በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡
ስትራቴጂስቱና የግብርና ባለሙያዉ፣ ዶክተር ይልማ ከበደ፤ ክፍል 1
በዛሬዉ ጽሑፌ በግብርናዉ መስክ ከፍተኛ ዕዉቀትና የሥራ ልምድ ስላካበቱትና ይህንንም ለተተኪዉ ትውልድ በማስተላለፍ ላይ ሰለሚገኙት ስለ ዶክተር ይልማ ከበደ አስነብባችኋለሁ፡፡
ዶከተር ይልማ ከበደ ከ40 ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ በምግብ ዋስትና ላይ የሰሩ ሲሆን በተለይም በሰብል ማሻሻያ፣ በዘር ሲስተም እና በመሳሰሉት ላይ በሀገር ዉስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸዉ፡፡ እስካሁን ድረስ የሠሩባቸዉ ድርጅቶችም በርካታ ሲሆኑ እነርሱም የምርምር ማዕከላትን፣ የግል ድርጅቶችን፣ እና ግብረ ሠናይ ድርጅቶችን ያካትታል። ከነዚሁ ድርጅቶች ጋር በምርምር እና ስትራቴጂ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገዉ ሰርተዋል፡፡ ለዚሁም ነዉ ከግብርና ባለሙያነታቸዉ በተጨማሪ ስትራቴጂስቱ የሚል መጠሪያ የሰጠኋቸዉ፡፡
የዶክተር ይልማ ከበደን የትምህርት ዝግጁነትና የሥራ ልምድ እንዲሁም አስተዋጽኦ ከዚህ በታች በአጭሩ አቀርባለሁ፡፡
የትምህርት ዝግጁነት
- ፉል ብራይት ፖስት ዶክ (post doc)፣ ከፐርዱ ዩኒቨርስቲ፣ አሜሪካ
- ፒ ኤች ዲ፣ በዕጽዋት ቢሪዲንግ እና ጄኔቲክስ፣ ከቴክሳስ ኤ ኤንድ ኤም ዩኒቨርስቲ፣ አሜሪካ
- የሁለተኛ ወይም የማስተር ዲግሪ፣ በሰብል ፊዚዮሎጂ፣ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ገልፍ፣ ካናዳ
- የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በዕጽዋት ሣይንስ፣ ከሃረማያ ዩኒቨርስቲ፣ ኢትዮጵያ
የሥራ ልምድና ቀደም ብሎ የነበራቸዉ ከፍተኛ ኃላፊነቶች
- አባል፤ የምርምር ፕሮግራም መሪ ኮሚቴ፤ የደረቅ ሥፍራ ሰብሎች (Dryland Cereals-CGIAR)
- አባል፣ የመማክርት ቡድን፤ የአግራ ፓስ (AGRA-PASS)
- አባል፤ ዓለም አቀፍ የስኮላር ሺፕ ኮሚቴ፤ ፓዮኒር ሃይ ብሪድ (Pioneer Hi-Bred)
- አባል፤ የሰብል ብዝሀ ዘር ኮሚቴ፣ ዩ ኤስ ዲ ኤ /ኤ አር ኤስ (USDA/ARS)
- ኃላፊ፣ የሰብሎች ማሻሻያ ፕሮግራሞችን የሚገመግም ታስክ ፎርስ፤ ኢክሪሳት (ICRISAT)
- ኃላፊ፤ በምዕራብ፣ ምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የሰብል ማሻሻያ ፕሮግራሞች ላይ ምክር የሚሰጥ ቡድን፣ ኢክሪሳት (ICRISAT)
- ከፍተኛ የፕሮግራም ኦፊሰር፤ ቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን (BMGF)፤ እ አ አ ከ2008 እስከ 2016 ይህንን ፕሮግራም ሲመሩ የብዕርና አገዳ ሰብሎች ምርታማነት እንዲያድግ የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፈዋል። በተለይም የማሽላና ዳጉሣ ምርታማነት እንዲያድግ በሚያስችል ፕሮጀክት ውስጥ በመሳተፍ ጉልህ ሚና ተጫዉተዋል። በዚሁ በተሳተፉበት የስትራቴጅ ንድፍም በኢትዮጵያ የግብርና ልማት ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ የኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ (በአሁኑ አጠራር የኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት) እንዲቋቋም መሠረት ጥሏል።
- አስተባባሪ እና ተመራማሪ፤ ዱ ፑንት /ፓዮኒር ሃይ ብሪድ (DuPont/Pioneer Hi-Bred)፤ እ አ አ ከ1992 እስከ 2008 በካምፓኒዉ የማሽላ ፕሮግራምን በቴክሳስ፣ ሜክሲኮ፣ ህንድ እና አዉስትራሊያ ባስተባበሩበት ወቅት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንዲወጡ ከማስደረጋቸዉም በላይ በርካታ የበቆሎ፣የማሽላ እና የሱፍ ዝርያች በተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች እንዲጸድቁና እንዲሰራጩ አስችለዋል
- ተመራማሪና አስተባባሪ፤ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የማሽላ ፕሮግራም
- የማዕከል ዳይሬክቴር፤ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የመልካሳ ምርምር ማዕከል
ባሁኑ ጊዜ የሚሳተፉባቸዉ የኮሚቴ ወይም የማማከር ኃላፊነት
- አባል፣ የአስተዳድር ቦርድ፤ ኢክሪሳት (ICRISAT)
- ሊቀመንበር፣ የፕሮግራም ኮሚቴ፤ ኢክሪሳት (ICRISAT)
- አባል፣ የሰብል ማሻሻያ ፕሮግራሞችን ገምጋሚ ቡድን። ቴክኖሎጂዎችን መፈተሽ፣ የዘር አቅርቦትን ማሳደግን እና የፕሮግራሞች ተጽዕኖን መገምገም፤ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኪዉንስላንድ፣ አውስትራሊያ
- አባል፤ የአማካሪ ቦርድ፤ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቱት
ያሳተሟቸዉ ጽሑፎች፤ ከ40 የሚበልጡ በተለያዩ የግብርና መስኮች ላይ ያተኮሩ ጽሑፎችን አበርክተዉልናል፡፡
መዋዕለ ንዋይ የማስገኘት (grant making) ችሎታቸዉና ልምዳቸዉ፤ ዶክተር ይልማ የተለያዩ ሀገራት በጋራ ፕሮጀክቶች ነድፈዉ ከለጋሽ ድርጅቶች ወይም ሀገራት የፋይናንስ ዕርዳታ የሚያገኙበትን መንገድ በመንደፍና በማስተባበር ሰርተዋል። ለምሳሌቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን (BMGF) ይሰሩ በነበረበት ወቅት በአፍሪካ በተለይ የማሽላና የዳጉሳ ምርጥ ዘሮች እንዲገኙ በሚደረጉ ምርምሮችና ምርጥ ዝርያዎችን ለማሰራጨት ተብሎ የተፈቀደዉን ከ200 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ለአግራና ኢክሪሳት እንዲፈቀድ ከፍተኛ ሚና ተጫዉተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ፋይናንስ የማስገኘት ፕሮጀክቶች ዉስጥ ቁልፍ ሚና ተጫዉተዋል።

ምስሉ የሚያሳየዉ ኢክሪሳት (ICRISAT) በሚባለዉና መቀመጫዉን ህንድ ሀገር ያደረገ ዓለም አቀፍ የሰብል ምርምር ድርጅት የቦርድ አባላትን ሲሆን ዶክተር ይልማም (በስተግራ የሚታዩት) በአሁኑ ወቅት የዚሁ ከፍተኛ ኃላፊነት የተሰጠዉ ቦርድ አባል ሆነዉ በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ምንጭ፤ https://www.icrisat.org/101st-governing-board-meeting-at-icrisat-headquarters-in-hyderabad/
የላቀ የግብርና ሣይንስ (Advaces in Agricultural Science) ሲምፖዚየም፤ በዚህ ርዕስ ሥር እኔ (የዚህ ብሎግ ጸሐፊ) ሁለት ሲምዚየሞችን በአዲስ አበባ አዘጋጅቼ ነበር። በሁለቱም ሲምፖዚየሞች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ተመራማሪዎች፣ የየኒቨርስቲ መምህራንና የተጋበዙ እንግዶች የተገኙ ሲሆን ዶከተር ይልማም በሁለቱም ሲምፖዚሞች ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።
ጥቅምት 14 ቀን 2007 (እ አ አ ኦክቶበር 24፣ 2014) በተካሄደዉና ምርምር በኢትዮጵያ ግብርና ልማት፤ የሚጠበቁ ነገሮች እና ዕድሎች (R4D in the Ethiopian Agriculture: Expectations and Opportunities) በሚል ርዕስ ሥር በተካሄደዉ በመጀመሪያዉ ሲምፖዚየም ላይ ዶክተር ይልማ በምርምር እና በልማት ሥራ የተገኙ ትምህርቶች፣የግል ተሞክሮዬ (Lessons learned from a career in research and development: a personal experience) በሚል ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆነ በተካሄደዉ የፓናል ውይይትም ላይ ተሳትፈዋል።
በተጨማሪም ጥቅምት 14፣ 2012 ዓ.ም. (እ. ኤ. አ. ኦክቶበር 25, 2019) በተካሄደዉ ሁለተኛዉ የላቀ የግብርና ሣይንስ (Advances in Agricultural Science) ሲምፖዚየም ከመሳተፋቸዉም በተጨማሪ በተካሄዱ ውይይቶች ላይ ተሳትፈዋል።

ምስሉ የምያሳየዉ ጥቅምት 14 ቀን 2007 (እ አ አ ኦክቶበር 24፣ 2014) በተካሄደዉ የመጀመሪያዉ የላቀ የግብርና ሣይንስ (Advances in Agricultural Science) ሲምፖዚየም ተሳታፊዎችን ሲሆን ዶክተር ይልማ ከፊት ተርታ (ከግራ ወደ ቀኝ) ሶስተኛዉ ናቸዉ። ፎቶ፤ ዘሪሁን ታደለ

ምስሉ የሚያሳየዉ ጥቅምት 14፣ 2012 ዓ.ም. (እ. ኤ. አ. ኦክቶበር 25, 2019) በተካሄደዉ ሁለተኛዉ የላቀ የግብርና ሣይንስ (Advances in Agricultural Science) ሲምፖዚየም ተሳታፊዎችን ነዉ።
በአጠቃላይ ዶክተር ይልማ ያላቸዉን ዕዉቀትና ረዘም ያለ የሥራ ልምድ በመጠቀም በሙያዉና በሥራዉ ጠንካራ የሆነ ትዉልድ ለመገንባት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዚሁም ምስክር የሚሆነዉ በቅርቡ በተካሄደዉ 19ኛዉ የኢትዮጵያ የሰብል ባለሙያዎች ኮንፈረንስ ላይ ወጣት ተመራማሪዎች ጽሑፎቻቸዉን ለማሳተም እና የምርምር ዉጤታቸዉን በኮንፈረንስ ለማቅረብ በሚያስቡበት ወቅት ሊያማክሯቸው እንደሚችሉ ቃል መግባታቸዉ ነዉ፡፡ እኔም እኚህን ታላቅ ምሁር እንጠቀምባቸዉ እላለሁ፡፡
በክፍል 2 ጽሑፌ ዶክተር ይልማ በማሽላ ምርምር እና ልማት ላይ ያደረጉትን አስተዋጽኦ በሚመለከት እጽፋልሁ፡፡ እስከዛዉ መልካሙን እመኛለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መጋቢት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. (March 18, 2023)