ግብርናችንን ለማዘመን፤ የኮሮና ቫይረስ በግብርናችን ላይ

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የኮሮና ቫይረስ በግብርናችን ላይ

የዛሬ ሶስት ወራት ገደማ ዉሃን በሚባለዉ የቻይና ከተማ አካባቢ የጀመረዉና በአጭር ጊዜ ዓለማችንን በመላ በማዳረስ ላይ ስለሚገኘዉ በኮሮና ቫየረስ ወይም በሣይንሣዊ ስሙ coronavirus disease-19 (ወይም ባጭሩ Covid-19) ምክንያት ስተትከሰትዉ በሽታ ብዙ ተብሏል። ይህችን አጭር ብሎግ እስከምጽፍበት ድረስ 245,484 የሚሆን የዓለማችን ህዝብ በበሽታዉ የተያዘ ሲሆን ከዚህ ዉስጥ 10,031 የሚሆኑት በሞት እንደተለዩን ከሚወጣዉ ሪፖርት ማወቅ ይቻላል። ይህም የበሽታዉን የመግደል አቅም ወደ 4% ያደርሰዋል ማለት ነዉ። ከአጠቃላይ ሟቾች ዉስጥ 66.4% የሆኑት ከቻይናና ከኢጣሊያን ዉስጥ ናቸዉ። ነገር ግን በበጎ ጎኑ መታየት የሚገባዉ በበሽታዉ ከተያያዙት ህመምትኞች መካከል 86,035 የሚሆኑት ከህመሙ ሊፈወሱ መቻላቸዉ ሲሆን ሌሎችም በማገገም ላይ እንደሚገኙ ነዉ። ሌላዉ ተስፋ የሚሰጠው ነገር ከሶስት ወራት ከፍተኛ ዉጊያ በኋላ ቻይና በዚህ በሽታ ላይ ድል እየተቀዳጀች እንደሆነ ነዉ። ለዚህም ማሳያ የሚሆነዉ ለመጀመሪያ ጊዜ ላለፉት ሁለት ተከታታይ ቀናት በበሽታዉ በአገሯ ውስጥ አዲስ የተጠቃ ሰዉ አለመመዝገቡ ነዉ። የዚህን ክፉ በሽታ መስፋፋት ለመግታት ህብረተሰቡ ማድረግ ስላለበት ጥንቃቄ እያንዳንዱ ሀገር የራሱን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልክ መመሪያ ያስተላለፈ ከመሆኑም በተጨማሪ ለተግባራዊነቱም ቁጥጥር በማድረግ ላይ ይገኛል።

የዛሬዉ ጽሁፌ የሚያተኩረዉ ይህ በሽታ በኢኮኖሚያችን በተለይም በግብርናችን ላይ ያደርሳል ተብሎ የሚገመተውን ጠባሳ ለማሳየትና ይህንንም ጠንክረን ማለፍ እንድንችል የራሴን ምክር ለመለገስ ነዉ።

የዛሬ አምስት ዓመታት ገደማ በምዕራብ የአፍሪካ ሀገራት በተከሰተዉ የኢቦላ በሽታ ምክንያት የምግብ ወይም የእህል ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ ነበር። ለዚህ ዋናዉ ምክንያት በኢቦላ በሽታ አምራቹም ኃይል በመጠቃቱ እንደሆነ ይገመታል። ከሁሉ የሚያስደንቀዉ ግን ምንም እንኳ በኮኖና ቫይረስ ምክንያት የተከሰተዉ በሽታ በቻይና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ለማሳደር ቢችልም የምግብ ዋጋ ላይ የጎላ ለውጥ እንዳላሳየ አንድ ዘገባ ይጠቁማል።

ከህንድ ሀገር የወጣ ጽሁፍ እንደሚያሳዉ ሀገሪቱ ከቻይና ጋር ባላት ከፍተኛ የምግብ ሸቀጦች ንግድ ምክንያት በቻይና በተከሰተዉ ወረርሽኝ ምክንያት በህንድ ሀገር የምግብ አቅርቦት ላይ አሉታዊ ጎን እንደሚኖረዉ ይተነብያል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የንግድና ዕድገት ድርጅት ግምት በዚሁ የኮሮና ቫይረስ ምክንያት በዚህ በያዝነዉ የአዉሮፓዉያን ዓመት ብቻ የዓለማችን ኢኮኖሚ ቢያንስ በአንድ ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚቀዛቀስ ነዉ።.

ምንም እንኳ በተለያየ የዓለማችን አካባቢዎች ያሉ ህዝቦች የግብርና እና የንጽህና መገልገያ እቃዎችን ከዚህ በፊት ባልታየ ሁኔታ በማግበስበስ ላይ የሚገኙ ቢሆንም በምዕራቡ ዓለም የጎላ የዋጋ ጭማሪ የታየ አይመስለም። ለምሳሌ እኔ የምኖርበት ሀገር በከፍተኛ የኮኖና ቫይረስ ጥቃት ምክንያት በሰዎች ዝውውር ላይ እገዳ ቢደረግም በምግብና ተዛማች ዕቃዎች ላይ የሚደረገዉ ዝውውር እገዳ ያልተጣለበት በመሆኑ የዋጋ ጭማሪ ሊታይ አልቻለም። ከዚህ ሌላ በከተማ ዉስጥ የሰዎች እንቅስቃሴ ላይ የተገደበ ቢሆንም በጎረቤቴ የሚገኙ ገበሬዎች መደበኛ የእርሻ ሥራቸዉን በማከናወን ላይ ይገኛሉ። ይህ የሚያሳየዉ ምንም እንኳ ጊዜው የከፋ ቢሆንም ህይወት መቀጠል ስላለበትና ህብረተሰቡም ለምግቡ በገበሬዉ ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ የሀገሪቱ ገበሬዎች ኃላፊነታቸዉን በመወጣት ላይ ይገኛሉ።

በመጨረሻም የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክቴር ጄኔራል የሆኑት ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለአፍሪካ ሀገራት በአጽንኦት እንደተናገሩት በአህጉሩ የሚገኙ ሀገራት በኮሮና ቫይረስ ሊደርስ የሚችለዉን ጥቃት ለመከላከል ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል ባሉት እኔም የዛሬውን ጽሑፌን እደመድማለሁ።

ወደፊት በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መጋቢት 11፣ 2012 ዓ.ም. (March 20, 2020)

አስተያየት ያስቀምጡ