በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፡፡
ፈጣን የሰብል ማሻሻያ (Speed Breeding)፤ ክፍል 2
በክፍል 1 ጽሑፌ የሰብል ማሻሻያ በማድረግ አንድን ዝርያ ለማስለቀቅ ቢያንስ ከ10 እስከ 12 ዓመታት እንደሚፈጅ ጽፌ ነበር። በዛሬዉ ጽሑፌ የሰብል ማሻሻያ የሚወስደዉን ይህን ረጅም ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳጠር የሚረዳዉንና ፈጣን የሰብል ማሻሻያ (Speed Breeding) ተብሎ ስለተሰየመዉ አስደናቂ ፈጠራ አስነብባችኋለሁ።
ይህ የ Speed Breeding መንገድ ለመጀሪያ ጊዜ ሪፖርት የተደረገዉ የዛሬ አምስት ዓመት ከተለያዩ ሀገራት የተዉጣጡ 29 ተመራማሪዎች በጋራ ባሳተሙት ጽሑፍ ነዉ። ጽሑፉም የሚከተለዉ ነዉ፡፡ Ghosh et al. 2018. Seed breeding in growth chambers and glasshouses for crop breeding and model plant research. Nature Protocols 13: 2944–2963.
የዚህ ዉጤት ዋናዉ ሚስጥሩ ተክሎችን በየቀኑ ለረጅም ጊዜ ብርሃን በመስጠት አበባ ለማበብ እና ፍሬ ለማፍራት የሚወስድባቸዉን ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ማሳጠር ነዉ። የዚህ ፈር ቀዳጅ ሥራ ዉጤታማ የሆነዉ ለማበብ ረዘም ያለ ብርሃን በሚያስፈልጋቸዉ (ወይም long-day በሚባሉ) ሰብሎች ነዉ። የዚህ ምርምር ሥራም long-day ከሆኑት ሰብሎች መካከል በስንዴ፣ ሲናር፣ ሽምብራ፣ አተር እና ጓያ ላይ አመርቂ ውጤት አሳይቷል።
Speed Breeding ዉጤታማ የሚሆነዉ ተክሎችን የተለያዩ የአየር ሁኔታችን መቆጣጠር የሚቻልበት ሥፍራ በማሳደግ ሲሆን በዋናነት ቁጥጥር የሚደረግባቸው የብርሃን ዓይነትና ጥራት፣ የብርሃን ርዝመት ወይም ርዝመት፣ የአየር ሙቀት እና የአየር እርጥበት ናቸዉ።
- የብርሃን ዓይነትና ጥራትን በሚመለከት በተለምዶ PAR የሚባለውንና 400 እስከ 700 nm ሲሆን ሰማያዊ፣ ቀይ እና ፋር ቀይ የተባሉትን ያካትታል። የአምፑሎች ዓይነትም LEDs ወይም LED እና ሃሎጅን የሚባሉት ናቸዉ፡፡
- የብርሃን ጊዜ ደግሞ 22 ሰዓት ብርሃንና ሁለት ሰዓት ብቻ ጭለማ ይሆናል ማለት ነዉ።
- የአየር ሙቀት ደግሞ በ22 ሰዓቱ የብርሃን ጊዜ 22 ድግሪ ሴንቲግሬድ ሲሆን በተቀረዉ የሁለት ሰዓት የጭለማ ጊዜ 17 ድግሪ ሴንቲግሬድ ነዉ።
- የአየር እርጥበት ከ60 እስከ 70% መካከል ያለዉ ተስማሚ ነዉ።
ከላይ የተገለጹት መስፈርቶች በመጠቀም speed breeding በተወሰኑ ሰብሎች ላይ አመርቂ ውጤት ሊያስገኝ ችሏል። ከዚህ በታች በሥዕሉ እንደሚታየዉ 22 ሰዓት ብርሃን በመጠቀም በአንድ ዓመት ብቻ እስከ 6 ጊዜ የስንዴ፣ የገብስ ወይም የሽንብራ ዘር ማጨድ እንደሚቻል ሲሆን የሰብል አዳቃዮች በተለምዶ በሚጠቀሙበት መንገድ ግን በዓመት ሊገኝ የሚችለዉ ሶስት ጊዜ ብቻ ነዉ። ስለዚህ የ speed breeding መንገድ በክፍል አንድ ለገለጽኩት single seed descent (ነጠላ ዘር መዉረድ) መንገድ እጅግ አመቺ ነዉ፡፡

ከላይ በምሥሉ በግራ በኩል የሚታዩት 22 ሰዓት ብርሃን እና 2 ሰዓት ጭለማ በመጠቀም 6 የስንዴ፣ ገብስ ወይም ሽምብራ ሰብሎችን በአንድ ዓመት ማግኘት እንደሚቻል ነዉ፡፡ በቀኝ በኩል የሚታዩት ደግሞ በተለምዶ መንገድ ሊመረት የሚቻለዉ በዓመት ሶስት ሰብሎች መሆኑን ነዉ፡፡ ምንጭ፤ በከፊል የተወሰደዉ ከ Ghosh et al. 2018. Seed breeding in growth chambers and glasshouses for crop breeding and model plant research. Nature Protocols 13: 2944–2963 ነዉ፡፡
የዚህ የፈጣን ሰብል ማሻሻያ መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ ሪፖርት ከተደረገበት እ አ አ 2018 ጀምሮ ከፍተኛ አድናቆትንና ተቀባይነትን ያተረፈ ሲሆን በተለያዩ ሰብሎች የሚሰሩ ተመራማሪዎች ስብሎቻቸዉን በአጭር ጊዜ ለማሻሻል እንዲያስችላቸዉ መጠነኛ ለውጥ በማድረግ ብቻ ውጤታማ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ ለምሳሌ cowpea (ላም አተር) ላይ የተደረገዉ ሙከራ እንደሚያሳየዉ እስከ ስምንት ስብሎችን በአንድ ዓመት ሊያገኙ ችለዋል፡፡ ምንጭ፣ Edet and Ishil. 2020. Plant Methods 18:106.
ምንም እንኳ የመጀመሪያ ሥራዎች እንደሚያሳዩት ይህ ፈጣን የሰብል ማሻሻያ መንገድ ዉጤታማ የሆነዉ ረዘም ያለ የብርሃን ሰዓት ለሚያስፈልጋቸዉ ሰብሎች ብቻ ቢሆንም የተወሰኑ የብርሃን ሁኔታዎችን በማስተካከል አጠር ያለ የብርሃን ሰዓት ለሚያስፈልጋቸዉ ሰብሎችም ተግባራዊ ሊሆን ችሏል፡፡ በዚሁ መሠረት አጠር ያለ ብርሃን በሚያስፈልጋቸዉ እንደ ሩዝ፣ አኩሪ አተር እና አማራንተስ ላይ በመስራት እስከ አምስት ሰብሎችን በዓመት ለማጨድ ተችሏል፡፡ ምንጭ፤ Jähne et al. 2020. Theoretical and Applied Genetics 133: 2335-2342.
የዚህ የፈጣን የሰብል ማሻሻያ መንገድ ያለዉን ከፍተኛ ጥቅም በመረዳት የሰብል ተመራማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ ሀገራትም ማዕከል እስከማቋቋም ደርሰዋል፡፡ ለምሳሌ የህንድ መንግሥት በቅርቡ SpeedBreed የሚባል ማዕከል ቫራናሲ በሚባል ሥፍራ አስመርቋል፡፡

በህንድ ጠቅላይ ሚኒስቴር ተመርቆ ሥራዉን የጀመረዉ የፈጣን ሰብል ማሻሻያ ማዕከል ይህን ይመስላል፡፡ ማዕከሉ በዉስጡ ለፈጣን የሰብል ማሻሻያ የሚያገለግሉ በርካታ ክፍሎች አሉት፡፡ ምንጭ፤ https://www.irri.org/news-and-events/news/speedbreed-crop-breeding-center-built-speed
ማጠቃለያ
የፈጣን ሰብል ማሻሻያ ጥቅምን ከላይ ለመግለጽ ሞክሬአለሁ፡፡ ዋናዉ ጥቅሙ የሰብል ማሻሻያ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ማጠሩ ነዉ፡፡ በተለይም ድንገተኛ እክሎች ለምሳሌ የሰብል በሽታ ቢከሰት ባፋጣኝ የማዳቀል እና የሰብል ማሻሻያ ፕሮግራሞችን እንድናከናዉን ይረዳናል፡፡ የዚህ የፈጣን ሰብል ማሻሻያ እንድንጠቀም የሚረዳን መሰረተ ልማት በሀገራችን እስካሁን ድረስ የለም፡፡ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያስፈልግ ግን ጥርጥር የለኝም፡፡ ለምሳሌ ሰብሎቻችን በተደጋጋሚ ለበሽታዎች ይጠቃሉ፡፡ በተለይም ይህ ጥቃት በስንዴዎቻችን ላይ ይጠናል፡፡ ዋግ የሚባላዉ በሽታ መልኩንና ባህርዩን እየቀያየረ በቅርቡ ጸድቀዉ የወጡ ዝርያዎችንም ጭምር ሳይቀር በከፍተኛ ደረጃ ያጠቃል፡፡ ገበሬዎቻችንም ያለ ምርት ያስቀራቸዋል፡፡ ስለዚህ ቢያንስ አንድ የፈጣን ሰብል ማሻሻያ ማዕከል በብሔራዊ ደረጃ ማቁቋም አስፈላጊ አይደለም ትላላችሁ? በኔ አስተያየት አስፈላጊ ነዉ እላለሁ፡፡
በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥር 11 ቀን 2015 ዓ.ም. (January 19, 2023)