ግብርናችንንለማዘመን፤ ጤፋችንን የዘከሩ ቴምብሮች

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፡፡

ጤፋችንን የዘከሩ ቴምብሮች

የፖስታ ቤት ቴምብሮች ለመጀመሪያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋሉት በእንግሊዝ በ1840 እንደሆነና ኢትዮጵያም የመጀመሪያዉን ቴምብር መጠቀም የጀመረችዉ ከ54 ዓመታት በሃላ በ1894 እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ቴምብሮች የተለያዩ ማራኪ ሥፍራዎችን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን፣ ታሪካዊ ክስተቶችን እና ወደፊት የሚከናወኑ ታላላቅ ስብሰባዎችን ለማስተዋወቅ ጥቅም ላይ ይዉላሉ፡፡ ምንም እንኳ የቴምብሮች ዓይነት በየጊዜዉ የሚለዋወጡ ቢሆንም እኔ በግሌ ብዙ ጊዜ እመለከት የነበረዉ በኢትዮጵያ በሰሜን ተራሮችና እና በባሌ ተራሮች ብቻ የሚገኘዉን የቀይ ቀበሮ ምስል የያዘዉን ነበር፡፡

ምስሉ የሚያሳየዉ ብዙ ጊዜ በኢትዮጵያ ቴምብሮች ላይ እመለከት የነበረዉን ቀይ ቀበሮ ወይም ሰሜን ቀበሮን ነዉ፡፡

ነገር ግን ላለፉት በርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ በርካታ የተለያዩ ዓይነት ቴምብሮችን ማሳተሟና ሥራ ላይ ማዋሏ እሙን ነዉ፡፡ በተለያዩ ሀገራት በርካታ ሰዎች ቴምበር ማሰባሰብ ላይ ፍላጎት ያላቸዉ ሲሆን በኢትዮጵያም በትርፍ ጊዜያቸዉ ቴምብር መሰብሰብ የሚያስደስታቸዉ ሰዎች አሉ፡፡

እኔም የዛሬ 33 ዓመት እ አ አ በ1990 የኢትዮጵያ ፖስታ ቤት ካሳተማቸዉ ቴምብሮች መካከል ጤፍን በተመለከተ የታተሙትን አምስት ቴምብሮች ይመለከታል፡፡ ጤፍን በተመለከተ የታተሙ ቴምብሮች ከዚያ በላይ ሊሆኑ ቢችሉም እኔ ቴምብሮቹን ያገኘሁት የዛሬ 30 ዓመት ገደማ የጤፍ ተመራማሪ በነበርኩ ጊዜ ነዉ፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ እነዚህ አምስት ቴምብሮች ከኔ ጋር ናቸዉ፡፡ እኔም የጤፍ ምርምሬን ቀጥዬበታለሁ፡፡

ከዚህ በታች በምስሉ እንደሚታየው አምስቱ ቴምብሮች የተለያዩ ተግባራትን ይወክላሉ፡፡ ቴምብሮችም 5፣ 10፣ 20፣ 75 እና 85 ሳንቲም ዋጋ ነበራቸዉ፡፡

በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት እ አ አ 1990 የታተሙ ጤፍን በተመለከተ የታተሙ አምስት ቴምብሮች

ማጠቃለያ

የፖስታ አገልግሎት ጤፍን በተመለከተ ሌሎች ቴምብሮችን አሳትሞ ከሆን መረጃ የለኝም፡፡ ቢሆንም እነዚህ አምስት ቴምብሮችም ቢሆኑ ጤፍን ለመላዉ ዓለም ለማስተዋወቅ ከፍትኛ ድርሻ አላቸዉ፡፡ እንደሚታወቀዉ ሁሉ ጤፋችን ብዙ የምንወድለት ባህርያት እንዳሉት ሁሉ አንዳንድ መሻሻል ያለባቸዉ ባህርያትም አሉት፡፡ መሻሻል ካለባቸዉ ዉስጥ በዋናነት የምጠቀሱት በሄክታር የሚገኘዉ ምርት አነስተኝነትና የምርጥ ዝርያዎች አብዘኛዉ ገበሬ ዘንድ አለመድረሳቸዉ ነዉ፡፡ ስለዚህ የጤፍን ምርት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ በምርምር፣ በልማት እና ፖሊሲ የተሳተፍን ሁሉ በጋራ በመስራት የጤፍ ምርትን ማሳደግ ይኖርብናል፡፡ ምርቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ካለበት 18 ኩንታል በሄክታር ከፍ እንደሚል ጥርጥር የለኝም፡፡ ምክንያቱም ምርጥ ዝርያንና አስፈላጊዉን ግባት የተጠቀሙ ገበሬዎች በሄክታር እስከ 35 ኩንታል ማምረት ችለዋልና፡፡

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥር 12 ቀን 2015 ዓ.ም. (January 20, 2023)

አስተያየት ያስቀምጡ