በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሑፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤
የጤፉ መሐንዲስ፤ ዶክተር ታረቀ በርሄ፤ ክፍል 2
ማስገንዘቢያ፤ በተለይ ካልተገለጸ በስተቀር ሁሉም ጊዜ የተጻፈዉ እንደ አዉሮፓ አቆጣጠር ነዉ።
በክፍል አንድ ስለ ዶክተር ታረቀ በርሄ አጠር ያለ የህይወት ታሪክና የሥራ ልምድ ለማሳየት ሞክሬአለሁ። በዛሬዉ ጽሑፌ ደግሞ ስለ እኚህ የጤፍ መሐንዲስ በሰፊዉ ስለሚታወቁበት አስደናቂ ግኝት በጥያቄና መልስ መልክ አቀርባለሁ።
ጥያቄ፤ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ሀገራት ያደረጉትን ሥራ የዛሬ 10 ዓመት ካጠናቀቁ በኋላ ጡረታ ወጥተዉ ቁጭ አሉ? ጡረታ ወጥቼ አላረፍኩም። በህይወት ዘመኔ ያካበትኩትን የሥራ ልምድ በመጠቀም የጤፍና የሩዝ ምርታማነት እንዲያድግ ኢትዮጵያ ዉስጥ ATA ተብሎ በተቋቋመው ተቋም የሩዝ ቫሊዉ ቼይን ፕሮግራም ዳይሬክቴር ሆኜ ሠርቻለሁ።
የጤፍ ማዳቀል ሲነሣ የእርስዎ ስም ይነሳል። እንዲሁም የእርስዎ ስም ሲነሳ የጤፍ ስም ይነሳል። እስቲ በጤፍ ተመራማሪዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት ሰለተሰጥዎት ክስተት ቢያወሱኝ፤ በጤፍ ማዳቀል ላይ ሁለት አበይት እክሎች ነበሩ። የመጀመሪያዉ የጤፍ አበባ በማለዳ ብቻ ለአጭር ጊዜ እንደሚከፈት አለመታወቁ ነዉ። ሁለተኛዉ ደግሞ የጤፍ አበባ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ያለ አጉሊ መነጽር በአይናችን ብቻ የማዳቀል ሥራ ማከናወን አለመቻላችን ነዉ። ስለዚህ የተሳካ የጤፍ ማዳቀል ሥራ ለማከናወን ሦስት ነገሮች እንዲሟሉ ያስፈልጋል። እነዚህም 1ኛ) ከ30-40 እጥፍ የሚጎላ ባይኖኩላር ማይክሮስኮፕ፣ 2ኛ) እጅግ የተሳለና ቀጭን ፎርሴፕስ እና 3ኛ) የማይንቀጠቀጥ እጅ ናቸዉ። እኔ በጤፍም ሆነ በሌሎች ሰብሎች ተመራማሪዎች ዘንድ በሰፊዉ ልታወቅበት የቻልኩት የጤፍ አበባ በማለዳ ብቻ ለአጭር ጊዜ የሚከፈትበትን ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ ማግኘቴ ብቻ ሳይሆን ይህንኑ ግኝት በመጠቀምና እንዲሁም የራሴን የዓላማ ጽናት በማከል ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳካ የጤፍ ማዳቀል ሥራ ለማከናወን በመቻሌ ነዉ።
እንዴት ይህንን አስደናቂ ግኝት ሊያገኙ ቻሉ? ለዚህ ግኝት ልበቃ የቻልኩት በሥራዬ ላይ በነበረኝ ከፍተኛ ትዕግሥትና የዓላማ ጽናት ሲሆን ወደምፈልገዉ ግብ ለመድረስም በነበረኝ ቁርጠኝነት ነዉ።

በምርምር ዉጤትዎ በመመርኮዝ በርካታ ጽሑፎች አሳትመዋል። ነገር ግን ስለ ጤፍ አበባ አከፋፈትና እንዲሁም ማዳቀል ያገኙትን አስደናቂ ግኝት የት ነዉ ያሳተሙት? በርካታ ጽሑፎች ባሳትምም ከዚህ ግኝቴ ጋር በሚገናኝ ያሳተምኳቸዉ ጽሑፎች ከዚህ በታች ያሉት ናቸዉ።
- Berhe T. 1975. Breakthrough in tef breeding technique. Food and Agriculture Organization (FAO) Information Bulletin, Cereal Improvement and Production for Near East Project 12(3):11-13, FAO, Rome.
- Berhe T. 1976. Brighter prospects for improving Eragrostis tef by breeding. In: Proceedings on Evaluation of Seed Protein alternatives by Mutation Breeding, 5-9 May 1975, Vienna, Austria. International Atomic Energy Agency (IAEA), Vienna. pp. 129-135.
- Berhe T. 1976. The door is open for green evolution in tef. pp. 208-213. In: Proceedings of the Sixth Annual Research Seminar, 12-14 Nov 1975, Addis Ababa, Ethiopia. Institute of Agricultural Research (IAR), Addis Ababa.
- Addis Zemen Gazetta. 1975. ዓመት-ምህረቱን እንጂ የህትመቱን ቀን አላስታዉስም።

በርካታ ሽልማቶችና እዉቅና እንዳገኙ ይታወቃል። እስቲ ከነዚህ ዉስጥ ዋነኞቹን ቢገልጹልኝ፤ በዉጭ ሀገራትም ሆነ በአገር ዉስጥ የተሸለምኳቸዉና የተሰጠኝ እዉቅና በአራት ከፍሎ ማየት ይቻላል።
- ከአለማያ የእርሻ ኮሌጅ የእጽዋት ሣይንስ ተመራቂዎች መካከል የላቀ ዉጤት በማግኘቴ (በ1969)
- የዕውቅና ሠርቲፊኬት
- በ50ኛዉ ዓመት የአለማያ ዩኒቨርስቲ ምሥረታ በዓል (በ2005)
- በመጀመሪያዉ የአፍሪካ ሩዝ ኮንግረስ (በ2006)
- ከሣሣካዋ አፍሪካ በታዋቂዉ የአረንጓዴ አብዮት መሐንዲስ ዶክተር ኖሮማን ቦርሎግ እና በቀድሞዉ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ካርተር የተፈረመ (በ2006)
- የወርቅ ሜዳሊያና ሠርቲፊኬት የተሸለምኩበት
- በ40ኛዉ ዓመት የደብረ ዘይት ምርምር ማዕከል ምሥረታ በዓል (በ2005)
- በ50ኛው ዓመት የኢትዮጵያ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ምሥረታ በዓል (በ2008)
- የክብር ዶክትሬት ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ (በ2014)
ከኢትዮጵያዊያን ተመራማሪዎች መካከል እንደ ጀግና (hero) የሚቆጥሯቸዉን ሶስት ምሁራን ቢጠቅሱልኝ፤ በጤፍ ምርምር ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ናቸዉ ብዬ የምገምታቸዉ ዶክተር መላክ ኃይል መንገሻ፣ ዶክተር ሠይፉ ከተማ እና ዶክተር ክበበው አሰፋ ናቸዉ።
ካልዎት ረዥም ልምድ በመነሣት ለወደፊቱ የጤፍ ምርምር የሚለግሱት ምክር ባጭሩ ቢያካፍሉኝ፤ በህይወት ዘመኔ የጤፍ ምርት በሄክታር ከ80 እስከ 100 ኩንታል እንደሚደርስ ምኞቴ ነዉ።
ስለዶክተር ታረቀ በርሄ በሁለት ክፍል የቀረበዉ ጽሑፌ በዚህ ያበቃል። ከርሳቸዉ ረዥም የሥራ ልምድ በተለይም በጤፍ ምርምር ካበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ብዙ የምንማረዉ ይኖራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
በሌላ ጽሁፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ የካቲት 15፣ 2012 ዓ.ም. (February 23, 2020)