ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለውጥ — የኛ አስተዋጽኦ

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለውጥ — የኛ አስተዋጽኦ

ከዚህ ቀደም “የአየር ንብረት ለውጥ — ምልክቶቹ” በሚለዉ ጽሑፌ ለአየር ንብረት መለወጥ እንደ ማስረጃ ከምንጠቅሳቸዉ ክስተቶች ውስጥ ዋናዎቹን ጠቅሼ ነበር። እነርሱም 1ኛ) የአየርና የባህር ሙቀት መጨመር፣ 2ኛ) የዝናም እጥረት ወይም ድርቅ መባባስ፣ 3ኛ) የጎርፍ መብዛት፣ 4ኛ) የግሪንሃዉስ ጋዝ መጠን መጨመር፣ 5ኛ) የበረዶ ክምችት መመናመን፣ 6ኛ) የባህር ወለል ከፍ ማለት፣ እና 7ኛ) የባህር ዉሃ ወደ አሲዳማነት መቀየር ናቸዉ። በመቀጠልም በተከታታይ በጻፍኳቸው ሰባት ብሎጎች የአየር ንብረት ለውጥ በብዝሀ ሕይወታችን፣ በሰብሎቻችን፣ በአረም መስፋፋት፣ በደናችን፣ በውሃችን፣ በእንስሳቶቻችን እና በጤናችን ላይ የሚያደርስዉን አደጋ ለማሳየት ሞክሬአለሁ። በዛሬዉ ጽሑፌ ደግሞ ለዚህ ለአየር ንብረት ለውጥ የሰዉ ልጅ አስተዋጽኦን ለማሳየት ነዉ። በተለይ ትኩረት የማደርገዉ በግሪን ሀዉስ ጋዝ ላይ ነዉ።

ከዚህ በፊት ለማሳየት እንደሞከርኩት ግሪን ሃዉስ ጋዝ የሚል ስያሜ የተሰጣቸዉ ወደ ሰባት የሚጠጉ ጋዞች አሉ። እነርሱም የዉሃ ትነት (H2O)፣ ካርቦንዳይኦክሳይድ (Carbon dioxide CO2)፣ ሚቴን (Methane CH4)፣ ኦዞን (Ozone O3)፣ ናይትረስ ኦክሳይድ (Nitrous oxide N2O)፣ ክሎሮፍሎሮካርቦንስ (Chlorofluorocarbons CFCs) እና ሃይድሮፍሎሮካርቦንስ (Hydrofluorocarbons HCFCs & HFCs) ናቸዉ። የነዚህ የግሪንሃዉስ ጋዞች በአካባቢያችን መከማቸት በቀጥታም ሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ጉዳት ያደርሱብናል።

ለነዚህ የግሪን ሃዉስ ጋዞች በአካባቢያችን መከማቸት ግብርናችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። የዓለም አቀፍ የእርሻ ምርምር ማዕከላትን የሚስተባብረዉ ድርጅት ሪፖርት መሠረት በደን ጭፍጨፋና የመሬት አጠቃቀም ምከንያት በያመቱ ከ2.2 እስክ 6.6 ቢሊዮን ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ ከባቢ አየር ያፈተልካል። ይህም በዓለማችን ካለዉ አጠቃላይ የግሪን ሃዉስ ጋዝ ውስጥ ከ4 እስከ 14% የሆነዉን ይሸፍናል። በተመሣሣይ መልኩ ኤ.ኤ.አ. በ2050 የአለምን ህዝብ የምግብ ፍላጎት ለማርካት 10 ሚሊዮን ስኬዌር ኪሎ ሜትር የሆነ ቦታ መመንጠር ይኖርበታል። በዚሁ ምንጣሮ ምክንያት 3 ሚሊዮን ቶን የሚሆን ካርቦንዳይኦክሳይድ ያፈተለካል ማለት ነዉ።

የከብት እርባታም ከፍተኛ መጠን ያላቸዉን የግሪን ሃዉስ ጋዞች ወደ አካባቢያችን ይረጫል። ከላይ በተገለጸዉ ሪፖርት መሠረት የእንስሳት እርባታ 7.1 ቢሊዮን ቶን የሚሆን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ ከባቢያችን የሚለቅ ሲሆን ይህም የአለማችንን 14.5% ይሆናል። በተለይ የሥጋና የወተት ከብቶች ከፍተኛ መጠን ያለዉን የግሪን ሃዉስ ጋዞች ወደ አካባቢያችን የሚለቁ ሲሆን የዶሮ እርባታ እጅግ ዝቅተኛ መጠን ያለውን ድርሻ ይይዛል።

ሀገራችንን በተመለከተ የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት መረጃ እንደሚሳየዉ በከፍተኛ መጠን ወደ አካባቢያችን የሚረጨዉ የግሪን ሃዉስ ጋዝ ወስጥ ከእርሻ ጋር የሚገናኙት ሚቴን እና ናይትረስ ኦክሳይድ የሚባሉት ናቸዉ።

በምሥሉ የሚታየዉ እ.ኤ.አ. በ2016 በኢትዮጵያ ወስጥ ከእርሻ ጋር በተገናኘ ወደ አካባቢያችን የሚያፈተልኩትን የግርን ሀዉስ ጋዦች ነዉ። ጥሬ መረጃዉ የተገኘዉ ከዓለም የምግብ ድርጅት ድህረ ገጽ ሲሆን ወደ ምሥሉ ቀይሬዋለሁ።

ሀገራችንን በተመለከተ Climate and Clean Air Coalition (CCAC) በሚለዉ ስብስብ ጠለቅ ያለ ጥናት ተደርጎ ነበረ። በጥናታቸዉ ከተገኙት ውጤቶች መካከል በወተት ከብቶች በኩል ወደ አካባቢያችን የሚረጩትን የግሪን ሃዉስ ጋዞች የሚያሳየዉን ካርታ በመዋስ ለዛሬዉ ጽሑፌ ከዚህ በታች አቅርቤያለሁ። በጥናቱ መሠረት በወተት ከብቶች ምከንያት ወደ አካባቢያችን ከሚረጨው የግሪን ሀዉስ ጋዝ ዉስጥ 97.3% ቱን የሚይዘዉ ሚቴን ሲሆን ናይትረስ ኦክሳይድና ካርቦን ዳይኦክሳይድ የተቀረዉን እጅግ ዝቅተኛ ድርሻ ይይዛሉ።

ከላይ የሚታየዉ በኢትዮጵያ በወተት ከብቶች ምክንያት ወደ አካባቢያችን የሚረጩትን የግሪን ሃዉስ ጋዞች መጠን ነዉ። ምሥሉ ከዚህ ድህረ ገጽ የተወሰደ ነዉ።

ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ያለዉን የግሪን ሃዉስ ጋዝ መጠን የገመገመ ሌላ ጥናት እንደሚያሳየዉ በአካባቢያችን ካለ የግሪን ሃዉስ ጋዝ ውስጥ 42% ከከብት እርባታ የመጣ ሲሆን 37% ደግሞ ከዛፍ መቁረጥ የተነሣ ነዉ።

በአጠቃላይ የዛሬዉ ጽሑፌ የሚያሳየዉ እርሻችን ለግሪን ሀዉስ ጋዝ መከማቸት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለዉ ነዉ። በተለይ ደግሞ የሥጋ ከብቶችና የወተት ላሞች የላቀ ድርሻ ይወስዳሉ።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 15፤ 2011 ዓ.ም.

አስተያየት ያስቀምጡ