ግብርናችንንለማዘመን፤ በግብርናችን ላይ የተደቀኑትን እክሎች ለመቋቋም ያለን ዝግጁነት

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡

በግብርናችን ላይ የተደቀኑትን እክሎች ለመቋቋም ያለን ዝግጁነት

ግብርናችን ለተለያዩ ሠዉ ሰራሽ እና የተፈጥሮ እክሎች ወይም ተድራጎቶች የተጋለጠ ነዉ። እነዚህም ከግብርና በሚገኙ የተለያዩ ምርቶቻችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። በተፈጥሮ ብቻ የሚከሰቱ እነዚህ የምርት ማነቆዎችን ብቻ ብንመለከት በርካታዎችን መዘርዘር ይቻላል። እነዚህም በዋናነት ከአየር ንብረት እና አፈር ጋር የተገናኙ ናቸዉ።

ከአየር ንብረት ጋር የሚገናኙት የዝናብ እጥረት ወይም መብዛት፣ የአየር ሙቀት ከተፈለገዉ በላይ መብዛት ወይም ማነስ፣ የአየር እርጥበት ከሚፈለገዉ መጠን ውጭ መሆን እና ሌሎችንም የሚያካትት ሲሆን አፈርን በተመለከተ የአፈር ኮምጣጤን፣ የአፈር ጨዋማነት፣ የአፈር መሸርሸርን፣ የአፈር ለምነትና ሌሎችንም ይጨምራል። በአየር ንብረት ለዉጥ እየተከሰቱ የመጡ እነዚህ የምርት ማነቆዎች ማየቱም እየተለመደ መጥቷል።  ከዚህ በተጨማሪ እንደ በሽታና ተባይ ያሉትም ሰብሎቻችንን ክፉኛ ይፈታተኑታል። አንዳንዶቹም ሰብሎቻችንን ከነጭራሹ የማዉደም አቅም አላቸዉ።

ምስሉ የሚያሳየዉ በጨው የተጎዳ መሬት ሲሆን የጨዉ መጠኑ ከፍተኛ በመሆኑ ለምግብነት ወይም ለሌላ አገልግሎት የሚዉሉ ተክሎችን ማብቀል አስቸጋሪ ነው። እኔም ቀደም ብዬ በሰራሁበት የመካከለኛዉ አዋሽ ባንዳነድ ሥፍራዎች በጨዉ የተጠቃ መሬት ማየት የተለመደ ነበር። ምንጭ፤ https://www.biosaline.org/news/2018-07-17-6571

በአሁኑ ጽሑፌ የእነዚህ የምርት ማነቆዎችን ዓይነትና ብዛት ለመዘርዘር ሳይሆን ከነዚህ የምርት ማነቆች ዉስጥ አንዱ ወይም ሁለቱ በከፍተኛ ደረጃ ቢከሰቱ የበለጠ ጉዳት እንዳያደርሱ ራሳችንን አዘጋጅተን አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዳለብን ላማስገንዘብ ነዉ። ባለን ልምድ እነዚህ የተፈጥሮ አደጋዎች ከጊዜ ወደጊዜ ይከሰታሉ። አንዳንዶቹም በቋሚነት አብረዉን አሉ።

ለዚህ አንዱ የመፍትሔፍ አካል ሊሆን የሚችለዉ ከዚህ በፊት በሌላ ብሎጌ የገለጽኩት የፈጣን ሰብል ማሻሻያ መንገድ ነዉ። ምክንያቱም የፈጣን የሰብል ማሻሻያ በአጭር ጊዜ ወስጥ የሚፈለገዉን ባህርይ የያዘ ዝርያ ሊያስገኝልይ ያቻላልና። በርግጥ ሌሎች ዘዴዎችም ይኖራሉ። ለሁሉም እነዚህ በቋሚነት ያሉና በደንገት የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመግታት ተዘጋጅተን መጠበቅ ይኖርብናል ብዬ እገምታለሁ።

እዚህ ላይ ከሌሎች ሀገሮች ልምድ መውሰድ እንችላለን። ለምሣሌ እ አ አ በ2011 በጃፓን ሀገር በተከሰተዉ ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ የተነሣ ወደ 20 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ የሩዝ መሬት ጨዋማ በሆነ የባህር ዉሃ ተጥለቀለቀ። መሬቱን ያጥለቀለቀዉ ውሃ ቦታውን ሲለቅ እርሻዉ ግን በጨዉ እንደተበከለ ቀረ። በሀገሪቱ የሚገኙ ሳይንስቶች ያላሰለሰ ጥረት በማድረግና ወደ ስድስት ሺህ የሚጠጉ በሙቴሽን ብሪዲንግ የተገኙ የሩዝ ዝርያዎችን በመምረጥና በመፈተሽ የአፈር ጨዋማነትን የሚቋቋም አንድ ዝርያ ለማግኘት ችለዋል። ይህ በአገሪቱ የተደቀነዉን ችግር ለመፍታት በአጭር ጊዜ የተደረገዉ ጥረትና አስደናቂ ዉጤት ለእኛም ትምህርት ሊሆነን ይችላል።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም. (January 23, 2023)

አስተያየት ያስቀምጡ