ግብርናችንንለማዘመን፤ታዋቂዉ የጤፍ ታክሶኖሚስት፤ ታደሰ ኤባ፤ ክፍል 2

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ታዋቂዉ የጤፍ ተመራማሪና ታክሶኖሚስት፤ ታደሰ ኤባ፤ ክፍል 2

የክፍል 1 ጽሑፌ የጤፍ ተመራማሪ የነበሩት ዶ/ር ታደሰ ኤባ እ አ አ በ1975 ባሳትሙትና ‘Tef (Eragrostis tef) cultivar: Morphology and Classification’. Part II. Experiment Station Bulletin 66. Addis Ababa University, College of Agriculture, Dire Dawa, Ethiopia በሚለዉ መጽሐፋቸዉ ላይ ያጠነጠነ ነበር፡፡ በዚህ ድንቅ ሥራቸዉ ዶ/ር ታደሰ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚበቅሉ የጤፍ ዝርያዎችን በማሰባሰብና በጥልቀት በማጥናት እንዲሁም ዝርያዎቹ እርስ በርስ ያላቸዉን ቅርበትና ርቀት በሳይንሳዊ መንገድ በማጥናትና በመተንተን አቅርበዉልናል፡፡ በእኔ ግምት በእሳቸዉ ደረጃ የተለያዩ የጤፍ ዝርያዎችን አጥንቶና በተገቢዉ ምድብ ከፋፍሎ ያሳየን ሳይንቲስት አላየሁም፡፡ ስለዚህ የእሳቸዉ መጽሐፍ የጤፍ ዝሪያዎች ለመከፋፈል እንደ መመሪያ ሆኖ ያገለግለናል፡፡

ለዚሁ ድንቅ ስጦታቸዉ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ በጤፍ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያለን ተመራማሪዎች ከሶስት ዓመት በፊት በብሔራዊ ዝሪያ አጽዳቂ ኮሚቴ የጸደቀልንን አዲስ የጤፍ ዝርያ ‘ኤባ’ ብለን ሰይመናዋል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ይኸዉ የኤባ ዝርያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአምራቾች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን የዘር ጥያቄዉ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ለማስረጃም ያህል በሶስት ሥፍራዎች የኤባ ዝርያ በመስክ ላይ የነበረዉን እድገትና በፎቶግራፍ አስደግፌ ከዚህ በታች ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡

ምንጃር ላይ ኤባ ዝርያን ከዘሩና ካደነቁት ሁለት አርሶ አደሮች ጋር ሆኜ የተነሳሁት እ እ አ ኦክቶበር 2021፡፡ ፎቶ አባተ በቀለ (ዶ/ር)

ሸንኮራ ላይ አንጋፋዉ የጤፍ ተመራማሪ ዶ/ር ክበበው አሰፋ ከኤባ ዝርያ ፊት ለፊት፣ እ አ አ ኦክቶበር 2022፡፡ ፎቶ ዘሪሁን ታደለ

አርሶ አደሩ በኤባ ማሳ ዉስጥ በምዕራብ አርሲ ዞን፣ አዳባ ወረዳ፣ ፉሩና ቀበሌ፤ እ አ አ ኦክቶበር 2022፤ ፎቶ ዘሪሁን ታደለ

በጤፍ ምርምር ካደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በተጨማሪ የጉጉል ፍለጋ እንደሚያሳየኝ ዶ/ር ታደሰ ኤባ ከነ ዶ/ር አማረ ጌታሁን ጋር በመሆን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ የእፅዋት ናሙናችን በማሰባሰብ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ይህም የዛሬ 45 አመት ገደማ መሆኑ ነዉ፡፡

በመቀጠልም እ አ አ ከ1968 እስከ 1971 ድረስ የመጀመሪያዉ የእፅዋት ጄኔቲክ ሀብት ማዕከል (PGRC/E) ወይም ያሁኑ የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት (EBI) ዳይሬክቴር ሆነዉ ለሶስት ዓመታት እንዳገለገሉየመሥራያ ቤት ድረ ገጽ ያሳያል https://ebi.gov.et/ ፡፡ ምንም እንኳ ይኸዉ ምሥሪያ ቤት የአሁኑን ስም ከማግኘቱ በፊት በተለያየ ወቅት በተለያየ ስም (PGRC/E, EBIR, IBC, EBI) ቢጠራም እስካሁን ድረስ ባብዘኛዉ ሰዉ የሚታወቀዉ ‘ጂን ባንክ’ በሚለዉ ስም ነዉ፡፡

ከኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት (EBI) ድረ ገጽ ያገኘሁት መረጃ እንደሚያሳየዉ የዶ/ር ታደሰ ኤባ ፎቶ ይህን ይመስላል፡፡ https://ebi.gov.et/ accessed 20.12.2022፡፡ እንደሚመስለኝ ይህ ፎቶ ዶ/ር ታደሰ የመሥራይ ቤቱ የመጀመሪያዉ ዳይሬክተር የነበሩ ጊዜ የተነሱት ነዉ፡፡

ማጠቃለያ

ዶ/ር ታደሰ ኤባ የዛሬ 50 ዓመት አካባቢ በተለያዩ የጤፍ ዓይነቶች ላይ ባደረጉት ጥልቅ ምርምር ዝርያዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመከፋፈል ድንቅ ሥራ ሰርተዋል፡፡ ይህንኑ ሥራቸዉን በመጽሐፍ አሳትመዉልናል፡፡ ነገር ግን መጽሐፋቸዉ በአሁኑ ጊዜ ለተጠቃሚዎች በቀላሉ ሊገኝ ባለመቻሉ የሚመለከታቸዉ አካላት ለሁሉም በሚዳረስበት መንገድ (open access) አሳትመዉ አቅርቦቱን እንዲያሳድጉ የራሴን ሀሳብ አቀርባለሁ፡፡ በስማቸዉ የሰየምነዉ የጤፍ ዝርያም ረዘም ላለ ጊዜ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቶ እንደሚቆይም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዶ/ር ታደሰ ኤባ የቀድሞዉን የእፅዋት ጄኔቲክ ሀብት ማዕከል (PGRC/E) ወይም የአሁኑን የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት (EBI) የመጀመሪያው ዳይሬከር በመሆን መምራታቸዉም ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚሁ በሁለት ክፍሎች ያዘጋጀሁትን ስለ ዶ/ር ታደሰ ኤባ የሚያወሳዉን ጽሑፍ አጠናቅቃለሁ፡፡ እኝህ ታላቅ የጤፍ ምሁርም የዛሬ ስድስት ወር ገደማ ክዚህ አለም በሞት እንደተለዩን ሰምቻለሁ፡፡ ለዘመዶቻቸውና ባልደረቦቻቸዉ መጽናናትን እመኛለሁ፡፡

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ታህሳስ 11፣ 2015 ዓ.ም. (December 20, 2022)

አስተያየት ያስቀምጡ