ግብርናችንንለማዘመን፤የጤፉ መሐንዲስ ሲታወሱ

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የጤፉ መሐንዲስ፤ ዶ/ር ታረቀ በርሔ ሲታወሱ

የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ ማለትም በየካቲት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. (February 21, 2020) እና የካቲት 15 ቀን  2012 ዓ.ም. (February 23, 2020) በጻፍኳቸዉ ሁለት ብሎጎች በጤፍ ምርምር ፈር ቀዳጅ ሥራ ሰለሰሩት ዶ/ር ታረቀ በርሔ ጽፌ ነበር፡፡ በወቅቱ የጻፍኳቸዉ ብሎጎች በቀጥታ ለራሳቸዉ ካደረኩላቸዉ ቃለ መጠይቅ በመመርኮዝ ነበር፡፡

እኚህ ታላቅ ሰዉ በአሁኑ ጊዜ በአጠገባችን የሉም፡፡ በቅርቡ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዉናል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በፊት ስለ እሳቸዉ የጻፍኳቸውን ብሎግችና የዛሬዉን አንድ ላይ ባማጣመር ለዶ/ር ታረቀ ማስታውሻ ይሆን ዘንድ የሚከተለውን አቀርባለሁ፡፡

የካቲት 13 ቀን 2012 .. (February 21, 2020) ብሎጌ የተወሰደ

የዛሬዉ ጽሑፌ የሚያተኩረዉ ለጤፍ ምርምር ፈር ቀዳጅ ዉጤት ላገኙትና ይህም በጥቅም ላይ እንዲዉል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉት ስለ ዶክተር ታረቀ በርሔ ነዉ። እኚህን ከፍተኛ ተመራማሪ እኔ የጤፍ መሐንዲስ እላቸዋለሁ። ምክንያቱም ለምርምር እጅ አልሰጥ ብላ ባስቸገረችዉ ጤፍ ላይ ድል ሊቀዳጁ የቻሉ የመጀመሪያዉ ሰዉ በመሆናቸዉ ነዉ። ከእርሳቸዉ አስደናቂ ግኝት በፊት ጤፍን በማዳቀል ማሻሻል እንደማይቻል ነበር የሚታመነዉ። ምክንያቱም የጤፍ አበባ የሚከፈትበት ጊዜ ሊታወቅ ባለመቻሉ ነዉ። እንደዉም የጤፍ አበባ ፈጽሞ አይከፈትም የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሶ ነበር። ነገር ግን ዶክተር ታረቀ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ የጤፍ አበባ ሊከፈት የሚችል መሆኑንና የማዳቀል ሥራዎችም በሰብሉ ላይ ማድረግ እንደሚቻል ለመጀመሪያ ጊዜ ያረጋገጡ ናቸዉ። የእሳቸዉ የጥናት ዉጤትም እንደሚያሳየዉ የጤፍ አበባ የሚከፈተዉ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ተኩል በጠቅላላዉ ለ30 ደቂቃ ብቻ እንደሆነ ነዉ። ዶክተር ታረቀ ይህንን አስደናቂ ዉጤት ያገኙት የዛሬ 47 ዓመት በ1975 ነዉ።

ምስጋና ለዶ/ር ታረቀ ይሁንና የብሔራዊ ጤፍ ምርምር ፕሮግራም በማዳቀል ሥራ ላይ ትኩረት በማድረግ በርካታ የጤፍ ዝርያዎች እንዲጸድቁና ገበሬ ዘንድ እንዲደርሱ ለማድረግ ተችሏል፡፡ በአርሶ አደሩ ዘንድ አድናቆትን ያተረፉና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎችም ሊገኙ ችለዋል፡፡  በዚሁ በማዳቀል ሥራ እስካሁን ድረስ ወደ 30 የሚጠጉ የጤፍ ዝርያዎች የጸደቁ ሲሆን ዝርዝራቸዉንም ከዚህ በታች በቀረበዉ ሠንጠረዥ ማየት ይቻላል፡፡

በማዳቀል የተገኙ የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎች በኢትዮጵያ

ተራ ቁየዝርያዉ ስምየጸደቀበት ዓመት    (እ አ አ) ተራ ቁየዝርያዉ ስምየጸደቀበት ዓመት    (እ አ አ)
1መናገሻ1982 15አቦላ2015
2መልኮ1982 16ንጉሥ2017
3ጊቤ1983 17ፍላጎት2017
4ጸደይ1984 18ተስፋ2017
5ዱከም1995 19ህብር2017
6ዝቋላ1995 20አረካ2017
7ቁንጮ2006 21ኤባ2019
8አማራጭ2006 22ቦራ2019
9ገመቺስ2006 23ዋሸራ2019
10ሲማዳ2009 24መና2019
11ላቀች2009 25አክሱማዊት2020
12ቦሰት2012 26ቢሾፍቱ2020
13ኮራ2014 27ታኩሳ2021
14ዳግም2016 28ቦኒ2021

ምንጭ፤ Assefa K, Chanyalew S, Tadele Z, Jifar H, Kebede W, Fikre T, Tolossa K, Genet Y. 2022. Tef Breeding. In: Assefa K, Chanyalew S, Girma D, Tadele Z. (eds.). Principles and Practices of Tef Improvement. Ethiopian Institute of Agricultural Research (EIAR) and Agricultural Transformation Institute (ATI), Addis Ababa, Ethiopia. pp. 95-125

ከዚህ አንጋፋ የጤፍ ምርምር ባለዉለታ ከሆኑት ከዶክተር ታረቀ በርሔ ጋር ያደረኩት ቃለ-መጠይቅ እነሆ።

መቼና የት ተወለዱ? የተወለድኩት ጃንዋሪ 22፣ 1943 ሲሆን በትግራይ ክልል ሥር በምትገኘዉና ከውቅሮ ከተማ 15 ኪ. ሜ. በምትርቀዉ አብርሃ በምትባለዉ መንደር ነው።.

ዩኒቨርስቲ ከመግባትዎ በፊት የት ተማሩ? የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩት አሥመራ በሚገኘዉ ሰባተኛዉ ቀን አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በጂማ የእርሻና ቴክኒክ ትምህርት ቤት አጠናቅቄአለሁ።

ዶክተር ታረቀ በርሄ (በስተግራ) ኖቮምበር 2011 ከጤፍ ተመራማሪዎች ጋር በደብረ ዘይት ምርምር ማዕከል የተነሱት ፎቶ።ሌሎች በምሥሉ የሚታዩት ከግራ ወደ ቀኝ፤ ዶክተር አንድረስስ ቢንደር፣ ዶክተር ኮሪና ኤስፌልድ፣ አቶ መንግሥቱ ደምሴ፣ ዶክተር ዘሪሁን ታደለ፣ ዶክተር ክበበዉ አሰፋና ዶክተር ገረመዉ ቡልቶሳ ናቸዉ።

የዩኒቨርሲቲ ትምህርትዎንስ የት ተማሩ? የባችለር ድግሬዬን በዕጽዋት ሣይንስ በቀድሞ አጠራሩ ኃይለ ሥላሤ ዩኒቨርስቲ የአለማያ እርሻ ኮሌጅ (በአሁኑ አጠራሩ፤ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ) በ1969 አግኝቻለሁ። በመቀጠልም የማስትሬት ዲግሪዬን በአግሮኖሚ በአሜሪካ ፑልማን ከሚገኘዉ የዋሺንግተን ስቴት ዩኒቨርስቲ በ1974 ተቀብያለሁ። ፒ ኤች ዲ ደግሞ በአሜሪካ ከሚገኘዉ የኔብራስካ ዩኒቨርስቲ በፕላንት ቢሪዲንግና ጄኔቲክስ በ1981 ለማግኘት ችያለሁ።

ለበርካታ ዓመታት ከኢትዮጵያ ዉጭ በተለያዩ የኃላፊነት ሥፍራዎችና ሀገሮች እንደሠሩ ይታወቃል። ከዚህ ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ዉስጥስ ርተዋልን? አዎን፣ ለስምንት ዓመታት አገልግያለሁ። ከ1969 እስከ 1972 የጤፍ ተመራማሪ ሆኜ በደብረ ዘይት እርሻ ምርምር ማዕከል የሠራሁ ሲሆን ከ1974 እስከ 1977 ደግሞ በደብረዘይት ከነበረብኝ የጤፍ ምርምር በተጨማሪ በአለማያ እርሻ ኮሌጅ አስተምር ነበር።

ከኢትዮጵያ ውጭ በነበሩበት ወቅት በምን ላይ እንደተሳተፉና የኖሩበትን ሀገራት ቢገልጹልኝ፤

  • ከ1982 እስከ 1986 ድረስ INTSORMIL ለሚባለዉ ድርጅት የማሽላና ዳጉሣ ተመራማሪ ሆኜ ሱዳን ሀገር ዉስጥ ሠርቻለሁ።
  • ከ1987 እስከ 1989 ድረስ IITA ለሚባለው ዓለም አቀፍ ተቋም የበቆሎ ተመራማሪ ሆኜ በዛየር (በአሁኑ፤ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ) አገልግያለሁ።
  • ከ1989 እስከ 1991 ድረስ Global 2000 ለሚባለዉ ድርጅት ከፍተኛ የበቆሎ አግሮኖሚስት : ሆኜ በዛምቢያ ሀገር ሠርቻለሁ።
  • ከ1991 እስከ 1996 ድረስ SG 2000 ለሚባለዉ ድርጅት ከፍተኛ የሰብል ሣይንቲስት ሆኜ ጋና ሀገር ሠርቻለሁ።
  • ከ1996 እስከ 2004 ድረስ SG 2000 ለሚባለዉ ድርጅት ጊኒያ በምትባለዉ ሀገር ዳይሬክቴር ሆኜ ሠርቻለሁ።
  • ከ2005 እስከ 2010 ድረስ ሳሳካዋ አፍሪካ በሚባለዉ ድርጅት የአህጉሩ የሩዝ ፕሮግራም ዳይሬክቴር ሆኜ የሰራሁ ሲሆን በዚህ ኃላፊነቴም የተሻሻሉ የሩዝ ቴክሎጂዎች ለኢትዮጵያ፣ ማሊ፣ ናይጄሪያ እና ኡጋንዳ እንዲደርሱ ለማድረግ ችያለሁ።
  • ክጃኑዋሪ እስከ ጁን 2011 ድረስ USAID/ARD/TASMOA በመባል ለተቀናጀ ድርጅት ተቀማጭነቴ ላይቤሪያ ሀገር ሆኖ የሩዝ ዘር ዳይሬክቴር በመሆን የተሻሻሉ የሩዝ ቴክሎጂዎች በአምራቹ ዘንድ እንዲሰርጹ ለማድረግ ችያለሁ።

የካቲት 15፣ 2012 ዓ.ም. (February 23, 2020) ብሎጌ የተወሰደ

ጥያቄ፤ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ሀገራት ያደረጉትን ሥራ የዛሬ 10 ዓመት ካጠናቀቁ በኋላ ጡረታ ወጥተዉ ቁጭ አሉ?  ጡረታ ወጥቼ አላረፍኩም። በህይወት ዘመኔ ያካበትኩትን የሥራ ልምድ በመጠቀም የጤፍና የሩዝ ምርታማነት እንዲያድግ ኢትዮጵያ ዉስጥ ATA (Agricultural Transformation Agency ባሁኑ አጠራር ATI Agricultural Transformation Institute) ተብሎ በተቋቋመው ተቋም የሩዝ ቫሊዉ ቼይን ፕሮግራም ዳይሬክቴር ሆኜ ሠርቻለሁ።

የጤፍ ማዳቀል ሲነሣ የእርስዎ ስም ይነሳል። እንዲሁም የእርስዎ ስም ሲነሳ የጤፍ ስም ይነሳል። እስቲ በጤፍ ተመራማሪዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት ሰለተሰጥዎት ክስተት ቢያወሱኝበጤፍ ማዳቀል ላይ ሁለት አበይት እክሎች ነበሩ። የመጀመሪያዉ የጤፍ አበባ በማለዳ ብቻ ለአጭር ጊዜ እንደሚከፈት አለመታወቁ ነዉ። ሁለተኛዉ ደግሞ የጤፍ አበባ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ያለ አጉሊ መነጽር በአይናችን ብቻ የማዳቀል ሥራ ማከናወን አለመቻላችን ነዉ። ስለዚህ የተሳካ የጤፍ ማዳቀል ሥራ ለማከናወን ሦስት ነገሮች እንዲሟሉ ያስፈልጋል። እነዚህም 1ኛ) ከ30-40 እጥፍ የሚጎላ ባይኖኩላር ማይክሮስኮፕ፣ 2ኛ) እጅግ የተሳለና ቀጭን ፎርሴፕስ እና 3ኛ) የማይንቀጠቀጥ እጅ ናቸዉ። እኔ በጤፍም ሆነ በሌሎች ሰብሎች ተመራማሪዎች ዘንድ በሰፊዉ ልታወቅበት የቻልኩት የጤፍ አበባ በማለዳ ብቻ ለአጭር ጊዜ የሚከፈትበትን ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ ማግኘቴ ብቻ ሳይሆን ይህንኑ ግኝት በመጠቀምና እንዲሁም የራሴን የዓላማ ጽናት በማከል ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳካ የጤፍ ማዳቀል ሥራ ለማከናወን በመቻሌ ነዉ።

እንዴት ይህንን አስደናቂ ግኝት ሊያገኙ ቻሉ? ለዚህ ግኝት ልበቃ የቻልኩት በሥራዬ ላይ በነበረኝ ከፍተኛ ትዕግሥትና የዓላማ ጽናት ሲሆን ወደምፈልገዉ ግብ ለመድረስም በነበረኝ ቁርጠኝነት ነዉ።

የጤፍ አበባ ይህንን ይመስላል። ሁለቱ ረዘም ያሉ ጸጉራም አካላት የሴቴዉን ወገን የሚወክሉት ስቲግማ ሲሆኑ አጠር ብለዉ ያሉት ሦስት ጥንዶች አንተር ተብለዉ የሚጠሩትን የወንዴዉን ፖለን የያዙ ናቸዉ። በቀኝ በኩል የሚታየዉ ስኬል ባር 1 ሚ ሜ ይወክላል። ፎቶ፣ ሬጉላ ብሎሽ፣ በርን ዩኒቨርስቲ፣ ስዊዘርላንድ።

በምርምር ዉጤትዎ በመመርኮዝ በርካታ ጽሑፎች አሳትመዋል። ነገር ግን ስለ ጤፍ አበባ አከፋፈትና እንዲሁም ማዳቀል ያገኙትን አስደናቂ ግኝት የት ነዉ ያሳተሙት? በርካታ ጽሑፎች ባሳትምም ከዚህ ግኝቴ ጋር በሚገናኝ ያሳተምኳቸዉ ጽሑፎች ከዚህ በታች ያሉት ናቸዉ።

  1. Berhe T. 1975. Breakthrough in tef breeding technique. Food and Agriculture Organization (FAO) Information Bulletin, Cereal Improvement and Production for Near East Project 12(3):11-13, FAO, Rome.
  2. Berhe T. 1976. Brighter prospects for improving Eragrostis tef by breeding. In: Proceedings on Evaluation of Seed Protein alternatives by Mutation Breeding, 5-9 May 1975, Vienna, Austria. International Atomic Energy Agency (IAEA), Vienna. pp. 129-135.
  3. Berhe T. 1976. The door is open for green evolution in tef. pp. 208-213. In: Proceedings of the Sixth Annual Research Seminar, 12-14 Nov 1975, Addis Ababa, Ethiopia. Institute of Agricultural Research (IAR), Addis Ababa.
  4. Addis Zemen Gazetta. 1975. ዓመት-ምህረቱን እንጂ የህትመቱን ቀን አላስታዉስም።

እ.ኤ.አ. ከኦክቶበር 22 እስክ 24፣ 2019 በቢሾፍቱ በተካሄደዉ ዓለም-አቀም የጤፍ ወርክሾፕ ላይ ዶክተር ታረቀ በርሄ ንግግር ሲያደርጉ ይታያል። ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ

በርካታ ሽልማቶችና እዉቅና እንዳገኙ ይታወል። እስቲ ከነዚህ ዉስጥ ዋነኞቹን ቢገልጹልኝ፤ በዉጭ ሀገራትም ሆነ በአገር ዉስጥ የተሸለምኳቸዉና የተሰጠኝ እዉቅና በአራት ከፍሎ ማየት ይቻላል።

  1. ከአለማያ የእርሻ ኮሌጅ የእጽዋት ሣይንስ ተመራቂዎች መካከል የላቀ ዉጤት በማግኘቴ (በ1969)
  2. የዕውቅና ሠርቲፊኬት
  3. በ50ኛዉ ዓመት የአለማያ ዩኒቨርስቲ ምሥረታ በዓል (በ2005)
  4. በመጀመሪያዉ የአፍሪካ ሩዝ ኮንግረስ (በ2006)
  5. ከሣሣካዋ አፍሪካ በታዋቂዉ የአረንጓዴ አብዮት መሐንዲስ ዶክተር ኖሮማን ቦርሎግ እና በቀድሞዉ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ካርተር የተፈረመ (በ2006)
  6. የወርቅ ሜዳሊያና ሠርቲፊኬት የተሸለምኩበት
  7. በ40ኛዉ ዓመት የደብረ ዘይት ምርምር ማዕከል ምሥረታ በዓል (በ2005)
  8. በ50ኛው ዓመት የኢትዮጵያ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ምሥረታ በዓል (በ2008)
  9. የክብር ዶክትሬት ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ (በ2014)

ከኢትዮጵያዊያን ተመራማሪዎች መካከል እንደ ጀግና (hero) የሚቆጥሯቸዉን ሶስት ምሁራን ቢጠቅሱልኝ፤ በጤፍ ምርምር ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ናቸዉ ብዬ የምገምታቸዉ ዶክተር መላክ ኃይል መንገሻ፣ ዶክተር ሠይፉ ከተማ እና ዶክተር ክበበው አሰፋ ናቸዉ።

ካልዎት ረዥም ልምድ በመነሣት ለወደፊቱ የጤፍ ምርምር የሚለግሱት ምክር ባጭሩ ቢያካፍሉኝ፤ በህይወት ዘመኔ የጤፍ ምርት በሄክታር ከ80 እስከ 100 ኩንታል እንደሚደርስ ምኞቴ ነዉ።

ስለዶክተር ታረቀ በርሄ በሁለት ክፍል የቀረበዉ ጽሑፌ በዚህ ያበቃል። ከርሳቸዉ ረዥም የሥራ ልምድ በተለይም በጤፍ ምርምር ካበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ብዙ የምንማረዉ ይኖራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

በመጨረሻም ለዶ/ር ታረቀ ቤተሰቦች እና ወዳጆች መጽናናትን እመኛለሁ፡፡

ወደፊት በሌላ ጽሁፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ታህሳስ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. (December 21, 2022)

አስተያየት ያስቀምጡ