ግብርናችንን ለማዘመን፤ የኮሮና ቫይረስ በግብርናችን ላይ፣ ክፍል 2

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የኮሮና ቫይረስ በግብርናችን ላይ፣ ክፍል 2

የዛሬ ሶስት ወራት ገደማ ዉሃን በሚባለዉ የቻይና ከተማ አካባቢ የጀመረዉና በአጭር ጊዜ ዓለማችንን በማዳረስ ላይ ስለሚገኘዉና በኮሮና ቫየረስ ወይም በሣይንሣዊ ስሙ coronavirus disease-19 (ወይም ባጭሩ Covid-19) ምክንያት ስለሚከሰተዉ በሽታ በሰፊዉ ተዘግቧል። Corona የሚለዉ ቃል በዚህች አጭር ጊዜ ዉስጥ ከ2.6 ቢሊዮን በላይ በሆኑ መጣጥፎች ዉስጥ የተገለጸ ሲሆን በአማርኛም ኮሮና የሚለዉ ስም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ በሆኑ ጽሑፎች ተገልጿል። ይህ የሚያሳየን ቫይረሱ በጤናችን ላይ በማድረስ ላይ ያለዉን ከፍተኛ ተጽእኖ ነዉ። ከዚሁ ቫይረስ ጋር በተያያዘ እስካሁን ድረስ 395,647 የሚሆን የዓለማችን ህዝብ የተጠቃ ሲሆን ከዚህ ዉስጥ 17,241 የሚሆኑት በሞት ሊቀጠፉ ችለዋል። የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣዉ መረጃ እንደሚያሳየዉ ቫይረሱ እጅግ በከፍተኛ ፍጥነት በመስፋፋት ላይ ሲሆን እንደምሳሌነት የሚቀርበዉ የመጀመሪያዎቹ አንድ መቶ ሺህ ሰዎች የተጠቁት በ67 ቀናት ዉስጥ ሲሆን የሚቀጥሉት መቶ ሺህ ሰዎች ደግሞ በ11 ቀናት ብቻ ነበር። የሚገርመዉ ደግሞ የመጨረሻዎቹ አንድ መቶ ሺህ ሰዎች የተጠቁት በአራት ቀናት ብቻ መሆኑ ነዉ። ከአንድ ቀን በፊት የዓለም የጤና ድርጅትና ፊፋ በጋራ ባወጡት መግለጫ ህብረተሰቡ በዚህ አደገኛ ቫይረስ እንዳይጠቃ ማድረግ ስለሚኖርበት ጥንቃቄ ግንዛቤ ለመስጠት የተለያዩ አገራትን የሚወክሉ 28 ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የተመረጡ ሲሆን እነርሱም በ13 ቋንቋዎች መልክታቸዉን ያደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ብዙዎች እንደሚስማሙት በዚህ ክፉ ቫይረስ ምክንያት የዓለማችን ኢኮኖሚ በዚህ በያዝነው የአውሮፓዉያኑ 2020 እና በሚቀጥሉት ተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስበትና አንዳንድ ሀገራትም ከሚደርስባቸዉ የኢኮኖሚ ድቀት ለማገገም ረዥም ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸዉ ነዉ። በከፍተኛ ደረጃ የቫይረሱ ሰለባ በሆነችበት ቻይና በቅርቡ በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ባሉ ድርጅቶች ላይ የተደረገዉ ጥናት እንደሚያሳየዉ 80 ፐርሰንት የሚሆኑ ድርጅቶች ወደ ቀድሞ ሥራቸዉ ሊመለሱ አለመቻላቸዉ ነዉ። እንዲሁም በጥናቱ ከተካተቱት ዉስጥ 20 ፐርሰንት የሚሆኑት ደግሞ የነበራቸዉ ጥሬ ገንዘብ ከአንድ ወር ያልዘለቀ ሲሆን እስከ ሶስት ወር የሚቆይ ጥሬ ገንዘብ የነበራቸዉ 64 ፐርሰንት የሚሆኑት ብቻ ነበሩ።

ዩ ኤስ ኤድ የሚባለዉ የአሜሪካ መንግሥት የበጎ አድራጊ ድርጅት ባልደረባ የሆኑ ኤክስፐርቶች ኮኖና ቫይረስ በዓለማችን የምግብ ዋስትና ላይ ሊያደርስ ይችላል ተብሎ የሚገመተዉን ክስተት በቅርቡ በጻፉት ብሎግ አስነብበዉናል። እንደ እነዚህ ጸሐፊያን አባባል እያንዳንዱ ሀገር የኮኖና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት የሚያደርገዉ ዝግጁነትና የሚነድፈዉ ፖሊሲ በምግብ ዋስትና ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል።

በዚሁ የኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሚደርሰዉን ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግር እንዴት መቀነስ እንደሚቻል ሌላ ጽሑፍ የጻፉት ደግሞ ሲሞንታ በልትራሚ የተባሉ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባልደረባ ናቸዉ። እንደ ጸሐፊዋ አባባል በዚሁ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለከፍተኛ አደጋ የሚጋለጡ ሀገራት በተለይም በመልማት ላይ ያሉ ሀገራት በሽታዉን ለመከላከል የሚደረገዉ ዕርዳታ ብቻ ሳይሆን የምግብ ዋስትናቸዉንም ለማስጠበቅ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸዉ ያስገነዝባሉ። የዓለም የምግብ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትቱዩት (IFPRI) በዚሁ የኮሮና ቫይረስና የምግብ ዋስትና ላይ ትኩረት ያደረጉ አምስት የብሎግ ጽሁፎችን በልዩ እትም አትሞ አዉጥቷል። እነዚህን ማንበቡ ጠቃሚ ይመስለኛል።

ወደፊት በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መጋቢት 15 ፣ 2012 ዓ.ም. (March 24, 2020)

አስተያየት ያስቀምጡ