ግብርናችንን ለማዘመን፤ ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች

ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች በመባል የሚታወቀዉ እጅግ አደገኛ ተባይ ሲሆን በእንግሊዘኛዉ አጠራር Fall armyworm የሚባል ሲሆን በሳይንሳዊ ስያሜው ደግሞ Spodoptera frugiperda ይባላል። ይህ የገበሬዎቻችን ክፉ ጠላት አባ ጨጓሬ የሚመስል ሲሆን በእድገቱ የመጨረሻዉ ዘመን ወደ የእሳት እራትነት ይቀየራል። የእሳት እራቶቹ ከሚጥሉት እንቁላሎች የሚፈለፈሉት አባ ጨጓሬዎች ናቸዉ ሰብሎቻችንን በአጭር ጊዜ ዉስጥ ያለርህራሄ አመድ የሚያደርጉት። ደጋጎቹ እናት የእሳት እራቶች ግን መልካቸዉ ለተመልካች ከመማረኩም በላይ እራሳቸዉ በቀጥታ በሰብል ላይ የጎላ ጉዳት አያደርሱም። ቢሆንም ራቅ ወዳለ ሥፍራ በቀላሉ በመብረርና በርካታ እንቁላሎችን በመጣል እንዲሁም ከእንቁላሎቹ የሚፈለፈለዉ ተምች በአጭር ጊዜ መጠነ ሰፊ ጥቃት እንዲያደርስ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ። ምክንያቱም ጉልምሱ የእሳት እራት በአንድ ሌሊት እስከ 100 ኪ. ሜ . መብረር ይችላልና ነዉ። ለዚህ ረዥም ርቀት በረራ ዋና ምክንያቱ የእሳት ራቶቹ ጠንካራ ክንፎች ናቸዉ።

በምስሉ በስተግራ የሚታየው ጉልምሱ የእሳት እራት ሲሆን በስተቀኝ የሚታየዉ ደግሞ በሰብሎቻችን ላይ ከፍተኛ ጥቃት የሚያደርሰዉን አባ ጨጓሬ መሳዩን ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች ነዉ።

በሞቃታማ አካባቢዎች ያሉ ምቹ የአየር ሁኔታዎች እና እፅዋቶች ይህ ተባይ በዓመት በርካታ ጊዜ እንዲራባ ያስችለዋል። ይህ አባ ጨጓሬ መሳዩ አደገኛ ተባይ የማያጠቃዉ የሰብል ዓይነት የለም ማለት ይቻላል። እስካሁን በተደረገዉ ጥናት ወደ 80 የሚጠጉ የሰብል ወይም የተክል ዓይነቶች በዚህ ተባይ ይጠቃሉ። በተለይ በእድገት ላይ ያሉ የበቆሎ ተክሎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቁ ሲሆን እንደ ዳጉሳና ማሽላ የመሳሰሉትም ለከፋ አደጋ ይጋለጣሉ።

የተባዩ ሥርጭት

የዚህ አደገኛ ተምች መነሻዉ ሰሜናዊና ደቡባዊ አሜሪካ ሲሆን በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየዉ በናይጄሪያ ሲሆን ይህም የተከሰተዉ ከሶስት አመት በፊት እ.ኤ.አ. በጃኒዋሪ 2016 ነበር፡፡ ለዘመናት ከኖረበት ሁለቱ የአሜሪካ አህጉራት ወደ አፍሪካ የመጣዉ ከመንገደኛ ወይም ከዕቃ ጋር በአይሮፕላን ተሳፍሮ እንደሆነ ይገመታል። አንዴ የአፍሪካን አህጉር ከረገጠ በኋላ ግን የማንንም የትራንስፖርት ዕርዳታ ሳያስፈልገዉ በራሳቸዉ ክንፍ እየበረሩና እንቁላሎቻቸዉን በበቆሎ እርሻ ላይ መዝራት ተያያዙት። የተዘሩት እንቁላሎችም ሲፈለፈሉ አባ ጨጓሬዎቹ በሰብል ላይ ጥቃት ማድረስ ጀመሩ። በዚሁ መሠረት በጃኒዋሪ 2016 በናይጄሪያ ብቻ የታየዉ ይህ ተባይ ከ10 ወራት በኋላ በኖቮምበር 2017 በተጨማሪ ሰድስት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ላይ ጥቃት ያደረሰ ሲሆን ከሶስት ተጨማሪ ወራት በኋላ በፌብሪዋሪ 2017 በደቡባዊ የአህጉሪቱ ክፍል ወደሚገኙ ሰባት ሀገሮች ሊስፋፋ ችሏል። ከሁለት ተጨማሪ ወራት በኋላ በአፕሪል 2017 የጥቃት አድማሱን በማስፋፋት ዘጠኝ ተጨማሪ አገራት ላይ ጥቃት ሊያደርስ ችሏል። የሚገርመዉ ተባዩ በአፍሪካ አህጉር በታየ በአንድ ዓመቱ በዲሴምቤር 2017 ወደ 38 የአፍሪካ አገሮች ሊዛመት ችሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህ ተባይ የአፍሪካን አህጉር አዳርሶ ወደ ኤሺያም ተሸጋግሯል። በዚሁ መሠረት በ2019 በህንድ፣ ሚያንማር፣ ሲሪላንካ፣ ታይላንድና የመን ድረስ ሊዛመት ችሏል።

ይህ ፈጣን ሁሉን አውዳሚው ተምች ተብሎ የተሰየመዉ ተባይ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየዉ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ሸካ ዞን እ.ኤ.አ. ማርች 2017 ሲሆን የዛሬ አመት የወጣ ሪፖርት እንደሚያሳዉ ተባዩ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በ417 ወረዳዎች እንደ ተሰራጨ ነዉ።

ምስሉ የሚያሳየዉ በአፍሪካ የፈጣን ሁሉን አውዳሚው ተምች ሥርጭትን ነዉ። የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ተባዩ ባንድ ዓመት ውስጥ 38 የአፍሪካ ሀገራትን አዳርሷል። የምሥሉ ምንጭ፣ CIMMYT

የጥቃቱ ሁኔታና መጠን

አባጨጓሬው የበቆሎ ቅጠልን ከመብላቱም በተጨማሪ የሰብሉ ዋናውንና አናቱ ላይ የሚገኘውን የእድገት ክፍሉን ያጠቃል፡፡ በትልልቆቹ የበቆሎ ሰብሎች ላይ ደግሞ ቆረቆንዳቸው ድረስ በመዝለቅ እየቦረቦረ ሊያጠቃ ይችላል፡፡ በቅርቡ በተሰላዉ ግምት በኢትዮጵያ በቆሎ ከሚዘራበት 2.1 ሚሊየን ሄክታር ማሳ ዉስጥ 22 ፐርሰንቱ በዚህ ተምች ተጥቅቶ ነበር፡፡ ተገቢዉ የቁጥጥር እርምጃ ካልተወሰደ በዚሁ ጥቃት ከ12.3 እስከ 31 ሚሊየን ኩንታል የሚሆን የበቆሎ ምርት ሊወድም የሚችል ሲሆን ይህም በገንዘብ ሲተመን ከ8.2 እስከ 20.3 ቢሊዮን ብር ይደርሳል፡፡

ተባዩን በቁጥጥር ሥር ለማድረግ በሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ደረጃ በመደረግ ላይ የሚደረገዉን ርብርብና ስለ መከላከያ ዘዴዎች ወደፊት እዘግባለሁ።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆንልን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ መስከረም 1፣ 2012 ዓ.ም. (September 12, 2019)

አስተያየት ያስቀምጡ