በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤
የአየር ንብረት ለውጥ — በሰብሎቻችን
የአየር ንብረት ለዉጥ በተለያዩ ሴክቴሮች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ እንደሚገኝና ለወደፊቱም በከፋ ሁኔታ እንደሚቀጥል በተለያዩ መድረኮች በመገለጽ ላይ ይገኛል። የዛሬዉ ጽሁፌ የሚያተኩረዉ የአየር ንብረት ለዉጥ በሰብሎቻችን ላይ ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቀዉን ተፅዕኖ በአጭሩ ለማሳየት ነዉ። እንደሚታወቀው ሁሉ ሰብሎቻችን አጠቃቀማቸዉንን መሠረት ባደረገ በተለያዩ ክፍሎች ይመደባሉ። ከነዚህ ዉስጥ ዋነኞቹ 1ኛ) ብርዕና አገዳ (ምሳሌ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ በቆሎ፣ ዳጉሣ)፤ 2ኛ) ጥራጥሬ (ባቄላ፣ አተር፣ ሽምብራ፣ ምስር፣ ጓያ፣ ግብጦ)፤ 3ኛ) ሥራ ሥር (ድንች፣ ስኳር ድንች፣ እንሰት)፤ 4ኛ) የቅባት እህል (ኑግ፣ ተልባ፣ ኦቾሎኒ)፤ 5ኛ) አትክልት (ጎመን፣ ቲማቲም፣ ካሮት)፤ 6ኛ) ፍራፍሬ (ማንጎ፣ ብርቱካን፣ ሙዝ፣ አናናስ)፤ 7ኛ) የስኳር ሰብሎች (ሸንኮራ አገዳ)፤ 8ኛ) የጭረት ሰብሎች (ጥጥ)፤ 9ኛ) ንቃት ሰጪ (ቡና፣ ሻይ) እና 10ኛ) የከብት መኖ (አልፋልፋና የተለያዩ የሣር ዓይነቶች) ናቸዉ። እነዚህና ስማቸዉ ከላይ ያልተገለጹት ሰብሎች በተለያየ የአየር ንብረትና የአፈር ሁኔታ ይተከላሉ ወይም ይዘራሉ። ቢሆንም ለእያንዳንዱ ሰብል ምቹ የሆነ የአየር ንብረትና የአፈር ሁኔታ ሊገኝላቸዉ አይቻልም። ስለዚህ እነዚህ ሰብሎች ካለዉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በመጋፈጥ በማደግና ያላቸዉን የመጨረሻ ጉልበት አሟጠዉ የተወሰነም ቢሆን ምርት ይሰጣሉ። ያቺኑ ከብዙ ጥቃት ተርፋ የቀረችዉን ምርት ደግሞ ገበሬዎቻችን አጭደዉና ወቅተዉ ለራሳቸዉ ቤተሰብና ለሌሎች ተመጋቢዎችም እንዲደርስ ያደርጋሉ።
የአየር ንብረት ለዉጥ በሰብሎቻን ምርት ላይ የሚያደርሰዉ ተፅዕኖ በሰፊዉ ተጠንቷል። እነዚሁ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዓለማችን በአማካይ ይህ መጥፎ ክስተት የሚያደርሰዉ የምርት ቅነሳ ከ3.5-12.9% በስንዴ፣ ከ34.6-35.6% በበቆሎ እና ከ10-15% በሩዝ እንደሚሆን ነዉ። ለዛሬዉ ጽሑፌ የተወሰኑትን በተለይም በአፍሪካ ላይ የሚተኩሩትን ለማሳየት እሞክራለሁ።ከሁለት ዓመታት በፊት የታተመዉ ጽሑፍ የአየር ንብረት ለዉጥ በአፍሪካ እ.ኤ.አ. በ2030 ሊያደርስ ይችላል ተብሎ የሚገመትዉን ያሳያል (ምሥል 1)።

ጽሑፉ አፍሪካን እንደ ቅርበታቸውና የአየር ንብረት ተመሣሣይነታቸዉ በአምስት ከፍለዉ ያሳየ ሲሆን ትኩረት ያደረገዉም በበቆሎ፣ ማሽላና ስንዴ ላይ ነዉ። በምሥሉ እንደሚታየዉ በመጪዉ 11 ዓመታት ውስጥ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት በደቡባዊ የአፍሪካ አካባቢዎች ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ የሚጠበቅ ሲሆን በተለይ በቆሎ በ28.5%፣ ስንዴ ደግሞ በ15.8% እንደሚቀንስ ይጠበቃል። በትንበያዉ መሠረት ሀገራችን በምትገኝበት የምሥራቃዊዉ የአፍሪካ ክፍል በበቆሎ ላይ መጠነኛ የምርት ቅናሽ የሚያሳይ ቢሆንም ከሌሎቹ የአፍሪካ አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ በማሽላና ስንዴ ላይ የምርት መቀነስ ሳይሆን የምርት ዕድገት ይጠበቃል። ይህ በምሥራቃዊዉ የአፍሪካ አካባቢ የሚጠበቀዉ የምርታማነት መጨመር ዋናዉ ምክንያት በትንበያዉ መሠረት በአካባቢዉ የዝናም መጠን መጨመር ነዉ። በሌሎች አካባቢዎች በተለይ በደቡባዊው የአህጉሪቷ አካባቢ የምርት ማሽቆልቆል ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቀውም ከዝናም እጥረት ጋር ግንኙነት አለው።
ሀገራችንን በተመለከተ ከሦስት ወራት በፊት በዓለም አቅፍ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ የልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ታትም የወጣዉን አጠር ያለ ሪፖርት ማጤን ያስፈልጋል። ይህ በዝናም መጠንና በአየር ሙቀት በመመርኮዝ የተደረገዉ ትንበያ የተሠራዉ ሀገሪቱን በሰድስት ዋና አካባቢዎችበመክፈል ነዉ። እነርሱም 1ኛ) ለድርቅ ተጠቂ ከፍተኛ ሥፍራዎች፣ 2ኛ) ለድርቅ ተጠቂ ዝቅትኛ ሥፍራዎች፣ 3ኛ) አስተማማኝ ርጥበት ያላቸዉ ዝቅተኛ ሥፍራዎች፣ 4ኛ) አስተማማኝ ርጥበት ያላቸዉ ከፍተኛ ሥፍራዎች (ብርዕና አገዳ ሰብሎች)፣ 5ኛ) አስተማማኝ ርጥበት ያላቸዉ ከፍተኛ ሥፍራዎች (እንሰት) እና 6ኛ) አርብቶ አደር ሥፍራዎች ናቸው። ከዚህ በታች በምሥል 3 እንደሚታየዉ ትንበያዉ በተደረገባቸዉ እ.ኤ.አ. በ2035፣ 2055 እና 2085 ላይ ሲሆን ጥናቱ መሠረት ያደረገዉም እ.ኤ.አ. በ2013 የነበረዉን የሶስቱን ሰብሎች የምርታማነት መጠን ነዉ። ከምሥሉ መረዳት እንደሚቻለዉ የበቆሎ ምርታማነት እየጨመረ እንደሚሄድና ከዛሬ 66 ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ. በ2013 ከነበረዉ መጠን በ4.2% ብልጫ እንደሚያሳይ ነዉ። በሌላ በኩል የስንዴ ምርታማነት እየቀነሰ እንደሚሄድ ይገመታል። ከሁለቱ ሰብሎች በተለየ ሁኔታ የተተነበየዉ ለማሽላ ነዉ። ምንም እንኳ እስከ 2055 ድረስ በመጠኑም ቢሆን የማሽላ ምርታማነት እየጨመረ ቢሄድም በ2085 ወደ 1% የሚጠጋ የምርት ማሽቆልቆል ያሳያል።
እዚህ ላይ እንቆቅልሽ ሊሆንብን የሚችለዉ በአፍሪካ ደረጃ በተሠራዉ ጥናት (ምሥል 1) እና በዚህ ኢትዮጵያን መሠረት ባደረገው ጥናት (ምሥል 2) ዉጤቶች መካከል ያለዉ የጎላ ልዩነት ሲሆን በተለይ በስንዴ ምርታማነት ላይ የተደረጉት ትንበያዎች እጅግ የተራራርቁ መሆናቸዉ ነዉ።


ማጠቃለያ
በአፍሪካ ደረጃ የተሠሩት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ያለችበት በምሥራቃዊዉ የአህጉሪቷ ከፍል የዝናም መጠን እንደሚጨምርና የአንዳንድ ሰብሎች (በተለይ የስንዴ) ምርት እንደሚጨምር ያሳያሉ። በሌላ በኩል በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የተሠራዉ ጥናት ደግሞ የአየር ንብረት ለዉጥ በሰብሎቻችን ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ትፅዕኖ እንዳለዉ ያሳያሉ። ስለዚህ ጠለቅ ያለ ጥናት በማድረግ ከዚህ ቀደም የተተነበዩ ሥራዎችን ማረጋገጥ ይኖርብናል።በመቀጠልም ይደርሳል ተብለዉ የሚጠበቁ መጥፎ ክስተቶችን ለመታደግ ስትራቴጂዎችን በመንድፍ ለተግባራዊነቱ መንቀሳቅስ ይኖርብናል። የአየር ንብረት ለዉጥ በሰብሎቻችን ላይ በሚያደርሱብት ሁኔታ ላይ ከተጠኑ ጥናቶች መካከል አብዛኞቹ የተካሄዱት በተለምዶ የብርዕና አገዳ ሰብሎች ብለን በምንጠራቸው እንደ ስንዴ፣ በቆሎና ማሽላ በመሳሰሉት ላይ ነዉ። በሌሎች በመግቢያዬ ላይ በተጠቀስኳቸዉ የሰብሎች ዓይነቶች ላይ የተጠና ጥናት እጅግ አነስተኛ ነዉ። የአየር ንብረት ለዉጥ ግን ለነዚህ ጥናት ባልተደረገባቸዉ የሰብል ዓይነቶች ላይም ርህራሄ ስለማይኖረዉ ጥናታችንን በሁሉም ሰብሎችንን ማድረግ ይኖርብናል። ከላይ እንዳሳሰብኩት የምንነድፈዉ ስትራቴጂም እነዚህንም ሰብሎች ማጠቃለል ይኖርበታል።
በሚቀጥለዉ ጽሑፌ የአየር ንብረት ለዉጥ በሌሎች ሴክተሮች ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቀውን ለማሳየት እሞክራለሁ።
እስከዚያዉ በቸር ይግጠመን።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 9፤ 2011 ዓ.ም.