ግብርናችንንለማዘመን፤ፈጣን የሰብል ማሻሻያ (Speed Breeding)፤ ክፍል 1

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ፈጣን የሰብል ማሻሻያ (Speed Breeding)፤ ክፍል 1

የሰብል ተመራማሪዎች በዋናነት ትኩረት አድርገዉ የሚሰሩት የሰብል ምርት እንዲያድግ ነው፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለዉ የምርት ማነቆ በሆኑት ላይ ትኩረት በማድረግ ነዉ፡፡ እነዚህ የምርት ማነቆዎች ወይም ተዳርጎቶች በርካታ ቢሆኑም በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል ድርቅ፣ የዉሃ ማቆር፣ ሙቀት፣ የሰብል መጋሸብ ወ ዘ ተ ን ያካትታሉ፡፡

እንደሚታወቀዉ ሁሉ ሰብሎቻችንን ለማሻሻል በርካታ መንገዶች አሉ፡፡ እስካሁን ድረስ በሰፊዉ በጥቅም ላይ የዋሉት የመረጣ (selection) እና የማዳቀል (hybridization) መንገዶች ናቸዉ፡፡ የማዳቀል ሥራ የሚሰራዉ የተለያዩ ባህርይ ያላቸዉን ሁለት ተክሎች በማጣመር ሁለቱም ጥሩ ባህርያት በሰብላችን ውስጥ እንዲካተት ለማድረግ ታስቦ ነዉ፡፡ ለምሳሌ  የዛሬ 15 አመት ገደማ በብሄራዊ የዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ ጸድቆ የወጣውና በአምራቾች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈዉ ቁንጮ የተባለዉ የጤፍ ዝርያ የተገኘዉ የተለያዩ ባህርይ ያላቸዉን ሁለት የጤፍ ዝርያዎችን በማዳቀልና መጠነ ሰፊ መረጣ በማካሄድ ነዉ፡፡ ሁለቱ ለዚህ አገልግሎት የዋሉት የጤፍ ዝርያች ዱከም እና ማኛ ይባላሉ፡፡ የዱከም ዝርያ ከፍ ያለ ምርት የሚሰጥ ሲሆን የፍሬው መልክ ነጣ ያለ ቢሆንም በሸማቾች ዘንድ ያለዉ ተቀባይነት አነስተኛ ነዉ፡፡ በሌላ በኩል ማኛ የተባለዉ ዝርያ ስሙ እነደሚያመለክተዉ ፍሬዉ እጅግ በጣም ነጭ በመሆኑ በተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አለዉ፡፡ ነገር ግን የዚህ ዝርያ ምርት አነስተኝ ነዉ፡፡ ስለዚህ በሥራዉ የተሳፉት የጤፍ ተመራማሪዎች ዋና አላማ አድርገዉ የተነሱት ሁለቱን የጤፍ ዝርያዎች በማዳቀልና በተለያዩ ወካይ የጤፍ አብቃይ ሥፍራዎች በመፈተሽ ፍሬዉ እንደማኛ ነጭ፣ ምርቱ ደግሞ እንደ ዱከም ከፍ ያለ ለማግኘት ነበር፡፡ በርግጥ ሥራቸዉ መና አልቀረም፡፡ እንዳሰቡት ሆኖላቸዉ ሁለቱንም ጥሩ ባህርይ የያዘ ቆንጮ የሚባል ዝርያ እ አ አ በ2006 ለማስለቀቅ ችለዋል፡፡

ከማዳቀል አንስቶ ዝርያ እስከማጸደቅ ባለዉ ሂደትም የተለያዩ ተመራማሪዎች የተለያየ መንገድ ይጠቀማሉ፡፡ ለምሳሌ የብሄራዊ የጤፍ ምርምር ነጠላ ዘር መውረድ (single seed descent) የሚባለዉን መንገድ የጠቀማል፡፡ ከዚህ በታች በሥእሉ እንደሚታየዉ በዚህ መንገድ ከተጠቀምን ዝርያ ከማጸደቃችን በፊት እስከ ከ11 እስከ 12 የሰብል ወቅቶች ይፈጃል፡፡ በዚህ የሰብል ማሻሻያ መንገድ ለምንፈልገዉ ባህርይ የምንመርጠዉ ከሰባተኘዉ ወቅት በኋላ በመሆኑ እስከ ስድስተኛዉ ወቅት ድረስ አንድ ዘር ብቻ በመዉሰድ ወደ ሚቀጥለዉ ደረጃ እናስተላልፋለን ማለት ነዉ፡፡ በዚሁ መሰረት እስከ ስድስተኛዉ የሰብል ወቅት ወይም ደረጃ ያሉትን በመስታወት ቤት በማሳደግ ወይም በመስኖ በመጠቀም በአመት ሁለቴ ወይም ሶስቴ በማሳደግ የሚያስፈልገዉን ጊዜ ማሳጠር ይቻላል፡፡ ነገር ግን PVT and NVT የሚባሉት በአገሪቱ ወካይ በሆኑ ሥፍራዎች ስለሚፈተሹና አብዘኞቹ ሥፍራዎች የመስኖ አቅርቦት ስለሌላቸዉ በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ለማሳደግ እንገደዳለን፡፡

ከላይ በምሳሌነት  እንደሚታየዉ ጠላ ዘር መውረድ (single seed descent) መንገድ ከማዳቀል ጀምሮ እስከ ዝርያ ማጽደቅ ያለዉ ሂደት እስከ 12 የሰብል ወቅት ወይም አመታት ይፈጃል፡፡ በመስኖ የመጠቀም እድሉ ካለ በአመት ሁለት የሰብል ወቅቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ አንድ ዝርያ ለማዉጣት የሚፈጀዉ ጊዜ በተወሰነ አመታት ሊያጥር ያችላል፡፡

ምንጭ፣ ተሻሽሎ የተወሰደ Chanyalew et al. 2019. Tef (Eragrostis tef) breeding. In: Al-Khayri JM, Jain SM, Johnson DV (Eds.), Advances in Plant Breeding strategies: cereals. Springer Nature AG.

ምንም እንኳ ይህ የ single seed descent ሆነ ሌሎች የሰብል ማሻሻያ መንገዶች ጠቃሚ ቢሆኑም እና በርካታ የተለያዩ ሰብሎችን ዝርያ ለማስለቀቅ ከፍተኛ አስተዋጸዖ ቢያደርጉም ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስዱ በመሆኑ ለድንገተኛ (emergency) ወቅት ላይደርሱ ይችላሉ፡፡ በተለይም ሰብሎቻችንን በድግግሞሽ የሚያጠቁ በሽታዎችን ለመግታት ያዳግታል፡፡ ምክንያቱም የማሻሻያዉ ፕሮግራም በሂደት ላይ እያለ በሰብሎቻችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ ይችላል፡፡

በዚሁ መሰረት የሰብል ማሻሻያ የሚወስደዉን ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳጠር በተደረገዉ ጥረት በቅርቡ ጥሩ ዜና ደርሶናል፡፡ ይህም ፈጣን የሰብል ማሻሻያ (Speed Breeding) ተብሎ ተሰይሟል፡፡ እኔ በክፍል 2 ስለዚሁ ፈጣን የሰብል ማሻሻያ በሰፊዉ አስነብባለሁ፡፡

እስከዛዉ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. (January 16, 2023)

አስተያየት ያስቀምጡ