉት ግን በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። 1ኛ) ቦታው ፐርማፍሮስት የተባለ በተፈጥሮ ዓመቱን በሙሉ እጅግ ቀዝቃዛ የሆነ ሥፍራ ሲሆን 120 ሜትር በተራራ ሥር ተቆፍሮ የተዘጋጀና ያለተጨማሪ ማቀዝቀዣ ዘርን ለረጅም ጊዜ ማስቀመጥ በመቻሉ፤ 2ኛ) ቦታው ሰዉ ሰራሽ ከሆኑ አዳጋዎች እጅግ የራቀ በመሆኑ፤ 3ኛ) በአካባቢዉ የሚሊታሪ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ እገዳ የተጣለበት በመሆኑ፤ 4ኛ) በአካባቢዉ የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ መኖሩ እና 5ኛ) አካባቢዉ ከመሬት መንቀጥቀጥና ከመሳሰሉት የጂኦሎጂ እቅሰቃሴዎች የራቀ በመሆኑና የሬዴሽን መጠኑም አነስትኛ በመሆኑ ናቸዉ።

ከአንድ መቶ ሜትር በላይ በተራራ ዉስጥ ተቆፍሮ የተሰራዉና በዓለም ትልቁና ቀዝቃዛዉ የስቫልባርድ ጂን ባንክ የዉጭ ዕይታ ይህንን ይመስላል።

የስቫልባርድ የዘር ማከማቻ መቼ ሥራዉን ጀመረ? ይህ የዘር ባንክ ተመርቆ ሥራውን የጀመረዉ እ.ኤ.አ. ፌብሪዋሪ 26 በ2008 ነበር። በተመረቀበት ወቅትም ሁለት መቶ ሺህ ዓይነት ዝርያዎችን ለመቀበል ችሏል።

የስቫልባርድ የዘር ማከማቻ ስፋት ምን ያህል ነዉ? ሶስት ትልልቅ የዘር ማስቀመጫ ክፍሎች ዘንድ የሚደረሰዉ 145 ሜትር የሆነ ተራራ ሥር የተቆፈረ ዋሻ ከታለፈ በኋላ ነዉ። የእያንዳንዱ የዘር ማስቀመጫ ክፍል ርዝመት 27 ሜትር፣ ጎኑ 10 ሜትር እና የጣራዉ ከፍታ 6 ሜትር ነዉ።

በዘር ባንኩ ዘሮች በምን ዓይነት ሙቀት እንዲቀመጡ ይደረጋል? እያንዳንዱ የዘር ዓይነት በታሽገ ዕቃ ዉስጥ ከተደረገ በኋላ ሙቀቱ ከዜሮ በታች 18 ሴንቲ ግሬድ በሆነ ክፍል ዉስጥ እንዲቀመጥ ይደረጋል።

የስቫልባርድ የዘር ማከማቻ ምን ያህል ዘር ሊያስቀምጥ ይችላል? ይህ የዘር ባንክ በአለማችን ትልቁ ሲሆን 4.5 ሚሊዮን በባር ኮድ የተዘጋጁ የዘር ዓይነቶች በተገቢዉ መልክ እንዲያስቀምጥ ተደርጎ የተሠራ ነዉ። ከእያንዳንዱ የዘር ዓይነት 500 ፍሬ የሚያስቀምጥ ሲሆን በድምሩ 2.25 ቢሊዮን ፍሬ ማስቀመጥ ይችላል።

እስካሁን ምን ያህል ዘር በስቫልባርድ የዘር ማከማቻ ተቀምጧል? እስካሁን ድረስ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የዘር ዓይነቶች ተከማችተዉ ይገኛሉ።

ዘሮቻቸዉን በማስቀመጥ እነማን ተሳትፈዋል? እስካሁን ድረስ 76 ሀገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዘሮቻቸዉን ወደዚህ የዘር ባንክ በመላክ እንዲቀመጥላቸዉ አድርገዋል። ከታች በስዕሉ እንደሚታዉ በዓለም አቀፍ የእርሻ ምርምር ማዕከላት ሥር የታቀፉት 11 ድርጅቶች ከፍተኛ የሆነዉን የብዝሀ ሕይወት በማበርከት የቀዳሚነቱን ቦታ ይዘዋል። እነዚህ 11 ድርጅቶች ለጅን ባንኩ ያስረከቡት የዘር ዓይነት በኃላፊነት ከሚሰሩባቸዉ ሰብሎች ጋር የተያያዙ ናቸዉ። ለምሳሌ እያንዳንዳቸዉ ከመቶ ሺህ በላይ የዘር ዓይነቶች ለጂን ባንኩ የላኩትን ብናይ CIMMYT የሚባል ድርጅት 158 ሺህ የስንዴና የበቆሎ ዝርያዎችን በመላክ የቅድሚያዉን ሥፍራ ሲይዝ፣ IRRI የሚባል ድርጅት 125 ሺህ የሩዝ ዝርያዎችንና ICRISAT የሚባል ድርጅት ደግሞ 111 ሺህ የሚደርሱ የአምስት ዓይነት ዝርያዎችን በመላክ ተከታዩን ሥፍራ ይዘዋል። የሀገራትን አስተዋጽኦ ከተመለከትን ደግሞ 120 ሺህ ዝርያዎችን በመላክ አሜርካ ስትመራ ተከታዩን ሥፍራ ጀርመን፣ አዉስትራሊያና ካናዳ ይዘዋል።

ከተለያዩ ዓለም አቀፍም ሆነ ብሔራዊ ድርጅቶች በአደራ እንዲቀመጡ ወደ ታዋቂዉ የስቫልባርድ የዘር ማስቀመጫ ባንክ የተላኩ ዝርያዎች ብዛት። ጥሬ መረጃዉ ከዚህ ቀጥሎ ካለዉ ዌብሳየት የተገኘ ሲሆን ለዚህ መጣጥፍ በሚያመች መልኩ በጸሐፊዉ ተቀነባብሯል https://www.seedvault.no

ዘሮቻቸዉን ወደ ባንክ በመላክ የአፍሪካ ተሳትፎ ምን ይመስላል? በግልጽ እንደሚታየዉ የአፍሪካ ተሳትፎ እጅግ አነስተኛ ነዉ። ሳዴክ በሚባል መጠሪያ የሚታወቁት በደቡባዊ አፍሪካ አካባቢ ያሉ አገሮች በሦስት ዙር ከላኩት 4086፣ ኬንያ በሁለት ዙር ከላከችዉ 1314፣ ናይጄሪያ በሁለት ዙር ከላከችዉ 800 እና ኡጋንዳ በሁለት ዙር ከላከችዉ 777 ዓይነት ዝርያዎች በስተቀር ኢትዮጵያን ጨምሮ የሌላ አፍሪካ ሀገር ተሳትፎ አይታይም። የብዝሀ ሕይወቷን ባለመስነካት የምትታወቀዉ ብራዚል እንኳ ካላት የብዝሀ ሕይወት ጋር ተመጣጣኝ ባይሆንም 1319 ዓይነት ዝርያዎቿን ለዚህ ግዙፍና ዘመናዊ የዘር ባንክ አበርክታለች።

ዘሮቻቸዉን በስቫልባርድ ያስቀመጡ በሚፈልጉበት ወቅት መልሰዉ መውሰድ ይችላሉን? የዚህ ታላቅ የዘር ባንክ ዓይነተኛ ባህርይ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተሰባሰቡ ምርጥ ዝርያዎችን እጅግ ቀዝቃዛ በሆነ ሥፍራ በማስቀመጥ የዘሮቹን ዕድሜ ማራዘም ብቻ ሳይሆን አስቀማጮቹ ዘሮቻቸዉን በፈለጉበት ወቅት መልሰዉ መዉሰድ መቻላቸዉ ነዉ። ለዚሁም እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችለዉ ኢካርዳ በሚባል ስያሜ የሚታወቀዉንና ዝናም አጠር በሆኑ የዓለማችን ክፍሎች በምርምርና ልማት ላይ የሚሳተፍ ድርጅትን ነወ። ይህ ዓለም አቀፍ ድርጅት ከስምንት ዓመታት በፊት በሶሪያ ጦርነት ሳይቀሰቀስ ዋና መሥራያ ቤቱም ሆነ የዘር ባንኩ ይገኙ የነበሩት አሌፖ በምትባል የሀገሪቷ ትልቅ ከተማ ዉስጥ ነበር። ሆኖም አሌፖ አንዷ የጦርነቱ ማዕከል ስለነበረች ኢካርዳ ሀገሪቱን ለቆ ለመዉጣት በቅቷል። ሆኖም ጦርነቱ ከመከሰቱ ቀደም ብሎ ኢካርዳ ያለዉን የዘር ባንክ ወደ ስቫልባርድ ጂን ባንክ ሰለላከ ዘሮቹ ከአደጋ ሊተርፉ ችለዋል። ኢካርዳም ከደረሰበት አደጋ አገግሞና የምርምር ሥፍራዎቹን በቱርክ፣ ሞሮኮና ኢትዮጵያ ባስቀጠለበት ወቅት ከዚህ ቀደም በስቫልባርድ ያስቀመጠዉን ዘር በማስመጣት የምርምር ሥራዉ እንዳይስተጓጓል አድርጓል።

ማጠቃለያ፣ ለወደፊቱ ትውልድ ጠቃሚ የሚሆን የብዝሀ ህይወትን በጥንቃቄ አስጠብቆ በማስተላፍ ካለዉ ድርሻ አንፃር አንዳንዶች የስቫልባርድ የዘር ባንክን ከኖህ መርከብ ጋር ያመሳስሉታል። ምንም እንኳ በርካታ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ምርጥ ዝርያዎቻቸዉን በዚህ በዓለም ቀዝቃዛው የጂን ባንክ እንዲጠበቅላቸዉ ቢያደርጉም የአህጉራችን ተሳትፎ እጅግ አነስተኛ ነዉ፤ የሀገራችንማ ከነጭራሹ የለም። ዕንቁ ዝርያዎቻችንን ለመጪዉ ትዉልድ ለማስተላለፍ ያለንን ብዝህ ሕይወት በዚህ በተመሰከረት የዘር ባንክ ማስቀመጥ የለብንም ትላላችሁን? በኔ እምነት በዚህ ባንክ ዘሮቻችንን ብናስቀምጥ እናተርፋለን እንጂ አንከስርም። ይህንን ተግባራዊ ካደረግን ዕንቁ ዝርያዎቻችን በተፈጥሮም ሆነ ሰዉ ሰራሽ ምክንያት ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን ተሻግረዉ ለወደፊቱ ትዉልድ ሊደርሱ ይችላሉ። ስለዚህ ለተግባርነቱ ከአሁኑ መንቀሳቅስ አለብን እላለሁ።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እንገናኝ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ግንቦት 25፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ ዕንቁ ዝርያዎቻችንን ለመጪዉ ትዉልድ 1

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ዕንቁ ዝርያዎቻችንን ለመጪዉ ትዉልድ

ክፍል አንድ

በአሁኑ ወቅት 250 የሰብሎች ዓይነቶች በጥቅም ላይ ይዉላሉ። ቢሆንም ግማሹን የዓለም ሕዝብ የምግብ ኮታ የሚሸፍኑት አራት ሰብሎች ብቻ ናቸዉ። እነርሱም ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሩዝ እና ድንች ናቸዉ። ቢሆንም በመልማት ባሉ ሀገሮች በሰፊዉ በጥቅም ላይ የዋሉ እንደ ማሽላ፣ ዳጉሣ፣ ካሳቫ፣ ጤፍ፣ ወ.ዘ.ተ. ሚናም መዘንጋት የለብንም።

የብዝሀ ሕይወት ወይም ባዮዳይቨርሲቲ መኖር ለአንድ ሀገር ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል። ከጥቅሞቹም ዉስጥ ለምግብ ዋስትና በተለይም በቂና ጠቃሚ ንጥረ ነገር ያለው ምግብ እንዲኖር ማስቻል ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ ብዝሀ ሕይወት በአየር ንብረት ለውጥም ሆነ በሌላ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ የሰብሎቻችንን ዕድገትም ሆነ ምርታማነት የሚፈታተኑትን ማነቆዎች እንድንጋፈጥ ያስችለናል። እነዚህ የምርት ማነቆዎችም በዝናም እጥረት የሚመጣ ድርቅን እና በተለያዩ ነፍሳት የሚከሰቱ በሽታውን ያካትታሉ። በዚህ መሠረት የአንድ ሰብል ዓይነትን ብቻ ብንወስድ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ብዝሀ ሕይወት ቢኖረዉ ባንድ አጋጣሚ የሚከሰት የምርት ማነቆን (ለምሳሌ በሽታ፣ ተባይ፣ ድርቅ) የሚቋቋም ዝርያ የማግኘት ዕድላችን ከፍተኛ ነዉ።

በሌላ በኩል የብዝሀ ሕይወት መመናመን ወይም ባንዳንድ ሥፍራዎች ከነጭራሹ መጥፋት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ለማስረጃ ያህል ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች የጠፉትን የሰብል ዝርያዎች ከዚህ በታች ማየት ይቻላል።

  • ከዓለም በአማካይ 75% የሰብል ዝርያዎች፣
  • ከቻይና ወደ 90% የሚጠጉ የሩዝ ዝርያዎች፣
  • ከሜክሲኮ ወደ 80% የሚጠጉ የበቆሎ ዝርያዎች፣
  • ከህንድ ወደ 90% የሚጠጉ የሩዝ ዝርያዎች፣
  • ከአሜሪካ ወደ 90% የሚጠጉ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎች ናቸዉ።

እዚህ ላይ ‘’ዝርያ’’ የሚለዉን ቃል የተጠቀምኩት ለረጅም ጊዜ ምርምር ከተደረገባቸዉ በኋላ በገበሬ ማሣ እንዲዘሩ ከመንግሥት ፍቃድ የተሰጣቸዉን ዝርያዎች ሳይሆን በተፈጥሮ የሚበቅሉትንና በእንግሊዘኛዉ አጠራር accession ብለን የምንጠራዉን ለማመልከት ነዉ።

በዓለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ ያሽቆለቆለዉን የብዝሀ ሕይወት ለመታደግና ይህ መጥፎ ክስተት ወደፊት እንዳያጋጥም እያንዳንዱ ሀገር በሀገሩ የሚገኙትን የተለያዩ ዓይነት ተክሎች፣ እንስሳት እና የሌሎች ብዝሀ ሕይወት እንዲጠበቅ የራሳቸዉን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። እነዚህ ከተለያዩ ሥፍራዎች ተሰብስበዉ ባንድ ሥፍራ ለረጅም ጊዜ የሚቀመጡት ናሙናዎች በተወሰነላቸዉ የሙቀትና የአየር ርጥበት መሆን ይገባል። ለምሳሌ የዘር ናሙና ከሆነ የሙቀት መጠኑ ከዜሮ ሴንቲ ግሬድ በታችና የአየር ርጥበቱም እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ክፍል ወይም ማስቀመጫ መሆን ይገባል። ይህ የተወሰነ የአየር ሙቀትና ርጥበት ሳያቋርጥ ተግባራዊ መሆን ይገባዋል። ያለበለዚያ የናሙናዎቹ ተመልሰዉ የመብቀል ሁኔታ አዳጋች ይሆናል፤  ረዥም ጊዜ የተለፋበት ሥራም ከንቱ ይሆናል።

ይህ እንዳይከሰት እያንዳንዱ ሀገር መጀመሪያ ናሙናዎችን በማሰባሰብ ከዚያም ከላይ በተገለጹት ተስማሚ ሥፍራዎች እንዲቀመጡ ያደርጋሉ። በዚህ ሁኔታ ናሙናዎቻችንን ረዘም ላለ ጊዜ የምናስቀምጥበት ሥፍራ ጂን ባንክ ይባላል። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም የዘሮቹ የመብቅል ችሎታ እንዳይዳከም ወይም ከነጭራሹ እንዳይጠፋ በመስክ ላይ በመዝራትና የተሰበሰበዉን አዲስ ዘር ወደ ጂን ባንክ እንደገና በመመለስ ለተጨማሪ ዓመታት እንዲቆዩ ያደርጓቸዋል።

ባሁኑ ጊዜ በዓለማችን ወደ 100 በሚጠጉ ሀገራት ወደ 1400 የሚጠጉ ጂን ባንኮች ይኖራሉ። እነዚሀም በአጠቃላይ ወደ 6.5 ሚሊዮን የሚጠጉ የተለያዩ ዝርያዎች ወይም አክሴሽኖች የያዙ ናቸዉ። በጂን ባንክ የሚቀመጥ እያንዳንዱ ናሙና የራሱ የሆነ መገለጫ እንዲኖረዉ አስፈላጊ ከሆኑ መረጃዎች ጋር አብሮ ይዘጋጃል። እነዚህ መረጃዎችም የፓስፖርት ዳታ ሲባሉ በዉስጣቸዉ ከሚያካትቱት ውስጥ ናሙናዉ ከየት እንደተገኘ ወይም እንድተሰበሰበ (የቦታዉን ትክክለኛ ሥፍራ) እና መቼ እንደተሰበሰበ ይገኝበታል።

በኢትዮጵያ ይህንን ሥራ በበላይነት የሚያስተባብረው እ.ኤ.አ. ብ1976 የተመሠረተዉና ስሙንና መዋቅሩን ከሶስት ጊዜ ያላነሰ የቀያየረዉና በአሁኑ መጠሪያዉ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት በመባል የሚታወቀዉ መንግስታዊ የሆነ ድርጅት ነዉ። ኢንስቲትዩቱ በተክሎች፣ በእንስሳት እና በጥቃቅን ነፍሳት ብዝሀ ሕይወት ላይ የሚሠራ ሲሆን ከተክሎች ደግሞ ለሰዉም ሆነ ለእንስሳት ምግብነት በሚያገለግሉና ለመድኃኒትም በሚዉሉ ተክሎች ላይ ትኩረት ያደርጋል። የኢንስቲትዩቱ መረጃ እንደሚያሳየዉ የተሟላ የፓስፖርት መረጃ ያላቸዉ 64 ሺህ ዓይነት ናሙናዎች በጂን ባንኩ በደህና ሁኔታ ተጠብቀዉ ይገኛሉ። ኢንስቲትዩቱ በአዲስ አበባ ካለው ትልቁ የጂን ባንክ በተጨማሪ በመቱ፣ ሀዋሳ፣ ሀረር፣ መቀሌ፣ ጎባ፣ ባህር ዳር እና አሶሳ የብዝሀ ሕይወት ማዕከላት አሉት። ከዚህ በተጨማሪ በፍቼ ሁለተኛዉ ወይም ዱፕሊኬት ጂን ባንክ የሚለዉን ያስተዳድራል። ይህ ዱፕሊኬት ጂን ባንክ የሚያገለግለው ባጋጣሚ በዋናዉ ጂን ባንክ ላይ መጥፎ ክስተት ቢያጋጥም ለመጠባበቂያነት እንዲያገለግል ተብሎ የታለመ ይመስለኛል። በዚሁ አጋጣሚ መግለጽ የሚያስፈልገዉ በዓለም ካሉ ወደ ስምንት ከሚጠጉ የአሁኖቹ ሰብሎች ከተገኙባቸዉ አካባቢዎች አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ ነዉ። በዚህ ‘’ኢትዮጵያ’’ ተብሎ በተሰየመዉ አካባቢ ከተገኙ ሰብሎች ዉስጥ ጤፍ፣ ቡና፣ እንሰት እና ኑግ በቀደምትነት ይጠቀሳሉ።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ የጤፍ ብዝሀ ሕይወት መካከል የተወሰኑት በሆለታ እርሻ ምርምር ማዕከል አድገዉ ይታያሉ። ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ

ከዚህ ከተገለጸዉ ዉጭ የተለያዩ ዓይነት ተክሎችን ብዝሀ ዘር በመስክ ላይም እንዲጠበቁ ይደረጋል። በዚሁ መሠረት እያንዳንዱ ሀገር የራሱ የሆኑ ብርቅዬና ለአደጋ ሊጋለጡ የደረሱትን ጭምር የሚያሳድጉበትና ለወደፊቱ የሚያቆዩበት ጋርደኖች ወካይ በሆኑ የሀገሪቱ ከፍሎች አለዉ። አንዳንዶቹ ጋርደኖች ደግሞ ከሀገራቸዉም አልፈዉ በሌላዉ ዓለምም ያሉ የተክል አይነቶችንም በመንከባከብ ለጎብኚዎች ያስተዋዉቃሉ። ከነዚህ ዉስጥ በዓለም ዝናን ካተረፉት መካከል በሪዮ ዴ ጃኔሮ ብራዚል የሚገኘዉ የጃርዲም ጋርደን፣ በኒዉዮርክ የሚገኘዉ የብሩክልን ጋርደን፣ በለንደን የሚገኘዉ የኪዉ  ጋርደን፤ በሲንጋፖር የሚገኘዉና እና በስድኒ አዉስትራሊያ የሚገኘዉ የሮያል ጋርደን ሊጠቀሱ ይችላሉ።

በዓለም ያሉ የዕፅዋት ጋርደኖችን የሚያስተባብር BGCI የሚባል ድርጅት እ.ኤ.አ. በ1987 ተመስርቶ መጠነ ሰፊ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል። በዚሁ ድርጅት አባልነት የታቀፉ በርካታ ጋርደኖች ሲኖሩ ከአፍሪካ በኡጋንዳ የሚገኘዉ የኢንቴቤ ጋርደን፣ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘዉ የኪርስቴን ቦሽ ጋርደን ሲሆኑ ከኢትዮጵያ ደግሞ በቅርቡ ተመርቆ የተከፈተዉ የአዲስ አበባዉ የጉለሌ ጋርደን እና በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ሥር የሚተዳደሩት የጂማዉና የሻሸመኔው ጋርደኖች ይገኛሉ።

በክፍል ሁለት ጽሑፌ በብዝሀ ህይወት ላይ የተደቀኑትን መጥፎ ክስተቶች በዘላቂነት ለመታደግ የመፍትሔ ሀሃብ ተብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቀረበዉንና ባሁኑ ወቅት የሚገኝበትን ሁኔታ ለማሳየት እሞክራሉሁ። እስከዚያው በቸር ይግጠመን።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ግንቦት 24፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የቡናችን ነገር እጅግ ያሳስባል 2

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የቡናችን ነገር እጅግ ያሳስባል

ክፍል ሁለት

የዓለም የእርሻና የምግብ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየዉ እ.ኤ.አ. በ2017 በአጠቃላይ በዓለማችን የተመረተዉ ቡና 155.4 ሚሊዮን ከረጢት ወይም ጆኒያ ነበር። በኩንታል ፋንታ ከረጢት ወይም ጆኒያ የሚለዉን ቃል የተጠቀምኩበት ምክንያት ቡና ባብዘኛው ገበያ ላይ የሚቀርበዉ 60 ኪ.ግ. በሚመዝኑ መያዣዎች ሲሆን ኩንታል የሚለዉ ቃል ደግሞ 100 ኪ.ግ. የሚመዝን ዕቃን ለመግለጽ ስለምንጠቀምበት ነዉ። ከላይ በተጠቀሰዉ ዓመት ቡናን በከፍተኛ ደረጃ በማምረት የታወቁት የላይኞቹ 10 ሀገራትና ያላቸዉ ድርሻ (በአጠቃላይ በዓለም ከሚመረተው ሲነጻጸር) የሚከተሉት ናቸዉ። 1ኛ) ብራዚል 28.7%፣ 2ኛ) ቬትናም 16.5%፣ 3ኛ) ኮሎምቢያ 8.1%፣ 4ኛ) ኢንዶኔሺያ 7.2%፣ 5ኛ) ሆንዱራስ 5.1%፣ 6ኛ) ኢትዮጵያ 5.1%፣ 7ኛ) ፔሩ 3.7%፣ 8ኛ) ህንድ 3.3%፣ 9ኛ) ጉቴማላ 2.6% እና 10ኛ) ኡጋንዳ 2.2%። በግልጽ እንደሚታየዉ በዓለም ከሚመረትዉ ቡና 45.2% የሚሆነዉ በብራዚልና እና በቬትናም መሆኑ ነዉ። ከሁሉ የሚያስገርመዉ በአሁኑ ውቅት በሁለተኛ ደረጃ የምትገኘዉ ቬትናም ወደ ቡና ማምረት ቢዝነስ የገባችዉ ባለፉት 25 ዓመታት ብቻ መሆኑ ነዉ። እዚህ ላይ መታየት የሚገባዉ እነዚህ ሀገራት ቡናን ማምረት ብቻ ሳይሆን ከሚያመርቱት ቡና ምን ያህሉን ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያገኙ ነዉ። እነዚህን ከፍተኛ የቡና አምራች ሀገሮችን በዚህ መሥፈርት ብናያቸዉ የሚከተለዉን እናገኛለን። ብራዚል 68.0%፣ ቬትናም 90.8%፣ ኮሎምቢያ 97.4%፣ ኢንዶኔሺያ 61.7%፣ ሆንዱራስ 65.2%፣ ኢትዮጵያ 33.9%፣ ፔሩ 69.1%፣ ህንድ 80.3%፣ ጉቴማላ 73.4% እና ኡጋንዳ 78.5% የሆነዉን የአጠቃላይ ምርታቸዉን ወደ ውጭ ገበያ ይልካሉ፤ የዉጭ ምንዛሪም ያገኙበታል። በግልጽ እንደሚታየዉ ከቡና ምርቷ እጅግ ዝቅተኛ የሆነዉን ድርሻ ወደ ውጭ ሀገር የምትልከዉ ኢትዮጵያ ናት። ይህም ሊሆን የቻለዉ የሀገር ዉስጥ ፍጆታ ከፍተኛ በመሆኑ ነዉ። ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በቡና ምርት በዓለም በ6ኛ ደረጃ ላይ ብትገኝም ከላይ በተጠቀሰዉ ዓመት ወደ ውጭ የላከችዉ ቡና መጠን ግን በ10ኛ ደረጃ ካለችዉ ከኡጋንዳም በታች ነበር። ያም ቢሆን ከ30 እስከ 35% የሚሆነዉን የዉጭ ምንዛሪ በማስገኘት ቡና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታል።

እዚህ በሥዕሉ እንደሚታየዉ ‘’ኢትዮጵያ’’ የሚል ሥያሜ ተጽፎበት በታዋቂዉ የቡና ሻጭ ድርጅት በዉጭዉ ዓለም ለሽያጭ ቀርቧል። በፓኮው ላይ ደግሞ ቡናዉ አረቢካ ከሚባለው የቡና የተገኘ መሆኑንና በኢትዮጵያ ያሉ ቡና አብቃዮች ረዥም ጊዜ ወስደዉ ያደረቁት እንደሆነ ከመገለጹም በተጨማሪ የቡናዉ ጣዕም ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል።

በክፍል አንድ ጽሑፌ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት በቡናችን ላይ በአሁኑ ወቅት ያጋጠመዉንና ወደፊትም ያጋጥመዋል ተብሎ የሚጠበቀዉን መጥፎ ክስተት ገልጬ ነበር። የጽሑፌ መነሻም የነበረዉ በዘርፉ በታወቁ ተመራማሪዎች በተደረጉ መጠነ ሠፊ ጥናቶችና በቅርብ ጊዜ ለህትመት በበቁ ሁለት ጽሑፎች ሲሆን እነርሱም Coffee Farming and Climate Change in Ethiopia እና Resilience potential of the Ethiopian coffee sector under climate change የሚባሉት ናቸዉ። በዛሬዉ ጽሑፌ ደግሞ ይህንን መጥፎ ክስተት ለመታደግ የመፍትሔ ሀሳብ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉትን አቀርባለሁ።

የመፍትሔ ሀሳብ ተብለዉ በጸሐፊያኑ የቀረቡት 12 ቢሆኑም ክዚህ በታች የተወሰኑትን በጭሩ አቀርባለሁ። ዝርዝሩን በታተሙት ጽሑፎች ማግኘት ይቻላል።

1ኛ) ወቅታዊ፣ትክክለኛና በሳይንስ የተደገፈ ዉሣኔ እንዲኖር ማድረግ፤

2ኛ) የአየር ንብረት ለውጥ በቡና ላይ የሚያመጣዉን ተፅዕኖ በቅርበት መከታተል፤

3ኛ) ከዚህ በፊት ቡና በማይበቅልባቸዉ ከፍታ ቦታዎች ለቡና ተክል የሚኖራችዉን ተስማሚነት ማጥናት፤

4ኛ) ለዛፎችና ለአፈር እንክብካቤ ማድረግ፤

5ኛ) የቡናን ምርታማነትና ጥራት ማሳደግ፤

6ኛ፟) ገበሬዎች ለሚሸጡት ቡና ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ማድረግ፤

7ኛ) የቡና ተክልን የአደጋ ተቋቋሚነት ለማሳደግ የሚረዱ እርምጃዎችን መዉሰድ፤ እነርሱም እርከን መሥራትን፣ የቡና ዛፍን በወቅቱ መከርክምን፣ የጥላ ዛፍ እንዲኖር ማድረግንና የመስኖ አጠቃቀምን ይመለከታል።

8ኛ) የሀገሪቱ ቡና ያለበትን ሁኔታ በወቅቱ የሚያሳውቅና ተከታታይነቱንም በበላይነት የሚያስተዳድር አካል እንዲቋቋም ማድረግ ናቸዉ።

በዚሁ አጋጣሚ የራሴን ሥጋትና የመፍትሔ ሀሳቦች ለአንባቢያን ማካፈል እወዳለሁ።

1ኛ) በሦስት ዋና የአየር ንብረት መለኪዎች (ማለትም የዝናም መጠን፣ የአየር ሙቀት እና የአየር ርጥበት) በመመርኮዝ የቀረቡት ጽሑፎች እንደሚያሳዩት የወደፊቶቹ የቡና እርሻዎቻችን የሚኖሩት ከፍ ባሉ ሥፍራዎች ላይ ነዉ። ይህ በርካታ ጥያቄዎችን ሊያመጣ ይችላል። ከነዚህ ዉስጥ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል። የቡና ተክል ዕድገትና ምርት እንዲሁም የቡና ጣዕም ላይ ከአየር ንብረት በተጨማሪ የአፈር ዓይነትም ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ይገመታል። የአሁኑ ጥናት ይህን አላካተተትም። ስለዚህ ወደፊት የሚደረጉ ጥናቶች የአፈሩን ዓይነትና ሌሎች ተዛማጅ ባህርያትን ማጥናት ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት ከፍ ባሉ ሥፍራዎች የሚበቅሉ ሌሎች የሰብል ዓይነቶችስ ዕጣ ምን ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም ምክንያቱም እርሻቸው በቡና የሚተካ ከሆነ ማለቴ ነዉ። ከዚህ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ሌላ ሰብል የሚያመርቱ ገበሬዎችስ እንዴት እርሻቸዉን በቀላሉ ወደ ቡና ሊቀይሩ እንደሚችሉ ማወቅ ያስፈልጋል።

2ኛ) በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት ታዋቂዉ የአረቢካ ቡናችን በአግባቡ ምርት ሊያፈራ የማይችልባቸዉ ቦታዎች ተለይተዉ ቀርበዋል። ስለዚህ ከፍተኛ የአየር ሙቀትም ሆነ ተባይና በሽታ በተሻለ ሁኔታ መቋቋም የሚችለዉን የሮቡስታ የቡና አይነት በሀገራችን የምናላምድበት መንገድ ቢፈጠር የሚል ሀሳብ አቀርባለሁ። ነገር ግን መጠነ ሰፊ የሆነ ሥራ በዚህ ለሀገራችን አዲስ በሆነ የቡና አይነት ላይ ከመጀመራችን በፊት ወካይ በሆኑ የሀገሪቷ ሥፍራዎች ጥልቅ የሆነ ምርምር ማካሄድ ያስፈልጋል። በዓለማችን የሮቡስታን ቡና በሰፊዉ ከሚያበቅሉ ሀገራትም ልምድ መዉሰድ ጠቃሚ ነዉ።

ምንም እንኳ ባብዘኛዉ የቡና ጠጪዮች ዘንድ የአረቢካ ቡና የበለጠ ተመራጭ ቢሆንም የሮቡስታ ቡናም የራሱ የሆኑ ጠንካራ ጎኖች አሉት። የሚከተሉትን መለኪያዎች ለማነጻጸሪያነት ማየት ይቻላል።

መለኪያዎች የአረቢካ ቡና የሮቡስታ ቡና
ተስማሚ ሥፍራ ከፍተኛ (እስክ 2000 ሜ) ዝቅተኛ (እስክ 1000 ሜ.)
ተስማሚ የአየር ሙቀት 15-25 ሴ.ግ. 20-30 ሴ.ግ.
የተክሉ ትልቅነት አነስ ያለ ከፍ ያለ
ተባይ የመቋቋም ችሎታው ዝቅተኛ ከፍተኛ
በሽታ የመቋቋም ችሎታው ዝቅተኛ ከፍተኛ
የምርት መጠን ዝቅተኛ ከፍተኛ
የካፊን መጠን ዝቅተኛ ከፍተኛ
ጣፋጭነት ጠፈጥ ያለ መረር ያለ

በመጨረሻም ታዋቂ የሆኑ የቡና ብራንዶቻችንን እንዳናጣና ከዘገየ ደግሞ ወደቀድሞ ሁኔታ መመለስ አዳጋች ስለሚሆን ወደ መፍትሔዉ በፍጥነት መሄድ ይኖርብናል። ለዚሁም የሁሉም የድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ያስፈልጋል።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እንገናኝ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ግንቦት 22፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የቡናችን ነገር እጅግ ያሳስባል

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የቡናችን ነገር እጅግ ያሳስባል

ክፍል አንድ

እንደሚታወቀዉ ሁሉ ቡና በዓለማችን እጅግ ተወዳጅ መጠጥ ነዉ። በዓለማችን ሁለት የቡና ዓይነቶች በሰፊዉ ይበቅላሉ፣ በገበያም ላይም ይዉላሉ። እነርሱም አራቢካ እና ሮቡስታ ተብለው ይታወቃሉ። በዓለም ላይ የአረቢካ ቡና ስልሳ ፐረሰንት በሆነ መሬት ላይ ሲተከል በተቀረዉ አርባ ፐርሰንት መሬት ላይ ደግሞ የሮቡስታ ቡና ይተከላል። የአራቢካ ቡና በሰፊዉ የሚበቅለው ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ ባሉ ሀገሮችና በመካከለኛዉና ደቡብ አሜሪካ ሀገሮች ነዉ። በሌላ በኩል የሮቡስታ ቡና በሰፊዉ የሚበቅለዉ በመካከለኛዉና ምዕራብ የአፍሪካ እና በደቡብ ምሥራቅ ባሉ የኤሲያ ሀገሮች ነው። ይህ የሚያሳየዉ እነዚህ ሁለት የቡና ዓይነቶች የሚበቅሉበት የአየር ንብረትና የአፈር ሁኔታ የተለያየ መሆኑ ነዉ። በተጠቃሚዎች ዘንድ ከሁለቱ የቡና ዓይነቶች የአራቢካ ቡና የበለጠ ተመራጭ ነዉ። ይህም በጣዕሙና ለጠጪዎች በሚሰጠዉ ዕርካታ የተነሣ ነዉ። በዚሁ መሠረት በገበያ ላይ የአረቢካ ቡና ከሮቡስታ ቡና በላይ ከፍ ያለ ዋጋ ያወጣል። ስለዚህ ለሽያጭ የቀረበዉ ቡና የአረቢካ ዓይነት ብቻ ከሆነ በፓኮዉ ላይ በፎቶዉ ላይ እንደሚታየዉ 100% አረቢካ ተብሎ ይጻፍበታል። ሸማቹም ቡናዉ ሙሉ በሙሉ የአረቢካ ቡና ከሆነ ከፍ ያለ ክፍያ ቢፈጽምም አይቆጨዉም።

ወደ ሀገራችን ስንመለስ ምንም እንኳ በሀገሪቷ በሙሉ የሚመረተዉ ቡና በተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ተመራጭ ያለዉ የአረቢካ ቡና ብቻ ቢሆንም ሀገሪቱ ለረጅም ጊዜ በዓለም ገበያ ተመጣጣኝ ዋጋ ልታገኝ አልቻለችም። በዚሁ መሠረት በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል የሚመረቱትና የራሳቸዉ የሆነ ልዩ ጣዕም ያላቸዉ እንደ ይርጋጨፌ፣ ሐረር፣ ሲዳሞ የመሳሰሉት የቡና ዓይነቶች (ወይም ብራንዶች) በዉጭዉ ዓለም ዕዉቅና ተነፍጓቸዉ ቆይቶ ነበር። ሆኖም በተለምዶ የቡና ጦርነት ተብሎ በሚታወቀዉና በኢትዮጵያ መንግሥትና ዋናዉ ጽህፈት ቤቱ በአሜሪካን ሀገር በሚገኘዉ በስታርበክስ መካከል በነበረዉ ከፍተኛ አለመግባባት ኦክስፋም ተብሎ የሚጠራዉ ግብረ ሠናይ ድርጅት ከፍተኛ እግዛ ለኢትዮጵያ በማድረጉ ከላይ የተጠቀሱት የቡና ብራንዶች በአሜሪካና ሌሎቸ ሀገሮች ዕውቅና እንዲኖራቸዉ ሆኗል። በነዚሀ ሀገራት ያሉ የቡና ጠጪዎችም ከላይ የተገለጹትን የቡና ብራንዶች ለይቶ ማወቅ ብቻ ሳይሆን የሚፈልጉትን የቡና ብራንድ በገበያ ሊያገኙ ችለዋል። በዚህ መሠረት የተለያዩ የኢትዮጵያ የቡና ብራንዶች እንደ ጥራታቸዉ ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ ሊያገኙ ችለዋል።

የዛሬዉ ብሎጌ የሚያተኩረዉ በአሁኑ ወቅት በቡናችን ላይ የተደቀነበትን አሳሳቢ የተፈጥሮ ክስተት ለአንባቢያን ለማስገንዘብ ሲሆን ይህንን አደጋ ለመታደግም ሁላችንም የየራሳችንን አስተዋዖ እንድናበረክት ነዉ። የጽሑፌ መነሻ ሀሳብም በቅርብ ጊዜ በጥናት ላይ ተመርኩዘዉ የታተሙ ሁለት ጽሁፎች ሲሆኑ እነርሱም Coffee Farming and Climate Change in Ethiopia እና Resilience potential of the Ethiopian coffee sector under climate change የሚባሉት ናቸዉ። እነዚህ ሁለት ጽሑፎች ኢትዮጵያ የሚገኙ የቡና አብቃይ ሥፍራዎችን ሁሉ ባገናዘበ መልኩ የተሠሩ ዉጤቶች ናቸዉ። የጥናቱ ዋና አካላት በእንግሊዝ ሀገር የሚገኘዉና የብዝሀ ሕይወትን በመንከባከብ የሚታወቀዉ የኪዉ ጋርደንና በኢትዮጵያ ያሉ ተመራማሪዮች ናቸዉ። በኢትዮጵያ በኩል በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል ዕዉቁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባና የጉለሌ የዕጽዋት ጋርደን ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰዉ ይገኙበታል። ፕሮፌሰር ሰብስቤ ከሌሎች ሁለት የሥራ ባልደረቦቻቸዉ ጋር በመሆን እ.ኤ.አ. ብ2010 ባሳትሙት Atlas of the potential vegetation of Ethiopia በሚባል መጽሐፍቸዉም ጭምር ይታውቃሉ። ፕሮፌሰር ሰብስቤ ሰፊ ጥናት ከማካሄዳቸዉም በተጨማሪ በመስኩ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጾዖ ባለፈዉ ዓመት በእንግሊዝ ሀገር ከ350 ዓመታት በፊት የተቋቋመዉ የታዋቂዉ የሮያል ሶሳዪቲ አባል ለመሆን በቅተዋል። በዚህ አጋጣሚ ከላይ የተገለጹትን የቡና ጥናቶች እንዲካሄዱ በመዋዕለ ንዋይ ለረዱት ለእንግሊዝ፣ ኖርዌና ዴንማርክ መንግሥታት ምሥጋና ይገባቸዋል።

ጥናቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ የቡና አብቃይ ሥፍራዎችን እንደ ኩታ ገጠምነታቸዉ በአምስት ዋና ክፍሎች የሚከፍል ሲሆን 16 የቡና ሥፍራዎችንም ለይቶ ያቀርባል። ጥናቱም በዋናነት መሠረት ያደረገው ባለፉት 40 ዓመታት በነዚህ ቡና አብቃይ ሥፍራዎች የተከሰተዉን የአየር ንብረት ለውጥ ነዉ። የጥናቱ ዉጤት እንደሚያሳየዉ እ.ኤ.አ. ከ1960 እስከ 2006 ድረስ ባሉት 46 ዓመታት ብቻ በኢትዮጵያ የአየር ሙቀት በ1.3 ድግሪ ሴንቲ ግሬድ ከፍ ብሎ ታይቷል። ከዚህ በተጨማሪ ለቡና ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ ቀዝቃዛ ሌሊቶች አጥረው ታይተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ጥናቱ ባካተተዉ 46 ዓመታት የበልግ ዝናም መጠን በተለይም በደቡብ ምሥራቅ ባሉ የቡና አብቃይ ሥፍራዎች ከ15 እስክ 20% አንሶ ተገኝቷል። ይህ መጠነ ሰፊ ጥናት በተለያዩ የአየር መለኪያ መሣሪያዎች ብቻ የተመረኮዘ ሳይሆን ለአራት ዓመታት በርካታ ቁጥር ያላቸዉ በተለያዩ የቡና አብቃይ ሥፍራዎች የሚገኙ ገበሬዎችንም በማነጋገር ነበር። ከገበሬዎች ቃለ ምልልስ የተገኘዉ ውጤት ከአየር መለኪያ መሣሪዎች ከተገኘዉ ጋር ተመሣሣይነት አለዉ። ገበሬዎቹ የአየር ንብረት ለውጥ በቡና ተክላቸዉም ሆነ ምርታቸዉ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው ከተገነዘቡ ቆይቷል። ይህ መጥፎ የተፈጥሮ ክስተት ከመምጣቱ በፊት በየዓመቱ ምርት ያገኙ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን አንድ ደህና ምርት በየሁለት ዓመት ወይም ባንዳንድ ሥፍራዎች በየአምስት ዓመት ብቻ ማግኘት ከጀመሩ ሰንበትበት ብሏል።

በአጠቃላይ እነዚህ ጽሁፎች በሀገሪቱ ያሉ የቡና አብቃይ ሥፍራዎች በአሁን ወቅት የገጠማቸዉን የአየር ንብረት ለውጥ ከማሳወቃቸዉም በላይ በሚቀጥሉት አሥርት ዓመታትም ሊያጋጥማቸዉ ይችላል ተብሎ የሚገመተዉን በሣይንሳዊ መንገድ መተንተናቸዉ ነው። በነዚህ ጥናቶች መሠረት ከዚህ በፊት የቡና አብቃይ ከነበሩትሥፍራዎች መካከል በምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ በአርሲና በዘጌ ያሉ ቦታዎች በአሁኑ ወቅት ለቡና ተክል ተስማሚ ሆነዉ አልተገኙም። ወደፊትም ወደ ቀድሞ የአምራችነታቸዉ ሁኔታ የመመለስ ዕድላቸዉ የመነመነ ነዉ። በጥናቱ መሠረት እስከሚቀጥሉት 20 ዓመታት ደግሞ በባሌ ያሉ መሬቶችም ለቡና እርሻ ተስማሚ አይሆኑም። ከዚያም ቀጥሎ ባሉት ከ20 እስክ 50 ዓመታት ደግም ከስምጥ ሸለቆ ሰሜን ያሉ ሥፍራዎች ቡናን የማያበቅሉ ሲሆን የትንበያው መጨረሻ በሆነዉ ከ50 እስከ 80 ዓመታት ባሉት ጊዜያት ደግሞ ከስምጥ ሸለቆ ደቡብ ያሉ ሥፍራዎችም ተመሣሣይ ዕድል ይገጥማቸዋል። ምንም እንኳ በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል ያሉ የቡና አብቃይ ሥፍራዎች እስከሚቀትሉት 80 ዓመታት ቡናን በማብቀል እንደሚቆዩ ቢገመትም ባንዳንድ ሥፍራዎች የተስማሚነት ደረጃቸዉ እንደሚቀንስ ይጠበቃል። ይህ በኢትዮጵያም ሆነ በሌላ ዓለም ለሚገኙ የቡና አፍቃሪዎች አስደንጋጭ ዜና ነዉ። በያመቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በቡና ለምታገኘዉ ሀገራችንም ጭምር።

ስለዚህ ቡናችን እያየነው እንዳይጠፋብን ካሁኑ ሁላችንም የድርሻችንን ማበርከት ይኖርብናል። ከዘገየ ወደ ቀድሞ ሁኔታ መመለስ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ፈጽሞ ላይሆንም ይችላል። ከላይ በጥናት ላይ ተደግፎ የቀረበዉን በተለይ የሐረር እና የባሌ የቡና ዓይነቶች ላይ የተደቀነዉን ሳነብ ከረጅም ዓመታት በፊት የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ‘‘ቡና’’ ተብሎ በሚጠራዉ ኮርስ መምህራችን የነበሩት ታዋቂዉ የጅማ እርሻ ምርምር የቡና ተመራማሪ ዶክተር መስፍን አምሐ ትዝ አሉኝ። በዚህ አጋጣሚ ማስገንዘብ የምፈልገዉ የሐረር ቡና ተብሎ የሚታወቀዉ የቡና ብራንድ በምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ አካባቢዎች የሚመረተዉን የቡና ዓይነት የሚወክል ነዉ። እኚሁ መምህር በክፍል ዉስጥ ይሰጡ ከነበረዉ ሌክቸር በተጨማሪ ባንድ ውቅት ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ የቡና ማቀነባበሪያ ለጉብኝት ወስደዉን ነበር። ይህ መለስተኛ ማቀነባበሪያ ቡናን በመቁላትና በማሸግ በተለይም የሐረርን ቡና ለውጭ ሀገር ገበያ በሚቀርብበት መንገድ የሚያዘጋጅ ነበር። የሐረር ቡና የሚታወቅበት የራሱ የሆነ ልዩ ጣዕም ያለዉ ሲሆን ይህም ወደ ጣፋጭነት የሚያደላ ነዉ። በዚሁ ጣዕሙ የተነሣ በመካከለኛዉ ምሥራቅ ባሉ ሀገራት ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፈ ነበር። ታዲያ እንደዚህ ታዋቂ የሆነዉን የሐረርና ሌሎችም የቡና ዓይነቶኛችን ልናጣ ነዉን? ምንስ ይበጀናል? ወደ ተግባርም በፍጥነት ልንሄድ አይገባንምን?

የጥናቱ ተሣታፊዎች በርካታ መደረግ የሚገባቸዉን ምክር ለግሰዋል። እነዚህና ሌሎች የመፍትሔ ሀሳቦች በሚቀጥለዉ ጽሑፌ አቀርባለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ግንቦት 18፤ 2011 ዓ.ም.