ግብርናችንን ለማዘመን፤ የአየር ንብረት ለውጥ — በብዝሀ ሕይወት

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የአየር ንብረት ለውጥ — በብዝሀ ሕይወታችን

ባለፈዉ ጽሑፌ የአየር ንብረት ለዉጥ በመከስት ላይ እንዳለና ለዚህም ማረጋገጫ ከሆኑት ምልክቶች መካከል ጥቂቶቹን ለማሳየት ሞክሬአለሁ። እነዚህ ምልክቶችም 1ኛ) የአየርና የባህር ሙቀት መጨመር፣ 2ኛ) የዝናም እጥረት ወይም ድርቅ መባባስ፣ 3ኛ) የጎርፍ መብዛት፣ 4ኛ) የግሪንሃዉስ ጋዝ መጠን መጨመር፣ 5ኛ) የበረዶ ክምችት መመናመን፣ 6ኛ) የባህር ወለል ከፍ ማለት እና 7ኛ) የባህር ዉሃ ወደ አሲዳማነት መቀየር ናቸዉ።

በዛሬዉ ጽሑፌ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ በብዝሀ ሕይወት ሀብታችን ላይ የሚያደርሰዉን አሉታዊ ተፅዕኖ ለማሳየት እሞክራለሁ። በቅርቡ በዓለም አቀፍ ድርጅት የታተመዉን ሪፖርት በሚመለከት በሁለት ክፍል  “አንድ ሚሊዮን ፍጥርቶቻችን ሊጠፉ” በሚል የጻፍኩትን ማስታወስ እፈልጋለሁ። ከዚህ በተጨማሪ የአየር ንብረት ለዉጥ በቡናችን ላይ በማድረስ ላይ ያለዉን በሁለት ክፍል ከትቤ ነበር። በዚህ መሠረት በአየር ሙቀት መጨመርና ዓመታዊ የዝናም መጠን መቀንስ ምክንያት እስከ 60% የሚደርሱ የቡና አብቃይ መሬቶቻችን ለቡና እርሻ ምቹ እንደማይሆኑ ነዉ።

ምንም እንኳ በርካታ ከአየር ንብረት ለዉጥ ጋር የሚገናኙ መንስኤዎች ፍጥረታቶቻችንን ለዚህ የከፋ አደጋ ቢያጋልጡም ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት የአየር ሙቅትና የካቦን ዳዮክሳይድ መጠን መጨመር ናቸዉ። እነዚህና ሌሎች በአየር ንብረት ለዉጥ የሚመጡ መጥፎ ክስተቶችን መቋቋም ያልቻሉ ፍጥረታቶቻችን በሂደት ከምድራችን ይጠፋሉ።

የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት በድህረ ገጹ እንዳሰፈረዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ብቻ ሳይሆን የሰዉ ልጅም ለብዝሀ ሕይወት መመናመንና መጥፋት ከፍተኛ ድርሻ እንዳበረከተ ነዉ። በተለይም የብዝሀ ሕይወት መኖሪያን በማጥፋትና በምትኩ ሌላ አዲስ ፍጡር ወደ አካባቢ በማስገባትና የሰዉ ልጅ የብዝሀ ሕይወት መጥፋትን በ100–1000 እጥፍ አፋጥኖታል። ከላይ የተገለጸዉ ሪፖርት ይፋ ሲደረግ ትኩረት ያደረገዉ በዓለም እና በአህጉር ደረጃ በፍጥረታት ላይ ሊከሰት ይችላል ተብሎ የሚጠበቀውን ነዉ።

ወደ ሀገራችን ስንመጣ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት በብዝሀ ሕይወታችን ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን በሚመለከት የተወሰኑ ጥናቶች ተካሄደዋል። እ.ኤ.አ. በ2009 የተጻፈ ሪፖርት እንደሚያሳየዉ በኢትዮጵያ በየአሥር ዓመት የአየር ሙቀት በ0.4 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይጨምራል። ይህ በመቶና ሺህ ዓመታት ሲሰላ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ዕድገትን ያሳያል።

ቢሆንም በርካታ ሥራዎች የተሠሩትና በመሠራት ላይ ያሉት እንዴት አደጋዉን ተቁቁመን የብዝሀ ሕይወታችንን በምናስጠብቅበት የምፍትሔ አቅጣጫ ላይ ነዉ።

ከተደረጉት ጥረቶች ዉስጥ ዋናዎቹ በአገሪቱ ወካይ በሆኑ ሥፍራዎች ብሔራዊ ፓርኮችንና መካነ ዕፅዋት (ወይም ቦታኒካል ጋርደን) በማቋቋም የተለያዩ አገር በቀል ፍጥረቶቻችን ከነጭራሹ እንዳይጠፉ በተወሰነ ደረጃ ለመታደግ ሙከራ ማድረግ ነበር። በዚህ መሠረት በአገሪቱ ስምንት የሚጠጉ ፓርኮች የተቋቋሙ ሲሆን እነርሱም የሰሜን፣ የባሌ፣ የአዋሽ፣ የአቢያታ-የሻላ፣ የነጭ ሣር፣ የኦሞ፣ የማጎ እና የያንጉዲ ራሳ ብሄራዊ ፓርኮች ናቸዉ። በነዚህ ፓርኮች በርካታ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ፍጥረታት ይኖራሉ።  ተክሎችን በተመለከትም የብዝሀ ሕይወታችንን ለመጠበቅና ለወደፊቱ ትውልድ ለማስቀጠል የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት 64 ሺህ ዓይነት ናሙናዎች በአዲስ አበባ ባለዉ የጂን ባንክ ያለዉ ሲሆን በተጨማሪም በመቱ፣ ሀዋሳ፣ ሀረር፣ መቀሌ፣ ጎባ፣ ባህር ዳር እና አሶሳ የብዝሀ ሕይወት ማዕከላት አሉት። ከዚህ ሌላ በፍቼ ሁለተኛዉ ወይም ዱፕሊኬት ጂን ባንክ አለዉ። ከዚህ ሌላ ሊጠቀስ የሚገባዉ ከስድስት ወራት በፊት ተመርቆ ለህዝብ ክፍት የሆነዉ የጉለሌ መካነ ዕፅዋትና አካባቢዊ መናፈሻ ነዉ። ይህ መናፈሻ በ705 ሄክታር ላይ ያረፈ ሲሆን የሚተዳረዉም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጋራ ነው። በዚህ ማዕከል ዉስጥ እስከ 700 የሚደርሱ አገር በቀል የተክል ዓይነቶች በደህና ሁኔታ ተጠብቀዉ የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ ዉስጥ 65 የሚሆኑት ለመጥፋት በአደገኛ ሁኔታ ያሉ ናቸዉ።

ከላይ በሰዕሉ እንደሚታየዉ ለብዝሀ ሕይወታችን መመናመንና ከነጭራሹ መጥፋት የተለያዩ መንሴኤዎች ቢኖሩም ከላይ የተገለጹት ዋናዎቹ ናቸዉ።

በከፍተኛ ሁኔታ በመመናመን ላይ ስለሚገኙት የብዝሀ ሕይወታችን ሁኔታ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመስጠት የተለያዩ መድረኮች ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሲዘጋጁ ቆይተዋል። በትምህርት ቤቶችም ካሪኩለም ጭምር የብዝሀ ሕይወት ሁኔታ ትኩረት እንዲሰጠዉ ተደርጓል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር አክሊሉ ዳለሎ እ.ኤ.አ. በ2012 ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፋቸዉ እንዳሳዩት የአየር ንብረት ለዉጥና የብዝሀ ሕይወት መመናመን አሳሳቢነት በሚመለከት በሁለተኛ ደረጃ በሚሰጡት የባዮሎጂ ትምህርተ ክፍሎች ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል። ስለዚህ በዚህ የሚያልፉ ተማሪዎች የተወሰነም ቢሆን ግንዛቤ ሊያገኙ ችለዋል።

ማጠቃለያ፤ የአየር ንብረት ለውጥ በመከሰት ላይ እንዳለ በርካታ መረጃዎች ያሉ ሲሆን ወደፊትም የበለጠ ተስፋፍቶ እንደሚቀጥል በሣይንሳዊ መንገድ የተሠሩ ትንበያዎች ያሳያሉ።በተለይ በብዝሀ ሕይወታችን ላይ ከፍተኝ የሆነ አሉታዊ ጎን እንዳለዉ ለማወቅ ተችሏል። የአየር ንብረት ለዉጥ በሌሎች ሴክተሮች ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቀዉን ደግሞ በተከታታይ ጽሑፎች አቀርባለሁ።

እስከዚያዉ በቸር ይግጠመን።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 8፤ 2011 ዓ.ም.

አስተያየት ያስቀምጡ