ግብርናችንንለማዘመን፤ የጤፍን ፍሬ በእንክብል የማሳደግ አስፈላጊነት፤ ክፍል 1

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡

የጤፍን ፍሬ በእንክብል የማሳደግ አስፈላጊነት፤ ክፍል 1

በዚህ ጽሑፌ የዘር እንክብል ብዬ የተጠቀምኩት በእንግሊዘኛዉ ሲድ ፔሌቲንግ (seed pelleting) የሚባለዉን ይወክላል በሚል ነዉ። ምናልባት የተሻለ ቃል ከተገኘ ወደፊት አስተካክላለሁ።

ቃሉ የሚያመለክተዉ የፍሬዉን መጠን በማሳደግ ለተለያዩ ጠቃሚ የግብርና ተግባራት ሥራ ላይ የሚዉልወን እንክብልን ነዉ። በዚህ መሠረት የእንክብሉ መጠን በከፍተኛ ደረጃ ሊያድግ ይችላል ወይም የዘሩ ቅርጽ ለማሽን መዝሪይ እንዲያመች ተደርጎ ይሰራል ማለት ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ የተባይ ወይም የበሽታ መከላከያ መድሃኒትም በእንክብሉ ላይ በመጨመር እንክብሉ ለተለያዩ ጥቅሞች ያገለግላል ማለት ነዉ።

እዚህ ላይ ማወቅ ያለብን ባንድ እንክብል ወስጥ የሚኖረዉ የዘር ብዛት አንድ ብቻ ሲሆን ባጋጣሚ የተለያዩ ግብአቶች አጠቃቀም የተነሣ ከአንድ በላይ ዘር በተወሰኑት እንክብሎች ውስጥ ሊኖሩ ይችላል።

እንክብሉን ለመሥራት የሚረዱ የተለያዩ መሳሪያዎች በገበያ ላይ አሉ። እነዚህም በላቦራቶሪ ውስጥ ማስቀመጥ የምንችላቸዉ አነስተኛ ማሽኖች አንስቶ በፋብሪካ ደረጃ አገልግሎት ላይ የሚዉሉ ግዙፍ ማሽኖችም ያካትታል።

በአጭሩ እንክብልን ለመሥራት የሚከተሉት ግብአቶች ያስፈልጋሉ።

  • ዘር
  • ፓውደር፤ የተፈጨ የእንጨት ፍቅፋቂ፣ ሸክላ አፈር፣ ወዘተ። እዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባን ይህ የእንክብሉን መጠን ለማሳደግ የምንጠቀምበት ፓዉደር በዘሩ ላይ ስለሚጣበቅ በዘሩ ላይ አሉታዊ ጎን እንይኖነዉ ማወቅ ያስፈልጋል። ያለበለዚያ የዘር ብቅለት በከፍተኛ ደረጅ ይሰናከላል።
  • ግሉ ውይም ማጣበቂያ
  • ውሃ

እነዚህ ግባቶችንም በሚከተለዉ መንገድ የዘር እንክብል ለመሥራት ጥቅም ላይ ይዉላል።

እንክብሉ ሲሰራ ዘሩ በፓውደሩ ሙሉ በሙሉ ይሸፈናል። ቢሆንም ዘሩን እና ሌሎች ግባቶችን በቋሚነት በተተመነት ፍጥነት የሚያሽከረክረዉን የማሽኑ ክፍል እና የእንክብኑ ግባቶች ከሆኑት ደግሞ እንደ ፓዉደርና ማጣበቂያ ያሉት የአጨማመር ፍጥነት በእንክብሉ ጥራት ላይ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።

የዘር እንክብልን ለመሥራት ባብዘኛዉ ከዚህ በታች በተመለከተዉ ቅድመ ተከተል ነዉ።

  • በመጀመሪያ ለእንክብል ልንጠቀምበት ያሰብነዉን ዘር በማሽኑ ውስጥ ወደሚገኘዉ ሰሃን ወይም ትሬ ላይ መጨመር፣
  • በመቀጠልም ትሬዉን ያለማቋረጥ እንዲሽከረከር ማድረግ፣
  • ዘሮቹ እስኪረጥቡ ድረስ ማሽኑ ዉሃ እንዲረጭ ማደረግ፣
  • በመቀጠልም ማሽኑ እንክብሉን ለማሳደግ የሚረዳዉን ፓዉደር የረጠበዉ ዘር ላይ በስ ሱ እንዲረጭ ማድረግ፣ በዚህን ጊዜ ፓዉደሩ ዘሩ ላይ ይጣበቃል።
  • ቀጥሎ ፓውደሩን ዘሩ ላይ እንዲጣበቅ የሚረዳዉን ማጣበቂያ ውይም ግሉ በትንሹ የረጠበዉ ዘር ላይ እንዲረጭ ማድረግ፣
  • በመቀጠልም የተሰሩት እንክብሎች ከማሽኑ እንዲወጡና በተፈለገዉ የእንክብል መጠን ያለቱን ወደ ማድረቂያ ማሽን ማዛወር፣ የማድረቂያ ሁኔታ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልጋል። ምክንያቱም የሙቀት መጠንና የማድረቂያ ጊዜ ውይም ሰዓት መስተካከል ይኖርበታልና።

የዘር እንክብል ከሚያስገኝልን ጥቅሞች መካከል ዋናዎቹ የሚከተለት ናቸዉ።

  • የዘር ፍሬያቸዉ እጅግ አነስተኛ የሆኑና ክብደታቸዉም በጣም ዝቅተኛ የሆኑ ሰብሎችን በቀላሉ መዝራት ስለማይቻል በእንክብል መልክ በማሳደግና ከበድ እንዲሉ በማድረግ በቀላሉ በማሽን ወይም በእጅ ለመዝራት ይቻላል። ለምሳሌ የካሮትና የሽንኩርት ዘሮች እንዲሁም ጤፍ በዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።
  • የአንዳድ ዘሮች ውጫዊ ቅርጻቸዉ ክብ ባለመሆኑ በማሽን ለመዝራት አመቺ አይደሉም። ስለዚህ የእንክብልን ዘዴ በመጠቀም ዘሩ በማሽን ለመዝርት አመቺ ይሆናል። ለምሳሌ በአዉሮፓና አሜሪክ በሰፊዉ የሚበቅለዉና ስኳርን ለማምረት አገልግልት ላይ የዋለዉን ሹገር ቢት የሚባለዉ ሰብል የውጭዉ የዘሩ ቅርጽ ወጥነት የሌለዉ በመሆኑ በማሽን ለመዝራት አመቺ አይደለም። የእንክብልን ዜዴ በመጠቀም ክብ ቅርጽ ያለዉና በቀላሉ በማሽን ሊዘራ የሚችል ዘር በጥቅም ላይ ሊዉል ችሏል።

ከላይ ያሉት ምስሎች የሚያሳዩት የሹገር ቢት ዘር ሲሆኑ በግራ በኩል ያለዉ ዘሩ እንደታጨደ የሚመስለዉን ሲሆን በቀኝ በኩል ያለዉ ደግሞ በእንክብል መልክ የተሰራዉን ዘር ነዉ። ምንጭ፤ https://www.amazon.com/SeedRanch-Sugar-Beet-Seed-Lbs/dp/B01KLMKQVY

https://depositphotos.com/4322868/stock-photo-sugar-beet-seed.html

  • ባንዳንድ ሰብሎች ላይ እንክብልን በመጠቀም የብቅለት ጊዜን ማፋጠን ተችሏል።
  • ስብሎቻችን በተለያዩ በሽታዎችና ተባዮች እንዳይጠቁ እንክብሉን ከሰራን በኋላ በተሰራዉ እንክብል ላይ በስሱ ተባዩን ወይም በሽታዉን የሚከላከል መድሃኒት ማልበስ እንችላልን። ይህ በተሰራዉ እንክብል ላይ በተጨማሪነት የሚሰራዉ ተግባር የዘር ኮቲንግ (seed coating) ይባላል። በዚሁ መሠረት እንክብሉ ጥጨማሪ ጠቀሜታ ይኖረዋል ማለት ነዉ።

በአጠቃላይ የዘር እንክብል ዘዴን በመጠቀም የምንዘራዉን ዘር በተፈለገዉ ርቀት እንዲቀመጥ በማድረግ ለእያንዳንዱ ሰብል የሚያስፈልገዉን የተክል ብዛት እንዲጠበቅ ማድረግ እንችላለን። ያለበለዚያ የተክሉ ብዛት ከተወሰነ መጠን በላይ የበዛ ከሆነ ተክሎቹ እርስ በርሳቸው ለብርሃን፣ ለውሃ እና ለማዕድን ሽሚያ ያደርጋሉ። የሚደርሰዉ ጉዳት በዚህ ብቻ ሳያበቃ ተክሎቹ ሲለሚጋሸብቡ ወይም ስለሚወድቁ የምርት ጥራትና መጠን በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ ይችላል።

በክፍል 2 ጽሑፌ የጤፍ ፍሬ ወይም ዘርን በእንክብል መልክ በማሳደግ የተገኘዉን ውጤት አስነብባችኋለሁ። ወደፊትም ይህን መንገድ በሰፊዉ በመጠቀም የጤፍ ምርትን እንዴት ልናሳድግ እንደምንችል ለማሳየት እሞክራለሁ። እስከዛዉ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥር 19 ቀን 2015 ዓ.ም. (January 27, 2023)

አስተያየት ያስቀምጡ