ግብርናችንን ለማዘመን፤ የማሽላዉ አባት፣ ክፍል 4

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የማሽላዉ አባት፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን

ክፍል 4

በሦስት ተከታታይ ክፍሎች በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉትና በማድረግም ላይ ስለሚገኙት የ84 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ስለሆኑት ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን ስለ ዕድገታቸዉ፣ የሥራ ልምዳቸዉ፣ የሥራ ባልደረቦቻቸዉ በተለይም በሰፊዉ ስለሚታወቁበት የማሽላ ምርምር የሚያትቱ ጽሑፎች አቅርቤ ነበር። በዛሬዉ ክፍል 4 እና የመጨረሻ ጽሑፌ ደግሞ በማሽላ ላይ ስለነበረዉና በአሁኑ ጊዜም ስላለዉ ምርምር ተጨማሪ መረጃ የሚሰጡኝ ሲሆን ገጠመኞቻቸዉንም ያጫውቱኛል።

ምስሉ የሚያሳየዉ ዶክተር ብርሃኔ በአንድ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ሆነዉ ነዉ።

ማስገንዘቢያ፣ ካልተገለጸ በስተቀር በጽሑፉ ውስጥ የተጠቀሱት ቀናት ሁሉ እንደ አዉሮፓውያን አቆጣጠር ነዉ።

ጥያቄ፤ በአሜሪካ ብሔራዊ የምርምር ካዉንስል በ1996 የታተመዉ Lost Crops of Africa በሚለዉ መጽሐፍ ከገጽ 181-182 ስለ ኢትዮጵያ ማሽላ ተጽፏል። በተለይም ወተት በጉንጬ እና ማርጩቄ ስለሚባሉት ታዋቂ የማሽላ ዓይነቶች። እንደ ጽሑፉ አባባል እነዚህ ሁለት ዝሪያዎች ምንም እንኳ የፕሮቲን መጠናቸዉ ከፍተኛ ቢሆንም በምርምራቸዉ ወደፊት ሊገፉ አልቻሉም። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰዉ እነዚህ ሁለት ዝሪያዎች በቀላሉ ለወፍ፣ ተባይና በሽታ ስለሚጠቁ ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ ወተት በጉንጬ እና ማርጩቄ ሲፈጩ የሚሰጡት ዱቄት ጥራቱ ዝቅተኛ እንደሆነ ይገልጻል። ይህ መረጃ ትክክል ነዉን?

ዶክተር ብርሃኔ፤ ወተት በጉንጬ ወይም ማርጩቄ የሚባሉት ሁለት የተለያዩ ስያሜዎች ቢሰጣቸዉም ሁለቱም ስሞች የአንድ የማሽላ ዓይነትን ይወክላሉ። ይህ የማሽላ ዓይነት ጣፋጭ ከመሆኑም በተጨማሪ በዉስጡ ከፍተኛ የሆነ ላይሲን የተባለ አስፈላጊ ንጥረ ነገርና ፕሮቲን ይዟል። ይህ የማሽላ ዓይነት ከወሎ አካባቢ የተገኘ ነዉ። ከላይ በጠቀስከዉ መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸዉ ምንም እንኳ የዚህ ማሽላ ዓይነት እጅግ ከፍተኛ የሆነ ለሰዉነታችን ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮች በዉስጡ ቢይዝም የተደረጉት ሰፋ ያሉ ጥናቶች የተጠበቀዉን ያህል ውጤት ሊያመጡ አልቻሉም። ምክንያቱም በተደረጉት የማዳቀል ሥራዎች የወተት በጉንጬን ጥሩ ጎኖች በመውሰድ ከፍተኛ ምርት ወደሚሰጡት የማሽላ ዓይነቶች ማስተላለፍ አለመቻሉ ነዉ። የወተት በጉንጬ ደካማ ጎኑ በፍሬዉ ዉስጥ ያለው ኢንዶስፐርም (endosperm) ተብሎ የሚታወቀዉ ክፍል ለስላሳና የተሰባበረ በመሆኑ የፍሬዉ ክብደትም አነስተኛ ነዉ። ይህም የወተት በጉንጬ ማሽላ ሲፈጭ የሚሰጠዉ የዱቄት መጠን በጣም ዝቅ ያለ እንዲሆን ያደርገዋል። በዚሁ ምክንያት ይህ የማሽላ ዓይነት በብዛት የሚበቅልበት አካባቢ ጥቅም ላይ የሚዉለዉ በእሸትነቱ ጊዜ በመቁላትና በመመገብ ነዉ እንጂ በመፍጨትና በምግብ መልክ በመጠቀም አይደለም።

ጥያቄ፤ እርስዎ ከነበሩበት ወቅት ጋር ሲያወዳድሩት ባሁኑ ጊዜ የማሽላ ምርምርና ምርታማነት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ዶክተር ብርሃኔ፤ በሌሎቹ የሀገራችን ሰብሎች ምርምር ላይ እንደሚታየዉ ሁሉ የማሽላ ምርምርም በመስኩ የሰለጠነ የሰዉ ኃይል ረዘም ላለና ተከታታይነት ባለዉ መልኩ ለማቆየት አልቻለም። ምንም እንኳ ይህ የሰለጠነ የሰዉ እጥረት የምርምር ፕሮግራሙን በከፍተኛ ሁኔታ ቢፈታተነዉም ለተለያዩ ሥነ ምህዳር ላላቸዉ አካባቢዎች የተሻሻሉ ዝሪያዎችን በማስለቀቅ ወደ ገበሬው እንዲደርሱ ለማድረግ ተችሏል። በቅርብ ጊዜያት ከተለቀቁትና አምራቹ ዘንድ ከደረሱት የማሽላ ዝሪያዎች መካከል ዲቃላ ያልሆኑና የዲቃላ ማሽላ ዓይነቶችም ይገኙበታል። እነዚህም ጎብዬ፣ ተሻለ፣ ብርሃን፣ ESH1 እና ESH2 የተባሉትን ያካትታል። በዚሁ ምክንያት ባለፉት ዓመታት የማሽላ ምርታማነት እየጨመረ መሄዱ ምርምሩ ወደፊት እየሄደ እንደሆነ ያሳያል። እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት አሜሪካን ሀገር ከሚገኘዉ የፐርዱ ዩኒቨርስቲ በመሆን በኢትዮጵያ የማሽላ ማሻሻያ ፕሮግራም ዉስጥ የላቀ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ስለሚገኙት ሰለ ፕሮፌሰር ገቢሣ ኢጀታ ነዉ።

ጥያቄ፤ በሥራ ዘመንዎ ወቅት ፋታ የማይሰጥ የሥራ ጫና የነበርዎት መቼ ነበር? በዚያን ወቅት በቀን ለስንት ሰዓት ይሠሩ ነበሩ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ ለማሽላ ተመራማሪዎች ፋታ የማይሰጡ ጊዜያት በወቅት ላይ የተመሠረቱ ናቸዉ። በተለያዩ ሙከራ ጣቢያዎች የሚላኩ ዘሮችን ከማዘጋጀትና ማደራጀት አንስቶ በወቅቱ እንዲዘሩ ማድረግ፣ መረጃ መሰብሰብና መረጣ ማካሄድ፣ በመቀጠልም በወቅቱ እንዲታጨዱና እንዲወቁ ያለዉ ጊዜ ሁሉ የቅርብ ክትትል ይፈልጋል። በተለይም ዘር ከዘራን በኋላ ዝናብ እንዲዘንብልን በናፍቆት የምንጠብቀዉ ጊዜና የምንጸልየዉ አንዱ የሥራችን አካል ነበር። የምርምራችንን ጊዜም ለማፋጠን ከዋናዉ የሰብል ወቅት በተጨማሪ በመልካ ወረር ምርምር ጣቢያ በመስኖ በመታገዝ ስለምንሠራ ዓመቱን ሙሉ እረፍት አለ ማለት አይቻልም። በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የማሽላ ሙከራ ጣቢያዎችን መጎብኘት አንዱ ኃላፊነቴ ስለነበር በሀገሪቷ በሙሉ ሰፋ ያለ ጉዞ አካሄድ ነበር። በዋናዉ የሰብል ወቅት በቢሮና በመስክ በቀን ከ12 ሰዓታት በላይ ማሳለፍ የሚኖርብኝ ጊዜ የነበረ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ከሥራ መልስ ቤት የምሠራቸዉ የጽሑፍ ሥራዎችም ነበሩኝ።

ጥያቄ፤ በሥራ ዓለም ያጋጠሞት ገጠመኝ ወይም ፈታኝ ወቅት ካለ ቢያካፍሉኝ፤

ዶክተር ብርሃኔ፤ በርካታ ገጠመኞች ወይም ፈታኝ ጊዜያት ነበሩብኝ። የተወሰኑትን በተለይም ከማሽላ ሥራዬ ጋር የሚገናኙትን ባጭሩ ከዚህ በታች ለመጥቀስ እወዳለሁ።

  1. የመጀመሪያዉ ገጠመኜ የማስትሬት ትምህርቴን አጠናቅቄ በ1964 ከዉጭ እንደተመለስኩ በአለማያ እርሻ ኮሌጅ የአሜሪካ መምህሮቻችንን በኢትዮጵያኖች መተካቱ የተጀመረበት ወቅት ነበር። ስለዚህ በዚሁ በ1964 የትምህርት ዘመን በእኔና ሦስት የሥራ ባልደረቦች በዚህ በመተካካቱ ፕሮግራም እንድንካተት በመደረጉ ከፍተኛ የሥራ ድርሻና ኃላፊነት ወደቀብን። በዚህ ጊዜ በኔና በሥራ ባልደረቦቼ ላይ የነበረዉ ፈታኝ ሁኔታና ጭንቀት የማይረሳኝ ነዉ።
  2. ሁለተኛዉ ገጠመኜ በእርሻ ኮሌጁ መምህር በሆንኩ በአምስተኛዉ ዓመት ማለትም በ1969 መጨረሻ ላይ ተደራራቢ ኃላፊነቶች የወደቁብኝ ወቅት ነበር። ከእነዚህ ኃላፊነቶች ዉስጥ አንዱ የዕጽዋት ሣይንስ ዲፓርትመንት ኃላፊ መሆን ሲሆን ሌላዉ ደግሞ የብርዕና አገዳ የምርምር ክፍል ኃላፊነትም ደርቤ እንዲይዝ መደረጉ ነበር። በተመሣሣይ ወቅት የተለያዩ ኮርሶችም ማስተማር ነበረብኝ። ይህን ሁሉ የኃላፊነትና የማስተማር ሥራ በማስፈጽምበት ወቅት የምከተለዉ አንዳችም መመሪያ አልነበረም። እንደ አርአያ ሆኖልኝ የምከተለዉ ሰዉም አልነበረኝም።
  3. ሶስተኛዉ ገጠመኜ በ1976 በህይወቴ ዉስጥ ካደረኳቸዉ ከፍተኛ ውሳኔዎች መካከል አስቸጋሪዉንና ከባዱን የወሰንኩበት ዓመት ነበር። ይህም የአለማያ ኮሌጅ ግቢን ለቅቄ IDRC ከተባለዉ የካናዳዉ የዕርዳታ ድርጅት ባገኘሁት ድጋፍ ያቋቋምኩትን የብሔራዊ የማሽላ ማሻሻያ ፕሮግራም ለማስተባበር አዳማ አካባቢ ወደሚገኘዉ ወደ መልካሳ ምርምር ጣቢያ ለመጓዝ መወሰኔ ነበር።
  4. ሌላዉ ገጠመኜ ወይም ፈታኝ ወቅት ከዚሁ ወደ መልካሳ ከተጓዝኩበት ውሳኔ ጋር ይገናኛል። ይኸዉም ለሁለት አለቆች ሪፖርት ማድረግ ያለብኝ ስለነበረ ነዉ። አንዱ አለቃዬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር የነበረዉ የአለማያ እርሻ ኮሌጅ ሲሆን ሁለተኛዉ አለቃዬ ደግሞ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ነበር። የአስተዳደር ሥራዎችን በተመለከተ በአለማያ ሥር የነበርኩ ሲሆን በሥራ ማስፈጸም በኩል በእርሻ ምርምር ሥር ነበርኩ።
ዶክተር ብርሃኔ የ52 ዓመት የትዳር ጓደኛቸዉ ከሆኑት ከወይዘሮ ገነት ታደሰ ጋር በሎዛን ስዊዘርላንድ የሚገኘዉን የኦሎምፒክ ሙዚየም በጎበኙበት ወቅት።

በ1979 የኢትዮጵያ ሁኔታ የተረጋጋ አልነበረም። በዚሁ ምክንያት ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሰባሰብናቸዉን ወደ 5,000 የሚጠጉ የማሽላ ዓይነቶችን ልናጣ የምንችልበት ሁኔታ ላይ ደርሰን ነበር። ይህም እንዳይከሰት አንድ አስቸጋሪ ዉሳኔ መወሰን ነበረብኝ። ይህም እነዚህ ዕንቁ ዝሪያዎችን በሦስት የተለያዩ ቦታዎች እንዲቀመጡ ማድረግ ነበር። እነዚህ ዘሮች በአስተማማኝነት እንዲቀመጡ ያደረኩባቸዉ ሥፍራዎች በአዲስ አበባ የሚገኘዉ የብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት፣ ICRISAT የተባለው በህንድ ሀገር በሃድራባድ የሚገኘዉ ዓለም አቀፍ ድርጅት እና ዋሽንግተን ዲ ሲ የሚገኘዉ USDA የተባለዉ የአሜሪካ የእርሻ ዲፓርትመንት ናቸዉ።

በ1982 ICRISAT ለሚባለዉ ዓለም አቀፍ ድርጅት በምሠራበት ወቅት የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የማሽላ ማሻሻያ ማዕከል በናይሮቢ ማቋቋም ነበረብኝ። ይህንንም ምንም መሠረት ካልነበረበት ሁኔታ ተነሥቼ ማቋቋም ሰለነበረብኝ አንዱ ፈታኝ ወቅት ነበር።

ሌላው በህይወቴ ሙሉ የማልረሳዉ ትዝታዬ በ1988 ሜሩ በምትባለዉ የኬንያ ከተማ አካባቢ በኔና በአራት ኬንያዊያን ፕሮፊሽናል የሥራ ባልደረቦቼ ላይ የደረሰብን አሰቃቂ የመኪና አደጋ ነዉ። በዚህ የከፋ አደጋ ሁለቱ ኬንያውያን የሞቱበት በተረፍነዉ ላይም ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰብን ነበር። የዚህን የከፋ አደጋ ሁኔታ ከጭንቅላቴ ውስጥ ፍቄ ላወጣዉ አልቻልኩም።

በዚሁ ከዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን ጋር በአራት ከፍሎች የቀረቡ ቃለ መጠይቆች አበቃለሁ። በርካታ ትምህርት እንደወሰዳችሁ አምናለሁ።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኝላችኋለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥቅምት 2፣ 2012 ዓ.ም. (October 13, 2019)

አስተያየት ያስቀምጡ