በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤
የጤፉ መሐንዲስ፤ ዶ/ር ታረቀ በርሄ፤ ክፍል 1
ማስገንዘቢያ፤ በተለይ ካልተገለጸ በስተቀር ሁሉም ጊዜ የተጻፈዉ እንደ አዉሮፓ አቆጣጠር ነዉ። እንደሚታወቀዉ ሁሉ ጤፍ አገር-በቀል ብቻ ሳይሆን በሰፊዉ ጥቅም ላይ የዋለ ሰብላችንም ነዉ። የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጄንሲ መረጃ እንደሚያሳየዉ በያመቱ 6.5 ሚሊዮን አባወራዎች ጤፍን ይዘራሉ። በኢትዮጵያ የአንድ ቤተሰብ አማካይ አምስት ሰዉ አድርግን ብንወስድ 32.5 ሚሊዮን ሰዉ በጤፍ ግብርና ይሳተፋል ማለት ነዉ። ከዚያ ደግሞ ወደ ሻጩ ከሄድን ከጅምላ ነጋዴ እስከ ቸርቻሪ ድረስ በርካታ የማህረሰቡ ሰዎች በጤፍ ንግድ ይሳተፉሉ። በተመሣሣይ መልኩ ጤፍን በመፍጨት፣ በመጋገር፣ ወዘተ የሚሳተፉትን ካሰላን ደግሞ ቁጥሩ የበለጠ ይጨምራል። የጤፍ ፍሬ ከገለባዉ ከወጣ በኋላ የሚገኘዉ ጭድ ወይም ተረፍ-ምርትም ለከብት መኖ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለዉ በመሆኑ በከብት ማደለብና ሌሎች ተዛማች መስኮች የሚሳተፉትንም መገመት ይቻላል። ለዚህ ነዉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ጤፍን ሁለቴ የምንመገበዉ። የቀጥታዉ የጤፍ ፍሬ ተፈጭቶ በሚጋገረዉ ወይም በሚሠራዉ እንጄራ፣ ገንፎ፣ ጨጨብሳ፣ ጩኮ፣ ኬክ፣ ወዘተ ሲሆን የተዘዋዋሪዉ ደግሞ የጤፍ ጭድን የተመገቡ ከብቶችን ስንመገብ ነዉ።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጤፍ ከኢትዮጵያ ውጭ ብዙም የማይታወቅ በመሆኑ በሰብሉ ላይ የሚደረገዉ ጥናት በሚፈለገዉ ደረጃ ሊሆን አልቻለም። በዚሁ ምክንያት የጤፍ ምርታማነት ዝቅትኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቢሆንም በርካታ ተመራማሪዎች በጤፍ ምርምር ጉልህ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ከነዚህ አንጋፋ ተመራማሪዎች መካከል ዶክተር መላከ ኃይል መንገሻ የመጀመሪያዉ ኢትዮጵያዊ የጤፍ ተመራማሪ ነበሩ ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። ለፒ ኤች ዲ ማጠናቀቂያ በአሜሪካ ከሚገኘዉ የፐርዱ ዩኒቨርስቲ በ1964 Eragrostis tef (Zucc.) Trotter: its embryo sac development, genetic variability, and breeding behavior በሚል ከሠሩት ቴሲስ በተጨማሪ ከዚህ በታች የተገለጹትን ሁለት ጠቃሚ ጽሑፎች አበርክተዉልናል።
- Mengesha MH, Pickett RC, Davis RL. 1965. Genetic variability and interrelationship of characters in Teff, Eragrostis tef (Zucc.) Trotter. Crop Science 5(2): 155-157
- Mengesha MH. 1966. Chemical composition of teff compared with that of wheat, barley and grain sorghum. Economic Botany 20: 268–273
ከኚህ የጤፍ ተመራማሪ ቀጥሎ በርካታ የሀገራችንም ሆነ የውጭ ሀገራት ተመራማሪዎች የጤፍ ምርምርን ከፍ ለማድረግ የበኩላቸዉን ድርሻ አበርክተዋል።
የዛሬዉ ጽሑፌ የሚያተኩረዉ ለጤፍ ምርምር ፈር ቀዳጅ ዉጤት ላገኙትና ይህም በጥቅም ላይ እንዲዉል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉት ስለ ዶክተር ታረቀ በርሄ ነዉ። እኚህን ከፍተኛ ተመራማሪ እኔ የጤፍ መሐንዲስ እላቸዋለሁ። ምክንያቱም ለምርምር እጅ አልሰጥ ብላ ባስቸገረችዉ ጤፍ ላይ ድል ሊቀዳጁ የቻሉ የመጀመሪያዉ ሰዉ በመሆናቸዉ ነዉ። ከእርሳቸዉ አስደናቂ ግኝት በፊት ጤፍን በማዳቀል ማሻሻል እንደማይቻል ነበር የሚታመነዉ። ምክንያቱም የጤፍ አበባ የሚከፈትበት ጊዜ ሊታወቅ ባለመቻሉ ነዉ። እንደዉም የጤፍ አበባ ፈጽሞ አይከፈትም የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሶ ነበር። ነገር ግን ዶክተር ታረቀ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ የጤፍ አበባ ሊከፈት የሚችል መሆኑንና የማዳቀል ሥራዎችም በሰብሉ ላይ ማድረግ እንደሚቻል ለመጀመሪያ ጊዜ ያረጋገጡ ናቸዉ። የእሳቸዉ የጥናት ዉጤትም እንደሚያሳየዉ የጤፍ አበባ የሚከፈተዉ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ተኩል በጠቅላላዉ ለ30 ደቂቃ ብቻ እንደሆነ ነዉ። ዶክተር ታረቀ ይህንን አስደናቂ ዉጤት ያገኙት የዛሬ 44 ዓመት በ1975 ነዉ።
ከዚህ አንጋፋ የጤፍ ምርምር ባለዉለታ ከሆኑት ከዶክተር ታረቀ በርሄ ጋር ያደረኩት ቃለ-መጠይቅ እነሆ።
መቼና የት ተወለዱ? የተወለድኩት ጃንዋሪ 22፣ 1943 ሲሆን በትግራይ ክልል ሥር በምትገኘዉና ከውቅሮ ከተማ 15 ኪ. ሜ. በምትርቀዉ አብርሃ በምትባለዉ መንደር ነው።.
ዩኒቨርስቲ ከመግባትዎ በፊት የት ተማሩ? የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩት አሥመራ በሚገኘዉ ሰባተኛዉ ቀን አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በጂማ የእርሻና ቴክኒክ ትምህርት ቤት አጠናቅቄአለሁ።

የዩኒቨርሲቲ ትምህርትዎንስ የት ተማሩ? የባችለር ድግሬዬን በዕጽዋት ሣይንስ በቀድሞ አጠራሩ ኃይለ ሥላሤ ዩኒቨርስቲ የአለማያ እርሻ ኮሌጅ (በአሁኑ አጠራሩ፤ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ) በ1969 አግኝቻለሁ። በመቀጠልም የማስትሬት ዲግሪዬን በአግሮኖሚ በአሜሪካ ፑልማን ከሚገኘዉ የዋሺንግተን ስቴት ዩኒቨርስቲ በ1974 ተቀብያለሁ። ፒ ኤች ዲ ደግሞ በአሜሪካ ከሚገኘዉ የኔብራስካ ዩኒቨርስቲ በፕላንት ቢሪዲንግና ጄኔቲክስ በ1981 ለማግኘት ችያለሁ።
ለበርካታ ዓመታት ከኢትዮጵያ ዉጭ በተለያዩ የኃላፊነት ሥፍራዎችና ሀገሮች እንደሠሩ ይታወቃል። ከዚህ ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ዉስጥስ ሠርተዋልን? አዎን፣ ለስምንት ዓመታት አገልግያለሁ። ከ1969 እስከ 1972 የጤፍ ተመራማሪ ሆኜ በደብረ ዘይት እርሻ ምርምር ማዕከል የሠራሁ ሲሆን ከ1974 እስከ 1977 ደግሞ በደብረዘይት ከነበርብኝ የጤፍ ምርምር በተጨማሪ በአለማያ እርሻ ኮሌጅ አስተምር ነበር።
ከኢትዮጵያ ውጭ በነበሩበት ወቅት በምን ላይ እንደተሳተፉና የኖሩበትን ሀገራት ቢገልጹልኝ፤
- ከ1982 እስከ 1986 ድረስ INTSORMIL ለሚባለዉ ድርጅት የማሽላና ዳጉሣ ተመራማሪ ሆኜ ሱዳን ሀገር ዉስጥ ሠርቻለሁ።
- ከ1987 እስከ 1989 ድረስ IITA ለሚባለው ዓለም አቀፍ ተቋም የበቆሎ ተመራማሪ ሆኜ በዛየር (በአሁኑ፤ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ) አገልግያለሁ።
- ከ1989 እስከ 1991 ድረስ Global 2000 ለሚባለዉ ድርጅት ከፍተኛ የበቆሎ አግሮኖሚስት : ሆኜ በዛምቢያ ሀገር ሠርቻለሁ።
- ከ1991 እስከ 1996 ድረስ SG 2000 ለሚባለዉ ድርጅት ከፍተኛ የሰብል ሣይንቲስት ሆኜ ጋና ሀገር ሠርቻለሁ።
- ከ1996 እስከ 2004 ድረስ SG 2000 ለሚባለዉ ድርጅት ጊኒያ በምትባለዉ ሀገር ዳይሬክቴር ሆኜ ሠርቻለሁ።
- ከ2005 እስከ 2010 ድረስ ሳሳካዋ አፍሪካ በሚባለዉ ድርጅት የአህጉሩ የሩዝ ፕሮግራም ዳይሬክቴር ሆኜ የሰራሁ ሲሆን በዚህ ኃላፊነቴም የተሻሻሉ የሩዝ ቴክሎጂዎች ለኢትዮጵያ፣ ማሊ፣ ናይጄሪያ እና ኡጋንዳ እንዲደርሱ ለማድረግ ችያለሁ።
- ክጃኑዋሪ እስከ ጁን 2011 ድረስ USAID/ARD/TASMOA በመባል ለተቀናጀ ድርጅት ተቀማጭነቴ ላይቤሪያ ሀገር ሆኖ የሩዝ ዘር ዳይሬክቴር በመሆን የተሻሻሉ የሩዝ ቴክሎጂዎች በአምራቹ ዘንድ እንዲሰርጹ ለማድረግ ችያለሁ።
ከዶክተር ታረቀ ጋር ያደረኩት ቃለ መጠየቅ በዚህ አያበቃም። በክፍል 2 እስክንገናኝ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ የካቲት 13፣ 2012 ዓ.ም. (February 21, 2020)