ግብርናችንን ለማዘመን፤ የማሽላዉ አባት
በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤
ውድ አንባቢያን
የማሽላዉ አባት በሚል ርዕስ ሥር የዶ/ር ብርሃኔ ገብረኪዳንን አመርቂ የምርምር ውጤትና ተሞክሮ በአራት ብሎጎች ጽፌ ነበር፡፡ ዶ/ር ብርሃኔ በማሽላና ሌሎች ሰብሎች ምርምር ብቻ ሳይወሰኑ በዓለም አቀፍ ተቋማት በኃላፊነት ጭምር አገልግለዋል፡፡ክሁሉም የሚያስደንቀዉ ላለፉት 62 ዓመታት ካደረጉት የጎላ ተሳትፎ በተጨማሪ እስካሁንም ድረስ የሀገራችንን ግብርና በተመለከተ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ መሆናቸዉ ነዉ፡፡ ለማስረጃም ያህል የዚህ ብሎግ ጸሐፊ ከዚህ ቀደም እ አ አ በ2014 እና 2019 ባዘጋጃቸዉ ሁለት ሲምፖዚየሞች ላይ የፓናል ውይይት በመምራትና የመክፈቻ ንግግር በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በተጨማሪም ከአንድ ሳምንት በኋላ ጥር 8 ቀን 2018 (እ አ አ ጃንዋሪ 16፣ 2026) በሚካሄደዉ 3ኛዉ ሲምፖዚየም ላይም ለመሳተፍ ቃል ገብተዋል፡፡ እኔም በተሳታፊዎች ስም ከፍተኛ ምስጋናዬን ላቀርብላቸዉ እወዳለሁ፡፡

ምስሉ የሚያሳየዉ እ አ አ ፌብሪዋሪ 25፣ 2016 በግብርና ምርምር ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደዉ ኢግዝቢሽን ላይ የዚህ ብሎግ ጸሐፊ ከአንጋፋ ተመራማሪዎች ጋር የተነሳዉ ፎቶ ሲሆን ዶ/ር ብርሃኔ ከግራ ወደ ቀኝ 6ኛው ናቸዉ፡፡ ታዋቂዉ የስንዴ ተመራማሪ ዶ/ር ተስፋዬ ተሰማ 3ኛዉ ሲሆኑ የዚህ ብሎግ ጸሐፊ 4ኛዉ ነዉ፡፡
ለአንባቢያን እንዲያመች ከዚህ በፊት ዶ/ር ብርሃኔን በተመለከተ የጻፍኳቸዉን አራት ብሎጎች አንድ ላይ በማጠናቀር ከዚህ በታች አቅርቤአለሁ፡፡
መልካም ንባብ ይሁንላችሁ፡፡
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ታህሳስ 30፣ 2018 ዓ.ም. (January 8, 2026)
የማሽላዉ አባት፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን
ክፍል 1
የዛሬዉ ጽሑፌ በግብርናዉ መስክ ላለፉት 55 ዓመታት በሀገር አቀፍም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉትና በአሁኑ ጊዜም በማድረግ ላይ ለሚገኙት አንጋፋ የግብርና ባለሙያ ላይ ያተኩራል። እኝህ ባለሙያም ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን ይባላሉ። ዶክተር ብርሃኔ ያልተሳተፉበት የሥራ መስክ አለ ማለት አይቻልም። ለረጅም ጊዜ በዩኒቨርስቲ የእርሻ ባለሙያዎችን አሰልጥነዋል፣ በተመራማሪነት በተለያዩ ሰብሎች ላይ ሠርተዋል፣ እንዲሁም በሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለበርካታ ዓመታት በኃላፊነት ሠርተዋል።
የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸዉን በእርሻ ለመማር አንጋፋዉን የአለማያ እርሻ ኮሌጅ (የአሁኑ የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ) ከተቀላቀሉበት 1957 ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የድርሻቸዉን እያበረከቱ ይገኛሉ። እኔ ራሴ በቅርቡ ባዘጋቸዋቸዉና በርካታ የግብርና ምርምርና ልማት ባለሙያዎች በተሳተፉበት ሁለት መድረኮች ልምዳቸዉን እንዲያካፍሉ ላደረኩላቸዉ ጥሪ በደስታ ነበር የተቀበሉት።

ማስገንዘቢያ፣ ካልተገለጸ በስተቀር በጽሁፉ ውስጥ የተጠቀሱት ቀናት ሁሉ እንደ አዉሮፓውያን አቆጣጠር ነዉ።
ስለ ዶክተር ብርሃኔ የሚተርከዉ የዛሬዉ ጽሑፌን በቃለ መጠይቅ መልክ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
ጥያቄ፤ በቅድሚያ ትምህርትዎን የት ተማሩ?
ዶክተር ብርሃኔ፤ የመጀመሪያ ዲግሬዬን በዕጽዋት ሳይንስ በከፍተኛ ማዕረግ ያገኘሁት በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር በሚገኘዉ የአለማያ እርሻ ኮሌጅ (የአሁኑ ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ) በ1961 ሲሆን የማስትሬት ዲግሪዬን በአግርኖሚ በአሜሪካ ሀገር ከሚገኘዉ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኔብራስካ በ1964 ነዉ። የዶክትሬት ዲግሪዬን ደግሞ እዚያዉ አሜሪካ ከሚገኘዉ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሚኔሶታ በ1969 ነዉ። ሰለዚህ ሶስተኛ ዲግሬዬን ካገኘሁ ዘንድሮ 50 ዓመት ሞላዉ ማለት ነዉ። ጊዜዉ ይሮጣል ልበል።
ጥያቄ፤ የዩኒቨርስቲ መምህር ሆነው የትና መቼ አገለገሉ? ያስተምሩ የነበረዉስ የትኛዉን ኮርስ ነበር?
ዶክተር ብርሃኔ፤ የቀድሞ የአለማያ እርሻ ኮሌጅ (የአሁኑ ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ) ባልደራባ ሆኜ በመምህርነት ያገለገልኩት ከ1964 እስከ 1982 ባሉት ዓመታት ሲሆን በመሃከሉ ለዶክትሬት ትምህርቴ ወደ ዉጭ ከሄድኩበት ሶስት ዓመታት በስተቀር ለ15 ዓመታት በኮሌጁ አስተምሬአለሁ። አስተምራቸዉ የነበሩት ኮርሶች በርካታ የነበሩ ሲሆን እነርሱም ፕላንት ቢሪዲንግ፣ ጄኔቲክስ፣ ባዮሜትሪ፣ ክሮፒንግ ሲስቴም የሚባሉትን ያካትታል።
ጥያቄ፤ እኔ እንደማዉቀዉ አንድ መምህር አንድ ወይም ሁለት ኮርስ ብቻ ነዉ የሚያስተምረዉ። እርስዎ እንዴት እነዚህ የተለያዩ ኮርሶችን ሊያስተምሩ ቻሉ? እውቀቱ ቢኖርዎትም ከፍተኛ የዝግጅት ጊዜ መውሰዱ አይቀርም ብዬ ነዉ የምጠይቅዎት?
ዶክተር ብርሃኔ፤ በርግጥ ኮርሶቹን አስተምር የነበረዉ በተለያዩ የትምህርት ወቅቶች ነዉ። ነገር ግን አንድ ኮርስ እንኳ ለማስተማር ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልግ ነበር። ምክንያቱም ተማሪዎቹ በትምህርታቸዉ ጠንካራ ስለነበሩ የሚጠይቁንን ጥያቄዎች መመለስ እንድንችል በቂ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልገን ነበር። ከማስተማር ሥራዬ በተጨማሪ ምርምርና የዲፓርትመንት አስተዳደር እሠራ ነበር።
ጥያቄ፤ ምርምርን በተመለከተ በሀገር ዉስጥ በምን መስክ ተሳትፈዋል?
ዶክተር ብርሃኔ፤ በአለማያ ኮሌጅ ተቀጥሬ የመጀመሪያ የምርምር ሥራዬን የጀመርኩት በ1964 ሲሆን የሥራ ድርሻዬም የገብስ አዳቃይ ነበር። በገብስ ምርምር ለሁለት ዓመታት ብቻ ነዉ የቆየሁት። ምክንያቱም ለዶክትሬት ትምህርቴ ወደ አሜሪካን ሀገር መሄድ ስለነበረብኝ። ለዶክትሬት የሚያበቃኝን ምርምር በገብስ ማሻሻል ነዉ የሠራሁት። አለማያ እንደተመለስኩ የምርምር አቅጣጫዬም ወደ በቆሎ አዳቃይነት ተቀየረ። ብዙም ሳይቆይ ከሁለት ዓመታት በኋላ ምርምሬን ከበቆሎ ወደ ማሽላ በመቀየር በሰፊዉ ወደ ምታወቅበት የማሽላ ምርምር ውስጥ ገባሁ። የማሽላ አዳቃይ በመሆንም ከ1973 እስከ 1982 ድረስ ለ10 ዓመታት በአለማያ ኮሌጅና በአዳማ መልካሳ በሚገኙ ጣቢያዎች አገልግያለሁ።
ጥያቄ፤ ወደ ውጭ ሀገር ከመሄድዎ በፊት በሀገር ውስጥ በኃላፊነት የሠሩባቸዉ ጊዜያት ካሉ ቢገልጹልኝ?
ዶክተር ብርሃኔ፤ በሥራ ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ በኃላፊነት የሠራሁት የሀረማያ እርሻ ኮሌጅ የዕጽዋት ሣይንስ ዲፓርትመንት ኃላፊ ሆኜ ነዉ። በዚህ ኃላፊነቴም ከ1969 እስከ 1975 ለስድስት ዓመታት ቆይቻለሁ። በተጨማሪም ከ1973 እስከ 1982 ባሉት 10 ዓመታት የብሔራዊ ማሽላ ምርምር አስተባባሪ በመሆን አገልግያለሁ።
ጥያቄ፤ ለበርካታ ዓመታት ከኢትዮጵያ ዉጭ በነበሩበት ወቅት የሠሩባቸዉ የኃላፊነት ቦታዎች የትኞቹ ናቸዉ?
ዶክተር ብርሃኔ፤ ከ1982 እስከ 2002 ባሉት 21 ዓመታት በተለያዩ ሀገራት እና የኃላፊነት ደረጃዎች ሠርቻለሁ። እነዚህም ይህንን ይመስላሉ።
- 1982 እስከ 1986፤ በአፍሪካ ህብረትና ኢክሪሳት የሚባል አለም አቀፍ ድርጅት የተቋቋመ የማሽላ ምርምር ፕሮግራም ውስጥ የምሥራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ አስተባባሪ
- ከ1986 እስከ 1987፤ ዋና መሥሪያ ቤቱ ሜክሲኮ ሀገር የሚገኘዉ ሲሚት የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት በዋና መሥሪያ ቤቱ የበቆሎ ተመራማሪ
- ከ1987 እስከ 1991፤ በናይሮቢ ኬኒያ የሲሚት የምሥራቃዊ አፍሪካ የበቆሎ ተመራማሪና የቡድን መሪ
- ከ1991 እስከ 1993፤ በሀራሬ ዚምባብዌ የሲሚት የደቡባዊ አፍሪካ የበቆሎ ተመራማሪና የቡድን መሪ
- ከ1993 እስከ 1994፤ በአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኔብራስካ ኢንትሶርሚል የሚባል የዓለም አቀፍ የማሽላና ቡልቱክ ፕሮግራም ተባባሪ ዳይሬክቴር
- ከ1994 እስከ 2002፤ በአሜሪካ የሚገኘዉ የቪርጂኒያ ቴክ ዩኒቨርሲቲ የተቀናጀ የተባይ አጠባበቅ ፕሮግራም ዳይሬክቴር
ጥያቄ፤ ይህ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ የዘለቀዉን በተለያዩ ሀገራት ያደረጉትን አገልግሎት ካጠናቀቁ በኋላ ወዴት ሄዱ?
ዶክተር ብርሃኔ፤ በ2002 ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩ። አማረዉ የሚባል በአሜሪካን መንግሥት የሚደገፍ ፕሮጀከት ኃላፊ በመሆን ሠርቻለሁ። ይህ ሁለገብ የሆነ ፕሮጀክት ትኩረት አድርጎ ይሠራ የነበረዉ በአማራ ክልል በማክሮ ፋይናንስ፣ ግብርና ምርምርና ስርጸት እንዲሁም የዉሃ ተፋሰሶች ጥበቃ ላይ ነበር። የፕሮጀክቱን መምራትና ማስተባበር ሥራ እሠራ የነበረው ከባህር ዳር ከተማ ሆኜ ነበር። በዚህ ፕሮጀከት በኃላፊነት እስከ 2008 የቆየሁ ሲሆን ይህም ለሰባት ዓመታት መሆኑ ነዉ።
ጥያቄ፤ የአማረዉ ፕሮክጀት ከተጠናቀቀ 11 ዓመታት ሆነዉ። እርስዎ ግን እስካሁንም በቃኝ አላሉም። በአሁኑ ጊዜ በምን ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ?
ዶክተር ብርሃኔ፤ አቅሜ በፈቀደዉ መጠን በሙያዬ እያገለገልኩ እገኛለሁ። በአሁኑ ወቅት የቨርጂኒያ ቴክ የተቀናጀ የተባይ አጠባበቅ ፕሮግራም የአፍሪካ ክፍል አማካሪ ነኝ።የኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚም ምክትል ፕሬዘዳንት ሆኜ ሳገለግል ቆይቼ አሁን ለተረኛ አስረክቤ ወጥቼአለሁ። ከዚህ በተጨማሪ በርካታ ድርጅቶችን በቦርድ አባልነት ወይም ፈቃደኝነት እያገለገልኩ እገኛለሁ።
በዶክተር ብርሃኔ ላይ የሚያተኩረዉ ጽሑፌ በዚህ አያበቃም። በሚቀጥለዉ ጽሑፌ በሰፊዉ ስለሚታወቁበት የማሽላ ምርምር እንዲሁም ለኢትዮጵያ ግብርና ያላቸዉን ራዕይና መልእክት አስነብባችኋለሁ።
እስከዚያዉ መልካሙን እመኝላችኋለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መስከረም 25፣ 2012 ዓ.ም. (October 6, 2019)
የማሽላዉ አባት፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን
ክፍል 2
በክፍል አንድ ጽሑፌ በግብርናዉ መስክ ላለፉት 55 ዓመታት በሀገር አቀፍም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉትና በማድረግም ላይ ስለሚገኙት ስለ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን አጠቃላይ የሥራ ልምዳቸዉና በሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ደረጃ በኃላፊነት ስላሳለፉበት ሁኔታ አስነብቤ ነበር። በዛሬዉ ጽሑፌ ደግሞ እኚሁ አንጋፋ የግብርና ምሁር በተለይ ስለሚታወቁበት የማሽላ ምርምር ላይ አተኩራለሁ። በክፍል አንድ እንደቀረበዉ ሁሉ የዛሬዉ ጽሑፌም ከምሁሩ ጋር በተደረገዉ ቃለ መጠይቅ መልክ ይቀርባል።
ማስገንዘቢያ፣ ካልተገለጸ በስተቀር በጽሑፉ ውስጥ የተጠቀሱት ቀናት ሁሉ እንደ አዉሮፓውያን አቆጣጠር ነዉ።
ጥያቄ፣ በክፍል አንድ እንደገለጹልኝ የመጀመሪያ የምርምር ሥራዎን በሀረማያ ኮሌጅ የጀመሩት በገብስ ላይ ነበር። ለሶስት ዓመታት ብቻ በገብስ ምርምር ከቆዩ በኋላ ለዶክትሬት ትምህርትዎ ወደ አሜሪካን ሄዱ። ትምህርትዎን አጠናቅቀዉ ሲመለሱ የበቆሎ ተመራማሪ ሆኑ። የምርምር አቅጣጫዎን ከገብስ ወደ በቆሎ የቀየሩብት ዋናው ምክንያት ምንድነው?
ዶክተር ብርሃኔ፣ እንደአጋጣሚ ሆኖ ትምህርቴን በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሚኔሶታ በምጨርስበት የመጨረሻ ዓመት ላይ ሲግራም (Seagram) የሚባለዉ የካናዳ ዊስኪ አምራች ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ ለበቆሎ ምርምር ጠቀም ያለ መዋዕለ ንዋይ እንደሚሰጡኝ ፍንጭ ሰጥተዉኝ ነበር። በጊዜዉ ይህንን ያደረጉበት ዋናዉ ምክንያት ለዊስኪ ምርታችዉ የሚዉል በርከት ያለ በቆሎ ረዘም ላለ ጊዜ ከኢትዮጵያ ለመግዛት ፍላጎት ስለነበራቸዉ ነዉ። በዚያዉም ለኢትዮጵያ ልማት አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አስበዉ ነበር። ለዚህ ሁሉ ዓላማቸዉ የተሻሻሉ የበቆሎ ዝሪያዎች እንደሚያስፈልጉ ግልጽ ነበር። በዚሁ መሠረት ወደ አለማያ እንደተመለስኩ የተባለዉን የፋይናንስ ጥያቄ በፕሮፖዛል መልክ ለዚሁ ሲግራም ለተባለዉ ኩባንያ አስገብቼ ለበቆሎ ምርምር የሚዉል ጠቀም ያለ የገንዘብ ድጎማ አገኘሁና ወደ በቆሎ ማሻሻል ምርምር ማድላት ጀመርኩ። በዚሁ የተነሣ የገብስ ማሻሻል ሙያዬን ትኩረት እየቀነስኩ ሄድኩ ማለት ነው።
ጥያቄ፣ በበቆሎ ምርምርም የቆዩት ለሁለት ዓመታት ብቻ ነበር። በብዙዎች ዘንድ በሰፊዉ ወደ ሚታወቁበት የማሽላ ምርምር ገቡ። ለምን በበቆሎ ምርምር መቆየት አልፈለጉም?
ዶክተር ብርሃኔ፣ በበቆሎ ላይ ምርምር በምሠራበት ወቅት የማሽላ ምርምርንም ደርቤ እሠራ ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት በወቅቱ በዕጽዋት ሣይንስ ዲፓርትመንት ሌላ የማሽላ ምርምርን በኃላፊነት የሚሠራ የሰለጠነ የሰዉ ኃይል ስላልነበረ ነዉ። ሌላዉ ደግሞ በወቅቱ በማሽላ ምርምር እንደ ሊቅ ከሚቆጠሩት ዶክተር ሂዮ ዶጌት ከተባሉ ምሁር ጋር የቅርብ የምርምር ግንኙነት ፈጥሬ ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ዶክተር ዶጌት አይ ዲ አር ሲ (IDRC International Development Research Center) ከተባለ የካናዳ ግብረ ሠናይ ድርጅት የኢትዮጵያ የማሽላ ምርምር በአፍሪካ ግንባር ቀደም እንዲሆን የሚያስችል ሰፋ ያለ የምርምርና የሰው ኃይል ማሰልጠኛ እንዳቋቁም የሚረዳኝ የገንዝብ ድጋፍ እንዳገኝ አመቻቹልኝ። አለማያ አካባቢ ማሽላ ቀዳሚ ሰብል በመሆኑና አዲስ ከIDRC ባገኘሁት ጠቀም ያለ የገንዘብ ድጋፍ ትኩረቴን ወደ ማሽላ አዞርኩ። በዚሁ መሠረት የበቆሎዉን ምርምር ከሥልጠና በቅርቡ ለተመለሰዉ ለዶክተር ደጀኔ መኮንን አስተላለፍኩ። እኔም ከማሽላ ጋር የጠበቀ ግንኙነቴን ጀመርኩ ማለት ነዉ።
ጥያቄ፣ ከ1973 እስከ 1982 ድረስ ባሉት አሥር ዓመታት የማሽላ አዳቃይና የብሔራዊ ማሽላ ምርምር አስተባባሪ ነበሩ። የሥራ ምድብዎ ደግሞ ሀረማያና አዳማ ነበሩ። እነዚህ ሁለት ጣቢያዎች የተራራቁ ብቻ ሳይሆኑ በሁለት ድርጅቶች (እርሻ ኮሌጅና እርሻ ምርምር) ሥር የሚተዳደሩ ነበሩ። በነዚህ ሁለት ጣቢያዎች እንዴት ባንድ ጊዜ ይሠሩ ነበር?
ዶክተር ብርሃኔ፣ ከላይ እንደገለጽኩት የማሽላ ምርምር የጀመርኩት አለማያ ነዉ። ይህም ሆኖ ምርምሬ የሚያተኩረዉ በመላ ኢትዮጵያ ነበር። ከካናዳዉ የእርዳታ ድርጅትም ያደረግነዉ ስምምነትም ይህንኑ መሠረት ያደረገ ነበር። ስለዚህ የተለያየ ስነምህዳር ያላቸዉን የማሽላ አብቃይ የኢትዮጵያ አካባቢዎችን የሚወክሉ የማሽላ ምርምር ጣቢያዎች መምረጥ ነበረብን። እነዚህ ስነምህዳሮችም ወይና ደጋ፣ ዝናም አጠር ቆላ፣ ዝናም ጠገብ ቆላ የመሣሰሉት ናቸዉ። ይህንን ሥራ በቅድሚያ እናካሄድ የነበረዉ ወደ ምሥራቅ ባጋደለው አለማያ ነበር። መሃል ኢትዮጵያ ሆኖ ለአገር አቀፍ ማሽላ ምርምር ማስተባበሪያ የሚሆን ቦታ ሳፈላልግ አዳማ አካባቢ ያለዉን የመልካሳ ምርምር ጣቢያ ተስማሚ ሆኖ አገኘሁት። በዚህም ምክንያት ከእርዳታ ድርጅቱ ያገኘሁትን ድጋፍ ሁሉ፣ ቁሳቁስ፣ የሰዉ ኃይልና ገንዘብ ይዤ ወደ አዳማ መልካሳ ገባሁ። ከዚህም ሥፍራ ሆኜ የሀገር አቀፉን የማሽላ ምርምር መሥራትና ማስተባበር ጀመርኩ። ይህን ሁሉ ስናደርግ በጊዜዉ የእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ምንም የማሽላ ምርምር ሥራ አልነበረዉም። ሙሉዉን ኃላፊነት ለኛ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር ለነበረዉ ለአለማያ እርሻ ኮሌጅ ነበር የሰጡን።
ጥያቄ፣ በክፍል አንድ በነገሩኝ መረጃ ተመርኩዤ ሳሰላዉ በሀገር ዉስጥ እና በውጭ ሀገራት በማሽላ ላይ በአጠቃላይ ለ18 ዓመታት በበቆሎ ላይ ደግሞ በአጠቃላይ ለ10 ዓመታት በምርምር ሥራ ተሣትፈዋል። ከበቆሎና ከማሽላ በዬትኛዉ ሰብል ላይ ምርምር መሥራት ይቀላል? ለምን?
ዶክተር ብርሃኔ፣ በቆሎና ማሽላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም የዲቃላ ዝሪያዎች ከመጠቀማቸዉ አንጻር ሲታይ ተመሣሣይ ጸባይ አላቸዉ። የበቆሎ ዲቃላ ዝሪያዎች የማዉጣትና የመጠቀም ሥራ በአለም አቀፍ ደረጃ በጣም የዳበረ ነዉ። የማሽላም ሥራ በተከታይነት ይታወቃል። እነዚህ አለም አቀፍ ልምዶች በሀገር ዉስጥ ለሚሠሩ ሥራዎች በጣም ጠቃሚ መሠረቶች ናቸዉ። በኢትዮጵያ ደረጃ ማሽላ ሀገር በቀል ሰብል ከመሆኑ አንጻርና በጣም የተለያዩ ዓይነቶች ስላሉን ይህንን መሠረት አድርጎ ብዙ ጠቃሚ ሥራዎች መሥራት ይቻላል። የዓለም አቀፍ የማሽላ ምርምር ህብረተሰብ ከኢትዮጵያ የማሽላ ምርምር ተጠቅሟል፣ እኛም ከነሱ ተጠቅመናል። ለምሳሌ ICRISAT የሚባለዉ ዓለም አቀፍ ማዕከል ሲመሠረት በዋነኝነት የተጠቀመዉ የኢትዮጵያ ማሽላ ዝሪያዎች ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ታዋቂዉን E-35 የተባለዉን መጥቀስ ይቻላል። እኛም ብዙ ዝሪያዎች በተለይም ለዲቃላ ማሽላ መሥሪያ የሚያገለግሉ ዓይነቶችን ከዓለም ማህበረሰብ ወስደናል። ከICRISAT ከመጡ ዝሪያዎች እንደ ኮቦማሽ፣ ብርማሽ፣ 76T1-23 የተባሉት ለሀገራችን ገበሬዎች የተለቀቁ ናቸዉ። ስለዚህ የበቆሎና የማሽላ ምርምር ሥራዎች ተደጋጋፊና ተመሣሣይ ናቸዉ። ዲቃላ ያልሆኑ ዝሪያዎች በማዉጣትና ለተጠቃሚዉ በማድረስ የማሽላዉ ምርምር ሊቀል ይችላል። ያለዉ ልምድና ሁኔታ ይሄዉ ነዉ።

ከላይ በምሥሉ የሚታዩት ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡ የማሽላ አናቶች ናቸዉ። ፎቶ፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን
ጥያቄ፤ የኢትዮጵያ የማሽላ ማሻሻያን በብሔራዊ ደረጃ በሚያስተባብሩበት ወቅት የምርምር ፕሮግራሙ እንዴት ነበር የተቀናጀዉ?
ዶክተር ብርሃኔ፤ በማሽላ ላይ እናደርግ የነበረዉ ምርምር የአገሪቱን ስነ ምህዳር ወይም አግሮ ኢኮሎጂ በመመርኮዝ በሶስት ክፍሎች በመክፈል ነበር። እነርሱም፣ 1ኛ) ዝናም አጠር ዝቅተኛ ሥፍራዎች፤ እነዚህ ሥፍራዎችን በመወከል በማሽላ ላይ በዋናነት ምርምር እናካሄድ የነበረዉ በመልካሳ፣ ቆቦ፣ አላማጣ፣ ሁመራና ሚኤሶ ነበር። 2ኛ) መካከለኛ ሥፍራዎች፤ እነዚህ ሥፍራዎችን በመወከል በዋናነት ምርምር እናካሄድ የነበረዉ በባኮና ጂማ ነበር። 3ኛ) ከፍተኛ ሥፍራዎች፤እነዚህ ሥፍራዎችን በመወከል በዋናነት ምርምር እናካሄድ የነበረዉ በአለማያና አርሲ ነጌሌ ነበር። ይህንን ሥራ ለማጠናከርና ለመደገፍ በተለይም ከሰብል ማምረቻ ወቅት ዉጭ በበጋዉ ወራት የማዳቀል ሥራና የዘር ብዜት ለማከናወን በመስኖ የመልካ ወረር ምርምር ጣቢያ (የአሁኑን ወረር ምርምር ማዕከል) እንጠቀም ነበር።
ጥያቄ፤ ከዚህ የተቀናጀ የምርምር ፕሮግራም ለገበሬዎች የደረሱ ምርጥ የማሽላ ዝሪያዎች ነበሩን?
ዶክተር ብርሃኔ፤ አዎ፣ በርካታ ምርጥ ዝሪያዎች እንዲለቀቁ አድርገናል። ከነዚህ ውስጥ አለማያ 70፣ ኢ ቲ ኤስ 2752፣ ጋምቤላ 1107፣ ዴዴሳ 1057፣ መልካማሽ 79፣ ባኮማሽ እና ብርማሽ የተባሉት ሊጠቀሱ ይቻላል። በወቅቱ ከተለቀቁት ዝሪያዎች መካካል በአጭር ጊዜ የሚያፈራዉና ድርቅን መቋቋም የሚችለዉ 76T1-23 የሚባለዉ ዝሪያ እስከ ዛሬ ድረስም በምርት ላይ ይገኛል።

ምሥሉ የሚያሳየዉ በቆቦ አካባቢ ያለዉን የዲቃላ ማሽላ ምርምርን ነዉ። ፎቶ፤ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን
ጥያቄ፤ በኢትዮዮጵያ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚበቅሉ የማሽላ ዓይነቶችን በተገቢዉ መንገድ በማሰባሰብም ይታወቃሉ። ምን ያህል አገር በቀል የማሽላ ዓይነቶችን ሊያሰባስቡ ችለዋል?
ዶክተር ብርሃኔ፤ በሀገሪቱ በተለያዩ ማሽላ አብቃይ ሥፍራዎች በመዘዋወር ከ5000 በላይ የሆኑ የማሽላ ዓይነቶችን በማሰባሰብ ለጥናት እንዲበቁ አድርገናል። ዘሮቹ ሳይበላሹ ለረዥም ጊዜ ተጠብቀዉ እንዲቆዩም በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲቱዩት እንዲቀመጡ አድርገናል።
ጥያቄ፤ ኢኮኖሚክ ቦታኒ በሚባለዉ የጆርናል መጽሔት በ1973 ባሳተሙት ጽሑፍዎ ውስጥ በአለማያ ኮሌጅ ከተለቀቁት ዝሪያዎች መካከል በቁመቱ አጠር ያለ ነገር ግን ከፍ ያለ ምርት ይሰጥ የነበረዉ ቁልቢ ድዋርፍ የተባለዉ ዝሪያ በገበሬዉ ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኝ እንዳልቻለ ነዉ። የአካባቢዉ ገበሬዎች ይህንን ምርጥ ዝሪያ ለምን ሊቀበሉ አልቻሉም።
ዶክተር ብርሃኔ፤ በአካባቢዉ ገበሬዉ ማሽላን ለተለያዩ ነገሮች ይጠቀማል። ፍሬዉን ለራሱ ይመገባል፣ ቅጠሉን ለከብቶቹ ይመግባል፣ ግንዱን ደግሞ ለማገዶነት ይጠቀማል። ምንም እንኳ ምርታቸዉ ደህና ቢሆንም በቁመት አጭሮቹ ዝሪያዎች አነስ ያለ ግንድና ቅጠል ስለሚኖራቸዉ በገበሬዎች ዘንድ አይወደዱም ነበር።
ጥያቄ፣ እስካሁን ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከኢትዮጵያ በኩል የተደረግልዎት ዕዉቅና ካለ ቢነግሩኝ፤
ዶክተር ብርሃኔ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተመሠረተበትን ሀምሳኛ ዓመት በዓሉን ሲያከብር ለሀገሪቱ ግብርና ምርምር የላቀ አስተዋጽኦ እንዳበረከትኩ የሚገልጽ የምስክር ወረቀት ሰጥቶኛል። የኢትዮጵያ የሰብል ማሻሻያ ጉባኤ በ1978 የቀዳሚ ተመራማሪነት ዕዉቅና ስጥቶኛል። እንዲሁም የመልካሳ ምርምር ማዕከል ለማሽላ ምርምር ላበረከትኩት አስተዋጽኦ ባሁኑ ዓመት ሠርቲፊኬት ሰጥቶኛል።
ጥያቄ፣ ለኢትዮጵያ ግብርና ያልዎት ራዕይ ምን ይመስላል?
ዶክተር ብርሃኔ፣ ምርምርን በተመለከተ እያንዳንዱ ሰብል ሀገር አቀፍ በሆነ መንገድ የፖለቲካ ክልሎችን ሳይከተል ሁሉንም ሥነ ምህዳሮችን ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ ሥራ ላይ እንዲዉል ምኞቴ ነዉ። በተጨማሪም በብዛት በሀገር ዉስጥ የተቋቋሙ ዩኒቨርስቲዎች በአካባቢያቸዉ ያለዉን ምርምርና የቴክኖሎጂ ስርጸት ከማስተማር ሥራቸዉ ጋር አቀናጅተዉ እንዲሠሩ ምኞቴ ነዉ። ሌላዉ ምኞቴ የኢትዮጵያ ግብርናን ከማዘመን አንጻር የዩኒቨርስቲና ቴክኒካል ኮሌጅ ተመራቂዎች የራሳቸዉን እርሻ እንዲያቋቋሙና እንዲመሩ መንግሥት የሚያስፈልጋቸዉን ድጋፍ ሁሉ እንዲያደርግላቸዉ ነዉ።
ጥያቄ፣ ይህ ራዕይዎ እንዲሳካ ይረዳል ብለዉ የሚገምቱት መልእክት ካለ።
ዶክተር ብርሃኔ፣ ከላይ ያነሳኋቸዉ ምኞቶቼ እንዲሳኩ ዋናዉ የመንግሥት ፖሊሲና አመራር ነዉ። የሚመለከታቸዉ በአመራር ላይ ያሉ ኃላፊዎች አስፈላጊ እርምጃዎች ይወስዳሉ የሚል ተስፋ አለኝ።
በዶክተር ብርሃኔ ላይ የሚያተኩረዉ ጽሑፌ በዚህ አያበቃም። በክፍል 3 ስለ ዕድገታቸዉ፣ ተማሪዎቻቸዉና የማሽላ ዝሪያዎች የሚነግሩኝን አካፍላችኋለሁ። እስከዚያዉ መልካሙን እመኛለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መስከረም 28፣ 2012 ዓ.ም. (October 9, 2019)
የማሽላዉ አባት፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን
ክፍል 3
በክፍል አንድና ሁለት ጽሑፌ በግብርናዉ መስክ ላለፉት 55 ዓመታት በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉትና በማድረግም ላይ ስለሚገኙት ስለ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን አጠቃላይ የሥራ ልምዳቸዉና በሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ደረጃ በኃላፊነት ስላሳለፉበት ጊዜ ስለነበረዉ ሁኔታ ያደረኩላቸዉን ቃለ መጠይቅ አቅርቤ ነበር። በተጨማሪም በኢትዮጵያ የማሽላ ምርምር ላይ ስላደረጉት አስተዋጽኦ የሚያወሳ ጽሑፍም አስነብቤ ነበር። በዛሬዉ ጽሑፌ ደግሞ ስለ ዕድገታቸዉ፣ የሥራ ጸባያቸዉና ተማሪዎቻቸዉ የነገሩኝን አካፍላችኋለሁ።
ማስገንዘቢያ፣ ካልተገለጸ በስተቀር በጽሑፉ ውስጥ የተጠቀሱት ቀናት ሁሉ እንደ አዉሮፓውያን አቆጣጠር ነዉ።
ጥያቄ ፤ ከዚህ ቀደም በቀረቡት ሁለት ክፍሎች በርካታ ጥያቄዎች ጠይቄዎት ነበር። ነገር ግን ስለ ዕድገትዎና የልጅነት ጊዜዎ ሳልጠይቅዎት ቀረሁ። ለመሆኑ መቼና የት ተወለዱ?
ዶክተር ብርሃኔ፤ የተወለድኩት ኦግስት 12፣ 1936 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ነሐሴ 6፣ 1928) የአዲስ አበባ መሃል በነበረዉ የአራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ ነዉ። እንደሚታወቀዉ በዚያ እኔ በተወለድኩበት ወቅት የኢጣሊያ ወረራ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተስፋፋ የነበረበት ጊዜ ነበር።
ጥያቄ፤ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትዎን የት ተማሩ?
ዶክተር ብርሃኔ፤ በዚሁ የኢጣሊያ ወረራ ምክንያት መላዉ ቤተሰቤ ከአዲስ አበባ ለቆ ለመሄድ ተገደደ። ለዚሁም አመቺ ይሆናል ተብሎ የተመረጠዉ ሥፍራ ከአዲስ አበባ ራቅ ያለ ገጠራማ መንደር ነበር። ይህም መንደር የሚገኘዉ ሙህር በሚባለዉ የጉራጌ አካባቢ ነበር። ፊደል የቆጠርኩት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ልማድ መሠረት በአካባቢዉ በሚገኘዉ ታዋቂዉ የሙህር ገዳም ኢየሱስ ነበር። ከሦስት ዓመታት የገዳም ኢየሱስ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቴ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተዛዉሬ መደበኛ ትምህርቴን ጀመርኩ። በዚሁ መሠረት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ለገሀር አካባቢ በሚገኘዉ የቀድሞ በየነ መርዕድ ትምህርት ቤት ተከታትዬ አጠናቀኩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን Point-4 Program (በአሁኑ USAID) ተብሎ በሚጠራዉ በአሜሪካን መንግሥት ድጋፍ በተቋቋመዉ በወቅቱ የጅማ የእርሻ ቴክኒካል ትምህርት ቤት (Jimma Agricultural Technical School – JATS) ገብቼ ልማር ችያለዉ። በጂማ የነበረዉን ትምህርቴን እንዳጠናቀኩ አለማያ ወደሚገኘዉ በወቅቱ Imperial Ethiopian College of Agricultural and Mechanical Arts ይባል በነበረዉ የእርሻ ኮሌጅ ገብቼ የመጀመሪያ ዲግሬዬን ለማግኘት ችያለሁ።
ጥያቄ፤ እርስዎ በአለማያ እርሻ ኮሌጅ ያስተማሯቸዉ ተማሪዎች በአሁኑ ጊዜ በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ? ስለ ጥቂቶቹ ቢገልጹልኝ።
ዶክተር ብርሃኔ፤ በአለማያ ኮሌጅ ለበርካታ ዓመታት ባስተማርኩበት ወቅት የተለያዩ ኮርሶች ከኔ የወሰዱ ተማሪዎች በርካታ ናቸዉ። በርካታ ከመሆናቸዉም የተነሣ ቆጥሬ ልደርስባቸዉ አልችልም። በዚሁ ምክንያት አንዳንዶቹ ባሁኑ ጊዜ የት እንዳሉም ማወቅ ያዳግተኛል። ይህ ቃለ መጠይቅ ከማሽላ ምርምር ጋር በነበረኝ ሁኔታ ላይ ስለሚያተኩር በክፍል 2 ቃለ መጠይቄ ስለገለጽኩትና IDRC ተብሎ በሚጠራዉ የካናዳ ዕርዳታ ድርጅት በተገኘ ድጋፍ ባቋቋምኩት የኢትዮጵያ ማሽላ ማሻሻያ ፕሮግራም (ወይም ባጭሩ ESIP ተብሎ ይጠራ በነበረዉ) ውስጥ ለረዥም ጊዜ ከኔ ጋር በቅርበት ከሠሩት ጋር አተኩራለሁ። ይህንኑ የማሽላ ማሻሻያ ፕሮግራም በጀመርኩበት በ1973 ከአለማያ እርሻ ኮሌጅ በባችለር ዲግሪ በቅርብ የተመረቁ አራት ወጣቶች ተቀላቀሉኝ። እነርሱም አጥናዉ አይተንፍሱ፣ ገቢሣ እጀታ፣ ሰለሞን ኬቤታ እና ይልማ ከበደ የተባሉት ናቸዉ። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ አበበ መንክር የተባለ ሌላ የዚሁ ኮሌጅ ተመራቂ ፕሮጀክታችንን ተቀላቀለ። እነዚህ ስማቸዉ ከላይ የጠቅስኳቸዉ የሥራ ባልደረቦቼ ለተከታታይ ትምህርት ወደ ካናዳና አሜሪካ ተላኩ። ከአጥናዉ በስተቀር ሁሉም እስከ ዶክትሬት ደረጃ ሊማሩ ችለዋል። አጥናዉ ከሁለተኛ ዲግሪ በኋላ ትምህርቱን አልቀጠለበትም። ከነዚህ የቀድሞ የማሽላ ማሻሻያ ፕሮግራም ባልደረቦቼ መካከል ዶክተር ገቢሣ በዓለም የሚታወቀዉን የዓለም የምግብ ሽልማት (World Food Prize የሚባለውን) የተሸለመ ሲሆን ባሁኑ ጊዜ በአሜሪካ የፐርዱ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ነዉ። ዶክተር ይልማ ደግሞ ከላይ የተጠቀሰዉን የማሻላ ማሻሻያ ፕሮግራም አስተባባሪ በመሆን ለረዥም ዓመታት ሠርቷል። በመቀጠልም ፓዮኒር በተባለዉ ግዙፍ የዘር ማምረቻ ኩባንያ እና ቀጥሎም ቢልና ሜሊንዳ ጌትስ በሚባለዉ በዓለማችን ትልቁ ግብረ ሠናይ ድርጅት የማሽላ ከፍተኛ ኤክስፐርት በመሆን አገልግሏል። ዶክተር ሰለሞን ደግሞ በካናዳ የእርሻ ዲፓርትመንት ውስጥ የገብስና ሲናር ምርምር ኃላፊ በመሆን አገልግሏል። ዶክተር አበበ ባሁኑ ጊዜ IITA ተብሎ በሚጠራዉ ዓለም አቀፍ የምርምር ማዕከል ዉስጥ የበቆሎ ማሻሻል የፕሮግራም መሪ ነዉ።
ጥያቄ፤ በረዥም የሥራ ዘመንዎ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰፊዉ የተጓዙ ይመስለኛል። ከተጓዙበት ሥፍራ ያልተጓዙበትን መጥራት ሳይቀል አይቀርም። እስካሁን የትኛዉን የሀገሪቱን ክፍል ለማየት ዕድሉን አላገኙም?
ዶክተር ብርሃኔ፤ ማሽላ አብቃይ የሆኑ ሥፍራዎችን ሁሉ ለማየት ዕድሉ ገጥሞኛል፣ ኤርትራንም ጨምሮ።
ጥያቄ፤ እርስዎ የኢትዮጵያ የማሽላ ምርምርን በሚያስተባብሩት ወቅት የሰብሉ ምርት እንዳያድግ አንቀዉ ከያዙት ዉስጥ ዋናዎቹ የትኞቹ ነበሩ?
ዶክተር ብርሃኔ፤ የማሽላ ምርታማነት እንዳያድግ በከፍተኛ ደረጃ የሚፈታተኑት እንደ ቅደም ተከተላቸዉ ከትልቁ ወደ ትንሹ የሚከተሉት ናቸው።
- የዝናም እጥረትና ድርቅ፣
- ተባይና ወፍ በተለይም ግንድ ሠርሳሪዉ ትልና ግሪሳ የሚባለዉ የወፍ መንጋ፣
- የአረም ጥቃት ሲሆን ባንዳንድ ሥፍራዎች የአቀንጭራ ችግር፣
- ለተለያየ ሥነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ ምርጥ ዝሪያዎች አለመኖር እና
- ተስማሚ የሰብል እንክብካቤ ዘዴዎች አለመኖር ናቸዉ።

ጥያቄ፤ ገበሬዎች ለማሽላቸዉ የተለያየ ስያሜ ይሰጧቸዋል። ከነዚህ ዉስጥ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ወተት በጉንጬ፣ ወፍ አይበላሽ፣ ስንዴ ለምኔ፣ ቂጥኝ አይፈሬ፣ ጋን ሰበር እና ፈንዲሻ የተባሉት ይገኙበታል። እነዚህ ስሞች ምንን ያመለክታሉ?
ምሥሉ የሚያሳየዉ ቆቦ አካባቢ በደህና ሁኔታ አድጎ ያለ የማሽላ ማሳን ነዉ። ፎቶ፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን
ዶክተር ብርሃኔ፤ ወተት በጉንጬ የተባለዉ ዝሪያ በእሸትነቱ ተጠብሶ ሲበላ በተመጋቢዎች ዘንድ ጣፋጭ ሆኖ ተወዳጅ ከመሆኑም በተጨማሪ ከፍተኛ ላይስን እና በጠቅላላዉ ከፍተኛ የሆነ ፕሮቲን በዉስጡ የያዘ ነዉ። ወፍ አይበላሽ የተባለዉ ዝሪያ ደግሞ ፍሬዉ ጎምዛዛ ስለሆነ የወፎች ጥቃት አይደርስበትም። ስንዴ ለምኔ የሚባለዉ ዝሪያ ደግሞ ከሱ የሚጋገረዉ ዳቦ ከስንዴ ከሚጋገረዉ ጋር በጥራቱ ተቀራራቢነት ስላለዉ ነዉ። ቂጥኝ አይፈሬ የተባለ ስያሜ የተሰጠዉ ዝሪያ ደግሞ የአቀንጭራ ጥቃትን ለመቋቋም በመቻሉ ነዉ። ጋን ሰበር የተባለዉ ዝሪያ ደግሞ ኃይለኛና ጥሩ ጠላ የሚያስጠምቅ ነዉ። ፈንዲሻ የተባለዉ ዝሪያ ሲቆላ ፈንድቶ ጥሩ ካሽ ካሽ የሚል መክሰስ ይሆናል።
ከዶክተር ብርሃኔ ላይ ያደረኩት ቃለ መጠይቅ በዚህ አያበቃም። በክፍል 4 በማሽላ ላይ ስለሚደረገዉ ምርምር ተጨማሪ መረጃ የሚሰጡኝ ሲሆን ገጠመኞቻቸዉንም ያጫውቱኛል። እስከዚያዉ መልካም ጊዜ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥቅምት 2፣ 2012 ዓ.ም. (October 13, 2019)
የማሽላዉ አባት፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን
ክፍል 4
በሦስት ተከታታይ ክፍሎች በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉትና በማድረግም ላይ ስለሚገኙት የ84 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ስለሆኑት ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን ስለ ዕድገታቸዉ፣ የሥራ ልምዳቸዉ፣ የሥራ ባልደረቦቻቸዉ በተለይም በሰፊዉ ስለሚታወቁበት የማሽላ ምርምር የሚያትቱ ጽሑፎች አቅርቤ ነበር። በዛሬዉ ክፍል 4 እና የመጨረሻ ጽሑፌ ደግሞ በማሽላ ላይ ስለነበረዉና በአሁኑ ጊዜም ስላለዉ ምርምር ተጨማሪ መረጃ የሚሰጡኝ ሲሆን ገጠመኞቻቸዉንም ያጫውቱኛል።
ማስገንዘቢያ፣ ካልተገለጸ በስተቀር በጽሑፉ ውስጥ የተጠቀሱት ቀናት ሁሉ እንደ አዉሮፓውያን አቆጣጠር ነዉ።

ምስሉ የሚያሳየዉ ዶክተር ብርሃኔ በአንድ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ሆነዉ ነዉ።
ጥያቄ፤ በአሜሪካ ብሔራዊ የምርምር ካዉንስል በ1996 የታተመዉ Lost Crops of Africa በሚለዉ መጽሐፍ ከገጽ 181-182 ስለ ኢትዮጵያ ማሽላ ተጽፏል። በተለይም ወተት በጉንጬ እና ማርጩቄ ስለሚባሉት ታዋቂ የማሽላ ዓይነቶች። እንደ ጽሑፉ አባባል እነዚህ ሁለት ዝሪያዎች ምንም እንኳ የፕሮቲን መጠናቸዉ ከፍተኛ ቢሆንም በምርምራቸዉ ወደፊት ሊገፉ አልቻሉም። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰዉ እነዚህ ሁለት ዝሪያዎች በቀላሉ ለወፍ፣ ተባይና በሽታ ስለሚጠቁ ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ ወተት በጉንጬ እና ማርጩቄ ሲፈጩ የሚሰጡት ዱቄት ጥራቱ ዝቅተኛ እንደሆነ ይገልጻል። ይህ መረጃ ትክክል ነዉን?
ዶክተር ብርሃኔ፤ ወተት በጉንጬ ወይም ማርጩቄ የሚባሉት ሁለት የተለያዩ ስያሜዎች ቢሰጣቸዉም ሁለቱም ስሞች የአንድ የማሽላ ዓይነትን ይወክላሉ። ይህ የማሽላ ዓይነት ጣፋጭ ከመሆኑም በተጨማሪ በዉስጡ ከፍተኛ የሆነ ላይሲን የተባለ አስፈላጊ ንጥረ ነገርና ፕሮቲን ይዟል። ይህ የማሽላ ዓይነት ከወሎ አካባቢ የተገኘ ነዉ። ከላይ በጠቀስከዉ መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸዉ ምንም እንኳ የዚህ ማሽላ ዓይነት እጅግ ከፍተኛ የሆነ ለሰዉነታችን ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮች በዉስጡ ቢይዝም የተደረጉት ሰፋ ያሉ ጥናቶች የተጠበቀዉን ያህል ውጤት ሊያመጡ አልቻሉም። ምክንያቱም በተደረጉት የማዳቀል ሥራዎች የወተት በጉንጬን ጥሩ ጎኖች በመውሰድ ከፍተኛ ምርት ወደሚሰጡት የማሽላ ዓይነቶች ማስተላለፍ አለመቻሉ ነዉ። የወተት በጉንጬ ደካማ ጎኑ በፍሬዉ ዉስጥ ያለው ኢንዶስፐርም (endosperm) ተብሎ የሚታወቀዉ ክፍል ለስላሳና የተሰባበረ በመሆኑ የፍሬዉ ክብደትም አነስተኛ ነዉ። ይህም የወተት በጉንጬ ማሽላ ሲፈጭ የሚሰጠዉ የዱቄት መጠን በጣም ዝቅ ያለ እንዲሆን ያደርገዋል። በዚሁ ምክንያት ይህ የማሽላ ዓይነት በብዛት የሚበቅልበት አካባቢ ጥቅም ላይ የሚዉለዉ በእሸትነቱ ጊዜ በመቁላትና በመመገብ ነዉ እንጂ በመፍጨትና በምግብ መልክ በመጠቀም አይደለም።
ጥያቄ፤ እርስዎ ከነበሩበት ወቅት ጋር ሲያወዳድሩት ባሁኑ ጊዜ የማሽላ ምርምርና ምርታማነት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ዶክተር ብርሃኔ፤ በሌሎቹ የሀገራችን ሰብሎች ምርምር ላይ እንደሚታየዉ ሁሉ የማሽላ ምርምርም በመስኩ የሰለጠነ የሰዉ ኃይል ረዘም ላለና ተከታታይነት ባለዉ መልኩ ለማቆየት አልቻለም። ምንም እንኳ ይህ የሰለጠነ የሰዉ እጥረት የምርምር ፕሮግራሙን በከፍተኛ ሁኔታ ቢፈታተነዉም ለተለያዩ ሥነ ምህዳር ላላቸዉ አካባቢዎች የተሻሻሉ ዝሪያዎችን በማስለቀቅ ወደ ገበሬው እንዲደርሱ ለማድረግ ተችሏል። በቅርብ ጊዜያት ከተለቀቁትና አምራቹ ዘንድ ከደረሱት የማሽላ ዝሪያዎች መካከል ዲቃላ ያልሆኑና የዲቃላ ማሽላ ዓይነቶችም ይገኙበታል። እነዚህም ጎብዬ፣ ተሻለ፣ ብርሃን፣ ESH1 እና ESH2 የተባሉትን ያካትታል። በዚሁ ምክንያት ባለፉት ዓመታት የማሽላ ምርታማነት እየጨመረ መሄዱ ምርምሩ ወደፊት እየሄደ እንደሆነ ያሳያል። እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት አሜሪካን ሀገር ከሚገኘዉ የፐርዱ ዩኒቨርስቲ በመሆን በኢትዮጵያ የማሽላ ማሻሻያ ፕሮግራም ዉስጥ የላቀ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ስለሚገኙት ሰለ ፕሮፌሰር ገቢሣ ኢጀታ ነዉ።
ጥያቄ፤ በሥራ ዘመንዎ ወቅት ፋታ የማይሰጥ የሥራ ጫና የነበርዎት መቼ ነበር? በዚያን ወቅት በቀን ለስንት ሰዓት ይሠሩ ነበሩ?
ዶክተር ብርሃኔ፤ ለማሽላ ተመራማሪዎች ፋታ የማይሰጡ ጊዜያት በወቅት ላይ የተመሠረቱ ናቸዉ። በተለያዩ ሙከራ ጣቢያዎች የሚላኩ ዘሮችን ከማዘጋጀትና ማደራጀት አንስቶ በወቅቱ እንዲዘሩ ማድረግ፣ መረጃ መሰብሰብና መረጣ ማካሄድ፣ በመቀጠልም በወቅቱ እንዲታጨዱና እንዲወቁ ያለዉ ጊዜ ሁሉ የቅርብ ክትትል ይፈልጋል። በተለይም ዘር ከዘራን በኋላ ዝናብ እንዲዘንብልን በናፍቆት የምንጠብቀዉ ጊዜና የምንጸልየዉ አንዱ የሥራችን አካል ነበር። የምርምራችንን ጊዜም ለማፋጠን ከዋናዉ የሰብል ወቅት በተጨማሪ በመልካ ወረር ምርምር ጣቢያ በመስኖ በመታገዝ ስለምንሠራ ዓመቱን ሙሉ እረፍት አለ ማለት አይቻልም። በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የማሽላ ሙከራ ጣቢያዎችን መጎብኘት አንዱ ኃላፊነቴ ስለነበር በሀገሪቷ በሙሉ ሰፋ ያለ ጉዞ አካሄድ ነበር። በዋናዉ የሰብል ወቅት በቢሮና በመስክ በቀን ከ12 ሰዓታት በላይ ማሳለፍ የሚኖርብኝ ጊዜ የነበረ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ከሥራ መልስ ቤት የምሠራቸዉ የጽሑፍ ሥራዎችም ነበሩኝ።
ጥያቄ፤ በሥራ ዓለም ያጋጠሞት ገጠመኝ ወይም ፈታኝ ወቅት ካለ ቢያካፍሉኝ፤
ዶክተር ብርሃኔ፤ በርካታ ገጠመኞች ወይም ፈታኝ ጊዜያት ነበሩብኝ። የተወሰኑትን በተለይም ከማሽላ ሥራዬ ጋር የሚገናኙትን ባጭሩ ከዚህ በታች ለመጥቀስ እወዳለሁ።
- የመጀመሪያዉ ገጠመኜ የማስትሬት ትምህርቴን አጠናቅቄ በ1964 ከዉጭ እንደተመለስኩ በአለማያ እርሻ ኮሌጅ የአሜሪካ መምህሮቻችንን በኢትዮጵያኖች መተካቱ የተጀመረበት ወቅት ነበር። ስለዚህ በዚሁ በ1964 የትምህርት ዘመን በእኔና ሦስት የሥራ ባልደረቦች በዚህ በመተካካቱ ፕሮግራም እንድንካተት በመደረጉ ከፍተኛ የሥራ ድርሻና ኃላፊነት ወደቀብን። በዚህ ጊዜ በኔና በሥራ ባልደረቦቼ ላይ የነበረዉ ፈታኝ ሁኔታና ጭንቀት የማይረሳኝ ነዉ።
- ሁለተኛዉ ገጠመኜ በእርሻ ኮሌጁ መምህር በሆንኩ በአምስተኛዉ ዓመት ማለትም በ1969 መጨረሻ ላይ ተደራራቢ ኃላፊነቶች የወደቁብኝ ወቅት ነበር። ከእነዚህ ኃላፊነቶች ዉስጥ አንዱ የዕጽዋት ሣይንስ ዲፓርትመንት ኃላፊ መሆን ሲሆን ሌላዉ ደግሞ የብርዕና አገዳ የምርምር ክፍል ኃላፊነትም ደርቤ እንዲይዝ መደረጉ ነበር። በተመሣሣይ ወቅት የተለያዩ ኮርሶችም ማስተማር ነበረብኝ። ይህን ሁሉ የኃላፊነትና የማስተማር ሥራ በማስፈጽምበት ወቅት የምከተለዉ አንዳችም መመሪያ አልነበረም። እንደ አርአያ ሆኖልኝ የምከተለዉ ሰዉም አልነበረኝም።
- ሶስተኛዉ ገጠመኜ በ1976 በህይወቴ ዉስጥ ካደረኳቸዉ ከፍተኛ ውሳኔዎች መካከል አስቸጋሪዉንና ከባዱን የወሰንኩበት ዓመት ነበር። ይህም የአለማያ ኮሌጅ ግቢን ለቅቄ IDRC ከተባለዉ የካናዳዉ የዕርዳታ ድርጅት ባገኘሁት ድጋፍ ያቋቋምኩትን የብሔራዊ የማሽላ ማሻሻያ ፕሮግራም ለማስተባበር አዳማ አካባቢ ወደሚገኘዉ ወደ መልካሳ ምርምር ጣቢያ ለመጓዝ መወሰኔ ነበር።
- ሌላዉ ገጠመኜ ወይም ፈታኝ ወቅት ከዚሁ ወደ መልካሳ ከተጓዝኩበት ውሳኔ ጋር ይገናኛል። ይኸዉም ለሁለት አለቆች ሪፖርት ማድረግ ያለብኝ ስለነበረ ነዉ። አንዱ አለቃዬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር የነበረዉ የአለማያ እርሻ ኮሌጅ ሲሆን ሁለተኛዉ አለቃዬ ደግሞ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ነበር። የአስተዳደር ሥራዎችን በተመለከተ በአለማያ ሥር የነበርኩ ሲሆን በሥራ ማስፈጸም በኩል በእርሻ ምርምር ሥር ነበርኩ።

ዶክተር ብርሃኔ የ52 ዓመት የትዳር ጓደኛቸዉ ከሆኑት ከወይዘሮ ገነት ታደሰ ጋር በሎዛን ስዊዘርላንድ የሚገኘዉን የኦሎምፒክ ሙዚየም በጎበኙበት ወቅት።
- በ1979 የኢትዮጵያ ሁኔታ የተረጋጋ አልነበረም። በዚሁ ምክንያት ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሰባሰብናቸዉን ወደ 5,000 የሚጠጉ የማሽላ ዓይነቶችን ልናጣ የምንችልበት ሁኔታ ላይ ደርሰን ነበር። ይህም እንዳይከሰት አንድ አስቸጋሪ ዉሳኔ መወሰን ነበረብኝ። ይህም እነዚህ ዕንቁ ዝሪያዎችን በሦስት የተለያዩ ቦታዎች እንዲቀመጡ ማድረግ ነበር። እነዚህ ዘሮች በአስተማማኝነት እንዲቀመጡ ያደረኩባቸዉ ሥፍራዎች በአዲስ አበባ የሚገኘዉ የብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት፣ ICRISAT የተባለው በህንድ ሀገር በሃድራባድ የሚገኘዉ ዓለም አቀፍ ድርጅት እና ዋሽንግተን ዲ ሲ የሚገኘዉ USDA የተባለዉ የአሜሪካ የእርሻ ዲፓርትመንት ናቸዉ።
- በ1982 ICRISAT ለሚባለዉ ዓለም አቀፍ ድርጅት በምሠራበት ወቅት የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የማሽላ ማሻሻያ ማዕከል በናይሮቢ ማቋቋም ነበረብኝ። ይህንንም ምንም መሠረት ካልነበረበት ሁኔታ ተነሥቼ ማቋቋም ሰለነበረብኝ አንዱ ፈታኝ ወቅት ነበር።
- ሌላው በህይወቴ ሙሉ የማልረሳዉ ትዝታዬ በ1988 ሜሩ በምትባለዉ የኬንያ ከተማ አካባቢ በኔና በአራት ኬንያዊያን ፕሮፊሽናል የሥራ ባልደረቦቼ ላይ የደረሰብን አሰቃቂ የመኪና አደጋ ነዉ። በዚህ የከፋ አደጋ ሁለቱ ኬንያውያን የሞቱበት በተረፍነዉ ላይም ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰብን ነበር። የዚህን የከፋ አደጋ ሁኔታ ከጭንቅላቴ ውስጥ ፍቄ ላወጣዉ አልቻልኩም።
በዚሁ ከዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን ጋር በአራት ከፍሎች የቀረቡ ቃለ መጠይቆች አበቃለሁ። በርካታ ትምህርት እንደወሰዳችሁ አምናለሁ።
በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኝላችኋለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥቅምት 2፣ 2012 ዓ.ም. (October 13, 2019)