በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤
የአየር ንብረት ለውጥ — በደናችን (ዛፎቻችን)
እንደሚታወቀዉ ሁሉ ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት ወደ 40% የሚጠጋዉ የሀገራችን ክፍል በደን የተሸፈነ ነበር። የዛሬ 35 ዓመታት ገደማ ደን (ወይም ፎረስትሪ) የሚባለዉን ኮርስ ያሰተማሩን መምህር እንደነገሩን ከሆነ በዚያን ወቅት ደን የሀገሪቱን 2-3% ብቻ ይሸፍን ነበር። ነገር ግን በርካታ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩን በኢትዮጵያ ባሁኑ ጊዜ የደን ድርሻ ወደ 10-15% አድጓል። ይህ መረጃ ትክክል ከሆነ በሀገሪቱ ዉስጥ ከፍተኛ የደን ተከላ ተደርጓል ማለት ነዉ። መረጃው ትክክለኛ ከሆነ ለማለት ያስገደደኝ በኢትዮጵያ ደንን የምናገኘዉ በተወሰኑ ሥፍራዎች ብቻ ሰለሆነና ይህም በኔ ግምት ከላይ ከተጠቀሰዉ ቁጥር የሚያንስ ስለሚመስለኝ ነዉ። ቢሆንም ከላይ የተገለጸዉ 10-15% የደን ሽፋን በቂ ነዉ ማለቴ አይደለም። ምክንያቱም እስከ 90% የሚሆን መሬታቸዉን በደን የሸፈኑ ሀገሮችም ስላሉ ነዉ።
በቂ ደን እንዲኖረን አዲስ ዛፍ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉት መልሰዉ እንዳይጨፈጨፉ እንክብካቤ ልናደርግላቸዉ ይገባናል። የዛፎችን ጭፍጨፋ በተመለከተ በአስረስ ጫካ ላይ የደረሰዉ ዓይነት ግፍ እስካሁን ትዝ ይለኛል። ምንም እንኳ የመሬታቸዉን መጠን በዉል ባላዉቀውም እኔ ያደኩበት አካባቢ አቶ አስረስ የሚባሉ በንጉሡ ዘመን የመሬት ባለቤት የነበሩ ሰዉ ነበሩ። እኝህ ሰዉ በመሬታቸዉ ላይ በርካታ ባህር ዛፍ በመትከል በእንክብካቤ ይዘዉት ነበር። ታዲያ የየካቲት 25 ቀን 1967ቱ መሬት ላራሹ አዋጅ መጥቶ ያንን እሳቸዉ ተክለዉና በደህና ሁኔታ የተንከባከቡትን ደን ሙሉ በሙሉ ወረሰባቸዉ። ደኑ ከርሳቸዉ ቁጥጥር ዉጭ ከሆነ በኋላ ማንም በአካባቢዉ የሚያልፍ ሰዉ በፈለገዉ መንገድ እንዲጨፈጭፍ ከልካይ አልነበረዉም። ደግነቱ አቶ አስረስ የተከሉት ባህር ዛፍ ሆነና እንደፈለጉ ቢጨፈጭፉት እንደገና እያቆጠቆጠ እስከዛሬም አለ። አለ ይባል እንጂ ዛፎቹ በተደጋጋሚ የመጨፍጨፍ አደጋ ሰለደረሰባቸዉ የጥራት ደረጃቸዉ በጣም ዝቅተኛ ነዉ። ምንም እንኳ በግሌ መሬት ላራሹን ብደግፍም ባፈጻጸሙ ላይ በነበረበት ችግር ምክንያት በተለይ እንደ አቶ አስረስ ዓይነት በመሬታቸዉ ላይ የልማት ሥራ ሲሰሩ የነበሩ ሁሉ በራሳቸዉ ጥረት ያለሙት ደን በመወረሱና ያለከልካይ ለበርካታ ዓመታት እንዲጨፈጭፍ በመፈቀዱ ከዚያ በኋላ በግላቸዉ ዛፍ የሚተክሉ ግለሰቦችን ማግኘት አስቸጋሪ ነበር ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም። ምክንያቱም አንድ ቀን የአስረስ ዕጣ ይደርሰናል ብለዉ ሰለሚሰጉ ነዉ።

ሁለተኛዉ መጠነ ሰፊ የደን ጭፍጨፋ ያየሁት በጋምቤላ አካባቢ ነዉ። በ1977 በሀገራችን በደረሰዉ ድርቅ ምክንያት የተጎዱ ወገኖቻችንን ለማስፈር በተደረገዉ ዘመቻ ጊሎ አቦል የሚባል ሥፍራ ተመድበን ለሶስት ወራት አቅማችን በፈቀደዉ መጠን ቤትም ባይሆን ጊዜያዊ ማረፊያ ስንሰራ ቆይተን ነበር። ታዲያ በመመለሻችን ቀን በአዉቶቢስ ውስጥ ሆኜ ያየሁትን ዓይነት የደን ጭፍጨፋ እስካሁን አላየሁም። እጅግ ሰፊ የሆነ መሬት ላይ የነበሩ ትላልቅ ዛፎች በዶዘር እንዲገረሰሱ ከተደረጉ በኋላ ገሚሶቹ ከቦታዉ ተነስተዋል፤ የተቀሩት ደግሞ እዚያዉ ለዘመናት ከቆሙበት ሥፍራ አጠገብ ተጋድመዉ ነበር። እንደመሰለኝ የደን ምንጣሮ የተደረገዉ ለምግብ የሚሆኑ ሰብሎችን ለመዝራት ታስቦ ነዉ።
በሌላ በኩል በታዋቂዊዉ የናሽናል ጂኦግራፊክ መጽሔት ላይ Ethiopia’s ‘church forests’ are incredible oases of green በሚል በቅርቡ የታተመዉ ጽሑፍ እንደሚሳየዉ ጥናት በተደረገባቸዉ በርካታ የሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢ እንደታየዉ በቤተ ክርስቲያናት አካባባቢ ዛፎች ሳይቆረጡ በደህና ሁኔታ ተጠብቅዉ ሊቆዩ ችለዋል። ይህንንም ከዚህ በታች ባለዉ ምሥል ማየት ይቻላል። በዚሁ መሠረት የአካባቢዉ ብዝሀ ሕይወትም ሊጠበቅ ችሏል። በዚህ በጎ ሥራ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ካደረጉት መካከል የካሊፎኒያ ሣይንስ አካዳሚ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሜግ ሎውማን በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።በኢትዮጵያ በኩል በጥናቱ የተሣተፉት ዶክተር ወርቁ ሙላትና ዶክተር አለማየሁ ዋሴ ይገኙበታል። ቤዛ የምትባል ከዚህ ሥራ ጋር የምትገናኝ መጽሔት በእንግሊዘኛና አማርኛ አሳትመዉ ለአንባቢያን አድርሰዋል። እኔም በኦንላይን ገዝቼ ለማንበብ ችያለሁ። የመጽሔቱ የፊት ሽፋን ከዚህ በታች በምስሉ ይታያል።

በሀገራችን በርካታ የዛፍ ተከላ ፕሮግራሞች ባለፉት ሶስት አሥርት ዓመታት ተካሂደዉ ነበር። ከነዚህ ዉስጥ በደንገጎ፣ ቁሉቢ፣ ሙኔሣ ወዘተ ትዝ ይለኛል። በዚህ አጋጣሚ መጥቀስ የምፈልገዉ በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በተለምዶ “አዱኛ ላይብረሪ” ተብሎ የሚጠራ የደን መምህር በነበሩት በአቶ አዱኛ የተተከለ አካባቢዉን በጥሩ ሁኔታ የለወጠ ሥፍራ ነበር። ካለው የጸጥታ ሁኔታ የተነሣ በርካታ ተማሪዎች ይህን ጫካ እንደማጥኛ ሥፍራ አድርገዉ ይጠቀሙበት ነበር። በዚህ አገለግሎቱም ነው “አዱኛ ላይብረሪ” የሚለዉን ሥያሜ ያገኘዉ።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ዛፎች ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ። ምክንያቱም ዛፎች ወደ አካባቢያችን የሚለቀቀውን ዋነኛ የግሪን ሀዉስ ጋዝ አካል የሆነውን ካርቦን ዳይኦክሳይድን አምቀዉ ስለሚይዙ ነዉ። ከአንድ ዛፍ ጠቅላላ ክብደቱ ዉስጥ ግማሹን የሚይዘዉ ካርቦን ነዉ። እንደ አንድ ሪፖርት ግምት አንድ 12 ዓመት የሆነውና 600 ኪ.ግ. የሚከብድ ዛፍ በዉስጡ 859 ኪ.ግ. ካርቦን ዳይኦክሳይድ አምቆ የሚይዝ ሲሆን ይህም በዓመት 72 ኪ.ግ. ማለት ነዉ። በዚሁ ሪፖርት መሠረት በ200 ሄክታር ላይ ያለ ደን (በአንድ ሄክታር 650 ዛፍ ቢኖር) በ12 ዓመት 111,670 ቶን (ወይም 111 ሚሊዮን ኪ.ግ.) ካርቦን ዳይኦክሳይድ አምቆ ይዟል ማለት ነዉ። ይህ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ነዉ። ስለዚህ አንድ ዛፍ ተቆረጠና ተቃጠለ ስንል በውስጡ የያዘዉ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ አካባቢያችን አፈተለከ ማለት ነዉ። በተመሣሣይ መልኩ ምንጣሮና ቃጠሎ በአንድ ሄክታር ወይም በሺሆች በሚቆጠሩ ሄክታሮች ላይ ቢደርስ ምን ያህል ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ አካባቢያችን እንደሚያፈተልክ መገመት ይቻላል።
ማጠቃለያ
በቅርቡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሁሉም ዜጋ ዛፍ እንዲተክል ጥሪ ማቅረባቸዉ ይታወሳል። እንዲተከል የጠየቁትም አራት ቢሊዮን ዛፍ ሲሆን በነፍስ ወከፍ 40 ዛፍ ይደርሰናል ማለት ነዉ። ይህንኑ ራሳቸዉ አርአያ በመሆን የመጀመሪዋዉን ዛፍ በግንቦት አጋማሽ 2011 ካስጀመሩ ወዲህ እስካሁን ድረስ በርካታ ዛፎችን በመትከል ላይ ይገኛሉ። በቅርቡ ከመገናኛ ብዙሃን እንደሰማሁት በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ አንድ መቶ ዛፋቸዉን ተክለዋል። ከላይ በተሰላዉ መሠረት አራት ቢሊዮኑ ዛፍ 3.4 ቢሊዮን ቶን የሚሆን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ አካባቢያችን እንዳያፈተልክና ጉዳት እንዳያደርስብን ያደርጋል ማለት ነው።
እኛስ በተራችን እነዚህን ከሀገራችንም አልፎ ለአህጉራችንም ሆነ ለዓለማችን እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ዛፎችን በመትከል ተሳትፎ አድርገናል ወይ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ዛፎቹን ለመትከል ፍላጎት ያለን ደግም የሚከተሉት መረጃዎች ያስፈልጉናል። በአካባቢያችን ያሉ የከተማም ሆነ የገጠር ቀበሌዎች ይህንን የዛፍ ተከላ ዘመቻ ለመምራት ዝግጁ ናቸዉን? በእያንዳንዱ ቀበሌ የሚተከሉት ዛፎች ወይም ችግኞች ተለይተው ታውቀዋልን? በቂ አቅርቦትስ አለ ወይ? ተከላዉ የሚካሄድበት ቦታስ ተለይቶ ታዉቆአልን? ይህ ሁሉ መረጃ ካለ እያንዳንዱ ቀበሌ ይህንን የዛፍ ተከላ ፕሮግራም ቢያስተባብሩ ዉጤታማ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ዛፎች በርካታ ጥቅም ቢኖራቸዉም የዛሬዉ ጽሑፌ ያተኮረዉ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሰዉን ቀዉስ በመከላከል ላይ ባላቸዉ አስተዋጽኦ ላይ ነው። በሚቀጥሉት ተከታታይ ጽሑፎቼ የአየር ንብረት ለዉጥ በከብቶቻችን፣ ዉሃችንና ጤናችን ላይ ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቁዉን ለማሳየት እሞክራለሁ።
እስከዚያዉ በቸር ይግጠመን።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 12፤ 2011 ዓ.ም.