ግብርናችንን ለማዘመን፤ የማሽላዉ አባት፣ ክፍል 2

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የማሽላዉ አባት፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን

ክፍል 2

በክፍል አንድ ጽሑፌ በግብርናዉ መስክ ላለፉት 55 ዓመታት በሀገር አቀፍም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉትና በማድረግም ላይ ስለሚገኙት ስለ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን አጠቃላይ የሥራ ልምዳቸዉና በሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ደረጃ በኃላፊነት ስላሳለፉበት ሁኔታ አስነብቤ ነበር። በዛሬዉ ጽሑፌ ደግሞ እኚሁ አንጋፋ የግብርና ምሁር በተለይ ስለሚታወቁበት የማሽላ ምርምር ላይ አተኩራለሁ። በክፍል አንድ እንደቀረበዉ ሁሉ የዛሬዉ ጽሑፌም ከምሁሩ ጋር በተደረገዉ ቃለ መጠይቅ መልክ ይቀርባል።

ማስገንዘቢያ፣ ካልተገለጸ በስተቀር በጽሑፉ ውስጥ የተጠቀሱት ቀናት ሁሉ እንደ አዉሮፓውያን አቆጣጠር ነዉ።

ጥያቄ፣ በክፍል አንድ እንደገለጹልኝ የመጀመሪያ የምርምር ሥራዎን በሀረማያ ኮሌጅ የጀመሩት በገብስ ላይ ነበር። ለሶስት ዓመታት ብቻ በገብስ ምርምር ከቆዩ በኋላ ለዶክትሬት ትምህርትዎ ወደ አሜሪካን ሄዱ። ትምህርትዎን አጠናቅቀዉ ሲመለሱ የበቆሎ ተመራማሪ ሆኑ። የምርምር አቅጣጫዎን ከገብስ ወደ በቆሎ የቀየሩብት ዋናው ምክንያት ምንድነው?

ዶክተር ብርሃኔ፣ እንደአጋጣሚ ሆኖ ትምህርቴን በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሚኔሶታ በምጨርስበት የመጨረሻ ዓመት ላይ ሲግራም (Seagram) የሚባለዉ የካናዳ ዊስኪ አምራች ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ ለበቆሎ ምርምር ጠቀም ያለ መዋዕለ ንዋይ እንደሚሰጡኝ ፍንጭ ሰጥተዉኝ ነበር። በጊዜዉ ይህንን ያደረጉበት ዋናዉ ምክንያት ለዊስኪ ምርታችዉ የሚዉል በርከት ያለ በቆሎ ረዘም ላለ ጊዜ ከኢትዮጵያ ለመግዛት ፍላጎት ስለነበራቸዉ ነዉ። በዚያዉም ለኢትዮጵያ ልማት አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አስበዉ ነበር። ለዚህ ሁሉ ዓላማቸዉ የተሻሻሉ የበቆሎ ዝሪያዎች እንደሚያስፈልጉ ግልጽ ነበር። በዚሁ መሠረት ወደ አለማያ እንደተመለስኩ የተባለዉን የፋይናንስ ጥያቄ በፕሮፖዛል መልክ ለዚሁ ሲግራም ለተባለዉ ኩባንያ አስገብቼ ለበቆሎ ምርምር የሚዉል ጠቀም ያለ የገንዘብ ድጎማ አገኘሁና ወደ በቆሎ ማሻሻል ምርምር ማድላት ጀመርኩ። በዚሁ የተነሣ የገብስ ማሻሻል ሙያዬን ትኩረት እየቀነስኩ ሄድኩ ማለት ነው።

ጥያቄ፣ በበቆሎ ምርምርም የቆዩት ለሁለት ዓመታት ብቻ ነበር። በብዙዎች ዘንድ በሰፊዉ ወደ ሚታወቁበት የማሽላ ምርምር ገቡ። ለምን በበቆሎ ምርምር መቆየት አልፈለጉም?

ዶክተር ብርሃኔ፣ በበቆሎ ላይ ምርምር በምሠራበት ወቅት የማሽላ ምርምርንም ደርቤ እሠራ ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት በወቅቱ በዕጽዋት ሣይንስ ዲፓርትመንት ሌላ የማሽላ ምርምርን በኃላፊነት የሚሠራ የሰለጠነ የሰዉ ኃይል ስላልነበረ ነዉ። ሌላዉ ደግሞ በወቅቱ በማሽላ ምርምር እንደ ሊቅ ከሚቆጠሩት ዶክተር ሂዮ ዶጌት ከተባሉ ምሁር ጋር የቅርብ የምርምር ግንኙነት ፈጥሬ ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ዶክተር ዶጌት አይ ዲ አር ሲ (IDRC International Development Research Center) ከተባለ የካናዳ ግብረ ሠናይ ድርጅት የኢትዮጵያ የማሽላ ምርምር በአፍሪካ ግንባር ቀደም እንዲሆን የሚያስችል ሰፋ ያለ የምርምርና የሰው ኃይል ማሰልጠኛ እንዳቋቁም የሚረዳኝ የገንዝብ ድጋፍ እንዳገኝ አመቻቹልኝ። አለማያ አካባቢ ማሽላ ቀዳሚ ሰብል በመሆኑና አዲስ ከIDRC ባገኘሁት ጠቀም ያለ የገንዘብ ድጋፍ ትኩረቴን ወደ ማሽላ አዞርኩ። በዚሁ መሠረት የበቆሎዉን ምርምር ከሥልጠና በቅርቡ ለተመለሰዉ ለዶክተር ደጀኔ መኮንን አስተላለፍኩ። እኔም ከማሽላ ጋር የጠበቀ ግንኙነቴን ጀመርኩ ማለት ነዉ።

ጥያቄ፣ ከ1973 እስከ 1982 ድረስ ባሉት አሥር ዓመታት የማሽላ አዳቃይና የብሔራዊ ማሽላ ምርምር አስተባባሪ ነበሩ። የሥራ ምድብዎ ደግሞ ሀረማያና አዳማ ነበሩ። እነዚህ ሁለት ጣቢያዎች የተራራቁ ብቻ ሳይሆኑ በሁለት ድርጅቶች (እርሻ ኮሌጅና እርሻ ምርምር) ሥር የሚተዳደሩ ነበሩ። በነዚህ ሁለት ጣቢያዎች እንዴት ባንድ ጊዜ ይሠሩ ነበር?

ዶክተር ብርሃኔከላይ እንደገለጽኩት የማሽላ ምርምር የጀመርኩት አለማያ ነዉ። ይህም ሆኖ ምርምሬ የሚያተኩረዉ በመላ ኢትዮጵያ ነበር። ከካናዳዉ የእርዳታ ድርጅትም ያደረግነዉ ስምምነትም ይህንኑ መሠረት ያደረገ ነበር። ስለዚህ የተለያየ ስነምህዳር ያላቸዉን የማሽላ አብቃይ የኢትዮጵያ አካባቢዎችን የሚወክሉ የማሽላ ምርምር ጣቢያዎች መምረጥ ነበረብን። እነዚህ ስነምህዳሮችም ወይና ደጋ፣ ዝናም አጠር ቆላ፣ ዝናም ጠገብ ቆላ የመሣሰሉት ናቸዉ። ይህንን ሥራ በቅድሚያ እናካሄድ የነበረዉ ወደ ምሥራቅ ባጋደለው አለማያ ነበር። መሃል ኢትዮጵያ ሆኖ ለአገር አቀፍ ማሽላ ምርምር ማስተባበሪያ የሚሆን ቦታ ሳፈላልግ አዳማ አካባቢ ያለዉን የመልካሳ ምርምር ጣቢያ ተስማሚ ሆኖ አገኘሁት። በዚህም ምክንያት ከእርዳታ ድርጅቱ ያገኘሁትን ድጋፍ ሁሉ፣ ቁሳቁስ፣ የሰዉ ኃይልና ገንዘብ ይዤ ወደ አዳማ መልካሳ ገባሁ። ከዚህም ሥፍራ ሆኜ የሀገር አቀፉን የማሽላ ምርምር መሥራትና ማስተባበር ጀመርኩ። ይህን ሁሉ ስናደርግ በጊዜዉ የእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ምንም የማሽላ ምርምር ሥራ አልነበረዉም። ሙሉዉን ኃላፊነት ለኛ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር ለነበረዉ ለአለማያ እርሻ ኮሌጅ ነበር የሰጡን።

ጥያቄ፣ በክፍል አንድ በነገሩኝ መረጃ ተመርኩዤ ሳሰላዉ በሀገር ዉስጥ እና በውጭ ሀገራት በማሽላ ላይ በአጠቃላይ ለ18 ዓመታት በበቆሎ ላይ ደግሞ በአጠቃላይ ለ10 ዓመታት በምርምር ሥራ ተሣትፈዋል። ከበቆሎና ከማሽላ በዬትኛዉ ሰብል ላይ ምርምር መሥራት ይቀላል? ለምን?

ዶክተር ብርሃኔ በቆሎና ማሽላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም የዲቃላ ዝሪያዎች ከመጠቀማቸዉ አንጻር ሲታይ ተመሣሣይ ጸባይ አላቸዉ። የበቆሎ ዲቃላ ዝሪያዎች የማዉጣትና የመጠቀም ሥራ በአለም አቀፍ ደረጃ በጣም የዳበረ ነዉ። የማሽላም ሥራ በተከታይነት ይታወቃል። እነዚህ አለም አቀፍ ልምዶች በሀገር ዉስጥ ለሚሠሩ ሥራዎች በጣም ጠቃሚ መሠረቶች ናቸዉ። በኢትዮጵያ ደረጃ ማሽላ ሀገር በቀል ሰብል ከመሆኑ አንጻርና በጣም የተለያዩ ዓይነቶች ስላሉን ይህንን መሠረት አድርጎ ብዙ ጠቃሚ ሥራዎች መሥራት ይቻላል። የዓለም አቀፍ የማሽላ ምርምር ህብረተሰብ ከኢትዮጵያ የማሽላ ምርምር ተጠቅሟል፣ እኛም ከነሱ ተጠቅመናል። ለምሳሌ ICRISAT የሚባለዉ ዓለም አቀፍ ማዕከል ሲመሠረት በዋነኝነት የተጠቀመዉ የኢትዮጵያ ማሽላ ዝሪያዎች ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ታዋቂዉን E-35 የተባለዉን መጥቀስ ይቻላል።  እኛም ብዙ ዝሪያዎች በተለይም ለዲቃላ ማሽላ መሥሪያ የሚያገለግሉ ዓይነቶችን ከዓለም ማህበረሰብ ወስደናል። ከICRISAT ከመጡ ዝሪያዎች እንደ ኮቦማሽ፣ ብርማሽ፣ 76T1-23 የተባሉት ለሀገራችን ገበሬዎች የተለቀቁ ናቸዉ። ስለዚህ የበቆሎና የማሽላ ምርምር ሥራዎች ተደጋጋፊና ተመሣሣይ ናቸዉ። ዲቃላ ያልሆኑ ዝሪያዎች በማዉጣትና ለተጠቃሚዉ በማድረስ የማሽላዉ ምርምር ሊቀል ይችላል። ያለዉ ልምድና ሁኔታ ይሄዉ ነዉ።

ከላይ በምሥሉ የሚታዩት ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡ የማሽላ አናቶች ናቸዉ። ፎቶ፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን

ጥያቄ፤ የኢትዮጵያ የማሽላ ማሻሻያን በብሔራዊ ደረጃ በሚያስተባብሩበት ወቅት የምርምር ፕሮግራሙ እንዴት ነበር የተቀናጀዉ?

ዶክተር ብርሃኔ፤ በማሽላ ላይ እናደርግ የነበረዉ ምርምር የአገሪቱን ስነ ምህዳር ወይም አግሮ ኢኮሎጂ በመመርኮዝ በሶስት ክፍሎች በመክፈል ነበር። እነርሱም፣ 1ኛ) ዝናም አጠር ዝቅተኛ ሥፍራዎች፤ እነዚህ ሥፍራዎችን በመወከል በማሽላ ላይ በዋናነት ምርምር እናካሄድ የነበረዉ በመልካሳ፣ ቆቦ፣ አላማጣ፣ ሁመራና ሚኤሶ ነበር። 2ኛ) መካከለኛ ሥፍራዎች፤ እነዚህ ሥፍራዎችን በመወከል በዋናነት ምርምር እናካሄድ የነበረዉ በባኮና ጂማ ነበር። 3ኛ) ከፍተኛ ሥፍራዎች፤እነዚህ ሥፍራዎችን በመወከል በዋናነት ምርምር እናካሄድ የነበረዉ በአለማያና አርሲ ነጌሌ ነበር። ይህንን ሥራ ለማጠናከርና ለመደገፍ በተለይም ከሰብል ማምረቻ ወቅት ዉጭ በበጋዉ ወራት የማዳቀል ሥራና የዘር ብዜት ለማከናወን በመስኖ የመልካ ወረር ምርምር ጣቢያ (የአሁኑን ወረር ምርምር ማዕከል) እንጠቀም ነበር።

ጥያቄ፤ ከዚህ የተቀናጀ የምርምር ፕሮግራም ለገበሬዎች የደረሱ ምርጥ የማሽላ ዝሪያዎች ነበሩን?

ዶክተር ብርሃኔ፤ አዎ፣ በርካታ ምርጥ ዝሪያዎች እንዲለቀቁ አድርገናል። ከነዚህ ውስጥ አለማያ 70፣ ኢ ቲ ኤስ 2752፣ ጋምቤላ 1107፣ ዴዴሳ 1057፣ መልካማሽ 79፣ ባኮማሽ እና ብርማሽ የተባሉት ሊጠቀሱ ይቻላል። በወቅቱ ከተለቀቁት ዝሪያዎች መካካል በአጭር ጊዜ የሚያፈራዉና ድርቅን መቋቋም የሚችለዉ 76T1-23 የሚባለዉ ዝሪያ እስከ ዛሬ ድረስም በምርት ላይ ይገኛል።

ምሥሉ የሚያሳየዉ በቆቦ አካባቢ ያለዉን የዲቃላ ማሽላ ምርምርን ነዉ። ፎቶ፤ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን

ጥያቄ፤ በኢትዮዮጵያ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚበቅሉ የማሽላ ዓይነቶችን በተገቢዉ መንገድ በማሰባሰብም ይታወቃሉ። ምን ያህል አገር በቀል የማሽላ ዓይነቶችን ሊያሰባስቡ ችለዋል?

ዶክተር ብርሃኔ፤ በሀገሪቱ በተለያዩ ማሽላ አብቃይ ሥፍራዎች በመዘዋወር ከ5000 በላይ የሆኑ የማሽላ ዓይነቶችን በማሰባሰብ ለጥናት እንዲበቁ አድርገናል። ዘሮቹ ሳይበላሹ ለረዥም ጊዜ ተጠብቀዉ እንዲቆዩም በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲቱዩት እንዲቀመጡ አድርገናል።

ጥያቄ፤ ኢኮኖሚክ ቦታኒ በሚባለዉ የጆርናል መጽሔት በ1973 ባሳተሙት ጽሑፍዎ ውስጥ በአለማያ ኮሌጅ ከተለቀቁት ዝሪያዎች መካከል በቁመቱ አጠር ያለ ነገር ግን ከፍ ያለ ምርት ይሰጥ የነበረዉ ቁልቢ ድዋርፍ የተባለዉ ዝሪያ በገበሬዉ ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኝ እንዳልቻለ ነዉ። የአካባቢዉ ገበሬዎች ይህንን ምርጥ ዝሪያ ለምን ሊቀበሉ አልቻሉም።

ዶክተር ብርሃኔ፤ በአካባቢዉ ገበሬዉ ማሽላን ለተለያዩ ነገሮች ይጠቀማል። ፍሬዉን ለራሱ ይመገባል፣ ቅጠሉን ለከብቶቹ ይመግባል፣ ግንዱን ደግሞ ለማገዶነት ይጠቀማል። ምንም እንኳ ምርታቸዉ ደህና ቢሆንም በቁመት አጭሮቹ ዝሪያዎች አነስ ያለ ግንድና ቅጠል ስለሚኖራቸዉ በገበሬዎች ዘንድ አይወደዱም ነበር።

ጥያቄ፣ እስካሁን ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከኢትዮጵያ በኩል የተደረግልዎት ዕዉቅና ካለ ቢነግሩኝ፤

ዶክተር ብርሃኔ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተመሠረተበትን ሀምሳኛ ዓመት በዓሉን ሲያከብር ለሀገሪቱ ግብርና ምርምር የላቀ አስተዋጽኦ እንዳበረከትኩ የሚገልጽ የምስክር ወረቀት ሰጥቶኛል። የኢትዮጵያ የሰብል ማሻሻያ ጉባኤ በ1978 የቀዳሚ ተመራማሪነት ዕዉቅና ስጥቶኛል። እንዲሁም የመልካሳ ምርምር ማዕከል ለማሽላ ምርምር ላበረከትኩት አስተዋጽኦ ባሁኑ ዓመት ሠርቲፊኬት ሰጥቶኛል።

ጥያቄ፣ ለኢትዮጵያ ግብርና ያልዎት ራዕይ ምን ይመስላል?

ዶክተር ብርሃኔ፣ ምርምርን በተመለከተ እያንዳንዱ ሰብል ሀገር አቀፍ በሆነ መንገድ የፖለቲካ ክልሎችን ሳይከተል ሁሉንም ሥነ ምህዳሮችን ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ ሥራ ላይ እንዲዉል ምኞቴ ነዉ። በተጨማሪም በብዛት በሀገር ዉስጥ የተቋቋሙ ዩኒቨርስቲዎች በአካባቢያቸዉ ያለዉን ምርምርና የቴክኖሎጂ ስርጸት ከማስተማር ሥራቸዉ ጋር አቀናጅተዉ እንዲሠሩ ምኞቴ ነዉ። ሌላዉ ምኞቴ የኢትዮጵያ ግብርናን ከማዘመን አንጻር የዩኒቨርስቲና ቴክኒካል ኮሌጅ ተመራቂዎች የራሳቸዉን እርሻ እንዲያቋቋሙና እንዲመሩ መንግሥት የሚያስፈልጋቸዉን ድጋፍ ሁሉ እንዲያደርግላቸዉ ነዉ።

ጥያቄ፣ ይህ ራዕይዎ እንዲሳካ ይረዳል ብለዉ የሚገምቱት መልእክት ካለ።

ዶክተር ብርሃኔ፣ ከላይ ያነሳኋቸዉ ምኞቶቼ እንዲሳኩ ዋናዉ የመንግሥት ፖሊሲና አመራር ነዉ። የሚመለከታቸዉ በአመራር ላይ  ያሉ ኃላፊዎች አስፈላጊ እርምጃዎች ይወስዳሉ የሚል ተስፋ አለኝ።

በዶክተር ብርሃኔ ላይ የሚያተኩረዉ ጽሑፌ በዚህ አያበቃም። በክፍል 3 ስለ ዕድገታቸዉ፣ ተማሪዎቻቸዉና የማሽላ ዝሪያዎች የሚነግሩኝን አካፍላችኋለሁ። እስከዚያዉ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መስከረም 28፣ 2012 ዓ.ም. (October 9, 2019)

አስተያየት ያስቀምጡ