ግብርናችንን ለማዘመን፤ የኢንዱስትሪዉ አብዮትና የከፋዉ ረሃብ፤ ክፍል 2

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡

የኢንዱስትሪዉ አብዮትና የከፋዉ ረሃብ፤ ክፍል 2

በክፍል 1 ጽሑፌ ስለ መጀመሪያዉ የኢንዱስትሪ አብዮት አመጣጥና የሰዎች ባንድ አካባቢ መስፈር ለማሳየት ሞክሬአለሁ። ለነዚህ ባንድ አካባቢ ለሰፈሩ የፋብሪካ ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው በተመጣጣኝ ዋጋ በአማራጭነት የቀረበዉ ምግብ ድንች ነበር። ድንች የኢንዱስትሪ አብዮት በእንግሊዝ ሀገር ከመከሰቱ አንድ መቶ ዓመት በፊት ከአሜሪካ አህጉር ወደ አዉሮፓ አህጉር ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣዉና በአጭር ጊዜ የተስፋፋ ሰብል ነበር። የድንች ምርት ከፍተኛ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በዉስጡ ከፍተኛ ካርቦሃይድሬት ያለዉ በመሆኑ ምክንያት በፋብሪካ ውስጥ ለሚሰሩ ሠራተኞች የጉልበት ምንጫቸዉ ነበር።

ታዲያ ድንች በከፍተኛ ሁኔታ በጥቅም ላይ በዋለበት ጊዜና የኢንዱስትሪዉ አብዮትም እየተስፋፋ በነበረበት ወቅት አንድ አሰቃቂ ክስተት ተፈጠረ። ይህም በከፍተኛ ሁኔታ የተንሰራፋ ረሃብ ነበር። በተለይም በወቅቱ ከእንግሊዝ ጋር አንደ አንድ ሀገር በምትቆጠረዉ አይርላንድ ዉስጥ የተከሰተ ነዉ። ይህ ክፉ ረሃብ የተከሰተዉ እ አ አ ከ1845 እስከ 1852 ባሉት ሰባት ዓመታት ነበር። ረሃቡም ትልቁ ረሃብ ወይም የአይርላንድ የድንች ረሃብ ተብሎ ይታወቃል። በዚሁ ረሃብ የተነሣ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሰዉ ሲሞት ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጋ ደግሞ ለመሰደድ ችሏል። በተለይም የአይርላንዶች በከፍተኛ ደረጃ ወደ አሜሪካ ለመሰደድ መንስኤዉ የዚህ የከፋ ረሃብ ነበር። በዚሁ ከፍተኛ የሞትና ስደት ምክንያት የአይርላንድ ህዝቧ ብዛት በ25% ሊቀንስ ችሏል።

በአይርላንድ የተከሰተዉ የታላቁ ረሃብ በዚህና በሌሎች ምስሎች ይመሰላል። ምንጭ፤ https://www.science-photo.de/bilder/12902897-The-Irish-Famine-1845-1849-1900

ለዚህ ረሃብ መከሰት ዋናዉ መንስዔ በወቅቱ በከፍተኛ ደረጃ ለምግብነት የሚያገለግለዉ የድንች ምርት በበሽታ ምክንያት ከምርት ውጭ መሆን ነበር። ከዚህ በታች እንደሚታየዉ በሽታዉ የድንችን ተክል ብቻ ሳይሆን የሚበላዉን የድንች አካልም በከፍተኛ ደረጃ ያጠቃል። ይህ በሽታም የድንች ሌት ብላይት (Potato late blight) ተብሎ ተሰይሟል። ይህ የድንች በሽታም የዕጽዋት በሽታ ምርምር (Plant Pathology) እንዲጀመርና እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል።

ከላይ በምስሉ እንደሚታየዉ የድንች በሽታ በተክሉም ሆነ በድንቹ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። ምንጭ፤ ተክል: https://www.vegetables.cornell.edu/crops/potatoes/late-blight/  ድንች፤ https://farmtario.com/news/ontaglate-blight-in-potatoes-detected-in-norfolk-county/

ይህ ሚሊዮኖችን ለአደጋ ያጋለጠዉ የድንች በሽታ መንስኤዉ ፋይቶፍትራ ኢንፌስታንስ (Phytophtra infestans) የተባለ ረቂቅ ህዋስ እንደሆነ የታወቀዉ ቆይት ብሎ ነዉ።

ከታች በምሥሉ እንደሚታየዉ የዚህ ረቂቅ ህዋስ መነሻዉ አሜሪካ ሲሆን በሽታዉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አዉሮፓ ተሻግሮ እና የድንችን እርሻ በማውድም እ አ አ ከ1845 ጀምሮ የተከሰተዉን ረሃብ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።

ምስሉ የሚያሳየዉ የድንች ምርትን በከፍተኛ ደረጃ የጎዳዉ ፋይቶፍትራ ኢንፌስታንስ (Phytophtra infestans) የተባለው ረቂቅ ህዋስ ሥርጭትን ነዉ። መነሻዉ አሜሪካ ሲሆን ከ1845 ጀምሮ ለሰባት ዓመታት በአይርላንድ ለተከሰተዉ ከፍተኛ ረሃብ መነሻ የሆነዉ በቀዩ መስመር የሚታየዉ ነዉ። ምንጭ፤ https://elifesciences.org/articles/00731

ማጠቃለያ

ምንም እንኳ እጅግ በርካታ ምርምር በተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ቢደረግም እና አመርቂ ዉጤት ቢገኝም ፋይቶፍትራ ኢንፌስታንስን በቀላሉ በቁጥጥር ሥር ማድረግ አልተቻለም። እስከ ዛሬም ድረስ ቀላል ያልሆነ ጉዳት በድንቻችን ላይ እያደረሰ ይገኛል። ምክንያቱም ጥቃት በጀመረ ጥቂት ጊዜያት ውስጥ የድንችን ተክል ሊያወድም ይችላል። የጥቃት አድማሱንም በማስፋት በበርካታ ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። የተቀናጀ የበሽታ ቅጥጥርን ማድርግ እንደሚያስፈልግ ይመከራል። ይህም የተሻሻሉ የድንች ዝርያዎች፣ ኬሚካሎች እና በተለይም የሰብል ፈረቃ መጠቀምን ያካትታል።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም. (January 23, 2023)

አስተያየት ያስቀምጡ