በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤
የማሽላዉ አባት፣ ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን
ክፍል 1
የዛሬዉ ጽሑፌ በግብርናዉ መስክ ላለፉት 55 ዓመታት በሀገር አቀፍም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉትና በአሁኑ ጊዜም በማድረግ ላይ ለሚገኙት አንጋፋ የግብርና ባለሙያ ላይ ያተኩራል። እኝህ ባለሙያም ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን ይባላሉ። ዶክተር ብርሃኔ ያልተሳተፉበት የሥራ መስክ አለ ማለት አይቻልም። ለረጅም ጊዜ በዩኒቨርስቲ የእርሻ ባለሙያዎችን አሰልጥነዋል፣ በተመራማሪነት በተለያዩ ሰብሎች ላይ ሠርተዋል፣ እንዲሁም በሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለበርካታ ዓመታት በኃላፊነት ሠርተዋል።
የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸዉን በእርሻ ለመማር አንጋፋዉን የአለማያ እርሻ ኮሌጅ (የአሁኑ የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ) ከተቀላቀሉበት 1957 ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የድርሻቸዉን እያበረከቱ ይገኛሉ። እኔ ራሴ በቅርቡ ባዘጋቸዋቸዉና በርካታ የግብርና ምርምርና ልማት ባለሙያዎች በተሳተፉበት ሁለት መድረኮች ልምዳቸዉን እንዲያካፍሉ ላደረኩላቸዉ ጥሪ በደስታ ነበር የተቀበሉት።

ማስገንዘቢያ፣ ካልተገለጸ በስተቀር በጽሁፉ
ውስጥ የተጠቀሱት ቀናት ሁሉ እንደ አዉሮፓውያን አቆጣጠር ነዉ።
ስለ ዶክተር ብርሃኔ የሚተርከዉ የዛሬዉ ጽሑፌን በቃለ መጠይቅ መልክ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
ጥያቄ፤ በቅድሚያ ትምህርትዎን የት ተማሩ?
ዶክተር ብርሃኔ፤ የመጀመሪያ ዲግሬዬን በዕጽዋት ሳይንስ በከፍተኛ ማዕረግ ያገኘሁት በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር በሚገኘዉ የአለማያ እርሻ ኮሌጅ (የአሁኑ ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ) በ1961 ሲሆን የማስትሬት ዲግሪዬን በአግርኖሚ በአሜሪካ ሀገር ከሚገኘዉ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኔብራስካ በ1964 ነዉ። የዶክትሬት ዲግሪዬን ደግሞ እዚያዉ አሜሪካ ከሚገኘዉ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሚኔሶታ በ1969 ነዉ። ሰለዚህ ሶስተኛ ዲግሬዬን ካገኘሁ ዘንድሮ 50 ዓመት ሞላዉ ማለት ነዉ። ጊዜዉ ይሮጣል ልበል።
ጥያቄ፤ የዩኒቨርስቲ መምህር ሆነው የትና መቼ አገለገሉ? ያስተምሩ የነበረዉስ የትኛዉን ኮርስ ነበር?
ዶክተር ብርሃኔ፤ የቀድሞ የአለማያ እርሻ ኮሌጅ (የአሁኑ ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ) ባልደራባ ሆኜ በመምህርነት ያገለገልኩት ከ1964 እስከ 1982 ባሉት ዓመታት ሲሆን በመሃከሉ ለዶክትሬት ትምህርቴ ወደ ዉጭ ከሄድኩበት ሶስት ዓመታት በስተቀር ለ15 ዓመታት በኮሌጁ አስተምሬአለሁ። አስተምራቸዉ የነበሩት ኮርሶች በርካታ የነበሩ ሲሆን እነርሱም ፕላንት ቢሪዲንግ፣ ጄኔቲክስ፣ ባዮሜትሪ፣ ክሮፒንግ ሲስቴም የሚባሉትን ያካትታል።
ጥያቄ፤ እኔ እንደማዉቀዉ አንድ መምህር አንድ ወይም ሁለት ኮርስ ብቻ ነዉ የሚያስተምረዉ። እርስዎ እንዴት እነዚህ የተለያዩ ኮርሶችን ሊያስተምሩ ቻሉ? እውቀቱ ቢኖርዎትም ከፍተኛ የዝግጅት ጊዜ መውሰዱ አይቀርም ብዬ ነዉ የምጠይቅዎት?
ዶክተር ብርሃኔ፤ በርግጥ ኮርሶቹን አስተምር የነበረዉ በተለያዩ የትምህርት ወቅቶች ነዉ። ነገር ግን አንድ ኮርስ እንኳ ለማስተማር ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልግ ነበር። ምክንያቱም ተማሪዎቹ በትምህርታቸዉ ጠንካራ ስለነበሩ የሚጠይቁንን ጥያቄዎች መመለስ እንድንችል በቂ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልገን ነበር። ከማስተማር ሥራዬ በተጨማሪ ምርምርና የዲፓርትመንት አስተዳደር እሠራ ነበር።
ጥያቄ፤ ምርምርን በተመለከተ በሀገር ዉስጥ በምን መስክ ተሳትፈዋል?
ዶክተር ብርሃኔ፤ በአለማያ ኮሌጅ ተቀጥሬ የመጀመሪያ የምርምር ሥራዬን የጀመርኩት በ1964 ሲሆን የሥራ ድርሻዬም የገብስ አዳቃይ ነበር። በገብስ ምርምር ለሁለት ዓመታት ብቻ ነዉ የቆየሁት። ምክንያቱም ለዶክትሬት ትምህርቴ ወደ አሜሪካን ሀገር መሄድ ስለነበረብኝ። ለዶክትሬት የሚያበቃኝን ምርምር በገብስ ማሻሻል ነዉ የሠራሁት። አለማያ እንደተመለስኩ የምርምር አቅጣጫዬም ወደ በቆሎ አዳቃይነት ተቀየረ። ብዙም ሳይቆይ ከሁለት ዓመታት በኋላ ምርምሬን ከበቆሎ ወደ ማሽላ በመቀየር በሰፊዉ ወደ ምታወቅበት የማሽላ ምርምር ውስጥ ገባሁ። የማሽላ አዳቃይ በመሆንም ከ1973 እስከ 1982 ድረስ ለ10 ዓመታት በአለማያ ኮሌጅና በአዳማ መልካሳ በሚገኙ ጣቢያዎች አገልግያለሁ።
ጥያቄ፤ ወደ ውጭ ሀገር ከመሄድዎ በፊት በሀገር ውስጥ በኃላፊነት የሠሩባቸዉ ጊዜያት ካሉ ቢገልጹልኝ?
ዶክተር ብርሃኔ፤ በሥራ ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ በኃላፊነት የሠራሁት የሀረማያ እርሻ ኮሌጅ የዕጽዋት ሣይንስ ዲፓርትመንት ኃላፊ ሆኜ ነዉ። በዚህ ኃላፊነቴም ከ1969 እስከ 1975 ለስድስት ዓመታት ቆይቻለሁ። በተጨማሪም ከ1973 እስከ 1982 ባሉት 10 ዓመታት የብሔራዊ ማሽላ ምርምር አስተባባሪ በመሆን አገልግያለሁ።
ጥያቄ፤ ለበርካታ ዓመታት ከኢትዮጵያ ዉጭ በነበሩበት ወቅት የሠሩባቸዉ የኃላፊነት ቦታዎች የትኞቹ ናቸዉ?
ዶክተር ብርሃኔ፤ ከ1982 እስከ 2002 ባሉት 21 ዓመታት በተለያዩ ሀገራት እና የኃላፊነት ደረጃዎች ሠርቻለሁ። እነዚህም ይህንን ይመስላሉ።
- 1982 እስከ 1986፤ በአፍሪካ ህብረትና ኢክሪሳት የሚባል አለም አቀፍ ድርጅት የተቋቋመ የማሽላ ምርምር ፕሮግራም ውስጥ የምሥራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ አስተባባሪ
- ከ1986 እስከ 1987፤ ዋና መሥሪያ ቤቱ ሜክሲኮ ሀገር የሚገኘዉ ሲሚት የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት በዋና መሥሪያ ቤቱ የበቆሎ ተመራማሪ
- ከ1987 እስከ 1991፤ በናይሮቢ ኬኒያ የሲሚት የምሥራቃዊ አፍሪካ የበቆሎ ተመራማሪና የቡድን መሪ
- ከ1991 እስከ 1993፤ በሀራሬ ዚምባብዌ የሲሚት የደቡባዊ አፍሪካ የበቆሎ ተመራማሪና የቡድን መሪ
- ከ1993 እስከ 1994፤ በአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኔብራስካ ኢንትሶርሚል የሚባል የዓለም አቀፍ የማሽላና ቡልቱክ ፕሮግራም ተባባሪ ዳይሬክቴር
- ከ1994 እስከ 2002፤ በአሜሪካ የሚገኘዉ የቪርጂኒያ ቴክ ዩኒቨርሲቲ የተቀናጀ የተባይ አጠባበቅ ፕሮግራም ዳይሬክቴር
ጥያቄ፤ ይህ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ የዘለቀዉን በተለያዩ ሀገራት ያደረጉትን አገልግሎት ካጠናቀቁ በኋላ ወዴት ሄዱ?
ዶክተር ብርሃኔ፤ በ2002 ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩ። አማረዉ የሚባል በአሜሪካን መንግሥት የሚደገፍ ፕሮጀከት ኃላፊ በመሆን ሠርቻለሁ። ይህ ሁለገብ የሆነ ፕሮጀክት ትኩረት አድርጎ ይሠራ የነበረዉ በአማራ ክልል በማክሮ ፋይናንስ፣ ግብርና ምርምርና ስርጸት እንዲሁም የዉሃ ተፋሰሶች ጥበቃ ላይ ነበር። የፕሮጀክቱን መምራትና ማስተባበር ሥራ እሠራ የነበረው ከባህር ዳር ከተማ ሆኜ ነበር። በዚህ ፕሮጀከት በኃላፊነት እስከ 2008 የቆየሁ ሲሆን ይህም ለሰባት ዓመታት መሆኑ ነዉ።
ጥያቄ፤ የአማረዉ ፕሮክጀት ከተጠናቀቀ 11 ዓመታት ሆነዉ። እርስዎ ግን እስካሁንም በቃኝ አላሉም። በአሁኑ ጊዜ በምን ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ?
ዶክተር ብርሃኔ፤ አቅሜ በፈቀደዉ መጠን በሙያዬ እያገለገልኩ እገኛለሁ። በአሁኑ ወቅት የቨርጂኒያ ቴክ የተቀናጀ የተባይ አጠባበቅ ፕሮግራም የአፍሪካ ክፍል አማካሪ ነኝ።የኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚም ምክትል ፕሬዘዳንት ሆኜ ሳገለግል ቆይቼ አሁን ለተረኛ አስረክቤ ወጥቼአለሁ። ከዚህ በተጨማሪ በርካታ ድርጅቶችን በቦርድ አባልነት ወይም ፈቃደኝነት እያገለገልኩ እገኛለሁ።
በዶክተር ብርሃኔ ላይ የሚያተኩረዉ ጽሑፌ በዚህ አያበቃም። በሚቀጥለዉ ጽሑፌ በሰፊዉ ስለሚታወቁበት የማሽላ ምርምር እንዲሁም ለኢትዮጵያ ግብርና ያላቸዉን ራዕይና መልእክት አስነብባችኋለሁ።
እስከዚያዉ መልካሙን እመኝላችኋለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መስከረም 25፣ 2012 ዓ.ም. (October 6, 2019)