በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤
የአየር ንብረት ለውጥ — የካርቦን ገበያ፣ ታክስና ፈንድ
ካርቦን በተመለከተ በሰፊዉ አገልግሎት ላይ የዋለዉ ካርቦን ዴቲንግ (Carbon dating) ተብሎ የሚታወቀዉ ሲሆን ይህም የአንድን ናሙና ወይም ቅርስ ዕድሜ ለማወቅ የሚያስችለን ነዉ። በዚሁ መንገድ በመጠቀም የአንድ የቆየ አጥንት ወይም ስባሪ እንጨት ዕድሜ መገመት እንችላለን ማለት ነዉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የካርቦን ገበያ፣ የካርቦን ታክስና የካርቦን ፈንድ የሚሉትን ቃላትም መስማት ጀምረናል። ለመሆኑ እነዚህ ድሮ ያልተለመዱ ቃላት ከየት ብቅ አሉ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። እነዚህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተዋወቅናቸዉ የመጡት ቃላት የአየር ንብረት ለውጥን ለመታደግ የመፍትሔ አካል ሊሆኑ ይችላሉ ተብለዉ የመጡ ናቸዉ። የነዚህን አዳስ ቃላት ዋና ዓላማና አጠቃቀም ከዚህ በታች በአጭሩ ለማሳየት እሞክራለሁ።
የካርቦን ታክስ (ቀረጥ)፤ ይህ የሚያመለክተዉ ካርቦን ላይ መሠረት ያደረገ ኢነርጂ የሚጠቀሙ ድርጅቶችም ሆነ ግለሰቦች የሚከፍሉት ታክስ ነዉ። እነዚህ ካርቦን ላይ የተመሠረቱ የምንላቸዉ እንደ ድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅ፤ የተፈጥሮ ጋዝ ሲሆኑ ስንጠቀማቸዉ ወይም ሲቃጠሉ ከፍተኛ የሆነ የግሪን ሀዉስ ጋዝ በተለይም ካርቦንዳይኦክሳይድን ወደ ከባቢያችን የሚለቁት ናቸዉ። ። ስለዚህ የግሪን ሀዉስ ጋዝን ከከካባቢያችን ለመቀነስ የኢነርጂዉ ተጠቃሚዎች ካርቦንዳይኦክሳይድን ወደ ከባቢያችን በሚለቁት መጠን ታክስ ይጣልባቸዋል። በዚህ መሠረት አካባቢውን ብዙ የበከለ ብዙ ቀረጥ ይከፍላል ማለት ነዉ። ተጠቃሚዎችም በተለይ ትላልቅ ካምፓኒዎች ከሚጣልባቸዉ ከፍተኛ የካርቦን ታክስ ነፃ ለመሆን አማራጭ የኢነርጂ ምንጮችን ለመጠቀም ይገደዳሉ። በዚሁ ምክንያት ነዉ በአሁኑ ጊዜ በተለምዶ “ንፁህ ኢነርጂ” የተባሉትን እንደ ንፋስ፣ የፀሐይ ብርሃን እና ዉሃ የመሳሰሉት በጥቅም ላይ እየዋሉና ህብረተሰቡም እነዚህ የኢነርጂ ምንጮችን ለመጠቀም ያለዉ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ነዉ።
የካርቦን ገበያ፤ በአንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት የካርቦን ገበያ የሚባልም አለ። ይህም ማለት ካምፓኒዎች በነፃ መልቀቅ የሚፈቅድላቸዉ የካርቦንዳይኦክሳይድ ኮታ ይሰጣቸዋል። አማራጭ የኢነርጂ ምንጭ በመጠቀም የተሰጣቸዉን ኮታ መጠቀም የማይችሉ ካምፓኒዎች ደግሞ ከተሰጣቸዉ የኮታ ዉስጥ ያልተጠቀሙትን ከኮታ በላይ ለሚጠቀሙት መሸጥ ይችላሉ። ለምሳሌ ከ50 የሚበልጡ በስዊዘርላንድ የሚገኙ የሲሚንቶ፣ የኬሚካልና የብረታ ብረት ፋብሪካዎች የዚህን የካርቦን ገበያ መንገድ ይከተላሉ። በአዉሮፓ ደግሞ ከአሥር ሺህ በላይ የሆኑ ድርጅቶች በዚህ የካርቦን ገበያ ተጠቃሚ ናቸዉ።
የካርቦን ፈንድ፤ ይህ ፈንድ የተቋቋመዉ የአየር ንብረትን ለመግታት ይረዳል ተብሎ ከታሰቡት አንዱ የሆነዉን የዛፍ መትከልና ደን መንከባከብ በተለይ በመልማት ላይ ያሉ ሀገሮች ለሚያደርጉት አስተዋጽኦ በገንዘብ ለመደገፍ ነዉ። በዚህ ፈንድ የተሣተፉት ሀገሮች 47 ሲሆኑ ከነዚህ ዉስጥ 18 ከአፍሪካ፣ 18 ከላቲን አሜሪካ እና 11 ከኤሲያ እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። ከነዚህ ዉስጥ ኢትዮጵያም አንዷ ናት። በዚህ የ1.3 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት 17 ሀገሮች በፋይናንስ ድጋፍ ያደርጋሉ።
የባዮካርቦን ፈንድ፤ ይህም ከላይ እንደተጠቀሰዉ የካርቦን ፈንድ ሁሉ የምድራችንን የደን ሽፋን በመጨመር ካርቦንዳይኦክሳይድ ወደ ከባቢያችን እንዳያፈተልክ ለማድረግ የታሰበ ሲሆን ፕሮጀክቱ በመልማት ላይ ካሉ አምስት ሀገሮች ጋር በጋራ ይሠራል። እነርሱም ኮሎምቢያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢንዶኔሺያ፣ ሜክሲኮ እና ዛምቢያ ናቸዉ። በፋይናንስ በኩል ፕሮጀክቱ በዓለም ባንክ ይረዳል። እዚህ ላይ በደቡባዊ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘዉን የሁምቦ ባዮካርቦን ፈንድ መጥቀስ ያስፈልጋል። ይህ ደን የሚሸፍነዉ 2700 ሄክታር መሬት ሲሆን ከዚህ በፊት ከጥቅም ዉጪ የሆነ ሥፍራ ነዉ። ለአራት ዓመታት በሥፍራዉ በተደረገዉ የልማት ሥራ የእህል ምርትም ከፍ ሊል ችሏል። ሌላዉ በባዮካርቦን ፈንድ የሚታገዘዉ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይም በቡና አብቃይ ሥፍራዎች ትኩረት በማድረግ ላይ የሚገኘዉ ነዉ። ከሶስት ወራት በፊት የታተመዉ ጽሑፍ ገርባ ዲማ በሚባለዉ በደቡባዊዉ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኝ ደን ዉስጥ ያለዉን የካርቦን ክምችት ያሳያል። በጥናቱ መሠረት በደኑ ውስጥ ያለዉ አማካይ የካርቦን ክምችት 508.9 ቶን በሄክታር ነዉ። እንደ ጥናቱ ተሳታፊዎች ይህ የካርቦን መጠን ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለደኑ ተገቢዉን ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ ሀገሪቱ ከባዮካርቦን ፈንድ የምታገኘዉን ገንዝብ ማሳደግ እንዳለባት ያሳስባሉ።
በተመሣሣይ መልኩ ከጀርመን መንግሥት ጋር በትብብር የሚሠራዉ የካርቦን ገበያ ሪፖርት እንደሚያሳየዉ ትብብሩ በኢነርጂ፣ ትራንስፖርትና ቆሻሻ ማስወገድ ላይ ያተኩራል። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ የፕሮጀክት ሥያሜዎች በርካታ ፕሮጀክቶች ሥራ ላይ ዉለዋል።
እዚህ ላይ ዛፍ መትከልና የደን እክብካቤ ላይ ትኩረት የተሰጠዉ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ዛፎች ከፍተኛ እገዛ ሰለሚያደርጉ ነዉ። ምክንያቱም ዛፎች ወደ አካባቢያችን የሚለቀቀውን ዋነኛ የግሪን ሀዉስ ጋዝ አካል የሆነውን ካርቦንዳይኦክሳይድን አምቀዉ ስለሚይዙ ነዉ። ከዚህ በፊት “የአየር ንብረት ለዉጥ — ዛፎቻችን” በሚለዉ ጽሑፌ ተዛማች መረጃን ጠቅሼ ለማሳየት እንደሞከርኩት ከአንድ ዛፍ ጠቅላላ ክብደቱ ዉስጥ ግማሹን የሚይዘዉ ካርቦን ነዉ። በዚሁ መሠረት 12 ዓመት የሆነውና 600 ኪ.ግ. የሚከብድ ዛፍ በዉስጡ 859 ኪ.ግ. ካርቦን ዳይኦክሳይድ አምቆ የሚይዝ ሲሆን በ200 ሄክታር ላይ ያለ ደን (በአንድ ሄክታር 650 ዛፍ ቢኖር) በ12 ዓመት 111,670 ቶን (ወይም 111 ሚሊዮን ኪ.ግ.) ካርቦንዳይኦክሳይድ አምቆ ይዟል ማለት ነዉ። ነገር ግን በዚህ በ200 ሄክታር ላይ ያለ ደን የመቃጠል አደጋ ቢያጋጥመዉ ከላይ የተጠቀሰዉ የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን አካባቢያችን አፈተለከ ማለት ነዉ። በዚሁ መሠረት በአየር ንብረት ለዉጥ ለሚደርሰዉ መጥፎ ክስተት የራሱን አሰተዋጽኦ ያደርጋል።
እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ዛፍ እንትከል ሲባል የተተከለዉ አይቆረጥም ማለት አይደለም። ከዚህ በታች በምሥሉ እንደሚታየዉ በሚቆረጡት ዛፎች ምትክ አዲስ ዛፍ በወቅቱ መትከል ያስፈልጋል።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 17፤ 2011 ዓ.ም.