በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤
የአንበጣ መንጋ ወረርን!!!
ክፍል 1
አንበጣና ፌንጣ በዝምድናቸዉ ይቀራረባሉ። በተለይም አንበጣ አጭር ቀንድ ወይም አንቴና ካለዉ ፌንጣ ጋር እጅግ ይቀራረባል። ፌንጣ የሚባሉት ባብዘኛዉ በጓሮአችን በተናጠል የሚታዩት ሲሆኑ አንበጣ ብለን የምንጠራቸዉ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ በመራባት በሰብሎቻችን ላይ እጅግ ከፍተኛ ዉድመት የሚያደርሱት ናቸዉ። እነዚህ በማንኛዉም አረንጓዴ ተክል ላይ በመዝመት ያለ አንዳች ርህራሄ የሚያወድሙት ፍጡሮች የበረሃ አንበጣ ወይም በሣይንሳዊ አጠራር Locusta migratoria ወይም ተጓዡ አንበጣ ወይም Schistocerca gregaria ይባላሉ። በአሁኑ ወቅት ይህ የአንበጣ መንጋ ሀገራችንን ጨምሮ በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ላይ ከፍተኛ ዉድመት እያደረሰ ነዉ። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ሁሉም አንበጣዎች በሰብሎቻችንን ጥቃት አለማድረሳቸዉ ነዉ። አንበጣዎች በሰብሎቻችን ላይ ጥቃት የሚያደርሱት በከፍተኛ ሁኔታ ሲራቡና አካላዊና የባህርይ ለውጥ ካደረጉ ብቻ ነዉ።
የዛሬ ጽሑፌን በጥያቄና መልስ መልክ አቀርባለሁ።
- በአንበጣና ፌንጣ መካከል ያለዉ የባህርይና አካላዊ ለዉጥ ምን ይመስላል? በሁለቱ ፍጥረታት መካከል ያለዉ ልዩነት ከዚህ በታች ባለዉ ሠንጠረዥ ባጭሩ ቀርቧል።
| ፌንጣ | አንበጣ | |
| የኑሮ ሁኔታ | በተናጠል | በመንጋ (በተናጠል የሚኖርም አለ) |
| የሰውነቱ መጠን | ተለቅ ያለ | አነስተኛ |
| ክንፍ | አጭር | ረዥምና ጠንካራ |
| የዉጭዉ መልክ | ቡኒ ውይም አረንጓዴ | ከብሩህ ቀይ ወደ ቢጫነት ይቀየራል |
| የመብረር ሁኔታ | መዝለል ብቻ | ረዥም ርቀት የመብረር ችሎታ |
| የሚመገበዉ | ሣር | ሰብልና ማንኛዉንም አረንጓዴ ተክል |
- ሰላማዊ የሆነ አንበጣ እንዴት ወደ አውዳሚ መንጋነት ይቀየራል? አንበጣ ባብዘኛዉ በተናጠል የሚኖር ሲሆን በተወሰነ ምክንያት በተናጠል የመኖር ሁኔታን ትቶ ወደ መንጋነትና አውዳሚነት ይቀየራል። የድርቅ ወቅትን ተከትሎ አረንጓዴ ተክሎች (ሰብሎቻችንን ጨምሮ) ባፋጣኝ ሲያድጉ አንበጣዎቹ በፍጥነትና በብዛት እንዲራቡ አመቺ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል። እነዚህ በከፍተኛ መጠን የተባዙ አንበጣዎች የአካላዊም ሆነ የባህርይ ለዉጥ ያካሂዳሉ።
- ወደ አዉዳሚነት የሚቀየሩት አንበጣዎች ምን ዓይነት አካላዊ ለዉጥ ያካሂዳሉ? ክንፎቹ በተለይ ከኋላ ያሉት ወደ ረዥምና ጠንካራነት ይለወጣሉ። ይህም አንበጣዎቹ ረጅም ርቀት ለመብረር ያስችላቸዋል።
- እነዚህ ወደ አዉዳሚነት የሚቀየሩት አንበጣዎች ምን ዓይነት የመልክ ለዉጥ ያካሂዳሉ? ከብሩህ ቀይ ወደ ቢጫማነት ይቀየራሉ።

በከፍተኛ መጠን የተባዙ አንበጣዎች ምን ዓይነት የባህርይ ለዉጥ ያካሂዳሉ? ከጨዋነት ወደ አዉዳሚነት እንዲሁም በተናጠል ከመኖር ወደ መንጋነትና ወራሪት ይቀየራሉ።
እነዚህ በከፍተኛ መጠን የተባዙ አንበጣዎች ምን ዓይነት የሆርሞን ለዉጥ ያካሂዳሉ? በአንበጣዎቹ አንጎል ዉስጥ የሚገኘዉ ሴሮቶኒን (serotonin) የተባለዉ ሆርሞን ከላይ ለተጠቀሱት የባህርይ ለዉጥ መንስኤ እንደሆኑ ከአሥር ዓመት በፊት የተሠራ ጥናት አረጋግጧል። ይህ የአንበጣዎቹን ባህርይ የሚቀይረዉ ሆርሞን በሰዉ ልጅ አንጎል ዉስጥም የሚገኝ ሲሆን ዋና ሚናዉ ዲፕሬሽን፣ ቁጡነት፣ እና የመሳሰሉት ላይ ተጽእኖ አለዉ።
አንድ አንበጣ ምን ያህል ይመገባል? አንድ አንበጣ በቀን የራሱን ክብደት ያህል መመገብ የሚችል ሲሆን ይህም እስከ ሶስት ግራም ሊሆን ይችላል።
የአንድ አንበጣ መንጋ ምን ያህል ሊሆን ይችላል? የአንድ አንበጣ መንጋ መጠን እንደሁኔታዉ ሊለያይ ቢችልም እስከ 50 ሚሊዮን ነፍሳት ሊኖሩት ይችላል።
በአንድ መንጋ ያለ አንበጣ ምን ያህል ሰብል ሊያወድም ይችላል? አንድ መጠነኛ የሆነ የአንበጣ መንጋ በቀን እስከ 80 ሺህ ቶን (ወይም 80 ሚሊዮን ኪ.ግ.) ሰብል ወይም አረንጓዴ ተክል ሊመገብ ወይም በሌላ አነጋገር ሊያወድም ይችላል። ይህ መጠንም እስከ 100 ሺህ ሰዉ ለአንድ ዓመት ሊመግብ እንደሚችል ይገመታል።
የአንድ አንበጣ መንጋ ምን ያህል ሊጓዝ ይችላል? እነዚህ አውዳሚ አንበጦች በንፋስ ታግዘዉ የሚበሩ ሲሆን በሰዓት ከ15 እስከ 20 ኪ. ሜ. ሊበሩ ይችላሉ። በቀን እስከ 130 ኪ.ሜ. እንደሚበሩ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከዚህ በፊት በዓለማችን የተከሰቱ የአንበጣ ጉዳቶች ምን ይመስላሉ? የአንበጣ መንጋ ከፍተኛ ጉዳት ያደርስ እንደነበረ በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት ብቻ ወደ ስድስት የሚጠጉ ለበርካታ ዓመታት የቆዩ በአንበጣ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳቶች በዓለማችን ተከስተዋል። እነዚህ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆዩ መጠነ ሰፊ ጉዳቶች በእንግሊዘኛዉ አጠራር plaque ተብለዉ ይጠራሉ። እ.ኤ.አ. ከ1985 እስከ 1989 ድረስ የነበረዉ ይህ ክስተት 43 በአፍሪካና ኤሲያ የሚገኙ አገሮችን ያጠቃ ሲሆን በአፍሪካ ብቻ 5.5. ሚሊዮን ሄክታር የሚሆን እርሻ ላይ ጉዳት አድርሷል። በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ሌሎች የጎረቤት ሀገራት ላይም ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ ነበር።

በአሁኑ ወቅት በሀገራችንና አካባቢ ስለተከሠተዉ የአንበጣ ጥቃት በክፍል 2 እጽፋለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ኅዳር 3፣ 2012 ዓ.ም. (November 13, 2019)