በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤
የቆላ ስንዴን በመስኖ ያስተዋወቁን ፤ ዶ/ር ጀማል መሐመድ፤ ክፍል 1
መስኖን በመጠቀም የቆላ ስንዴ ምርምርን በመካከለኛዉ አዋሽ ከመጀመራቸዉ ቀደም ብሎ ዶ/ር ጀማል መሐመድ በደጋዉ የሀገራችን ክፍል በስፋት በሚመረተዉ ስንዴ ምርምር ላይ ከፍ ያለ ልምድ አካብተዉ ነበር። የሶስተኛ ድግሬያቸዉን በጀርመን ሀገር ለመማር ዕድል ሲያገኙ ለዚሁ ማሟያ የሚሆን የምርምር ሥራቸዉን ከላይ በጠቀስኩት መስክ ለመሥራት አቀዱ፣ ለተግባራዊነቱም ተንቀሳቀሱ። ጊዜዉ እ አ አ በ 1985 የዛሬ 37 ዓመት መሆኑ ነዉ።
በዚሁ መሠረት የቆላ አየር ንብረት ወደ ሚወክለዉና የአዋሽ ወንዝን በመስኖ በመጠቀም የተለያዩ ሰብሎችን የሚያመርተውን የመልካ ወረር እርሻ ምርምር ማዕከል (ባሁኑ አጠራር የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል)ን መረጡ። በወቅቱ የወረር ማዕከል የታወቀዉ በሰብሎች (ጥጥ፤ ኦቾሎኒ፤ ሰሊጥ)፣ በመስኖ፣ በአፈር እና በእንስሳት ምርምር ላይ ነበር። ከላይ የተጠቀሱት ሰብሎች ሞቃታማ የአየር ፀባይ ስለሚስማማቸዉ በዋናዉ የሰብል ወቅት በመስክ ላይ ምርምራቸዉ ይከናወናል። በአካባቢዉ ያሉ ስፋፊ የመንግሥት እርሻዎች ደግሞ ትኩረት አድርገዉ የሚሰሩት በጥጥ ላይ ነበር። በወቅቱ በመካከለኛው አዋሽ የነበሩት የወረር፣ የመልካ ሰዲ፣ የአሚባራ (የዕርዳታ ማስተባበሪይ ኮሚሽን የሚያስተዳድረዉ) እና ወደ 100 ኪሜ ራቅ ብሎ የሚገኘዉ የአሚባራ እርሻ የሚባሉ ሲሆን በኔ ግምት በድምሩ ወደ 10 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ ጥጥ ያበቅሉ ነበር። ቀስ በቀስ መሬቱ በጨዉ እየተበላ ከመቸገሩ በፊት የመልካ ሰዲ እርሻ የሙዝ እርሻም ነበረዉ። በታችኛዉ አዋሽ ሥር በዱብቲና አሳይታ አካባቢ የነበሩት እርሻዎችም ሰፋፊ የጥጥ እርሻዎች ነበሯቸዉ።
ሳላደንቀዉ የማላልፈዉ ነገር በዚያን ጊዜ የነበሩት የመንግሥት እርሻዎች ማሳዎቻቸው እጅግ ማራኪ መሆኑ ነዉ። ከጥጥ ለቀማ በስተቀር የተቀሩት የእርሻ ከንዋኔዎች ዘመናዊነትን የተላበሱ ነበር፤ ማለትም ሜካናዜሽን ይጠቀሙ ነበር ማለት ይቻላል። በእርሻ ምርምር ማዕከል የነበርን የሥራ ባልደረቦች በመንግሥት እርሻ በነበሩ ማሳዎች ጥራት እንቀና ነበር ብል የዋሸሁ አይመስለኝም። ምክንያቱም የእኛ ማሳዎች አንዳንዴ ዘመናዊነት ይጎድላቸዋል። ለዚሁም ዋናዉ መንስዔ እኛ ሙከራ የምናካሄደዉ እጅግ አነስተኛ በሆነ ማሳ ላይ ስለሆነ በሜካናዜሽን ልንሰራ ሁኔታዉ ሰለማይፈቅድልን ነዉ።
ሌላዉ አስደናቂ ነገር እያንዳንዱ የመንግሥት እርሻ የማሳ ኃላፊ ነበረዉ። ይኸ ኃላፊ ያለመታከት ማሳዉን በሞተር ብስክሌት ማየት የቀን ሥራዉ ብቻ ሳይሆን የሰዓታት ተግባሩ ነበር። ማሳዎቹ የመስኖ ውሃ እጥረትም ሆነ ብዛት ካለበት በቅርበት ያያል፣ ለመፍትሔውም በፍጥነት ይንቀሳቀሳል። ከሁሉም በላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚደረገዉ በተባይ ላይ ነው። የጥጥ ተክል በተለይ ጥጡን የያዘዉ እምቡጥ በከፍተኛ ደረጃ በተባይ ይጠቃል። እንደ ቦል ወርም (boll worm) ጥጥን በተደጋጋሚ የሚያጠቃ፣ ተመራማሪዉንም ሆነ የልማት ሰራተኛዉን የሚፈታተን እንዲሁም የልማት መሥሪያ ቤቱን ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ ያለ አይመስለኝም። ምክንያቱም በአንድ የስብል ወቅት ብቻ በርካታ ርጭቶች ማድረግ ስለሚያስፈልግ ነዉ።
የምርምር ማዕከላችን እና የመንግሥት እርሻዎች በቅርበት እንሰራ ነበር። እርሻዎቻቸውንም የእኛ የተባይ ጥበቃ ክፍል ባልደረቦች በየጊዜዉ ይጎበኙ ነበር። ከማሳዎች በሚወሰዱ ናሙናዎች ላይ በመመርኮዝ ስለ ተባይ አመጣጥ ትንበያ ያደርጋሉ። ይህም ወቅታዊ ርጭት እንዲደረግ ይረዳል። ከዚህ በተጨማሪ በማዕከላችን የተዋቀረዉና እኔም የአግሮኖሚ ዘርፍን በመወከል አባል የሆንኩበት የብሔራዊ የጥጥ ምርምር ቡድን በመካከለኛዉም ሆነ በታችኛዉ አዋሽ በሚገኙ እርሻዎች ጉብኝትና ግምገማ ያደርግ ነበር።
የወረርን ነገር ስነሳ ስለ ቆላ ስንዴና የዶ/ር ጀማል አስተዋጽኦ የጀመርኩትን ዘነጋሁ። ታዲያ ነገሩ እንደዚህ ነዉ።
በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት በመደበኛዉ የሰብል ወቅት በመካከለኛዉም ሆነ በታችኛው አዋሽ ስንዴን ለመዘራት አይቻለም። የዶ/ር (በወቅቱ አቶ) ጀማል ምርምር ዓላማም በመደበኛዉ የሰብል ወቅት ስንዴ ለመዝራት አይደለም። ዋናዉ የዶ/ር ጀማል ዓላማ በዋናው የሰብል ወቅት ጥጥ ከተዘራና ለቀማ ከተከናወነ በኋላ መሬቱ ታርሶና ለስልሶ ስንዴ ቢዘራ የሚቀጥለዉ ወቅት የጥጥ ማሳ ዝግጅት ከመድረሱ በፊት ስንዴ የሚታጨድበትን ሁኔታ ለማጥናት የተወጠነ ነዉ። ስለዚህ ዋናዉ ዓላማ ሁለት ሰብሎች በዓመት የሚመረቱበትን ሁኔታ ለማጥናት ነበር። በተለይ ደግሞ ስንዴ ከፍተኛ ሙቀት መቋቋም ስለማይችል አጠር ባለ ጊዜ የሚደርሱና ለአካባቢዉ የአየር ፀባይና አፈር ዓይነት የሚስማሙ የስንዴ ዝርያዎችን ለማግኘት ነበር።
በዚሁ መሠረት ስንዴን ባማከለ የተለያዩ የምርምር ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ወደ ሥራ ገቡ። እ አ አ በ1985 የመጀመሪያ ዓመት የምርምር ሥራቸውን በማከናዉእን ላይ ሳሉ እኔም በዚያዉ ዓመት ከሀረማያ ዩኒቨርስቲ በባችለር ዲግሪ ተመርቄና በእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ተቀጥሬ የወረር ግብርና ማዕከልን ተቀላቀልኩ። በማዕከሉም የስንዴ አግሮኖሚስት በመሆን ከዶ/ር ጀማል ጋር በቅርበት እንድሰራ ተመደብኩ። ስለዚህ ጀማሪ ተመራማሪ በሚል ማዕረግ የዕለት ተዕለት ሥራዬ የስንዴ ምርምር መረጃዎች መሰብሰብ ነበር። ዶ/ር ጀማል የሥራ ፍቅር አስተምረዉኛል። በዚያ የወረር ሞቃታማ አየር ቀኑን ሙሉ ሚዳ ላይ ስንሰራ እንዉል ነበር። እንደኔ በደጋዉ የሀገራችን ክፍል ተወልዶ እና ላደገ የወረር ሀሩር ቀላል ፈተና አልነበረም።
በምርምሩ ዉጤት መሰረት ባጭር ጊዜ የሚደርሱና ክጥቅምት እስከ የካቲት ባለዉ ጊዜ ውስጥ ከማሳ ዝግጅት አንስቶ እስከ ዘር እና አጭዳ የሚደርሱ ዝርያዎች ሊገኙ ችለዋል። ከነዚህም ዉስጥ ብሉ ጄይ፣ ቼናብ 70 እና ፓቮን 76 የሚባሉ ዝርያዎች ትዝ ይሉኛል። ከዝርያ በተጨማሪ ተስማሚ የዘር ወቅት፣ የዘር መጠን፣ የመዝሪያ ርቀት፣ የማዳበሪያ ዓይነትና መጠን ወ ዘ ተ ላይ ምርምር እናካሄድ ነበር። ክዶ/ር ጀማል ጋር ያደረግነዉ ምርምርም በርካታ ግኝቶችን አስገኝቷል። በፒ ኤች ዲ ቴሲሳቸዉም ይህንኑ ዘግበዋል፤ በሳይንሳዊ መጽሔቶችም አሳትመዋል። የቴሲሳቸዉ ርዕስም ከዚህ የሚከተለዉ ነዉ። Potentials and Possibilities of Double Cropping Wheat After Cotton Under Irrigation in Awash Valley, Ethiopia. Justus-Liebig-Univertsitöät ; Giessen, Germany. 1989.
በአጠቃላይ እንደ ዶ/ር ጀማል ግምት ስንዴን ከጥጥ አስከትለን በመዝራት በአዋሽ ሸለቆ ብቻ እስከ 500 ሺህ ኩንታል ስንዴ ማምረት እንደሚቻል ነዉ። የስንዴዉ ተረፈ ምርት የሆነዉ ገለባዉና ጭዱም ደግሞ ለእንስሳት መኖነት ያገለግላል። ስለዚህ ስንዴ እና ጥጥን በማፈራረቅ በዓመት ሁለት ሰብል መዝራቱ ለሀገራችን ምግብ ዋስትና ከፍተኛ አስተዋ|ጽኦ ይኖረዋል በማለት ዶ/ር ጀማል የምርምር ሥራቸዉን ያጠናቅቃሉ።
ስለ ዶ/ር ጀማል የምጽፈው በዚህ አያበቃም። በክፍል ሁለት ዶ/ር ጀማል የተሳተፉባቸዉ ሌሎች የሥራ መስኮችና ከኔም ጋር በቅርቡ አብረን ልንሰራ ያቀድነውን የምርምር ፕሮጀክት አስነብባችኋለሁ።
እስከዛዉ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ታህሳስ 15፣ 2015 ዓ.ም. (December 24, 2022)