ግብርናችንን ለማዘመን፤ የማሽላዉ አባት፣ ክፍል 3

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የማሽላዉ አባት፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን

ክፍል 3

በክፍል አንድና ሁለት ጽሑፌ በግብርናዉ መስክ ላለፉት 55 ዓመታት በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉትና በማድረግም ላይ ስለሚገኙት ስለ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን አጠቃላይ የሥራ ልምዳቸዉና በሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ደረጃ በኃላፊነት ስላሳለፉበት ጊዜ ስለነበረዉ ሁኔታ ያደረኩላቸዉን ቃለ መጠይቅ አቅርቤ ነበር። በተጨማሪም በኢትዮጵያ የማሽላ ምርምር ላይ ስላደረጉት አስተዋጽኦ የሚያወሳ ጽሑፍም አስነብቤ ነበር። በዛሬዉ ጽሑፌ ደግሞ ስለ ዕድገታቸዉ፣ የሥራ ጸባያቸዉና ተማሪዎቻቸዉ የነገሩኝን አካፍላችኋለሁ።

ማስገንዘቢያ፣ ካልተገለጸ በስተቀር በጽሑፉ ውስጥ የተጠቀሱት ቀናት ሁሉ እንደ አዉሮፓውያን አቆጣጠር ነዉ።

ጥያቄከዚህ ቀደም በቀረቡት ሁለት ክፍሎች በርካታ ጥያቄዎች ጠይቄዎት ነበር። ነገር ግን ስለ ዕድገትዎና የልጅነት ጊዜዎ ሳልጠይቅዎት ቀረሁ። ለመሆኑ መቼና የት ተወለዱ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ የተወለድኩት ኦግስት 12፣ 1936 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ነሐሴ 6፣ 1928) የአዲስ አበባ መሃል በነበረዉ የአራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ ነዉ። እንደሚታወቀዉ በዚያ እኔ በተወለድኩበት ወቅት የኢጣሊያ ወረራ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተስፋፋ የነበረበት ጊዜ ነበር።

ጥያቄ፤ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትዎን የት ተማሩ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ በዚሁ የኢጣሊያ ወረራ ምክንያት መላዉ ቤተሰቤ ከአዲስ አበባ ለቆ ለመሄድ ተገደደ። ለዚሁም አመቺ ይሆናል ተብሎ የተመረጠዉ ሥፍራ ከአዲስ አበባ ራቅ ያለ ገጠራማ መንደር ነበር። ይህም መንደር የሚገኘዉ ሙህር በሚባለዉ የጉራጌ አካባቢ ነበር። ፊደል የቆጠርኩት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ልማድ መሠረት በአካባቢዉ በሚገኘዉ ታዋቂዉ የሙህር ገዳም ኢየሱስ ነበር። ከሦስት ዓመታት የገዳም ኢየሱስ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቴ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተዛዉሬ መደበኛ ትምህርቴን ጀመርኩ። በዚሁ መሠረት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ለገሀር አካባቢ በሚገኘዉ የቀድሞ በየነ መርዕድ ትምህርት ቤት ተከታትዬ አጠናቀኩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን Point-4 Program (በአሁኑ USAID) ተብሎ በሚጠራዉ በአሜሪካን መንግሥት ድጋፍ በተቋቋመዉ በወቅቱ የጅማ የእርሻ ቴክኒካል ትምህርት ቤት (Jimma Agricultural Technical School – JATS) ገብቼ ልማር ችያለዉ። በጂማ የነበረዉን ትምህርቴን እንዳጠናቀኩ አለማያ ወደሚገኘዉ በወቅቱ Imperial Ethiopian College of Agricultural and Mechanical Arts ይባል በነበረዉ የእርሻ ኮሌጅ ገብቼ የመጀመሪያ ዲግሬዬን ለማግኘት ችያለሁ።

ጥያቄ፤ እርስዎ በአለማያ እርሻ ኮሌጅ ያስተማሯቸዉ ተማሪዎች በአሁኑ ጊዜ በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ? ስለ ጥቂቶቹ ቢገልጹልኝ።

ዶክተር ብርሃኔ፤ በአለማያ ኮሌጅ ለበርካታ ዓመታት ባስተማርኩበት ወቅት የተለያዩ ኮርሶች ከኔ የወሰዱ ተማሪዎች በርካታ ናቸዉ። በርካታ ከመሆናቸዉም የተነሣ ቆጥሬ ልደርስባቸዉ አልችልም። በዚሁ ምክንያት አንዳንዶቹ ባሁኑ ጊዜ የት እንዳሉም ማወቅ ያዳግተኛል። ይህ ቃለ መጠይቅ ከማሽላ ምርምር ጋር በነበረኝ ሁኔታ ላይ ስለሚያተኩር በክፍል 2 ቃለ መጠይቄ ስለገለጽኩትና IDRC ተብሎ በሚጠራዉ የካናዳ ዕርዳታ ድርጅት በተገኘ ድጋፍ ባቋቋምኩት የኢትዮጵያ ማሽላ ማሻሻያ ፕሮግራም (ወይም ባጭሩ ESIP ተብሎ ይጠራ በነበረዉ) ውስጥ ለረዥም ጊዜ ከኔ ጋር በቅርበት ከሠሩት ጋር አተኩራለሁ። ይህንኑ የማሽላ ማሻሻያ ፕሮግራም በጀመርኩበት በ1973 ከአለማያ እርሻ ኮሌጅ በባችለር ዲግሪ በቅርብ የተመረቁ አራት ወጣቶች ተቀላቀሉኝ። እነርሱም አጥናዉ አይተንፍሱ፣ ገቢሣ እጀታ፣ ሰለሞን ኬቤታ እና ይልማ ከበደ የተባሉት ናቸዉ። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ አበበ መንክር የተባለ ሌላ የዚሁ ኮሌጅ ተመራቂ ፕሮጀክታችንን ተቀላቀለ። እነዚህ ስማቸዉ ከላይ የጠቅስኳቸዉ የሥራ ባልደረቦቼ ለተከታታይ ትምህርት ወደ ካናዳና አሜሪካ ተላኩ። ከአጥናዉ በስተቀር ሁሉም እስከ ዶክትሬት ደረጃ ሊማሩ ችለዋል። አጥናዉ ከሁለተኛ ዲግሪ በኋላ ትምህርቱን አልቀጠለበትም። ከነዚህ የቀድሞ የማሽላ ማሻሻያ ፕሮግራም ባልደረቦቼ መካከል ዶክተር ገቢሣ በዓለም የሚታወቀዉን የዓለም የምግብ ሽልማት (World Food Prize የሚባለውን) የተሸለመ ሲሆን ባሁኑ ጊዜ በአሜሪካ የፐርዱ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ነዉ። ዶክተር ይልማ ደግሞ ከላይ የተጠቀሰዉን የማሻላ ማሻሻያ ፕሮግራም አስተባባሪ በመሆን ለረዥም ዓመታት ሠርቷል። በመቀጠልም ፓዮኒር በተባለዉ ግዙፍ የዘር ማምረቻ ኩባንያ እና ቀጥሎም ቢልና ሜሊንዳ ጌትስ በሚባለዉ በዓለማችን ትልቁ ግብረ ሠናይ ድርጅት የማሽላ ከፍተኛ ኤክስፐርት በመሆን አገልግሏል። ዶክተር ሰለሞን ደግሞ በካናዳ የእርሻ ዲፓርትመንት ውስጥ የገብስና ሲናር ምርምር ኃላፊ በመሆን አገልግሏል። ዶክተር አበበ ባሁኑ ጊዜ IITA ተብሎ በሚጠራዉ ዓለም አቀፍ የምርምር ማዕከል ዉስጥ የበቆሎ ማሻሻል የፕሮግራም መሪ ነዉ።

ጥያቄ፤ በረዥም የሥራ ዘመንዎ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰፊዉ የተጓዙ ይመስለኛል። ከተጓዙበት ሥፍራ ያልተጓዙበትን መጥራት ሳይቀል አይቀርም። እስካሁን የትኛዉን የሀገሪቱን ክፍል ለማየት ዕድሉን አላገኙም?

ዶክተር ብርሃኔ፤ ማሽላ አብቃይ የሆኑ ሥፍራዎችን ሁሉ ለማየት ዕድሉ ገጥሞኛል፣ ኤርትራንም ጨምሮ።

ጥያቄ፤ እርስዎ የኢትዮጵያ የማሽላ ምርምርን በሚያስተባብሩት ወቅት የሰብሉ ምርት እንዳያድግ አንቀዉ ከያዙት ዉስጥ ዋናዎቹ የትኞቹ ነበሩ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ የማሽላ ምርታማነት እንዳያድግ በከፍተኛ ደረጃ የሚፈታተኑት እንደ ቅደም ተከተላቸዉ ከትልቁ ወደ ትንሹ የሚከተሉት ናቸው።

  1. የዝናም እጥረትና ድርቅ፣
  2. ተባይና ወፍ በተለይም ግንድ ሠርሳሪዉ ትልና ግሪሳ የሚባለዉ የወፍ መንጋ፣
  3. የአረም ጥቃት ሲሆን ባንዳንድ ሥፍራዎች የአቀንጭራ ችግር፣
  4. ለተለያየ ሥነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ ምርጥ ዝሪያዎች አለመኖር እና
  5. ተስማሚ የሰብል እንክብካቤ ዘዴዎች አለመኖር ናቸዉ።
ምሥሉ የሚያሳየዉ ቆቦ አካባቢ በደህና ሁኔታ አድጎ ያለ የማሽላ ማሳን ነዉ። ፎቶ፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን

ጥያቄ፤ ገበሬዎች ለማሽላቸዉ የተለያየ ስያሜ ይሰጧቸዋል። ከነዚህ ዉስጥ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ወተት በጉንጬ፣ ወፍ አይበላሽ፣ ስንዴ ለምኔ፣ ቂጥኝ አይፈሬ፣ ጋን ሰበር እና ፈንዲሻ የተባሉት ይገኙበታል። እነዚህ ስሞች ምንን ያመለክታሉ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ ወተት በጉንጬ የተባለዉ ዝሪያ በእሸትነቱ ተጠብሶ ሲበላ በተመጋቢዎች ዘንድ ጣፋጭ ሆኖ ተወዳጅ ከመሆኑም በተጨማሪ ከፍተኛ ላይስን እና በጠቅላላዉ ከፍተኛ የሆነ ፕሮቲን በዉስጡ የያዘ ነዉ። ወፍ አይበላሽ የተባለዉ ዝሪያ ደግሞ ፍሬዉ ጎምዛዛ ስለሆነ የወፎች ጥቃት አይደርስበትም። ስንዴ ለምኔ የሚባለዉ ዝሪያ ደግሞ ከሱ የሚጋገረዉ ዳቦ ከስንዴ ከሚጋገረዉ ጋር በጥራቱ ተቀራራቢነት ስላለዉ ነዉ። ቂጥኝ አይፈሬ የተባለ ስያሜ የተሰጠዉ ዝሪያ ደግሞ የአቀንጭራ ጥቃትን ለመቋቋም በመቻሉ ነዉ። ጋን ሰበር የተባለዉ ዝሪያ ደግሞ ኃይለኛና ጥሩ ጠላ የሚያስጠምቅ ነዉ። ፈንዲሻ የተባለዉ ዝሪያ ሲቆላ ፈንድቶ ጥሩ ካሽ ካሽ የሚል መክሰስ ይሆናል።

ከዶክተር ብርሃኔ ላይ ያደረኩት ቃለ መጠይቅ በዚህ አያበቃም። በክፍል 4 በማሽላ ላይ ስለሚደረገዉ ምርምር ተጨማሪ መረጃ የሚሰጡኝ ሲሆን ገጠመኞቻቸዉንም ያጫውቱኛል። እስከዚያዉ መልካም ጊዜ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ጥቅምት 2፣ 2012 ዓ.ም. (October 13, 2019)

አስተያየት ያስቀምጡ