ግብርናችንን ለማዘመን፤የጤፍ ምርትና ምርታማነትን የበለጠ ለማሳደግ

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሑፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡

የጤፍ ምርትና ምርታማነትን የበለጠ ለማሳደግ

ጤፍ በሀገራችን እጅግ ተፈላጊና ጠቃሚ ሰብል ነዉ። በተለይም በየእለቱ የምንመገበዉን እንጄራ ለማዘጋጀት እንደዋና ግባት የምንጠቀመዉ ጤፍን በመሆኑ ነዉ። ከእንጄራ በተጨማሪ ጤፍ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን ለመሥራት ጥቅም ላይ ይዉላል። ባለፉት ዓመታት የሀገራችን ህዝብ በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ የጤፍ ተጠቃሚም እንዲሁ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሀገራችን ህዝብ ቁጥር በየ 25 አመታት በእጥፍ ያድጋል። በዚሁ መሠረት የሰብል ምርታችን በተመሣሣይ ደረጃ ካላደገ የምግብ አቅርቦታችን ላይ ላይ የጎላ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል። የምርት ዕድገት ለሁሉም የሰብል አይነቶች ቢያስፈልግም በጤፍ ላይ ግን ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ጤፍ የምግባችን ቁልፍ ስብል ነውና።

ምስል 1 እንደሚያሳየዉ ጤፍ በየአመቱ ወደ ሶስት ሚሊዮን በሚጠጋ መሬት ላይ የሚመረት ሲሆን ከሌሎች በሀገሪቱ ከሚመረቱ ሰብሎች ጋር ሲወዳደር ከፍተኛዉ ነው። ጤፍን ተከትሎ በሀገራችን በሰፊው የሚዘሩ ሰብሎች እንደ ቅደም ተከተላቸዉ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ማሽላ እና ገብስ ናቸዉ።

ምንም እንኳ ጤፍ የሚዘራበት የመሬት ስፋት ከሌሎች ሰብሎች ጋር ሲወዳደር በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ቢቀመጥም አጠቃላይ ምርትን በተመለከተ ግን ጤፍ በቆሎና ስንዴን ተከትሎ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ምክንያቱም የጤፍ ምርታማነት ከሁሉም የብርእና አገዳ ሰብሎች ጋር ሲወዳደር እጅግ ዝቅተኛዉ በመሆኑ ነዉ፡፡ በምስሉ እንደሚታየዉ አማካይ የሀገሪቷ የጤፍ ምርታማነት 19 ኩንታል በሄክታር ብቻ ሲሆን የበቆሎ 42 እና የስንዴ 31 ኩንታል በሄክታር ናቸዉ፡፡

ስለዚህ ይህን ዝቅተኛ የጤፍ ምርታማነት ለማሳደግ በሁሉም መስክ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጤፍ በኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ አግሮኢኮሎጂዎች የሚዘራ ሲሆን ከሌሎች ሰብሎች በተሻለ ድርቅንና የዉሃ ማቆርን ይቋቋማል፡፡

ምስል 1፤ በ2014 ዓ ም በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ የተመረቱ የብርእና አገዳ ሰብሎች የመሬት ስፋት፣ አጠቃላይ የምርት መጠን እና ምርታማነት፡፡ ምንጭ፤ Ethiopian Statistics Service. 2022. Agricultural Sample Survey 2021/22 (2014EC). Vol. 1. Reports on Area and Production of Major Crops Meher Season. Statistical Bulletin 593, Addis Ababa, Ethiopia.

በኢትዮጵያ በ2014 ዓ ም አጠቃላይ የጤፍ ምርት 56.1 ሚሊዮን ኩንታል የነበረ ሲሆን ከዚህ ዉስጥ 93.5% የሚሆነዉ የተመረተዉ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ነዉ፡፡ በዚሁ መሠረት 29.9 ሚሊዮን ኩንታል ከኦሮሚያ ክልል እና 22.5 ሚሊዮን ኩንታል ከአማራ ክልል ነዉ፡፡ ምስል 2 እንደሚያሳየዉ እያንዳንዳቸዉ ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚያመርቱ ዞኖች 18 ሲሆኑ ሰባቱ ከአማራ ክልል የተቀሩት 11 ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ናቸዉ፡፡ እያንዳንዳቸዉ ከሶስት ሚሊዮን ኩንታል ጤፍ የሚያመርቱ ዞኖች ደግሞ ምስራቅ ጎጃም፣ ሰሜን ሸዋ እና ደቡብ ጎንደር ከአማራ ክልል ሲሆኑ ምእራብ ሸዋ፣ ደቡብ ምእራብ ሸዋ፣ ምስራቅ ሸዋና ሰሜን ሸዋ ከኦሮሚያ ክልል ናቸዉ፡፡ ይህ የሚያሳየን የጤፍ ምርት በከፍተኛ ደረጃ የሚመረተዉ በመካከለኛዉና በምእራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ነዉ፡፡ ሰለዚህ የጤፍን ከፍተኛ ፍላጎት በከፊልም ለመመለስ በነዚህ ከፍተኛ አምራች የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት በማድረግ ምርታማነት የሚሻሻልበትን መንገድ መቀየስ ያስፈልጋል፡፡ ምርጥ ዝርያዎችን ጨምሮ የምርት ግባቶች ለገበሬዉ እንዲዳረሱ የኢክስቴንሽን ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ምስል 2፤ በየአመቱ እያንዳንቸዉ ከአንድ ሚልዮን ኩንታል በላይ ጤፍ የሚያመርቱ ዞኖች፡፡ ሁም ዞኖች በአማራና በኦሮሚያ የሚገGእኙ ናቸዉ፡፡ ምንጭ፤ Ethiopian Statistics Service. 2022. Agricultural Sample Survey 2021/22 (2014EC). Vol. 1. Reports on Area and Production of major crops Meher Season. Statistical Bulletin 593, Addis Ababa, Ethiopia.

በመለስተኛ የጤፍ አምራች ሥፍራዎችም የጤፍ ምርታማነትን ማሳደግ አስፈላጊ ነዉ፡፡ ያለበለዚያ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየናረ የመጣዉን የጤፍ ዋጋ ከዚህም በበለጠ ደረጃ እንዳያጨምር ከፍተኛ ሥጋት ስላለኝ ነዉ፡፡

የዚህን ጥረት ላማገዝ ያህል፣ በ2014/15 የመኸር ዘመን በጤፍ ምርምር ፕሮጀክታችን ከሚደረገዉ የምርጥ ዘር ሥርጭት በተጨማሪ ለሙከራ ያህል ጤፍ በአነስተኛ ደረጃ በሚበቅልበት በምእራብ አርሲ ዞን በአዳባ ወረዳ ሶስት የጤፍ ዝርያዎችን ፈቃደኛ በሆኑ ገበሬዎች ማሣ ላይ ፈትሸን ነበር፡፡ ዉጤትም እጅግ የሚያመረቃ ነበር፡፡ በተለይም ኤባ የተባለዉን ዝርያ የዘራ ገበሬ በሄከታር 40 ኩንታል ለማግኘት ችሏል፡፡ ውጤቱን ያዩ እና የሰሙ ገበሬዎችም የዚህን ምርጥ ዘር ጥያቄ በከፍተኛ ደረጃ አቅርበዉልናል፡፡ በተጠየቀዉ ደረጃ ምላሽ መስጠት ባንችልም በ2015/16 መኸር ዘመን የሚሆን ሶስት ምርጥ ዝርያዎችን (ማለትም ኤባ፣ ፍላጎት እና ኩሊ የተባሉትን) በወረዳዉ ሥር ለሚገኙ ሶስት ቀበሌዎች እና 35 ገበሬዎችች እንዲከፋፈል በወረዳዉ የግብርና ጽ/ቤት በኩል ዘር ለማቅረብ ችለናል፡፡ ከነዚህ ሥፍራዎች የሚገኘዉ ምርትም ለዘር ብቻ እንዲሆን በማድረግ የምርጥ ዝርያዎች ሥርጭትን ለማስፋፋት እንችላለን፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በገበሬዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን ለማትረፍ የቻለዉ የኤባ ዝርያ በምስል 3 ታይቷል፡፡

በአንዳንድ ምርጥ የጤፍ ተስማሚ ሥፍራዎች የከተሞች መስፋፋትም አሉታዊ ጎን አለዉ፡፡ ስለዚህ የከተሞች ማስፋፊያ ፕላን ስናውጣ የግብርና ምርታችንን በማይጎዳ መልኩ ቢሰራ መልካም ነዉ፡፡

ምስል 3፣ ከፍተኛ አድናቆትን በገበሬዎቻችን ዘንድ እያተረፈ የመጣዉ ኤባ ተብሎ የተሰየመዉ የጤፍ ዝርያ በምንጃር፣ ሸንኮራ እና አዳባ ፉሩና፡፡ ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ፡፡

በአጠቃላይ ጤፍ በተጠቃሚዉ ዘንድ ያለዉን ከፍተኛ ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት ትኩረት ይሰጠዉ እላለሁ፡፡ ሌሎች የሀገራችን ሰብሎች እንደ ስንዴ፣ በቆሎ እና ማሽላ ያሉት የምርምር ፕሮግራማቸዉ በከፍተኛ ደረጃ በአለም አቀፍ የምርምር ተቋማት ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ በተቃራኒዉ የጤፍ ምርምር በዚህ በኩል የሚያገኘዉ ጥቅም እጅግ አነስተኛ ነው፡፡

ወደፊት በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. (August 7, 2023)

አስተያየት ያስቀምጡ