ግብርናችንን ለማዘመን፤ የስንዴ ልማት በመስኖ፤ ክፍል 1

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የስንዴ ልማት በመስኖ፤ ክፍል 1

ቀደም ብሎ ‘የኢትዮጵያ የስንዴ አብዮት‘ በሚል ርዕስ በጻፍኩት ብሎጌ ለማሳየት እንደሞከርኩትሚያዚያ 12 ቀን 2011 የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ከግብርና ምሁራን ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ በከፍተኛ ደረጃ የስንዴ ምርትን ለማሳደግ ዕቅድ እንደተነደፈ አሳዉቀዉ ነበር። ይህም ከዉጭ ወደ ሀገሪቱ የሚገባዉን የስንዴ መጠን በሂደት እንዲቀንስና ከአራት ዓመታት በኋላ ከነጭራሹ እንደሚገታ ገልጸዉ ነበር። በዚሁ መሠረት በዋናዉ የመኸር ወቅት ከሚመረተዉ ስንዴ በተጨማሪ የመስኖ ዉሃን በመጠቀም በዓመት ሁለት ጊዜ የሚመረትበት ሁኔታ ተነድፎ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገዉ የተቀናጀ ሥራ በበርካታ ሥፍራዎች ስንዴን በመስኖ የማልማቱ ሥራ እየተካሄደ ይገኛል። ከነዚህ ሥፍራዎች ዉስጥ የመካከለኛዉና የታችኛዉ አዋሽ አካባቢዎች ይገኙበታል። በነዚሁ ሥፍራዎች የስንዴ የዘር ብዜት እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን ዋና ዓላማዉም የተባዛዉ ዘር በሚቀጥለዉ ዓመት እየተስፋፋ ለሚካሄደዉ የስንዴ እርሻ በዘርነት እንዲያገለግል ታስቦ ነዉ።

እኔም ይህንኑ የልማት ሥራ በቦታዉ ተገኝቼ ለማየት በራሴ ፍላጎት ከአስር ቀናት በፊት ወደ ሰመራ ተጓዝኩኝ። ከዚያም አንዱ የልማት ማዕከል ወደ ሆነችዉ ወደ ዱብቲ አቀናሁ። ዱብቲንና አሳይታን የዛሬ 32 ዓመት ገደማ አውቃቸዋለሁ። በወቅቱ የመልካ ወረር ምርምር ማዕከል (በአሁኑ አጠራር፣ የወረር ምርምር ማዕከል) ተመራማሪ በመሆኔ በታችኛዉ አዋሽ የነበረዉን የጥጥ ልማት ለመገምገም የብሔራዊ የጥጥ ምርምር ኮሚቴ ከነበርነዉ ጋር እንጓዝ ነበር። እነዚህም ዶክተር በዳዳ ግርማ (አዳቃይ)፣ አቶ አባቡ ደምሴ (ኢንቶሞሎጂስት፣ በአሁኑ ጊዜ በህይወት የሌሉ)፣ ዶክተር ገረመዉ ተረፈ (ፓቶሎጂስት)፣ ዶክተር ጥላሁን ወርዶፋ (የመስኖ መሐንዲስ)፣ እኔም አግሮኖሚስት እና ሌሎችንም ያካተተ ቡድን ነበር። ምንም እንኳ በመካከለኛዉ አዋሽ የሚገኘዉ የወረር ምርምር ማዕከላችን የአየር ፀባይ አዳጋች የነበረ ቢሆንም ወደ 300 ኪ.ሜ. ከማዕከላችን ርቀዉ የሚገኙት የዱብቲ፣ የአሳይታና የሎጊያ የአየር ፀባይ ደግሞ ከዚህ የባሰ ነበር። በዚያ ፈታኝ የአየር ፀባይ ዉስጥ በተመደብንበት የጥጥ መደብ እያንዳንዱን የጥጥ ቅጠልና እምቡጥ አገላብጠን አይተን በተባይ ወይም በበሽታ የተጠቃዉን እንመዝግብ ነበር። ዉጤቱንም ቀጥሎ በምናደርገዉ ግምገማችን ላይ እንጠቀምበት ነበር። በአሁኑ ጊዜ የአፋር ክልል ዋና ከተማ ሆና የምታገለግለዉ የሠመራ ከተማ በዚያን ጊዜ አልተቆረቆረችም ነበር። ምንም እንኳ ሠመራ በቅርቡ የተመሠረተች ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ያሉባት ከተማ ከመሆኗም በተጨማሪ የሠመራ ዩኒቨርሲቲና የሠመራ ሡልጣን አሊሚራህ ሀንፋሬ ኤርፖርት ይገኙባታል።

ምንም እንኳ በአሁኑ ጊዜ የምርምር ፕሮግራሜ በጤፍ ላይ ያተኮረ ቢሆንም ከመሃል ሀገር ራቅ ብሎ የሚገኘዉን የስንዴ እርሻ ለመጎብኘት ፍላጎት ያደረብኝ በሁለት ዋና ምክንያቶች ነዉ። የመጀመሪያዉ የአሁኑ የስንዴ ልማት ሀገሪቷ በያመቱ ወደ አገር ዉስጥ የምታስመጣውን የስንዴ መጠን የሚቀንስ በመሆኑ ይህንን ከፍተኛ የልማት ሥራ በቅርበት ሆኜ ለመመልከት ነዉ። ሁለተኛወ ምክንያቴ እኔም ከረጅም ጊዜ በፊት ከሀረማያ ዩኒቨርስቲ (በወቅቱ ኮሌጅ) በባችለር ዲግሪ ትምህርቴን እንደጨረስኩ የተመደብኩት በወረር ምርምር ማዕከል በቆላ ሰብሎች ላይ ምርምር ለማካሄድ ነበር። የስንዴ ምርምርም አንዱና ዋነኛዉ የምርምር ፕሮግራሜ ነበር። በዚሁ መሠረት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ስንዴንና የስንዴ ምርምርን በትኩረት ነዉ የምከታተለዉ። ምክንያቱም እንደ አግሮኖሚስት በበርካታ የስንዴ ምርምር ፕሮግራሞች ላይ ለመሳተፍ ችያለሁና ነዉ። በወቅቱ ዶክተር ጀማል መሐመድ የተባሉ ትምህርታቸዉን በጀርመን ሀገር በመከታተል ላይ የነበሩ ተመራማሪ ለዶክትሬት ትምህርታቸዉ ማሟያ የሚሆን የምርምር ሥራቸዉን በቆላ ስንዴ ላይ በማዕከላችን ይሠሩ ነበር። እኔም የምርምር ሥራዬን ሀ ብዬ ስጀምር በዚሁ የቆላ ስንዴ ፕሮግራም ላይ ተመድቤ የምርምር ሥራዬን ተያያዝኩኝ። የአዋሽ ወንዝን በመስኖ በመጠቀም በስንዴና በሌሎች ሰብሎች በርካታ የምርምር ሥራዎችን እንሠራ ነበር። አካባቢዉ የጥጥ እርሻ የተስፋፋበት በመሆኑ የምርምሩ ፕሮግራሙም ትኩረት የተሰጠዉ ለጥጥ ነበር። የስንዴ ምርምር ፕሮግራም ዋናዉ ትኩረት የነበረዉ በዓመት ሁለት ጊዜ ሰብል ለማምረት የሚቻልበትን ሁኔታ ለማጥናት ነበር። በዚሁ መሠረት ጥጥ በዋናዉ የሰብል ወቅት ተተክሎና ተለቅሞ ከማሣዉ ላይ ከተነሳ በኋላ የአየር ሙቀቱ በሚቀንስበት የጥቅምት ወር ስንዴን ለመዝራት ነበር። የስንዴ እርሻ ከዚያ በፊት በአካባቢዉ ያልተለመደ በመሆኑ ሙከራዎቻችን የዝሪያ መረጣ፣ የዘር መጠን፣ የዘር ወቅት፣ የማዳበሪያ መጠን፣ የዉሃ መጠንና ሌላም የምርምር ዓይነቶችን ያካተተ ነበር። በአነስተኛ የመሬት ስፋት ባላቸዉ የምርምር ማዕከላችን የምንሰራዉን ሥራ ስፋፊ በሆኑ በአካባቢዉ ባሉ የመንግሥት እርሻ ማሳዎች ላይም እንፈትሽ ነበር። እኔም በዚህ የስንዴ ምርምርና ልማት በነበረኝ ተሳትፎ ተመርጬ ሜክሲኮ ሀገር በሚገኘዉ ዓለም አቀፍ የበቆሎና የስንዴ ምርምር ማዕከል ለሰባት ወራት የተሰጠዉን ሥልጠና ለመከታትል ችያለዉ። ይህ በስንዴ አግርኖሚ ላይ የተዘጋጀዉ ሥልጠና የቲዎሪና የተግባር ትምህርት ያካተተ ከመሆኑም በላይ ከዚያ ቀደም ብሎ በዩኒቨርስቲ ቆይታዬ ካገኘሁት በላይ ከፍተኛ ዕዉቀት የገበየሁበት ነበር ማለት ይቻላል። ስለዚህ ነው ስንዴና የስንዴ ምርምር ከልቤ ውስጥ ናቸዉ የምለዉ።

የአሳይታ ከተማ ከፊል ገጽታ። ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፣ የካቲት 26፣ 2012 ዓ.ም.
የሎጊያ ከተማ ከፊል ገጽታ። ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፣ የካቲት 26፣ 2012 ዓ.ም.
የሠመራ ከተማ ከፊል ገጽታ። ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፣ የካቲት 26፣ 2012 ዓ.ም.
የሠመራ ከተማ ከፊል ገጽታ። ፎቶ ዘሪሁን ታደለ፣ የካቲት 26፣ 2012 ዓ.ም.

የዚህ ጽሑፍ ክፍል ሁለት በሚቀጥለዉ ብሎጌ ይቀርባል። እስከዚያዉ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መጋቢት 6፣ 2012 ዓ.ም. (March 15, 2020)

አስተያየት ያስቀምጡ