ግብርናችንን ለማዘመን፤ የቆላ ስንዴን በመስኖ ያስተዋወቁን ፤ ዶ/ር ጀማል መሐመድ፤ ክፍል 3

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የቆላ ስንዴን በመስኖ ያስተዋወቁን ፤ ዶ/ር ጀማል መሐመድ፤ ክፍል 3

በዛሬዉ ጽሑፌ ከዶ/ር ጀማል መሐመድ ጋር ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጋራ ልንሰራ ስላቀድነዉ የምርምር ፕሮግራምና ስለገጠመን አስደንጋጭ ክስተት አስነብባችኋለሁ።

የዛሬ አራት ዓመት ገደማ እ አ አ በፍብሪዋሪ 2019 የድሮ አለቃዬ የነበሩትን ዶ/ር በዳዳ ግርማን ለማግኘት ወደ ቁሉምሳ አሰላ ለመሄድ ጉዞ ስጀምር በዚያን ቀን አዳማ እንዳሉ ሰለነገሩኝ እኔም ጉዞዬን ወደአሉበት ሥፍራ አደረኩ። ዶ/ር በዳዳንም የቅርብ ጓደኛቸው ከሆኑት ከዶ/ር ጀማል ጋር በዶ/ር ጀማል ቤት ሲጨዋወቱ አገኘኋቸሁ። እኔም በዚያች አጋጣሚ ለ34 ዓመታት የተለኋቸሁን ዶ/ር ጀማልን ለማግኘት ዕድሉ ገጠመኝ። በአዋሽ በረሃ ውስጥ በሚገኘዉ የመልካ ወረር እርሻ ምርምር ማዕከል የያኔዉ አቶ ጀማል ለዶክትሬታቸዉ ማሟያ ይሆን ዘንድ በቆላ ስንዴ ላይ ምርምር ሲሰሩ እኔም ከዩኒቨርስቲ በባችለር ተመርቄ በዚሁ ሰብል ላይ አብሬአቸዉ እንድሰራ የተመደብኩበት ዓመት ነበር።

የኛ ምረቃ በመደበኛዉ የምረቃ ጊዜ የተከናወነ አልነበረም። በ1977 (ወይም እ አ አ በ1984) በሀገራችን በተከሰተዉ ከፍተኛ ረሃብ መሰረት በድርቅና ረሃብ የተጎዱ ዜጎቻችንን በምዕራቡ የሀገራችን ክፍል ለማስፈር መንግሥት ባወጣዉ ዕቅድ መሰረት በሀገሪቱ ያሉ ዩኒቨርስቲዎች በሙሉ ተዘግተዉ ለሰፋሪዎች በዘመቻ ቤት እንድንሰራ ተላክን። የኛ አለማያ ኮሌጅም የካራማራ ብርጌድ ተብሎ ጋምቤላ በሚገኘዉ የጊሎ አቦል ሥፍራ ተመደብን። ለሶስት ወራት በዘመቻዉ ከቆየንና የጎደለብንን የትምህርት ክፍል ካሟላን በኋላ የተመረቅነዉ በታህሳስ 1978 (እ አ አ ዲሴምበር 1985) ነበር። በዚህ ምክንያት ነዉ እኔም ወደ አዲሱ የምርምር ማዕከሌ ስሄድ ያጋጠመኝ በመስክ ላይ ያለ የስንዴ ማሳ የሆነዉ። ያለበለዚያ በመደበኛዉ ወቅት ብንመረቅ ኖሮ የጥጥ ማሳ ነበር የሚጋጥመኝ። ምክንያቱም የስንዴ ተክል በመደበኛዉ የሰብል ወቅት ያለዉን ከፍተኛ ሙቀት መቋቋም ስለማይችል ነዉ።

ዶ/ር ጀማልም ከረጅም ጊዜ የውጭ ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዉ ወልጀጂ የግብርና ኢንዱስትሪ (Woljeejii Agricultural Insdustry PLC, WAI) የሚባል ጽ/ቤቱ ቢሾፍቱ የሆነ ድርጅት ከፍተዉ እ አ አ ከ2015 ጀምሮ እየሰሩ እንደሆነ ገለጹልኝ። ዶ/ር ጀማልም የድርጅቱ ማናጄርና አሰልጣኝ ሲሆኑ ድርጅታቸዉም ትኩረት አድርጎ የሚሰራዉ ጠቃሚ የሆኑ ረቂቅ ህዋሳት (effective microorganisms) ወይም በአጭሩ EM በመጠቀም ነዉ። በዚሁ መስክ በመሥራት ላይ ያሉትን ሥራቸዉን አስጎቡኝ። ይህ EM ቴክኖሎጂ በተለያዩ መስኮች ተግባራዊ ይሆናል። ከነዚህም ውስጥ የዶሮች መኖ፣ የከብቶች መኖ፣ ቆዳና ሌጦ ዝግጅት እንዲህም የአፈር ለምነት ለማሳደግ ጥቅም ላይ ይዉላል። በለተይም በዚህ መስክ የሚዘጋጁት የተለያዩ ዉጤቶች አካባቢያችንን ከመበከል የነጹ ናቸዉ ማለት ይቻላል። ዶ/ር ጀማልም ክሚመለከታችዉ መንግሥታዊ ድርጅቶች እዉቅናና ፍቃድ ተሰጥቷቸዉ ይሰሩ ነበር።

እኔም የዶ/ር ጀማል EM ቴክኖሎጂ የጤፍ ምርትን ሊያሳድግ የሚችልበትን በተለይም ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ጥቅም ላይ የሚዉልበትን መንገድ በጋራ ማጥናት የሚቻል ከሆነ ብዬ በጠየኳቸዉ ጊዜ ፍቃደኛ ሆነዉ በመገኘታቻዉ አዲስ ፕሮጀከት ነድፈን መንቀሳቀስ ጀምረን ነበር። EM ቴክኖሎጂ በሰብል ማሻሻያ ላይ ያለዉን አቅምና ተስፋ ወደፊት አስነብባችኋለሁ።

በጋራ ለምንሰራዉ አዲሱ ፕሮጀክታችንም የተለያዩ ግባቶችን በማጠናቀርና ከሚመለከታቸዉ ተሳታፊ ግለሰቦች መረጃዎችን በማሰባሰብ ላይ ነበርኩ። ዶ/ር ጀማልም ፌብሪዋሪ 1፣ 2021 በተጻፈ ኢሜላቸዉ ጠቃሚ መረጃዎች ልከዉልኝ ነበር።

ይህ በዚህ እንዳለ እ አ አ ማርች 2፣ 2022 (ማለትም የዛሬ 10 ወር) በተጻፈ ኢሜል ዶ/ር ጀማል በጠና እንደታመሙ ተነገረን። እኔም የዛሬ 37 ዓመት ወደ ሥራ ዓለም ስገባ የስንዴ ምርምርን ያስተዋወቁኝ እኝህ ከፍተኛ ተመራማሪን በህመማቸዉ ምክንያት ላናግራቸዉ ባልችልም ልጃቸዉንና የቅርብ ጓደኛቸዉ የሆኑትን ዶ/ር በዳዳን ለማነጋገር ቻልኩ። ዶ/ር ጀማል በሆስፒታል እርዳታ ሲደረግላቸዉ ቆይቶ እ አ አ ማርች 27፣ 2022 በተወለዱ 76 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩን። በ EM ቴክኖሎጂ በርካታ ሥራዎች ለመሥራት ዕቅድ የነበራቸዉ እኚህ ጠንካራ ሰዉ እስከ ወዲያኛዉ አሸለቡ።

በጋራ ልንሰራ ላቀድነዉ ፕሮጀክት ብለዉ ዶ/ር ጀማል ከሁለት ዓመት በፊት ያጋሩኝን አጭር የህይወት ታሪካቸዉን ከዚህ በታች አቀርባለሁ።

የትዉልድ ጊዜ፤ ሜይ 18፣ 1946 (እ አ አ)

የትዉልድ ሥፍራ፤ ጎሬ

የትምህርት ዝግጁነት

  • ዲፕሎማ (1967 እ አ አ) በአጠቃላይ እርሻ፤ ከጂማ የእርሻና ቴክኒክ ት/ቤት
  • ባችለር (1972 እ አ አ) በዕጽዋት ሳይንስ፤ ከእርሻ ኮሌጅ፣ ቀደማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርስቲ
  • ማስትሬት (1977 እ አ አ) በዕጽዋት ማዳቀል፡ ከኖርዝ ካሮሊና ዩኒቨርሲቲ፣ አሜሪካ
  • ፒ ኤች ዲ (1989 እ አ አ) በዕጽዋት ማዳቀልና አግሮኖሚ፤ ዩስቲስ ሊቢግ ዩኒቨርስቲ፣ ጀርመን

የሥራ ልምድ

  • 1972 – 1989 (እ አ አ) ተመራማሪ፤ በእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት
  • 1989 – 1991 (እ አ አ) ከፍተኛ ተመራማሪ፤ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ናይሮቢ፣ ኬንያ
  • 1991 – 1997 (እ አ አ) ከፍተኛ ሌክቸረር፤ ናሽናል ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሌሴቶ
  • 1997 – 2015 (እ አ አ) ተባባሪ ፕሮፈሰር፤ ናሽናል ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሌሴቶ
  • 2015 – 2022 (እ አ አ) ማናጄር እና አሰልጣኝ፤ WAI አዳማ

በማስተማር መስክ፤ የተለያዩ ኮርሶችን በዩኒቨርስቲ ደረጃ አስተምረዋል

በምርምር መስክ፤ በተለያዩ ሰብሎችና ሀገሮች የተሳተፉ ሲሆን እነዚህም ስንዴ፣ ማሽላ እና ድንችን ያካትታል

ያጸድቋቸዉ ዝርያዎች ብዛት፤ 9 (ስንዴ፣ ማሽላ፣ በቆሎ፣ ነጭ ሽንኩርት)

የማማከር ሥራ፤ በርካታ ናቸዉ

በሥራቸው ምክንያት የጎበኟቸዉ ሀገራት ብዛት፤ 26

ያሳተሟቸዉ ጽሑፎች ብዛት

  • 11 ቴክኒካል ሪፖርቶች
  • 13 የጆርናል ወረቀቶች
  • 22 የኮንፈረንስ ወረቀቶች

በዚሁ ስለ ዶ/ር ጀማል የጻፍኳቸዉን ብሎጎቼን አበቃለሁ።

ለወዳጆቻቸዉና ዘመዶቻቸዉ መፅናናትን እመኛለሁ።

በሌላ ጽሑፍ እስከምንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ታህሳስ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. (December 26, 2022)

አስተያየት ያስቀምጡ