ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለዉጥ አሳሳቢነት

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለዉጥ አሳሳቢነት

ስለ አየር ንብረት ለዉጥና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ስለሚያደርስብን ተጸዕኖ ከዚህ በፊት በጻፍኳቸዉ ጽሑፎቼ ለማሳየት ሞክሬአለሁ። ቢሆንም የአየር ንብረት ለዉጥ በማድረስ ላይ ስላለዉ ጉዳትና ወደፊትም ያደርሳል ተብሎ ስለሚጠበቀዉ አሉታዊ ጎኖች በርካታ መረጃዎች በመቅረብ ላይ ስላሉ እነዚህን ለአንባቢያን ማድረሱ ተገቢ ይመስለኛል። ምክንያቱም በአየር ንብረት ምክንያት ሊደርሱ የሚችሉ ክስተቶችን ከወዲሁ በመረዳት በከፊልም ቢሆን መፍትሔ ሊሆን የሚችል እርምጃ ለመዉሰድ ስለሚቻል ነዉ። የአየር ንብረት ለዉጥ የሚያደርሰዉ ክስተት መጠነ ሰፊ ብቻ ሳይሆን በበርካታ መንገድ ተጽእኖ ያሳድራል። ለምሳሌ ከአምስት ዓመታት በፊት የወጣ ሪፖርት እንደሚያሳየዉ የአየር ንብረት ለዉጥ የአፍሪካ አህጉርን በስምንት መንገዶች በመጉዳት ላይ ይገኛል። እነዚህም፤

1ኛ) በአየር ሁኔታ (weather) ለዉጥ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች በከፍተኛ ዝናም ምክንያት የጎርፍ ሁኔታ የሚከሰት ሲሆን በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ እጅግ መጠኑ ባነሰ የዝናም መጠን ምክንያት ድርቅ ይከሰታል።

2ኛ) በዉሃ መጠንና ጥራት፤ ከላይ በተራ ቁጥር አንደተጠቀሰዉ በተለዋዋጭ የዝናም መጠን እና የአየር ሙቀት ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የዉሃ ክምችቶች ሊመናመኑ ችለዋል። ባብዘኛዉ እንደምሳሌ የሚወሰደዉ በአፍሪካ ትልቁ በሆነዉ የኪሎማንጃሮ ተራራ ላይ የሚገኘዉ የበረዶ ክምችት እጅግ እየተመናመነ መምጣቱ ነዉ። ይህንን በ90 ዓመታት ብቻ የተከሰተዉን ከፍተኛ የሆነ ክስተት በምሥል 1 ማየት ይቻላል።

3ኛ) በምግብ እጥረትና ጥራት፣ 4ኛ) በጤናችን፣ 5ኛ) በመጠለያችን፣ 6ኛ) ለጥቃት በተዳረጉ ዜጎች፣ 7ኛ) በደህንነት እና 8ኛ) በሥርዓተ ምህዳር (ecosystem) ናቸዉ።

የዓለም የሜትሮሎጂ ድርጅትን ሪፖርት ጠቅሶ ቢቢሲ በቅርቡ (እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 3፣ 2019) በዘገበዉ መሠረት ያሳለፍነዉ አሥርት ዓመታት ማለትም ከ2010 እስከ 2019 የነበሩት ከፍተኛ የአየር ሙቀት የተመዘገበባቸዉ ናቸዉ። ከዚህ በተጨማሪ አደገኛዉ የግሪን ሃውስ ጋዝ እንዲጨምር ከሚያደርጉት ውስጥ የካርቦን ዳዮክሳይድና ናይትረስ ኦክሳይድ መጠንም በከፍተኛ መጠን ጨምረዉ የተገኙበት ነዉ።

ከላይ የተጠቀሱትን በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት የሚደርሱ ክስተቶች ለመግታት ጥረቶች በመካሄድ ላይ ናቸዉ። ከነዚህ ዉስጥ በአፍሪካ ደረጃ ካሉት 350Africa.org የሚባለዉን መጥቀስ ይቻላል። ድርጅቱ ውይም እንቅስቃሴዉ 350 የሚለዉን ሥያሜ የወሰድዉ በዓለማችን ለጤናማ ኑሮ ያመቻል ተብሎ የታሰበዉ የካርቦንዳኦክሳይድ መጠን 350 ከሚሊዮን እጅ በመሆኑ ነዉ። ይህ እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት በጋና፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ፣ ኬንያ፣ ኮትዲቮር እና የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ምሥል 1፤ እ.ኤ.አ. በ1912 በኪሎማንጃሮ ተራራ ላይ የነበረዉ የበረዶ ክሞችት እና ከ90 ዓመታት በኋላ በ2002 በተመሣሣይ ሥፍራ የነበረዉ የበረዶ መጠን። የመረጃዉ ምንጭ

በተለያየ ሁኔታ የሚያጋጥሙን ሥጋቶች (risks) በስሌት ከማቅረቡም በተጨማሪ የመፍትሔ ሀሳቦችንም የሚያቀርብ መቀመጫዉን በተለያዩ የዓለማችን ከተሞች ያደረገ ማፕል ክሮፍት የተባለ ድርጅት አለ። በተለያዩ ሁኔታዎች የሚያጋጥሙንን ሥጋቶች በሦስት ዋና እና በ12 ንዑሳን ክፍሎች ለይቶ የሚያሳይ ሲሆን ለዚህ ጽሑፌ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት ሊከሰት በሚችለዉ ላይ አተኩራለሁ።

በዚሁ መሠረት በድርጅቱ ድህረ ገጽ ጎልቶ እንደሚታየዉ 84% የሚሆኑ በዓለማችን በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኙ ከተሞች በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት ለሚከሰት አደጋ የተጋለጡ ናቸዉ። በምሥል 2 እንደሚታየዉ በከፍተኛ ደረጃ ለዚህ የተጋለጡት በአፍሪካ ያሉ ከተሞች ናቸዉ። በሪፖርት መሠረት እ. ኤ.አ. ከ2018 እስከ 2035 ባሉት ዓመታት ዓመታዊ የህዝባቸዉ ዕድገት ከ3% በላይ የሆኑት ተጋላጭ ናቸዉ። በምሳሌነት ከተገለጹት ከተሞች መካከል ዓመታዊ የህዝባቸዉ እድገት ይህንን ይመስላል። ካምፓላ ኡጋንዳ 5.1%፣ ዳሬ ሰላም ታንዛኒያ 4.8%፣ አቡጃ ናይጄሪያ 4.5%፣ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ 4.3%፣ ሉዋንዳ አንጎላ 3.7% እና ሌጎስ ናይጄሪያ 3.5% ናቸዉ።

ምሥል 2፤ በተለያዩ አህጉራት ያሉ ከተሞች ለአየር ንብረት ለውጥ ያላቸዉ ተጋላጭነት (Vulnerability) ነዉ።  ምንጭ

እንደ መፍትሔ የተጠቀሱትን በሌላ ጽሁፌ አቀርባለሁ። እስከዚያዉ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥር 4፣ 2012 ዓ.ም. (January 13, 2020)

አስተያየት ያስቀምጡ