በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤
ዲጂታላይዜሽን
ዲጂታላይዜሽን የሚለዉ ቃል በቅርቡ በብዙ መስኮች በጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። የሚያመለክተዉም የምናገኛቸዉን መረጃዎች በዲጂታል ወይም በኮምፒተር ወይም በተመሣሣይ ቴክኖሎጂ ሊነበቡና ጥቅም ላይ የሚዉሉበት መንገድ ማለት ነዉ። በግብርና ላይ በጥቅም ላይ የምናዉለውን የዚህን ቴክኖሎጂ ዲጂታላይዜሽን ፎር አግሪከልቸር (Digitalization for agriculture) ወይም በምህጻረ ቃል D4Ag ይባላል። ይህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ረቀቅ ባለና ዘመናዊነትን በተላበሰ መልኩ ግብናችንን እንድናዘምን ያስችለናል ማለት ነዉ። ለምሣሌ በመስኖ ዉሃ የሚታገዝ ግብርና ባለበት ሥፍራ መቼና የት አካባቢ ተጨማሪ ውሃ እንደሚያስፈልግ ማወቅ ያስችለናል። ይህንን ለምሳሌ ጠቀስኩ እንጂ ዲጂታላይዜሽን በበርካታ መስኮች ግብርናችንን ያግዛል።
በአፍሪካ ውስጥ በግብርና ዲጂታላይዜሽን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ከሚገኙት ድርጅቶች መካከል ሲ ቲ ኤ (CTA) አንዱ ነዉ። ይህ እ.ኤ.አ. በ1983 የተቋቋመዉና መቀመጫዉን በሆላንድ ሀገር በምትገኘዉ ዋገኒንገን ያደረገዉ ዓለም-አቀፍ ማዕከል በአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት እና በአዉሮፓ ህብረት መካከል የተመሠረት ሲሆን በመዋዕለ ንዋይ የሚደገፈዉም በአዉሮፓ ህብረት ነዉ። ላላፉት ዘጠኝ ዓመታት ማዕከሉን በዳይሬክትሬነት በመምራት ላይ የሚገኙት በመስኩ ከፍተኛ ልምድ ያላቸዉ ኢትዮጵያዊዉ አቶ ሚካኤል ኃይሉ ናችው። ምንም እንኳ ይህ ማዕከል አነስተኛ ቢሆንም ከእርሻ ጋር ተዛማችነት ባላቸዉ መስኮች በተለያዩ ሀገሮች መጠነ-ሰፊ ሥራ ይሠራል። ባሁኑ ጊዜ ትኩረት አድርጎ የሚሠራዉ በወጣት፣ ዲጂታላይዜሽን እና የአየር ንብረት ለዉጥ መቋቋም ላይ ነዉ። ዲጂታላይዜሽንን በተመለከተ ማዕከሉ ረቀቅ ያለ ወይም ፒሪሲሽን ግብርናን ማስተዋወቅ፣ የሳተላይት መረጃን ለዚሁ ተግባር ማዋል፣ ድሮን የተባሉ ዘመናዊ መሣሪዎችንና ሌሎች ተዛማች ያላቸዉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በመልማት ላይ ባሉ ሀገሮች ያሉ ያሉ ገበሬዎች ምርታማነትን እንዴት እንደሚያሳድጉ አስተዋጾኦ ማድረግ ናቸዉ።

በግሌም ሲ ቲ ኤ ባለዉለታዬ ነዉ። የዛሬ 25 ዓመታት ገደማ በኢትዮጵያ እርሻ ምርምር ኢንስትቲዩት በምሠራበት ወቅት እኔና የሥራ ባልደረቦቼ ስፖር (SPORE) የተባለውን የድርጅቱ መጽሔትና ሌሎች መጽሐፍት ያለ አንዳች ክፍያ ባለንበት ድረስ ይልኩልን ነበር። እነዚህ ሕትመቶችም በምርምር ሥራዎቻችን ላይ ከፍተኛ እገዛ አድርገዉልናል። ከዚህ በተጨማሪ የዛሬ 12 ዓመት ባዘጋጀሁት ዓለም-አቀፍ ኮንፈረንስ ከአፍሪካ ሀገራት ተሳታፊ ለነበሩ በርካታ ተመራማሪዎች ወጪአቸዉን ሸፍኖልኛል። ለዚህ ሁሉ ዉለታ ማዕከሉ ምሥጋና ሊደርሰዉ ይገባል።
ወደ ተነሣሁበት ነጥቤ ስመለስ ሲ ቲ ኤ “The Digitalisation of African Agriculture Report, 2018-2019” በሚል ርዕስ 241 ገጽ ያለዉ መጽሐፍ በቅርቡ አሳትሟል። በፒ ዲ ኤፍ መልክ ያለዉን የመጽሐፉን ሙሉ ይዘት ከላይ ካለዉ ድህረ ገጽ ማግኘት ይቻላል። ከርዕሱ መረዳት እንደሚቻለዉ መጽሐፉ በአፍሪካ አህጉር በግብርናዉ መስክ ዲጂታላዬዜሽን ያስመዘገበዉንና ወደፊትም ያለዉን ተስፋ ያሳያል። እኔም በመጽሐፉ ወስጥ ካሉት ዋና ነጥቦች ውስጥ የተወሰኑትን በአጭሩ አሳያለሁ።
በሪፖርቱ መሠረት በአሁኑ ጊዜ በአህጉሩ ያለዉ የግብርና ዲጂታላዬዜሽን የሚከተለዉን ይመስላል።
- በዛ የሚሉ የግብርና ዲጂታላዬዜሽን ሥራዎች ያሉት በምሥራቅ አፍሪካ ሲሆን በተለይም ኬኒያ ከፍተኛ ድርሻዉን ትይዛላች።
- የግብርና ዲጂታላዬዜሽን በመጠቀም የሰብል ምርታማነት ሊያድግ ችሏል።
- በአጠቃቀም በኩል ቴክኖሎጂዉን ከተጠቀሙት ዉስጥ 70% ቱ ወጣቶች ናቸዉ።
- የግብርና ዲጂታላዬዜሽን የአየር ንብረት ለዉጥን ለመቋቋም አስተአጽኦ አድርጓል።
- ምንም እንኳ ከ40 እስከ 50% የሚጠጉ ገበሬዎች ሴቶች ቢሆኑም የግብርና ዲጂታላዬዜሽን ለመጠቀም የተመዘገቡት ግን 25% ብቻ ናቸዉ።
ከዚህ በተጨማሪ ሪፖርቱ የግብርና ዲጂታላዬዜሽንን በአፍሪካ ውስጥ ለማስፋፋት ያለዉን ተስፋና እክሎች ያሳያል። ይህንን የግብርና ዲጂታላዬዜሽን በአፍሪካ ለማስፋፋት ይረዳሉ ተብለዉ የተገመቱትን የመፍትሔ ሃሳቦችንም አቅርቧል። ከነዚህ ዉስጥ ዋናዎቹ የሰው ሥልጠና ደረጃን ማሳደግ፣ ለተከታታይነቱ የሚረዳ የቢዝነስ ሞዴል መሥራት፣ የሴቶችን ሚና መጨመር፣ ጥራት ያለዉ መረጃ ማደራጀትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መሥራት ይገኙበታል።
አዳዲስ ቴክሎሎጂዎች በተመለከተ በአፍሪካ በሥራ ላይ ከዋሉት ውስጥና በሪፖርቱ ከተገለጹት የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል።
- The internet of things (IoT) የሚባለዉ ግዙፍ የሆኑ መረጃዎችን በስማርት ስልክ፣ ድሮንና ሳተላይት በመጠቀም የሚሰበሰብና የሚያጠናቅር ሲሆን በኬኒያ፣ ናይጄሪያ፣ ሩዋንዳ እና በተወሰነ ደረጃም በሴኔጋል በጥቅም ላይ ዉሏል
- Big data፤ ግዙፍ ዳታ ወይም መረጃ የሚያጠናቅርና በተግራዊነትም ላይ የሚያተኩር ነው።
- Machine learning›፤ አርቲፊሻል ኢንተሊጄንስ በመጠቀም የሚሠራና ሲስተሙ ራሱን አስተምሮና አሻሽሎ እንዲቀርብ የሚያስችለዉ ሲሆን በኬኒያና በኡጋንዳ ሥራ ላይ ዉሏል።
- BLOCKCHAIN፤ በብዙ መስኮች ለገበሬዎች ጥቅም የሚሰጥ ሲሆን በማላዊና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጥቅም ላይ ዉሏል።
በዓለም በቴክኖሎጂ የታወቁ ድርጅቶችም የግብርና ዲጂታላዬዜሽን የፈጠራ ሥራ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ሪፖርቱ ያሳያል። በሪፖርቱ ትንበያ መሠረት በአፍሪካ የግብርና ዲጂታላዬዜሽን ተጠቃሚዎች ቁጥር አሁን ካለው 26 ሚሊዮን በሶስት ዓመታት ዉስጥ ማለትም እ.ኤ.አ. በ2022 ወደ 80 ሚሊዮን እንደሚያድግና በ2030 ወደ 200 ሚሊዮን ከፍ እንደሚል ትንበያ ይሰጣል።
ሪፖርቱ ከዚህ በተጨማሪ ስድስት የአፍሪካ ሀገሮች በግብርና ዲጂታላዬዜሽን ያሉበትን ሁኔታ በአባሪነት አቅርቧል። እነርሱም ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ሴኒጋል፣ ኬኒያና ሩዋንዳና ሲሆኑ የሳህል አካባቢ ሀገሮች ስብስብ የሆኑትም ኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ቻድ እና ሞሪታኒያ ተካተዋል። ኢትዮጵያን በተመለከተ በሪፖርቱ የተለያየ ክፍል ከተገለጸዉ በተጨማሪ ከገጽ 175 እስከ 177 በኢትዮጵያ ከግብርና ዲጂታላዬዜሽን ጋር የተገናኘ የሚከተለውን መረጃ ይሰጣል። በግብርናዉ መስክ ዲጂታላዬዜሽን እንዲተዋወቅ እየተደረገ ሲሆን ይህም እ.ኤ.አ. በ2010 በተቋቋመዉ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ ሲሆን ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በጋራ ይሠራል። በዚሁ መሠረት ለገበሬዉ የምክር አገልግሎት የሚሰጥ 80-28 የኤስ ኤም ኤስ መስመር በመክፈት እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። ይህ Ethiopia 80-28 hotline የሚባለዉ የምክር አገልግሉት አራት ሚሊዮን የተመዘገቡ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን ከአፍሪካ ትልቁ ነዉ። የተደራሽነት አድማሱንም ለማስፋት በግብርና ኢክስቴንሽን ሠራተኞች፣ በመምህራን እና በጤና ሠራተኞች በኩል ይሠራል።
በአጠቃላይ የግብርና ዲጂታላዬዜሽን ለገበሬዉ ብቻ ሳይሆን በምርምሩም፣ በንግዱም እንዲሁም በሌሎች ሴክተሮች ለሚገኘዉ ህብረተሰብ አስፈላጊ ነዉ። ከላይ እንደተጠቀሰዉ በኢትዮጵያ ለገበሬዎች የምክር አገልግሎት የሚሰጥ የኤስ ኤም ኤስ አገልግሎት በሥራ ላይ እንደዋለ ያሳያል። ዋናዉ ጥያቄ በኢትዮጵያ አገልግሎቱን ለመጠቀም የተመዘገቡ አራት ሚሊዮን ተጠቃሚዎች (ገበሬዎች) ሁሉ በአግባቡ አገልግሎቱን ያገኛሉን? የሚያገኙትስ አገልግሎትስ ምን ዓይነት መረጃዎች በዉስጡ ያካትታል? የመረጃዉ ጥራትና አስታማማኝነትስ ምን ያህል ነዉ? ከምክር አግልግሎት በተጨማሪ በኬኒያና ሌሎች ሀገራት ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችስ መቼ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ?
በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 23፤ 2011 ዓ.ም. (June 30, 2019)