ግብርናችንን ለማዘመን፤ የጤፉ መሐንዲስ

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የጤፉ መሐንዲስ፤ ዶ/ር ታረቀ በርሄ፤ ክፍል 1

ማስገንዘቢያ፤ በተለይ ካልተገለጸ በስተቀር ሁሉም ጊዜ የተጻፈዉ እንደ አዉሮፓ አቆጣጠር ነዉ። እንደሚታወቀዉ ሁሉ ጤፍ አገር-በቀል ብቻ ሳይሆን በሰፊዉ ጥቅም ላይ የዋለ ሰብላችንም ነዉ። የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጄንሲ መረጃ እንደሚያሳየዉ በያመቱ 6.5 ሚሊዮን አባወራዎች ጤፍን ይዘራሉ። በኢትዮጵያ የአንድ ቤተሰብ አማካይ አምስት ሰዉ አድርግን ብንወስድ 32.5 ሚሊዮን ሰዉ በጤፍ ግብርና ይሳተፋል ማለት ነዉ። ከዚያ ደግሞ ወደ ሻጩ ከሄድን ከጅምላ ነጋዴ እስከ ቸርቻሪ ድረስ በርካታ የማህረሰቡ ሰዎች በጤፍ ንግድ ይሳተፉሉ። በተመሣሣይ መልኩ ጤፍን በመፍጨት፣ በመጋገር፣ ወዘተ የሚሳተፉትን ካሰላን ደግሞ ቁጥሩ የበለጠ ይጨምራል። የጤፍ ፍሬ ከገለባዉ ከወጣ በኋላ የሚገኘዉ ጭድ ወይም ተረፍ-ምርትም ለከብት መኖ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለዉ በመሆኑ በከብት ማደለብና ሌሎች ተዛማች መስኮች የሚሳተፉትንም መገመት ይቻላል። ለዚህ ነዉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ጤፍን ሁለቴ የምንመገበዉ። የቀጥታዉ የጤፍ ፍሬ ተፈጭቶ በሚጋገረዉ ወይም በሚሠራዉ እንጄራ፣ ገንፎ፣ ጨጨብሳ፣ ጩኮ፣ ኬክ፣ ወዘተ ሲሆን የተዘዋዋሪዉ ደግሞ የጤፍ ጭድን የተመገቡ ከብቶችን ስንመገብ ነዉ።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጤፍ ከኢትዮጵያ ውጭ ብዙም የማይታወቅ በመሆኑ በሰብሉ ላይ የሚደረገዉ ጥናት በሚፈለገዉ ደረጃ ሊሆን አልቻለም። በዚሁ ምክንያት የጤፍ ምርታማነት ዝቅትኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  ቢሆንም በርካታ ተመራማሪዎች በጤፍ ምርምር ጉልህ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ከነዚህ አንጋፋ ተመራማሪዎች መካከል ዶክተር መላከ ኃይል መንገሻ የመጀመሪያዉ ኢትዮጵያዊ የጤፍ ተመራማሪ ነበሩ ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። ለፒ ኤች ዲ ማጠናቀቂያ በአሜሪካ ከሚገኘዉ የፐርዱ ዩኒቨርስቲ በ1964 Eragrostis tef (Zucc.) Trotter: its embryo sac development, genetic variability, and breeding behavior በሚል ከሠሩት ቴሲስ በተጨማሪ ከዚህ በታች የተገለጹትን ሁለት ጠቃሚ ጽሑፎች አበርክተዉልናል።

  1. Mengesha MH, Pickett RC, Davis RL. 1965. Genetic variability and interrelationship of characters in Teff, Eragrostis tef (Zucc.) Trotter. Crop Science 5(2): 155-157
  2. Mengesha MH. 1966. Chemical composition of teff compared with that of wheat, barley and grain sorghum. Economic Botany 20: 268–273

ከኚህ የጤፍ ተመራማሪ ቀጥሎ በርካታ የሀገራችንም ሆነ የውጭ ሀገራት ተመራማሪዎች የጤፍ ምርምርን ከፍ ለማድረግ የበኩላቸዉን ድርሻ አበርክተዋል።

የዛሬዉ ጽሑፌ የሚያተኩረዉ ለጤፍ ምርምር ፈር ቀዳጅ ዉጤት ላገኙትና ይህም በጥቅም ላይ እንዲዉል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉት ስለ ዶክተር ታረቀ በርሄ ነዉ። እኚህን ከፍተኛ ተመራማሪ እኔ የጤፍ መሐንዲስ እላቸዋለሁ። ምክንያቱም ለምርምር እጅ አልሰጥ ብላ ባስቸገረችዉ ጤፍ ላይ ድል ሊቀዳጁ የቻሉ የመጀመሪያዉ ሰዉ በመሆናቸዉ ነዉ። ከእርሳቸዉ አስደናቂ ግኝት በፊት ጤፍን በማዳቀል ማሻሻል እንደማይቻል ነበር የሚታመነዉ። ምክንያቱም የጤፍ አበባ የሚከፈትበት ጊዜ ሊታወቅ ባለመቻሉ ነዉ። እንደዉም የጤፍ አበባ ፈጽሞ አይከፈትም የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሶ ነበር። ነገር ግን ዶክተር ታረቀ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ የጤፍ አበባ ሊከፈት የሚችል መሆኑንና የማዳቀል ሥራዎችም በሰብሉ ላይ ማድረግ እንደሚቻል ለመጀመሪያ ጊዜ ያረጋገጡ ናቸዉ። የእሳቸዉ የጥናት ዉጤትም እንደሚያሳየዉ የጤፍ አበባ የሚከፈተዉ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ተኩል በጠቅላላዉ ለ30 ደቂቃ ብቻ እንደሆነ ነዉ። ዶክተር ታረቀ ይህንን አስደናቂ ዉጤት ያገኙት የዛሬ 44 ዓመት በ1975 ነዉ።

ከዚህ አንጋፋ የጤፍ ምርምር ባለዉለታ ከሆኑት ከዶክተር ታረቀ በርሄ ጋር ያደረኩት ቃለ-መጠይቅ እነሆ።

መቼና የት ተወለዱ? የተወለድኩት ጃንዋሪ 22፣ 1943 ሲሆን በትግራይ ክልል ሥር በምትገኘዉና ከውቅሮ ከተማ 15 ኪ. ሜ. በምትርቀዉ አብርሃ በምትባለዉ መንደር ነው።.

ዩኒቨርስቲ ከመግባትዎ በፊት የት ተማሩ? የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩት አሥመራ በሚገኘዉ ሰባተኛዉ ቀን አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በጂማ የእርሻና ቴክኒክ ትምህርት ቤት አጠናቅቄአለሁ።

ዶክተር ታረቀ በርሄ (በስተግራ) ኖቮምበር 2011 ከጤፍ ተመራማሪዎች ጋር በደብረ ዘይት ምርምር ማዕከል የተነሱት ፎቶ።ሌሎች በምሥሉ የሚታዩት ከግራ ወደ ቀኝ፤ ዶክተር አንድረስስ ቢንደር፣ ዶክተር ኮሪና ኤስፌልድ፣ አቶ መንግሥቱ ደምሴ፣ ዶክተር ዘሪሁን ታደለ፣ ዶክተር ክበበዉ አሰፋና ዶክተር ገረመዉ ቡልቶሳ ናቸዉ።

የዩኒቨርሲቲ ትምህርትዎንስ የት ተማሩ? የባችለር ድግሬዬን በዕጽዋት ሣይንስ በቀድሞ አጠራሩ ኃይለ ሥላሤ ዩኒቨርስቲ የአለማያ እርሻ ኮሌጅ (በአሁኑ አጠራሩ፤ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ) በ1969 አግኝቻለሁ። በመቀጠልም የማስትሬት ዲግሪዬን በአግሮኖሚ በአሜሪካ ፑልማን ከሚገኘዉ የዋሺንግተን ስቴት ዩኒቨርስቲ በ1974 ተቀብያለሁ። ፒ ኤች ዲ ደግሞ በአሜሪካ ከሚገኘዉ የኔብራስካ ዩኒቨርስቲ በፕላንት ቢሪዲንግና ጄኔቲክስ በ1981 ለማግኘት ችያለሁ።

ለበርካታ ዓመታት ከኢትዮጵያ ዉጭ በተለያዩ የኃላፊነት ሥፍራዎችና ሀገሮች እንደሠሩ ይታወቃል። ከዚህ ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ዉስጥስ ርተዋልን? አዎን፣ ለስምንት ዓመታት አገልግያለሁ። ከ1969 እስከ 1972 የጤፍ ተመራማሪ ሆኜ በደብረ ዘይት እርሻ ምርምር ማዕከል የሠራሁ ሲሆን ከ1974 እስከ 1977 ደግሞ በደብረዘይት ከነበርብኝ የጤፍ ምርምር በተጨማሪ በአለማያ እርሻ ኮሌጅ አስተምር ነበር።

ከኢትዮጵያ ውጭ በነበሩበት ወቅት በምን ላይ እንደተሳተፉና የኖሩበትን ሀገራት ቢገልጹልኝ፤

  • ከ1982 እስከ 1986 ድረስ INTSORMIL ለሚባለዉ ድርጅት የማሽላና ዳጉሣ ተመራማሪ ሆኜ ሱዳን ሀገር ዉስጥ ሠርቻለሁ።
  • ከ1987 እስከ 1989 ድረስ IITA ለሚባለው ዓለም አቀፍ ተቋም የበቆሎ ተመራማሪ ሆኜ በዛየር (በአሁኑ፤ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ) አገልግያለሁ።
  • ከ1989 እስከ 1991 ድረስ Global 2000 ለሚባለዉ ድርጅት ከፍተኛ የበቆሎ አግሮኖሚስት : ሆኜ በዛምቢያ ሀገር ሠርቻለሁ።
  • ከ1991 እስከ 1996 ድረስ SG 2000 ለሚባለዉ ድርጅት ከፍተኛ የሰብል ሣይንቲስት ሆኜ ጋና ሀገር ሠርቻለሁ።
  • ከ1996 እስከ 2004 ድረስ SG 2000 ለሚባለዉ ድርጅት ጊኒያ በምትባለዉ ሀገር ዳይሬክቴር ሆኜ ሠርቻለሁ።
  • ከ2005 እስከ 2010 ድረስ ሳሳካዋ አፍሪካ በሚባለዉ ድርጅት የአህጉሩ የሩዝ ፕሮግራም ዳይሬክቴር ሆኜ የሰራሁ ሲሆን በዚህ ኃላፊነቴም የተሻሻሉ የሩዝ ቴክሎጂዎች ለኢትዮጵያ፣ ማሊ፣ ናይጄሪያ እና ኡጋንዳ እንዲደርሱ ለማድረግ ችያለሁ።
  • ክጃኑዋሪ እስከ ጁን 2011 ድረስ USAID/ARD/TASMOA በመባል ለተቀናጀ ድርጅት ተቀማጭነቴ ላይቤሪያ ሀገር ሆኖ የሩዝ ዘር ዳይሬክቴር በመሆን የተሻሻሉ የሩዝ ቴክሎጂዎች በአምራቹ ዘንድ እንዲሰርጹ ለማድረግ ችያለሁ።

ከዶክተር ታረቀ ጋር ያደረኩት ቃለ መጠየቅ በዚህ አያበቃም። በክፍል 2 እስክንገናኝ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ የካቲት 13፣ 2012 ዓ.ም. (February 21, 2020)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለዉጥ አሳሳቢነት

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለዉጥ አሳሳቢነት

ስለ አየር ንብረት ለዉጥና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ስለሚያደርስብን ተጸዕኖ ከዚህ በፊት በጻፍኳቸዉ ጽሑፎቼ ለማሳየት ሞክሬአለሁ። ቢሆንም የአየር ንብረት ለዉጥ በማድረስ ላይ ስላለዉ ጉዳትና ወደፊትም ያደርሳል ተብሎ ስለሚጠበቀዉ አሉታዊ ጎኖች በርካታ መረጃዎች በመቅረብ ላይ ስላሉ እነዚህን ለአንባቢያን ማድረሱ ተገቢ ይመስለኛል። ምክንያቱም በአየር ንብረት ምክንያት ሊደርሱ የሚችሉ ክስተቶችን ከወዲሁ በመረዳት በከፊልም ቢሆን መፍትሔ ሊሆን የሚችል እርምጃ ለመዉሰድ ስለሚቻል ነዉ። የአየር ንብረት ለዉጥ የሚያደርሰዉ ክስተት መጠነ ሰፊ ብቻ ሳይሆን በበርካታ መንገድ ተጽእኖ ያሳድራል። ለምሳሌ ከአምስት ዓመታት በፊት የወጣ ሪፖርት እንደሚያሳየዉ የአየር ንብረት ለዉጥ የአፍሪካ አህጉርን በስምንት መንገዶች በመጉዳት ላይ ይገኛል። እነዚህም፤

1ኛ) በአየር ሁኔታ (weather) ለዉጥ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች በከፍተኛ ዝናም ምክንያት የጎርፍ ሁኔታ የሚከሰት ሲሆን በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ እጅግ መጠኑ ባነሰ የዝናም መጠን ምክንያት ድርቅ ይከሰታል።

2ኛ) በዉሃ መጠንና ጥራት፤ ከላይ በተራ ቁጥር አንደተጠቀሰዉ በተለዋዋጭ የዝናም መጠን እና የአየር ሙቀት ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የዉሃ ክምችቶች ሊመናመኑ ችለዋል። ባብዘኛዉ እንደምሳሌ የሚወሰደዉ በአፍሪካ ትልቁ በሆነዉ የኪሎማንጃሮ ተራራ ላይ የሚገኘዉ የበረዶ ክምችት እጅግ እየተመናመነ መምጣቱ ነዉ። ይህንን በ90 ዓመታት ብቻ የተከሰተዉን ከፍተኛ የሆነ ክስተት በምሥል 1 ማየት ይቻላል።

3ኛ) በምግብ እጥረትና ጥራት፣ 4ኛ) በጤናችን፣ 5ኛ) በመጠለያችን፣ 6ኛ) ለጥቃት በተዳረጉ ዜጎች፣ 7ኛ) በደህንነት እና 8ኛ) በሥርዓተ ምህዳር (ecosystem) ናቸዉ።

የዓለም የሜትሮሎጂ ድርጅትን ሪፖርት ጠቅሶ ቢቢሲ በቅርቡ (እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 3፣ 2019) በዘገበዉ መሠረት ያሳለፍነዉ አሥርት ዓመታት ማለትም ከ2010 እስከ 2019 የነበሩት ከፍተኛ የአየር ሙቀት የተመዘገበባቸዉ ናቸዉ። ከዚህ በተጨማሪ አደገኛዉ የግሪን ሃውስ ጋዝ እንዲጨምር ከሚያደርጉት ውስጥ የካርቦን ዳዮክሳይድና ናይትረስ ኦክሳይድ መጠንም በከፍተኛ መጠን ጨምረዉ የተገኙበት ነዉ።

ከላይ የተጠቀሱትን በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት የሚደርሱ ክስተቶች ለመግታት ጥረቶች በመካሄድ ላይ ናቸዉ። ከነዚህ ዉስጥ በአፍሪካ ደረጃ ካሉት 350Africa.org የሚባለዉን መጥቀስ ይቻላል። ድርጅቱ ውይም እንቅስቃሴዉ 350 የሚለዉን ሥያሜ የወሰድዉ በዓለማችን ለጤናማ ኑሮ ያመቻል ተብሎ የታሰበዉ የካርቦንዳኦክሳይድ መጠን 350 ከሚሊዮን እጅ በመሆኑ ነዉ። ይህ እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት በጋና፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ፣ ኬንያ፣ ኮትዲቮር እና የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ምሥል 1፤ እ.ኤ.አ. በ1912 በኪሎማንጃሮ ተራራ ላይ የነበረዉ የበረዶ ክሞችት እና ከ90 ዓመታት በኋላ በ2002 በተመሣሣይ ሥፍራ የነበረዉ የበረዶ መጠን። የመረጃዉ ምንጭ

በተለያየ ሁኔታ የሚያጋጥሙን ሥጋቶች (risks) በስሌት ከማቅረቡም በተጨማሪ የመፍትሔ ሀሳቦችንም የሚያቀርብ መቀመጫዉን በተለያዩ የዓለማችን ከተሞች ያደረገ ማፕል ክሮፍት የተባለ ድርጅት አለ። በተለያዩ ሁኔታዎች የሚያጋጥሙንን ሥጋቶች በሦስት ዋና እና በ12 ንዑሳን ክፍሎች ለይቶ የሚያሳይ ሲሆን ለዚህ ጽሑፌ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት ሊከሰት በሚችለዉ ላይ አተኩራለሁ።

በዚሁ መሠረት በድርጅቱ ድህረ ገጽ ጎልቶ እንደሚታየዉ 84% የሚሆኑ በዓለማችን በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኙ ከተሞች በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት ለሚከሰት አደጋ የተጋለጡ ናቸዉ። በምሥል 2 እንደሚታየዉ በከፍተኛ ደረጃ ለዚህ የተጋለጡት በአፍሪካ ያሉ ከተሞች ናቸዉ። በሪፖርት መሠረት እ. ኤ.አ. ከ2018 እስከ 2035 ባሉት ዓመታት ዓመታዊ የህዝባቸዉ ዕድገት ከ3% በላይ የሆኑት ተጋላጭ ናቸዉ። በምሳሌነት ከተገለጹት ከተሞች መካከል ዓመታዊ የህዝባቸዉ እድገት ይህንን ይመስላል። ካምፓላ ኡጋንዳ 5.1%፣ ዳሬ ሰላም ታንዛኒያ 4.8%፣ አቡጃ ናይጄሪያ 4.5%፣ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ 4.3%፣ ሉዋንዳ አንጎላ 3.7% እና ሌጎስ ናይጄሪያ 3.5% ናቸዉ።

ምሥል 2፤ በተለያዩ አህጉራት ያሉ ከተሞች ለአየር ንብረት ለውጥ ያላቸዉ ተጋላጭነት (Vulnerability) ነዉ።  ምንጭ

እንደ መፍትሔ የተጠቀሱትን በሌላ ጽሁፌ አቀርባለሁ። እስከዚያዉ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥር 4፣ 2012 ዓ.ም. (January 13, 2020)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአንበጣ መንጋ ወረርን!!! ክፍል 2

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአንበጣ መንጋ ወረርን!!!

ክፍል 2

በክፍል 1 በአንበጣና ፌንጣ መካከል ያለዉን ልዩነት ለማሳየት ሞክሬአለሁ። እንዲሁም ሰላማዊ የነበረዉ አንበጣ አካላዊና የባህርይ ለውጥ በማድረግ አረንጓዴ የሆነ ማንኛዉንም ተክል ለማዉደም በመንጋ በመጓዝ ጥቃት እንደሚያደርስ ለማሳየት ሞክሬአለሁ። አንበጦቹ በሰላም ከሚኖሩበት ወደ ጥቃት እንዲሄዱ የሚገፋፋቸዉ በአንጎላቸዉ ዉስጥ የሚገኝ ሴሮቶንኒን የተባለ ሆርሞን እንደሆነም መግለጼ ይታወቃል። ይህ ሆርሞን በሰዉ ልጅ አንጎልም ዉስጥ የሚገኝ ሲሆን ከቁጡነት፣ ድፕሬሽን እና ከመሣሠሉት ባህርያዎቻችን ላይ ተጽእኖ እንዲያሳድሩ ይታመናል።

በዛሬዉ ጽሑፌ በአሁኑ ጊዜ በመከሰት ላይ ያለዉ የአንበጣ መንጋ ጥቃት ምን እንደሚመስል ለማሳየት እሞክራለሁ።የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅትን ጠቅሶ ቢቢሲ ከሶስት ቀናት በፊት ባሳተመዉ ጽሑፍ እንደሚያሳየዉ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እየተቃጣ ያለዉ የአንበጣ ጥቃት በአጭር ጊዜ በቁጥጥር ሥር መዋል ካልቻለ የጎረቤት ሀገራት ወደሆኑት ወደ ኬኒያ፣ ኤርትራ እና ሱዳን ሊዛመት እንደሚችል ነው።

ላይ የሚታዩት ስድስት ካርታዎች የሚያሳዩት ከሚያዚያ 2011 እስከ ጥቅምት 2012 (ኢ. ኤ.. አ. ከአፕሪር እስከ ኦክቶበር 2019) የነበረዉን የአንበጣ መንጋ ሥርጭትን ነዉ። (ሀ) አፕሪል 2019 (ለ) ሜይ 2019 (ሐ) ጁላይ 2019 (መ) ኦጉስት 2019 (ሠ) ኦክቶበር 2019 (ረ)ቭኦክቶበር 2019። ምንጭ

ከላይ በካርታዎቹ ዉስጥ የሚታዩት ምልክቶች የሚከተሉትን ይወክላሉ።

  • አረንጓዴ (ሰላም)፤ ምንም የአንበጣ ጥቃት አልደረሰም። ቢሆንም ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል።
  • ቢጫ (ጥንቃቄ)፤ ጥቃት ሊደርስ ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የመቆጣጠር እርምጃም መወሰድ ያስፈልጋል።
  • ብርቱካናማ (ጥቃት)፤ የሰብሎች ጥቃት ይደርሳል። የክትትልና መከላከል እርምጃ መዉሰድ ያስፈልጋል።
  • ቀይ (አደገኛ)፤ ከፍተኛ የሰብል ጥቃት ይደርሳል። ከፍተኛ የክትትልና መከላከል ዕርምጃ መዉሰድ ያስፈልጋል።

በዚሁ መሠረት በአፕሪል 2019 አረንጓዴ የነበረዉ የኢትዮጵያ አካባቢ ከስድስት ወራት በኋላ በኦክቶበር 2019 ወደ ቀይ ወይም አደገኛነት ተቀይሯል ማለት ነዉ።

በዚሁ ሪፖርት መሠረት ከዘጠኙ የኢትዮጵያ ክልሎች ዉስጥ በአራቱ ማለትም በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ የአንበጣ ጥቃት በመድረስ ላይ ይገኛል። በተለይም በሰሜናዊ የአማራ ክልል የጤፍ እርሻ ሙሉ በሙሉ የወደመበት ሥፍራ እንዳለ ተዘግቧል። የምግብና እርሻ ድርጅት ሪፖርትም በተለያየ ወቅት የነበረዉን የአንበጣ ሥርጭትንና ጥቃትን ያሳያል

በሚቀጥለዉ በሌላ ብሎግ እስክንገናኝ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ኅዳር 3፣ 2012 ዓ.ም. (November 13, 2019)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአንበጣ መንጋ ወረርን!!! ክፍል 1

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአንበጣ መንጋ ወረርን!!!

ክፍል 1

አንበጣና ፌንጣ በዝምድናቸዉ ይቀራረባሉ። በተለይም አንበጣ አጭር ቀንድ ወይም አንቴና ካለዉ ፌንጣ ጋር እጅግ ይቀራረባል። ፌንጣ የሚባሉት ባብዘኛዉ በጓሮአችን በተናጠል የሚታዩት ሲሆኑ አንበጣ ብለን የምንጠራቸዉ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ በመራባት በሰብሎቻችን ላይ እጅግ ከፍተኛ ዉድመት የሚያደርሱት ናቸዉ። እነዚህ በማንኛዉም አረንጓዴ ተክል ላይ በመዝመት ያለ አንዳች ርህራሄ የሚያወድሙት ፍጡሮች የበረሃ አንበጣ ወይም በሣይንሳዊ አጠራር Locusta migratoria ወይም ተጓዡ አንበጣ ወይም Schistocerca gregaria ይባላሉ። በአሁኑ ወቅት ይህ የአንበጣ መንጋ ሀገራችንን ጨምሮ በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ላይ ከፍተኛ ዉድመት እያደረሰ ነዉ። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ሁሉም አንበጣዎች በሰብሎቻችንን ጥቃት አለማድረሳቸዉ ነዉ። አንበጣዎች በሰብሎቻችን ላይ ጥቃት የሚያደርሱት በከፍተኛ ሁኔታ ሲራቡና አካላዊና የባህርይ ለውጥ ካደረጉ ብቻ ነዉ።

የዛሬ ጽፌን በጥያቄና መልስ መልክ አቀርለሁ።

  • በአንበጣና ፌንጣ መካከል ያለዉ የባህርይና አካላዊ ለዉጥ ምን ይመስላል? በሁለቱ ፍጥረታት መካከል ያለዉ ልዩነት ከዚህ በታች ባለዉ ሠንጠረዥ ባጭሩ ቀርቧል።
  ፌንጣ አንበጣ
የኑሮ ሁኔታ በተናጠል በመንጋ (በተናጠል የሚኖርም አለ)
የሰውነቱ መጠን ተለቅ ያለ አነስተኛ
ክንፍ አጭር ረዥምና ጠንካራ
የዉጭዉ መልክ ቡኒ ውይም አረንጓዴ ከብሩህ ቀይ ወደ ቢጫነት ይቀየራል
የመብረር ሁኔታ መዝለል ብቻ ረዥም ርቀት የመብረር ችሎታ
የሚመገበዉ ሣር ሰብልና ማንኛዉንም አረንጓዴ ተክል
  • ሰላማዊ የሆነ አንበጣ እንዴት ወደ አውዳሚ መንጋነት ይቀየራል? አንበጣ ባብዘኛዉ በተናጠል የሚኖር ሲሆን በተወሰነ ምክንያት በተናጠል የመኖር ሁኔታን ትቶ ወደ መንጋነትና አውዳሚነት ይቀየራል። የድርቅ ወቅትን ተከትሎ አረንጓዴ ተክሎች (ሰብሎቻችንን ጨምሮ) ባፋጣኝ ሲያድጉ አንበጣዎቹ በፍጥነትና በብዛት እንዲራቡ አመቺ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል። እነዚህ በከፍተኛ መጠን የተባዙ አንበጣዎች የአካላዊም ሆነ የባህርይ ለዉጥ ያካሂዳሉ።
  • ወደ አዉዳሚነት የሚቀየሩት አንበጣዎች ምን ዓይነት አካላዊ ለዉጥ ያካሂዳሉ? ክንፎቹ በተለይ ከኋላ ያሉት ወደ ረዥምና ጠንካራነት ይለወጣሉ። ይህም አንበጣዎቹ ረጅም ርቀት ለመብረር ያስችላቸዋል።
  • እነዚህ ወደ አዉዳሚነት የሚቀየሩት አንበጣዎች ምን ዓይነት የመልክ ለዉጥ ያካሂዳሉ? ከብሩህ ቀይ ወደ ቢጫማነት ይቀየራሉ።
በተናጠል የሚኖሩና የጎላ ጉዳት የማያደርሱብን አንበጣዎች እና በመንጋ በመኖር በሰብሎቻችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱብን አንበጣዎች የተወሰነ አካላዊ ልዩነት አላቸዉ። ምስሉ የተወሰደዉ ከዚህ ድህረገጽ ነዉ።

በከፍተኛ መጠን የተባዙ አንበጣዎች ምን ዓይነት የባህርይ ለዉጥ ያካሂዳሉ? ከጨዋነት ወደ አዉዳሚነት እንዲሁም በተናጠል ከመኖር ወደ መንጋነትና ወራሪት ይቀየራሉ።

እነዚህ በከፍተኛ መጠን የተባዙ አንበጣዎች ምን ዓይነት የሆርሞን ለዉጥ ያካሂዳሉ? በአንበጣዎቹ አንጎል ዉስጥ የሚገኘዉ ሴሮቶኒን (serotonin) የተባለዉ ሆርሞን ከላይ ለተጠቀሱት የባህርይ ለዉጥ መንስኤ እንደሆኑ ከአሥር ዓመት በፊት የተሠራ ጥናት አረጋግጧል። ይህ የአንበጣዎቹን ባህርይ የሚቀይረዉ ሆርሞን በሰዉ ልጅ አንጎል ዉስጥም የሚገኝ ሲሆን ዋና ሚናዉ ዲፕሬሽን፣ ቁጡነት፣ እና የመሳሰሉት ላይ ተጽእኖ አለዉ።

አንድ አንበጣ ምን ያህል ይመገባል? አንድ አንበጣ በቀን የራሱን ክብደት ያህል መመገብ የሚችል ሲሆን ይህም እስከ ሶስት ግራም ሊሆን ይችላል።

የአንድ አንበጣ መንጋ ምን ያህል ሊሆን ይችላል? የአንድ አንበጣ መንጋ መጠን እንደሁኔታዉ ሊለያይ ቢችልም እስከ 50 ሚሊዮን ነፍሳት ሊኖሩት ይችላል።

በአንድ መንጋ ያለ አንበጣ ምን ያህል ሰብል ሊያወድም ይችላል? አንድ መጠነኛ የሆነ የአንበጣ መንጋ በቀን እስከ 80 ሺህ ቶን (ወይም 80 ሚሊዮን ኪ.ግ.) ሰብል ወይም አረንጓዴ ተክል ሊመገብ ወይም በሌላ አነጋገር ሊያወድም ይችላል። ይህ መጠንም እስከ 100 ሺህ ሰዉ ለአንድ ዓመት ሊመግብ እንደሚችል ይገመታል።

የአንድ አንበጣ መንጋ ምን ያህል ሊጓዝ ይችላል? እነዚህ አውዳሚ አንበጦች በንፋስ ታግዘዉ የሚበሩ ሲሆን በሰዓት ከ15 እስከ 20 ኪ. ሜ. ሊበሩ ይችላሉ። በቀን እስከ 130 ኪ.ሜ. እንደሚበሩ መረጃዎች ያሳያሉ።

ከዚህ በፊት በዓለማችን የተከሰቱ የአንበጣ ጉዳቶች ምን ይመስላሉ? የአንበጣ መንጋ ከፍተኛ ጉዳት ያደርስ እንደነበረ በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት ብቻ ወደ ስድስት የሚጠጉ ለበርካታ ዓመታት የቆዩ በአንበጣ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳቶች በዓለማችን ተከስተዋል። እነዚህ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆዩ መጠነ ሰፊ ጉዳቶች በእንግሊዘኛዉ አጠራር plaque ተብለዉ ይጠራሉ። እ.ኤ.አ. ከ1985 እስከ 1989 ድረስ የነበረዉ ይህ ክስተት 43 በአፍሪካና ኤሲያ የሚገኙ አገሮችን ያጠቃ ሲሆን በአፍሪካ ብቻ 5.5. ሚሊዮን ሄክታር የሚሆን እርሻ ላይ ጉዳት አድርሷል። በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ሌሎች የጎረቤት ሀገራት ላይም ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ ነበር።

እ. ኤ.አ. በ1968 በኢትዮጵያና አካባቢ የተከሰተዉ መጠነ ሠፊ የአንበጣ ጥቃት ወይም plaque ይህን ይመስል ነበር። የምስሉ ምንጭ

በአሁኑ ወቅት በሀገራችንና አካባቢ ስለተከሠተዉ የአንበጣ ጥቃት በክፍል 2 እጽፋለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ኅዳር 3፣ 2012 ዓ.ም. (November 13, 2019)

International Tef Workshop

The Third International Tef Workshop was held from October 22 to 24, 2019 at Adulala Resort in Bishoftu, Ethiopia. The first two International Tef workshops were: the First held in Addis Ababa from October 16 to 19, 2000 and the Second held in Bishoftu from November 7 to 9, 2011. In this the Third International Tef Workshop, a total of 170 researchers, development workers, farmers and invited guests were participated.

As shown above, the motto of the Third International Tef Workshop was ‘Tef Improvement: from where to where?’

Participants of the Third International Tef Workshop were drawn from different institutions in Ethiopia as well as from abroad. Those participated from abroad include researchers who are actively involved in tef and those planning to do research on this valuable crop. In addition, donors of tef improvement participated. Outside Ethiopia, countries represented at the workshop were USA, UK, Japan, Switzerland, Kenya and others. In this three-day workshop, all topics related to tef improvement were presented and thoroughly discussed.

The Third International Tef Workshop was officially opened by H.E. Mr. Umer Hussein, Minster, Ministry of Agriculture (left) and the welcome address by Dr. Mandefro Negussie, Director General of Ethiopian Institute of Agricultural Research (right).

The workshop was officially opened by H.E. Mr. Umer Hussein, Minster, Ministry of Agriculture. The welcome address was made by Dr. Mandefro Negussie, Director General of the Ethiopian Institute of Agricultural Research. Earlier, Dr. Kebebew Assefa from Debere Zeit Agricultural Research Center introduced objectives and program of the workshop. Dr. Kebebew is a senior tef researcher who has been actively working on this crop for the last 36 years. In the opening session, representatives of Agricultural Transformation Agency of Ethiopia and Syngenta Foundation for Sustainable Agriculture also gave speech.

The key-note address was made by Prof. Endashaw Bekele from Addis Ababa University on ‘Tef: past, present and future’. Prof. Endashaw has extensively published in different topics of tef research. In his speech, Prof. Endashaw, indicated that tef is the gift Ethiopia gave to the world. He also stressed the need to further improve the research on tef.

In general, 24 papers were presented under six major categories. These are i) agro-ecology and seed systems, ii) genetic resources and breeding, iii) genomics and biotechnology, iv) soils and crop management, v) crop protection, vi) utilization, socio economics and extension. Apart from these scientific presentations, three farmers with significant contributions to tef technology dissemination gave short speeches. These are Ms Bekelech Tola, Mr. Sisay from Boset Woreda and Mr. Amha Abraham from Amuri Seed Producers.

Objectives and program of the workshop were introduced by Dr. Kebebew Assefa (left) while Mr George Osure gave speech representing Syngenta Foundation for Sustainable Agriculture (right).

Partial view of workshop participants

The 24 papers presented at the workshop and presenters were:

I) Agro-ecology and seed systems

1. Ecology and farming systems by Tamene Mekonnen

2. Tef seed system and input supply by Dr. Abebe Atilaw

II) Genetic resources and breeding

3. Taxonomy, origin and genetic resources by Dr. Habte Jifar

4. Genetics by Dr. Solomon Chanyalew

5. Breeding by Dr. Kebebew Assefa

III) Genomics and biotechnology

6.Molecular breeding by Dr. Dejene Girma

7. Biotechnology by Dr. Endale Gebre

8. Genomics by Dr. Dejene Girma

9. Progress and prospects of genome editing in tef improvement by Mitiku Asfaw

Partial view of workshop participants

IV) Soils and crop management

10. Morphology and anatomy by Tara Wight

11. Physiology by Dr. Zerihun Tadele

12. Agronomy by Dr. Almaz Meseret

13. Soil fertility management by Dr. Yifru Abera

14. Water management by Ashebir Haile

15. Mechanization by Dereje Alemu

16. Response of tef grain physico-chemical properties to soil and meteorological factors by Anteneh Abewa

V) Crop protection

17. Weed management by Rezene Fissehaie

18. Disease management by Ashenafi Gemechu

19. Insect pest management by Dr. Tebkew Damte

VI) Utilization, socio economics and extension

20. Food value by Dr. Workneh Abebe

21. Feed value by Tekleyohannes Berhanu

22. Economics of Tef by Dr. Setotaw Ferede

23. Tef technology transfer by Dr. Elias Zerfu

24. Tef value chain by Dr. Bart Minten

See you next time with another topic.

Zerihun Tadele, University of Bern, Switzerland፣ ጥቅምት 24፣ 2012 ዓ.ም. (November 4, 2019)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ ዓለም አቀፍ የጤፍ አዉደ ጥናት

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ዓለም አቀፍ የጤፍ አዉደ ጥናት

ቦሾፍቱ የተካሄደዉ ሦስተኛዉ ዓለም አቀፍ የጤፍ አዉደ ጥናት መሪ ቃል “የጤፍ ምርምርና ልማት፣ ከዬት ወደ የት?” የሚል ነበር።

ሦስተኛዉ ዓለም አቀፍ የጤፍ አዉደ ጥናት ከጥቅምት11 እስከ 13 ቀን 2012 ዓ.ም. (እ. ኤ. አ. ኦክቶበር 22 እስከ 24፣ 2019) ቢሾፍቱ በሚገኘዉ አዱላላ ሪዞርት ተካሂዷል። ለማስታወስ ያህል የመጀመሪያዉ ዓለም አቀፍ የጤፍ አዉደ ጥናት የተካሄደዉ እ. ኤ. አ. ከኦክቶበር 16 እስከ 19, 2000 በአዲስ አበባ ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ የዛሬ ስምንት ዓመት እ. ኤ. አ. ኖቮምበር 7 እስከ 9, 2011 በቢሾፍቱ ነበር። በአሁኑ ሦስተኛዉ ዓለም አቀፍ የጤፍ አዉደ ጥናት ላይ በአጠቃላይ ወደ 170 የሚጠጉ ተመራማሪዎች፣ የልማት ሠራተኞች፣ ገበሬዎች፣ እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

ከኢትዮጵያ ውጭ በጤፍ ላይ በአሁኑ ጊዜ ምርምር በማድረግ ላይ ያሉና በቅርቡ ወደ ጤፍ ምርምር ለመግባት በዕቅድ ላይ ያሉ ተመራማሪዎችና ምርምርሩን በመዋዕለ ንዋይ በመርዳት ላይ የሚገኙ አካላትም ተገኝተዋል። ከእነዚህ ከዉጭ ሀገር ከመጡ ተሳታፊዎች መካከል ከአሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጃፓን፣ ስዊዘርላንድ፣ እስራኤል እና ኬንያ የመጡ እንግዶች ይገኙበታል። በዚሁ ለሦስት ቀናት በቆየዉ አዉደ ጥናት ላይ ጤፍን በሚመለከት በተለያዩ መስኮች የተደረጉ የምርምር ዉጤቶች ቀርበዉ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

አዉደ ጥናቱን በንግግር የከፈቱት የግብርና ሚኒስትሩ የተከበሩ አቶ ኡመር ሁሴን ሲሆኑ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት ደግሞ የእርሻ ምርምር ኢንቲትዩቱት ዳይሬክቴር ጄኔራል ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሤ ናቸዉ። የአዉደ ጥናቱን ዓላማና ፕሮግራም ያስተዋወቁት ደግሞ ዶክተር ክበበዉ አሰፋ ናቸዉ። ዶክተር ክበበዉ ላለፉት 36 ዓመታት በጤፍ ላይ ምርምር በማድረግ ላይ የሚገኙ አንጋፋ ተመራማሪ ናቸዉ። በዚሁ የመክፈቻ ፕሮግራም ላይ የኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ እና የሲንጄንታ ፍዉንዴሽን ተወካዮች በየተራ አጠር ያለ ንግግር አድርገዋል።

ሦስተኛዉን ዓለም አቀፍ የጤፍ አዉደ ጥናት የከፈቱት የግብርና ሚኒስትሩ የተከበሩ አቶ ኡመር ሁሴን (በስተግራ) እና የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የእርሻ ምርምር ኢንቲትዩቱት ዳይሬክቴር ጄኔራል ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሤ (በስተቀኝ)።

በአዉደ ጥናት ላይ ጠቋሚ ንግግር (key note address) እንዲያደርጉ የተጋበዙት ደግሞ በጤፍ ላይ በርካታ የምርምር ዉጤቶችን ያበረከቱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲዉ ፕሮፌሰር እንዳሻዉ በቀለ ናቸዉ። ፕሮፌሰር እንዳሻዉ “Tef: past, present and future” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፋቸዉ በርካታ ነጥቦችን ዘርዝረዋል። ከነዚም ዉስጥ ኢትዮጵያ ጤፍን ለዓለም በስጦታ ያቀረበች ሰብል ነዉ ብለዋል። የጤፍ ምርምርንም አሁን ከሚገኝበት ደረጃ በተሻለ ሁኔታ ማሳደግ አለብን ብለዋል።

በአዉደ ጥናቱ የቀረቡት የምርምር ጽሑፎች በስድስት ክፍሎች ተከፍለዉ የቀረቡ ሲሆን በጤፍ ላይ የተሠሩ ሥራዎች በሙሉ የተዳሰሱ ነበር ማለት ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ በጤፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ከሚገኙ ገበሬች መካከል ወ/ሮ በቀለች ቶላ፣ አቶ ሲሳይ (ከቦሰት ወረዳ)፣ እና አቶ አምሀ አብርሃም (ከአሙሪ የዘር ድርጅት) በየተራ ንግግር አድርገዋል።

ስድስቱ ክፍሎች ሀ) አግሮኢኮሎጂና የዘር ሲስተም፣ ለ) ጄኔቲክስና ብሪዲንግ፣ ሐ) ጄኖሚክስና ባዮቴክኖሎጂ፣ መ) አፈርና ሰብል እንክብካቤ፣ ሠ) ሰብል ጥበቃ እና ረ) ሶሺዮ ኢኮኖሚክስ እና ኢክስቴንሽን ሲሆኑ በአጠቃላይ 24 ጽሑፎች ቀርበዋል።

የአዉደ ጥናቱን ዓላማና ፕሮግራም ያስተዋወቁት  ዶክተር ክበበዉ አሰፋ (በስተግራ) እና ሲንጄንታ ፍዉንዴሽንን በመወከል ንግግር ያደረጉት ሚስተር ጆርጅ አሱሬ (በስተቀኝ)።

የአዉደ ጥናቱ ተሣታፊዎች በከፊል

በአዉደ ጥናቱ የቀረቡት 24 የምርምር ጽሑፎች የሚከተሉት ናቸዉ።

ሀ) አግሮኢኮሎጂና የዘር ሲስተም

1. Ecology and farming systems በታመነ መኮንን

2. Tef seed system and input supply በዶክተር አበበ አጥላዉ

ለ) ጄኔቲክስና ብሪዲንግ

3. Taxonomy, origin and genetic resources በዶክተር ሀብቴ ጅፋር

4. Genetics በዶክተር ሰለሞን ጫንያለዉ

5. Breeding በዶክተር ክበበዉ አሰፋ

ሐ) ጄኖሚክስና ባዮቴክኖሎጂ

6.Molecular breeding በዶክተር ደጀኔ ግርማ

7. Biotechnology በዶክተር እንዳለ ገብሬ

8. Genomics በዶክተር ደጀኔ ግርማ

9. Progress and prospects of genome editing in tef improvement በምትኩ አስፋዉ

የአዉደ ጥናቱ ተሣታፊዎች በከፊል

መ) አፈርና ሰብል እንክብካቤ

10. Morphology and anatomy በታራ ዋይግት

11. Physiology በዶክተር ዘሪሁን ታደለ

12. Agronomy በዶክተር አልማዝ መሠረት

13. Soil fertility management በዶክተር ይፍሩ አበራ

14. Water management በአሸብር ኃይሌ

15. Mechanization በደረጀ አለሙ

16. Response of tef grain physico-chemical properties to soil and meteorological factors በአንተነህ አበዋ

ሠ) ሰብል ጥበቃ

17. Weed management በአቶ ረዘነ ፍስሃዬ

18. Disease management በአሸናፊ ገመቹ

19. Insect pest management በዶክተር ጠብቀዉ ዳምጤ

ረ) ሶሺዮ ኢኮኖሚክስ እና ኢክስቴንሽን

20. Food value በዶክተር ወርቅነህ አበበ

21. Feed value በተክለዮሃንስ ብርሃኑ

22. Economics of Tef በዶክተር ስጦታዉ ፈረደ

23. Tef technology transfer በዶክተር ኤልያስ ዘርፉ

24. Tef value chain በዶክተር ባርት ሚንተን

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥቅምት 23፣ 2012 ዓ.ም. (November 3, 2019)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ ሲምፖዚየም ለግብርና ምሁራን

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ምፖዚየም ለግብርና ምሁራን

Advances in Agricultural Sciences ተብሎ የተሰየመዉ ሁለተኛዉ ሲምፖዚየም አዲስ አበባ በሚገኘዉ የግብርና ምርምር የስብሰባ አዳራሽ ጥቅምት 14፣ 2012 ዓ.ም. (እ. ኤ. አ. ኦክቶበር 25, 2019) ተካሂዶ ነበር። የዚህ ዓይነቱ የመጀመሪያዉ ሲምፖዚየም የተካሄደዉ ከአምስት ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 24 በ2014 ሲሆን የተካሄደበትም ሥፍራ ይኸዉ የግብርና ምርምር የስብሰባ አዳራሽ ነበር።  ለማስታወስ ያህል መጀመሪያ በነበረዉ ሲምፖዚየም ጽሑፎቻቸዉን ያቀረቡትና የጽሁፎቻቸዉ ርዕሶች የሚከተሉት ነበሩ።

  1. ፕሮፌሰር ገቢሳ እጀታ (ፐርዱ ዩኒቨርስቲ፣ አሜሪካ) Research for development (R4D): Mantra or Practice?
  2. ፕሮፌሰር ተስፋዬ መንግሥቴ (ፐርዱ ዩኒቨርስቲ፣ አሜሪካ) Application of translational research for crop improvement
  3. ዶክተር ይልማ ከበደ (ቢል እንደ ሜሊንዳ ጌትስ ፋዉንዴሽን፣ አሜሪካ) Lessons learned from a career in research and development: a personal experience
  4. ዶክተር መላኩ ገድል (አይ አይ ቲ ኤ፣ ናይጄሪያ) Contributions of International agricultural research centers to research and development of national agricultural research systems
  5. ዶክተር ዘሪሁን ታደለ (በርን ዩኒቨርስቲ፣ ስዊዘርላንድ) Transcending the status quo ante of tef research

ጽሑፎቹ ከቀረቡ በኋላ በአምስቱ የጽሑፍ አቅራቢዎች የፓናል ውይይት የተደረገ ሲሆን የፓናል ውይይቱን የመሩት አንጋፋዉ ምሁር ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን ነበሩ። ይህን የመጀመሪያዉን ሲምፖዚየም በንግግር የከፈቱት በወቅቱ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክቴር ጄኔራል የነበሩት ዶክተር ፈንታሁን መንግሥቱ ሲሆኑ ሲምፖዚየሙን የዘጉት ደግሞ በወቅቱ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ዶክተር አዱኛ ዋቅጅራ ናቸዉ።

በአሁኑ ሁለተኛዉ ሲምፖዚየም ወደ 200 የሚጠጉ ከተለያዩ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተዉጣጡ ምሁራን ተሳትፈዋል። በሲምፖዚየሙ መግቢያ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት ስምፖዚየሙን ያዘጋጁትና የዚህም ብሎግ ጸሐፊ የሆኑት በስዊዘርላንድ ሀገር የሚገኘዉ የበርን ዩኒቨርስቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ዘሪሁን ታደለ ናቸዉ። ስምፖዚየሙን በንግግር እንዲከፍቱ የተጋበዙት ደግሞ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን ናቸዉ። ዶክተር ብርሃኔ በአገር አቀፍ ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በሚመለከት በዚሁ ብሎግ ሥር በተከታታይ አራት ጽሑፎች መቅረባቸዉ ይታወሳል። በዚሁ የመክፈቻ ንግግራቸዉ ዶክተር ብርሃኔ ስለ አገር በቀል ሰብሎች፣ ስለ ብዝሀ ህይወት ጥበቃ፣ ከፍተኛ ምርት ስለሚሰጡ ዝሪያዎች አስፈላጊነት፣ ስለ ሣይንስና ሥልጠና አስፈላጊነት እንዲሁም ትኩረት ሊደረግባቸዉ ስለሚገቡ ነጥቦች በዝርዝር አቅርበዋል።

ጥቅምት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተካሄደዉ የሁለተኛዉ ሲምፖዚየም ተሳታፊዎች

በዚሁ የአንድ ቀን ሲምፖዚየም ሰባት ምሁራን በሁለት ምድብ ተከፍለዉ ጽሑፎቻቸዉን ያቀረቡ ሲሆን ሁለት የፓናል ውይይቶችም ተካሂደዋል። የመጀመሪያዉ ምድብ የአየር ንብረት ለዉጥና ቴክኖሎጂ የሚል ሲሆን ጽሑፎቻቸዉን ያቀረቡት ምሁራንና የጽሑፎቻቸዉ ርዕሶች የሚከተሉት ናቸዉ።

  1. ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰዉ (አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ) Future of coffee farming in different climate change scenarios in Ethiopia
  2. ዶክተር ታደለ ተፈራ (ኢ ሲ ፔ፣ አዲስ አበባ) Harnessing multiple benefits of push-pull technology in Ethiopia
  3. ዶክተር ግርማ ታቦር (ኮርቴቫ፣ አሜሪካ) Biotechnology for the benefit of agriculture and society
ሲምፖዚየሙን በንግግር የከፈቱት ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን (በስተግራ) እና በቡናችን ላይ የተደቀነዉን አደጋ ያወጉን ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰዉ (በስተቀኝ)።
  • 4.  ፕሮፌሰር የሆሹዋ ሳራንጋ (ሂብሩ ዩኒቨርስቲ ጄሩሳሌም፣ እስራኤል) Ancestral QTL alleles from emmer wheat enhance drought resistance & productivity of modern wheat

ከአራቱ ጽሑፎች ቀጥሎ በተደረገዉ የፓናል ውይይት የተሳተፉት ከላይ ጽሑፎቻቸዉን ያቀረቡት አራቱ ምሁራንና የአዲስ አበባ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር አዳነ አብርሃም ሲሆኑ የፓናል ውይይቱን የመሩት የመቀሌ ዩኒቨርስቲዉ ፕሮፌሰር ምትኩ ኃይሌ ናቸዉ።

የፓናል አንድ ተሣታፊዎች (ከግራ ወደ ቀኝ)፤ ሺራን ቤንዜቭ (የፕሮፌሰር የሆሹዋ ሳራንጋ ተወካይ)፣ ዶክተር ግርማ ታቦር፣ ፕሮፌሰር ምትኩ ኃይሌ (አወያይ)፣ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰዉ፣ ዶክተር ታደለ ተፈራ እና ዶክተር አዳነ አብርሃም።

በሁለተኛዉ ምድብ የቀረቡት ጽሑፎች የጄኔቲክስና የዕጽዋት ሣይንስ የወደፊት ተስፋ የሚል ሲሆን ጽሑፎቻቸዉን ያቀረቡ ምሁራንና የጽሑፎቻቸዉ ርዕሶች የሚከተሉት ናቸዉ።

  1. ዶክተር ናኦሚ ናካያማ (ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኤዴንብራ፣ እንግሊዝ) Touch-based enhancement of crop resilience: applying mugifumi to cereals
  2. ዶክተር ታካዮሺ ኢሺ (ቶቶሪ ዩኒቨርስቲ፣ ጃፓን) Chromosome elimination in plant wide hybridization for sustainable agriculture in future dryland
  3. ፕሮፌሰር ጆን ማኬይ (ኮሎራዶ ስቴት ዩኒቨርስቲ፣ አሜሪካ) Plant genetics to adapt to and reduce climate change (በቪዲዮ ኮንፈረንስ)

ከሶስቱ ጽሑፎች ቀጥሎ በተደረገዉ ሁለተኛዉ የፓናል ውይይት የተሳተፉት ከላይ ጽሑፎቻቸዉን ካቀረቡት ሶስት ምሁራን በተጨማሪ ዶክተር ጥልዬ ፈይሳ (አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ) እና ዶክተር መላኩ ገድል (አይ አይ ቲ ኤ፣ ናይጄሪያ) ሲሆኑ የፓናል ውይይቱን የመሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲዉ ፕሮፌሰር እንዳሻዉ በቀለ ናቸዉ።

የፓናል ሁለት ተሣታፊዎች (ከግራ ወደ ቀኝ)፤ ዶክተር ታካዮሺ ኢሺ፣ ዶክተር መላኩ ገድል፣ ፕሮፌሰር እንዳሻዉ በቀለ (አወያይ)፣ ዶክተር ናኦሚ ናካያማ፣ ዶክተር ጥልዬ ፈይሳ እና ፕሮፌሰር ጆን ማኬይ (በቪዲዮ ኮንፈረንስ)

የፓናል ሁለት ተሣታፊዎች (ከግራ ወደ ቀኝ)፤ ዶክተር ታካዮሺ ኢሺ፣ ዶክተር መላኩ ገድል፣ ፕሮፌሰር እንዳሻዉ በቀለ (አወያይ)፣ ዶክተር ናኦሚ ናካያማ፣ ዶክተር ጥልዬ ፈይሳ እና ፕሮፌሰር ጆን ማኬይ (በቪዲዮ ኮንፈረንስ)

በመጨረሻም የግብርና ምርምር ዳይሬክቴር ጄኔራል ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሤ የመዝግያ ንግግር በማድረግ ሲምፖዚይሙ በታቀደለት ሰዓት ከቀኑ 11 ሰዓት ተጠናቋል። በሲምፖዚየሙ በቀረቡት ጽሑፎችና በፓናል ውይይት ሰለተደረገባቸዉ ነጥቦች በሌላ ብሎግ እጽፋለሁ።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥቅምት 21፣ 2012 ዓ.ም. (November 1, 2019)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የማሽላዉ አባት፣ ክፍል 4

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የማሽላዉ አባት፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን

ክፍል 4

በሦስት ተከታታይ ክፍሎች በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉትና በማድረግም ላይ ስለሚገኙት የ84 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ስለሆኑት ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን ስለ ዕድገታቸዉ፣ የሥራ ልምዳቸዉ፣ የሥራ ባልደረቦቻቸዉ በተለይም በሰፊዉ ስለሚታወቁበት የማሽላ ምርምር የሚያትቱ ጽሑፎች አቅርቤ ነበር። በዛሬዉ ክፍል 4 እና የመጨረሻ ጽሑፌ ደግሞ በማሽላ ላይ ስለነበረዉና በአሁኑ ጊዜም ስላለዉ ምርምር ተጨማሪ መረጃ የሚሰጡኝ ሲሆን ገጠመኞቻቸዉንም ያጫውቱኛል።

ምስሉ የሚያሳየዉ ዶክተር ብርሃኔ በአንድ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ሆነዉ ነዉ።

ማስገንዘቢያ፣ ካልተገለጸ በስተቀር በጽሑፉ ውስጥ የተጠቀሱት ቀናት ሁሉ እንደ አዉሮፓውያን አቆጣጠር ነዉ።

ጥያቄ፤ በአሜሪካ ብሔራዊ የምርምር ካዉንስል በ1996 የታተመዉ Lost Crops of Africa በሚለዉ መጽሐፍ ከገጽ 181-182 ስለ ኢትዮጵያ ማሽላ ተጽፏል። በተለይም ወተት በጉንጬ እና ማርጩቄ ስለሚባሉት ታዋቂ የማሽላ ዓይነቶች። እንደ ጽሑፉ አባባል እነዚህ ሁለት ዝሪያዎች ምንም እንኳ የፕሮቲን መጠናቸዉ ከፍተኛ ቢሆንም በምርምራቸዉ ወደፊት ሊገፉ አልቻሉም። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰዉ እነዚህ ሁለት ዝሪያዎች በቀላሉ ለወፍ፣ ተባይና በሽታ ስለሚጠቁ ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ ወተት በጉንጬ እና ማርጩቄ ሲፈጩ የሚሰጡት ዱቄት ጥራቱ ዝቅተኛ እንደሆነ ይገልጻል። ይህ መረጃ ትክክል ነዉን?

ዶክተር ብርሃኔ፤ ወተት በጉንጬ ወይም ማርጩቄ የሚባሉት ሁለት የተለያዩ ስያሜዎች ቢሰጣቸዉም ሁለቱም ስሞች የአንድ የማሽላ ዓይነትን ይወክላሉ። ይህ የማሽላ ዓይነት ጣፋጭ ከመሆኑም በተጨማሪ በዉስጡ ከፍተኛ የሆነ ላይሲን የተባለ አስፈላጊ ንጥረ ነገርና ፕሮቲን ይዟል። ይህ የማሽላ ዓይነት ከወሎ አካባቢ የተገኘ ነዉ። ከላይ በጠቀስከዉ መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸዉ ምንም እንኳ የዚህ ማሽላ ዓይነት እጅግ ከፍተኛ የሆነ ለሰዉነታችን ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮች በዉስጡ ቢይዝም የተደረጉት ሰፋ ያሉ ጥናቶች የተጠበቀዉን ያህል ውጤት ሊያመጡ አልቻሉም። ምክንያቱም በተደረጉት የማዳቀል ሥራዎች የወተት በጉንጬን ጥሩ ጎኖች በመውሰድ ከፍተኛ ምርት ወደሚሰጡት የማሽላ ዓይነቶች ማስተላለፍ አለመቻሉ ነዉ። የወተት በጉንጬ ደካማ ጎኑ በፍሬዉ ዉስጥ ያለው ኢንዶስፐርም (endosperm) ተብሎ የሚታወቀዉ ክፍል ለስላሳና የተሰባበረ በመሆኑ የፍሬዉ ክብደትም አነስተኛ ነዉ። ይህም የወተት በጉንጬ ማሽላ ሲፈጭ የሚሰጠዉ የዱቄት መጠን በጣም ዝቅ ያለ እንዲሆን ያደርገዋል። በዚሁ ምክንያት ይህ የማሽላ ዓይነት በብዛት የሚበቅልበት አካባቢ ጥቅም ላይ የሚዉለዉ በእሸትነቱ ጊዜ በመቁላትና በመመገብ ነዉ እንጂ በመፍጨትና በምግብ መልክ በመጠቀም አይደለም።

ጥያቄ፤ እርስዎ ከነበሩበት ወቅት ጋር ሲያወዳድሩት ባሁኑ ጊዜ የማሽላ ምርምርና ምርታማነት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ዶክተር ብርሃኔ፤ በሌሎቹ የሀገራችን ሰብሎች ምርምር ላይ እንደሚታየዉ ሁሉ የማሽላ ምርምርም በመስኩ የሰለጠነ የሰዉ ኃይል ረዘም ላለና ተከታታይነት ባለዉ መልኩ ለማቆየት አልቻለም። ምንም እንኳ ይህ የሰለጠነ የሰዉ እጥረት የምርምር ፕሮግራሙን በከፍተኛ ሁኔታ ቢፈታተነዉም ለተለያዩ ሥነ ምህዳር ላላቸዉ አካባቢዎች የተሻሻሉ ዝሪያዎችን በማስለቀቅ ወደ ገበሬው እንዲደርሱ ለማድረግ ተችሏል። በቅርብ ጊዜያት ከተለቀቁትና አምራቹ ዘንድ ከደረሱት የማሽላ ዝሪያዎች መካከል ዲቃላ ያልሆኑና የዲቃላ ማሽላ ዓይነቶችም ይገኙበታል። እነዚህም ጎብዬ፣ ተሻለ፣ ብርሃን፣ ESH1 እና ESH2 የተባሉትን ያካትታል። በዚሁ ምክንያት ባለፉት ዓመታት የማሽላ ምርታማነት እየጨመረ መሄዱ ምርምሩ ወደፊት እየሄደ እንደሆነ ያሳያል። እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት አሜሪካን ሀገር ከሚገኘዉ የፐርዱ ዩኒቨርስቲ በመሆን በኢትዮጵያ የማሽላ ማሻሻያ ፕሮግራም ዉስጥ የላቀ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ስለሚገኙት ሰለ ፕሮፌሰር ገቢሣ ኢጀታ ነዉ።

ጥያቄ፤ በሥራ ዘመንዎ ወቅት ፋታ የማይሰጥ የሥራ ጫና የነበርዎት መቼ ነበር? በዚያን ወቅት በቀን ለስንት ሰዓት ይሠሩ ነበሩ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ ለማሽላ ተመራማሪዎች ፋታ የማይሰጡ ጊዜያት በወቅት ላይ የተመሠረቱ ናቸዉ። በተለያዩ ሙከራ ጣቢያዎች የሚላኩ ዘሮችን ከማዘጋጀትና ማደራጀት አንስቶ በወቅቱ እንዲዘሩ ማድረግ፣ መረጃ መሰብሰብና መረጣ ማካሄድ፣ በመቀጠልም በወቅቱ እንዲታጨዱና እንዲወቁ ያለዉ ጊዜ ሁሉ የቅርብ ክትትል ይፈልጋል። በተለይም ዘር ከዘራን በኋላ ዝናብ እንዲዘንብልን በናፍቆት የምንጠብቀዉ ጊዜና የምንጸልየዉ አንዱ የሥራችን አካል ነበር። የምርምራችንን ጊዜም ለማፋጠን ከዋናዉ የሰብል ወቅት በተጨማሪ በመልካ ወረር ምርምር ጣቢያ በመስኖ በመታገዝ ስለምንሠራ ዓመቱን ሙሉ እረፍት አለ ማለት አይቻልም። በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የማሽላ ሙከራ ጣቢያዎችን መጎብኘት አንዱ ኃላፊነቴ ስለነበር በሀገሪቷ በሙሉ ሰፋ ያለ ጉዞ አካሄድ ነበር። በዋናዉ የሰብል ወቅት በቢሮና በመስክ በቀን ከ12 ሰዓታት በላይ ማሳለፍ የሚኖርብኝ ጊዜ የነበረ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ከሥራ መልስ ቤት የምሠራቸዉ የጽሑፍ ሥራዎችም ነበሩኝ።

ጥያቄ፤ በሥራ ዓለም ያጋጠሞት ገጠመኝ ወይም ፈታኝ ወቅት ካለ ቢያካፍሉኝ፤

ዶክተር ብርሃኔ፤ በርካታ ገጠመኞች ወይም ፈታኝ ጊዜያት ነበሩብኝ። የተወሰኑትን በተለይም ከማሽላ ሥራዬ ጋር የሚገናኙትን ባጭሩ ከዚህ በታች ለመጥቀስ እወዳለሁ።

  1. የመጀመሪያዉ ገጠመኜ የማስትሬት ትምህርቴን አጠናቅቄ በ1964 ከዉጭ እንደተመለስኩ በአለማያ እርሻ ኮሌጅ የአሜሪካ መምህሮቻችንን በኢትዮጵያኖች መተካቱ የተጀመረበት ወቅት ነበር። ስለዚህ በዚሁ በ1964 የትምህርት ዘመን በእኔና ሦስት የሥራ ባልደረቦች በዚህ በመተካካቱ ፕሮግራም እንድንካተት በመደረጉ ከፍተኛ የሥራ ድርሻና ኃላፊነት ወደቀብን። በዚህ ጊዜ በኔና በሥራ ባልደረቦቼ ላይ የነበረዉ ፈታኝ ሁኔታና ጭንቀት የማይረሳኝ ነዉ።
  2. ሁለተኛዉ ገጠመኜ በእርሻ ኮሌጁ መምህር በሆንኩ በአምስተኛዉ ዓመት ማለትም በ1969 መጨረሻ ላይ ተደራራቢ ኃላፊነቶች የወደቁብኝ ወቅት ነበር። ከእነዚህ ኃላፊነቶች ዉስጥ አንዱ የዕጽዋት ሣይንስ ዲፓርትመንት ኃላፊ መሆን ሲሆን ሌላዉ ደግሞ የብርዕና አገዳ የምርምር ክፍል ኃላፊነትም ደርቤ እንዲይዝ መደረጉ ነበር። በተመሣሣይ ወቅት የተለያዩ ኮርሶችም ማስተማር ነበረብኝ። ይህን ሁሉ የኃላፊነትና የማስተማር ሥራ በማስፈጽምበት ወቅት የምከተለዉ አንዳችም መመሪያ አልነበረም። እንደ አርአያ ሆኖልኝ የምከተለዉ ሰዉም አልነበረኝም።
  3. ሶስተኛዉ ገጠመኜ በ1976 በህይወቴ ዉስጥ ካደረኳቸዉ ከፍተኛ ውሳኔዎች መካከል አስቸጋሪዉንና ከባዱን የወሰንኩበት ዓመት ነበር። ይህም የአለማያ ኮሌጅ ግቢን ለቅቄ IDRC ከተባለዉ የካናዳዉ የዕርዳታ ድርጅት ባገኘሁት ድጋፍ ያቋቋምኩትን የብሔራዊ የማሽላ ማሻሻያ ፕሮግራም ለማስተባበር አዳማ አካባቢ ወደሚገኘዉ ወደ መልካሳ ምርምር ጣቢያ ለመጓዝ መወሰኔ ነበር።
  4. ሌላዉ ገጠመኜ ወይም ፈታኝ ወቅት ከዚሁ ወደ መልካሳ ከተጓዝኩበት ውሳኔ ጋር ይገናኛል። ይኸዉም ለሁለት አለቆች ሪፖርት ማድረግ ያለብኝ ስለነበረ ነዉ። አንዱ አለቃዬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር የነበረዉ የአለማያ እርሻ ኮሌጅ ሲሆን ሁለተኛዉ አለቃዬ ደግሞ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ነበር። የአስተዳደር ሥራዎችን በተመለከተ በአለማያ ሥር የነበርኩ ሲሆን በሥራ ማስፈጸም በኩል በእርሻ ምርምር ሥር ነበርኩ።
ዶክተር ብርሃኔ የ52 ዓመት የትዳር ጓደኛቸዉ ከሆኑት ከወይዘሮ ገነት ታደሰ ጋር በሎዛን ስዊዘርላንድ የሚገኘዉን የኦሎምፒክ ሙዚየም በጎበኙበት ወቅት።

በ1979 የኢትዮጵያ ሁኔታ የተረጋጋ አልነበረም። በዚሁ ምክንያት ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሰባሰብናቸዉን ወደ 5,000 የሚጠጉ የማሽላ ዓይነቶችን ልናጣ የምንችልበት ሁኔታ ላይ ደርሰን ነበር። ይህም እንዳይከሰት አንድ አስቸጋሪ ዉሳኔ መወሰን ነበረብኝ። ይህም እነዚህ ዕንቁ ዝሪያዎችን በሦስት የተለያዩ ቦታዎች እንዲቀመጡ ማድረግ ነበር። እነዚህ ዘሮች በአስተማማኝነት እንዲቀመጡ ያደረኩባቸዉ ሥፍራዎች በአዲስ አበባ የሚገኘዉ የብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት፣ ICRISAT የተባለው በህንድ ሀገር በሃድራባድ የሚገኘዉ ዓለም አቀፍ ድርጅት እና ዋሽንግተን ዲ ሲ የሚገኘዉ USDA የተባለዉ የአሜሪካ የእርሻ ዲፓርትመንት ናቸዉ።

በ1982 ICRISAT ለሚባለዉ ዓለም አቀፍ ድርጅት በምሠራበት ወቅት የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የማሽላ ማሻሻያ ማዕከል በናይሮቢ ማቋቋም ነበረብኝ። ይህንንም ምንም መሠረት ካልነበረበት ሁኔታ ተነሥቼ ማቋቋም ሰለነበረብኝ አንዱ ፈታኝ ወቅት ነበር።

ሌላው በህይወቴ ሙሉ የማልረሳዉ ትዝታዬ በ1988 ሜሩ በምትባለዉ የኬንያ ከተማ አካባቢ በኔና በአራት ኬንያዊያን ፕሮፊሽናል የሥራ ባልደረቦቼ ላይ የደረሰብን አሰቃቂ የመኪና አደጋ ነዉ። በዚህ የከፋ አደጋ ሁለቱ ኬንያውያን የሞቱበት በተረፍነዉ ላይም ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰብን ነበር። የዚህን የከፋ አደጋ ሁኔታ ከጭንቅላቴ ውስጥ ፍቄ ላወጣዉ አልቻልኩም።

በዚሁ ከዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን ጋር በአራት ከፍሎች የቀረቡ ቃለ መጠይቆች አበቃለሁ። በርካታ ትምህርት እንደወሰዳችሁ አምናለሁ።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኝላችኋለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥቅምት 2፣ 2012 ዓ.ም. (October 13, 2019)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የማሽላዉ አባት፣ ክፍል 3

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የማሽላዉ አባት፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን

ክፍል 3

በክፍል አንድና ሁለት ጽሑፌ በግብርናዉ መስክ ላለፉት 55 ዓመታት በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉትና በማድረግም ላይ ስለሚገኙት ስለ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን አጠቃላይ የሥራ ልምዳቸዉና በሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ደረጃ በኃላፊነት ስላሳለፉበት ጊዜ ስለነበረዉ ሁኔታ ያደረኩላቸዉን ቃለ መጠይቅ አቅርቤ ነበር። በተጨማሪም በኢትዮጵያ የማሽላ ምርምር ላይ ስላደረጉት አስተዋጽኦ የሚያወሳ ጽሑፍም አስነብቤ ነበር። በዛሬዉ ጽሑፌ ደግሞ ስለ ዕድገታቸዉ፣ የሥራ ጸባያቸዉና ተማሪዎቻቸዉ የነገሩኝን አካፍላችኋለሁ።

ማስገንዘቢያ፣ ካልተገለጸ በስተቀር በጽሑፉ ውስጥ የተጠቀሱት ቀናት ሁሉ እንደ አዉሮፓውያን አቆጣጠር ነዉ።

ጥያቄከዚህ ቀደም በቀረቡት ሁለት ክፍሎች በርካታ ጥያቄዎች ጠይቄዎት ነበር። ነገር ግን ስለ ዕድገትዎና የልጅነት ጊዜዎ ሳልጠይቅዎት ቀረሁ። ለመሆኑ መቼና የት ተወለዱ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ የተወለድኩት ኦግስት 12፣ 1936 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ነሐሴ 6፣ 1928) የአዲስ አበባ መሃል በነበረዉ የአራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ ነዉ። እንደሚታወቀዉ በዚያ እኔ በተወለድኩበት ወቅት የኢጣሊያ ወረራ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተስፋፋ የነበረበት ጊዜ ነበር።

ጥያቄ፤ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትዎን የት ተማሩ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ በዚሁ የኢጣሊያ ወረራ ምክንያት መላዉ ቤተሰቤ ከአዲስ አበባ ለቆ ለመሄድ ተገደደ። ለዚሁም አመቺ ይሆናል ተብሎ የተመረጠዉ ሥፍራ ከአዲስ አበባ ራቅ ያለ ገጠራማ መንደር ነበር። ይህም መንደር የሚገኘዉ ሙህር በሚባለዉ የጉራጌ አካባቢ ነበር። ፊደል የቆጠርኩት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ልማድ መሠረት በአካባቢዉ በሚገኘዉ ታዋቂዉ የሙህር ገዳም ኢየሱስ ነበር። ከሦስት ዓመታት የገዳም ኢየሱስ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቴ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተዛዉሬ መደበኛ ትምህርቴን ጀመርኩ። በዚሁ መሠረት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ለገሀር አካባቢ በሚገኘዉ የቀድሞ በየነ መርዕድ ትምህርት ቤት ተከታትዬ አጠናቀኩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን Point-4 Program (በአሁኑ USAID) ተብሎ በሚጠራዉ በአሜሪካን መንግሥት ድጋፍ በተቋቋመዉ በወቅቱ የጅማ የእርሻ ቴክኒካል ትምህርት ቤት (Jimma Agricultural Technical School – JATS) ገብቼ ልማር ችያለዉ። በጂማ የነበረዉን ትምህርቴን እንዳጠናቀኩ አለማያ ወደሚገኘዉ በወቅቱ Imperial Ethiopian College of Agricultural and Mechanical Arts ይባል በነበረዉ የእርሻ ኮሌጅ ገብቼ የመጀመሪያ ዲግሬዬን ለማግኘት ችያለሁ።

ጥያቄ፤ እርስዎ በአለማያ እርሻ ኮሌጅ ያስተማሯቸዉ ተማሪዎች በአሁኑ ጊዜ በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ? ስለ ጥቂቶቹ ቢገልጹልኝ።

ዶክተር ብርሃኔ፤ በአለማያ ኮሌጅ ለበርካታ ዓመታት ባስተማርኩበት ወቅት የተለያዩ ኮርሶች ከኔ የወሰዱ ተማሪዎች በርካታ ናቸዉ። በርካታ ከመሆናቸዉም የተነሣ ቆጥሬ ልደርስባቸዉ አልችልም። በዚሁ ምክንያት አንዳንዶቹ ባሁኑ ጊዜ የት እንዳሉም ማወቅ ያዳግተኛል። ይህ ቃለ መጠይቅ ከማሽላ ምርምር ጋር በነበረኝ ሁኔታ ላይ ስለሚያተኩር በክፍል 2 ቃለ መጠይቄ ስለገለጽኩትና IDRC ተብሎ በሚጠራዉ የካናዳ ዕርዳታ ድርጅት በተገኘ ድጋፍ ባቋቋምኩት የኢትዮጵያ ማሽላ ማሻሻያ ፕሮግራም (ወይም ባጭሩ ESIP ተብሎ ይጠራ በነበረዉ) ውስጥ ለረዥም ጊዜ ከኔ ጋር በቅርበት ከሠሩት ጋር አተኩራለሁ። ይህንኑ የማሽላ ማሻሻያ ፕሮግራም በጀመርኩበት በ1973 ከአለማያ እርሻ ኮሌጅ በባችለር ዲግሪ በቅርብ የተመረቁ አራት ወጣቶች ተቀላቀሉኝ። እነርሱም አጥናዉ አይተንፍሱ፣ ገቢሣ እጀታ፣ ሰለሞን ኬቤታ እና ይልማ ከበደ የተባሉት ናቸዉ። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ አበበ መንክር የተባለ ሌላ የዚሁ ኮሌጅ ተመራቂ ፕሮጀክታችንን ተቀላቀለ። እነዚህ ስማቸዉ ከላይ የጠቅስኳቸዉ የሥራ ባልደረቦቼ ለተከታታይ ትምህርት ወደ ካናዳና አሜሪካ ተላኩ። ከአጥናዉ በስተቀር ሁሉም እስከ ዶክትሬት ደረጃ ሊማሩ ችለዋል። አጥናዉ ከሁለተኛ ዲግሪ በኋላ ትምህርቱን አልቀጠለበትም። ከነዚህ የቀድሞ የማሽላ ማሻሻያ ፕሮግራም ባልደረቦቼ መካከል ዶክተር ገቢሣ በዓለም የሚታወቀዉን የዓለም የምግብ ሽልማት (World Food Prize የሚባለውን) የተሸለመ ሲሆን ባሁኑ ጊዜ በአሜሪካ የፐርዱ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ነዉ። ዶክተር ይልማ ደግሞ ከላይ የተጠቀሰዉን የማሻላ ማሻሻያ ፕሮግራም አስተባባሪ በመሆን ለረዥም ዓመታት ሠርቷል። በመቀጠልም ፓዮኒር በተባለዉ ግዙፍ የዘር ማምረቻ ኩባንያ እና ቀጥሎም ቢልና ሜሊንዳ ጌትስ በሚባለዉ በዓለማችን ትልቁ ግብረ ሠናይ ድርጅት የማሽላ ከፍተኛ ኤክስፐርት በመሆን አገልግሏል። ዶክተር ሰለሞን ደግሞ በካናዳ የእርሻ ዲፓርትመንት ውስጥ የገብስና ሲናር ምርምር ኃላፊ በመሆን አገልግሏል። ዶክተር አበበ ባሁኑ ጊዜ IITA ተብሎ በሚጠራዉ ዓለም አቀፍ የምርምር ማዕከል ዉስጥ የበቆሎ ማሻሻል የፕሮግራም መሪ ነዉ።

ጥያቄ፤ በረዥም የሥራ ዘመንዎ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰፊዉ የተጓዙ ይመስለኛል። ከተጓዙበት ሥፍራ ያልተጓዙበትን መጥራት ሳይቀል አይቀርም። እስካሁን የትኛዉን የሀገሪቱን ክፍል ለማየት ዕድሉን አላገኙም?

ዶክተር ብርሃኔ፤ ማሽላ አብቃይ የሆኑ ሥፍራዎችን ሁሉ ለማየት ዕድሉ ገጥሞኛል፣ ኤርትራንም ጨምሮ።

ጥያቄ፤ እርስዎ የኢትዮጵያ የማሽላ ምርምርን በሚያስተባብሩት ወቅት የሰብሉ ምርት እንዳያድግ አንቀዉ ከያዙት ዉስጥ ዋናዎቹ የትኞቹ ነበሩ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ የማሽላ ምርታማነት እንዳያድግ በከፍተኛ ደረጃ የሚፈታተኑት እንደ ቅደም ተከተላቸዉ ከትልቁ ወደ ትንሹ የሚከተሉት ናቸው።

  1. የዝናም እጥረትና ድርቅ፣
  2. ተባይና ወፍ በተለይም ግንድ ሠርሳሪዉ ትልና ግሪሳ የሚባለዉ የወፍ መንጋ፣
  3. የአረም ጥቃት ሲሆን ባንዳንድ ሥፍራዎች የአቀንጭራ ችግር፣
  4. ለተለያየ ሥነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ ምርጥ ዝሪያዎች አለመኖር እና
  5. ተስማሚ የሰብል እንክብካቤ ዘዴዎች አለመኖር ናቸዉ።
ምሥሉ የሚያሳየዉ ቆቦ አካባቢ በደህና ሁኔታ አድጎ ያለ የማሽላ ማሳን ነዉ። ፎቶ፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን

ጥያቄ፤ ገበሬዎች ለማሽላቸዉ የተለያየ ስያሜ ይሰጧቸዋል። ከነዚህ ዉስጥ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ወተት በጉንጬ፣ ወፍ አይበላሽ፣ ስንዴ ለምኔ፣ ቂጥኝ አይፈሬ፣ ጋን ሰበር እና ፈንዲሻ የተባሉት ይገኙበታል። እነዚህ ስሞች ምንን ያመለክታሉ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ ወተት በጉንጬ የተባለዉ ዝሪያ በእሸትነቱ ተጠብሶ ሲበላ በተመጋቢዎች ዘንድ ጣፋጭ ሆኖ ተወዳጅ ከመሆኑም በተጨማሪ ከፍተኛ ላይስን እና በጠቅላላዉ ከፍተኛ የሆነ ፕሮቲን በዉስጡ የያዘ ነዉ። ወፍ አይበላሽ የተባለዉ ዝሪያ ደግሞ ፍሬዉ ጎምዛዛ ስለሆነ የወፎች ጥቃት አይደርስበትም። ስንዴ ለምኔ የሚባለዉ ዝሪያ ደግሞ ከሱ የሚጋገረዉ ዳቦ ከስንዴ ከሚጋገረዉ ጋር በጥራቱ ተቀራራቢነት ስላለዉ ነዉ። ቂጥኝ አይፈሬ የተባለ ስያሜ የተሰጠዉ ዝሪያ ደግሞ የአቀንጭራ ጥቃትን ለመቋቋም በመቻሉ ነዉ። ጋን ሰበር የተባለዉ ዝሪያ ደግሞ ኃይለኛና ጥሩ ጠላ የሚያስጠምቅ ነዉ። ፈንዲሻ የተባለዉ ዝሪያ ሲቆላ ፈንድቶ ጥሩ ካሽ ካሽ የሚል መክሰስ ይሆናል።

ከዶክተር ብርሃኔ ላይ ያደረኩት ቃለ መጠይቅ በዚህ አያበቃም። በክፍል 4 በማሽላ ላይ ስለሚደረገዉ ምርምር ተጨማሪ መረጃ የሚሰጡኝ ሲሆን ገጠመኞቻቸዉንም ያጫውቱኛል። እስከዚያዉ መልካም ጊዜ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥቅምት 2፣ 2012 ዓ.ም. (October 13, 2019)

ግብርናችንን ለማዘመን፤ የማሽላዉ አባት፣ ክፍል 2

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የማሽላዉ አባት፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን

ክፍል 2

በክፍል አንድ ጽሑፌ በግብርናዉ መስክ ላለፉት 55 ዓመታት በሀገር አቀፍም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉትና በማድረግም ላይ ስለሚገኙት ስለ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን አጠቃላይ የሥራ ልምዳቸዉና በሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ደረጃ በኃላፊነት ስላሳለፉበት ሁኔታ አስነብቤ ነበር። በዛሬዉ ጽሑፌ ደግሞ እኚሁ አንጋፋ የግብርና ምሁር በተለይ ስለሚታወቁበት የማሽላ ምርምር ላይ አተኩራለሁ። በክፍል አንድ እንደቀረበዉ ሁሉ የዛሬዉ ጽሑፌም ከምሁሩ ጋር በተደረገዉ ቃለ መጠይቅ መልክ ይቀርባል።

ማስገንዘቢያ፣ ካልተገለጸ በስተቀር በጽሑፉ ውስጥ የተጠቀሱት ቀናት ሁሉ እንደ አዉሮፓውያን አቆጣጠር ነዉ።

ጥያቄ፣ በክፍል አንድ እንደገለጹልኝ የመጀመሪያ የምርምር ሥራዎን በሀረማያ ኮሌጅ የጀመሩት በገብስ ላይ ነበር። ለሶስት ዓመታት ብቻ በገብስ ምርምር ከቆዩ በኋላ ለዶክትሬት ትምህርትዎ ወደ አሜሪካን ሄዱ። ትምህርትዎን አጠናቅቀዉ ሲመለሱ የበቆሎ ተመራማሪ ሆኑ። የምርምር አቅጣጫዎን ከገብስ ወደ በቆሎ የቀየሩብት ዋናው ምክንያት ምንድነው?

ዶክተር ብርሃኔ፣ እንደአጋጣሚ ሆኖ ትምህርቴን በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሚኔሶታ በምጨርስበት የመጨረሻ ዓመት ላይ ሲግራም (Seagram) የሚባለዉ የካናዳ ዊስኪ አምራች ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ ለበቆሎ ምርምር ጠቀም ያለ መዋዕለ ንዋይ እንደሚሰጡኝ ፍንጭ ሰጥተዉኝ ነበር። በጊዜዉ ይህንን ያደረጉበት ዋናዉ ምክንያት ለዊስኪ ምርታችዉ የሚዉል በርከት ያለ በቆሎ ረዘም ላለ ጊዜ ከኢትዮጵያ ለመግዛት ፍላጎት ስለነበራቸዉ ነዉ። በዚያዉም ለኢትዮጵያ ልማት አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አስበዉ ነበር። ለዚህ ሁሉ ዓላማቸዉ የተሻሻሉ የበቆሎ ዝሪያዎች እንደሚያስፈልጉ ግልጽ ነበር። በዚሁ መሠረት ወደ አለማያ እንደተመለስኩ የተባለዉን የፋይናንስ ጥያቄ በፕሮፖዛል መልክ ለዚሁ ሲግራም ለተባለዉ ኩባንያ አስገብቼ ለበቆሎ ምርምር የሚዉል ጠቀም ያለ የገንዘብ ድጎማ አገኘሁና ወደ በቆሎ ማሻሻል ምርምር ማድላት ጀመርኩ። በዚሁ የተነሣ የገብስ ማሻሻል ሙያዬን ትኩረት እየቀነስኩ ሄድኩ ማለት ነው።

ጥያቄ፣ በበቆሎ ምርምርም የቆዩት ለሁለት ዓመታት ብቻ ነበር። በብዙዎች ዘንድ በሰፊዉ ወደ ሚታወቁበት የማሽላ ምርምር ገቡ። ለምን በበቆሎ ምርምር መቆየት አልፈለጉም?

ዶክተር ብርሃኔ፣ በበቆሎ ላይ ምርምር በምሠራበት ወቅት የማሽላ ምርምርንም ደርቤ እሠራ ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት በወቅቱ በዕጽዋት ሣይንስ ዲፓርትመንት ሌላ የማሽላ ምርምርን በኃላፊነት የሚሠራ የሰለጠነ የሰዉ ኃይል ስላልነበረ ነዉ። ሌላዉ ደግሞ በወቅቱ በማሽላ ምርምር እንደ ሊቅ ከሚቆጠሩት ዶክተር ሂዮ ዶጌት ከተባሉ ምሁር ጋር የቅርብ የምርምር ግንኙነት ፈጥሬ ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ዶክተር ዶጌት አይ ዲ አር ሲ (IDRC International Development Research Center) ከተባለ የካናዳ ግብረ ሠናይ ድርጅት የኢትዮጵያ የማሽላ ምርምር በአፍሪካ ግንባር ቀደም እንዲሆን የሚያስችል ሰፋ ያለ የምርምርና የሰው ኃይል ማሰልጠኛ እንዳቋቁም የሚረዳኝ የገንዝብ ድጋፍ እንዳገኝ አመቻቹልኝ። አለማያ አካባቢ ማሽላ ቀዳሚ ሰብል በመሆኑና አዲስ ከIDRC ባገኘሁት ጠቀም ያለ የገንዘብ ድጋፍ ትኩረቴን ወደ ማሽላ አዞርኩ። በዚሁ መሠረት የበቆሎዉን ምርምር ከሥልጠና በቅርቡ ለተመለሰዉ ለዶክተር ደጀኔ መኮንን አስተላለፍኩ። እኔም ከማሽላ ጋር የጠበቀ ግንኙነቴን ጀመርኩ ማለት ነዉ።

ጥያቄ፣ ከ1973 እስከ 1982 ድረስ ባሉት አሥር ዓመታት የማሽላ አዳቃይና የብሔራዊ ማሽላ ምርምር አስተባባሪ ነበሩ። የሥራ ምድብዎ ደግሞ ሀረማያና አዳማ ነበሩ። እነዚህ ሁለት ጣቢያዎች የተራራቁ ብቻ ሳይሆኑ በሁለት ድርጅቶች (እርሻ ኮሌጅና እርሻ ምርምር) ሥር የሚተዳደሩ ነበሩ። በነዚህ ሁለት ጣቢያዎች እንዴት ባንድ ጊዜ ይሠሩ ነበር?

ዶክተር ብርሃኔከላይ እንደገለጽኩት የማሽላ ምርምር የጀመርኩት አለማያ ነዉ። ይህም ሆኖ ምርምሬ የሚያተኩረዉ በመላ ኢትዮጵያ ነበር። ከካናዳዉ የእርዳታ ድርጅትም ያደረግነዉ ስምምነትም ይህንኑ መሠረት ያደረገ ነበር። ስለዚህ የተለያየ ስነምህዳር ያላቸዉን የማሽላ አብቃይ የኢትዮጵያ አካባቢዎችን የሚወክሉ የማሽላ ምርምር ጣቢያዎች መምረጥ ነበረብን። እነዚህ ስነምህዳሮችም ወይና ደጋ፣ ዝናም አጠር ቆላ፣ ዝናም ጠገብ ቆላ የመሣሰሉት ናቸዉ። ይህንን ሥራ በቅድሚያ እናካሄድ የነበረዉ ወደ ምሥራቅ ባጋደለው አለማያ ነበር። መሃል ኢትዮጵያ ሆኖ ለአገር አቀፍ ማሽላ ምርምር ማስተባበሪያ የሚሆን ቦታ ሳፈላልግ አዳማ አካባቢ ያለዉን የመልካሳ ምርምር ጣቢያ ተስማሚ ሆኖ አገኘሁት። በዚህም ምክንያት ከእርዳታ ድርጅቱ ያገኘሁትን ድጋፍ ሁሉ፣ ቁሳቁስ፣ የሰዉ ኃይልና ገንዘብ ይዤ ወደ አዳማ መልካሳ ገባሁ። ከዚህም ሥፍራ ሆኜ የሀገር አቀፉን የማሽላ ምርምር መሥራትና ማስተባበር ጀመርኩ። ይህን ሁሉ ስናደርግ በጊዜዉ የእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ምንም የማሽላ ምርምር ሥራ አልነበረዉም። ሙሉዉን ኃላፊነት ለኛ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር ለነበረዉ ለአለማያ እርሻ ኮሌጅ ነበር የሰጡን።

ጥያቄ፣ በክፍል አንድ በነገሩኝ መረጃ ተመርኩዤ ሳሰላዉ በሀገር ዉስጥ እና በውጭ ሀገራት በማሽላ ላይ በአጠቃላይ ለ18 ዓመታት በበቆሎ ላይ ደግሞ በአጠቃላይ ለ10 ዓመታት በምርምር ሥራ ተሣትፈዋል። ከበቆሎና ከማሽላ በዬትኛዉ ሰብል ላይ ምርምር መሥራት ይቀላል? ለምን?

ዶክተር ብርሃኔ በቆሎና ማሽላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም የዲቃላ ዝሪያዎች ከመጠቀማቸዉ አንጻር ሲታይ ተመሣሣይ ጸባይ አላቸዉ። የበቆሎ ዲቃላ ዝሪያዎች የማዉጣትና የመጠቀም ሥራ በአለም አቀፍ ደረጃ በጣም የዳበረ ነዉ። የማሽላም ሥራ በተከታይነት ይታወቃል። እነዚህ አለም አቀፍ ልምዶች በሀገር ዉስጥ ለሚሠሩ ሥራዎች በጣም ጠቃሚ መሠረቶች ናቸዉ። በኢትዮጵያ ደረጃ ማሽላ ሀገር በቀል ሰብል ከመሆኑ አንጻርና በጣም የተለያዩ ዓይነቶች ስላሉን ይህንን መሠረት አድርጎ ብዙ ጠቃሚ ሥራዎች መሥራት ይቻላል። የዓለም አቀፍ የማሽላ ምርምር ህብረተሰብ ከኢትዮጵያ የማሽላ ምርምር ተጠቅሟል፣ እኛም ከነሱ ተጠቅመናል። ለምሳሌ ICRISAT የሚባለዉ ዓለም አቀፍ ማዕከል ሲመሠረት በዋነኝነት የተጠቀመዉ የኢትዮጵያ ማሽላ ዝሪያዎች ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ታዋቂዉን E-35 የተባለዉን መጥቀስ ይቻላል።  እኛም ብዙ ዝሪያዎች በተለይም ለዲቃላ ማሽላ መሥሪያ የሚያገለግሉ ዓይነቶችን ከዓለም ማህበረሰብ ወስደናል። ከICRISAT ከመጡ ዝሪያዎች እንደ ኮቦማሽ፣ ብርማሽ፣ 76T1-23 የተባሉት ለሀገራችን ገበሬዎች የተለቀቁ ናቸዉ። ስለዚህ የበቆሎና የማሽላ ምርምር ሥራዎች ተደጋጋፊና ተመሣሣይ ናቸዉ። ዲቃላ ያልሆኑ ዝሪያዎች በማዉጣትና ለተጠቃሚዉ በማድረስ የማሽላዉ ምርምር ሊቀል ይችላል። ያለዉ ልምድና ሁኔታ ይሄዉ ነዉ።

ከላይ በምሥሉ የሚታዩት ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡ የማሽላ አናቶች ናቸዉ። ፎቶ፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን

ጥያቄ፤ የኢትዮጵያ የማሽላ ማሻሻያን በብሔራዊ ደረጃ በሚያስተባብሩበት ወቅት የምርምር ፕሮግራሙ እንዴት ነበር የተቀናጀዉ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ በማሽላ ላይ እናደርግ የነበረዉ ምርምር የአገሪቱን ስነ ምህዳር ወይም አግሮ ኢኮሎጂ በመመርኮዝ በሶስት ክፍሎች በመክፈል ነበር። እነርሱም፣ 1ኛ) ዝናም አጠር ዝቅተኛ ሥፍራዎች፤ እነዚህ ሥፍራዎችን በመወከል በማሽላ ላይ በዋናነት ምርምር እናካሄድ የነበረዉ በመልካሳ፣ ቆቦ፣ አላማጣ፣ ሁመራና ሚኤሶ ነበር። 2ኛ) መካከለኛ ሥፍራዎች፤ እነዚህ ሥፍራዎችን በመወከል በዋናነት ምርምር እናካሄድ የነበረዉ በባኮና ጂማ ነበር። 3ኛ) ከፍተኛ ሥፍራዎች፤እነዚህ ሥፍራዎችን በመወከል በዋናነት ምርምር እናካሄድ የነበረዉ በአለማያና አርሲ ነጌሌ ነበር። ይህንን ሥራ ለማጠናከርና ለመደገፍ በተለይም ከሰብል ማምረቻ ወቅት ዉጭ በበጋዉ ወራት የማዳቀል ሥራና የዘር ብዜት ለማከናወን በመስኖ የመልካ ወረር ምርምር ጣቢያ (የአሁኑን ወረር ምርምር ማዕከል) እንጠቀም ነበር።

ጥያቄ፤ ከዚህ የተቀናጀ የምርምር ፕሮግራም ለገበሬዎች የደረሱ ምርጥ የማሽላ ዝሪያዎች ነበሩን?

ዶክተር ብርሃኔ፤ አዎ፣ በርካታ ምርጥ ዝሪያዎች እንዲለቀቁ አድርገናል። ከነዚህ ውስጥ አለማያ 70፣ ኢ ቲ ኤስ 2752፣ ጋምቤላ 1107፣ ዴዴሳ 1057፣ መልካማሽ 79፣ ባኮማሽ እና ብርማሽ የተባሉት ሊጠቀሱ ይቻላል። በወቅቱ ከተለቀቁት ዝሪያዎች መካካል በአጭር ጊዜ የሚያፈራዉና ድርቅን መቋቋም የሚችለዉ 76T1-23 የሚባለዉ ዝሪያ እስከ ዛሬ ድረስም በምርት ላይ ይገኛል።

ምሥሉ የሚያሳየዉ በቆቦ አካባቢ ያለዉን የዲቃላ ማሽላ ምርምርን ነዉ። ፎቶ፤ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን

ጥያቄ፤ በኢትዮዮጵያ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚበቅሉ የማሽላ ዓይነቶችን በተገቢዉ መንገድ በማሰባሰብም ይታወቃሉ። ምን ያህል አገር በቀል የማሽላ ዓይነቶችን ሊያሰባስቡ ችለዋል?

ዶክተር ብርሃኔ፤ በሀገሪቱ በተለያዩ ማሽላ አብቃይ ሥፍራዎች በመዘዋወር ከ5000 በላይ የሆኑ የማሽላ ዓይነቶችን በማሰባሰብ ለጥናት እንዲበቁ አድርገናል። ዘሮቹ ሳይበላሹ ለረዥም ጊዜ ተጠብቀዉ እንዲቆዩም በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲቱዩት እንዲቀመጡ አድርገናል።

ጥያቄ፤ ኢኮኖሚክ ቦታኒ በሚባለዉ የጆርናል መጽሔት በ1973 ባሳተሙት ጽሑፍዎ ውስጥ በአለማያ ኮሌጅ ከተለቀቁት ዝሪያዎች መካከል በቁመቱ አጠር ያለ ነገር ግን ከፍ ያለ ምርት ይሰጥ የነበረዉ ቁልቢ ድዋርፍ የተባለዉ ዝሪያ በገበሬዉ ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኝ እንዳልቻለ ነዉ። የአካባቢዉ ገበሬዎች ይህንን ምርጥ ዝሪያ ለምን ሊቀበሉ አልቻሉም።

ዶክተር ብርሃኔ፤ በአካባቢዉ ገበሬዉ ማሽላን ለተለያዩ ነገሮች ይጠቀማል። ፍሬዉን ለራሱ ይመገባል፣ ቅጠሉን ለከብቶቹ ይመግባል፣ ግንዱን ደግሞ ለማገዶነት ይጠቀማል። ምንም እንኳ ምርታቸዉ ደህና ቢሆንም በቁመት አጭሮቹ ዝሪያዎች አነስ ያለ ግንድና ቅጠል ስለሚኖራቸዉ በገበሬዎች ዘንድ አይወደዱም ነበር።

ጥያቄ፣ እስካሁን ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከኢትዮጵያ በኩል የተደረግልዎት ዕዉቅና ካለ ቢነግሩኝ፤

ዶክተር ብርሃኔ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተመሠረተበትን ሀምሳኛ ዓመት በዓሉን ሲያከብር ለሀገሪቱ ግብርና ምርምር የላቀ አስተዋጽኦ እንዳበረከትኩ የሚገልጽ የምስክር ወረቀት ሰጥቶኛል። የኢትዮጵያ የሰብል ማሻሻያ ጉባኤ በ1978 የቀዳሚ ተመራማሪነት ዕዉቅና ስጥቶኛል። እንዲሁም የመልካሳ ምርምር ማዕከል ለማሽላ ምርምር ላበረከትኩት አስተዋጽኦ ባሁኑ ዓመት ሠርቲፊኬት ሰጥቶኛል።

ጥያቄ፣ ለኢትዮጵያ ግብርና ያልዎት ራዕይ ምን ይመስላል?

ዶክተር ብርሃኔ፣ ምርምርን በተመለከተ እያንዳንዱ ሰብል ሀገር አቀፍ በሆነ መንገድ የፖለቲካ ክልሎችን ሳይከተል ሁሉንም ሥነ ምህዳሮችን ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ ሥራ ላይ እንዲዉል ምኞቴ ነዉ። በተጨማሪም በብዛት በሀገር ዉስጥ የተቋቋሙ ዩኒቨርስቲዎች በአካባቢያቸዉ ያለዉን ምርምርና የቴክኖሎጂ ስርጸት ከማስተማር ሥራቸዉ ጋር አቀናጅተዉ እንዲሠሩ ምኞቴ ነዉ። ሌላዉ ምኞቴ የኢትዮጵያ ግብርናን ከማዘመን አንጻር የዩኒቨርስቲና ቴክኒካል ኮሌጅ ተመራቂዎች የራሳቸዉን እርሻ እንዲያቋቋሙና እንዲመሩ መንግሥት የሚያስፈልጋቸዉን ድጋፍ ሁሉ እንዲያደርግላቸዉ ነዉ።

ጥያቄ፣ ይህ ራዕይዎ እንዲሳካ ይረዳል ብለዉ የሚገምቱት መልእክት ካለ።

ዶክተር ብርሃኔ፣ ከላይ ያነሳኋቸዉ ምኞቶቼ እንዲሳኩ ዋናዉ የመንግሥት ፖሊሲና አመራር ነዉ። የሚመለከታቸዉ በአመራር ላይ  ያሉ ኃላፊዎች አስፈላጊ እርምጃዎች ይወስዳሉ የሚል ተስፋ አለኝ።

በዶክተር ብርሃኔ ላይ የሚያተኩረዉ ጽሑፌ በዚህ አያበቃም። በክፍል 3 ስለ ዕድገታቸዉ፣ ተማሪዎቻቸዉና የማሽላ ዝሪያዎች የሚነግሩኝን አካፍላችኋለሁ። እስከዚያዉ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መስከረም 28፣ 2012 ዓ.ም. (October 9, 2019)