ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለውጥ — በእንስሳዎቻችን

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለውጥ — በእንስሳዎቻችን

እንስሳዎቻችን የሚለዉን ቃል የተጠቀምኩት ማናቸውንም ለምግብ የምንጠቀማቸዉም ሆነ የማንጠቀማቸዉ እንዲሁም በዉሃ ውስጥም ሆነ በየብስ የሚኖሩ ከቦታ ወደ ቦታ ሊቀንሳቅሱ የሚችሉትን ፍጥረታት ለማመልከት ነዉ። ምንም እንኳ የሰዉ ልጅ ከላይ የተቀመጠዉን መስፈርት ቢያሟላም በዚህ ምድብ ዉስጥ አላተካተተም።

እንደ ሌላው ሴክተር ሁሉ የአየር ንብረት ለዉጥ በእንስሳዎቻችንም ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ ነዉ። አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየዉ ለምግብነት የምንጠቅምባቸዉ እንደ ከብት፣ በግ፤ ፍየልና ዶሮ ያሉት ከ10 እስከ 30 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሆነ የአየር ሙቀት ተስማሚ ሲሆን የሙቀቱ መጠን ከዚህ በላይ ከጨመረ ግን የመመገብ ፍላጎታቸዉ ላይ አሉታዊ ጎን አለዉ። በዚሁ ሪፖርት መሠረት የአየር ንብረት ለዉጥ በእንስሳት ላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ተጽእኖ ያሳድራል። በተመሣሣይ መልኩ ከዚህ ቀደም በመስኩ የተሠሩ የጥናት ሥራዎችን የገመገመዉ ጽሑፍ እንደሚያሳየዉ የአየር ንብረት ለዉጥ በተለያየ መንገድ በእንስሳዎቻችን ላይ የሚያደርሰዉ ተጽእኖ ከፍተኛ ነዉ። ከነዚህ ውስጥ ዋነኖቹ 1ኛ) በቂ ያልሆነና ጥራቱ የቀነሰ መኖ፣ 2ኛ) የውሃ እጥረት፣ 3ኛ) የበሽታ መከሰት፣ 4ኛ) የሚጨምረዉን የሙቀት መጠን መቋቋም አለመቻል እና 5ኛ) የእንስሳቱን የብዝሀ ሕይወት መቀነስ ናቸው። .ዝርዝሩን ከላይ በገለጽኩት ጽሑፍ ማግኘት ይቻላል። በተመሣሣይ መልኩ የአየር ንብረት ለዉጥ በዓሣ ምርት ላይ ለውጥ እንሚያመጣ ከዚህ በፊት “የአየር ንብረት ለውጥ — በዉሃችን” በሚል በጻፍኩት ጽሑፍ ለማሳየት ሞክሬለሁ። በዚሁ መሠረት ከአፍሪካ በትልቅነቱ በአንደኝነት ደረጃ የሚገኘዉ የቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ የተሠረዉ ጥናት እንደሚያሳየዉ በዝናም እጥረት ምክንያት  የሐይቁ  ከፍታ በሚያንስበት ወቅት የዓሣ ምርትም በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል።

ሀገራችንን በተመለከተ ከአምስት ዓመት በፊት ለህትመት የበቃወ ጽሑፍ እንደሚያሳየዉ በአየር ንብረት ለዉጥና የግጦሽ አጠቃቀም ጉድለት የተነሣ በቦረና አካባቢ የከብት እርባታዉ ከፍተኛ እክል ገጥሞታል። በቅርቡ የታተመ ሌላ ጽሑፍ እንደሚያሳየዉ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት በሚደርሰዉ ከፍተኛ የአየር ሙቀት ምክንያት የወተት ምርት በ38% ሊቀንስ ችሏል። እንደሚመስለኝ ይህ አሀዝ የተገኘዉ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ከተሠራ ጥናት ሳይሆን በሌላ ሀገር ከተሠራ ነው።

የአየር ንብረት ለዉጥ በተለይም ድርቅ በከብቶቻችን ላይ የከፋ ጉዳት ያደርሳል። ምሥሉ የተወሰደወ ከኦክስፋም ድህረ ገጽ ነው።

ከዓሣና ውሃ ጋር በተገናኘ በሀገራችን የተደረገዉ ጥናት እንደሚያሳየዉ በጣና ሐይቅ አካባቢ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዝናም መጠን፣ በአየር ሙቀት እና በአየር እርጥበት ላይ ከፍተኛ መለዋወጥ ተከስቷል። በተለይም ባለፉት 22 ዓመታት አማካይ የከፍተኛዉ የአየር ሙቀት በ3.1 ድግሪ ሴንቲ ግሬድ አድጓል። በኔ ግምት ይህ በዚህ አጭር ጊዜ የታየዉ የሙቀት መጨመር ከሌሎች የዓለማችን አካባቢዎች ከተመዘገበዉ ከፍ ያለ ይመስለኛል። ጥናቱ በተካሄደበት አካባቢ ላሉ ዓሣ አጥማጆች ከተደረገዉ ቃለ መጠይቅ መረዳት እንደሚቻለዉ 42.9% የሚሆኑት ዓሣ አጥማቾች የአየር ንብረት ለውጥ በዓሣ ምርታቸዉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰባቸዉ ነዉ።

በአጠቃላይ የአየር ንብረት ለዉጥ በእንስሳዎቻችን ላይ ያደርሳል ተብሎ በሚጠበቀው ክስተት ላይ ብዙም መረጃ ማግኘት አልቻልኩም። ስለዚህ በዚህ መስክ በቂ ጥናት ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ምክንያቱም ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቀዉን የአየር ንብረት በከፊልም ቢሆን መግታት ሰለሚያስፈልግ።

በሚቀጥለዉ ጽሑፌ የአየር ንብረት ለዉጥ በጤናችን ላይ ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቀዉን ለማሳየት እሞክራለሁ።

እስከዚያዉ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 14፤ 2011 ዓ.ም.

አስተያየት ያስቀምጡ