ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለውጥ — የካርቦን ገበያ፣ ታክስና ፈንድ

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለውጥ — የካርቦን ገበያ፣ ታክስና ፈንድ

ካርቦን በተመለከተ በሰፊዉ አገልግሎት ላይ የዋለዉ ካርቦን ዴቲንግ (Carbon dating) ተብሎ የሚታወቀዉ ሲሆን ይህም የአንድን ናሙና ወይም ቅርስ ዕድሜ ለማወቅ የሚያስችለን ነዉ። በዚሁ መንገድ በመጠቀም የአንድ የቆየ አጥንት ወይም ስባሪ እንጨት ዕድሜ መገመት እንችላለን ማለት ነዉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የካርቦን ገበያ፣ የካርቦን ታክስና የካርቦን ፈንድ የሚሉትን ቃላትም መስማት ጀምረናል። ለመሆኑ እነዚህ ድሮ ያልተለመዱ ቃላት ከየት ብቅ አሉ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። እነዚህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተዋወቅናቸዉ የመጡት ቃላት የአየር ንብረት ለውጥን ለመታደግ የመፍትሔ አካል ሊሆኑ ይችላሉ ተብለዉ የመጡ ናቸዉ። የነዚህን አዳስ ቃላት ዋና ዓላማና አጠቃቀም ከዚህ በታች በአጭሩ ለማሳየት እሞክራለሁ።

የካርቦን ታክስ (ቀረጥ)፤ ይህ የሚያመለክተዉ ካርቦን ላይ መሠረት ያደረገ ኢነርጂ የሚጠቀሙ ድርጅቶችም ሆነ ግለሰቦች የሚከፍሉት ታክስ ነዉ። እነዚህ ካርቦን ላይ የተመሠረቱ የምንላቸዉ እንደ ድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅ፤ የተፈጥሮ ጋዝ ሲሆኑ ስንጠቀማቸዉ ወይም ሲቃጠሉ ከፍተኛ የሆነ የግሪን ሀዉስ ጋዝ በተለይም ካርቦንዳይኦክሳይድን ወደ ከባቢያችን የሚለቁት ናቸዉ። ። ስለዚህ የግሪን ሀዉስ ጋዝን ከከካባቢያችን ለመቀነስ የኢነርጂዉ ተጠቃሚዎች ካርቦንዳይኦክሳይድን ወደ ከባቢያችን በሚለቁት መጠን ታክስ ይጣልባቸዋል። በዚህ መሠረት አካባቢውን ብዙ የበከለ ብዙ ቀረጥ ይከፍላል ማለት ነዉ። ተጠቃሚዎችም በተለይ ትላልቅ ካምፓኒዎች ከሚጣልባቸዉ ከፍተኛ የካርቦን ታክስ ነፃ ለመሆን አማራጭ የኢነርጂ ምንጮችን ለመጠቀም ይገደዳሉ። በዚሁ ምክንያት ነዉ በአሁኑ ጊዜ በተለምዶ “ንፁህ ኢነርጂ” የተባሉትን እንደ ንፋስ፣ የፀሐይ ብርሃን እና ዉሃ የመሳሰሉት በጥቅም ላይ እየዋሉና ህብረተሰቡም እነዚህ የኢነርጂ ምንጮችን ለመጠቀም ያለዉ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ነዉ።

የካርቦን ገበያ፤ በአንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት የካርቦን ገበያ የሚባልም አለ። ይህም ማለት ካምፓኒዎች በነፃ መልቀቅ የሚፈቅድላቸዉ የካርቦንዳይኦክሳይድ ኮታ ይሰጣቸዋል። አማራጭ የኢነርጂ ምንጭ በመጠቀም የተሰጣቸዉን ኮታ መጠቀም የማይችሉ ካምፓኒዎች ደግሞ ከተሰጣቸዉ የኮታ ዉስጥ ያልተጠቀሙትን ከኮታ በላይ ለሚጠቀሙት መሸጥ ይችላሉ። ለምሳሌ ከ50 የሚበልጡ በስዊዘርላንድ የሚገኙ የሲሚንቶ፣ የኬሚካልና የብረታ ብረት ፋብሪካዎች የዚህን የካርቦን ገበያ መንገድ ይከተላሉ። በአዉሮፓ ደግሞ ከአሥር ሺህ በላይ የሆኑ ድርጅቶች በዚህ የካርቦን ገበያ ተጠቃሚ ናቸዉ።

የካርቦን ፈንድ፤ ይህ ፈንድ የተቋቋመዉ የአየር ንብረትን ለመግታት ይረዳል ተብሎ ከታሰቡት አንዱ የሆነዉን የዛፍ መትከልና ደን መንከባከብ በተለይ በመልማት ላይ ያሉ ሀገሮች ለሚያደርጉት አስተዋጽኦ በገንዘብ ለመደገፍ ነዉ። በዚህ ፈንድ የተሣተፉት ሀገሮች 47 ሲሆኑ ከነዚህ ዉስጥ 18 ከአፍሪካ፣ 18 ከላቲን አሜሪካ እና 11 ከኤሲያ እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። ከነዚህ ዉስጥ ኢትዮጵያም አንዷ ናት። በዚህ የ1.3 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት 17 ሀገሮች በፋይናንስ ድጋፍ ያደርጋሉ።

የባዮካርቦን ፈንድ፤ ይህም ከላይ እንደተጠቀሰዉ የካርቦን ፈንድ ሁሉ የምድራችንን የደን ሽፋን በመጨመር ካርቦንዳይኦክሳይድ ወደ ከባቢያችን እንዳያፈተልክ ለማድረግ የታሰበ ሲሆን ፕሮጀክቱ በመልማት ላይ ካሉ አምስት ሀገሮች ጋር በጋራ ይሠራል። እነርሱም ኮሎምቢያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢንዶኔሺያ፣ ሜክሲኮ እና ዛምቢያ ናቸዉ። በፋይናንስ በኩል ፕሮጀክቱ በዓለም ባንክ ይረዳል። እዚህ ላይ በደቡባዊ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘዉን የሁምቦ ባዮካርቦን ፈንድ መጥቀስ ያስፈልጋል። ይህ ደን የሚሸፍነዉ 2700 ሄክታር መሬት ሲሆን ከዚህ በፊት ከጥቅም ዉጪ የሆነ ሥፍራ ነዉ። ለአራት ዓመታት በሥፍራዉ በተደረገዉ የልማት ሥራ የእህል ምርትም ከፍ ሊል ችሏል። ሌላዉ በባዮካርቦን ፈንድ የሚታገዘዉ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይም በቡና አብቃይ ሥፍራዎች ትኩረት በማድረግ ላይ የሚገኘዉ ነዉ። ከሶስት ወራት በፊት የታተመዉ ጽሑፍ ገርባ ዲማ በሚባለዉ በደቡባዊዉ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኝ ደን ዉስጥ ያለዉን የካርቦን ክምችት ያሳያል። በጥናቱ መሠረት በደኑ ውስጥ ያለዉ አማካይ የካርቦን ክምችት 508.9 ቶን በሄክታር ነዉ። እንደ ጥናቱ ተሳታፊዎች ይህ የካርቦን መጠን ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለደኑ ተገቢዉን ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ ሀገሪቱ ከባዮካርቦን ፈንድ የምታገኘዉን ገንዝብ ማሳደግ እንዳለባት ያሳስባሉ።

በተመሣሣይ መልኩ ከጀርመን መንግሥት ጋር በትብብር የሚሠራዉ የካርቦን ገበያ ሪፖርት እንደሚያሳየዉ ትብብሩ በኢነርጂ፣ ትራንስፖርትና ቆሻሻ ማስወገድ ላይ ያተኩራል። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ የፕሮጀክት ሥያሜዎች በርካታ ፕሮጀክቶች ሥራ ላይ ዉለዋል።

እዚህ ላይ ዛፍ መትከልና የደን እክብካቤ ላይ ትኩረት የተሰጠዉ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ዛፎች ከፍተኛ እገዛ ሰለሚያደርጉ ነዉ። ምክንያቱም ዛፎች ወደ አካባቢያችን የሚለቀቀውን ዋነኛ የግሪን ሀዉስ ጋዝ አካል የሆነውን ካርቦንዳይኦክሳይድን አምቀዉ ስለሚይዙ ነዉ። ከዚህ በፊት “የአየር ንብረት ለዉጥ — ዛፎቻችን” በሚለዉ ጽሑፌ ተዛማች መረጃን ጠቅሼ ለማሳየት እንደሞከርኩት ከአንድ ዛፍ ጠቅላላ ክብደቱ ዉስጥ ግማሹን የሚይዘዉ ካርቦን ነዉ። በዚሁ መሠረት 12 ዓመት የሆነውና 600 ኪ.ግ. የሚከብድ ዛፍ በዉስጡ 859 ኪ.ግ. ካርቦን ዳይኦክሳይድ አምቆ የሚይዝ ሲሆን በ200 ሄክታር ላይ ያለ ደን (በአንድ ሄክታር 650 ዛፍ ቢኖር) በ12 ዓመት 111,670 ቶን (ወይም 111 ሚሊዮን ኪ.ግ.) ካርቦንዳይኦክሳይድ አምቆ ይዟል ማለት ነዉ። ነገር ግን በዚህ በ200 ሄክታር ላይ ያለ ደን የመቃጠል አደጋ ቢያጋጥመዉ ከላይ የተጠቀሰዉ የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን አካባቢያችን አፈተለከ ማለት ነዉ። በዚሁ መሠረት በአየር ንብረት ለዉጥ ለሚደርሰዉ መጥፎ ክስተት የራሱን አሰተዋጽኦ ያደርጋል።

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ዛፍ እንትከል ሲባል የተተከለዉ አይቆረጥም ማለት አይደለም። ከዚህ በታች በምሥሉ እንደሚታየዉ በሚቆረጡት ዛፎች ምትክ አዲስ ዛፍ በወቅቱ መትከል ያስፈልጋል።

ምሥሉ እንደሚያሳየዉ በደህና ሁኔታ ተጠብቆ የሚገኝ ጫካ ነዉ። ጊዜቸዉ ደርሶ መቆረጥ ያለባቸዉ ዛፎች ተቆርጠዉ የሚታዩ ሲሆን በተቆረጡት ምትክ የተተከሉት ደግሞ ከፊት ለፊት በደህና ሁኔታ አቆጥቁጠዉ ይገኛሉ። ወደፊት ተራቸዉን ጠብቀዉ የሚቆረጡት ደግሞ ከጀርባ ይታያሉ። ፎቶ፤ ዘሪሁን ታደለ፣ ኮኒዝ፣ በርን. ሰኔ 9፣ 2011

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 17፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለውጥ — ህብረተሰቡ ምን ይላል?

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለውጥ — ህብረተሰቡ ምን ይላል?

በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በተለይም በአዉሮፓ ያሉ አክቲቪስቶች በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት ሰለሚከሰተዉ አስደንጋጭ ሁኔታ እጅግ ስላሳሰባቸዉ መንግሥታቸዉ ወይም አህጉሩ ጠበቅ ያለ አቋም እንዲወስዱ በየጊዜዉ እየወተወቷቸዉ ነው። በዚህ ብቻም ሳይወሰኑ የተቃውሞ ሰልፎችንም ጭምር በማደራጀት ድምፃቸዉን ያሰማሉ። ለአየር ንብረት መለወጥ እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት የአየርና የባህር ሙቀት መጨመር፣ የዝናም እጥረት ወይም ድርቅ መባባስ፣ የጎርፍ መብዛት፣ የግሪንሃዉስ ጋዝ መጠን መጨመር፣ የበረዶ ክምችት መመናመን፣ የባህር ወለል ከፍ ማለት እና የባህር ዉሃ ወደ አሲዳማነት መቀየር ናቸዉ።

ከዚህ ተያይዞ ያንዲት የስዊዲን ሀገር ወጣት ተማሪን አስተዋጽኦ መጥቀስ ያስፈልጋል። ስሟ ግሬታ ቱንበርግ ይባላል። በዓለም ዙሪያ የአየር ንብረት ለውጥን በሚመለከት ለህብረትሰቡ ግንዛቤ ለመስጠትና መንግሥታትም እርምጃ እንዲወስዱ ለማሳሰብ የወሰነች ናት። ተቃዉሞዋን የጀመረችዉ የዛሬ አንድ ዓመት (በኦግስት 20፣ 2018) ነዉ። በወቅቱ የዘጠነኛ ከፍል ተማሪ የነበረችዉ የ15 ዓመቷ ግሬታ ትምህርቷን አቋርጣ የሀገሪቱ ፓርላማ ህንጻ ፊት ብቻዋን ሆና ተቃዉሞዋን ማሰማት ጀመረች። ቤተሰቦቿ ትምህርቷን እንዳትተዉ ቢማጸኗትም እንዲሁም የትምህርት ቤት ጓደኞቿ ባይቀላቅሏትም መፈክሯን ይዛ የበረዶዉ፣ የዝናቡና የፀሐዩ መፈራረቅ ሳይበግራት ለወራት ፓርላማዉ ፊት ትቀመጥ ነበር። በዚህ ቆራጥ ዓላማዋና ድርጊቷ የዓለምን ትኩረት ሳበች። ይህች ወጣትም በተለያዩ መድረኮች ንግግር እንድታደርግ መጋበዝ ጀመረች። ከነዚህ ወስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰዉ የዓለማችን ታዋቂ ሰዎች የሚጋበዙበት በያመቱ በዳቮስ ስዊዘርላንድ የሚካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ነዉ። ከዚህ ሌላ በተለያዩ መድረኮችም ከሀገር መሪዎች ጭምር የመገናኘትና ድምጿን የማሰማት ዕድል አግኝታለች። የአየር ንብረት ለዉጥን በተመለከተ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ ትጋበዛለች። በርካታ ሽልማቶችንና ዕውቅናን ለማግኘት በቅታለች። የኖብል ተሸላሚ እንድትሆንም ጥሪ እየቀረበ ነዉ። ይህች ወጣት አይሮፕላን ከፍተኛ መጠን ያለዉ ካርቦንዳይኦክሳይድ ወደ ከባቢያችን ሰለሚረጭ ማዕቀብ አድርጋበታለች። ምንም እንኳ ጉዞዋ አንዳንድ ጊዜ ረዥም ጊዜ ቢወስድባትም ካንድ ሀገር ወደ ሌላ የምትጓዘዉ በባቡር ነዉ። ሌላዉ የግሬታ ባህርይ ራሷን ወደ ቬጋን መቀየሯ ነዉ። በዚሁ መሠረት ማንኛዉም ከእንስሳ የሚገኝ ነገር (እንደ ሥጋ፣ ወተት፣ አይብ፣ እንቁላል) አፏ አጠገብ አይደርሱም። ምከንያቱም እንሰሳዎቻችን ከፍተኛ የሆነ የግሪን ሀዉስ ጋስ ወደ አካባቢችን ስለሚረጩ ነዉ። ይህ በሷ ብቻ የተጀመረዉ የአየር ንብረት የተማሪዎች ተቃዉሞ ተስፋፍቶ ከሶስት ወራት በፊት (በማርች 15፣ 2019) በ112 ሀገራት ያሉ በግምት 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች እንዲሁም ከአንድ ወር በፊት (ሜይ 24፣ 2019) በ125 ሀገራት ያሉ ትማሪዎች ሊሳተፉበት ችለዋል።

የአየር ንብረቴ (My Climate) የሚለዉና በስዊዘርላንድ ትልቁ በሆነችው በዙሪክ ከተማ የተመሠረተው ይህ ፋዉንዴሽን https://www.myclimate.org/compensate/today/ ትንሽ የምለዉ አለኝ። ይህ ፋዉንዴሽን የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ በርካታ መረጃዎች በእንግሊዘኛና ጀርመንኛ ቋንቋዎች ያቀርባል። በተለይ በኑሮአችን ዉስጥ ምን ያህል ካርቦንዳይኦክሳይድ በከባቢያችን እንደምንረጭ ያሳየናል። ለምሳሌ በአይሮፕላን ስንበር፣ በመኪና ስንሄድ ወይም በመርከብ ስንቀዝፍ የምናቃጥለዉን የካርቦንዳይኦክሳይድ መጠን አስልቶ ይሰጠናል። ለምሳሌ እኔ ካለሁበት ሀገር ወደ ወደ ኢትዮጵያ የደርሶ መልስ በረራ ለማካሄድ ከጄኔቫ በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚደረገዉ ጉዞ አጭሩ ነዉ። ይህም ወደ 10400 ኪሎ ሜትር እንደሚሆን ይገመታል። በዚህ ድህረ ገጽ ስሌት መሠረት በረራዬ በኢኮኖሚ ከፍል ከሆነ የሚቃጠለዉ የካርቦንዳይኦክሳይድ መጠን 1.9 ቶን ሲሆን በቢዝነስ ክፍል ደግሞ 3.7 ቶን እና ፈርስት ክላስ በሚባለዉ ደግሞ 5.8 ቶን ነዉ። ስለዚህ ባንድ ጉዞ ለዓመቱ የተመደበልንን አንድ ቶን የካርቦንዳይኦክሳይድ መጠን አለፍን ማለት ነዉ። በተመሣሣይ መልኩ ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ በአይሮፕላን ደርሶ መልስ የሚጓዝ ሰዉ 0.25 ቶን የሚያቃጥል ሲሆን የዓመት ኮታዉን በአራት ጉዞዎች ያጠናቅቃል ማለት ነው።

የዚህ ፋዉንዴሽን ሌላው ዓላማ ከኮታችን በላይ የምንጠቀመዉን የካርቦንዳይኦክሳይድ መጠን በገንዘብ መልክ እንድንከፍልና የአየር ንብረትን ለመታደግ በሚደረጉ የልማት ሥራዎች ላይ በተለይም በመልማት ላይ ባሉ ሀገሮች እንዲዉል ማድረግ ነዉ። በዚሁ መሠረት ከላይ በተጠቀሰዉ የጄኔቫ – አዲስ አበባ ጉዞ ከኮታ በላይ ለተጠቀሙት ትርፍ ካርቦንዳይኦክሳይድ የኢኮኖሚ ክፍል ተጓዥ 55.00 ዶላር፣ የቢዝነስ ክፍል 106.00 ዶላር እና የፈርስት ክላስ 165.00 ዶላር እንዲከፍል ይጠበቅበታል።

በዚሁ የአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት ሊከሰት የሚችለዉን የካርቦንዳይኦክሳይድ መጠን ለህብረትሰቡ ግንዛቤ ለመስጠት ይኸዉ ፋዉንዴሽን ሰሞኑን ግዙፍ ባሉኖችን በትልልቅ ከተሞች አስቀምጧል። ከነዚህ ወስጥ እኔ በምኖርበት የበርን ከተማ የከተማዉ ማዕከል በሆነ ሥፍራ የተቀመጠመዉን ከዚህ በታች በምሥሉ ማየት ይቻላል።

በምሥሉ የሚታየዉ የግሪን ሃዉስ ጋዝ አካል ስለሆነዉ ካርቦንዳይኦክሳይድ ሲሆን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመስጠት በየከተማዉ ይህን የመሰለ ግዙፍ ባሎን በማስቀመጥ ነዉ። በባሎኑም ላይ የተጻፈዉ “የአየር ንብረትን ለመግታት የሚያስችል የካርቦን ኮታህ ወይም ኮታሽ የተወሰነ ነዉ። ዛሬ የት ነህ ወይም ነሽ” ይላል። በባሎኑ ላይ እንደሚታየዉ የአንድ ሰዉ የዓመቱ ኮታ አንድ ቶን ካርቦንዳይኦክሳይድ ነዉ። ፎቶ፤ ዘሪሁን ታደለ፣ በርን ከተማ ሰኔ 12, 2011 (June 19, 2019)

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 16፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለውጥ — የኛ አስተዋጽኦ

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለውጥ — የኛ አስተዋጽኦ

ከዚህ ቀደም “የአየር ንብረት ለውጥ — ምልክቶቹ” በሚለዉ ጽሑፌ ለአየር ንብረት መለወጥ እንደ ማስረጃ ከምንጠቅሳቸዉ ክስተቶች ውስጥ ዋናዎቹን ጠቅሼ ነበር። እነርሱም 1ኛ) የአየርና የባህር ሙቀት መጨመር፣ 2ኛ) የዝናም እጥረት ወይም ድርቅ መባባስ፣ 3ኛ) የጎርፍ መብዛት፣ 4ኛ) የግሪንሃዉስ ጋዝ መጠን መጨመር፣ 5ኛ) የበረዶ ክምችት መመናመን፣ 6ኛ) የባህር ወለል ከፍ ማለት፣ እና 7ኛ) የባህር ዉሃ ወደ አሲዳማነት መቀየር ናቸዉ። በመቀጠልም በተከታታይ በጻፍኳቸው ሰባት ብሎጎች የአየር ንብረት ለውጥ በብዝሀ ሕይወታችን፣ በሰብሎቻችን፣ በአረም መስፋፋት፣ በደናችን፣ በውሃችን፣ በእንስሳቶቻችን እና በጤናችን ላይ የሚያደርስዉን አደጋ ለማሳየት ሞክሬአለሁ። በዛሬዉ ጽሑፌ ደግሞ ለዚህ ለአየር ንብረት ለውጥ የሰዉ ልጅ አስተዋጽኦን ለማሳየት ነዉ። በተለይ ትኩረት የማደርገዉ በግሪን ሀዉስ ጋዝ ላይ ነዉ።

ከዚህ በፊት ለማሳየት እንደሞከርኩት ግሪን ሃዉስ ጋዝ የሚል ስያሜ የተሰጣቸዉ ወደ ሰባት የሚጠጉ ጋዞች አሉ። እነርሱም የዉሃ ትነት (H2O)፣ ካርቦንዳይኦክሳይድ (Carbon dioxide CO2)፣ ሚቴን (Methane CH4)፣ ኦዞን (Ozone O3)፣ ናይትረስ ኦክሳይድ (Nitrous oxide N2O)፣ ክሎሮፍሎሮካርቦንስ (Chlorofluorocarbons CFCs) እና ሃይድሮፍሎሮካርቦንስ (Hydrofluorocarbons HCFCs & HFCs) ናቸዉ። የነዚህ የግሪንሃዉስ ጋዞች በአካባቢያችን መከማቸት በቀጥታም ሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ጉዳት ያደርሱብናል።

ለነዚህ የግሪን ሃዉስ ጋዞች በአካባቢያችን መከማቸት ግብርናችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። የዓለም አቀፍ የእርሻ ምርምር ማዕከላትን የሚስተባብረዉ ድርጅት ሪፖርት መሠረት በደን ጭፍጨፋና የመሬት አጠቃቀም ምከንያት በያመቱ ከ2.2 እስክ 6.6 ቢሊዮን ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ ከባቢ አየር ያፈተልካል። ይህም በዓለማችን ካለዉ አጠቃላይ የግሪን ሃዉስ ጋዝ ውስጥ ከ4 እስከ 14% የሆነዉን ይሸፍናል። በተመሣሣይ መልኩ ኤ.ኤ.አ. በ2050 የአለምን ህዝብ የምግብ ፍላጎት ለማርካት 10 ሚሊዮን ስኬዌር ኪሎ ሜትር የሆነ ቦታ መመንጠር ይኖርበታል። በዚሁ ምንጣሮ ምክንያት 3 ሚሊዮን ቶን የሚሆን ካርቦንዳይኦክሳይድ ያፈተለካል ማለት ነዉ።

የከብት እርባታም ከፍተኛ መጠን ያላቸዉን የግሪን ሃዉስ ጋዞች ወደ አካባቢያችን ይረጫል። ከላይ በተገለጸዉ ሪፖርት መሠረት የእንስሳት እርባታ 7.1 ቢሊዮን ቶን የሚሆን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ ከባቢያችን የሚለቅ ሲሆን ይህም የአለማችንን 14.5% ይሆናል። በተለይ የሥጋና የወተት ከብቶች ከፍተኛ መጠን ያለዉን የግሪን ሃዉስ ጋዞች ወደ አካባቢያችን የሚለቁ ሲሆን የዶሮ እርባታ እጅግ ዝቅተኛ መጠን ያለውን ድርሻ ይይዛል።

ሀገራችንን በተመለከተ የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት መረጃ እንደሚሳየዉ በከፍተኛ መጠን ወደ አካባቢያችን የሚረጨዉ የግሪን ሃዉስ ጋዝ ወስጥ ከእርሻ ጋር የሚገናኙት ሚቴን እና ናይትረስ ኦክሳይድ የሚባሉት ናቸዉ።

በምሥሉ የሚታየዉ እ.ኤ.አ. በ2016 በኢትዮጵያ ወስጥ ከእርሻ ጋር በተገናኘ ወደ አካባቢያችን የሚያፈተልኩትን የግርን ሀዉስ ጋዦች ነዉ። ጥሬ መረጃዉ የተገኘዉ ከዓለም የምግብ ድርጅት ድህረ ገጽ ሲሆን ወደ ምሥሉ ቀይሬዋለሁ።

ሀገራችንን በተመለከተ Climate and Clean Air Coalition (CCAC) በሚለዉ ስብስብ ጠለቅ ያለ ጥናት ተደርጎ ነበረ። በጥናታቸዉ ከተገኙት ውጤቶች መካከል በወተት ከብቶች በኩል ወደ አካባቢያችን የሚረጩትን የግሪን ሃዉስ ጋዞች የሚያሳየዉን ካርታ በመዋስ ለዛሬዉ ጽሑፌ ከዚህ በታች አቅርቤያለሁ። በጥናቱ መሠረት በወተት ከብቶች ምከንያት ወደ አካባቢያችን ከሚረጨው የግሪን ሀዉስ ጋዝ ዉስጥ 97.3% ቱን የሚይዘዉ ሚቴን ሲሆን ናይትረስ ኦክሳይድና ካርቦን ዳይኦክሳይድ የተቀረዉን እጅግ ዝቅተኛ ድርሻ ይይዛሉ።

ከላይ የሚታየዉ በኢትዮጵያ በወተት ከብቶች ምክንያት ወደ አካባቢያችን የሚረጩትን የግሪን ሃዉስ ጋዞች መጠን ነዉ። ምሥሉ ከዚህ ድህረ ገጽ የተወሰደ ነዉ።

ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ያለዉን የግሪን ሃዉስ ጋዝ መጠን የገመገመ ሌላ ጥናት እንደሚያሳየዉ በአካባቢያችን ካለ የግሪን ሃዉስ ጋዝ ውስጥ 42% ከከብት እርባታ የመጣ ሲሆን 37% ደግሞ ከዛፍ መቁረጥ የተነሣ ነዉ።

በአጠቃላይ የዛሬዉ ጽሑፌ የሚያሳየዉ እርሻችን ለግሪን ሀዉስ ጋዝ መከማቸት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለዉ ነዉ። በተለይ ደግሞ የሥጋ ከብቶችና የወተት ላሞች የላቀ ድርሻ ይወስዳሉ።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 15፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለውጥ — በጤናችን

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለውጥ — በጤናችን

እንደሌላዉ ሴክተር ሁሉ የአየር ንብረት ለዉጥ በጤናችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማደረስ ላይ ይገኛል። የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ባወጣዉ ሪፖርት መሠረት እ.ኤ.አ. ከ2030 እስከ 2050 ባሉት 20 ዓመታት ውስጥ ከአየር ንብረት ለዉጥ ጋር በተያያዘ በያመቱ 250 ሺህ ሰዉ እንደሚሞት ይጠበቃል። ዝርዝሩን ከዚህ በታች ባለዉ ምሥል ማየት ይቻላል።

ምሥሉ የሚያሳየዉ እ.ኤ.አ. ከ2030 እስከ 2050 ባሉት ዓመታት ዉስጥ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት በያመቱ በዓለማችን ሊደርስ የሚችለዉን የሞት አደጋ ነው። የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርትን በመመርኮዝ ነዉ ምሥሉን የሳልኩት።

በሪፖርቱ መሠረት ለከፋ አደጋ የሚጋለጡት በአብዘኛዉ በመልማት ላይ ያሉ አገሮች ናቸዉ። ምክንያቱም ሊያጋጥም የሚችለዉን አደጋ ለመቋቋም ያላቸዉ ዝግጁነት አነስተኛ ሰለሆነ ነዉ። ቢሆንም ጥቃቱ ድንገተኛና አጣዳፊ ከሆነ የለሙ ሀገሮችም ከጥቃቱ ሊያመልጡ አይችሉም። ለዚህ እንደምሳሌ የሚጠቀሰዉ የዛሬ 16 ዓመት እ.ኤ.አ. በ2003 በአዉሮፓ በከፍተኛ የአየር ሙቀት ምክንያት እስከ 70 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች የሞቱበት ክስተት ነዉ። በተለይ ለዚህ ጥቃት የተጋለጡት አረጋዊያን ነበሩ።

የአየር ንብረት ለዉጥ በጤናችን ላይ በቅጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጽእኖ ያደርጋል። ይህንኑ በግልጽ ለማሳየት ቀደም ብሎ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና ሌሎች ድርጅቶች ትብብር የወጣዉን የፖሊሲ መግለጫ ተርጉሜ ከዚህ በታች ባለዉ ሠንጠረዥ አቅርቤዋለሁ።

ከላይ የተገለጸዉ መግለጫ እንደሚያሳየዉ በአፍሪካ የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘት በያመቱ 1.7 ሚሊዮን ሰዉ ለሞት ይዳረጋል። የተለያዩ የተቅማጥና እንዲሁም የወባ በሽታዎችም የበርካታ ዜጎችን ሕይወት ይቀጥፋሉ።

ሀገራችንን በተመለከተ ከአየር ንብረት ለዉጥ ጋር ተያይዞ ስለጤናቸን ሲወራ በብዛት የሚነገረዉ ስለ ወባ ነዉ። ምክንያቱም ከዛሬ 20 እና 30 ዓመታት በፊት የወባ በሽታ ባልነበረበት ከፍተኛ ቦታዎች በመዛመት ላይ በመገኘቱ ነዉ። ለዚህ እንደ ምከንያት የሚጠቀሰዉ እነዚህ ከፍታ ቦታዎች የአየር ሙቀታቸዉ መጨመር ነዉ። በዚህ አጋጣሚ መግለጽ የሚያስፈልገዉ የወባ በሽታ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በብዙ ሀገራት ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። በዓለማችን በየዓመቱ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆን ሰዉ በወባ ይሞታል። እንደሚታወቀዉ ሁሉ ለወባ በሽታ መንስኤ የሆነዉን ረቂቅ ተዉሃስ በማስተላልፍ የምትረዳዉ በተለምዶ ቢምቢ የምንላት ነፍስ ናት። ቢምቢዋ ወዳጅ መስላ ጠጋ ብላ ወባ ከያዘዉ ሰው ያመጣችዉን ረቂቅ ህዋስ እንደ ከትባት ትወገናለች።

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በቢምቢዎች የመጠቃት ዕድላችን ከሰዉ ሰዉ ይለያያል። በዚሁ መሠረት ቢቢዎችን ወደ እኛ የሚስባቸዉ ከሰዉነታችን የሚወጣው ሽታና የምንተነፍሰዉ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ነዉ። ለኔ ሌሎች ምከንያቶችም ያሉ ይመስለኛል። ለዚህ እንደ ምሳሌ የምጠቅሰዉ ራሴን ነዉ። በመካከለኛዉ አዋሽ በሚገኘዉ በወረር እርሻ ምርምር ማዕከል በቆየሁባቸዉ ከሶስት ዓመታት በላይ ጓደኞቼና የሥራ ባልደረቦቼ በተደጋጋሚ በወባ ሲያዙ እኔ ባጋጣሚም ሆነ በሌላ ምከንያት አንድም ቀን ሊያዝ አልቻልኩም። በአካባቢዉ ግን እጅግ ከፍተኛ የሆነ የወባ በሽታ ነበር።

ይህንኑ በኛ ግቢ ዉስጥ ወደ ነበረችዉ ክሊኒክ ከሚጎርፈዉ የሰዉ ብዛት መገንዘብ ይቻላል። ለህክምና የመጣዉ ሰዉ ደሙን ከሰጠ በኋላ ዉጤቱ ሲነገረዉ የሚጠብቀዉ ቫይቫክስ ወይም ፈልሲፓረም መባልን ነዉ። ምንም እንኳ በከፍተኛ ህመም ዉስጥ ቢሆኑም ቫይቫክስ ሲባሉ ፈገግ ይላሉ። ምክንያቱም እንደ ፈልሲፓረም ፋታ ሳይሰጥ ለክፉ አይሰጥምና ነዉ።

በዚህ አጋጥሚ መጥቀስ የምፈልገዉ ለጥጥ ለቀማ ከሌላ አካባቢ የሚመጡ በርካታ ዜጎቻንን የዚሁ የወባ ሰለባ መሆናቸዉ ነዉ። የአንድ ወጣት አሟሟት ግን እስካሁን ከፊቴ አይጠፋም። ቤቴ ወደ ክሊኒኩ መወሰጃ መንገድ ላይ ነበር። አንድ ቀን በግቢያችን ውስጥ በሥራ የነበሩ ሰዎች የሆነ ሰዉ መንገድ ላይ እንደወደቀ ነገሩን። ሄደን ስናየዉ ዕድሜዉ በግምት 20 ዓመት የሚሆን ወጣት በህይወት የለም። ። እንደሚመስለኝ ወደ ክሊኒክ የሚያደርሰዉ ሰው በማጣቱ ቢያንስ ከ500 ሜትር በላይ በራሱ ተራምዶ ክሊኒኩ ለመድረስ 50 ሜትር ሲቀረዉ ወደቆ በዚያዉ ቀረ፤ ማንም ሳይደርስለት ሞቶ ተገኘ። ያቺ ፈልሲፓረምን የያዘችዉ ክፉ ቢምቢ አግኝታዉ ነዉ ለዚህ ያበቃችዉ። እኛም በአካባቢዉ ያሉ ሰዎችን አስተባብረን ቀበርነዉ። የዚህ ወጣት መርዶ ለዘመዶቹ እንኳ እንዳይላክ መታወቂያ ኪሱ ዉስጥ አልተገኘም ነበር።

እዚህ ላይ መታወቅ የሚገባዉ ወባ የሚያሰታላልፉም ሆነ የማያስተላልፉ ቢምቢዎች አሉ። ኤክስፐርቶቹ የቢምቢዋን የአቋቋም ሁኔታ በማየት የቷ ዓይነት ቢምቢ እንደሆነች በርግጠኝነት ይናገራሉ። ስለዚህ በቢምቢ ተነከስን ማለት ወባ ያዘን ማለት አይደለም።

በሀገራችን የተደረገ ሌላ ጥናት እንደሚያሳየዉ ከአየር ንብረት ለዉጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ በሽታዎች እየጨመሩ በመምጣት ላይ እንደሆኑ ነዉ። እነዚህ ለህመምም ሆነ ለሞት የሚዳርጉት በሽታዎች እንደ ዉሃ ወለድ በሽታዎች፣ በአየር ብክለት የሚመጡ የመተንፈሻ አካል ህመሞች እና ሜኒንጂቲሥን ያካትታሉ።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 15፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለውጥ — በእንስሳዎቻችን

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለውጥ — በእንስሳዎቻችን

እንስሳዎቻችን የሚለዉን ቃል የተጠቀምኩት ማናቸውንም ለምግብ የምንጠቀማቸዉም ሆነ የማንጠቀማቸዉ እንዲሁም በዉሃ ውስጥም ሆነ በየብስ የሚኖሩ ከቦታ ወደ ቦታ ሊቀንሳቅሱ የሚችሉትን ፍጥረታት ለማመልከት ነዉ። ምንም እንኳ የሰዉ ልጅ ከላይ የተቀመጠዉን መስፈርት ቢያሟላም በዚህ ምድብ ዉስጥ አላተካተተም።

እንደ ሌላው ሴክተር ሁሉ የአየር ንብረት ለዉጥ በእንስሳዎቻችንም ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ ነዉ። አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየዉ ለምግብነት የምንጠቅምባቸዉ እንደ ከብት፣ በግ፤ ፍየልና ዶሮ ያሉት ከ10 እስከ 30 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሆነ የአየር ሙቀት ተስማሚ ሲሆን የሙቀቱ መጠን ከዚህ በላይ ከጨመረ ግን የመመገብ ፍላጎታቸዉ ላይ አሉታዊ ጎን አለዉ። በዚሁ ሪፖርት መሠረት የአየር ንብረት ለዉጥ በእንስሳት ላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ተጽእኖ ያሳድራል። በተመሣሣይ መልኩ ከዚህ ቀደም በመስኩ የተሠሩ የጥናት ሥራዎችን የገመገመዉ ጽሑፍ እንደሚያሳየዉ የአየር ንብረት ለዉጥ በተለያየ መንገድ በእንስሳዎቻችን ላይ የሚያደርሰዉ ተጽእኖ ከፍተኛ ነዉ። ከነዚህ ውስጥ ዋነኖቹ 1ኛ) በቂ ያልሆነና ጥራቱ የቀነሰ መኖ፣ 2ኛ) የውሃ እጥረት፣ 3ኛ) የበሽታ መከሰት፣ 4ኛ) የሚጨምረዉን የሙቀት መጠን መቋቋም አለመቻል እና 5ኛ) የእንስሳቱን የብዝሀ ሕይወት መቀነስ ናቸው። .ዝርዝሩን ከላይ በገለጽኩት ጽሑፍ ማግኘት ይቻላል። በተመሣሣይ መልኩ የአየር ንብረት ለዉጥ በዓሣ ምርት ላይ ለውጥ እንሚያመጣ ከዚህ በፊት “የአየር ንብረት ለውጥ — በዉሃችን” በሚል በጻፍኩት ጽሑፍ ለማሳየት ሞክሬለሁ። በዚሁ መሠረት ከአፍሪካ በትልቅነቱ በአንደኝነት ደረጃ የሚገኘዉ የቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ የተሠረዉ ጥናት እንደሚያሳየዉ በዝናም እጥረት ምክንያት  የሐይቁ  ከፍታ በሚያንስበት ወቅት የዓሣ ምርትም በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል።

ሀገራችንን በተመለከተ ከአምስት ዓመት በፊት ለህትመት የበቃወ ጽሑፍ እንደሚያሳየዉ በአየር ንብረት ለዉጥና የግጦሽ አጠቃቀም ጉድለት የተነሣ በቦረና አካባቢ የከብት እርባታዉ ከፍተኛ እክል ገጥሞታል። በቅርቡ የታተመ ሌላ ጽሑፍ እንደሚያሳየዉ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት በሚደርሰዉ ከፍተኛ የአየር ሙቀት ምክንያት የወተት ምርት በ38% ሊቀንስ ችሏል። እንደሚመስለኝ ይህ አሀዝ የተገኘዉ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ከተሠራ ጥናት ሳይሆን በሌላ ሀገር ከተሠራ ነው።

የአየር ንብረት ለዉጥ በተለይም ድርቅ በከብቶቻችን ላይ የከፋ ጉዳት ያደርሳል። ምሥሉ የተወሰደወ ከኦክስፋም ድህረ ገጽ ነው።

ከዓሣና ውሃ ጋር በተገናኘ በሀገራችን የተደረገዉ ጥናት እንደሚያሳየዉ በጣና ሐይቅ አካባቢ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዝናም መጠን፣ በአየር ሙቀት እና በአየር እርጥበት ላይ ከፍተኛ መለዋወጥ ተከስቷል። በተለይም ባለፉት 22 ዓመታት አማካይ የከፍተኛዉ የአየር ሙቀት በ3.1 ድግሪ ሴንቲ ግሬድ አድጓል። በኔ ግምት ይህ በዚህ አጭር ጊዜ የታየዉ የሙቀት መጨመር ከሌሎች የዓለማችን አካባቢዎች ከተመዘገበዉ ከፍ ያለ ይመስለኛል። ጥናቱ በተካሄደበት አካባቢ ላሉ ዓሣ አጥማጆች ከተደረገዉ ቃለ መጠይቅ መረዳት እንደሚቻለዉ 42.9% የሚሆኑት ዓሣ አጥማቾች የአየር ንብረት ለውጥ በዓሣ ምርታቸዉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰባቸዉ ነዉ።

በአጠቃላይ የአየር ንብረት ለዉጥ በእንስሳዎቻችን ላይ ያደርሳል ተብሎ በሚጠበቀው ክስተት ላይ ብዙም መረጃ ማግኘት አልቻልኩም። ስለዚህ በዚህ መስክ በቂ ጥናት ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ምክንያቱም ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቀዉን የአየር ንብረት በከፊልም ቢሆን መግታት ሰለሚያስፈልግ።

በሚቀጥለዉ ጽሑፌ የአየር ንብረት ለዉጥ በጤናችን ላይ ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቀዉን ለማሳየት እሞክራለሁ።

እስከዚያዉ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 14፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለውጥ — በውሃችን

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለውጥ — በዉሃችን

እንደሚታወቀዉ ውሃ በኑሮችን ወይም በህልዉናችን እጅግ ከፍተኛ ቦታ ይዞ ይገኛል። ምክንያቱም ብንታመም እንኳ ምግብ ሳንበላ የተወሰኑ ቀናት መቆየት ብንችልም ያለ ውሃ ግን እጅግ ከዚህ ያነሰ ጊዜ ነዉ የምንቆየዉ። የውሃ ጥቅም ተዘርዝሮ አያልቅም። ከነዚህ ውስጥ ለመጠጥ፣ ለንጽህና መጠበቂያ (ለሰዉነታችንና ለምንገለግልበት ቁሳቁስ)፣ ለእርሻ፣ ለኃይል ማመንጫ፣ ለትራንስፖርት (መርከብና ጀልባ)፣ እሳት ለማጥፋት እና ለስፖርት (መዋኛ) መጥቀስ ይቻላል። ልክ እንደ እሳት ዉሃም ከመጠን ሲያልፍ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። ይህም በጎርፍ መልክ አካባቢያችንን በማጥለቅልቅ ከመኖሪያ ሥፍራችን እንድንሰደድ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ዜጎቻችንን ህይወትም ይቅጥፋል። ለምሳሌ ያህል የዛሬ 15 ዓመት (ኢ.ኤ.አ. ዲሴምበር 26፣ 2006) ሱማትራ በምትባለዉ የኢንዶኔሺያ ደሴት ላይ በደረሰው ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ጋር ተያይዞ የባህር ውሃ የሰዉ ልጅ መኖሪያ ወደ ነበረዉ የየብስ ቦታዎች በአፋጣኝ በመዉረር ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። በነዚህ ሁለት ተያያዥ ክስተቶች የተነሣ ከ200 ሺህ በላይ ሰው እንደሞተ ይገመታል። በአህጉራችን ደግሞ የዛሬ ሶስት ወር ሞገድ ቀላቅሎ ባጭር ጊዜ በወረደዉ ከፍተኛ የዝናም መጠን ምክንያት በሞዛምቢክ፣ ዚምባቢዌ እና ማላዊ የሚኖሩ እስከ 750 የሚደርሱ ሰዎች ሞተዋል።

በኛ ሀገር በትላልቅ ከተሞች ከሚደርሱት ጎርፎች መካከል በቀደምትነት የሚጠቀሰዉ በድሬዳዋ በደቻቱ ወንዝ አማካይነት በተደደጋጋሚ የሚደርሰዉ ድንገተኛ ጎርፍ ነዉ። አንድ ጥናት እንደሚሳየዉ እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2010 ባሉት አሥር ዓመታት ውስጥ በስምንቱ ዓመታት የሰው ሕይወትን ጭምር የቀጠፈ የጎርፍ አደጋ በዚሁ ወንዝ አማካይነት ተከስቷል። ከነዚህ ውስጥ ትልቁ በ2006 የተከሰተዉ ሲሆን ከ600 በላይ ሰዎች የሞት አደጋ ደርሶባቸዋል። በተመሣሣይ መልኩ በሀገራችን የልማት ሥራ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርገዉ የአዋሽ ወንዝ በክረምቱ ወቅት ከደጋዉ የሀገሪቱ ክፍል ከበርካታ ገባሮቹ ሰብስቦ ያመጣዉን ከመጠን ያለፈ ዉሃ በመካከለኛዉና ታችኛዉ አዋሽ በሚኖሩ ዜጎቻችንን ያስፈራራበታል፤ አንዳንዴም ወደ መኖሪያቸዉ ሰብሮ ይገባል። እኔም የዛሬ 30 ዓመት እሰራበት በነበረዉ የወረር እርሻ ምርምር ማዕከል ምንም እንኳ በደህና ሁኔታ የተሠራ መከላከያ ግድብ ቢሠራም በድንገት ጥሶ ገብቶ ብዙ የተለፋበት የሙከራ ሥራዎቻችንና እኛንም ለክፉ አደጋ እንዳያጋልጠን በስጋት ነበር የምናሳልፈዉ። በተለይ በማዕከል ኃላፊነት የነበሩት ሰባቱንም ቀን ለሃያ አራት ሰዓታት ወንዙ የደረሰበትን ከፍታና የግድቡን ጥንካሬ በቅርበት ይከታተሉ ነበር።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የዉሃ ብዛት ወይም ማቆር በሰብሎቻችን ላይም ከፍተኛ አሉታዊ ጎን አለዉ። ምንም እንኳ ተክሎች ካርቦን ዳይኦክሳይድን ምግብ ለመሥራት ቢጠቀሙም ኦክሲጅን ደግሞ ለሌላ አስፈላጊ ሥራ ያስፈልጋቸዋል። በውሃ ውስጥ የኦክሲጂን ዝዉዉር በጣም ዘገምተኛ ነዉ። በአየር ዉስጥ ካለው ጋር ሲነጻጸር በዉሃ ውስጥ ያለዉ የኦክሲጂን መጠን በአሥር ሺህ ጊዜ ያነሰ ነዉ። ስለዚህ ዉሃ ባቆረበት ቦታ ያሉ ተክሎች ናይትሮጂን የተባለዉንና ለዕድገታቸዉ አስፈላጊ የሆነ ንጥረ ነገር ከመሬት ውስጥ ሊወስዱ አይችሉም። በዚሁ ምክንያት የናይትሮጅን መጠን አዲስ ባቆጠቆጡ ቅጠሎች ላይ ሲያንስ ተክሉ በአሮጌ ቅጠሎቹ ውስጥ ያለዉን ናይትሮጂን ወደ አዲሶቹ ቅጠሎች ያጓጉዛል። ለዚህ ነዉ የናይትሮጂን እጥረት ምልክት የሆነዉ ቢጫ መልክ በአሮጌዎቹ ቅጠሎች ላይ የምናየዉ። ሳላስበው በውሃ ብዛት ምክንያት በራሳችንም ሆነ በተክሎቻችን ላይ ስለሚደርሰዉ አደጋ ውስጥ ገባሁ እንጂ የዛሬዉ ጽሑፌ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት በዉሃችን ላይ የሚደርሰዉን ክስተት ለመዘገብ ነዉ።

የአየር ንብረት ለዉጥ በዉሃ ላይ ሰለሚያደርሰዉ ጉዳት በርካታ ጥናቶች ተካሂደዋል። በአፍሪካ በትልቅነታቸዉ ከሚታወቁት ሐይቆች መካከል የቪክቶሪያና የቻድ ሐይቆች ሊጠቀሱ ይችላሉ።  የቪክቶሪያ ሐይቅ በትልቅነቱ በአፍሪካ አንደኛ በዓለም ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በኬኒያ፣ ኡጋንዳና ታንዛኒያ ይዋሰናል። ከዚህ በፊት የታተመ ሪፖርት እንደሚያሳየዉ በዝናም እጥረት ምክንያት የቪክቶሪያ ሐይቅ የዉሃዉ ከፍታ በሚያንስበት ወቅት በዓሣ ምርት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ጎን ነበረዉ። የቻድ ሐይቅ ደግሞ በካሜሩን፣ ቻድ፣ ኒጀር እና ናይጀሪያ የሚዋሰን ሲሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአፍሪካ አንዱ ትልቅ ሐይቅ ነበር። በተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ድርጅት ባወጣዉ ሪፖርት መሠረት ባለፉት 60 ዓመታት ብቻ የቻድ ሐይቅ መጠን በ90% ቀንሷል። ሐይቁ የሸፈነዉ ስፋት ደግሞ እ.ኤ.አ. 1963 ከነበረበት 26 ሺህ ስኰዌር ኪሎ ሜትር አሽቆልቁሎ በአሁኑ ጊዜ 1500 ስኰዌር ኪሎ ሜትር ብቻ ነዉ።

ወደ ሀገራችን ስንመለስ በኢትዮጵያ ወደ ሰባት የሚጠጉ ትላልቅ የወንዝ ተፋሰሶች አሉ። እነርሱም ወደ ምዕራብ አቅጣጫ በመፍሰስ ከነጭ አባይ ጋር የሚቀላቅሉት ሶስቱ ወንዞች (አባይ፣ ተከዜና ባሮ)፣ ወደ ደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ በመፍሰስ ወደ ሱማሊያ የሚዘልቁት ሁለት ወንዞች (ዋቤ ሸበሌና ገናሌ)፣ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ወደ ሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ በመፍሰስ በጂቡቲ ድንበር ላይ ወደሚገኘዉ የአቤ ሐይቅ ጉዞዉን የሚያበቃዉ የአዋሽ ወንዝና ወደ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በመፍሰስ ኢትዮጵያና ኬኒያ ድንበር ላይ ወደሚገኘዉ የቱርካና ሐይቅ የሚገባዉ የጊቤ-ኦሞ ወንዝ ናቸዉ። እነዚህ ትላልቅ ወንዞች ስማቸዉ ይጠቀስ እንጂ እነርሱን ለዚህ ዝና ያበቋቸዉ በርካታ ገባር ወንዝች ናቸዉ። እነዚህን ታዋቂ ወንዞች ከነገባሮቻቸዉ የሚያሳየዉ በኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ድርጀት ባልደረባ የተሣለዉን ካርታ ከዚህ በታች ማየት ይቻላል።

በምሥሉ የሚታየው በኢትዮጵያ ታዋቂ የሆኑ ወንዞችና ገባሮቻቸዉ የሚፈሱበት አቅጣጫ ነዉ። በደማቅ ቀለም የሚታዩት ዋና የሆኑ ወንዞች ነዉ። የምሥሉ ምንጭ› https://www.academia.edu/7228560/drainage_in_ethiopia

ኢትዮጵያ ካሏት በርካታ ወንዞች በተጨማሪ ሐይቆችና የከርሰ ምድር ዉሃም ሊጠቀሱ ይቻላል። በብዙ ሀገራት ከሌሎች ሴክተሮች ጋር ሲወዳደር ለእርሻ የሚዉለው የውሃ መጠን ከፍተኛ ድርሻ ይይዛል። ኢትዮጵያ ባላት የከርሰ ምድር ዉሃ ላይ ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ለመስኖ እርሻ ልንጠቀምበት የምንችለዉ የከርሰ ምድር ዉሃ በቅርበት (ማለትም እስከ 20 ሜትር ጥልቀት) የሚገኘዉ በኦሞና በአዋሽ ወንዞች እና በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ነዉ። ቢሆንም የከርሰ ምድር ዉሃ እንደ ተጨማሪ ካልሆነ በስተቀር ለብቻዉ ለመስኖ እርሻ በቂ አቅርቦት እንደማይኖረዉ የጥናቱ ዉጤት ያሳያል።

እንደ አንዳንዶች ግምት ኢትዮጵያ በመስኖ ማልማት ከምትችለዉ 3.5 ሚሊዮን ሄክታር ዉስጥ እስካሁን የተጠቀመችበት 5% ብቻ ነዉ። ቢሆንም ባንዳንድ ሥፍራዎች በአየር ንብረት ለዉጥም ይሁን የመስኖ ዉሃን ከመጠን ባለፈ በመጠቀም መሆኑ በውል ባላዉቅም በገሪቱ የሚገኙ አንዳንድ ሐይቆች አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ከነዚህ ወስጥ ሙሉ በሙሉ ለመድረቅ የበቃዉ የሀረማያ ሀይቅ ነዉ። ለዚህ ራሴ ምስክር ልሆን እችላለሁ። ከ30 ዓመታት በፊት የሀረማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ሐይቁ በህይወት ነበር። ዛሬ ግን በቦታው የለም። እንደ አንዳንዶች አባባል የዝዋይና የአቢያታ ሐይቆች ለአደጋ እየተጋለጡ ነዉ። በቅርቡ ለህትመት የበቃዉ የጥናት ጽሑፍ እንደሚያሳየዉ በመቂና ከታር ወንዞች ምክንያት በደለል እየተሞላ የሚገኘዉ የዝዋይ ሐይቅ መነሻዉ ከአየር ንብረት ለዉጥ ጋር እንደሚገናኝ ነዉ።

የአየር ንብረት ለዉጥ በወንዞቻችን ላይ ሰለሚያደርሰዉ ክስተት በተመለከት ሰፊ ጥናት ተካሂዷል። በኢትዮጵያዉያን፣ ካናዳዊያንና ፊንላዳዊያን በጋራ በሠሩት ጥናት ላይ በመመርኮዝ በቅርቡ ለህትመት የበቃዉ ጽሑፍ አራት ተፋሰሶችን በጥናቱ አካቷል። እነዚህም አዋሽ፣ ባሮ፣ ገናሌና ተከዜ ናቸዉ። በጥናቱ መሠረት የተደረሰበት ትንበያ እንደሚያሳዉ እ.ኤ.አ. በ2050 የአየር ሙቀት በ2.3 ድግሪ ሴንቲግሬድ የሚጨምር ሲሆን በ2080 ደግሞ የ3.3 ድግሪ ሴንቲግሬድ ጭማሪ ያሳያል። በተመሣሣይ መልኩ ዓመታዊ የዝናም መጠን በ2050 በ3% የሚያድግ ሲሆን በ2080 በ6% እድገት ያሳያል። በዚሁ መሠረት የአራቱ ወንዞች የፍሰት መጠን በ2050 ከ3-18% እንዲሁም በ2080 ከ6-33% እድገት ያሳያል። ስለዚህ በሀገራችን በሚቀጥሉት 30 እና 60 ዓመታት ውስጥ የዝናም መጠንም ሆነ የወንዞች የፍሰት መጠን እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንደማይመጣ ይተነብያል። ለጥናቱ ተሣታፊዎችም እንቆቅልሽ የሆነባቸዉ ከዚህ ጥናት የተገኘዉ ትንበያ ከነባራዊዉ ሁኔታ ጋር አለመጣጣሙን ንዉ። ምክንያቱም በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች የዝናም መጠንም ሆነ የወንዝ ፍሰት እየቀነሰ ስለመጣ ነወ። እኔ ራሴ ባደኩበት አካባቢ የነበረ መጠነኛ ይዘት ያለዉ ወንዝ ነበር። ድሮ በልጅ አይኔ ትልቅ ወንዝ ይመስለኝ ነበር፤ በክረምት ሲሞላማ እጅግ ያሰፈራራን ነበር። ከብዙ ጊዜያት በኋላ ተመልሼ ሳየው ወንዝ ሳይሆን ትንሽ ኩሬ መስሎ ታየኝ። የአየር ንብረት ለዉጥ በዚህ ወንዝ ላይም ተጽእኖ አድርጎ ከሆነ መረጃ የለኝም።

በአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ ላይ የተደረገዉ ጥናት እንደሚያሳየዉ የአየር ሙቅትም ሆነ የዝናም መጠን ባንዳንድ ሥፍራዎች ሲጨምር በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ይቀንሳል። በዚሁ በአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ የተሠራ ሌላ ጥናት እንደሚያሳየዉ በሚጨምረዉ የአየር ሙቀት ምክንያት የዝናም መጠን እንደ ሚቀንስ ይጠበቃል። ስለዚህ ለመስኖ እርሻና ለሌሎች የልማት ሥራዎች የሚስፈልግ ዉሃ እጥረት እንደሚኖር ይተነብያል። ስለዚህ በተለያዩ ጊዜ የተደረጉ የጥናቱ ዉጤቶች ተመሣሣይነት የላቸዉም።

በሌላ በኩል በአባይ ወንዝና አካባቢዉ የተደረገዉ ጥናት እንደሚሳየዉ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት የዝናም መጠን ከ7 እስከ 48% ሲጨምር የወንዙ መጠን ደግሞ ከ21 እስከ 97% ያድጋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በሚከሰተዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት የዝናም ወቅት አሁን ካለው ከሰኔ እስከ መስከረም ወደ ሌላ ጊዜ እንደሚቀየር ይገመታል።

ማጠቃለያ

ከላይ የተጠቀሱት መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በዝናም መጠንና በወንዞች ተፋሰስ ላይ የተደረጉት ትንበያዎች ተመሣሣይነት የላቸዉም። አንዳንዶቹ ጥናቶች የዝናም መጠንም ሆነ የወንዞች ተፋሰስ ብዛት እንደሚጨምር ትንበያ ቢሰጡም ሌሎች ደግሞ በተቃራኒዉ ይቀንሳል ይላሉ። የሚገርመዉ ባንድ ወንዝ ላይ የተሠሩ ሁለት ጥናቶች የተለያየ ትንበያ መስጠታቸዉ ነዉ። በኔ ግምት ይህ ሊሆን የሚችለው ትንበያውን ለማድረግ ጥናቶቹ የተጠቀሙባቸዉ መንገዶች ወይም ሞዴሎች የተለያዩ ሊሆኑ ሰለሚችሉ ሲሆን ሌላዉ ደግሞ ለትንበያው እንደ መነሻ የተጠቀሙባቸዉ ዓመታት የተለያዩ ሊሆኑ ስለሚችሉ ነዉ። ሰለዚህ የተለያዩ ተፋሰስ አካባቢችን እንዲሁም የከርሰ ምድር ዉሃን የሚያካትት ጠልቅ ያለ ጥናት በብሔራዊ ደረጃ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

በሚቀጥሉት ተከታታይ ጽሑፎቼ የአየር ንብረት ለዉጥ በከብቶቻችንና በጤናችን ላይ ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቀዉን ለማሳየት እሞክራለሁ።

እስከዚያዉ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 13፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለውጥ — በደናችን (ዛፎቻችን)

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለውጥ — በደናችን (ዛፎቻችን)

እንደሚታወቀዉ ሁሉ ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት ወደ 40% የሚጠጋዉ የሀገራችን ክፍል በደን የተሸፈነ ነበር። የዛሬ 35 ዓመታት ገደማ ደን (ወይም ፎረስትሪ) የሚባለዉን ኮርስ ያሰተማሩን መምህር እንደነገሩን ከሆነ በዚያን ወቅት ደን የሀገሪቱን 2-3% ብቻ ይሸፍን ነበር። ነገር ግን በርካታ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩን በኢትዮጵያ ባሁኑ ጊዜ የደን ድርሻ ወደ 10-15% አድጓል። ይህ መረጃ ትክክል ከሆነ በሀገሪቱ ዉስጥ ከፍተኛ የደን ተከላ ተደርጓል ማለት ነዉ። መረጃው ትክክለኛ ከሆነ ለማለት ያስገደደኝ በኢትዮጵያ ደንን የምናገኘዉ በተወሰኑ ሥፍራዎች ብቻ ሰለሆነና ይህም በኔ ግምት ከላይ ከተጠቀሰዉ ቁጥር የሚያንስ ስለሚመስለኝ ነዉ። ቢሆንም ከላይ የተገለጸዉ 10-15% የደን ሽፋን በቂ ነዉ ማለቴ አይደለም። ምክንያቱም እስከ 90% የሚሆን መሬታቸዉን በደን የሸፈኑ ሀገሮችም ስላሉ ነዉ።

በቂ ደን እንዲኖረን አዲስ ዛፍ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉት መልሰዉ እንዳይጨፈጨፉ እንክብካቤ ልናደርግላቸዉ ይገባናል። የዛፎችን ጭፍጨፋ በተመለከተ በአስረስ ጫካ ላይ የደረሰዉ ዓይነት ግፍ እስካሁን ትዝ ይለኛል። ምንም እንኳ የመሬታቸዉን መጠን በዉል ባላዉቀውም እኔ ያደኩበት አካባቢ አቶ አስረስ የሚባሉ በንጉሡ ዘመን የመሬት ባለቤት የነበሩ ሰዉ ነበሩ። እኝህ ሰዉ በመሬታቸዉ ላይ በርካታ ባህር ዛፍ በመትከል በእንክብካቤ ይዘዉት ነበር። ታዲያ የየካቲት 25 ቀን 1967ቱ መሬት ላራሹ አዋጅ መጥቶ ያንን እሳቸዉ ተክለዉና በደህና ሁኔታ የተንከባከቡትን ደን ሙሉ በሙሉ ወረሰባቸዉ። ደኑ ከርሳቸዉ ቁጥጥር ዉጭ ከሆነ በኋላ ማንም በአካባቢዉ የሚያልፍ ሰዉ በፈለገዉ መንገድ እንዲጨፈጭፍ ከልካይ አልነበረዉም። ደግነቱ አቶ አስረስ የተከሉት ባህር ዛፍ ሆነና እንደፈለጉ ቢጨፈጭፉት እንደገና እያቆጠቆጠ እስከዛሬም አለ። አለ ይባል እንጂ ዛፎቹ በተደጋጋሚ የመጨፍጨፍ አደጋ ሰለደረሰባቸዉ የጥራት ደረጃቸዉ በጣም ዝቅተኛ ነዉ። ምንም እንኳ በግሌ መሬት ላራሹን ብደግፍም ባፈጻጸሙ ላይ በነበረበት ችግር ምክንያት በተለይ እንደ አቶ አስረስ ዓይነት በመሬታቸዉ ላይ የልማት ሥራ ሲሰሩ የነበሩ ሁሉ በራሳቸዉ ጥረት ያለሙት ደን በመወረሱና ያለከልካይ ለበርካታ ዓመታት እንዲጨፈጭፍ በመፈቀዱ ከዚያ በኋላ በግላቸዉ ዛፍ የሚተክሉ ግለሰቦችን ማግኘት አስቸጋሪ ነበር ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም። ምክንያቱም አንድ ቀን የአስረስ ዕጣ ይደርሰናል ብለዉ ሰለሚሰጉ ነዉ።

ይህ በምሥሉ ላይ የሚታየዉ ዛፍ በኢትዮጵያ በዕድሜ ትልቁ የሆነዉ ባህር ዛፍ ሲሆን እንጦጦ በሚገኘዉ የቀድሞ የሚኒሊክ ቤተ መንግሥት ዉስጥ ቆሞ ይገኛል። ለመሆኑ ይህ ግዙፍ ዛፍ ምን ያህል ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ አካባቢያችን እንዳያፈተልክ አምቆ ይዞልናል? ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ ኅዳር 22 ቀን 2011 ዓ.ም.

ሁለተኛዉ መጠነ ሰፊ የደን ጭፍጨፋ ያየሁት በጋምቤላ አካባቢ ነዉ። በ1977 በሀገራችን በደረሰዉ ድርቅ ምክንያት የተጎዱ ወገኖቻችንን ለማስፈር በተደረገዉ ዘመቻ ጊሎ አቦል የሚባል ሥፍራ ተመድበን ለሶስት ወራት አቅማችን በፈቀደዉ መጠን ቤትም ባይሆን ጊዜያዊ ማረፊያ ስንሰራ ቆይተን ነበር። ታዲያ በመመለሻችን ቀን በአዉቶቢስ ውስጥ ሆኜ ያየሁትን ዓይነት የደን ጭፍጨፋ እስካሁን አላየሁም። እጅግ ሰፊ የሆነ መሬት ላይ የነበሩ ትላልቅ ዛፎች በዶዘር እንዲገረሰሱ ከተደረጉ በኋላ ገሚሶቹ ከቦታዉ ተነስተዋል፤ የተቀሩት ደግሞ እዚያዉ ለዘመናት ከቆሙበት ሥፍራ አጠገብ ተጋድመዉ ነበር። እንደመሰለኝ የደን ምንጣሮ የተደረገዉ ለምግብ የሚሆኑ ሰብሎችን ለመዝራት ታስቦ ነዉ።

በሌላ በኩል በታዋቂዊዉ የናሽናል ጂኦግራፊክ መጽሔት ላይ Ethiopia’s ‘church forests’ are incredible oases of green በሚል በቅርቡ የታተመዉ ጽሑፍ እንደሚሳየዉ ጥናት በተደረገባቸዉ በርካታ የሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢ እንደታየዉ በቤተ ክርስቲያናት አካባባቢ ዛፎች ሳይቆረጡ በደህና ሁኔታ ተጠብቅዉ ሊቆዩ ችለዋል። ይህንንም ከዚህ በታች ባለዉ ምሥል ማየት ይቻላል። በዚሁ መሠረት የአካባቢዉ ብዝሀ ሕይወትም ሊጠበቅ ችሏል። በዚህ በጎ ሥራ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ካደረጉት መካከል የካሊፎኒያ ሣይንስ አካዳሚ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሜግ ሎውማን በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።በኢትዮጵያ በኩል በጥናቱ የተሣተፉት ዶክተር ወርቁ ሙላትና ዶክተር አለማየሁ ዋሴ ይገኙበታል። ቤዛ የምትባል ከዚህ ሥራ ጋር የምትገናኝ መጽሔት በእንግሊዘኛና አማርኛ አሳትመዉ ለአንባቢያን አድርሰዋል። እኔም በኦንላይን ገዝቼ ለማንበብ ችያለሁ። የመጽሔቱ የፊት ሽፋን ከዚህ በታች በምስሉ ይታያል።

ከላይ ያሉት ምሥሎች የሚያሣዩት (በስተግራ) ዛፎች እንዴት በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ተጠብቁዉ እንዳሉ ሲሆን (በስተቀኝ) ቤዛ ተብሎ የተሰየመዉ የዛፎች ጥበቃ ላይ የሚያተኩር መጽሔት ሽፋን ነው። ምንጭ፣ በስተግራ ያለው ከዚህ ድህረ ገጽ ሲሆን በስተቀኝ ያለዉ ከመጽሔቱ ሽፋን ፎቶ በዘሪሁን ታደለ።

በሀገራችን በርካታ የዛፍ ተከላ ፕሮግራሞች ባለፉት ሶስት አሥርት ዓመታት ተካሂደዉ ነበር። ከነዚህ ዉስጥ በደንገጎ፣ ቁሉቢ፣ ሙኔሣ ወዘተ ትዝ ይለኛል። በዚህ አጋጣሚ መጥቀስ የምፈልገዉ በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በተለምዶ “አዱኛ ላይብረሪ” ተብሎ የሚጠራ የደን መምህር በነበሩት በአቶ አዱኛ የተተከለ አካባቢዉን በጥሩ ሁኔታ የለወጠ ሥፍራ ነበር። ካለው የጸጥታ ሁኔታ የተነሣ በርካታ ተማሪዎች ይህን ጫካ እንደማጥኛ ሥፍራ አድርገዉ ይጠቀሙበት ነበር። በዚህ አገለግሎቱም ነው “አዱኛ ላይብረሪ” የሚለዉን ሥያሜ ያገኘዉ።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ዛፎች ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ። ምክንያቱም ዛፎች ወደ አካባቢያችን የሚለቀቀውን ዋነኛ የግሪን ሀዉስ ጋዝ አካል የሆነውን ካርቦን ዳይኦክሳይድን አምቀዉ ስለሚይዙ ነዉ። ከአንድ ዛፍ ጠቅላላ ክብደቱ ዉስጥ ግማሹን የሚይዘዉ ካርቦን ነዉ። እንደ አንድ ሪፖርት ግምት አንድ 12 ዓመት የሆነውና 600 ኪ.ግ. የሚከብድ ዛፍ በዉስጡ 859 ኪ.ግ. ካርቦን ዳይኦክሳይድ አምቆ የሚይዝ ሲሆን ይህም በዓመት 72 ኪ.ግ. ማለት ነዉ። በዚሁ ሪፖርት መሠረት በ200 ሄክታር ላይ ያለ ደን (በአንድ ሄክታር 650 ዛፍ ቢኖር) በ12 ዓመት 111,670 ቶን (ወይም 111 ሚሊዮን ኪ.ግ.) ካርቦን ዳይኦክሳይድ አምቆ ይዟል ማለት ነዉ። ይህ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ነዉ። ስለዚህ አንድ ዛፍ ተቆረጠና ተቃጠለ ስንል በውስጡ የያዘዉ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ አካባቢያችን አፈተለከ ማለት ነዉ። በተመሣሣይ መልኩ ምንጣሮና ቃጠሎ በአንድ ሄክታር ወይም በሺሆች በሚቆጠሩ ሄክታሮች ላይ ቢደርስ ምን ያህል ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ አካባቢያችን እንደሚያፈተልክ መገመት ይቻላል።

ማጠቃለያ

በቅርቡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሁሉም ዜጋ ዛፍ እንዲተክል ጥሪ ማቅረባቸዉ ይታወሳል። እንዲተከል የጠየቁትም አራት ቢሊዮን ዛፍ ሲሆን በነፍስ ወከፍ 40 ዛፍ ይደርሰናል ማለት ነዉ። ይህንኑ ራሳቸዉ አርአያ በመሆን የመጀመሪዋዉን ዛፍ በግንቦት አጋማሽ 2011 ካስጀመሩ ወዲህ እስካሁን ድረስ በርካታ ዛፎችን በመትከል ላይ ይገኛሉ። በቅርቡ ከመገናኛ ብዙሃን እንደሰማሁት በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ አንድ መቶ ዛፋቸዉን ተክለዋል። ከላይ በተሰላዉ መሠረት አራት ቢሊዮኑ ዛፍ 3.4 ቢሊዮን ቶን የሚሆን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ አካባቢያችን እንዳያፈተልክና ጉዳት እንዳያደርስብን ያደርጋል ማለት ነው።

እኛስ በተራችን እነዚህን ከሀገራችንም አልፎ ለአህጉራችንም ሆነ ለዓለማችን እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ዛፎችን በመትከል ተሳትፎ አድርገናል ወይ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ዛፎቹን ለመትከል ፍላጎት ያለን ደግም የሚከተሉት መረጃዎች ያስፈልጉናል። በአካባቢያችን ያሉ የከተማም ሆነ የገጠር ቀበሌዎች ይህንን የዛፍ ተከላ ዘመቻ ለመምራት ዝግጁ ናቸዉን? በእያንዳንዱ ቀበሌ የሚተከሉት ዛፎች ወይም ችግኞች ተለይተው ታውቀዋልን? በቂ አቅርቦትስ አለ ወይ? ተከላዉ የሚካሄድበት ቦታስ ተለይቶ ታዉቆአልን? ይህ ሁሉ መረጃ ካለ እያንዳንዱ ቀበሌ ይህንን የዛፍ ተከላ ፕሮግራም ቢያስተባብሩ ዉጤታማ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ዛፎች በርካታ ጥቅም ቢኖራቸዉም የዛሬዉ ጽሑፌ ያተኮረዉ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሰዉን ቀዉስ በመከላከል ላይ ባላቸዉ አስተዋጽኦ ላይ ነው። በሚቀጥሉት ተከታታይ ጽሑፎቼ የአየር ንብረት ለዉጥ በከብቶቻችን፣ ዉሃችንና ጤናችን ላይ ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቁዉን ለማሳየት እሞክራለሁ።

እስከዚያዉ በቸር ይግጠመን።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 12፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለውጥ — በአረሞች መስፋፋት

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለውጥ — በአረሞች መስፋፋት

አረም ማለት ከሚፈለግበት ቦታ ዉጭ የሚበቅል ተክል ንዉ። ልምግብነት የምንጠቀማቸዉ ስብሎችም እንድ አረም የሚቆጠሩብት ጊዜ ይኖራል። ለምሳሌ በስንዴ ማሣ ዉስጥ የገብስ ወይም የዳጉሣ ተክሎች ቢገኙ እንደ አረም ይቆጠራሉ። ምክንያቱም የስንዴዉን የጥራት ደረጃ ይቀንሳሉና ነዉ። አንዳንዶች አረምን ሲገልጹ “ያልተጋበዝ እንግዳ ይሉታል”። የሰብሎቻችንን የዘር ጥራት መቀነስ ብቻ ሳይሆን አረም ቢያንስ በሶስት መንገድ በምናሳድገዉ ተክል ላይ ትፅዕኖ ያደርሳል። እነዚህም የፀሐይ ብርሃንን፣ ውሃንና ከመሬት ውስጥ የሚገኙ ማዕድናትን በመሻማት ነው። እንደ እድገት ሁኔታቸዉና በተክሎቻችን ላይ በሚያደርሱት የተፅዕኖ ዓይነት አረሞች በሶስት ሊከፈሉ ይችላሉ። እነርሱም ቅጠለ-ሰፋፊ፣ ሣር-ነክ እና ጥገኛ ናቸዉ። ቅጠለ-ሰፋፊ አረሞች የፀሐይ ብርሃን ሰብሎቻችን ዘንድ እንዳይደርስ በመጋረድ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ። ቅጠለ-ሰፋፊ አረሞችን የምንቆጣጠር ከሆነ ሣር-ነክ የሆኑ አረሞች ደግሞ በተራቸው ጠንቅ መሆን ይጀምራሉ። ጥገኛ አረሞች (ወይም በእንግሊዘኛ ፓራሲቲክ ዊድስ) የሚባሉት ምንም እንኳ ለተመልካች ራሳቸዉን ችለዉ የሚያድጉ ቢመስሉም እነርሱ ግን በሌላዉ ተክል ላይ ተጣብቀዉና ዋናዉ ተክል ለፍቶ ያዘጋጀዉን ምግብ ይሻሙታል። እነዚህን የተለያዩ የአረም ዓይነቶች በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተለያዩ መንገዶች አሉ። ዉጤታነታቸዉም እንደዚሁ የተለያየ ነው።

ምሥሉ የሚታየዉ አቀንጭራ (ወይም ስትራይጋ) የሚባለዉ ጥገኛ አረም የበቆሎ ተክል ላይ ጥቃት ሲያደስ ነዉ። ምሥሉ የተገኘዉም ከዚህ ድህረ ገጽ ነዉ።

የዛሬዉ ጽሑፌ የሚያተኩረዉ የአየር ንብረት ለውጥ ለሰብሎቻችን ጠንቅ በሆኑ አረሞች ላይ የሚኖረዉ ተፅዕኖ ላይ ነዉ። ከአየር ንብረት ዉስጥ ለአረሞች መስፋፋት የሚረዱት የአየርና የአፈር ሙቀት፣ የዝናም መጠንና የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን በዋናነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ ለነዚህ ለአረሞች መስፋፋት መንስዔ በሆኑት ላይ የራሱ ተፅዕኖ እንዳለዉከዚህ በፊት በጻፍኳቸዉ ጽሑፎቼ ለማሳየት ሞክሬአለሁ።  ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚጨምረዉ የአየር ሙቀት ባብዘኞቹ ሰብሎቻችን ላይ አሉታዊ ጎን ቢኖረዉም ባንዳንድ አረሞች ላይ ግን የመስፋፋትና አካባቢዉን የመዉረር አዝማሚያ ያሳያል። በተመሣሣይ መልኩ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚጨምረዉ የአፈር ሙቀተም የአረም ዘሮች በፍጥነት በቅለዉ በሰብሎቻችን ላይ ጉዳት ማድረስ እንዲችሉ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። በዚሁ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚጨምረዉ የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠንም ለበርካታ የአረም ዓይነቶች ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጥናቶች ይስረዳሉ።

የአየር ንብረት ለውጥ በአረሞች ላይ የሚያመጣዉን ተፅዕኖ በሚመለከት በአውስትራሊያ ሣይንቲስቶች የተጻፈዉ የቴክኒክ መመሪያ በርካታ ነጥቦችን አካቷል። ይህም የተለያዩ አረሞች የሚስፋፉበትን ሁኔታና እነዚሁ አረሞችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል መወሰድ የሚገባ የመፍትሔ ሃሳቦችን ያቀርባል። እንደዚህ መመሪያ አባባል “ምንም እንኳ አረም በግብርናችንና በብዝሀ ሕይወታችን ላይ ጠንቅ ቢሆንም የአየር ንብረት ለውጥ ደግም እነዚህን ጠንቀኛ አረሞች ለመግታት በሁለት ምክንያት አዳጋች ያደርገዋል። የመጀመሪያዉ በርካታ የአረም ዓይነቶች ስለሚከሰቱ ለቁጥጥር አመቺ ባለመሆኑ ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ እነዚህ የአረም ዓይነቶች ከፍተኛ የተስፋፊነት ፀባይ ስለላቸዉ ነዉ። ምንም እንኳ ይህ መመሪያ የተዘጋጀዉ አውስትራሊያ ባለዉ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ቢሆንም ለሀገራችንንም ተመሣሣይ ዓይነት መመሪያ ቢዘጋጅ ጠቃሚ ይሆናል።

ሀገራችንን በተመለከተ በርካታ ተስፋፊ አረሞች የተመዘገቡ ሲሆን እነርሱም በአጭር ጊዜ ሰፋፊ ሥፍራዎችን በማጥቃት ለሰብሎቻችን ብቻ ሳይሆኑ ለመስኖ ውሃ ሥርጭትና ለሌሎችም ሴክተሮችም ጠንቅ እየሆኑ ይገኛሉ። በቅርቡ በዶክተር ኃይሉ ሽፈራዉና የሥራ ባልደረቦቻቸዉ ጥናታቸዉ ተጠናቀዉ ለህትመት የበቁ ሁለት ጽህሑፎች (1 እና 2) እንደሚያሳዩት ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ የተባለ ተክል በአጭር ጊዜ ወስጥ ተስፋፍቶ ተገኝቷል። ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ተብሎ የዛሬ 40 ዓመታት ገደማ ወደ አካባቢዉ እንዲገባ የተደረገዉ ይህ ተክል በአሁኑ ጊዜ ጠንቅ እየሆነ መጥቷል።

በተለይ ጥናቱ በተካሄደበት የአፋር ክልል ይህ አደገኛ ተክል ባጭር ጊዜ ውስጥ ለመስፋፋቱ ማስረጃ የሚሆነዉ ጥናቱ ባለፉት 31 ዓመታት የነበረዉን የዚህን አደገኛ ተክል ሥርጭት ከገመገመ በኋላ ነዉ።። ይህ በሳተላይት መረጃ ጭምር የታገዘዉ ጥናት እ.ኤ.አ. 1986፣ 2000 እና 2017 የነበረዉን የተክሉን ሥርጭት ግንዛቤ ውስጥ አስገብቷል። እንደ አጥኝዎቹ ግምት ይህ አደገኛ ተክል በያመቱ ከ30 ሺህ በላይ የሚሆን መሬት በመዉረር ላይ ይገኛል። ይህንን በአደገኛ ሁኔታ በመስፋፋት ላይ የሚገኘዉን ተክል ለመግታት የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር በብሔራዊ ደረጃ እስትራቴጂ በመቅርስ ለተግባራዊነቱ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

ክዚህ ሌላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየዉ የዚህ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የመስፋፋት የፕሮሶፒስ ፀባይ ከአየር ንብረት ለዉጥ ጋር እንደሚገናኝ ነዉ። በዚሁ መሠረት የሜዲተራኒያን፣ የመካከለኛዉ ምሥራቅና የሰሜን አሜሪካ አካባቢዎች ለዚህ አደገኛ ተክል በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቂ እንደሚሆኑ ነዉ።

ከላይ በምሥሉ የሚታየዉ ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ የሚባለው እጅግ በተፋጠነ ሁኔታ በተለይ በአፋር ክልል በመስፋፋት ላይ የሚገኝ ተክል ነዉ። የተክሉ ምሥል የተገኘዉ ከዚህ ድህረ ገጽ ነዉ።

በሚቀጥለዉ ጽሑፌ የአየር ንብረት ለዉጥ በሌሎች ሴክተሮች ላይ ያደርሳል ተብሎ የሚገመትዉን ለማሳየት እሞክራለሁ።

እስከዚያዉ በቸር ይግጠመን።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 10፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለውጥ — በሰብሎቻችን

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለውጥ — በሰብሎቻችን

የአየር ንብረት ለዉጥ በተለያዩ ሴክቴሮች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ እንደሚገኝና ለወደፊቱም በከፋ ሁኔታ እንደሚቀጥል በተለያዩ መድረኮች በመገለጽ ላይ ይገኛል። የዛሬዉ ጽሁፌ የሚያተኩረዉ የአየር ንብረት ለዉጥ በሰብሎቻችን ላይ ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቀዉን ተፅዕኖ በአጭሩ ለማሳየት ነዉ። እንደሚታወቀው ሁሉ ሰብሎቻችን አጠቃቀማቸዉንን መሠረት ባደረገ በተለያዩ ክፍሎች ይመደባሉ። ከነዚህ ዉስጥ ዋነኞቹ 1ኛ) ብርዕና አገዳ (ምሳሌ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ በቆሎ፣ ዳጉሣ)፤ 2ኛ) ጥራጥሬ (ባቄላ፣ አተር፣ ሽምብራ፣ ምስር፣ ጓያ፣ ግብጦ)፤ 3ኛ) ሥራ ሥር (ድንች፣ ስኳር ድንች፣ እንሰት)፤ 4ኛ) የቅባት እህል (ኑግ፣ ተልባ፣ ኦቾሎኒ)፤ 5ኛ) አትክልት (ጎመን፣ ቲማቲም፣ ካሮት)፤ 6ኛ) ፍራፍሬ (ማንጎ፣ ብርቱካን፣ ሙዝ፣ አናናስ)፤ 7ኛ) የስኳር ሰብሎች (ሸንኮራ አገዳ)፤ 8ኛ) የጭረት ሰብሎች (ጥጥ)፤ 9ኛ) ንቃት ሰጪ (ቡና፣ ሻይ) እና 10ኛ) የከብት መኖ (አልፋልፋና የተለያዩ የሣር ዓይነቶች) ናቸዉ። እነዚህና ስማቸዉ ከላይ ያልተገለጹት ሰብሎች በተለያየ የአየር ንብረትና የአፈር ሁኔታ ይተከላሉ ወይም ይዘራሉ። ቢሆንም ለእያንዳንዱ ሰብል ምቹ የሆነ የአየር ንብረትና የአፈር ሁኔታ ሊገኝላቸዉ አይቻልም። ስለዚህ እነዚህ ሰብሎች ካለዉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በመጋፈጥ በማደግና ያላቸዉን የመጨረሻ ጉልበት አሟጠዉ የተወሰነም ቢሆን ምርት ይሰጣሉ። ያቺኑ ከብዙ ጥቃት ተርፋ የቀረችዉን ምርት ደግሞ ገበሬዎቻችን አጭደዉና ወቅተዉ ለራሳቸዉ ቤተሰብና ለሌሎች ተመጋቢዎችም እንዲደርስ ያደርጋሉ።

የአየር ንብረት ለዉጥ በሰብሎቻን ምርት ላይ የሚያደርሰዉ ተፅዕኖ በሰፊዉ ተጠንቷል። እነዚሁ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዓለማችን በአማካይ ይህ መጥፎ ክስተት የሚያደርሰዉ የምርት ቅነሳ ከ3.5-12.9% በስንዴ፣ ከ34.6-35.6% በበቆሎ እና ከ10-15% በሩዝ እንደሚሆን ነዉ። ለዛሬዉ ጽሑፌ የተወሰኑትን በተለይም በአፍሪካ ላይ የሚተኩሩትን ለማሳየት እሞክራለሁ።ከሁለት ዓመታት በፊት የታተመዉ ጽሑፍ የአየር ንብረት ለዉጥ በአፍሪካ እ.ኤ.አ. በ2030 ሊያደርስ ይችላል ተብሎ የሚገመትዉን ያሳያል (ምሥል 1)።

ምሥል 1.  እዚህ የሚታየዉ በአየር ንብረት ለዉጥ ምከንያት እ.ኤ.አ. በ2030 በአምስት የአፍሪካ አካባቢዎች በበቆሎ፣ ማሽላና ስንዴ ምርት ላይ ሊደርስ የሚችለዉን ተፅዕኖ ነዉ። ጥሬ መረጃዉ ከዚህ ጽሑፍ የተገኘ ሲሆን ለዚህ መጣጥፌ እንዲያመቸኝ ወደ ሥዕል ቀይሬዋለሁ።

ጽሑፉ አፍሪካን እንደ ቅርበታቸውና የአየር  ንብረት ተመሣሣይነታቸዉ በአምስት ከፍለዉ ያሳየ ሲሆን ትኩረት ያደረገዉም በበቆሎ፣ ማሽላና ስንዴ ላይ ነዉ። በምሥሉ እንደሚታየዉ በመጪዉ 11 ዓመታት ውስጥ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት በደቡባዊ የአፍሪካ አካባቢዎች ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ የሚጠበቅ ሲሆን በተለይ በቆሎ በ28.5%፣ ስንዴ ደግሞ በ15.8% እንደሚቀንስ ይጠበቃል። በትንበያዉ መሠረት ሀገራችን በምትገኝበት የምሥራቃዊዉ የአፍሪካ ክፍል በበቆሎ ላይ መጠነኛ የምርት ቅናሽ የሚያሳይ ቢሆንም ከሌሎቹ የአፍሪካ አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ በማሽላና ስንዴ ላይ የምርት መቀነስ ሳይሆን የምርት ዕድገት ይጠበቃል። ይህ በምሥራቃዊዉ የአፍሪካ አካባቢ የሚጠበቀዉ የምርታማነት መጨመር ዋናዉ ምክንያት በትንበያዉ መሠረት በአካባቢዉ የዝናም መጠን መጨመር ነዉ። በሌሎች አካባቢዎች በተለይ በደቡባዊው የአህጉሪቷ አካባቢ የምርት ማሽቆልቆል ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቀውም ከዝናም እጥረት ጋር ግንኙነት አለው።

ሀገራችንን በተመለከተ ከሦስት ወራት በፊት በዓለም አቅፍ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ የልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ታትም የወጣዉን አጠር ያለ ሪፖርት ማጤን ያስፈልጋል። ይህ በዝናም መጠንና በአየር ሙቀት በመመርኮዝ የተደረገዉ ትንበያ የተሠራዉ ሀገሪቱን በሰድስት ዋና አካባቢዎችበመክፈል ነዉ። እነርሱም 1ኛ) ለድርቅ ተጠቂ ከፍተኛ ሥፍራዎች፣ 2ኛ) ለድርቅ ተጠቂ ዝቅትኛ ሥፍራዎች፣ 3ኛ) አስተማማኝ ርጥበት ያላቸዉ ዝቅተኛ ሥፍራዎች፣ 4ኛ) አስተማማኝ ርጥበት ያላቸዉ ከፍተኛ ሥፍራዎች (ብርዕና አገዳ ሰብሎች)፣ 5ኛ) አስተማማኝ ርጥበት ያላቸዉ ከፍተኛ ሥፍራዎች (እንሰት) እና 6ኛ) አርብቶ አደር ሥፍራዎች ናቸው። ከዚህ በታች በምሥል 3 እንደሚታየዉ ትንበያዉ በተደረገባቸዉ እ.ኤ.አ. በ2035፣ 2055 እና 2085 ላይ ሲሆን ጥናቱ መሠረት ያደረገዉም እ.ኤ.አ. በ2013 የነበረዉን የሶስቱን ሰብሎች የምርታማነት መጠን ነዉ። ከምሥሉ መረዳት እንደሚቻለዉ የበቆሎ ምርታማነት እየጨመረ እንደሚሄድና ከዛሬ 66 ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ. በ2013 ከነበረዉ መጠን በ4.2% ብልጫ እንደሚያሳይ ነዉ። በሌላ በኩል የስንዴ ምርታማነት እየቀነሰ እንደሚሄድ ይገመታል። ከሁለቱ ሰብሎች በተለየ ሁኔታ የተተነበየዉ ለማሽላ ነዉ። ምንም እንኳ እስከ 2055 ድረስ በመጠኑም ቢሆን የማሽላ ምርታማነት እየጨመረ ቢሄድም በ2085 ወደ 1% የሚጠጋ የምርት ማሽቆልቆል ያሳያል።

እዚህ ላይ እንቆቅልሽ ሊሆንብን የሚችለዉ በአፍሪካ ደረጃ በተሠራዉ ጥናት (ምሥል 1) እና በዚህ ኢትዮጵያን መሠረት ባደረገው ጥናት (ምሥል 2) ዉጤቶች መካከል ያለዉ የጎላ ልዩነት ሲሆን በተለይ በስንዴ ምርታማነት ላይ የተደረጉት ትንበያዎች እጅግ የተራራርቁ መሆናቸዉ ነዉ።

ምሥል 2.  እዚህ የሚታየዉ በአየር ንብረት ለዉጥ ምከንያት እ.ኤ.አ. በ2035፤ 2055 እና 2085 በኢትዮጵያ በበቆሎ፣ ማሽላና ስንዴ ምርት ላይ ሊደርስ የሚችለዉን ተፅዕኖ ነዉ።  መረጃዉ የተገኘው በቅርቡ ከታተመ ሪፖርት ነዉ።

†

ምሥል 3. ከላይ የሚታየዉ በ2003 በተከሰተዉ ከፍተኛ የዝናም እጥረት ምክንያት በላሊበላ አካባቢ የተዘሩ ሰብሎች ምርት ሳያፈሩ ደርቀው ነበር። ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ

ማጠቃለያ

በአፍሪካ ደረጃ የተሠሩት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ያለችበት በምሥራቃዊዉ የአህጉሪቷ ከፍል የዝናም መጠን እንደሚጨምርና የአንዳንድ ሰብሎች (በተለይ የስንዴ) ምርት እንደሚጨምር ያሳያሉ። በሌላ በኩል በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የተሠራዉ ጥናት ደግሞ የአየር ንብረት ለዉጥ በሰብሎቻችን ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ትፅዕኖ እንዳለዉ ያሳያሉ። ስለዚህ ጠለቅ ያለ ጥናት በማድረግ ከዚህ ቀደም የተተነበዩ ሥራዎችን ማረጋገጥ ይኖርብናል።በመቀጠልም ይደርሳል ተብለዉ የሚጠበቁ መጥፎ ክስተቶችን ለመታደግ ስትራቴጂዎችን በመንድፍ ለተግባራዊነቱ መንቀሳቅስ ይኖርብናል። የአየር ንብረት ለዉጥ በሰብሎቻችን ላይ በሚያደርሱብት ሁኔታ ላይ ከተጠኑ ጥናቶች መካከል አብዛኞቹ የተካሄዱት በተለምዶ የብርዕና አገዳ ሰብሎች ብለን በምንጠራቸው እንደ ስንዴ፣ በቆሎና ማሽላ በመሳሰሉት ላይ ነዉ። በሌሎች በመግቢያዬ ላይ በተጠቀስኳቸዉ የሰብሎች ዓይነቶች ላይ የተጠና ጥናት እጅግ አነስተኛ ነዉ። የአየር ንብረት ለዉጥ ግን ለነዚህ ጥናት ባልተደረገባቸዉ የሰብል ዓይነቶች ላይም ርህራሄ ስለማይኖረዉ ጥናታችንን በሁሉም ሰብሎችንን ማድረግ ይኖርብናል። ከላይ እንዳሳሰብኩት የምንነድፈዉ ስትራቴጂም እነዚህንም ሰብሎች ማጠቃለል ይኖርበታል።

በሚቀጥለዉ ጽሑፌ የአየር ንብረት ለዉጥ በሌሎች ሴክተሮች ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቀውን ለማሳየት እሞክራለሁ።

እስከዚያዉ በቸር ይግጠመን።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 9፤ 2011 ዓ.ም.

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለውጥ — በብዝሀ ሕይወት

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለውጥ — በብዝሀ ሕይወታችን

ባለፈዉ ጽሑፌ የአየር ንብረት ለዉጥ በመከስት ላይ እንዳለና ለዚህም ማረጋገጫ ከሆኑት ምልክቶች መካከል ጥቂቶቹን ለማሳየት ሞክሬአለሁ። እነዚህ ምልክቶችም 1ኛ) የአየርና የባህር ሙቀት መጨመር፣ 2ኛ) የዝናም እጥረት ወይም ድርቅ መባባስ፣ 3ኛ) የጎርፍ መብዛት፣ 4ኛ) የግሪንሃዉስ ጋዝ መጠን መጨመር፣ 5ኛ) የበረዶ ክምችት መመናመን፣ 6ኛ) የባህር ወለል ከፍ ማለት እና 7ኛ) የባህር ዉሃ ወደ አሲዳማነት መቀየር ናቸዉ።

በዛሬዉ ጽሑፌ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ በብዝሀ ሕይወት ሀብታችን ላይ የሚያደርሰዉን አሉታዊ ተፅዕኖ ለማሳየት እሞክራለሁ። በቅርቡ በዓለም አቀፍ ድርጅት የታተመዉን ሪፖርት በሚመለከት በሁለት ክፍል  “አንድ ሚሊዮን ፍጥርቶቻችን ሊጠፉ” በሚል የጻፍኩትን ማስታወስ እፈልጋለሁ። ከዚህ በተጨማሪ የአየር ንብረት ለዉጥ በቡናችን ላይ በማድረስ ላይ ያለዉን በሁለት ክፍል ከትቤ ነበር። በዚህ መሠረት በአየር ሙቀት መጨመርና ዓመታዊ የዝናም መጠን መቀንስ ምክንያት እስከ 60% የሚደርሱ የቡና አብቃይ መሬቶቻችን ለቡና እርሻ ምቹ እንደማይሆኑ ነዉ።

ምንም እንኳ በርካታ ከአየር ንብረት ለዉጥ ጋር የሚገናኙ መንስኤዎች ፍጥረታቶቻችንን ለዚህ የከፋ አደጋ ቢያጋልጡም ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት የአየር ሙቅትና የካቦን ዳዮክሳይድ መጠን መጨመር ናቸዉ። እነዚህና ሌሎች በአየር ንብረት ለዉጥ የሚመጡ መጥፎ ክስተቶችን መቋቋም ያልቻሉ ፍጥረታቶቻችን በሂደት ከምድራችን ይጠፋሉ።

የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት በድህረ ገጹ እንዳሰፈረዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ብቻ ሳይሆን የሰዉ ልጅም ለብዝሀ ሕይወት መመናመንና መጥፋት ከፍተኛ ድርሻ እንዳበረከተ ነዉ። በተለይም የብዝሀ ሕይወት መኖሪያን በማጥፋትና በምትኩ ሌላ አዲስ ፍጡር ወደ አካባቢ በማስገባትና የሰዉ ልጅ የብዝሀ ሕይወት መጥፋትን በ100–1000 እጥፍ አፋጥኖታል። ከላይ የተገለጸዉ ሪፖርት ይፋ ሲደረግ ትኩረት ያደረገዉ በዓለም እና በአህጉር ደረጃ በፍጥረታት ላይ ሊከሰት ይችላል ተብሎ የሚጠበቀውን ነዉ።

ወደ ሀገራችን ስንመጣ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት በብዝሀ ሕይወታችን ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን በሚመለከት የተወሰኑ ጥናቶች ተካሄደዋል። እ.ኤ.አ. በ2009 የተጻፈ ሪፖርት እንደሚያሳየዉ በኢትዮጵያ በየአሥር ዓመት የአየር ሙቀት በ0.4 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይጨምራል። ይህ በመቶና ሺህ ዓመታት ሲሰላ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ዕድገትን ያሳያል።

ቢሆንም በርካታ ሥራዎች የተሠሩትና በመሠራት ላይ ያሉት እንዴት አደጋዉን ተቁቁመን የብዝሀ ሕይወታችንን በምናስጠብቅበት የምፍትሔ አቅጣጫ ላይ ነዉ።

ከተደረጉት ጥረቶች ዉስጥ ዋናዎቹ በአገሪቱ ወካይ በሆኑ ሥፍራዎች ብሔራዊ ፓርኮችንና መካነ ዕፅዋት (ወይም ቦታኒካል ጋርደን) በማቋቋም የተለያዩ አገር በቀል ፍጥረቶቻችን ከነጭራሹ እንዳይጠፉ በተወሰነ ደረጃ ለመታደግ ሙከራ ማድረግ ነበር። በዚህ መሠረት በአገሪቱ ስምንት የሚጠጉ ፓርኮች የተቋቋሙ ሲሆን እነርሱም የሰሜን፣ የባሌ፣ የአዋሽ፣ የአቢያታ-የሻላ፣ የነጭ ሣር፣ የኦሞ፣ የማጎ እና የያንጉዲ ራሳ ብሄራዊ ፓርኮች ናቸዉ። በነዚህ ፓርኮች በርካታ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ፍጥረታት ይኖራሉ።  ተክሎችን በተመለከትም የብዝሀ ሕይወታችንን ለመጠበቅና ለወደፊቱ ትውልድ ለማስቀጠል የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት 64 ሺህ ዓይነት ናሙናዎች በአዲስ አበባ ባለዉ የጂን ባንክ ያለዉ ሲሆን በተጨማሪም በመቱ፣ ሀዋሳ፣ ሀረር፣ መቀሌ፣ ጎባ፣ ባህር ዳር እና አሶሳ የብዝሀ ሕይወት ማዕከላት አሉት። ከዚህ ሌላ በፍቼ ሁለተኛዉ ወይም ዱፕሊኬት ጂን ባንክ አለዉ። ከዚህ ሌላ ሊጠቀስ የሚገባዉ ከስድስት ወራት በፊት ተመርቆ ለህዝብ ክፍት የሆነዉ የጉለሌ መካነ ዕፅዋትና አካባቢዊ መናፈሻ ነዉ። ይህ መናፈሻ በ705 ሄክታር ላይ ያረፈ ሲሆን የሚተዳረዉም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጋራ ነው። በዚህ ማዕከል ዉስጥ እስከ 700 የሚደርሱ አገር በቀል የተክል ዓይነቶች በደህና ሁኔታ ተጠብቀዉ የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ ዉስጥ 65 የሚሆኑት ለመጥፋት በአደገኛ ሁኔታ ያሉ ናቸዉ።

ከላይ በሰዕሉ እንደሚታየዉ ለብዝሀ ሕይወታችን መመናመንና ከነጭራሹ መጥፋት የተለያዩ መንሴኤዎች ቢኖሩም ከላይ የተገለጹት ዋናዎቹ ናቸዉ።

በከፍተኛ ሁኔታ በመመናመን ላይ ስለሚገኙት የብዝሀ ሕይወታችን ሁኔታ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመስጠት የተለያዩ መድረኮች ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሲዘጋጁ ቆይተዋል። በትምህርት ቤቶችም ካሪኩለም ጭምር የብዝሀ ሕይወት ሁኔታ ትኩረት እንዲሰጠዉ ተደርጓል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር አክሊሉ ዳለሎ እ.ኤ.አ. በ2012 ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፋቸዉ እንዳሳዩት የአየር ንብረት ለዉጥና የብዝሀ ሕይወት መመናመን አሳሳቢነት በሚመለከት በሁለተኛ ደረጃ በሚሰጡት የባዮሎጂ ትምህርተ ክፍሎች ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል። ስለዚህ በዚህ የሚያልፉ ተማሪዎች የተወሰነም ቢሆን ግንዛቤ ሊያገኙ ችለዋል።

ማጠቃለያ፤ የአየር ንብረት ለውጥ በመከሰት ላይ እንዳለ በርካታ መረጃዎች ያሉ ሲሆን ወደፊትም የበለጠ ተስፋፍቶ እንደሚቀጥል በሣይንሳዊ መንገድ የተሠሩ ትንበያዎች ያሳያሉ።በተለይ በብዝሀ ሕይወታችን ላይ ከፍተኝ የሆነ አሉታዊ ጎን እንዳለዉ ለማወቅ ተችሏል። የአየር ንብረት ለዉጥ በሌሎች ሴክተሮች ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቀዉን ደግሞ በተከታታይ ጽሑፎች አቀርባለሁ።

እስከዚያዉ በቸር ይግጠመን።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 8፤ 2011 ዓ.ም.