ግብርናችንን ለማዘመን፤ ታዋቂዉ የጤፍ ታክሶኖሚስት፤ ታደሰ ኤባ፤ ክፍል 1

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ታዋቂዉ የጤፍ ተመራማሪና ታክሶኖሚስት፤ ታደሰ ኤባ፤ ክፍል 1

ዶ/ር ታደሰ ኤባን በይበልጥ የምናዉቃቸዉ በተለያዩ የጤፍ ዝርያዎች ላይ ጥልቅ ጥናት ካካሄዱ በኋላ ባበረከቱልን ሁለት መጽሐፍት ነዉ፡፡

እነርሱም

  1. እ አ አ በ1969 የታተመዉና ‘Tef (Eragrostis tef): the Cultivation, Usage and Some of the Known Diseases and Insect’. Part I. Experiment Station Bulletin 60. HSIU, College of Agriculture, Dire Dawa, Ethiopia እና
  2. በ1975 የታተመዉና ‘Tef (Eragrostis tef) cultivar: Morphology and Classification’. Part II. Experiment Station Bulletin 66. Addis Ababa University, College of Agriculture, Dire Dawa, Ethiopia የተባሉት ናቸዉ፡፡

የዛሬዉ ጽሑፌ የሚያተኩረዉ በሁለተኛዉ መጽሐፋቸዉ ላይ ነዉ፡፡ ይህ 73 ገጽ የያዘዉ መጽሐፋቸዉ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተጻፈ ሲሆን ከዚህ ዉስጥ 12 ገጾቹ በአማርኛ የተጻፉ ናቸዉ፡፡ በዚህ መጽሐፍቸዉ ዶ/ር ታደሰ በርካታ ቁም ነገሮች አበርክተውልናል፡፡

ለጤፍ ተመራማሪዎች በከፍተኛ ደረጃ የሚያገለግለዉ የሁለተኛዉ የዶ/ር ታደሰ ኤባ መጽሐፍ የፊት ሽፋን ይህንን ይመስላል፡፡  ምንጭ፤ Ebba T. 1975. Tef (Eragrostis tef) cultivar: Morphology and Classification. Part II. Experiment Station Bulletin 66. Addis Ababa University, College of Agriculture, Dire Dawa, Ethiopia

በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚበቅሉ የጤፍ ዝርያዎችን በማሰባሰብና በጥልቀት በማጥናት እንዲሁም ዝርያዎቹ እርስ በርስ ያላቸዉን ቅርበትና ርቀት በሳይንሳዊ መንገድ በማጥናትና በመተንተን በመጽሐፋቸዉ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ውጤታቸዉንም በማስረጃ ከማስደገፋቸዉም በላይ እያንዳንዱ ዝሪያ ከዬትኛዉ የሀገራችን ክፍል እንደተገኘም ጭምር አሳይተዋል፡፡

በመጽሐፋቸዉ ውስጥ ባስቀመጡት መለኪያና የሥርዓት ምደባ (ታክሶኖሚ) ላይ የሚሰሩ ሳይንቲስቶች በሚጠቀሙበት ዘዴ ተመርኩዘዉ የዝርያዎችን ትንታኔ እንዳሳዩ አሳይተዋል፡፡ እነዚህ ለታክሶኖሚ ስራቸዉ የሚያገለግሉ ክራይቴሪዎችን ለማሳየት በራሳቸዉ በሳሏቸዉ ሶስት ወካይ የሆኑና ድንቅ የሆኑ ሥዕሎች ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ሥዕሎቹን ራሳቸዉ ለመሳላቸዉ በሶስቱም ላይ ታ. ኤ. (ታደሰ ኤባ) የሚል ተጽፎባቸዉ ይታያል፡፡ ይህም ድንቅ የመሳል ችሎታቸዉን ያሳየናል፡፡

እነዚህ የጤፍ ዝርያዎችን የሚወክሉ ሶሰት የዶ/ር ታደሰ ኤባ ሥዕሎችና ገላጻቸዉን ጭምር ከዚህ በታች ማየት ይቻላል፡፡

ምንጭ፤ Ebba T. 1975. Tef (Eragrostis tef) cultivar: Morphology and Classification. Part II. Experiment Station Bulletin 66. Addis Ababa University, College of Agriculture, Dire Dawa, Ethiopia

ምንጭ፤ Ebba T. 1975. Tef (Eragrostis tef) cultivar: Morphology and Classification. Part II. Experiment Station Bulletin 66. Addis Ababa University, College of Agriculture, Dire Dawa, Ethiopia

ምንጭ፤ Ebba T. 1975. Tef (Eragrostis tef) cultivar: Morphology and Classification. Part II. Experiment Station Bulletin 66. Addis Ababa University, College of Agriculture, Dire Dawa, Ethiopia

ከላይ በተጠቀሱት መለኪዎች በመርኮዝ ዶ/ታደሰ የጤፍ ዝሪያዎችን በ35 ዓይነቶች የከፈሉ ሲሆን እያንዳንዱን ዝሪያ ከሌላው የሚለይበትን ባህርይ በመተንተን አቅርበዋል፡፡ ውጤታቸዉንም በፎቶግራፍ ጭምር አስደግፈዋል፡፡

ይህ የዶ/ር ታደሰ ኤባ መጽሐፍ ከዛሬ 47 ዓመታት በፊት የታተመ በመሆኑና በአሁኑ ጊዜ በቀላሉ ለአንባቢያን ሊገኝ የማይችል በመሆኑ በመጽሀፉ ዉስጥ የተጠቀሱትን 35 ዝሪያዎች ማሳየቱ ጠቃሚ መስሎ ስለታየኝ ከዚህ በታች በአጭሩ ቀርበዋል፡፡

ምንም እንኳ ዶ/ር ታደሰ በርካታ መለኪያዎችን በመጠቀም የምደባ ሥራ (ታክሶኖሚ) የሰሩ ቢሆንም እኔ ከዚህ በታች የማሳየዉ የዝሪያዉን ስም፣ የፍሬዉን ሽፋን ቀለም እና ዝሪያዉ ከየትኛዉ የጤፍ አብቃይ አካባቢ እንደተገኘ ብቻ ነው፡፡

  1. Ada አዳ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ ደብረ ብርሃን፣ 2750 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  2. Addisie አዲሴ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ ደብረ ዘይት፣ 2000 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  3. Adoensis አዶአንሲስ፤ የፍሬዉ ቀለም ቀይ፤ የተገኘበት ሥፍራ ነቀምቴ፣ 2400 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  4. Alba አልባ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ አድዋ
  5. Balami ባለሚ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ ደብረ ዘይት፣ 2000 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  6. Beten ብትን፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ ደብረ ዘይት፣ 2000 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  7. Bunninye ቡንኝ፤ የፍሬዉ ቀለም ቀይ፤ የተገኘበት ሥፍራ ነጆ፣ 2000 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  8. Burssa ቡርሳ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ ሐረር፣ 1856 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  9. Curati ኩራቲ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ ዳሞታ፣ 2400 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  10. Dabbi ዳቢ፤ የፍሬዉ ቀለም ቀይ፤ የተገኘበት ሥፍራ ባህር ዳር፣ 1840 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  11. Denkeye ድንክዬ፤ የፍሬዉ ቀለም ቀይ፤ የተገኘበት ሥፍራ ሐረር፣ 1856 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  12. Dschanger ጫንገር፤ የፍሬዉ ቀለም ቀይ፤ የተገኘበት ሥፍራ መምሳክ
  13. Enatite እናቲት፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ ደብረ ዘይት፣ 2000 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  14. Fesho ፌሾ፤ የፍሬዉ ቀለም ቀይ፤ የተገኘበት ሥፍራ ወሊሶ፣ 2200 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  15. Gea-Lamie ጂአ ለሜ፤ የፍሬዉ ቀለም ቀይ፤ የተገኘበት ሥፍራ ነጆ፣ 2750 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  16. Goferie ጎፈሬ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ ጂማ፣ 1750 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  17. Gommadie ጎማዴ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ አጋሮ፣ 1870 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  18. Gorradie ጎራዴ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ አለማያ፣ 2100 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  19. Hamrawe Murri ሀምራዊ ሙሪ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት አመሬሳ፣ 1860 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  20. Hatalla ሀተላ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ ሐረር፣ 1856 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  21. Janno ጃኖ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ ዳሞታ፣ 2140-2480 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  22. Karadebi ከራዴቢ፤ የፍሬዉ ቀለም ቀይ፤ የተገኘበት ሥፍራ ጊምቢ፣ 2100 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  23. Key Agachem ቀይ አጋቸም፤ የፍሬዉ ቀለም ቀይ፤ የተገኘበት ሥፍራ ደብረ ዘይት፣ 2000 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  24. Kaye Murri ቀይ ሙሪ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ ሂዳቡ ገናሲ፣ 2000 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  25. Manya ማኛ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ ደብረ ዘይት፣ 2100 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  26. Murri ሙሪ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ ዳሞታ፣ 2750 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  27. Purpurea ፑርፑርያ፤ የፍሬዉ ቀለም ቀይ፤ የተገኘበት ሥፍራ አድዋ
  28. Rosea ሮሲ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ ደብረ ዘይት፣ 2000 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  29. Rubicunda ሩቢኩንዳ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ አድዋ
  30. Shawa-Generra ሸዋ ጊሚራ፤ የፍሬዉ ቀለም ቀይ፤ የተገኘበት ሥፍራ ሸዋ ገሚራ፣ ከፋ
  31. Trotteriana ትሮትሪያና፤ የፍሬዉ ቀለም ቀይ፤ የተገኘበት ሥፍራ ዳሞታ፣ 2480 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  32. Tullu Nasy ቱሉ ናሲ፤ የፍሬዉ ቀለም ነጭ፤ የተገኘበት ሥፍራ ነጆ፣ 2400 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  33. Variegata ቫሪጋታ፤ የፍሬዉ ቀለም ቀይ፤ የተገኘበት ሥፍራ ነጆ። 1950 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ
  34. Viridis ቪርዲስ የፍሬዉ ቀለም ነጭ
  35. Zuccagniana ዙካኚያና፤ የፍሬዉ ቀለም ቀይ፤ የተገኘበት ሥፍራ ዳሞታ፣ 2480 ሜ ከባህር ጠረፍ በላይ

በክፍል 2 ዶ/ር ታደሰ ኤባ በጤፍ ምርምር ካበረኩት ከፍተኛ አስተዋዖ በተጨማሪ በሌላ መስክ ያበረከቱትን ለማካተት እሞክራለሁ፡፡ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ በጤፍ ማሻሻያ ላይ ያለን ተመራማሪዎች የኚህን አንጋፋ ሣይንቲስት አስተዋጽኦ ለማስታውስ ያደረግነዉን እዘግባለሁ፡፡

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ታህሳስ 11፣ 2015 ዓ.ም. (December 20, 2022)

አስተያየት ያስቀምጡ