ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለውጥ — በውሃችን

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለውጥ — በዉሃችን

እንደሚታወቀዉ ውሃ በኑሮችን ወይም በህልዉናችን እጅግ ከፍተኛ ቦታ ይዞ ይገኛል። ምክንያቱም ብንታመም እንኳ ምግብ ሳንበላ የተወሰኑ ቀናት መቆየት ብንችልም ያለ ውሃ ግን እጅግ ከዚህ ያነሰ ጊዜ ነዉ የምንቆየዉ። የውሃ ጥቅም ተዘርዝሮ አያልቅም። ከነዚህ ውስጥ ለመጠጥ፣ ለንጽህና መጠበቂያ (ለሰዉነታችንና ለምንገለግልበት ቁሳቁስ)፣ ለእርሻ፣ ለኃይል ማመንጫ፣ ለትራንስፖርት (መርከብና ጀልባ)፣ እሳት ለማጥፋት እና ለስፖርት (መዋኛ) መጥቀስ ይቻላል። ልክ እንደ እሳት ዉሃም ከመጠን ሲያልፍ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። ይህም በጎርፍ መልክ አካባቢያችንን በማጥለቅልቅ ከመኖሪያ ሥፍራችን እንድንሰደድ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ዜጎቻችንን ህይወትም ይቅጥፋል። ለምሳሌ ያህል የዛሬ 15 ዓመት (ኢ.ኤ.አ. ዲሴምበር 26፣ 2006) ሱማትራ በምትባለዉ የኢንዶኔሺያ ደሴት ላይ በደረሰው ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ጋር ተያይዞ የባህር ውሃ የሰዉ ልጅ መኖሪያ ወደ ነበረዉ የየብስ ቦታዎች በአፋጣኝ በመዉረር ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። በነዚህ ሁለት ተያያዥ ክስተቶች የተነሣ ከ200 ሺህ በላይ ሰው እንደሞተ ይገመታል። በአህጉራችን ደግሞ የዛሬ ሶስት ወር ሞገድ ቀላቅሎ ባጭር ጊዜ በወረደዉ ከፍተኛ የዝናም መጠን ምክንያት በሞዛምቢክ፣ ዚምባቢዌ እና ማላዊ የሚኖሩ እስከ 750 የሚደርሱ ሰዎች ሞተዋል።

በኛ ሀገር በትላልቅ ከተሞች ከሚደርሱት ጎርፎች መካከል በቀደምትነት የሚጠቀሰዉ በድሬዳዋ በደቻቱ ወንዝ አማካይነት በተደደጋጋሚ የሚደርሰዉ ድንገተኛ ጎርፍ ነዉ። አንድ ጥናት እንደሚሳየዉ እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2010 ባሉት አሥር ዓመታት ውስጥ በስምንቱ ዓመታት የሰው ሕይወትን ጭምር የቀጠፈ የጎርፍ አደጋ በዚሁ ወንዝ አማካይነት ተከስቷል። ከነዚህ ውስጥ ትልቁ በ2006 የተከሰተዉ ሲሆን ከ600 በላይ ሰዎች የሞት አደጋ ደርሶባቸዋል። በተመሣሣይ መልኩ በሀገራችን የልማት ሥራ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርገዉ የአዋሽ ወንዝ በክረምቱ ወቅት ከደጋዉ የሀገሪቱ ክፍል ከበርካታ ገባሮቹ ሰብስቦ ያመጣዉን ከመጠን ያለፈ ዉሃ በመካከለኛዉና ታችኛዉ አዋሽ በሚኖሩ ዜጎቻችንን ያስፈራራበታል፤ አንዳንዴም ወደ መኖሪያቸዉ ሰብሮ ይገባል። እኔም የዛሬ 30 ዓመት እሰራበት በነበረዉ የወረር እርሻ ምርምር ማዕከል ምንም እንኳ በደህና ሁኔታ የተሠራ መከላከያ ግድብ ቢሠራም በድንገት ጥሶ ገብቶ ብዙ የተለፋበት የሙከራ ሥራዎቻችንና እኛንም ለክፉ አደጋ እንዳያጋልጠን በስጋት ነበር የምናሳልፈዉ። በተለይ በማዕከል ኃላፊነት የነበሩት ሰባቱንም ቀን ለሃያ አራት ሰዓታት ወንዙ የደረሰበትን ከፍታና የግድቡን ጥንካሬ በቅርበት ይከታተሉ ነበር።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የዉሃ ብዛት ወይም ማቆር በሰብሎቻችን ላይም ከፍተኛ አሉታዊ ጎን አለዉ። ምንም እንኳ ተክሎች ካርቦን ዳይኦክሳይድን ምግብ ለመሥራት ቢጠቀሙም ኦክሲጅን ደግሞ ለሌላ አስፈላጊ ሥራ ያስፈልጋቸዋል። በውሃ ውስጥ የኦክሲጂን ዝዉዉር በጣም ዘገምተኛ ነዉ። በአየር ዉስጥ ካለው ጋር ሲነጻጸር በዉሃ ውስጥ ያለዉ የኦክሲጂን መጠን በአሥር ሺህ ጊዜ ያነሰ ነዉ። ስለዚህ ዉሃ ባቆረበት ቦታ ያሉ ተክሎች ናይትሮጂን የተባለዉንና ለዕድገታቸዉ አስፈላጊ የሆነ ንጥረ ነገር ከመሬት ውስጥ ሊወስዱ አይችሉም። በዚሁ ምክንያት የናይትሮጅን መጠን አዲስ ባቆጠቆጡ ቅጠሎች ላይ ሲያንስ ተክሉ በአሮጌ ቅጠሎቹ ውስጥ ያለዉን ናይትሮጂን ወደ አዲሶቹ ቅጠሎች ያጓጉዛል። ለዚህ ነዉ የናይትሮጂን እጥረት ምልክት የሆነዉ ቢጫ መልክ በአሮጌዎቹ ቅጠሎች ላይ የምናየዉ። ሳላስበው በውሃ ብዛት ምክንያት በራሳችንም ሆነ በተክሎቻችን ላይ ስለሚደርሰዉ አደጋ ውስጥ ገባሁ እንጂ የዛሬዉ ጽሑፌ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት በዉሃችን ላይ የሚደርሰዉን ክስተት ለመዘገብ ነዉ።

የአየር ንብረት ለዉጥ በዉሃ ላይ ሰለሚያደርሰዉ ጉዳት በርካታ ጥናቶች ተካሂደዋል። በአፍሪካ በትልቅነታቸዉ ከሚታወቁት ሐይቆች መካከል የቪክቶሪያና የቻድ ሐይቆች ሊጠቀሱ ይችላሉ።  የቪክቶሪያ ሐይቅ በትልቅነቱ በአፍሪካ አንደኛ በዓለም ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በኬኒያ፣ ኡጋንዳና ታንዛኒያ ይዋሰናል። ከዚህ በፊት የታተመ ሪፖርት እንደሚያሳየዉ በዝናም እጥረት ምክንያት የቪክቶሪያ ሐይቅ የዉሃዉ ከፍታ በሚያንስበት ወቅት በዓሣ ምርት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ጎን ነበረዉ። የቻድ ሐይቅ ደግሞ በካሜሩን፣ ቻድ፣ ኒጀር እና ናይጀሪያ የሚዋሰን ሲሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአፍሪካ አንዱ ትልቅ ሐይቅ ነበር። በተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ድርጅት ባወጣዉ ሪፖርት መሠረት ባለፉት 60 ዓመታት ብቻ የቻድ ሐይቅ መጠን በ90% ቀንሷል። ሐይቁ የሸፈነዉ ስፋት ደግሞ እ.ኤ.አ. 1963 ከነበረበት 26 ሺህ ስኰዌር ኪሎ ሜትር አሽቆልቁሎ በአሁኑ ጊዜ 1500 ስኰዌር ኪሎ ሜትር ብቻ ነዉ።

ወደ ሀገራችን ስንመለስ በኢትዮጵያ ወደ ሰባት የሚጠጉ ትላልቅ የወንዝ ተፋሰሶች አሉ። እነርሱም ወደ ምዕራብ አቅጣጫ በመፍሰስ ከነጭ አባይ ጋር የሚቀላቅሉት ሶስቱ ወንዞች (አባይ፣ ተከዜና ባሮ)፣ ወደ ደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ በመፍሰስ ወደ ሱማሊያ የሚዘልቁት ሁለት ወንዞች (ዋቤ ሸበሌና ገናሌ)፣ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ወደ ሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ በመፍሰስ በጂቡቲ ድንበር ላይ ወደሚገኘዉ የአቤ ሐይቅ ጉዞዉን የሚያበቃዉ የአዋሽ ወንዝና ወደ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በመፍሰስ ኢትዮጵያና ኬኒያ ድንበር ላይ ወደሚገኘዉ የቱርካና ሐይቅ የሚገባዉ የጊቤ-ኦሞ ወንዝ ናቸዉ። እነዚህ ትላልቅ ወንዞች ስማቸዉ ይጠቀስ እንጂ እነርሱን ለዚህ ዝና ያበቋቸዉ በርካታ ገባር ወንዝች ናቸዉ። እነዚህን ታዋቂ ወንዞች ከነገባሮቻቸዉ የሚያሳየዉ በኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ድርጀት ባልደረባ የተሣለዉን ካርታ ከዚህ በታች ማየት ይቻላል።

በምሥሉ የሚታየው በኢትዮጵያ ታዋቂ የሆኑ ወንዞችና ገባሮቻቸዉ የሚፈሱበት አቅጣጫ ነዉ። በደማቅ ቀለም የሚታዩት ዋና የሆኑ ወንዞች ነዉ። የምሥሉ ምንጭ› https://www.academia.edu/7228560/drainage_in_ethiopia

ኢትዮጵያ ካሏት በርካታ ወንዞች በተጨማሪ ሐይቆችና የከርሰ ምድር ዉሃም ሊጠቀሱ ይቻላል። በብዙ ሀገራት ከሌሎች ሴክተሮች ጋር ሲወዳደር ለእርሻ የሚዉለው የውሃ መጠን ከፍተኛ ድርሻ ይይዛል። ኢትዮጵያ ባላት የከርሰ ምድር ዉሃ ላይ ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ለመስኖ እርሻ ልንጠቀምበት የምንችለዉ የከርሰ ምድር ዉሃ በቅርበት (ማለትም እስከ 20 ሜትር ጥልቀት) የሚገኘዉ በኦሞና በአዋሽ ወንዞች እና በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ነዉ። ቢሆንም የከርሰ ምድር ዉሃ እንደ ተጨማሪ ካልሆነ በስተቀር ለብቻዉ ለመስኖ እርሻ በቂ አቅርቦት እንደማይኖረዉ የጥናቱ ዉጤት ያሳያል።

እንደ አንዳንዶች ግምት ኢትዮጵያ በመስኖ ማልማት ከምትችለዉ 3.5 ሚሊዮን ሄክታር ዉስጥ እስካሁን የተጠቀመችበት 5% ብቻ ነዉ። ቢሆንም ባንዳንድ ሥፍራዎች በአየር ንብረት ለዉጥም ይሁን የመስኖ ዉሃን ከመጠን ባለፈ በመጠቀም መሆኑ በውል ባላዉቅም በገሪቱ የሚገኙ አንዳንድ ሐይቆች አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ከነዚህ ወስጥ ሙሉ በሙሉ ለመድረቅ የበቃዉ የሀረማያ ሀይቅ ነዉ። ለዚህ ራሴ ምስክር ልሆን እችላለሁ። ከ30 ዓመታት በፊት የሀረማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ሐይቁ በህይወት ነበር። ዛሬ ግን በቦታው የለም። እንደ አንዳንዶች አባባል የዝዋይና የአቢያታ ሐይቆች ለአደጋ እየተጋለጡ ነዉ። በቅርቡ ለህትመት የበቃዉ የጥናት ጽሑፍ እንደሚያሳየዉ በመቂና ከታር ወንዞች ምክንያት በደለል እየተሞላ የሚገኘዉ የዝዋይ ሐይቅ መነሻዉ ከአየር ንብረት ለዉጥ ጋር እንደሚገናኝ ነዉ።

የአየር ንብረት ለዉጥ በወንዞቻችን ላይ ሰለሚያደርሰዉ ክስተት በተመለከት ሰፊ ጥናት ተካሂዷል። በኢትዮጵያዉያን፣ ካናዳዊያንና ፊንላዳዊያን በጋራ በሠሩት ጥናት ላይ በመመርኮዝ በቅርቡ ለህትመት የበቃዉ ጽሑፍ አራት ተፋሰሶችን በጥናቱ አካቷል። እነዚህም አዋሽ፣ ባሮ፣ ገናሌና ተከዜ ናቸዉ። በጥናቱ መሠረት የተደረሰበት ትንበያ እንደሚያሳዉ እ.ኤ.አ. በ2050 የአየር ሙቀት በ2.3 ድግሪ ሴንቲግሬድ የሚጨምር ሲሆን በ2080 ደግሞ የ3.3 ድግሪ ሴንቲግሬድ ጭማሪ ያሳያል። በተመሣሣይ መልኩ ዓመታዊ የዝናም መጠን በ2050 በ3% የሚያድግ ሲሆን በ2080 በ6% እድገት ያሳያል። በዚሁ መሠረት የአራቱ ወንዞች የፍሰት መጠን በ2050 ከ3-18% እንዲሁም በ2080 ከ6-33% እድገት ያሳያል። ስለዚህ በሀገራችን በሚቀጥሉት 30 እና 60 ዓመታት ውስጥ የዝናም መጠንም ሆነ የወንዞች የፍሰት መጠን እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንደማይመጣ ይተነብያል። ለጥናቱ ተሣታፊዎችም እንቆቅልሽ የሆነባቸዉ ከዚህ ጥናት የተገኘዉ ትንበያ ከነባራዊዉ ሁኔታ ጋር አለመጣጣሙን ንዉ። ምክንያቱም በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች የዝናም መጠንም ሆነ የወንዝ ፍሰት እየቀነሰ ስለመጣ ነወ። እኔ ራሴ ባደኩበት አካባቢ የነበረ መጠነኛ ይዘት ያለዉ ወንዝ ነበር። ድሮ በልጅ አይኔ ትልቅ ወንዝ ይመስለኝ ነበር፤ በክረምት ሲሞላማ እጅግ ያሰፈራራን ነበር። ከብዙ ጊዜያት በኋላ ተመልሼ ሳየው ወንዝ ሳይሆን ትንሽ ኩሬ መስሎ ታየኝ። የአየር ንብረት ለዉጥ በዚህ ወንዝ ላይም ተጽእኖ አድርጎ ከሆነ መረጃ የለኝም።

በአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ ላይ የተደረገዉ ጥናት እንደሚያሳየዉ የአየር ሙቅትም ሆነ የዝናም መጠን ባንዳንድ ሥፍራዎች ሲጨምር በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ይቀንሳል። በዚሁ በአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ የተሠራ ሌላ ጥናት እንደሚያሳየዉ በሚጨምረዉ የአየር ሙቀት ምክንያት የዝናም መጠን እንደ ሚቀንስ ይጠበቃል። ስለዚህ ለመስኖ እርሻና ለሌሎች የልማት ሥራዎች የሚስፈልግ ዉሃ እጥረት እንደሚኖር ይተነብያል። ስለዚህ በተለያዩ ጊዜ የተደረጉ የጥናቱ ዉጤቶች ተመሣሣይነት የላቸዉም።

በሌላ በኩል በአባይ ወንዝና አካባቢዉ የተደረገዉ ጥናት እንደሚሳየዉ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት የዝናም መጠን ከ7 እስከ 48% ሲጨምር የወንዙ መጠን ደግሞ ከ21 እስከ 97% ያድጋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በሚከሰተዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት የዝናም ወቅት አሁን ካለው ከሰኔ እስከ መስከረም ወደ ሌላ ጊዜ እንደሚቀየር ይገመታል።

ማጠቃለያ

ከላይ የተጠቀሱት መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በዝናም መጠንና በወንዞች ተፋሰስ ላይ የተደረጉት ትንበያዎች ተመሣሣይነት የላቸዉም። አንዳንዶቹ ጥናቶች የዝናም መጠንም ሆነ የወንዞች ተፋሰስ ብዛት እንደሚጨምር ትንበያ ቢሰጡም ሌሎች ደግሞ በተቃራኒዉ ይቀንሳል ይላሉ። የሚገርመዉ ባንድ ወንዝ ላይ የተሠሩ ሁለት ጥናቶች የተለያየ ትንበያ መስጠታቸዉ ነዉ። በኔ ግምት ይህ ሊሆን የሚችለው ትንበያውን ለማድረግ ጥናቶቹ የተጠቀሙባቸዉ መንገዶች ወይም ሞዴሎች የተለያዩ ሊሆኑ ሰለሚችሉ ሲሆን ሌላዉ ደግሞ ለትንበያው እንደ መነሻ የተጠቀሙባቸዉ ዓመታት የተለያዩ ሊሆኑ ስለሚችሉ ነዉ። ሰለዚህ የተለያዩ ተፋሰስ አካባቢችን እንዲሁም የከርሰ ምድር ዉሃን የሚያካትት ጠልቅ ያለ ጥናት በብሔራዊ ደረጃ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

በሚቀጥሉት ተከታታይ ጽሑፎቼ የአየር ንብረት ለዉጥ በከብቶቻችንና በጤናችን ላይ ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቀዉን ለማሳየት እሞክራለሁ።

እስከዚያዉ መልካሙን እመኛለሁ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 13፤ 2011 ዓ.ም.

አስተያየት ያስቀምጡ