በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤
የአንበጣ መንጋ ወረርን!!!
ክፍል 2
በክፍል 1 በአንበጣና ፌንጣ መካከል ያለዉን ልዩነት ለማሳየት ሞክሬአለሁ። እንዲሁም ሰላማዊ የነበረዉ አንበጣ አካላዊና የባህርይ ለውጥ በማድረግ አረንጓዴ የሆነ ማንኛዉንም ተክል ለማዉደም በመንጋ በመጓዝ ጥቃት እንደሚያደርስ ለማሳየት ሞክሬአለሁ። አንበጦቹ በሰላም ከሚኖሩበት ወደ ጥቃት እንዲሄዱ የሚገፋፋቸዉ በአንጎላቸዉ ዉስጥ የሚገኝ ሴሮቶንኒን የተባለ ሆርሞን እንደሆነም መግለጼ ይታወቃል። ይህ ሆርሞን በሰዉ ልጅ አንጎልም ዉስጥ የሚገኝ ሲሆን ከቁጡነት፣ ድፕሬሽን እና ከመሣሠሉት ባህርያዎቻችን ላይ ተጽእኖ እንዲያሳድሩ ይታመናል።
በዛሬዉ ጽሑፌ በአሁኑ ጊዜ በመከሰት ላይ ያለዉ የአንበጣ መንጋ ጥቃት ምን እንደሚመስል ለማሳየት እሞክራለሁ።የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅትን ጠቅሶ ቢቢሲ ከሶስት ቀናት በፊት ባሳተመዉ ጽሑፍ እንደሚያሳየዉ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እየተቃጣ ያለዉ የአንበጣ ጥቃት በአጭር ጊዜ በቁጥጥር ሥር መዋል ካልቻለ የጎረቤት ሀገራት ወደሆኑት ወደ ኬኒያ፣ ኤርትራ እና ሱዳን ሊዛመት እንደሚችል ነው።

ከላይ በካርታዎቹ ዉስጥ የሚታዩት ምልክቶች የሚከተሉትን ይወክላሉ።
- አረንጓዴ (ሰላም)፤ ምንም የአንበጣ ጥቃት አልደረሰም። ቢሆንም ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል።
- ቢጫ (ጥንቃቄ)፤ ጥቃት ሊደርስ ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የመቆጣጠር እርምጃም መወሰድ ያስፈልጋል።
- ብርቱካናማ (ጥቃት)፤ የሰብሎች ጥቃት ይደርሳል። የክትትልና መከላከል እርምጃ መዉሰድ ያስፈልጋል።
- ቀይ (አደገኛ)፤ ከፍተኛ የሰብል ጥቃት ይደርሳል። ከፍተኛ የክትትልና መከላከል ዕርምጃ መዉሰድ ያስፈልጋል።
በዚሁ መሠረት በአፕሪል 2019 አረንጓዴ የነበረዉ የኢትዮጵያ አካባቢ ከስድስት ወራት በኋላ በኦክቶበር 2019 ወደ ቀይ ወይም አደገኛነት ተቀይሯል ማለት ነዉ።
በዚሁ ሪፖርት መሠረት ከዘጠኙ የኢትዮጵያ ክልሎች ዉስጥ በአራቱ ማለትም በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ የአንበጣ ጥቃት በመድረስ ላይ ይገኛል። በተለይም በሰሜናዊ የአማራ ክልል የጤፍ እርሻ ሙሉ በሙሉ የወደመበት ሥፍራ እንዳለ ተዘግቧል። የምግብና እርሻ ድርጅት ሪፖርትም በተለያየ ወቅት የነበረዉን የአንበጣ ሥርጭትንና ጥቃትን ያሳያል።
በሚቀጥለዉ በሌላ ብሎግ እስክንገናኝ ድረስ መልካሙን እመኛለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ኅዳር 3፣ 2012 ዓ.ም. (November 13, 2019)