በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤
ትኩረት ለሀገር-በቀሉ ጤፋችን
ሀገር-በቀል የሚለዉን ቃል የተጠቀምኩት ኢንዲጂነስ የሚለዉን የእንግሊዘኛ ቃል ለመተካት ነዉ። በዚሁ መሠረት የጤፍ መነሻ ወይም መፈጠሪያ ኢትዮጵያ መሆኗን ለማሳየት ነዉ። ከጤፍ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የቡና፣ የእንሰት፣ የኑግና የመሣሣሉትም ሰብሎችም መነሻ ሀገር ናት።
ኢትዮጵያ ለጤፍ መነሻ ሀገር ብቻ ሳትሆን ስብሉ በሰፊዉ ጥቅም ላይ የዋለባትም ሀገር ናት። ስለዚህ ጤፍ በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጄንሲ መረጃ እንደሚያሳየዉ በያመቱ 6.5 ሚሊዮን አባወራዎች ጤፍን ይዘራሉ። በኢትዮጵያ የአንድ ቤተሰብ አማካይ አምስት ሰዉ አድርግን ብንወስድ 32.5 ሚሊዮን ሰዉ በጤፍ ግብርና ይሳተፋል ማለት ነዉ። ከዚያ ደግሞ ወደ ሻጩ ከሄድን ከጅምላ ነጋዴ እስከ ቸርቻሪ ድረስ በርካታ የማህረሰቡ ሰዎች በጤፍ ንግድ ይሳተፉሉ። በተመሣሣይ መልኩ ጤፍን በመፍጨት፣ በመጋገር፣ ወዘተ የሚሳተፉትን ካሰላን ደግሞ ቁጥሩ የበለጠ ይጨምራል። የጤፍ ፍሬ ከገለባዉ ከወጣ በኋላ የሚገኘዉ ጭድ ወይም ተረፍ-ምርትም ለከብት መኖ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለዉ በመሆኑ በከብት ማደለብና ሌሎች ተዛማች መስኮች የሚሳተፉትንም መገመት ይቻላል። ለዚህ ነዉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ጤፍን ሁለቴ የምንመገበዉ። የቀጥታዉ የጤፍ ፍሬ ተፈጭቶ በሚጋገረዉ ወይም በሚሠራዉ እንጄራ፣ ገንፎ፣ ጨጨብሳ፣ ጩኮ፣ ኬክ፣ ወዘተ ሲሆን የተዘዋዋሪዉ ደግሞ የጤፍ ጭድን የተመገቡ ከብቶችን ስንመገብ ነዉ። ከሁሉ የሚገርመዉ የጤፍ ገበያ በኢትዮጵያ ውስጥ ለዋጋ ንረት እንደማሳያነት መዋሉ ነዉ። ለዚህም እንድ ማሳያነት የሚሆነዉ ስለ ገበያ ውይይት ሲኖር መጀመሪያ የሚነሳዉ የጤፍ ዋጋ ስንት እንደደረሰ በመጠያየቅ ስለሆነ ነዉ።
በኢትዮጵያ ሰብሎቻችን የሚዘሩበትን የመሬት ስፋት ከወሰድን ጤፍን የሚወዳደረዉ የለም። በያመቱ ወደ ሶስት ሚሊዮን በሚጠጋ መሬት ላይ ይዘራልና ነዉ። ከዚህ በታች በምሥል 1 (በስተግራ) እንደሚታየዉ ከሌሎች የብርዕና አገዳ ሰብሎች ጋር ስናወዳድረዉ ጤፍ 29% የመሬት ድርሻ ሲይዝ፣ በቆሎ 21% እና ማሽላ 19% ይዘዉ ይከተላሉ። ነገር ግን ከእያንዳንዱ ሰብል የሚመረተዉን አጠቃላይ ምርት ከወሰድን ጤፍ በአንደኛ ደረጃ አይገኝም (ምሥል 1 በስተቀኝ)። ቦታዉን ለበቆሎ መልቀቅ ስለሚገደድ። ለዚህም ዋና ምክንያቱ የጤፍ ምርታማነት አነስተኛ በመሆኑ ነዉ።

በዚሁ ዝቅተኛ የጤፍ ምርታማነት ምክንያት የጤፍ ማሣዎች በሌሎች ከፍተኛ ምርታማነት ባላቸዉ ሰብሎች እንዲተኩ ጥረት ተደርጎ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። እዚህ ላይ “አጥፍቶ መጥፋት” በሚል ርዕስ ሙሉጌታ በሚባሉ ጸሐፊ የዛሬ 25 ዓመት የታተመ 292 ገጽ ያለዉ መጽሐፍን መጥቀስ ይቻላል። ምንም እንኳ በአሁኑ ጊዜ ይህ መጽሐፍ በእጄ ባይኖርም ከረጅም ጊዜ በፊት ባነበብኩበት ወቅት በገጽ 152 የተጻፈዉን ማስታሻዬ ላይ ጽፌ ነበር። የመጽሐፉ ደራሲ በዚህ ገጽ የሚተርከዉ ፕሬዘዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ለጉብኝት ወደ አርሲ ከፍለ ሀገር በሄዱብት ወቅት አጠገባቸዉ ከነበሩት ባለሥልጣን ጋር የተነጋገሩትን ነዉ። ፕሬዘዳንት መንግሥቱ ለባለሥልጣኑ እንዲህ ይሉታል “ጤፍ ዋጋ የሌለዉ ሰብል ስለሆነ በሶስት ዓመት ወስጥ በሌላ ሰብል መተካት አለብን”። ባለሥልጣኑም ”ጓድ መንግሥቱ እኔ ያለ ጤፍ አይሆንልኝም” ይላቸዋል። ፕሬዘዳንት መንግሥቱም መልሰዉ “እኔም ውሸቴን ነዉ እንጂ ያለ ጤፍ አይሆንልኝም” አሉ ይላል። መጽሐፉ ባሁኑ ጊዜ አጠገቤ ስለሌለ ከላይ ያሰፈርኩት በትክክል በመጽሀፉ ውስጥ እንደ ተገለጸዉ ለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም።
እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ፕሬዘዳንት መንግሥቱ ከባለሥልጣኑ ጋር ባደረጉት ንግግር ብቻ ሳይወሰኑ በፖሊሲ ደረጃም ጤፍ የምርት መጠኑ ዝቅተኛ ስለሆነ በሌሎች ምርታማ በሆኑ ሰብሎች መተካት እንዳለበትና ይህንኑ ለማስፈጸም ሙከራ ተደርጎ እንደነበረ ነዉ። ነገር ግን ይህ ሊሳካ አልቻለም። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ ልክ እንደ ባለሥልጣኑና እንደ ፕሬዘዳንት መንግሥቱ ያለ ጤፍ ስለማይሆንለት ነዉ። ምንም እንኳ በርካታ ምክንያቶች ሊዘረዘሩ ቢቻልም ገበሬዉ ጤፍን የሚዘራዉ በሁለት ዋና ምክንያቶች ይመስለኛል። የመጀመሪያዉ ከሌላዉ ሰብል በተሻለ ሁኔታ ጤፍ ገበያም ሆነ ተፈላጊ ስላለዉ ነዉ። ምክንያቱም ከማዕዳችን የማይለየዉ ጥራት ያለዉ እንጄራ የሚጋገረዉ ከጤፍ ስለሆነ ነዉ። ስለዚህ የዋጋ ንረት ቢኖርም ጤፍ ገዢ እንደማያጣ ገበሬዉ ጠንቅቆ ስለሚረዳ ነዉ። ሁለተኛዉ ምክንያት ደግሞ ከሌሎች ሰብሎች በተሻለ ደረጃ ጤፍ ለበርካታ የምርት እንቅፋቶች በቀላሉ እጁን ስለማይሰጥ ነዉ። ይህም ማለት ጤፍ ዝናም በሚያጥርበትም ሆነ በሚበዛበት ሥፍራ ከነ ስንዴና በቆሎ በተሻለ ሁኔታ የሚከሰተውን ነባራዊ ሁኔታ በመቋቋም ሊያድግና ምርት ሊሰጥ ስለሚችል ነዉ። በተለይም የሀገሪቱን 10% የሚሸፍነዉ የኮትቻ ወይም መረሬ መሬት ላይ ዝናም ሲበዛ የሚከሰትዉን የዉሃ ማቆር ተቋቁሞ የሚያድግ ሰብል ከጤፍና ሩዝ ዉጭ ማግኘት አዳጋች ስለሆነ ነው።
የኮትቻ መሬት ከተነሣ የዛሬ 25 ዓመታት ገደማ የሆለታ እርሻ ምርምር ማዕከል ተመድቤ በምሠራበት ወቅት የጊንጪን ኮትቻ መሬት አልረሳውም። ለጤፍ ምርምራችን በጊንጪ የሚገኘዉን ንዑስ ማዕከል እንደ መስክ የሙከራ ጣቢያ እንጠቀምበት ነበር። መሬቱ በደህና ሁኔታ ሳይርስ ጤፍ መዝራት ስለማንችል ጤፍን የምንዘራዉ ከሌሎቹ ሰብሎች ዘግየት ብለን ነበር። በዚህን ወቅት መሬቱ መራስ ብቻ ሳይሆን እጅግ ስለሚያጣብቅ በማሣችን ውስጥ የሙከራችንን ፕላን በአግባቡ ለማዉጣትና ለመዝራትም እንቸገር ነበር። ይህ እንደ ማስቲሽ የሚያጣብቅ ማሣ የቦት ጫማችንን ጥለን በባዶ እግራችን ጭቃውን እንድናቦካ ያስገድደን ነበር። እንደ ጊንጪ ዓይነት ጠንከር ያለ የኮትቻ አፈር ያየሁት በ1977 ድርቅ ምክንያት ለሠፈራ ለሚሄዱ ወገኖቻችን መጠለያ ለመሥራት ጊሎ አቦል በሚባል ጋምቤላ ወስጥ በሚገኝ ሥፍራ በዘመትን ጊዜ ነወ። ደግነቱ በጊሎ አቦል እንሠራ የነበረው መጠለያ እንጂ ከእርሻ ጋር የተገናኘ ስላልሆነ እንደ ጊንጪዉ ዓይነት ፈተና አላጋጠመንም ነበር። የጋምቤላዉ ዘመቻ የራሱ የሆኑ ተዳርጎቶች ነበሩት። ከእርሻ ጋር የተገናኝ ስላልሆነ አሁን አላነሳዉም።
ጤፍን በተመለከተ ምንም እንኳ ጫና ቢደረግበትም እንደተፈለገዉ የጤፍ መሬት እየቀነሰ ሳይሆን እየጨመረ ነዉ የመጣዉ። በምሥል 2 እንደሚታየዉ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1989 ዓ.ም. 1.84 ሚሊዮን ሄክታር የሚሸፍነዉ የጤፍ እርሻ በ2007 ወደ 2.87 ሚሊዮን ሄክታር ሊያድግ ችሏል። ይህ የ56% ዕድገት በሁለት አሥርት ዓመታት ዉስጥ ከፍተኛ ይመስለኛል።
የዓለም አቀፉ ማህረሰብ ጤፍንና አንዳንድ በመልማት ሀገር ያሉ ሰብሎችን “ወላጅ-አልባ ሰብሎች” ወይም በእንግሊዘኛዉ “ኦርፋን ክሮፕስ” ብለዉ ይጠሯቸዋል። ይህ “ወላጅ-አልባ” የሚለዉ ቃል ትክክለኛ ሥያሜ ባይሆንም የሚያመለክትዉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት አልተሰጠዉም ለማለት ነዉ። እነዚህ ወላጅ-አልባ የሚባሉት ሰብሎች ባብዘኛዉ በድሀ ሀገሮች እጅግ ጠቃሚና ተፈላጊ የሆኑ ሰብሎች ሲሆኑ በሰለጠኑት ሀገራት ግን ተጠቃሚነታቸዉ አነስተኛ ነዉ። በዚሁ መሠረት በምርምርም ሆነ በሌላ መስክ እነዚህ ሰብሎች ወደ ኋላ የቀሩ ናቸዉ። ሆኖም ባለፉት ሰላሳ እና አርባ ዓመታት በተለያየ የዓለማችን ክፍሎች የተቋቋሙ ዓለም-አቀፍ የምርምር ማዕከላት በተለምዶ ወላጅ-አልባ ተብለዉ ከሚታወቁት ውስጥ በተወሰኑት ላይ የምርምርና የልማት ሥራ በማስፋፋት ከፍተኛ ዉጤት ሊያገኙባቸዉ ችለዋል። ነገር ግን አንድም የዚህ ዓለም-አቀፍ የምርምር አካል ለጤፍ ትኩረት አድርጎ ሊሠራ አልቻለም። በዚህ የተነሣ ነዉ አንዳንዶቻችን ጤፍን “ትክክለኛዉ ወላጅ-አልባ” ብለን የምንጠራዉ። ምክንያቱም አንዳንድ “ወላጅ-አልባ” ሰብሎች ጉዲፈቻ ሲያገኙ ጤፍ ግን የሚያየዉ አልተገኘምና ነዉ።
በሀገራችንም ከሌሎቹ ሰብሎች ጋር ስናወዳድረዉ በቀድሞ ጊዜ የጤፍ ምርምር በቂ አቅርቦት አልነበረውም። ለዚህ እኔ ራሴ ምስክር ነኝ። በሆለታ እርሻ ምርምር የጤፍ ተመራማሪ በነበርኩበት ወቅት የምርምር ክፍላችን ምንም ዓይነት ተሽከርካሪ አልነበረዉም። ቢሆንም በሆለታ ማዕከል ከምንሠራዉ በተጨማሪ በርካታ የመስክ ሥራዎች በጊንጪ፣ ደንቢና ሌሎች ሥፍራዎችም ነበሩን። ታዲያ ምንም ተሽከርካሪ ሳይኖረን አርባና ሰማንያ ኪሎ ሜትር ድረስ በመጓዝ የምርምር ሥራዎችንን በታቀደዉ መሠረት ለማከናወን አዳጋች ይሆንብን ነበር። በወቅቱ ተሽከርካሪ የነበራቸው የምርምር ክፍሎች ትብብር ባይደረጉልን ኖሮ ምርምሮቻችንን ዳዋ በልቷቸዉ ይቀሩ ነበር፤ ማለቴ አረም ውጧቸዉ ለማለት ነዉ።

ስለ ጤፍ በዚህ ብቻ አላበቃም። ወደፊት በርካታ የምጽፍባቸዉ ነጥቦች አሉ። በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 21፤ 2011 ዓ.ም. (June 28, 2019)