ግብርናችንን ለማዘመን፤ የኢንዱስትሪዉ አብዮትና የከፋዉ ረሃብ፤ ክፍል 1

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ፡፡

የኢንዱስትሪዉ አብዮትና የከፋዉ ረሃብ፤ ክፍል 1

በተለምዶ የኢንዱስትሪ አብዮት ተብሎ የሚታወቀዉ የሚያመለክተዉ የሰዉ ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በእጅ ከሚሰሩ የማምረቻ መንገዶች ወደ ማሽኖች እና ተጓዳች ዕቃዎችን በመጠቀም ምርታማነትን ያሳደገበት ጊዜን ነዉ። በዚሁ ወቅት የብረት ማቅለጥና ጥቅም ላይ ማዋል፣ በእንፋሎት እና በዉሃ ኃይል የሚሰሩ መሣሪያዎች ሥራ ላይ ማዋል፣ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች መስፋፋት እና ለተለያዩ ተግባራት የሚዉሉ ኬሚካሎች የተገኙት ወቅት ነዉ።

የመጀመሪያዉ የኢንዱስትሪ አብዮት የተከናወነዉ እ አ አ ከ1760 እስከ 1840 ባለዉ ጊዜ ነዉ። ይህ የመጀመሪያዉ የኢንዱስትሪ አብዮት የተጀመረውና የተስፋፋዉ በእንግሊዝ ሀገር ሲሆን በመቀጠልም በቤልጂይም እና በፈረንሳይ እንደተስፋፋ ታሪክ ያስረዳናል።  ምንም እንኳ ጀርመን በወቅቱ ለነበረዉ የእንዱስትሪ አብዮት ጠቃሚ የሆነ የድንጋይ ከሰልና የብረት ማዕድናት ቢኖራትም ወደ እንዱስትሪ አብዮት የገባችዉ ዘግይቶ ነዉ። በመቀጠልም የኢንዱስትሪዉ አብዮት ወደ አሜሪካና ጃፓን ተሸጋገረ።

ከኢንዱስትሪ አብዮት በፊት በነበረዉ ጊዜ አብዘኛዉ ሰዉ የሚተዳደረዉ በግብርና ነበር። ቢሆንም ከግብርና የሚገኘዉ ምርት አነስተኛ በመሆኑ የህዝቡ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ እንደሆነ ይገመታል። የኢንዱስትሪ አብዮት በግብርናም መስክ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። ምክንያቱም አንዳንድ ለእርሻ ተግባር የሚዉሉ ማሽነሪዎችም በጥቅም ላይ ሊዉሉ የቻሉበት ወቅት ነበርና። ለምሳሌ አነስተኛ የዘር መዝርያ ማሽን እና ማዳበሪያዎች ተፈልስፈዉ ነበር።

በአጠቃላይ በመጀመሪያዉ የኢንዱስትሪ አብዮት ከተከናወኑ ዉስጥ የሚከተሉ አበይት ፈጠራዎች ወይም ክንዉኖችይጠቀሳሉ።

በጨርቃ ጨርቅ መስክ፤ ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸዉ የጥጥ ማዳመጫና ልብስ የሚሰሩ ፍብሪካዎች ተፈልስፈዋል።

የኃይል ምንጭን በሚመለከት፤ በድንጋይ ከሰልና የእንፋሎት ጉልበት የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች፣ መርከቦችና ባቡሮች በጥቅም ላይ ሊዉሉ ችለዋል።

ብረትን ለተለያዩ ተግባራት ሥራ ላይ ማዋል፤ የትላልቅ የብረት ማቅለጫ ፋብሪካዎች መፈልሰፍና የባቡር ሀዲድ፣ መርከብ ወ ዘ ተ ለመገንባት ሥራ ላይ መዋል።

አነስተኛ ማሽነሪዎችን በሚመለከት፤ ለተለያየ አገልግሉት የሚዉሉ በርካታ ማሽነሪዎች ሊፈለሰፉና ወደ ሥራ ሊገቡ ችለዋል።

ኬሚካልን በተመለከተ፤ ለተለያዩ ተግባራት የሚያገለግሉ ኬሚካሎች የተገኙ ሲሆን እነርሱም በጨርቃ ጨርቅ፣ ማዳበሪያ፣ ሲሚንቶ ወዘተ መስክ በሰፊዉ ሥራ ላይ የዋሉበት ጊዜ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ፈጠራዎች በተለያዩ መስኮች በጥቅም ላይ ሊዉሉ ችለዋል።

ስለዚህ የኢንዱስትሪ አብዮት በሰዉ ልጆች ታሪክ አንድ ከፍተኛ እመርታ ወይም ለዉጥ የታየበት ጊዜ ነበር። ይህ በቴክኖሎጂና ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ለዉጥ ያመጣዉ ክስተት በማህበራዊና ባህላዊ ድርጊቶች ላይም የጎላ ለዉጥ ሊያመጣ ችሏል። ምክንያቱም ሠራተኞች በፋብሪካዎች ተቀጥረዉ መስራት የጀመሩበት ጊዜ በመሆኑ የኑሮ ሁኔታቸዉ ከአሰሪያቸዉ በሚከፈላቸዉ አነስተኛ ደመወዝ እንዲመሰረት የተደረበት ነበር። ተገቢ የሆነ የአሰሪና ሰራተኛ ህጎች ስላልነበሩ አሰሪዎች ሰራተኞቻቸዉን በፈለጉት ጊዜ ሊያባርሯቸዉ ይችሉ ስለነበር ከሥራ ውጭ የሆኑ ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸዉ ለከፋ ችግር ይዳረጉ ነበር።

የእንዱስትሪ አብዮትን ከሚወክሉ ምስሎች አንዱ። ምንጭ፤ https://baristaguild.coffee/blog/leaves-beans-of-history-the-industrial-revolution

ከላይ የተጠቀሱት የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ በመምጣታቸዉ እና የሰዎች በሚሰሩበት ፋብሪካዎች አቅራቢያ መስፈር ሰለነበረባቸዉ የከተሞች መመስረትና መስፋፋት ሊመጣ ችሏል። በፋብሪካዎቹ ወስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞችና ቤተሰቦቻቸውም ረከስ ያለና በቂ ምግብ ያስፈልጋቸዉ ነበር። ለዚህ እንደ መፍትሔ የተቆጠረዉ  የኢንዱስትሪ አብዮት በእንግሊዝ ሀገር ከመከሰቱ አንድ መቶ ዓምት በፊት ከአሚሪካ አህጉር ወደ አዉሮፓ አህጉር ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣዉና ምርት ውስጥ የገባዉ አንድ አስደናቂ ሰብል ነበር። እሱም ድንች ነበር። ድንች በአጭር ጊዜ ዉስጥ ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ በሆኑ እጅግ ተወዳጅነትን አትርፎ አትርፎ ነበር።

በክፍል 2 ጽሑፌ ከኢንዱስትሪዉ አብዮት ጋር በቀጥታ ባይያዝም በተዘዋዋሪ መንገድ አስተዋጽኦ ስለነበረዉ በአዉሮፓ በተለይም በአይርላንድ ስለተከሰተዉ የከፋ ረሃብ አስነብባችኋለሁ። ከድንች ጋር የሚገናኝበትንም በጽሑፌ አካትታለሁ።

እስከዛዉ መልካሙን እመኛለሁ። ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. (January 22, 2023)

አስተያየት ያስቀምጡ