በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤
የአየር ንብረት ለውጥ — በአረሞች መስፋፋት
አረም ማለት ከሚፈለግበት ቦታ ዉጭ የሚበቅል ተክል ንዉ። ልምግብነት የምንጠቀማቸዉ ስብሎችም እንድ አረም የሚቆጠሩብት ጊዜ ይኖራል። ለምሳሌ በስንዴ ማሣ ዉስጥ የገብስ ወይም የዳጉሣ ተክሎች ቢገኙ እንደ አረም ይቆጠራሉ። ምክንያቱም የስንዴዉን የጥራት ደረጃ ይቀንሳሉና ነዉ። አንዳንዶች አረምን ሲገልጹ “ያልተጋበዝ እንግዳ ይሉታል”። የሰብሎቻችንን የዘር ጥራት መቀነስ ብቻ ሳይሆን አረም ቢያንስ በሶስት መንገድ በምናሳድገዉ ተክል ላይ ትፅዕኖ ያደርሳል። እነዚህም የፀሐይ ብርሃንን፣ ውሃንና ከመሬት ውስጥ የሚገኙ ማዕድናትን በመሻማት ነው። እንደ እድገት ሁኔታቸዉና በተክሎቻችን ላይ በሚያደርሱት የተፅዕኖ ዓይነት አረሞች በሶስት ሊከፈሉ ይችላሉ። እነርሱም ቅጠለ-ሰፋፊ፣ ሣር-ነክ እና ጥገኛ ናቸዉ። ቅጠለ-ሰፋፊ አረሞች የፀሐይ ብርሃን ሰብሎቻችን ዘንድ እንዳይደርስ በመጋረድ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ። ቅጠለ-ሰፋፊ አረሞችን የምንቆጣጠር ከሆነ ሣር-ነክ የሆኑ አረሞች ደግሞ በተራቸው ጠንቅ መሆን ይጀምራሉ። ጥገኛ አረሞች (ወይም በእንግሊዘኛ ፓራሲቲክ ዊድስ) የሚባሉት ምንም እንኳ ለተመልካች ራሳቸዉን ችለዉ የሚያድጉ ቢመስሉም እነርሱ ግን በሌላዉ ተክል ላይ ተጣብቀዉና ዋናዉ ተክል ለፍቶ ያዘጋጀዉን ምግብ ይሻሙታል። እነዚህን የተለያዩ የአረም ዓይነቶች በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተለያዩ መንገዶች አሉ። ዉጤታነታቸዉም እንደዚሁ የተለያየ ነው።

የዛሬዉ ጽሑፌ የሚያተኩረዉ የአየር ንብረት ለውጥ ለሰብሎቻችን ጠንቅ በሆኑ አረሞች ላይ የሚኖረዉ ተፅዕኖ ላይ ነዉ። ከአየር ንብረት ዉስጥ ለአረሞች መስፋፋት የሚረዱት የአየርና የአፈር ሙቀት፣ የዝናም መጠንና የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን በዋናነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ ለነዚህ ለአረሞች መስፋፋት መንስዔ በሆኑት ላይ የራሱ ተፅዕኖ እንዳለዉከዚህ በፊት በጻፍኳቸዉ ጽሑፎቼ ለማሳየት ሞክሬአለሁ። ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚጨምረዉ የአየር ሙቀት ባብዘኞቹ ሰብሎቻችን ላይ አሉታዊ ጎን ቢኖረዉም ባንዳንድ አረሞች ላይ ግን የመስፋፋትና አካባቢዉን የመዉረር አዝማሚያ ያሳያል። በተመሣሣይ መልኩ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚጨምረዉ የአፈር ሙቀተም የአረም ዘሮች በፍጥነት በቅለዉ በሰብሎቻችን ላይ ጉዳት ማድረስ እንዲችሉ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። በዚሁ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚጨምረዉ የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠንም ለበርካታ የአረም ዓይነቶች ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጥናቶች ይስረዳሉ።
የአየር ንብረት ለውጥ በአረሞች ላይ የሚያመጣዉን ተፅዕኖ በሚመለከት በአውስትራሊያ ሣይንቲስቶች የተጻፈዉ የቴክኒክ መመሪያ በርካታ ነጥቦችን አካቷል። ይህም የተለያዩ አረሞች የሚስፋፉበትን ሁኔታና እነዚሁ አረሞችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል መወሰድ የሚገባ የመፍትሔ ሃሳቦችን ያቀርባል። እንደዚህ መመሪያ አባባል “ምንም እንኳ አረም በግብርናችንና በብዝሀ ሕይወታችን ላይ ጠንቅ ቢሆንም የአየር ንብረት ለውጥ ደግም እነዚህን ጠንቀኛ አረሞች ለመግታት በሁለት ምክንያት አዳጋች ያደርገዋል። የመጀመሪያዉ በርካታ የአረም ዓይነቶች ስለሚከሰቱ ለቁጥጥር አመቺ ባለመሆኑ ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ እነዚህ የአረም ዓይነቶች ከፍተኛ የተስፋፊነት ፀባይ ስለላቸዉ ነዉ። ምንም እንኳ ይህ መመሪያ የተዘጋጀዉ አውስትራሊያ ባለዉ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ቢሆንም ለሀገራችንንም ተመሣሣይ ዓይነት መመሪያ ቢዘጋጅ ጠቃሚ ይሆናል።
ሀገራችንን በተመለከተ በርካታ ተስፋፊ አረሞች የተመዘገቡ ሲሆን እነርሱም በአጭር ጊዜ ሰፋፊ ሥፍራዎችን በማጥቃት ለሰብሎቻችን ብቻ ሳይሆኑ ለመስኖ ውሃ ሥርጭትና ለሌሎችም ሴክተሮችም ጠንቅ እየሆኑ ይገኛሉ። በቅርቡ በዶክተር ኃይሉ ሽፈራዉና የሥራ ባልደረቦቻቸዉ ጥናታቸዉ ተጠናቀዉ ለህትመት የበቁ ሁለት ጽህሑፎች (1 እና 2) እንደሚያሳዩት ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ የተባለ ተክል በአጭር ጊዜ ወስጥ ተስፋፍቶ ተገኝቷል። ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ተብሎ የዛሬ 40 ዓመታት ገደማ ወደ አካባቢዉ እንዲገባ የተደረገዉ ይህ ተክል በአሁኑ ጊዜ ጠንቅ እየሆነ መጥቷል።
በተለይ ጥናቱ በተካሄደበት የአፋር ክልል ይህ አደገኛ ተክል ባጭር ጊዜ ውስጥ ለመስፋፋቱ ማስረጃ የሚሆነዉ ጥናቱ ባለፉት 31 ዓመታት የነበረዉን የዚህን አደገኛ ተክል ሥርጭት ከገመገመ በኋላ ነዉ።። ይህ በሳተላይት መረጃ ጭምር የታገዘዉ ጥናት እ.ኤ.አ. 1986፣ 2000 እና 2017 የነበረዉን የተክሉን ሥርጭት ግንዛቤ ውስጥ አስገብቷል። እንደ አጥኝዎቹ ግምት ይህ አደገኛ ተክል በያመቱ ከ30 ሺህ በላይ የሚሆን መሬት በመዉረር ላይ ይገኛል። ይህንን በአደገኛ ሁኔታ በመስፋፋት ላይ የሚገኘዉን ተክል ለመግታት የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር በብሔራዊ ደረጃ እስትራቴጂ በመቅርስ ለተግባራዊነቱ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
ክዚህ ሌላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየዉ የዚህ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የመስፋፋት የፕሮሶፒስ ፀባይ ከአየር ንብረት ለዉጥ ጋር እንደሚገናኝ ነዉ። በዚሁ መሠረት የሜዲተራኒያን፣ የመካከለኛዉ ምሥራቅና የሰሜን አሜሪካ አካባቢዎች ለዚህ አደገኛ ተክል በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቂ እንደሚሆኑ ነዉ።

በሚቀጥለዉ ጽሑፌ የአየር ንብረት ለዉጥ በሌሎች ሴክተሮች ላይ ያደርሳል ተብሎ የሚገመትዉን ለማሳየት እሞክራለሁ።
እስከዚያዉ በቸር ይግጠመን።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 10፤ 2011 ዓ.ም.