በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡
የጤፍን ፍሬ በእንክብል የማሳደግ አስፈላጊነት፤ ክፍል 2
ባለፈዉ ጽሑፌ የዘር እንክብል (seed pelleting) ስለሚባለዉና የዘር ፍሬን በእንክብል መንገድ በመሥራት ምርታማነትን ማሳደግ እንደምንችል ለማሳየት ሞክሬአለሁ። በዛሬዉ ጽሑፌ ደግሞ ይህንን የዘር እንክብል በጤፍ ላይ በመጠቀም የተደረገዉን ጥረትና ውጤት በአጭሩ ለማስነበብ እሞክራለሁ።
ባለፈዉ ብሎጌ እንደገለጽኩት የዘር እንክብል በርካታ ጥቅሞች አሉት። ይህ የሰብል ማሻሻያ መንገድ ጤፍንም በዘመናዊ መንገድ ለማሻሻል ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል። ምክንያቱም የጤፍ ዘር ወይም ፍሬ በጣም አነስተኛ በመሆኑ ገበሬዎች አስፈላጊ የሆነ የዘር መጠን ሊጠቀሙ አይችሉም። ለጤፍ የሚመከረዉ የዘር ብዛት 10 ኪሎ ግራም በሄክታር ሲሆን ገበሬዎቻችን ግን ይህ የዘር መጠን በቂ መስሎ ሰለማይታያቸዉ እስከ 30 ወይም 40 ኪሎ በሄክታር ድረስ ይጠቀማሉ። ይህ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የዘር መጠን የጤፍን ተክሎች ለከፍተኛ መተፋፈግ ከመዳረጉም በላይ ሰብሉን ለመጋሸብ ያጋልጣል። የጋሸበ ተክል ደግሞ የምርት ብዛቱም ሆነ ጥራቱ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ማለት ነዉ። በጤፍ ላይ የሚከሰተዉን ይህን ከፍተኛ መጋሸብ ለመቀነስ ወይም ለመቋቋም የተለያዩ መንገዶች መጠቀም ይቻላል።
እነዚህ መንገዶችም በመጠኑ በጥናት ላይ ሲሆኑ ሌሎችም በጥቅም ላይ እየዋሉ ነዉ። ለምሳሌ የጤፍ ተክል ቁመት በማሳጠር ጠንከር ያለና መጋሸብን መቋቋም የሚችል ተክል ማግኘት ይቻላል። ሌላዉ መንገድ ደግሞ ቁመት የሚያሳጥሩ ሆርሞኖች (plant hormone) በተወሰነ መልክ በጤፍ ላይ የሚያጋጥመውን መጋሸብ መግታት ይቻላል። የዛሬዉ ጽሑፌ የሚያተኩረዉ የዘር እንክብልን በመጠቀም የጤፍ የዘር መጠንን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ብቻ ሳይሆን መጋሸብንም እንደሚቀንስ ነዉ።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉና ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ተመራማሪዎችና ተቋማት የጤፍ መጋሸብን ችግር ለመፍታት ከፈተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። አንዳንዶቹም አመርቂ ዉጤት እያገኙ ነዉ።
በዚሁ መሠረት በኢትዮጵያ እና ስዊዘርላንድ ባሉ ተመራማሪዎችና ተቋማት የተመሰረተዉ የጤፍ ማሻሻያ ፕሮጀክት የጤፍን ዘር ወይም ፍሬ በእንክብል መልክ ለማሳደግ ዕቅድ ነድፎ ወደ ሥራ ገብቷል። በዚሁ መሠረት የዘር እንክብልን ለመሥራት የሚያገለዉን በላቦራቶሪ ውስጥ የሚቀመጥ አነስተኛ ፔሌቴር (pelleter) ገዝቶ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቱት ሥር በሚገኘዉ የደብረ ዘይት ግብርና ማዕከል እንዲመሠረት ተደረገ፤ ሥልጠናም አስፈላጊ ለሆኑ ተመራማሪዎችና ቴክኒሻኖች ተሰጥቷል።

በምስሉ የሚታየዉ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቱት ሥር በሚገኘዉ የደብረ ዘይት ግብርና ማዕከል ውስጥ የሚገኘዉ የዘር እንክብልን ለመሥራት የሚጠቅመዉ ፔሌቴር (pelleter) ነዉ። ፎቶ፤ ዘሪሁን ታደለ

ምስሉ የሚያሳየዉ የዘር እንክብልን በጤፍ ላይ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሥልጠና በደብረ ዘይት ግብርና ማዕከል የሚገኙ ተመራማሪዎችና ቴክኒሻኖች ሲወስዱ ነዉ። ፎቶ፤ ዘሪሁን ታደለ
ከዚህ በታች በምስሉ እንደሚታየዉ የጤፍን ዘር በተለያየ መጠን በእንክብል መልክ በማሳደግ ተስማሚ የሆነዉን ለመምረጥ ሙከራ ተደርጓል። በክፍል 1 ጽሑፌ በገለጽኩት መሠረት የዘር እንክብል ለመሥራት ዘሩን ለማሳደግ ፓዉደር፣ ውሃ፣ ማጣበቂያ እና ዘር ያስፈልጋሉ። ዘሩን ለማሳደግ በዋናነት የሚረዳዉ ፓዉደር ከተለያዩ ነገሮች መጠቀም ይቻላል።

ከላይ በምስሉ የሚታየዉ በጤፍ ዘር ዙሪያ እንክብል በመሥራት የጤፍ ዘርን ለማሳደግ እንደምንችል ነዉ። በዚሁ መሠረት የ1000 ጤፍ ዘር በአማካይ ከሚመዝነዉ 0.38 ግራም እስከ 7.57 ግራም በማሳደግ በብቅለት እና እድገት ላይ ያለዉን ሁኔታ ለማጥናት ችለናል። በእንክብል ያልተሰራዉን ጤፍ እንደ አንድ ብንቆጥር (በምሥሉ በቀኝ በኩል የሚታየው ለማለት ነዉ) በግራ በኩል የሚታየዉ እስከ 20 እጥፍ ክብደት ይጨምራል ማለት ነዉ። ከላይ የሚታዩትን እንክብሎች ለመሥራት አገልሎት ላይ የዋሉት ፓውደሮች ለ5 እና15 እጥፍ የእንጨት ፍቅፋቂ ሲሆን ለ20 እጥፉ ደግሞ የሸክላ አፈር ነዉ። ፎቶ፤ ዘሪሁን ታደለ
የጤፍን ዘር በእንክብል መልክ መጠቀሙ ጤፍን በእጅና በብተና ከመዝራት ወጥታ በመዝሪያ ማሽን ወደ መዝራት ሊያሸጋግራት ይችላል። የጤፍ መዝራትን ለማቀላጠፍ የተለያዩ የመዝሪያ ማሽኖች ሊሰሩ የቻሉ ሲሆን አንዳንዶቹም በሙከራ ላይ ናቸዉ። የተለያዩ ተቋማትም ትኩረት አድርገዉ በመሥራት ላይ ሲሆኑ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰዉ በግብርና ምርምር ማዕከል ሥር የሚገኘዉ የመልካሳ ምርምር ማዕከል ነዉ። ማዕከሉ ከሰራቸዉ የጤፍ መዝሪያ መሣሪያዎች ውስጥ ከዚህ በታች የሚታየዉ በተለይም የኮትቻ አፈር ባለበት ቦታ ተመራጭ ነዉ። ምክንያቱም በጤፍ የዘር ወቅት ከመሬቱ እጅግ የመርጠብና የመጣበቅ ባህርይ የተነሳ ግዙፍ መሣሪያዎችን ወደ ማሣ ማስገባት አስቸጋሪ ስለሆነ ነዉ።

ምስሉ የሚያሳየዉ የጤፍ ዘርን በተለይም በኮትቻ ማሣ ላይ ለመዝራት በመልካሳ ምርምር ማዕከል የተሰራዉን መዝሪያ ነዉ። ፎቶ፤ ዘሪሁን ታደለ
በአጠቃላይ የጤፍ እንክብልን በመጠቀም የምንዘራዉን ዘር በተፈለገዉ ርቀት እንዲቀመጥ በማድረግ የሚፈለገዉን የተክል ብዛት ማግኘት እንችላለን። ያለበለዚያ የተክሉ ብዛት ከተወሰነ መጠን በላይ የበዛ ከሆነ ተክሎቹ እርስ በርሳቸው ለብርሃን፣ ለውሃ እና ለማዕድን ሽሚያ ያደርጋሉ። የሚደርሰዉ ጉዳት በዚህ ብቻ ሳያበቃ ተክሎቹ ስለሚጋሸቡ ወይም ስለሚወድቁ የምርት ጥራትና መጠን በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ ይችላል። በእንክብል መልክ የተሰራዉን የጤፍ ዘርንም በዘመናዊ የጤፍ መዝሪያ በመጠቀም የጤፍ ሜካናዜሽን ለማሳደግ እንችላለን።
በዚሁ በሁለት ክፍሎች ያቀረብኩትን ‘የጤፍን ፍሬ በእንክብል የማሳደግ አስፈላጊነት’ የሚለዉን ጽሑፌን አበቃለሁ።
በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥር 21 ቀን 2015 ዓ.ም. (January 29, 2023)