ግብርናችንን ለማዘመን፤ የስንዴ ልማት በመስኖ፣ ክፍል 2

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የስንዴ ልማት በመስኖ፣ ክፍል 2

በክፍል 1 ጽሑፌ ለማሳየት እንደሞከርኩት በሀገር ዉስጥ የስንዴ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ በታሰበዉና በአሁኑ ወቅት በመስኖ የሚለማዉን እርሻ ለመጎብኘት በነበረኝ ከፍተኛ ፍላጎት መሠረት የዚህ ፕሮጀክት አንዱ አካል ወደ ሆነው ወደ አፋር ክልል መቀመጫ ወደ ሆነችዉ ወደ ሠመራ ከዚያም የስንዴ ልማቱ ወደሚገኝበት ዱብቲና አካባቢዉ ተጓዝኩኝ። ምንም እንኳ በአሁኑ ጊዜ የምርምር አቅጣጫዬ በጤፍ ላይ ያተኮረ ቢሆንም የስንዴ እርሻን ለመጎብኘት ያነሳሳኝ በአሁኑ ወቅት በመካሄድ ላይ ያለዉን የስንዴ ልማትን በቅርበት ሆኜ ለማየት ነዉ። ሌላዉ ምክንያቴ የዩኒቨርስቲ ትምህርቴን በባችለር ዲግሪ ጨርሼ ወደ ሥራ ዓለም ስመደብ ለመጀመሪያ ጊዜ ምርምር ያካሄድኩት በስንዴ ላይ ስለነበር ነዉ። እኔ በዚያን ወቅት ተመድቤ የሠራሁበትና አሁን የጎበኘሁት አካባቢ በአየር ጸባይ ተቀራራቢነት አላቸዉ። ሁለቱም ሥፍራዎች የተራራቁ ቢሆኑም የአዋሽ ወንዝን በመጠቀም ነዉ የልማትም ሆነ የምርምር ሥራዎች የሚከናወንባቸዉ። በወረር ምርምር ማዕከል በስንዴ አግሮኖሚ ላይ የምርምር ሥራዬን በማከናዉንበት ወቅት የምርምር ፕሮግራሜ ትኩረት ያደረገዉ በአካባቢዉ ዋነኛ ሰብል የነበረዉን ጥጥን በማስከተል ስንዴ ሊዘራበት የሚችልበትን ሁኔታ ማጥናት ነበር። ከዚሁ ምርምሬ ጋር ተዛማችነት የነበረዉን ሥልጠናዉም በስንዴ አግሮኖሚ ላይ በዉጭ ሀገር ተከታትዬ ነበር። በዚህ የተነሣ ላለፉት ሶስት አሥርት ዓመታት በዓለም አቀፍም ሆነ በአገር አቀፍ ድረጃ የስንዴ ምርምርም ሆነ ልማት ያለበትን ሁኔታ በቅርበት ለመከታተል ፍላጎት ያደረብኝ።

ከዚህ በታች ባሉት ምስሎች እንደሚታየዉ በዱብቲና አካባቢዉ በመካሄድ ላይ ያለዉ የስንዴ የዘር ብዜት በደህና ሁኔታ እየተካሄደ እንደሆነ ነዉ። ከዚህ ሥፍራ የሚመረተው ስንዴም በሚቀጥለዉ ዓመት በሰፊዉ ለሚካሄደዉ የስንዴ እርሻ በዘርነት እንዲያገለግል የታሰበ ነዉ።

በአሁኑ ጊዜ በእሸትነት ደረጃ ላይ የሚገኘዉ የስንዴ ማሣ በዱብቲ አካባቢ። ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፤ የካቲት 26፣ 2012 ዓ.ም.

በዱብቲ አካባቢ ለአጨዳ የደረሰ የስንዴ ማሣ ዉስጥ ሆኜ። ፎቶ ደስታ ገብሬ፤ የካቲት 26፣ 2012 ዓ.ም.

ከዘር ብዜቱ በተጨማሪ የዳቦና የማኮሮኒ ስንዴን ያካተተተ የዝሪያ መረጣ ምርምርም በመካሄድ ላይ ይገኛል። ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፤ የካቲት 26፣ 2012 ዓ.ም.

በአካባቢዉ ወጣቶች በመልማት ላይ የሚገኘዉን የስንዴ ማሣ ደስታ ገብሬ ሲያሳየኝ። ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፤ የካቲት 26፣ 2012 ዓ.ም.

አነስተኛ ደረጃ የተከሰተዉን የስንዴ ዋግ በሽታ ለመግታት ርጭት ለማድረግ በዝግጅት ላይ። ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፤ የካቲት 26፣ 2012 ዓ.ም.

አልፎ አልፎ የአፈር ጨዋማነት በስንዴ ተክል ላይ ጉዳት ለማድረስ ችሏል። ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፤ የካቲት 26፣ 2012 ዓ.ም.

በአካባቢዉ ያለዉን የእርሻና የግጦሽ መሬት በከፍተኛ ደረጃ በመዉረር ላይ የሚገኘዉ ፕሮሶፒስ (Prosopis juliflora) የተባለዉ ተክል። ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፤ የካቲት 26፣ 2012 ዓ.ም.

አደገኛዉ የፕሮሶፒስ ተክል የመኪና መንገድንም ተከትሎ በሰፊዉ ተንሰራፍቶ ይታያል። ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፤ የካቲት 26፣ 2012 ዓ.ም.

የስንዴዉን የልማት ፕሮጀክት እዉን ለማድረግ በርካታ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳትፎ በማድረግ ላይ ናቸዉ። እኔም የልማቱን ሥፍራና እንዲሁም ከ30 ዓመታት በፊት የማዉቃቸዉን አሁን ግን በከፍተኛ ሁኔታ የተለወጡትን የዱብቲና የአሳይታና ከተሞችን ያስጎበኘንና በፕሮጀክቱ ዉስጥ ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኘዉን የእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆነዉን አቶ ደስታ ገብሬን ከልብ አመሰግናለሁ።

ወደፊት በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መጋቢት 7፣ 2012 ዓ.ም. (March 16, 2020)

አስተያየት ያስቀምጡ